ስቶፕ ኦቨር ቱሪዝም ለአገር ኢኮኖሚና ለቱሪዝም ዘርፉ ተዋንያንን ተጠቃሚነት ያሳድጋል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2017(ኢዜአ)፦ስቶፕ ኦቨር ቱሪዝም ለአገር ኢኮኖሚና ለቱሪዝም ዘርፉ ተዋንያን ተጠቃሚነት ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ገለጹ።

በኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትኩረት ከተሰጣቸው አምስት የኢኮኖሚ ምሰሶዎች መካከል ቱሪዝም አንዱ መሆኑ ይታወቃል።

"ስቶፕ ኦቨር ቱሪዝም"ደግሞ ተጓዦች ከመነሻ አገራቸው በሚነሱበት ጊዜ በመሸጋገሪያነት በኢትዮጵያ ሲያልፉ ጥቂት ቀናት በሀገሪቷ ቆይታ አድርገው ወደ መዳረሻ አገር እንዲሄዱ የሚያስችል የቱሪዝም ዓይነት ነው።

በዚህም አዲስ አበባን ከስቶፕ ኦቨር ቱሪዝም ተጠቃሚ የሚያደርጉ የቱሪዝም መሰረተ ልማቶች እየተገነቡ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ2024 የአፍሪካ የላቀ የቱሪዝም ትራንስፖርት ሽልማት ተበረከተለት

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት እና የቱሪዝም ሚኒስቴር በቱሪዝም ዘርፍ በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ የካቲት 25 ቀን 2017 ዓ.ም መፈራረማቸውም ይታወሳል።

ስምምነቱ በአዲስ አበባ የቆይታ ጊዜ ለሚኖራቸው መንገደኞች በተዘጋጀ ስቶፕ ኦቨር ፓኬጅ ላይ በጋራ መሥራት የሚያስችል ነው፡፡

የታላቋ ኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅቶች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት እንቁ ሙሉጌታ እንዳሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በርካታ አለም አቀፍ መዳረሻ ስላለው ተጓዦችን የስቶፕ ኦቨር ቱሪዝም ተጠቃሚ ለማድረግ ሰፊ እድል ተፈጥሯል።


 

በአዲስ አበባ የተከናወኑ የኮርደርና የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች ልማት እንዲሁም የቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ከተማዋን ለስቶፕ ኦቨር ቱሪዝም ተመራጭ ያደርጋታል ብለዋል።

የጳጉሜ ፌስቲቫል፣ ቱርና ትራቭል ባለቤት ሀይለአብ መረሳ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ብዝሃ ባህልና ታሪክ ያላት የበርካታ ቱሪዝም ሀብት ባለቤት በመሆኗ የስቶፕ ኦቨር ቱሪዝም በዘርፉ ለተሰማሩ ትልቅ እድልና ተስፋ መፍጠሩን ጠቁመዋል።

ስቶፕኦቨር ቱሪዝም ተጓዞች በቆይታቸው በሚያዩት ነገር ተማርከው በቀጣይ መጥተው በሰፊው እንዲጎበኙ እድል የሚፈጥርና ለአገር ገፅታ ግንባታ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ስለሆነም የዘርፉ ተዋንያን ጎብኚዎች የማይረሳ ጊዜ እንዲያሳልፉ ለማድረግ በቂ ዝግጅት ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የበርካታ መንገደኞች መዳረሻና መተላለፊያ በመሆኑ ለስቶፕ ኦሸር ቱሪዝም የጎላ ሚና እንዳለው የገለፁት ደግሞ የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሁንዴ ከበደ ናቸው።

ዘርፉ በከተማዋ ቆይታ ለሚኖራቸው መንገደኞች አዲስ አበባን እንዲጎበኙ እድል በመፍጠር የመዲናዋን ብሎም የሀገሪቱን ቱሪዝም ፍሰትና ገቢ ያሳድጋል ብለዋል፡፡

አዳዲስና ነባር የቱሪዝም መዳረሻዎች ልማትና የመሰረተ ልማት ዝርጋታ እየተከናወነ መሆኑን ተከትሎ በመዲናዋ ምቹ የቱሪዝም ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ይገኛሉ ብለዋል።

የኮሪደር ልማት ለትራንስፖርትና ለከተማዋ ገፅታ ካለው ሚና ባለፈ ለስቶፕ ኦቨር ቱሪዝም ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም