መንግሥት የኢትዮጵያ ወታደርና መምህራን ህይወትን የሚያሻሽሉ እርምጃዎችን ይወስዳል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
መንግሥት የኢትዮጵያ ወታደርና መምህራን ህይወትን የሚያሻሽሉ እርምጃዎችን ይወስዳል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27/2016(ኢዜአ)፦መንግስት የኢትዮጵያ ወታደርንና መምህራን ህይወትን የሚያሻሽሉ እርምጃዎችን እንደሚወስድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 36ኛ መደበኛ ስብሰባ እየተካሄደ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከምክር ቤቱ አባላት በአገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮችና የመንግሥት የሥራ አፈጻጸምን በተመለከተ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ እየሰጡ ነው።
በማብራሪያቸውም ኢትዮጵያን ከሚያስቀጥሉ ምሰሶዎች መካከል አርሶ አደር፣ ወታደርና መምህራን ወሳኝ ናቸው ብለዋል።
አርሶ አደሩ በሚደረግለት የማዳበሪያና ሌሎች ድጋፎች እያመረተ በኑሮ ሁኔታ ላይ ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ወታደርና መምህራን ደግሞ ለኢትዮጵያና ለትውልዷ ቀጣይነት ዋጋ የሚከፍሉ፣ እውቀታቸውንና ሕይወታቸውን ሳይሰስቱ የሚሰጡ ሆነው ሳለ በቂ ነገር ያላገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ነገ በልጆቻችን የተሻለ ነገር እንገኛለን ከሚል ተስፋ ውጭ በቂ ክፍያ እንዳላገኙ ጠቅሰው፥ የኢትዮጵያ መምህራንና ወታደሮች ታላቅ ክብር ይገባቸዋል ብለዋል።
መንግሥት ሕይወታቸውን ለማሻሻል ተጨማሪ እርምጃዎች እንደሚወስድ አረጋግጠዋል።