የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እድገት ማስመዝገብ በሚያስችል ሂደት ላይ ነው - የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ - ኢዜአ አማርኛ
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እድገት ማስመዝገብ በሚያስችል ሂደት ላይ ነው - የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 4/2017(ኢዜአ)፦ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያው የውጭ ምንዛሬ ግኝትን በማሳደግ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እድገት ማስመዝገብ በሚያስችል ሂደት ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ገለጹ።
መንግሥት የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ተግባራዊ ሲያደርግ ዘመናዊ የገንዘብ ፖሊሲ ለመተግበር፣ ጤናማ የፋይናንስ ሥርዓት ለመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲመራ ለማስቻል ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ክምችት 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል-የባንኩ ገዥ ማሞ ምህረቱ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ እንዳሉት፣ በኢትዮጵያ የቆየና ሥር የሰደደ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንደነበር አስታውሰዋል።
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራውን ተከትሎ ባንኩ የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ስርዓት ማሻሻያ አድርጓል ብለዋል።
በዚህም የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰንና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወጥተው የነበሩ መመሪያዎች ተሰባስበው አንድ ወጥ መመሪያ እንዲወጣ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
ላኪዎች ከነገ ጀምሮ ካመነጩት የውጭ ምንዛሬ 50 በመቶውን በመሸጥ ቀሪውን ላልተወሰነ ጊዜ በአካውንታቸው ማስቀመጥ ይችላሉ-ብሔራዊ ባንክ
በፍራንኮ ቫሉታ ይገቡ የነበሩ መሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች በመደበኛ የንግድ ባንኮች የመተማመኛ ሰነድ /LC/ እንዲገቡ ተወስኗል - የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ
ከተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያው በኋላ ዘመናዊ የገንዘብ ፖሊሲ በማውጣት የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግ መቻሉን ጠቁመዋል።
ከሪፎርሙ በኃላ የባንኮች የውጭ ምንዛሬ ግኝት ከኤክስፖርት ብቻ በወር በአማካኝ 500 ሚሊዮን ዶላር መድረሱን ገልጸዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ከሪፎርሙ በፊት ከነበረበት 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ዛሬ ላይ ወደ 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር አድጓል ብለዋል።
ባንኮች የሚገዙትና የሚያቀርቡት የውጭ ምንዛሬ በየቀኑ እየጨመረ መሆኑን የገለጹት የባንኩ ገዥ፤ ይህም ሪፎርሙ የተሳካ ሂደት ላይ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።
የግል ባንኮች የውጭ ምንዛሬ ሀብት መጨመሩን ጠቅሰው፤ ከሪፎርሙ በፊት ከነበረባቸው 518 ሚሊዮን ዶላር አሁን ላይ ከእዳ ነፃ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ባንኮች በሁለት ሳምንት ውስጥ በጀመሩት የእርስ በርስ የውጭ ምንዛሬ ግብይት ከ100 ሚሊየን ዶላር በላይ ግብይት መፈጸማቸውን ገልጸዋል፡፡
በአጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያዎች የተረጋጋ የውጭ ምንዛሬ እና ዘመናዊ የገንዘብ ፖሊሲ እንዲኖር ማስቻሉን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ላኪዎች ያመነጩትን የውጭ ምንዛሬ 50 በመቶ ወዲያውኑ በመሸጥ ቀሪውን 50 በመቶ ላልተወሰነ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለ አካውንታቸው ማስቀመጥ የሚችሉበት አሰራር ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል፡፡
ላኪዎች ካመነጩት የውጭ ምንዛሬ 50 በመቶውን ለባንኮች ወዲያውኑ በመሸጥ ቀሪውንም በአንድ ወር ውስጥ መሸጥ ይገደዱ እንደነበርም አንስተዋል።
በወቅቱ አሰራሩ በጊዜያዊነት ተግባራዊ ሲደረግ የተረጋጋ የውጭ ምንዛሬ ፍሰት እንዲኖር ከመፈለግ እንደነበር አቶ ማሞ አስታወሰዋል።