ቀጥታ፡

ከምርምር ማዕከሉ የሚወጡ የስንዴ ዝርያዎች የአርሶ አደሮችን ምርታማነት አሳድገዋል

ሮቤ ፤ ጥር 6/2018(ኢዜአ)፦ ከሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል ያገኟቸው የተሻሻሉ የስንዴ ዝርያዎች ምርታማነታቸውን በማሳደግ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው በባሌ ዞን የሲናና ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ።

የምርምር ማዕከሉ በበኩሉ የአርሶና አርብቶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በምርምር ያገኛቸውን የሰብል ዝርያዎች በማባዛት ተደራሽ ለማድርግ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

ከሲናና ወረዳ አርሶ አደሮች መካከል አቶ አወል ሀጅ ኢድሪስ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ ከዚህ በፊት የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በአግባቡ ተግባራዊ ባለማድረጋቸው ተጠቃሚ ሳይሆኑ ቆይተዋል።


 

ሆኖም ዓምና ከሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል ያገኙትን "ሳነቴ" የተሰኘ የስንዴ ዝርያ በአንድ ሄክታር ማሳቸው ላይ በማልማት 55 ኩንታል ምርት በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ያገኙት ምርት ቀደም ሲል ከሚዘሩት የአካባቢ ዝርያ ጋር ሲነፃፀር በ30 ኩንታል ብልጫ ማሳየቱን አስረድተዋል።


 

ምርታማነታቸውን ይበልጥ ለማሳደግ በ2017/018 የመኸር ወቅት የተሻሻሉ አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ በአንድ ሄክታር ይዞታቸው ላይ ካለሙት ''ቦኩ'' ከተሰኘ አዲስ የስንዴ ዝርያ 65 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁ አስረድተዋል።

ከምርምር ማዕከሉ ያገኙትን የስንዴ ዝርያ ሙሉ ፓኬጅ በመጠቀም ከ14 አርሶ አደሮች ጋር በመሆን በኩታ ገጠም 25 ሄክታር መሬት ማልማታቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላኛው የወረዳው አርሶ አደር ታጁ አብዱልቃድር ናቸው።


 

በአሁኑ ወቅት የሰብሉ ቁመና በመልካም ሁኔታ ላይ ስለሚገኝ የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁም ተናግረዋል።

አርሶ አደር ከድር ሐጅ መሐመድ በበኩላቸው፤ ከዚህ በፊት ሰብልን በወቅቱ በማረምና ፀረ አረም በመርጨት ረገድ ክፍተት ስለነበረባቸው የልፋታቸውን ያህል ምርት ሳያገኙ ቆይተዋል።


 

     የሻይ ልማትን ለማላቅ እየታተረች ያለችው ኢትዮጵያ

የማዕከሉ ተመራማሪዎች የሰጧቸውን የኤክስቴንሽን ምክር ሀሳብ በአግባቡ ተግባራዊ በማድረግ ከዘሩት የስንዴ ሰብል ከሄክታር እስከ 50 ኩንታል ምርት አገኛለሁ ብለው እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።

የሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታመነ ሚደቅሳ እንደገለጹት፣ ማዕከሉ የአርሶና አርብቶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን በምርምር በማፍለቅ ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል።


 

በተለይ ማእከሉ ለአካባቢው አርሶ አደሮች በቅርበት በምርምር የተደገፈ እገዛ በማድረግ ምርትና ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ እገዛ ማድረጉን አስረድተዋል። 

ይህን ተግባር በማጠናከርም በ2017/2018 ምርት ዘመን ብቻ ከማዕከሉ የተለቀቁ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ ከ150 ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የቅድመ መሥራች ዝርያዎችን እያባዛ እንደሚገኝ  አስታውቀዋል።

በ1978 ዓ.ም የተቋቋመው የሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል በስንዴ፣ ገብስና ሌሎች ስምንት መስኮች ላይ ያተኮሩ ምርምሮችን በማካሄድ ከ116 በላይ የምርምር ውጤቶችን ለተጠቃሚው ማድረስ መቻሉም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም