ቀጥታ፡

በህብረቱ ጉባኤ የሚተላለፉ ውሳኔዎች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠበቁ እንዲሆኑ ዝግጅት ተደርጓል - አምባሳደር ነብዩ ተድላ

 

አዲስ አበባ፤ ጥር 27/2017(ኢዜአ)፦በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የሚተላለፉ ውሳኔዎች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠበቁ እንዲሆኑ ዝግጅት መደረጉን በህብረቱ የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ነብዩ ተድላ ገለፁ።

38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ የካቲት 8 እና 9 ቀን 2017 ዓ.ም እንዲሁም 46ኛው የሕብረቱ የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ደግሞ ቀደም ብሎ የካቲት 5 እና 6 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

በአፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ነብዩ ተድላ የህብረቱን ጉባኤ ቅድመ ዝግጅት በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ለአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ተሳታፊዎች የቱሪዝም ሀብቶችን ለማስተዋወቅና ለማስጎብኘት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ ነው

ኢትዮጵያ የጉባኤው አስተናጋጅ እንደመሆኗ ለስኬቱ ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጀምሮ በቂ ዝግጅት ማድረጓን ጠቅሰዋል።

በተለይም የአዲስ አበባን የኮንፍረንስ ቱሪዝም ማዕከልነት ለማጠናከርና ሀገራዊ ገፅታችንን ለማስተዋወቅ ጉባኤውን እንደ መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም መታቀዱን  ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ለፓን አፍሪካኒዝም እና አህጉራዊ እድገት ያበረከተችውን አስተዋጽኦ ለማሳወቅ ተዘጋጅተናል - ካዴቶች

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የህብረቱ አባል ሀገር በመሆኗ በጉባኤው የሚቀርቡ አጀንዳዎች ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስጠብቁ እንዲሆኑ ትሰራለች ብለዋል።

በጉባኤው የሚተላለፉ ውሳኔዎች  ከሀገራዊ ፍላጎቶቻችን ጋር የተጣጣሙ እንዲሆኑ ንቁ ተሳትፎ ይደረጋል ያሉት አምባሳደር ነብዩ ለዚህም በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

በዘንድሮው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር እና የኮሚሽነሮች ምርጫን ጨምሮ ትላልቅ አጀንዳዎች ይጠበቃሉ።

 

የጉባኤው መሪ መልዕክት አፍሪካውያን በውጭ ኃይሎች ለተፈጸመባቸው በደል ካሳ እና ፍትሕ እንዲያገኙ በህብረት መቆም እንደሚገባ ትኩረት ሰጥቷል።

 

ህብረቱ በ37ኛ ጉባኤው ባዘጋጀው የአጀንዳ ፍሬ ሀሳብ ላይ ከዚህ ቀደም የተፈጸሙ ስህተቶችን ለመሻገር አፍሪካውያን በቅኝ ግዛት፣ በአፓርታይድ፣ በመዋቅራዊ መድሎ የተፈጸሙባቸው ግፎች ስትራቴጂካዊ በሆነ መንገድ በዝርዝር መለየት እንዳለባቸው ተመላክቷል።

 

አፍሪካውያን በተፈጸመባቸው በደል የደረሰባቸውን ግፍ በይፋ መግለፅ እና ሰንዶ መያዝ የፍትሕና የካሳ ሂደቱ የመጀመሪያ አካል ነው ብሏል የህብረቱ አጀንዳ ፍሬ ሀሳብ።

 

በካሳ ረገድም የፋይናንስ እና የልማት ኢንቨስትመንት ድጋፍ፣ ዓለም አቀፋዊ ተጠያቂነት፣ የባህል ልማት፣ የመሬት ባለቤትነት መብት፣ ማህበረሰባዊ የግንዛቤ ስራዎችና ሌሎችም ሊኖሩ እንደሚገባ አስቀምጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም