ካሜሮን ከአዘጋጇ ሞሮኮ ለግማሽ ፍጻሜ ለማለፍ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ካሜሮን ከአዘጋጇ ሞሮኮ ለግማሽ ፍጻሜ ለማለፍ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 1/2018 (ኢዜአ)፦ በሞሮኮ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከሁለት ቀናት እረፍት በኋላ ዛሬ በሩብ ፍጻሜ መርሃ ግብር ይመለሳል።
ምሽት አራት ሰዓት ላይ ካሜሮን ከሞሮኮ በፕሪንስ ሙላይ አብደላ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ የእግር ኳስ አፍቃሪያንን ትኩረት ስቧል።
በጥሎ ማለፉ ካሜሮን ደቡብ አፍሪካን፣ ሞሮኮ ታንዛንያን በማሸነፍ የመጨረሻ ስምንት ውስጥ ገብተዋል።
ሁለቱ ሀገራት በአፍሪካ ዋንጫ ሲገናኙ የአሁኑ ለአራተኛ ጊዜ ነው።
ግብጽ እ.አ.አ በ1986 ባዘጋጀችው 15ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ ሁለት ተገናኝተው አንድ አቻ ተለያይተዋል።
ሮጀር ሚላ ለካሜሮን፣ አብዱልከሪም ሜሪ ለሞሮኮ በወቅቱ ግቦቹን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።
እ.አ.አ በ1988 በሞሮኮ በተካሄደው 16ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በግማሽ ፍጻሜው ተጫውተው ካሜሮን በስሪል ቶማስ ማካናኪ ግብ 1 ለ 0 በማሸነፍ ለፍጻሜው አልፋለች። ካሜሮን በፍጻሜው ናይጄሪያን በማሸነፍ ዋንጫውን አንስታለች።
ሴኔጋል እ.አ.አ በ1992 ባዘጋጀችው 18ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ ሁለት ተገናኝተው ካሜሮን በአንድሬ ካና-ቢይክ 1 ለ 0 አሸንፋለች።
በአጠቃላይ ሁለቱ ቡድኖች በአህጉራዊው መድረክ ሶስት ጊዜ ተገናኝተው ካሜሮን ሁለት ጊዜ ስታሸንፍ አንድ ጊዜ አቻ ተለያይተዋል።
ሁለቱ ሀገራት ከ34 ዓመታት በኋላ ዳግም በአፍሪካ ዋንጫ ተገናኝተዋል።
አምስት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን በማንሳት ከግብጽ ቀጥሎ ስኬታማ የሆነችው ካሜሮን እና የአፍሪካ የወቅቱ ምርጥ ቡድን ተብላ የተሰየመችው ሞሮኮ የሚያደርጉት ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
አዘጋጇ ሞሮኮ የአፍሪካ ዋንጫን አንድ ጊዜ አንስታለች።
የሁለቱ ቡድኖች አሸናፊ ከናይጄሪያ እና አልጄሪያ አሸናፊ ጋር ይጫወታል።
በሌላኛው የሩብ ፍጻሜ መርሃ ግብር ማሊ ከሴኔጋል ምሽት አንድ ሰዓት ላይ በታንጀር ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በጥሎ ማለፉ ማሊ ቱኒዚያን፣ ሴኔጋል ሱዳንን በማሸነፍ ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቅለዋል።
ሀገራቱ በአፍሪካ ዋንጫው ሲገናኙ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
ቱኒዚያ እ.አ.አ በ2004 ባዘጋጀችው 24ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ ሁለት ተጫውተው አንድ አቻ ተለያይተዋል።
ሃቢብ ፍሬድሪክ ቤይ ለሴኔጋል፣ ድራማኔ ትራኦሬ ለማሊ በወቅቱ ግቦቹን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።
ከ22 ዓመታት በኋላ በአፍሪካ ዋንጫው ወደ ግማሽ ፍጻሜ ለማለፍ በሚደረግ ፍልሚያ ይገናኛሉ።
ማሊ በአፍሪካ ዋንጫ ትልቅ ውጤቷ በስምንተኛው እና በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችበት ነው። ሴኔጋል አንድ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን አንስታለች።
በኮከብ ተጫዋቾች ስብስብ የተሞላችው ሴኔጋል የማሸነፍ ቅድሚያ ግምቱን አግኝታለች። አንድም ጨዋታ ሳታሸንፍ ሩብ ፍጻሜ የደረሰችው ማሊ ለተጋጣሚዋ ጠንካራ ፈተና ትሆናለች ተብሎ ይጠበቃል።
የማሊ እና ሴኔጋል አሸናፊ በግማሽ ፍጻሜው ከግብጽ እና ኮትዲቯር አሸናፊ ጋር ይጫወታል።