የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ በሁሉም የህክምና ክፍሎቹ ለሕብረተሰቡ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 11/2017(ኢዜአ)፦ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ እንደወትሮው ሁሉ በሁሉም የህክምና ክፍሎቹ ለህብረተሰቡ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ገለጸ፡፡

ኢዜአ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ እና በአለርት ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአገልግሎት አሰጣጥና አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴን በተመለከተ በስፍራው ተገኝቶ ቅኝት አድርጓል፡፡

የአዳማ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የአገልግሎት አድማሱን እያሰፋ ይገኛል

በዚህም ሆስፒታሎቹ ለህብረተሰቡ መደበኛ አገልግሎቶች ሲሰጡም ተመልክቷል፡፡


 

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ፕሮቮስት ዶክተር ሲሳይ ስርጉ፤ ሆስፒታሉ በሁሉም የአገልግሎት ክፍሎቹ ለህብረተሰቡ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

በዚህም በተመላላሽ ህክምና፣ በድንገተኛ፣ በሁሉም የጽኑ ህሙማን ክፍሎች ፣ በእናቶች እና ህጻናት እንዲሁም በሁሉም ዘርፎች አገልግሎት በመሰጠት ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ሜዲካል ዳይሬክተር እና የቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ፈቃዱ ነጋሽ፤ እንደ ቀዶ ህክምና ክፍል ድንገተኛ የቀዶ ህክምናን ጨምሮ ሌሎችም ሲከናወኑ መዋላቸውን ገልጸዋል።


 

ሆስፒታሉ በሁሉም የሥራ ክፍሎች ህሙማንን በመቀበል አስፈላጊውን አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡

በአለርት ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የህክምና አገልግሎት ሲያገኙ ያነጋገርናቸው ታካሚዎች በሆስፒታሉ የተሟላ ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

ከአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች መካከልም ሸምሱ ከድር እንዳለው በቀጠሮው መሠረት እናቱን ለማሳከም ወደ ሆስፒታሉ በመምጣት የአገልግሎት ጊዜውን እየተጠባበቀ እንደሚገኝ ተናግሯል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም