ቀጥታ፡

በሲዳማ ክልል19ኛው የብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ባህላዊ እሴቶችን በሚያጠናክር አግባብ ይከበራል

ሀዋሳ፤  ህዳር 4 / 2017 (ኢዜአ)፡- በሲዳማ ክልል 19ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ባህላዊ  እሴቶችንና መልካም ግንኙነትን  በሚያጠናክር አግባብ  ከነገ ጀምሮ በድምቀት እንደሚከበር የክልሉ  ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባዔ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ አስታወቁ።

አፈ-ጉባዔዋ በዓሉን አስመልክተው ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳመላከቱት፤ በዓሉን በድምቀት ለማክበር  የክልሉ ምክር ቤት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተወጣጡ ዐቢይ እና ንዑሳን ኮሚቴዎችን አዋቅሮና እቅድ አውጥቶ ሲዘጋጅ  ቆይቷል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው

ህብረ ብሄራዊነትና አገራዊ አንድነትን በሚያጠናክር አግባብ በክልሉ 19ኛው የብሔሮች፣  ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ነገ መከበር እንደሚጀምር አስታውቀዋል።

የክልሉ ህዝብ በዓሉንና እሴቱን ጠብቆ ያቆየ መሆኑንና ይህንን ለማጽናት የበዓሉ መከበር ገንቢ ሚና እንዳለው አውስተዋል።

በብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች  መካከል መልካም ግንኙነትን ለማጠናከር ብሎም ትስስራቸውን ለማጎልበት እንደሚያስችል አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን መከበር የፌዴራል ስርዓቱን በፅኑ መሰረት ላይ ለመገንባት ሚናው የጎላ ነው

በዓሉን በማስመልከትም በህገ መንግስት አስተምህሮት ዙሪያ የህዝቡን ግንዛቤ የማጎልበት ስራ ለማጠናከር  በትምህርት ቤቶችና በህዝባዊ መድረኮች ውይይት እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።

ለዚህም በአካባቢው የሚገኙ የትምህርት ተቋማትን በኮሚቴው ውስጥ በማካተት ለህብረተሰቡ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እንደሚከናወን ገልጸዋል።

ከነገ ጀምሮ እስከ ህዳር 20/ 2017 ዓ.ም ድረስ በዓሉ በድምቀት ይከበራል ያሉት አፈ- ጉባዔዋ፤ በዚህም ደም በመለገስ እና የደረሰ የአርሶ አደሩን ሰብልበመሰብሰብና የጽዳት ዘመቻ በማካሄድ ንቁ ተሳትፎ የሚደረግበት ሁኔታ መመቻቸቱንም አመላክተዋል።

እንዲሁም ክልላዊ ሲምፖዚየሞች፣ አውደ ርዕይ፣ ፣ የፓናል ውይይቶች እና የባህል ልውውጦች በክብረ በዓሉ ላይ እንደሚካተቱ ገልጸዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ  በዓሉን ለማክበር ክልሉን አቋርጠው ወደ አርባ ምንጭ  ከተማ ለሚሄዱ እንግዶች  የክልሉ መንግስትና ህዝብ ደማቅ አቀባበል በማድረግ ለመሸኘት መዘጋጀቱንም አስታውቀዋል።

በተለይ የከተማዋ ነዋሪ፣በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች እንግዶችን በሀገር ወግና ባህል መሰረት ተቀብለው እንዲያስተናግዱም ወይዘሮ ፋንታዬ ጥሪ አቅርበዋል።

19ኛው የብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በአርባምንጭ ከተማ እንደሚከበር ቀደም ብሎ ተገልጿል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም