ቀጥታ፡

ብቁና ተወዳዳሪ ዜጎችን ለማፍራት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

አምቦ፤ ታህሳስ 17/2018 (ኢዜአ)፦ በሁሉም መስክ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጎችን ለማፍራት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ።

የትምህርት ሚኒስትሩን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በአምቦ ዩኒቨርስቲ የወሊሶ አዳሪ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የትምህርት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ዛሬ ተካሄዷል።

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት ጥራት ለማስጠበቅ ዘመናዊ የሕክምና መሳሪያዎችን ለማሟላት እየተሰራ ነው

በመርሃ ግብሩ ላይም የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንዳሉት፤ ሚኒስቴሩ ጥራት ያለው ትምህርትን ለሁሉም ዜጎች በፍትሃዊነት ለማዳረስ እየሰራ ነው።

ለዚህም በሁሉም መስክ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጎችን ለማፍራት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።

እንደ ትምህርት ሚኒስትሩ ገለፃ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት እንደ ሀገር 13 ልዩ ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት መታቀዱን ጠቁመው ለትምህርት ቤቶቹም አስፈላጊው ግብዓት ተሟልቶላቸው ወደ ስራ ይገባሉ።

በተያዘው ዓመትም አምስት አዳሪ ትምህርት ቤቶች ወደ ስራ እንደሚገቡ ሚኒስትሩ አመልክተዋል።

የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅም የመምህራንን አቅም የማጎልበት፣ የትምህርት ግብዓትን የማሟላትና የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙም ተናግረዋል።


 

የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ቶላ በሪሶ (ዶ/ር) በበኩላቸው በክልሉ የትምህርትን ጥራትን ለማስጠበቅ ቡኡራ ቦሩ በተሰኙ ትምህርት ቤቶች ላይ በስፋት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በክልሉ በአሁኑ ወቅት ከ19 ሺህ በላይ የቡኡራ ቡሩ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ተማሪዎችን ተቀብሎ በተሳካ ሁኔታ እያስተማረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የቡኡራ ቦሩ ትምህርት ቤቶች ሚና የጎላ መሆኑን ኃላፊው ጠቁመው ትምህርት ቤቶቹን ከማስፋፋት ጎን ለጎንም ግብዓትን የማሟላትና በቴክኖሎጂ የማስደገፍ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም