ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመምህራን የሰጡት እውቅና ይበልጥ እንድንሰራ የሚያበረታታ ነው - የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመምህራን የሰጡት እውቅና ይበልጥ እንድንሰራ የሚያበረታታ ነው - የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 28/2016(ኢዜአ)፦ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መምህራን በትውልድ ግንባታ ለሚያበረክቱት አስተዋጽኦ የሰጡት እውቅና ይበልጥ እንድንሰራ የሚያበረታታ ነው ሲል የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አስታወቀ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው 36ኛ መደበኛ ስብሰባ በመገኘት ከአባላቱ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም፤ኢትዮጵያን ከሚያስቀጥሉ ምሰሶዎች መካከል አርሶ አደር፣ ወታደርና መምህር ወሳኝ ናቸው ብለዋል።
መንግሥት የኢትዮጵያ ወታደርና መምህራን ህይወትን የሚያሻሽሉ እርምጃዎችን ይወስዳል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አርሶ አደሩ እያመረተ በኑሮ ሁኔታ ላይ ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ጠቅሰው፤ መምህራንና ወታደር ደግሞ ለኢትዮጵያና ለትውልዱ ቀጣይነት ዋጋ የሚከፍሉ፣ እውቀታቸውንና ሕይወታቸውን ሳይሰስቱ የሚሰጡ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
በመሆኑም ክብር ይገባቸዋል ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ መምህርን ማሕበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ዩሐንስ በንቲ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመምህራን የሰጡት እውቅና ትውልድን የመቅረጽ ተግባራችንን አጠናክረን እንድንቀጥል ተነሳሽነት የፈጠረ ነው ሲሉ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀገሪቱ የመጨረሻው ህግ አውጪ አካል በሆነው ምክር ቤት ፊት የሰጡት እውቅና ህብረተሰቡ ለመምህራን ዘወትር ክብር መስጠት እንዳለበት የሚያስገነዝብ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ መምህራን ሁሌም ሀገርና ትውልድን አስቀድመው እንደሚሰሩ ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ለዘመናት ባለፈችባቸው የትውልድ ግንባታ ሂደት ውስጥ መምህራን ትልቁን ሚና እንደሚይዙ ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይም ይህንን ሚናቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው የገለጹት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ መምህራን ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች አቅም በፈቀደ አግባብ መንግስት ለመመለስ እንደሚሰራ መግለጻቸውንም አድንቀዋል፡፡