ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት አምስት አመታት በሁሉም ዘርፎች አበረታች ውጤቶችን አስመዝግቧል- አቶ ጌቱ ወዬሳ - ኢዜአ አማርኛ
ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት አምስት አመታት በሁሉም ዘርፎች አበረታች ውጤቶችን አስመዝግቧል- አቶ ጌቱ ወዬሳ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 4/2017(ኢዜአ):- ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት አምስት አመታት በሁሉም ዘርፎች አበረታች ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻሉን የሐረሪ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ጌቱ ወዬሳ ገለጹ።
የሀረሪ ክልል ብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ደም ልገሳ አካሄዱ
የሐረሪ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት "የሀሳብ ልዕልና ለሁለተናዊ ብልጽግና" በሚል መሪ ሀሳብ የፓርቲውን 5ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በኪነ-ጥበብና የስነ-ጽሁፍ መርሃ ግብር አክብሯል።
በመርሃ-ግብሩ ላይ የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ጌቱ ወዬሳ፣ የፓርቲው ምክትል ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱልሀኪም ኡመርን ጨምሮ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች እና አባላት ተገኝተዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት አምስት ዓመታት በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች አበረታች ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻሉን ገልፀዋል።
በተለይም የሕዝቦችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ጀምሮ በማጠናቀቅ ኢትዮጵያን የብልጽግና ተምሳሌት እንድትሆን እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በሀገሪቱ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተሰጠው ትኩረት ከውጭ ይገባ የነበረውን ስንዴ በሀገር ውስጥ ከመተካት ባለፈ ወደ ውጭ በመላክ አበረታች ውጤት መመዝገቡን አመልክተዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ገቢራዊ እየሆነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ሀገሪቱን ለነዋሪዎች የተመቸች በማድረግ ቀድሞ የነበረውን ምልከታ ቀይሯል ነው ያሉት ኃላፊው።
በተለይ በሐረሪ ክልል በአረንጓዴ ልማት ታጅቦ እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር እና የጀጎል መልሶ ልማት ከተማውን ለኑሮ መቹ ከማድረግ ባለፈ የቱሪስቶች ፍሰት እና ቆይታ እንዲጨምር ማስቻሉን ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል ፓርቲው ወንድማማችነትና አብሮነትን በማጠናከር እውነተኛ ሕብረ-ብሄራዊነትን በተግባር በማረጋገጥ ቋንቋ እና የጋራ ማንነትን ለኢትዮጵያ ብልጽግና ምሰሶ እንዲሆኑ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
አቶ ጌቱ አክለውም ፓርቲው ለሰው ተኮር ስራዎች የሰጠው ትኩረት የዜጎችን ችግር በማቃለል ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ መቻሉን ጠቁመዋል።
የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን ሪፎርም በማድረግ እና በማዘመን ፍትሐዊ፤ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት የዜጎችን እርካታ ማሳደግ መቻሉንም እንዲሁ።
በቀጣይም በሁሉም ዘርፎች የተመዘገቡ አበረታች ስኬቶችን በውጤት አጅቦ ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሰራ መግለጻቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።