የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት እና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ የልማትና የዕድገት ግቦችን ለማሳካት እያገዘ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት እና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ የልማትና የዕድገት ግቦችን ለማሳካት እያገዘ ነው
በደሌ፤ ጥር 5/2018 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል እየተከናወነ የሚገኘው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት እና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ የልማትና የዕድገት ግቦችን ለማሳካት እያገዘ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።
በኦሮሚያ ክልል ለቀጣዮቹ ሁለት ወራት የሚከናወነው የዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ስራ በዛሬው ዕለት በክልል ደረጃ በቡኖ በደሌ ዞን ዳቦ ሐና ወረዳ ተጀምሯል።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ፣ የዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ስራ ከ6 ሺህ 300 በላይ ተፋሰሶች ላይ ይከናወናል ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት በክልሉ በተከናወነው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ የክልሉ የደን ሽፋን መጨመሩንና በብዙ ተጎድተው የነበሩ አከባቢዎች በማገገማቸው ምርታማነትም በመጨመር ላይ እንደሚገኝ አንስተዋል።
የተፋሰስ ልማት ስራው በተለይም በግብርናው ዘርፍ ተቀርጸው እየተተገበሩ የሚገኙ ኢንሼቲቮች ስኬት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።
በአጠቃላይ በክልሉ እየተከናወነ የሚገኘው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት እና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ የልማትና የዕድገት ግቦችን ለማሳካት ትልቅ አበርክቶ አለው ብለዋል።
ዘንድሮም በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ በጠንካራ የህዝብ ተሳትፎ ታጅቦ የሚከናወን መሆኑን ገልጸዋል።
የቡኖ በደሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አማን ደኑ በበኩላቸው በዞኑ የተጀመረው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በ222 ተፋሰሶች ላይ የሚከናወን መሆኑን ገልጸዋል።
በዞኑ በአየር ንብረት ለውጥ እና በአፈር አሲዳማነት ምክንያት የሚደርሰውን የምርታማነት መቀነስን ለመከላከል በተፋሰስ ልማቱ የሚከናወኑ ስራዎች እንደሚጠናከሩ ተናግረዋል።
በበጋው ወራት የተፋሰስ ልማት የሚከናወንበት መሬት በክረምቱ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በተለያዩ ቸግኞች ለመሸፈን የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
ለዚህም ከ200 ሚሊዮን በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች በዞኑ እየተዘጋጁ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተፋሰስ ልማት ስራው የተሳተፉ አርሶ አደሮችም ስራው በአፈርና እና ውሃ ሀብቶች ላይ የሚደርሱ ችግሮችን በመከላከል ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጥ በመሆኑ ዘንድሮም ተሳትፏቸውን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።