ቀጥታ፡

የፌዴራል ፖሊስ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ራሱን በሰው ኃይል እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አደራጅቷል 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 11/2018(ኢዜአ)፦ የፌዴራል ፖሊስ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ራሱን በሰው ኃይል እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማደራጀቱን  የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።

ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ፌዴራል ፖሊስ ዘመናዊ አደረጃጀት ከጀመረ 116 ዓመታት እንዳለፉት ተናግረዋል።

በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የሀገርን ሰላም እና ደህንነት እያረጋገጠ መቆየቱን ገልጸው፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ደግሞ ተጨባጭ ለውጥ በማድረግ የተሰጠውን ኃላፊነት በብቃት እየተወጣ መሆኑን አስረድተዋል።

ይህ ለውጥ፣ ፖሊስ የሰብዓዊ መብት፣ የህግና ሥርዓትን ባከበረ መልኩ የወንጀል መከላከልና የምርመራ ሥራዎችን በብቃት እንዲያከናውን አስችሎታል ብለዋል።

በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ስምሪት በመስጠት የወንጀል መከላከል አቅሙ ይበልጥ ማደጉንም ገልጸዋል።

የሀገርን ዘላቂ ሰላም ለማስጠበቅና የህግ የበላይነትን ለማስከበር ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በኃላፊነት እየሰራ እንደሆነ ተናግረዋል። 

ይህን ኃላፊነት የሚመጥን የሰው ኃይል በቁጥርም ሆነ በስልጠና ደረጃ እንዲያድግ፣ እንዲሁም የተሻለ ስልጠና ያገኙ ኦፊሰሮችን እያበቃ መሆኑን ጠቁመዋል።

የፌዴራል ፖሊስ የቴክኖሎጂ አቅሙን ለማሳደግ ሰፋፊ ስራዎች መስራቱን አንስተው በዚህም የተቋሙ የድሮን ኃይል፣ የዲጂታል መገናኛ ሬዲዮ፣ የኮማንድና ኮንትሮል ማዕከል እንዲሁም የዜጎች መተግበሪያ የሆነው EFPApp ባለቤት መሆኑን ጠቅሰዋል። 

እነዚህ ቴክኖሎጂዎች የፖሊስን ወንጀል የመከላከልና የመመርመር አቅም እያጎለበቱ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ከሌሎች ተቋማት ጋር ያለውን ትብብር እያጠናከረ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ከኢንተርፖል፣ ከአፍሪካ ፖሊስ ተቋም እና ከምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም