ኢትዮጵያ የስታርት አፕ እና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ማዕከል እየሆነች ነው - ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 21/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በመንግስት እና የግሉ ዘርፍ ትብብር የስታርት አፕ እና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ማዕከል እየሆነች ነው ሲሉ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ።

"ኢኖቬሽን አፍሪካ 2025" የአፍሪካ የትምህርት፣ አይ ሲ ቲ እና ክህሎት የሚኒስትሮች ስብሰባ "በ21ኛው ክፍለ ዘመን አፍሪካን ማስተማርና ማብቃት" በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ነው።


 

የትምህርት ሚኒስቴር፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከአፍሪካን ብሬይን ጋር በመተባበር ያዘጋጁት አህጉራዊ ጉባኤ ዛሬ ሁለተኛ ቀኑን ይዟል።

የኢኖቬሽን አፍሪካ 2025 ጉባኤ በሪፎርም፣ አቅም ግንባታ፣ የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሽግግር እንዲሁም ስትራቴጂካዊ ትብብር በመፍጠር የአፍሪካን መፃኢ ጊዜ ለመወሰን ያለመ ነው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) "ለኢኖቬሽን እና ትምህርት ሽግግር የዲጂታል ቴክኖሎጂን አቅም መገንባት" በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደውን የፓናል ውይይት አስጀምረዋል።

ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የኢኖቬሽን አፍሪካ 2025 ጉባኤ የበለጸገችና በቴክኖሎጂ ያደገች ሀገር ለመገንባት ወሳኝ ሁነት ነው።

በአፍሪካ የዲጂታል ክህሎት እና የቴክኖሎጂ ፈጠራ አቅምን በማሳለጥ ልማትና እድገትን ማቀላጠፍ ያስችላል ብለዋል።

ወጣቶችን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ማስታጠቅ ምርጫ ሳይሆን ግዴታ መሆኑን ተናግረዋል።

የአፍሪካ ወጣቶች ዓለም አቀፍ ተሳትፎ የሚወሰነው በሚኖራቸው የቴክኖሎጂ አቅም መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ሁሉን አቀፍ ፖሊሲ በመተግበር የዲጂታል ውጤታማነት እና ምርታማነትን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።

በአፍሪካ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት የጋራ ጥረትን እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ በትብብር በመስራት ሁሉንም የፈጠራ አቅሞች በመጠቀም ለወጣቶች ምቹ የዲጂታል ስነ ምህዳር ለመፍጠር ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።

አፍሪካን በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ወጣቶችን በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግ እና ሒሳብ ትምህርቶች ማብቃት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግ እና ሒሳብ ትምህርቶች ለእድገት ወሳኝ መሆናቸውን በመገንዘብ ያልተቋረጠ ጥረት እያደረገች መሆኑንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በመንግስትና የግሉ ዘርፍ የጋራ ጥረት የስታርት አፕ እና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ማዕከል እየሆነች ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ በኢንዱስትሪዎች እና ትምህርት ተቋማት መካከል ትብብርን በማዳበር ለስራ ፈጣሪዎች ምቹ ከባቢ እንዲኖር እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

ለችግሮቻችን መፍትሔ ለማበጀት ሁሉንም የኢኖቬሽን አቅም መጠቀም እንደሚገባ ገልጸው፣ ኢትዮጵያ ስታርት አፕን ለማሳደግ የፖሊሲ ዝግጅት እያደረገች መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም