ቀጥታ፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው

አሶሳ፤ ህዳር 4/2017 (ኢዜአ)፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 19ኛውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ አስካል አልቦሮ ተናገሩ።

ምክር ቤቱ ከከተማ እና ከወረዳ አፈጉባኤዎች እንዲሁም የኮሙኒኬሽን አመራር አባላት ጋር የበዓሉን አከባበር በተመለከተ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ አስካል አልቦሮ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን መከበሩ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

በዓሉ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውን እና እሴቶቻቸውን የሚያስተዋውቁበት እና በነፃነት እንዲያራምዱ ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።


 

19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በዓል በክልል ደረጃ በአሶሳ ከተማ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አፈጉባኤዋ ተናግረዋል።

ክልሉ የበርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች የሚኖሩበት መሆኑን ጠቅሰው በዓሉ ብዝሃነትን ያከበረ ህብረብሔራዊ አንድነት እንዲዳብር ያግዛል ብለዋል።

በዓሉን በክልሉ በሁሉም አካቢዎች በደማቅ ሁኔታ ለማክበር በየደረጃው ካሉ ምክር ቤቶች እና የኮሙኒኬሽን ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተራ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በአሶሳ ዩኒቨርስቲ የፌዴራሊዝም መምህር አዳሙ ጅባት በበኩላቸው በዓሉ ዜጎች በህገ መንግስቱ ላይ ያላቸው እምነት እንዲጨምር እና በልዩነት ውስጥ አንድነት መኖሩን የሚያሳይ እንደሆነ አብራርተዋል።

19ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ሀገራዊ መግባባት ለኅብረብሔራዊ አንድነት በሚል መሪ ሃሳብ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አስተናጋጅነት በአርባምንጭ ከተማ ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም