ቀጥታ፡

ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የድርሻችንን እንወጣለን - የሀገር ሽማግሌዎች

ሚዛን/ዲላ/ሶዶ/ ጂንካ፤ መጋቢት 18/2016(ኢዜአ):-ሀገራዊ የምክክር መድረክ የነበሩ ቂምና ቁርሾዎችን በዘላቂነት ፈትቶ የህዝቦችን አንድነት ስለሚያጠናክር ለስኬታማነቱ የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ የተለያየ አካባቢ የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ።

እንደ ሀገር የማያግባቡና ዘመናትን ያስቆጠሩ መሰረታዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትና ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ግብ ይዞ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ወደ ተግባር ገብቶ እየተንቀሳቀሰ ነው።

ኮሚሽኑ በምሥራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች በወረዳ ደረጃ አጀንዳ በማሰባሰብ ሂደት የሚሳተፉ ተወካዮች ልየታ እያካሄደ ነው

ኮሚሽኑ እንደ ሀገር መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ በምክክር ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር ተልዕኮ አንግቦ እየሰራ ይገኛል።

ይህ የኮሚሽኑ ተልዕኮ እንዲሳካ የበኩላቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የቤንች ሸኮ፣ የጌዴኦ፣ የወላይታ እና የአሪ ዞን የሀገር ሽማግሌዎች ገልጸዋል።

የሀገር ሽማግሌዎቹ የምክክር መድረኩ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል ዘመናትን ያስቆጠሩ ቂምና ቁርሾዎችን በማስወገድ ሀገርን በእርቅና በአንድነት ስለሚያሻግር ለስኬታማነቱ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ነው ያረጋገጡት።

በቤንች ሸኮ ዞን የሚዛን አማን ከተማ የሀገር ሽማግሌ አቶ ተካ ማሞ እንደገለጹት፣ ሀገራዊ ምክክሩ የሁሉንም ሀሳብ በመቀበል መሰረታዊና ወሳኝ ጉዳዮች ላይ መግባባትን ይፈጥራል የሚል ተስፋ አላቸው።


 

ሂደቱ የሀሳብ ፍትሃዊነት የሰፈነበት እንዲሆን የበሉላቸውን እንደሚወጡ የገለጹት የሀገር ሽማግሌው፣ ለኮሚሽኑ ስራ ውጤታማነት የሁሉም የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ ይሄንን ለህብረተሰቡ የማስገንዘብ ሥራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።  

በአካባቢው ያሉትን ሀገር በቀል የሰላም እሴቶችና ግጭት መፍቻ እውቀቶችን በማጋራት ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል። 

ሀገራዊ ምክክሩ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል የሚስተዋሉ ችግሮችን በውይይት ፈትቶ አብሮነትን ለማጠናከር ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ያነሱት ደግሞ የጌዴኦ ዞን የሀገር ሽማግሌ አቶ  ሃይቻ ሃይሉ ናቸው።

"በተለይ በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠሩ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት ለችግሮቹ ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀትና ሀገርን ወደ እድገት ጎዳና ለማሻገር መሠረት ይጥላል" ብለዋል።

እንደ ሀገር የተስተዋሉ የፖለቲካ ቅራኔዎች በየዘመናቱ ትውልድን ዋጋ ማስከፈላቸውን የጠቀሱት አቶ ሃይቻ፣ በምክክር መድረኮች እንዲህ ያሉ ልምዶች ቆመው ዘላቂ ሰላም ይመጣል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል። 

ሀገራዊ የምክክር መድረኩ ሀገርን በእርቅ በማሻገር ልማትን የሚያፋጥንና የህዝቦችን እንድነት ስለሚያጠናክር ለስኬታማነቱ የበኩላቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የወላይታ ብሔር የሀገር ሽማግሌ አቶ ገብረመድህን ቴቃ፤ "ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የህብረተሰብ ተወካዮች ልየታን ጨምሮ እያከናወናቸው ያሉ በርካታ ተግባራት ተስፋ ሰጪ ናቸው" ብለዋል። 

ኮሚሽኑ በሂደት ለሚያከናውናቸው እያንዳንዱ ተግባራት ስኬታማነት የሚችሉትን አስተዋጽኦ በማድረግ የኮሚሽኑ ተልዕኮ ግቡን እንዲመታ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል። 

"ሀገራዊ ምክክሩ በዘመናት ልዩነት የተስተዋሉ ጥላቻና አለመግባባቶችን በውይይት ፈትቶ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ጠቀሜታ እንዳለው ጽኑ እምነት አለኝ" ያሉት የሀገር ሽማግሌው፣ በአካባቢያቸው የህዝቡን ንቃተ ህሊና በማሳደግ የኮሚሽኑን ሥራ እየደገፉ መሆኑንና ይህንንም እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል።   

"በሀገራችን ቂምና ቁርሾ ተወግዶ ህዝቡ አንድነቱ እንዲጠናከርና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በሀገራዊ ምክክሩ የተጀመረው ተስፋ ሰጪ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት" ያሉት ደግሞ የአሪ ባላባት ባቢ አርማኮ ዲክሳ ናቸው።


 

ባቢ አርማኮ እንዳሉት ሀገራዊ ምክክሩ በስኬት ተጠናቆ የታሰበው ዘላቂ ሰላም እና ሀገራዊ አንድነት እንዲረጋገጥ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የራሱን አሻራ ማሳረፍ ይኖርባቸዋል።

"በተለይ የባህል መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴን በመጠቀም ህዝቡን በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ወደ ሚያግባቡ ሀሳቦች የማምጣት ኃላፊነታችንን መወጣት አለብን፤ እኔ ለዚህ ዝግጁ ነኝ" ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም