የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ለኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ ስርዓት የዘመናት ስብራት ምላሽ የሚሰጥ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ለኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ ስርዓት የዘመናት ስብራት ምላሽ የሚሰጥ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 2/2018(ኢዜአ)፦ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ለኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ ስርዓት የዘመናት ስብራት ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታን ዛሬ በይፋ አስጀምረዋል።
የአውሮፕላን ማረፊያው ግንባታ በሁለት ምዕራፍ የሚከናወን ሲሆን፤ ግንባታው ሲጠናቀቅ በዓመት 110 ሚሊየን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል።
የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ 60 ሚሊየን መንገደኞች የማስተናገድ አቅም በመያዝ እንደ አውሮውፓውያን አቆጣጠር በ2030 እንደሚጠናቀቅም ነው የተገለጸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፉት 80 ዓመታት የጥንታዊ ሀገር ምልክትና ኩራት ሆኖ ስኬታማ ስራ ማከናወኑን ተናግረዋል።
አየር መንገዱ በእነዚህ ዓመታት ያለፈባቸው መንገዶች አልጋ በአልጋ እንዳልነበሩ አስታውሰው፤ በኢትዮጵያ ያጋጠሙ የመንግስት ስርዓት መለዋወጥም ሆኑ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ሳይበግሩት በከፍተኛ ብቃት የአፍሪካ ኩራት መሆን መቻሉንም አብራርተዋል።
ከአየር መንገዱ የስኬታማነት ጉዞ ጀርባ ያለው ታላቅ ምስጢር ደግሞ ጠንካራ የኮርፖሬት ባህል መገንባት መቻሉ መሆኑንም አንስተዋል።
በዚህም አየር መንገዱ ጥቅሙን ባስጠበቀ መልኩ ያለምንም ጣልቃ ገብነት ነጻ ሆኖ በዓለም አቀፍ የቢዝነስ ህግ እየተመራ መቀጠሉን ነው የተናገሩት።
ለደህንነት ቅድሚያ የሚሰጥ፣ በፈጠራና ትጋት የሚሰሩ አመራሮች፣ በተደመረ አቅም የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በትጋትና ሃላፊነት የሚሸከሙ ሰራተኞች ያሉት መሆኑን አውስተው፤ ተቋሙ ዘወትር ለመማር ዝግጁ መሆኑ ደግሞ አየር መንገዱን ልዩ እንደሚያደርገውም አብራርተዋል።
ዛሬ ግንባታው የተጀመረው የአውሮፕላን ማረፊያው በዓመት 110 ሚሊዮን መንገደኞችን በማስተናገድ በዓለም ላይ ካሉ ጥቂት ግዙፍ አውሮፕላን ማረፊያዎች አንዱ እንደሚሆን ተናግረዋል።
አዲስ የሚገነባውን አውሮፕላን ማረፊያ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጋር የሚያገናኝና በአንድ ጊዜ 12 ተሽከርካሪ ማስተናገድ የሚችል የፍጥነት መንገድ እንዲሁም ፈጣን የባቡር መንገድ እንደሚገነባም ገልጸዋል።
የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ በሰማይ ለሚበሩ መርከቦቻችን እንደ ትልቅ ወደብ ሆኖ ያገለግላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህም ለኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ ስርዓት የዘመናት ስብራት ምላሽ የሚሰጥ ስለመሆኑ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በርካታ ፈተናዎችን ተቋቁሞ ስኬታማ እንደሆነ ሁሉ የሚገጥሙን ፈተናዎች ይበልጥ እንድንተጋ እና ለስኬታችን እንድንጸና ያደርጉናል ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ140 በላይ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች ያሉት ግዙፍ ኩባንያ ሲሆን፤ በተያዘው እኤአ 2026 ተጨማሪ አዳዲስ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን ወደ ስራ እንደሚያስገባም ይጠበቃል።