በኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ልማት ሽግግርን የሚያሳልጥ ምህዳር ተፈጥሯል - የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 22/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ልማት ሽግግርን የሚያሳልጥ ምህዳር መፈጠሩን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ(ዶ/ር) ገለጹ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ቁልፍ የልማት ዘርፎች ላይ የቴክኖሎጂ ልማትና ሽግግርን የማሳለጥ ዓላማን ያነገበ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ በማካሄድ ላይ ይገኛል።

ኢትዮጵያ የስታርት አፕ እና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ማዕከል እየሆነች ነው - ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)

በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ(ዶ/ር) እንዳሉት የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ልማትን ለማሳለጥ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።


 

በዚህም በኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ልማትና ግንባታ ሽግግርን የሚያሳልጥ ምህዳር መፈጠሩን አስታውቀዋል።

ባለፉት ሰባት ዓመታትም የክህሎትና የፈጠራ ልማትን ለማስፋት የሰው ሃብት ልማት፣ የፖሊሲ ዝግጅትና የአሰራር ሥርዓት በመፍጠር ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።

የዲጂታል ቴክኖሎጂ ልማትን ለማስፋትም ከተቋማት ጋር በመተባበር በመንግስትና የግል አጋርነት ጭምር ቀጣይነት ያላቸው ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።


 

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የዜጎችን የቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎት ለማበልጸግ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የ5 ሚሊዮን ኮደርስ ስልጠና ወሳኝ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ዜጎችም በ5 ሚሊዮን ኮደርስ ስልጠና ላይ በንቃት በመሳተፍ የቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎታቸውን ማበልጸግ የሚችሉበትን ዕድል መጠቀም እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመድረኩ በባዮ እና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ፣ በስፔስ ሳይንስና ጂኦ-ስፓሻል፣ በቴክኖሎጂ ልማትና ሽግግር ከሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ መስኮች ላይ የቴክኖሎጂ ልማትና ሽግግር ጉዳዮች ላይ የመነሻ ጽሁፎች ቀርበው ምክክር እንደሚደረግባቸው ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም