የሻይ ልማትን ለማላቅ እየታተረች ያለችው ኢትዮጵያ - ኢዜአ አማርኛ
የሻይ ልማትን ለማላቅ እየታተረች ያለችው ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ፤ታኅሣስ 28/2018 (ኢዜአ)፡-በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች ለሻይ ልማት ተስማሚና ምቹ ሥነ-ምኅዳር መኖሩን መረጃዎች ያመላክታሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአረንጓዴ ዐሻራ አካል የሆነው የሻይ ልማት ኢኒሼቲቭ ተከላ በጥሩ ሁኔታ እየተከወነ መሆኑን ሰሞኑን በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው አስታውቀዋል።
በመትከል የታየው መልካም ጅማሮ በአግሮ-ፕሮሰሲንግ ከተደገመ ሙሉ እንደሚሆንም አስገንዝበዋል።
በዚህም መሠረት የግሉ ዘርፍ ዕሴት በማከል ቢሳተፍ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ በተጨማሪ በኤክስፖርት ሀገራችንን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።
እስካሁን በኢትዮጵያ ስላለው የሻይ ልማት እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የቡና፣ሻይና ቅመማቅመም ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍቃዱ ደፈረስ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በቆይታቸውም፥ እስካሁን ባለው መረጃና ልየታ መሠረት በኢትዮጵያ ለሻይ ቅጠል ልማት ተስማሚና ምቹ የሆነ ከ6 ሚሊየን ሔክታር የሚልቅ መሬት መኖሩን አመላክተዋል።
ካለው የመልማት ዐቅም አንጻር እየለማ ያለው አነስተኛ መሆኑን አንስተው፤ በዘርፉ በቀጣይ የተሻለ ለመሥራት መንግሥት ትኩረት መስጠቱን ጠቁመዋል።
ለዚህም ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአረንጓዴ ዐሻራ አካል የሆነው የሻይ ልማት ኢኒሼቲቭ ተከላ በጥሩ ሁኔታ እየተከወነ መሆኑን መግለጻቸው ማሳያ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የሻይ ቅጠል ወደ ተለያዩ ሀገራት በመላክ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎቷን እንደምትደጉምም አንስተዋል።
ለአብነትም በ2017 የበጀት ዓመት 882 ነጥብ 45 ቶን የሻይ ቅጠል ምርት ወደ እንግሊዝ፣ ሕንድ እና ጀርመን በመላክ 1 ነጥብ 61 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን አረጋግጠዋል።
በተያዘው የበጀት ዓመትም 898 ቶን በመላክ 1 ነጥብ 72 ሚሊየን ዶላር ለማግኘት መታቀዱን ጠቁመው፤እስካሁን በእርሻ ልማቶች እና በአርሶ አደሮች በሻይ ቅጠል ተክል ከለማው 4 ሺህ 936 ሔክታር 4 ሺህ 854 ቶን ምርት መሰብሰቡን ጠቅሰዋል።
ከዚህ አንጻር ዘርፉ እንደ ሌሎች የወጪ ምርቶች የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው አስገንዝበው፤ በይበልጥ አጠናክሮ በማስቀጠል ሀገር የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ማድረግ እንደሚገባ አስረድተዋል።
የሻይ ቅጠል ተክል አንድ ጊዜ ከተተከለ ለ80 እና 90 ዓመታት ምርት በመስጠት የሚቆይና በየ15 ቀኑ ምርቱን በመልቀም ገቢ ማግኘት የሚያስችል ስለመሆኑም አስገንዝበዋል።
እንደ አቶ ፍቃዱ ገለጻ፤ በኢትዮጵያ በሰፋፊ እርሻዎች ውስጥ አምስት የሻይ ቅጠል ምርት ማዘጋጃ ፋብሪካዎች አሉ።
በሻይ ማዋሀድ (ዕሴት በመጨመር) ላይ ተሰማርተው ለሀገር ውስጥና ለዓለም አቀፍ ገበያ ልዩ ምርቶችን እያቀረቡ ያሉ ኩባንያዎችም፤ ኢትዮ አግሪ ሴፍት (ውሽውሽና ጉመሮ ሻይ ልማት)፣ ኢስት አፍሪካ አግሪ ቢዝነስ፣ ሄሪቴጅ ሻይ ኢትዮጵያ እና መታድ የግብርና ልማት መሆናቸውን አብራርተዋል።
የሻይ ቅጠል ተክል (Assam tea type) ወደ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የገባው በፈረንጆቹ 1927 የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳስ በነበሩት ጆርጅ ሆላንድ አማካኝነት እንደሆነም አውስተዋል።
ጆርጅ ሆላንድ ከውጭ ያመጡትን የሻይ ቅጠል ተክል ዘር በቦንጋ ከተማ ቶንጎላ አካባቢ ለሚኖሩ አርሶ አደሮች እንዲያለሙት ማሠራጨታቸውንም ጠቁመዋል።
በተጨማሪም በፈረንጆቹ 1928 የእንግሊዝ ቆንስል የነበሩት አብዱል መጅድ ከሕንድና ኬንያ የሻይ ቅጠል ተክል ፍሬዎችን በማስመጣት በኢሉአባቦር ዞን አሌ ወረዳ ጉመሮ አካባቢ ማሠራጨታቸውን አመላክተዋል።
እንዲሁም በኢትዮጵያ ከ1950 እስከ 1960 ዓ.ም አማራጭ የግብርና ልማት ማስፋፋት ሥራዎች አካል በመሆን የሻይ ቅጠል ልማት እና ኢንቨስትመንት ሥራ መጀመሩን አንስተዋል።
ልማቱ በተጠናከረ መልኩ የተጀመረው ሁለቱ ሰፋፊ የሻይ ቅጠል ተክል እርሻዎች በሚገኙባቸው በውሽውሽ እና ጉመሮ አካባቢዎች ከ1950 ዓ.ም ጀምሮ መሆኑንም ይጠቅሳሉ።
ከ1972 ዓ.ም ጀምሮም በቡናና ሻይ ልማት ሚኒስቴር እየተመራ በተጠናከረ መልኩ ሲሠራበት መቆየቱን አውስተዋል።
ከወቅቱ መንግሥት ለውጥ በኋላ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በመፍረሱ የሻይ ልማት ድርጅቶቹ ወደ ግል ይዞታ (ኢትዮ-አግሪሴፍት አ.ማ) ተዛውረው እየተመሩ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል።
በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ፣በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና ጋምቤላ ክልሎች በአራት የሻይ ልማት ድርጅቶች (ውሽውሽ፣ ጉመሮ፣ኢስት አፍሪካ (የጨዋቃ ኡቶ) እና ቨርዳንታ) እንዲሁም በአነስተኛ አርሶ አደሮች በአውት ግሮዎርስ ትሥሥር እና በኩታ ገጠም እየለማ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
እስካሁን ባለው መረጃም የሻይ ልማት ዘርፍ ከ80 ሺህ ለሚልቁ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፈጠሩን አስታውቀዋል።