ቀጥታ፡

አማድ ዲያሎ - የአፍሪካ እግር ኳስ  ብሩህ ተስፋ

ተጫዋቹ አዲሱ ሳሙኤል ኤቶ የሚል ስያሜ እየተሰጠው ይገኛል።

ፍጥነቱን ከዲዲየር ድሮግባ ጋር ያነጻጽሩታል።  ለተጋጣሚ ተጫዋቾች የራስ ምታት እና ፈተና የሆነውን ግራ እግሩን ከሌላኛው የግራ እግር ምትሃተኛ ሪያድ ማህሬዝ ጋር የሚያወዳድሩም አልጠፉም።


 

በዚህ አካሄዱ ከቀጠለ ያለ ምንም ጥርጥር ወደፊት በእግር ኳስ ከምንመለከታቸው ኮከቦች አንዱ ሊሆን ይችላል እየተባለለት ይገኛል።

ይህ ተጫዋች በማንችስተር ዩናይትድ የ147 ዓመታት ታሪክ ሀትሪክ የሰራ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ተጫዋች ነው።

እያወራን የምንገኘው የማንችስተር ዩናይትድ 16 ቁጥር ማልያ ለባሽ አማድ ዲያሎ ነው።

የ23 ዓመቱ ኮትዲቯራዊ ተስፈኛ ተጫዋች በቀያዮቹ ሴጣኖች እያሳየ ያለው ብቃት ከብዙዎች ዘንድ ሙገሳ አስችሮታል፣ አድናቆት እንዲጎርፍለት አድርጓል።

ወደ ኋላ መለስ እንበልና የአማድ ዲያሎን መነሻ እንመልከት።

ካሜሮን ከአዘጋጇ ሞሮኮ ለግማሽ ፍጻሜ ለማለፍ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው

አማድ የተወለደው እ.አ.አ ጁላይ 11 2002 በኮትዲቭዋር መዲና አቢጃን ነው።

ተጫዋቹ በአፍሪካ ምድር ቢወለድም ገና በህጻንነት እድሜው ነበር ወደ ጣልያን የተሰደደው። የእግር ኳስ ህይወቱን የጀመረው እ.አ.አ በ2014 በጣልያን ሬጂዮ ኢሚሊያ ግዛት በሚገኘው ቦካ ባርኮ የታዳጊ ቡድን ነው።

ቡድኑን በተቀላቀለበት ዓመት የገና በዓል (ክሪስማስን) በማስመልከት በተካሄደ ውድድር ላይ በ12 ዓመቱ ኮከብ ግብ አግቢ ሲሆን ያሳየው አስደማሚ ብቃት የብዙዎችን ቀልብ ሳበ።

ይህ የገና በዓል ውድድር አማድን እ.አ.አ በ2015 በቦካ ባርኮ ቡድን እንዲመዘገብ አደረገው።

ተጫዋቹ በቡድኑ ብዙም አልቆየም። የበርካታ የጣልያን ሴሪአ ክለቦች አይን አረፈበት። ብዙም ሳይቆይ በዛው በ2015 ወደ ጣልያኑ አትላንታ አመራ።


 

አማድ ከእ.አ.አ 2015 እስከ 2019 ለአትላንታ ታዳጊ ቡድን የተጫወተ ሲሆን እ.አ.አ 2019 እና 20 ለዋናው ቡድን ተጫውቷል።

ለዋናው ቡድን አራት ጨዋታዎችን አድርጎ ማስቆጠር የቻለው አንድ ግብ ብቻ ነው።

የእንግሊዙ ክለብ ማንችስተር ዩናይትድ ተጫዋቹ በጣልያኑ ክለብ ባሳየው ብቃት በ18 ዓመት እድሜው እ.አ.አ ጃንዋሪ ወር 2021 በአምስት ዓመት ኮንትራት በ37 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዩሮ አስፈርሞታል።

ተጫዋቹ ወደ ማንችተር ሲመጣ ቀጥታ ወደ ዋናው ቡድኑ አልተቀላቀለም። በቡድኑ ከ23 ዓመት በታች ጨዋታውን ማድረግ ጀመረ።

አማድ የመጀመሪያ ጨዋታውን ለማንችስተር ያደረገው እ.አ.አ ፌብሩዋሪ 18 2021 ቡድኑ ከሪያል ሶሲዬዳድ ጋር ባደረገው የዩሮፓ ሊግ ጨዋታ ነው። በዛው ዓመት በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ እና አውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ላይ የመጀመሪያ ጨዋታውን አድርጓል።

