ሠላምን በማፅናት ዕድገትና ብልፅግናን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው - ዶክተር ጌድዮን ጢሞቲዎስ - ኢዜአ አማርኛ
ሠላምን በማፅናት ዕድገትና ብልፅግናን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው - ዶክተር ጌድዮን ጢሞቲዎስ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 18/2017(ኢዜአ)፦ ሠላምን በማፅናት ዕድገትና ብልፅግናን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) ገለጹ።
ሚኒስትሩ በወቅታዊ ዓለም አቀፋዊ ፣ አህጉራዊ ፣ ቀጣናዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለከፍተኛ የመከላከያ ሠራዊቱ አመራሮች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
"የመሀሉ ዘመን" በሚል ርዕስ ትንታኔ ያቀረቡት ሚኒስትሩ በሀገራችን የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በተመዘገቡ ሁለንተናዊ ድሎች ሳንዘናጋ ለበለጠ ድል መትጋት ይገባል ብለዋል።
ሀገሩን የሚወድ የተሰለፈበትን ዓላማ የተረዳና ፕሮፌሽናል የሆነ ብሄራዊ የመከላከያ ሠራዊት ተገንብቷል -ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ
ታላቁን የህዳሴ ግድብ በከፍተኛ ፈተናዎች ውስጥ ገንብተን በማጠናቀቅ ሀገርና ህዝብን አንገት ከማስደፋት ለማዳን የተቻለበትና የጠላቶቻችንን የተቀናጀ ሴራ ያከሸፍንበት አንዱ ማሳያ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ሀገራዊ ኢኮኖሚያችን ፈተናዎችን በመቋቋም በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉንም ዓለም አቀፍና ሀገራዊ መረጃዎችን በማጣቀስ አብራርተዋል።
ባለፉት ዓመታት ብዙ ሀገራት በዲፕሎማሲው መስክ በትብብር ለመስራት ፍቃደኝነታቸውን ማሳየታቸውንና ይህንን በጎ ዕድል በመጠቀም ብሄራዊ ጥቅማችን ለማሳካት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
የባህር በር ተጠቃሚ ለመሆን የቀረበው ጥያቄም በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ፍትሃዊ አጀንዳ ሆኖ መያዙን ሚኒስትሩ አስረድትዋል።
ተለዋዋጭና ኢ-ተገማች በሆነው ዓለም አቀፋዊና ቀጣናዊ እንቅስቃሴ ያለንን ሁለንተናዊ ዝግጁነት በማረጋገጥና የተለያዩ ስልቶችን በመንደፍ ተጋላጭነታችንን ለመቀነስ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።
በተከተልነው የሰላም ስምምነት የፀና ወታደራዊ ድል ተመዝግቧል ያሉት ሚኒስትሩ የሚያጋጥሙ ውስጣዊ ችግሮችን በሰላምና በይቅርታ በመፍታት በሀገርና በህዝብ ላይ የሚደርሰውን ጥፋት ለመቀነስ መንግስት እየወሰደው ያለው በሳል እርምጃ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቡንም ተናግረዋል።
የሰላምን ጥሪ ባለመቀበል በሀይል ጥቅማችንን እናስከብራለን በማለት የሞከሩ የጥፋት ሀይሎች በተከተሉት የተሳሳተ ትርክትና ፖለቲካ ህዝቡ አንቅሮ እንደተፋቸውም ገልፀዋል።
የመከላከያ ሠራዊቱ ከሌሎች የፀጥታ ሀይሎች ጋር በመሆን በፅንፈኞች ላይ በወሰደው እርምጃም ለሀገርና ለህዝብ ስጋት ከመሆን ወርደው የራሳቸውን ህልውና ለማቆየት እየተቸገሩ መምጣታቸውን አንስተዋል ።
ሠላምን ለማፅናትና ብልፅግናን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ ገልፀው ጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችንም ባስመዘገባቸው ድሎች ሳይኩራራ ለበለጠ ተልዕኮ ራሱን ማዘጋጀት ይገባዋል ብለዋል።
በውይይቱ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላን ጨምሮ ከፍተኛ የሠራዊቱ አመራሮች ተገኝተዋል።