ቀጥታ፡

የብልጽግና ፓርቲ በመደመር እሳቤ ጠንካራ ሀገረ መንግስት የመገንባት ጥረት ውጤት እየተገኘበት ነው

ሆሳዕና፤ ጥር 6/2018(ኢዜአ)፦ የብልጽግና ፓርቲ በመደመር እሳቤና በህብረ ብሔራዊ አንድነት ጠንካራ ሀገረ መንግስት የመገንባት ጥረት  ውጤት እየተገኘበት መሆኑን የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንትና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርአት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አደም ፋራህ ገለጹ።

የብልጽግና ፓርቲ የበጀት ዓመቱ የስድስት ወራት ሥራዎችን አፈጻጸም የሚገመግም መድረክ በሆሳዕና ከተማ ማካሄድ ጀምሯል፡፡

በሀገሪቷ እየተከናወኑ የሚገኙ ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች የኢትዮጵያን እድገትና ማንሰራራት እውን የሚያደርጉ ናቸው

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንትና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርአት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አደም ፋራህ፤ በመደመር እሳቤና በህብረ ብሔራዊ አንድነት የብልጽግና ፓርቲ ጠንካራ ሀገረ መንግስት የመገንባት ጥረት የተሳካ ውጤት እየተገኘበት መሆኑን ገልጸዋል። 


 

አሰባሳቢ ትርክትን በማጎልበት ለሁሉም ዜጎች የምትመች የበለጸገች ሀገር በመገንባት ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ ዘመን ተሻጋሪ የልማት አሻራዎች እንዲቀመጡ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።፡

በኢትዮጵያ ጠንካራ ተቋም የመገንባት እንዲሁም ፈጠራንና ፍጥነትን መሰረት ያደረገ ጠንካራ አመራር በመፍጠር ረገድም ፓርቲው ስኬታማ ተግባራትን ማከናወኑን ገልጸዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን በማጠናቀቅ ለስኬት በማብቃት ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶችን እውን ለማድረግ እየተሰራ ስለመሆኑም አንስተዋል።


 

ዲጂታል ኢትዮጵያን ከመገንባት አንስቶ የአንድ እቅድና የአንድ ሪፖርት አካሄድን በመከተል የአመራሩና የአባላቱን አቅም የመገንባት ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውንም ጠቅሰዋል።

በ2018 በጀት ዓመት የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የተለያዩ ተግባራት ለማከናወን ታቅዶ በእቅዱ መሰረት እስካሁን ስኬታማ ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።


 

የዛሬው መድረክም በተለያዩ ዘርፎች በተከናወኑ ተግባራት የተገኙ ስኬቶችን በመገምገም አጠናክሮ ለማስቀጠልና ቀጣይ ተግባራት ላይ ለመምከር የሚያስችል መሆኑንም አንስተዋል።

በመድረኩ ላይ የሁሉም ክልሎችና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊዎችና የወጣት ክንፍ አመራሮች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም