ቀጥታ፡

የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ የአፍሪካ አቪዬሽን ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የተወሰደ ትልቅ እርምጃ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 2/2018(ኢዜአ)፦የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ የአፍሪካን አቪዬሽን እድገት አስሮ የያዘውን የመሰረተ ልማት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የተወሰደ ትልቅ እርምጃ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታን ዛሬ በይፋ አስጀምረዋል።  


 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታው በሁለት ምዕራፎች ተከፍሎ የሚከናወን ነው።

የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ለኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ ስርዓት የዘመናት ስብራት ምላሽ የሚሰጥ ነው

በመጀመሪያው ምዕራፍ የሚገነባው አውሮፕላን ማረፊያ በዓመት 60 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል ብለዋል።

በዚህ ምዕራፍ አንድ እጅግ ትልቅና ዘመናዊ እንዲሁም አንድ መለስተኛ የመንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናሎች እንደሚገነቡ ጠቅሰዋል።

ሁለት በተጓዳኝ የሚሰሩ የአውሮፕላን መንደርደሪያዎች እንዲሁም 180 አውሮፕላኖችን በአንድ ጊዜ ማቆም የሚያስችል ቦታ ይገነባልም ብለዋል።

በተጨማሪ 350 ማረፊያ ክፍሎች ያሉት ዘመናዊ ሆቴል በተርሚናሉ ውስጥ እንደሚገነባም ነው ዋና ሥራ አስፈፃሚው የተናገሩት።


 

በዓመት አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ቶን ጭነት የሚያስተናግድ የካርጎ ተርሚናል እና የአውሮፕላን ጥገና ማዕከልም በዚሁ ምዕራፍ እንደሚገነባ አስታውቀዋል።

አዲሱ አውሮፕላን ማረፊያ ከነባሩ የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጋር በፈጣን ባቡር እና በፈጣን የመኪና መንገድ እንደሚገናኝ አስረድተዋል።

ይህ ግዙፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ የአፍሪካን አቪዬሽን እድገት አስሮ የያዘውን የመሰረተ ልማት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የተወሰደ ትልቅ እርምጃ ነው ሲሉ ገልፀዋል።

ፕሮጀክቱ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ አህጉርም ትልቅ አርአያ እንደሚሆን ተናግረዋል።።

በተለይም የአፍሪካ ነፃ አህጉራዊ ንግድ ቀጣናን ተግባራዊነት ለማቀላጠፍና የአህጉሪቱን የንግድና የኢኮኖሚ ትስስር ለማጠናከር ቁልፍ ሚና ይጫወታል ብለዋል።


 

አውሮፕላን ማረፊያው ከፍተኛ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር የገለጹት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ ከአውሮፕላን ማረፊያው ጋር ተያይዞ የሚመሰረተው የኤርፖርት ከተማም በንግድ፣ በኢንዱስትሪና በቱሪዝም ዘርፎች ለአካባቢው ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመሠረተ ልማትና ፕላኒንግ ክፍል ኃላፊ አቶ አብረሃም ተስፋዬ በበኩላቸው፤ አካባቢው አሁን ለሚሰራውም ሆነ ለወደፊት ተያያዥ የማስፋፊያ ስራዎች አመቺ እንደሆነ ገልፀው፤ ቦታው ለታለመለት ግዙፍ ፕሮጀክት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ እንዳለው አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት የመሬት ጠረጋ (Earthwork) ስራዎችን የሚያከናውነው ኮንትራክተር ወደ ስራ ገብቷል ብለዋል።

የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ እ.ኤ.አ በ2030 እንደሚጠናቀቅ ጠቁመው፤ ለዋናው ግንባታ የሚሆኑ ተቋራጮችን የመምረጥ ሂደትም መጀመሩን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም