በሀገሪቷ እየተከናወኑ የሚገኙ ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች የኢትዮጵያን እድገትና ማንሰራራት እውን የሚያደርጉ ናቸው-አቶ አደም ፋራህ - ኢዜአ አማርኛ
በሀገሪቷ እየተከናወኑ የሚገኙ ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች የኢትዮጵያን እድገትና ማንሰራራት እውን የሚያደርጉ ናቸው-አቶ አደም ፋራህ
ወራቤ፤ ጥር 5/2018(ኢዜአ)፦በሀገሪቷ እየተከናወኑ የሚገኙ ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች የኢትዮጵያን እድገትና ማንሰራራት እውን የሚያደርጉ መሆናቸውን የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርአት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊ አደም ፋራህ ገለጹ።
በአቶ አደም ፋራህ የተመራ የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ልዑክ በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማና አካባቢው እየተከናወኑ የሚገኙ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ጎብኝቷል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርአት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊ አደም ፋራህ፤ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተከናወኑ ያሉ ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች የኢትዮጵያን እድገትና ማንሰራራት እውን የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ያሉ እምቅ ሃብቶችን በማልማት ጥቅም ላይ እንዲውሉ እየተደረገ መሆኑን አንስተው፣ በወራቤና አካባቢው የተመለከቷቸው የልማት ሥራዎች ለዚህ ጥሩ ማሳያ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በወራቤ ከተማ እየተሰራ የሚገኘው የኢንዱስትሪ መንደር ለበርካቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ለሀገር እድገትም ተጨማሪ አቅም ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።
በመሆኑም በሁሉም አካባቢዎች እምቅ ሃብቶችን ለይቶ በተደመረ አቅም በማልማት ለጋራ ጥቅም የማዋል ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በከተማዋ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማትም ለኑሮ ምቹና ዘመናዊ ከተሞችን የመገንባት ጥረት ማሳያ መሆኑንም አንስተዋል።