ቀጥታ፡

የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት በተጠናከረ ዝግጅትና ቅንጅት ይሰራሉ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 13/2018(ኢዜአ)፦ የሀገራችን ዘላቂ ሰላምና ደኅንነት እንዳይሰፍን የሚንቀሳቀሱ አሸባሪና ፅንፈኛ ቡድኖችን በመቆጣጠር የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት በተጠናከረ ዝግጅትና ቅንጅት ይሰራሉ ሲሉ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት ጋር በሀገራዊ የፀጥታ ዕቅድ ላይ በዋና መሥሪያ ቤቱ ውይይት አካሂዷል።


 

በውይይቱ ላይ ኮሚሽነሩ እንደገለጹት የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት ባካሄዱት የተቀናጀ ኦፕሬሽን በርካታ ፀረ-ሰላም ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

የፌዴራል ፖሊስ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ራሱን በሰው ኃይል እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አደራጅቷል

በሀገራችን ዘላቂ ሰላምና ደኅንነት እንዳይሰፍን የሚንቀሳቀሱ አሸባሪና ፅንፈኛ ቡድኖችን በመቆጣጠር የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የፀጥታና ደኅንነት ተቋማቱ በተጠናከረ ዝግጅትና ቅንጅት እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

በቀጣይም ሕግ የማስከበር ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አንስተው ከፊታችን የሚከበሩ ሀይማኖታዊ እና ሕዝባዊ በዓላት ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከናወኑ በቂ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል።


 

‌‎የፀጥታና ደኅንነት ተቋማቱ ሕዝባዊ፣ መንግስታዊ እና ሀይማኖታዊ በዓላት ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበሩ በተዘጋጀው ዕቅድ ላይ በቴክኖሎጂ የታገዘ፣ በመረጃ ላይ የተመሠረተ፣ የሕብረተሰቡን ተሳትፎ ያረጋገጠ ኦፕሬሽን ለማካሄድ የሚያስችል ኦረንቴሽንና ስምሪት በመውሰድ በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች በቅንጅት እንደሚሰሩ አቅጣጫ ተቀምጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም