ላኪዎች ከነገ ጀምሮ ካመነጩት የውጭ ምንዛሬ 50 በመቶውን በመሸጥ ቀሪውን ላልተወሰነ ጊዜ በአካውንታቸው ማስቀመጥ ይችላሉ-ብሔራዊ ባንክ

አዲስ አበባ፤ህዳር 4/2017(ኢዜአ)፦ላኪዎች ያመነጩትን የውጭ ምንዛሬ 50 በመቶ ወዲያውኑ በመሸጥ ቀሪውን 50 በመቶ ላልተወሰነ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለ አካውንታቸው ማስቀመጥ የሚችሉበት አሰራር ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገለጸ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ እንዳሉት፣ ላኪዎች ካመነጩት የውጭ ምንዛሬ 50 በመቶውን ለባንኮች ወዲያውኑ በመሸጥ ቀሪውንም በአንድ ወር ውስጥ መሸጥ ይገደዱ ነበር።

በወቅቱ አሰራሩ በጊዜያዊነት ተግባራዊ ሲደረግ የተረጋጋ የውጭ ምንዛሬ ፍሰት እንዲኖር ከመፈለግ እንደነበር አቶ ማሞ አስታውሰዋል።

ከነገ ጀምሮ ግን ላኪዎች ያመነጩትን የውጭ ምንዛሬ 50 በመቶ ወዲያውኑ በመሸጥ ቀሪውን 50 በመቶ ላልተወሰነ ጊዜ በአካውንታቸው ማስቀመጥ ይችላሉ ብለዋል።

ይህም ማለት ያመነጩትን የውጭ ምንዛሬ በአንድ ወር ውስጥ እንዲሸጡ አይገደዱም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም