ቀጥታ፡

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት ጥራት ለማስጠበቅ ዘመናዊ የሕክምና መሳሪያዎችን ለማሟላት እየተሰራ ነው

ጅማ፤ ታህሳስ 17/2018(ኢዜአ)፦በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት ጥራት ለማስጠበቅ ዘመናዊ የሕክምና መሳሪያዎችን ለማሟላት እየተሰራ  መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ጤና ኢንስቲትዩት ዘመናዊ የሕክምና መሳሪያዎችን ከትምህርት ሚኒስቴር በድጋፍ አግኝቷል።

የትምህርት ሚኒስቴር ለጅማ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ድጋፉን ያደረገው ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመተባበር መሆኑም በድጋፍ ርክክብ መርሃግብሩ ላይ ተገልጿል።

በርክክብ መርሃግብሩ ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኮራ ጡሹኔ እንዳሉት፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በጤናው ዘርፍ ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ሀይል ለማፍራት ከሚያከናውኑት ተግባር በተጓዳኝ ለህብረተሰቡ  የሕክምና አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል። 


 

በተቋማቱ የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት ጥራት ለማስጠበቅም ዘመናዊ የሕክምና መሳሪያዎችን ለማሟላት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ለእዚህም ሚኒስቴሩ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ ኮራ፤ ዛሬ ለጅማ ዩኒቨርሲቲ የተደረገው  የሕክምና መሳሪያ  ድጋፍ የዚሁ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጀማል አባፊጣ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት፤ የዩኒቨርሲቲው ጤና ኢንስቲትዩት በጤናው ዘርፍ በክህሎትና በስነ ምግባር የዳበረ የሰው ሀይልን ለማፍራት ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል።


 

ከዚህ በተጨማሪ ኢንስቲትዩቱ ለአካባቢው ማህበረሰብ የሕክምና አገልግሎትን በመስጠት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።

ዛሬ የተደረገው ዘመናዊ የሕክምና መሳሪያ ድጋፍ የመማር ማስተማር ስራውን ከማቀላጠፍ ባለፈ ኢንስቲትዩቱ የሚሰጠውን የሕክምና አገልግሎት ጥራት ለማሳደግ ከፍተኛ እቅም እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።


 

ዩኒቨርሲቲው በድጋፍ ያገኛቸው 25 ሚሊዮን ብር የሚያወጡት የሕክምና መሳሪያዎች ላፓሮስኮፒ፣ ኢሲዩ፣ ፔሸንት ሞኒተር፣ አልትራሳውንድና ኢንዶስኮፒ መሆናቸውንም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።

በሕክምና መሳሪያ ርክክብ ስነስርአቱ ላይ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኮራ ጡሹኔን ጨምሮ ከፍተኛ የሕክምና ባለሙያዎች እና የዩኒቨርስቲው አመራሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም