ቀጥታ፡

ፖሊስ ከዓለም አቀፍ ሁኔታዎች ጋር በተናበበ መልኩ ዝግጁነቱን ዘወትር አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 26/2017(ኢዜአ)፦ፖሊስ ከዓለም አቀፍ ሁኔታዎች ጋር  በተናበበ መልኩ ዘወትር መሠልጠን መታጠቅ እና መዘጋጀት አለበት ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።

116ኛው የኢትዮጵያ ፖሊስ ምሥረታ የማጠቃለያ መርሐ-ግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት ተከብሯል።
 
በመርሃ-ግብሩም ከጸጥታና ደህንነት ተቋማት ሪፎርም የፖሊስ አቅምና ተልዕኮ የመፈጸም ብቃትን ለማጠናከር የተከናወኑ ስራዎችን የሚያሳዩ ትርኢቶች ቀርበዋል።

ማንኛውንም አገራዊ ግዳጅ በብቃት መወጣት የሚችል የፖሊስ ሰራዊት ተገንብቷል - ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ ተቋም ግንባታ ውስጥ በጸጥታና ደህንነት ተቋማት ላይ የተሠራው የሪፎርም ስራ አመርቂ መሆኑን ተናግረዋል።



 
የሪፎርም ስራዎችም የፖሊስ ዝግጁነትንና አቅምን በእጅጉ ያሳደጉ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ እስከ አሁን የተከናወኑ አኩሪ ስራዎች ሳያዘናጓችሁ በቀጣይነት አቅም መገንባት እና ራሳችሁን ማሳደግ የወል ስራችሁ ሊሆን ይገባል በማለት አስገንዝበዋል።
 
ከዓለም ነባራዊ ሁኔታ ጋር በተናበበ መልኩ ዘወትር መሠልጠን መታጠቅ እና መዘጋጀት ያስፈልጋል ሲሉም ነው በአጽንኦት የተናገሩት።



 
ብሔራዊ ጥቅም፣ ሠላምና አንድነታችንን ማረጋገጥ የዘወትር ስራችን ሊሆን ይገባል ብለዋል።
 
የኢትዮጵያ ጠላቶች ፍላጎት እኛን መበተን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከዚህ አኳያ ብሔራዊ ፍላጎቶቻችንን ማወቅ፣ ሰላማችንን መጠበቅ፣ ተባብረን መትጋት እንዲሁም ከጎረቤቶቻችን ጋር በትብብር መስራት አለብን ብለዋል። 



 
በአርበኝነት መንፈስ የኢትዮጵያን አንድነትና ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ የዘወትር ስራችን ሊሆን ይገባል ሲሉም በአጽንዖት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም