የአዳማ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የአገልግሎት አድማሱን እያሰፋ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
የአዳማ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የአገልግሎት አድማሱን እያሰፋ ይገኛል

አዳማ፤ ግንቦት 9/2017(ኢዜአ)፦ የአዳማ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የአገልግሎት አድማሱን እያሰፋ እንደሚገኝ የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ስንታየሁ ተክሌ ገለጹ።
በሆስፒታሉ እያገኙት ያለው የህክምና አገልግሎት የሚመሰገን መሆኑን ታካሚዎች ተናግረዋል።
ዋና ሥራ አስኪያጁ ለኢዜአ እንደገለጹት ሆስፒታሉ ለማህበረሰቡ የተሟላ ህክምና መስጠትን እንዲሁም በጤናው ዘርፍ ደግሞ ብቁ ሀኪሞችን ለማፍራት አላማ አንግቦ እየሰራ ይገኛል።
በተለይም ሁሉንም አገልግሎት በአንድ ማዕከል መስጠት የሚያስችል አደረጃጀት በመዘርጋት የተገልጋዩን እርካታ ለማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።
ሆስፒታሉ በዓመት በተመላላሽ ህከምና ለ330 ሺህ፣ በቀዶ ጥገና ለ10ሺህ እንዲሁም ለ10 ሺህ ነፍሰ ጡር እናቶችም የማዋለድ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ሆስፒታሉ የሚሰጠውን አገልግሎት በማሻሻል ተገልጋይ ተኮር ለማድረግ የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።
የሆስፒታሉ የተመላላሽ ህክምና ዳይሬክተር ዶክተር ሹሙዝ አህመዩ በበኩላቸው ለተገልጋዮች ትኩረት መስጠትና ለስራችን ኃላፊነት መውሰድ ይገባል ብለዋል።
በተለይ የምንሰጠው የህክምና አገልግሎት የቡድን ስራ በመሆኑ ከባለሙያ ጋር በመሆን በስራ ክፍላችን በጥልቅ የስራ ዲሲፕሊን ተግባራችንን እየከወንን ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በሆስፒታሉ የሚሰጠውን ህክምና ለማግኘት የሚመጡ ተገልጋዮች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የሆስፒታሉ ጠቅላላ ሀኪም ዶክተር ጽዮን ጌታሁን ናቸው።
በዚህም ተገልጋዮችን የሚያረካ አገልግሎት ለመስጠት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
የገባነውን ቃል ኪዳን በማክበር ለህብረተሰባችን ተገቢውን የህክምና አገልግሎት እየሰጠን እንገኛለን ብለዋል።
በሆስፒታሉ የነርሶች አስተባባሪ ሲስተር ዓለምጸሀይ ወጋሳ የሆስፒታሉን የህክምና አገልግሎት ፍለጋ በርካታ ህሙማን ከሩቅ አካባቢ ጭምር የሚመጡ በመሆኑ የሆስፒታሉ መደበኛ አገልግሎት ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።
በአዳማ ከተማ የድሬ ነገያ ወረዳ ነዋሪው ታካሚ አቶ በላይነህ ይዘንጋው በሆስፒታሉ የቆየ የህክምና ክተትል የሚያደርጉ መሆናቸውን ገልጸው ዛሬም ከድሮ የተለየ የገጠመኝ ችግር የለም ብለዋል።
የደም ግፊትና የስኳር ህክምና ክትትል ለማድረግ ስመጣ የሆስፒታሉ ሃኪሞች በመልካም አቀባበል ለሰጡኝ አገልግሎት አመሰግናቸዋለሁ ሲሉም ገልጸዋል።
ሌላው በሆስፒታሉ ሲገለገሉ ያገኘናቸው አቶ በቀለ መኮንን በበኩላቸው ሆስፒታሉ የአገልግሎት አሰጣጡን እያሻሻለ በመምጣቱ ዛሬም እንደ ወትሮው የተሟላ ህክምና አግኝቻለሁ ብለዋል።
በሆስፒታሉ ውስጥ ህክምና ለማግኘት የሚመጡ ሰዎች ቁጥር ከመብዛቱ በስተቀር አገልግሎቱ መልካም መሆኑንም ተናግረዋል ።