ዲያሎ ከእ.አ.አ 2022-2023 ባለው ጊዜ ሬንጀርስ እና ሰንደርላንድ በውሰት የተጫወተ ሲሆን በቡድኖቹ ባደረጋቸው 47 ጨዋታዎች 16 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፏል።


 

እ.አ.አ በ2023/24 አማድ ወደ ማንችስተር ዩናይትድ በመመለስ በድጋሚ መጫወት ጀምሯል። በክለቡም ድንቅ ብቃቱን እያሳየ መምጣት ጀመረ።

እ.አ.አ ጥር 17 2025 ማንችስተር ዩናይትድ ከሊጉ ከወረደው ሳውዝሃምፐን ጋር በነበረው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር በ12 ደቂቃ ውስጥ ሶስት ግቦችን አስቆጥሮ ሀትሪክ በመስራት ቡድኑ 3 ለ 1 አንዲያሸንፍ ያደረገበት መንገድ አድናቆት አስችሮታል።

በዚህም አማድ በማንችስተር ዩናይትድ የ147 ታሪክ የመጀመሪያ ሀትሪክ የሰራ አፍሪካ ተጫዋች በመሆን አዲስ ታሪክ ጽፏል።

አማድ በቀያዮቹ ሴጣኖች ማልያ እስከ አሁን ባደረጋቸው 53 ጨዋታዎች 11 ግቦችን አስቆጥሯል።

ተጫዋቹ ከክለቡ በተጨማሪ ለኮትዲቯር ብሄራዊ ቡድን በመጫወት ላይ ይገኛል።

እ.አ.አ 2021 ኮትዲቯር ከኒጀር ጋር ባደረገችው ጨዋታ በ86ኛው ደቂቃ ተቀይሮ በመግባት ለብሄራዊ ቡድኑ የመጀመሪያ ጨዋታውን አድርጓል።

ለሀገሩ እስከ አሁን ባደረጋቸው 15 ጨዋታዎች አምስት ግቦችን አስቆጥሯል። የመጀመሪያ ጎሉን ኮትዲቯር በ2021 በወዳጅነት ጨዋታ ቡርኪናፋሶን 2 ለ 1 ስታሸነፍ ነበር ያስቆጠረው።

አማድ ዲያሎ ዘንድሮ በሞሮኮ አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ድንቅ ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል።

አማድ በውድድሩ ላይ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ሶስት ግቦችን ያስቆጠረ ሲሆን አንድ ለግብ የሚሆን ግብ አመቻችቶ አቀብሏል።

ኮትዲቯር ከሞዛምቢክ፣ ካሜሮን እና ቡርኪናፋሶ ጋር ባደረገቻቸው ጨዋታዎች የጨዋታው ኮከብ ሆኖ ተምርጧል።

የወቅቱ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ ኮትዲቯር ሩብ ፍጻሜ እንድትደርስ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ኮትዲቯር ከግብጽ በሩብ ፍጻሜው ነገ ከግብጽ ጋር  ምሽት አራት ሰዓት ላይ በአጋዲር ስታዲየም የምታደርገው ጨዋታ በጉጉጉት ይጠበቃል።  ሀገሩ በጠዋታው ላይ ከአማድ ብዙ ትጠብቃለች።

ወደ ክለብ እንቅስቃሴው ስንመለስ አማድ በማንችስተር ዩናይትድ ስብስብ ውስጥ ቁልፍ የሚባል ተጫዋች ነው።

ፈጣን ኳስን የማንከበላል ክህሎቱ፣ ፍጥነቱ ፣ የቴክኒክ አቅሙ፣ ጨዋታን የማንበብ ብቃቱ እና ሁለቱንም እግሩን የመጠቀም አቅሙ  አልፎም ተጫዋቾችን በቄንጥ የሚያልፍበት መንገድ ተጫዋቹን እያስወደሰው ነው።

አማድ ዲያሎ  ከክንፍ ተጫዋችነቱ ባሻገር የአጥቂ አማካይ ሆኖ መጫወትም ይችላል።

እ.አ.አ በ2020 የ18 ዓመት ልደቱን ተከትሎ ተጫዋቹ ስሙን ከአማድ ትራኦሬ ወደ አማድ ዲያሎ አስቀይሯል።

አማድ ካለው ድንቅ ብቃት አንጻር ወደፊት በክለብ እና ብሄራዊ ቡድን ደረጃ ድንቅ ጊዜን ካሳለፉ ታዋቂ የአፍሪካ ተጫዋቾች ተርታ የመሰለፉ ጉዳይ አያጠራጥርም።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም