ቀጥታ፡

የዲጂታል ኢትዮጵያ ትግበራ የከተሞችን አገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመን መሠረት ጥሏል

ጎንደር፤ ታኅሣስ 18/2018 (ኢዜአ)፡- የዲጂታል ኢትዮጵያ ትግብራ የከተሞችን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመን መሠረት መጣሉን የጎንደር ከተማ አስተዳደር የስማርት ሲቲ ዳይሬክተር ይልቃል ሙሉአለም (ዶ/ር) ገለጹ።

ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 መጠናቀቅን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን በቅርቡ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የጎንደር ከተማ አስተዳደር የስማርት ሲቲ ዳይሬክተር ይልቃል ሙሉአለም (ዶ/ር)  እንደገለጹት፤ ዲጂታል ኢትዮጵያ ከተሞችን በቴክኖሎጂ በማደራጀት ለተገልጋዩ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል።

ስማርት ሲቲን በመፍጠር የከተሞችን ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ አገልግሎቶች እንዲቀላጠፉ የራሱን ሚና እንደሚጫወትም ነው የገለጹት፡፡  

በተለይም ዲጂታል ፋይናንስን ለማቀላጠፍና ወንጀልን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዲጂታል ኢትዮጵያ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ለማሳካትና ወጥ የሆነ የመረጃ አያያዝን በማጠናከር ለሀገራዊ እድገት ጉልህ ድርሻ እያበረከተ መሆኑንም ነው የገለጹት። 

የአርተፊሻል ኢንተለጀንስና የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና መጀመር ዲጂታል ኢትዮጵያን ስኬታማ ለማድረግ ተጨማሪ አቅም እንደሚሆንም አስረድተዋል።

የመንግስት አገልግሎት በቴክኖሎጂ ታግዞ መሰጠቱ ተጠያቂነትንና ግልጸኝነትን በማስፈን ሲስተዋሉ የነበሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

እንደ ይልቃል (ዶ/ር) ገለጻ፤ ኢትዮጵያ እስከ 2030 የሚዘልቅ የዲጂታል ስትራቴጂ መንደፏ ዓለም አቀፍ ተቀባይነትና ተወዳዳሪነቷን የሚያሳድግ ነው። 

ከአማራ ክልል ከተሞች መካከል ጎንደር በስማርት ሲቲ ቴክኖሎጂ የመጀመሪያና ፈር ቀዳጅ ተግባራትን እያከናወነች መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ይህም የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማነቃቃት ያስችላል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን በቅርቡ በይፋ ማስጀመራቸው የሚታወስ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም