የዲጂታል ስትራቴጂ ትግበራ በዘርፉ ልማት ኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚያደርግ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዲጂታል ስትራቴጂ ትግበራ በዘርፉ ልማት ኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚያደርግ ነው
አርባ ምንጭ፤ ጥር 6/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የዲጂታል ስትራቴጂ ትግበራ በዘርፉ ልማት ሀገሪቷን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚያደርግ መሆኑን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ምሁራን ገለጹ።
በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 የተገኘውን ስኬት በመሰነቅ በዘርፉ ልማት የላቀ ስኬት ለማስመዝገብ የሚያስችል የቀጣይ አምስት ዓመታት ስትራቴጂክ ፕላን ይፋ መደረጉ ይታወቃል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂክ ዕቅድ የኤሌክትሪክ ኃይል እና የኢንተርኔት አገልግሎትን በማስፋት በተደመረ አቅም ለማሳካት የሚያስችል ዝግጅት በማድረግም ወደ ስራ ተገብቷል።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ለትምህርት ጥራትና ተደራሽነት መረጋገጥ የላቀ ሚና ይጫወታል
በዘመናዊ ዓለም ሁለንተናዊ ተወዳዳሪ ለመሆን ከምንም በላይ የዲጂታል ልማትና የቴክኖሎጂ አቅምን ማሳደግ መሰረታዊ ጉዳይ በመሆኑ መንግስት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ መሆኑም ይታወቃል።
በመሆኑም የዘርፉን ዕቅድና ትግበራ በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ምሁራን፤ የኢትዮጵያ የዲጂታል ስትራቴጂ ትግበራ በዘርፉ ልማት ሀገሪቷን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።
በዩኒቨርሲቲው ኮምፒዩቲንግና ሶፍትዌር ምህንድስና ፋካልቲ ዲን ጌታሁን ትዕግስቱ (ረዳት ፕሮፌሰር) የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ትግበራ በዘርፉ ልማት ጥሩ መሰረት ያኖረ ስለመሆኑ አስታውሰዋል።
ከዚህ ስኬት በመነሳትም የ2030 ስትራቴጂክ ዕቅድ ትግበራ በይፋ መጀመሩ ኢትዮጵያን በዲጂታል አገልግሎት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚያደርጋት መሆኑን ገልጸዋል።
በዩኒቨርሲቲው የኮምፒዩቲንግና ሶፍት ዌር መምህር ተመራማሪ እና የዲጂታል ትምህርት ክፍል ዳይሬክተር መሐመድ አበበ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የምትከተለው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ስርአት በቴክኖሎጂ እንዲደገፍ የዲጂታል አሰራር ምቹ መደላድል እየፈጠረ ነው፡፡
መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት ዜጎች በኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ዘመኑን የዋጀ የቴክኖሎጂ ዕውቀት እንዲጨብጡና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ዲጂታል አሰራሩ ዜጎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ እንዲሆኑና ወጥ የሆነ መረጃ እንዲኖራቸው ማስቻሉን ገልጸዋል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ኢትዮጵያን ካደጉ ሀገራት ጋር በዘርፉ ያላትን ተወዳዳሪነት የሚያሳድግ ብሎም የቴክኖሎጂ ማዕከል እንድትሆን የሚያስችል ነው።
በተለይ በኤሌክትሪክና ኔትዎርክ መሠረተ ልማት ማስፋፋት ላይ ትኩረት መደረጉ ዜጎች በፍትሃዊ መንገድ ዲጂታል አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያደርግ መሆኑን አስረድተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን ታህሳስ 11 ቀን 2018 ዓ.ም በይፋ ማስጀመራቸው የሚታወስ ነው።
በወቅቱም ስትራቴጂው ተደራሽነትን ማስፋት፣ እኩል ዕድል ማመቻቸት እና በተቋማትና ህዝብ መካከል መተማመንን መፍጠር ላይ ያተኮሩ ትልሞች እንዳሉት ማብራራታቸውም እንዲሁ።