በአሮሚያ ክልል በዲጂታል ቴክኖሎጂ አገልግሎት አሰጣጥን ማቀላጠፍ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአሮሚያ ክልል በዲጂታል ቴክኖሎጂ አገልግሎት አሰጣጥን ማቀላጠፍ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
አዲስ አበባ ፤ ታኅሣስ 18/2018 (ኢዜአ)፡- በአሮሚያ ክልል በዲጂታል ቴክኖሎጂ የመረጃ አያያዝና የአገልግሎት አሰጣጥን ይበልጥ ቀልጣፋ ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ባለስልጣን ገለጸ።
በክልሉ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ባለስልጣን ለብልፅግና ፓርቲ የአሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የበለፀገ "ሞሳጅ " የተሰኘ መተግበሪያ ዛሬ ተመርቆ ስራ ጀምሯል፡፡
የባለስልጣኑ ሀላፊ አቶ መኮንን በየነ እንዳመለከቱት፤ በክልሉ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ለማፋጠን በኢትዮ ቴሌኮም አማካኝነት የሞባይል ኔትዎርክ ሽፋን በገጠር ቀበሌዎች ተደራሽ ተደርጓል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የከተሞችን ዘመናዊነት ለማሳደግ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው
የዲጂታል ኢትዮጵያ ትግበራ የከተሞችን አገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመን መሠረት ጥሏል
ዛሬ የተመረቀው መተግበሪያ የፓርቲውን የውስጥ አሰራርና አስተዳደርን የሚያዘምንና ለሌሎች የመንግስት መስሪያ ቤቶች አርአያ በመሆን እድገትን ለማፋጠን እንደሚያግዝ አንስተዋል።
የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማስፋፋት የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥና መረጃዎችን ዲጂታላይዝድ በማድረግ ውጤታማ ተግባር መከናወኑን ጠቅሰው፤ ዘርፉን የማጠናከሩ ተግባር መቀጠሉንም ተናግረዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍና የአቅም ግንባታ ሀላፊ አቶ ነመራ ቡሊ እንደገለጹት፤ የበለፀገው መተግበሪያ ፓርቲው የዲጂታል ቴክኖሎጂ አሰራርን በመከተል ራሱን በማዘመን ሕዝቡ ጋር ለመድረሰ ታስቦ የተዘጋጀ እና የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ትልሞችን የሚደግፍ ነው።
የፓርቲውን አባላትና ሌሎችንም መረጃዎች ለመያዝ፤ ስርዓት ያለው የዳታ ሲስተም ለመዘርጋት፣ የእቅድና የግምገማ ስርዓትና የመዋቅርና የስራ አፈጻጸም የሚገመገምበት ዓይነተኛ መሳሪያ ነው ብለዋል።
በክልሉ የዲጂታል 2025 ትግበራ በሁሉም የልማት ዘርፎች አመርቂ ውጤት ማምጣቱንም አቶ ነመራ አስታውሰዋል።
የዲጂታል መሰረተ ልማትን የማሟላትና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ የእውቀትና ክህሎት ማሳደጊያ ስራን በማጠናከር ዲጂታል 2030ን እውን ለማድረግ ርብርብ እንደሚደረግም ገልጸዋል።