የአየር ኃይል የምስረታ በዓል የተቋሙን የጀግንነት ጉዞ፣ የተከፈለውን መስዋዕትነትና የተመዘገቡ ለውጦችን በሚያሳይ መልኩ ይከበራል - ኢዜአ አማርኛ
የአየር ኃይል የምስረታ በዓል የተቋሙን የጀግንነት ጉዞ፣ የተከፈለውን መስዋዕትነትና የተመዘገቡ ለውጦችን በሚያሳይ መልኩ ይከበራል
አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 16/2018 (ኢዜአ)፡-የአየር ኃይል የምስረታ በዓል የተቋሙን የጀግንነት ጉዞ፣ የተከፈለውን መስዋዕትነትና የተመዘገቡ የለውጥ ስኬቶችን በሚያሳይ መልኩ ከጥር 15 እስከ 19 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚከበር በኢትዮጵያ አየር ኃይል የአንደኛ አየር ምድብ አዛዥ ብርጋዴየር ጄኔራል ብሩክ ሰይፉ ገለፁ።
በበዓሉ ላይ "የአንበሶች ሰማይ! ኢትዮጵያ" በሚል የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከሌሎች አጋር ሀገራት ጋር በመሆን አስደናቂ የአየር ላይ ትርኢት እንደሚያቀርብም ተመላክቷል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል 90ኛ ዓመት የምስረታ ቀን አጠቃላይ እንቅስቃሴን የሚያሳይ ድረ-ገጽ ይፋ ሆነ
የአየር ሀይል የተመሰረተበት 90ኛ አመት ምክንያት በማድረግ ከፍተኛ ዝግጅት የተደረገበት የአየር ላይ ትርኢት ይካሄዳል-ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ
የኢትዮጵያ አየር ኃይል የአንደኛ አየር ምድብ አዛዥ ብርጋዴየር ጄኔራል ብሩክ ሰይፉ፤ የአየር ኃይሉን 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓል አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸው የኢትዮጵያ አየር ኃይል የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል "የኢትዮጵያ አየር ኃይል የነፃነትና የአንድነት ምልክት" በሚል መሪ ሃሳብ ከጥር 15 እስከ ጥር 19 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ ደማቅ መርሃ ግብሮች እንደሚከበር አስታውቀዋል።
በበዓሉ ከጥር 15 ቀን ጀምሮ በሚካሄደውና "የአንበሶች ሰማይ! ኢትዮጵያ" በተሰኘው መርሃ ግብር የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከሌሎች አጋር ሀገራት ጋር በመሆን አስደናቂ የአየር ላይ ትርኢት እንደሚያቀርብ አመላክተዋል።
በዚህም የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ የሩሲያ የአየር ኃይል ትርኢት ቡድን፣ የሞሮኮ እና የቼክ ሪፐብሊክ አየር ኃይሎች በጋራ በመሆን የጥቁር አንበሳ የአየር ትርኢት እንደሚያቀርቡ ጠቅሰዋል።
"የወደፊቱን የአቪዬሽን አቅም በጋራ እንገንባ" በሚል መሪ ሀሳብ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ የቻይና፣ ህንድ፣ አሜሪካ እና ደቡብ አፍሪካ ግዙፍ ኩባንያዎች የሚሳተፉበት ኤክስፖ እንደሚካሄድም ገልፀዋል።
ከ25 በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ የቴክኖሎጂ ተቋማት የደረሱበትን ደረጃ ለጉብኝት ክፍት የሚያደርጉበት "ስታቲክ ዲስፕለይ እና የአቪዬሽን ቴክኖሎጂ ኤክስፖ 2026" እንደሚካሄድም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የአህጉሪቱ የአቪዬሽን ማዕከል መሆኗን የምታረጋግጥበት "ፊውቸር አፍሪካ አየር ኃይሎች ፎረም" ለሶስተኛ ጊዜ እንደሚካሄድም ተናግረዋል።
"የጋራ ስራዎቻችንን አጠናክረን የተረጋጋ ዓለም እንገንባ" በሚል መሪ ሃሳብ በሚካሄደው መድረክ ላይ ከ38 በላይ የአፍሪካ ሀገራት የአየር ኃይል አዛዦችና ታላላቅ የአቪዬሽን ባለሙያዎች ይታደማሉ ነው ያሉት።
የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አዛዦችና የመንግስት ባለስልጣናት "ሀገርን በማገልገል የሚገኝን ክብር መዘከር" በሚል ርዕስ ከህዝቡ ጋር ውይይት እንደሚያደርጉም ጠቅሰዋል።
በዓሉ የአየር ኃይሉን የ90 ዓመት የጀግንነት ጉዞ፣ የተከፈለውን መስዋዕትነትና የተመዘገቡ የለውጥ ስኬቶችን በማሳየት ይከበራል ነው ያሉት።
መላው የሀገሪቱ ህዝብ በዚህ ታሪካዊ በዓል ላይ በመገኘት የኢትዮጵያ አየር ኃይል የደረሰበትን ዝግጁነት እንዲመለከት ጥሪ አቅርበዋል።
የበዓሉ አካል የሆነና "ለአየር ኃይል እድገት በሙሉ አቅሜ እሮጣለሁ" በሚል መሪ ሃሳብ ባሳለፍነው ህዳር 21 ቀን 2018 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ የ10 ኪሎ ሜትር ዓለም አቀፍ የጎዳና ላይ ሩጫ መካሄዱን አስታውሰዋል።
ይህ ውድድር በህዝብና በተቋሙ መካከል ያለውን ትስስር ያጠናከረና ለዋናው በዓል መሰረት የጣለ ታሪካዊ ኹነት ሆኖ ማለፉንም ገልጸዋል።