ማንኛውንም አገራዊ ግዳጅ በብቃት መወጣት የሚችል የፖሊስ ሰራዊት ተገንብቷል - ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል - ኢዜአ አማርኛ
ማንኛውንም አገራዊ ግዳጅ በብቃት መወጣት የሚችል የፖሊስ ሰራዊት ተገንብቷል - ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 26/2017(ኢዜአ)፦ማንኛውንም አገራዊ ግዳጅ በብቃት መወጣት የሚችል የፖሊስ ሰራዊት መገንባት ተችሏል ሲሉ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።
116ኛው የፖሊስ ቀን የምስረታ የማጠቃለያ በዓል በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በድምቀት ተከብሯል።
በዚሁ ወቅት መልዕክት ያስተላለፉት ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ፌዴራል ፖሊስ ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት ፈርጀ ብዙ በሆነ መልኩ የፖሊስን አቅም ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
ፌዴራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል አቅሙን ለማሳደግ ማህበረሰብ አቀፍና መረጃ መር የወንጀል መከላከል መርህን ተግባራዊ በማድረግ እየሰራ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም የሚሰጡትን ፖሊሳዊ ግዳጆች በብቃት መወጣት የሚችልና በሰው ሃይል፣ በአቅምና በዘመናዊ ትጥቅ የተደራጀ የፈጥኖ ደራሽ፣ የልዩ ፀረ ሽብር ኮማንዶ ሃይል ማቋቋም መቻሉን አስታውቀዋል፡፡
ከለውጡ በኋላ በወንጀል ምርመራ ዘርፍ መረጃና ማስረጃ መር የምርመራ ሂደት እየተከናወነ እንደሚገኝ አስታውቀው፤ ምርመራው በሰለጠነ የሰው ሃይልና የፎረንሲክ ውጤትን መሰረት አድርጎ ሰብዓዊ መብትን ባከበረ መልኩ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በምርመራ ዘርፉ ከለውጡ በኋላ የዲኤንኤ ምርመራ መጀመሩን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ አገልግሎቱን ለጎረቤት አገር መስጠት መጀመሩን አንስተዋል፡፡
ለወንጀል ምርመራ አጋዥ የሆኑና ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎችንና ትጥቆችን ማቅረብ መቻሉንም አስታወቀዋል፡፡
በዚህም በምርመራ ሂደት ጠንካራ አቅም መፍጠር መቻሉን አስታውቀዋል፡፡
የፌዴራል ፖሊስን የቴክኖሎጂ አቅም ለማሳደግ በተከናወኑ ተግባራት የፖሊስ የድሮን ሃይል፣ ዲጂታል መገናኛ ሬዲዮና የኮማንድ ኮንትሮል ማዕከል መመስረት መቻሉን ነው የገለጹት፡፡
በ2010 ዓ.ም የተከናወነውን አገራዊ ለውጥ ተከትሎ ማንኛውንም አገራዊ ግዳጅ በብቃት መወጣት የሚችል የፖሊስ ሰራዊት መገንባት መቻሉን ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል አስታውቀዋል፡፡
ፌዴራል ፖሊስ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ አንሰቶ ከሌሎች የፀጥታ ተቋማት ጋር በመሆን የግድቡን ደህንነት እያስጠበቀ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ፌዴራል ፖሊስ በትምህርት ዘርፉም የላቁ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ኮሚሽር ጄኔራሉ ተናግረዋል፡፡