ኢትዮጵያ ለፓን አፍሪካኒዝም እና አህጉራዊ እድገት ያበረከተችውን አስተዋጽኦ ለማሳወቅ ተዘጋጅተናል - ካዴቶች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለፓን አፍሪካኒዝም እና አህጉራዊ እድገት ያበረከተችውን አስተዋጽኦ ለማሳወቅ ተዘጋጅተናል - ካዴቶች
አዲስ አበባ፤ጥር 2/ 2017(ኢዜአ)፦በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ኢትዮጵያ ለፓን አፍሪካኒዝም እና አህጉራዊ እድገት ያበረከተችውን አስተዋጽኦ ለማሳወቅ መዘጋጀታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጡ ካዴቶች ገለጹ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ የሀገራቸውን በጎ ገጽታ ለመገንባት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት የሰለጠኑ ካዴቶች የተለያዩ የልማት ስራዎችን እንዲጎበኙ አድርጓል፡፡
በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚሰጡ ካዴቶች ለኢዜአ እንዳሉት፤ የአንድነትና ወዳጅነት ፓርኮች፣ ብሔራዊ ቤተ መንግስትና ሌሎች ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያ ትክክለኛ መልኮች ናቸው፡፡
ወጣት ግሎሪ ደበበ፣ አማኑኤል አምሳሉ፣ ሌሊሴ ቡዘና እና አደም መሀመድ ኢትዮጵያ እምቅ ሀብት ያላት ታላቅ ሀገር መሆኗን የሚገልጹ ፕሮጀክቶች መመልከታቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ በዲጅታል ቴክኖሎጂ፣ በታሪካዊ ቅርሶችና በተፈጥሮ ሀብት የበለጸገች መሆኗን ተረድተናል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ኢትዮጵያን የሚመጥን ሥራ እየሰሩ መሆኑን የገለጹት ካዴቶቹ፤ በአዲስ አበባና በክልሎች የተገነቡ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን በጥራትና በፍጥነት አጠናቆ ለህዝብ ክፍት መደረጋቸው ማሳያ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ አቅም መጠቀም በሚያስችል ሂደት ላይ መሆኗን የገለጹት ካዴቶቹ፤ ከለውጡ መንግሥት በኋላ አንገታችንን ቀና አድርገን መናገር የምንችልባቸው ፕሮጀክቶች እየተገነቡ መሆኑን መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡
በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤም የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚያሳዩ ፕሮጀክቶች እየተሰሩ መሆኑን በኩራት እንናገራለን ብለዋል።
ለአፍሪካ ሀገሮች ነፃነት፣ ለፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ መጎልበት እንዲሁም ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመስረት ያበረከተችውን ጉልህ አስተዋጽኦ ማስረዳት የሚያስችል አቅም መፍጠራቸውንም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የቀደመ ታሪኳ፣ የዛሬ ማንነቷ የነገ ትልሟ የተሰነደባቸው ፕሮጀክቶችን የማስተዋወቅ ሀላፊነታችንን በሚገባ እንወጣለንም ብለዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በበኩላቸው፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት እየተሰሩ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን ገጽታ የሚቀይሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የብሔራዊ ቤተ መንግሥት እድሳት፣ የአንድነትና ወዳጅነት ፓርኮች እንዲሁም ሌሎች ፕሮጀክቶች ትውልድ ተሻጋሪ ሥራዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ለአብነት የአንድነት ፓርክ ዛሬ ውብና የበርካታ ቱሪስቶች መዳረሻ ከመሆኑ በፊት ለእይታ የማይመች ቦታ እንደነበር አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያ የዲጅታል ዲፕሎማሲ ማሳያ የሆነው የሳይንስ ሙዚየም ለዓመታት ታጥሮ የቆየ እንደነበር ጠቅሰው፤ ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያስጀመሯቸው ፕሮጀክቶች የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት የሰለጠኑ ካዴቶች ጉብኝትም ለአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ተሳታፊዎች ስለኢትዮጵያ ታላቅነት ማስረዳት የሚችሉበት ማስረጃ እንዲኖራቸው ለማሳየት መሆኑን ተናግረዋል፡፡