ቀጥታ፡

ኮሚሽኑ በምሥራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች በወረዳ ደረጃ አጀንዳ በማሰባሰብ ሂደት የሚሳተፉ ተወካዮች ልየታ እያካሄደ ነው

ሐረር  ፤ መጋቢት 18/2016(ኢዜአ)፦ አገራዊ የምክክር ኮምሽን በምሥራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች በወረዳ ደረጃ  አጀንዳ በማሰባሰብ ሂደት የህብረተሰብ ክፍሎችን ወክለው የሚሳተፉ ተወካዮች ልየታ በማካሄድ ላይ መሆኑን ገለጸ።

በኢትዮዽያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የተመራውና ለቀጣይ አራት ቀናት የሚቆየው የተወካዮች ልየታ በአጀንዳ ማሰባሰብ ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችና ተጠባባቂዎች የሚመረጡበት መድረክ በሐረር ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በኮሚሽኑ የተሳታፊዎች ልየታ አስተባባሪ አቶ ሲሳይ ጎበሳ በወቅቱ እንደገለጹት አገራዊ የምምክር ኮሚሽኑ በአሁኑ ወቅት የሚታዩ የጋራ ችግሮችን ለመፍታት የሰው ሃይልና በጀት በመመደብ እየሰራ ነው።


 

በአሁኑ ወቅትም ኮሚሽኑ በተለያዩ ክልሎች ያለውን የሰው ሃይል በማሰማራት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያካተተ የተሳታፊ ልየታ ስራን በማገባደድ ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅትም በምስራቅና ምዕራብ ሀረርጌ ዞኖች ባሉ 36 ወረዳዎች በሀገራዊ ምክክሩ ላይ አጀንዳ በማሰባሰብ ሂደት የህብረተሰብ ክፍሎችን ወክለው የሚሳተፉ ተወካዮች ልየታ  እየተካሄደ  እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ከተሳታፊው ልየታ ጎን ለጎን ስለ ሀገራዊ ምክክሩ ጭብጥ ሃሳቦች ገለጻ የማድረግ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

በሐረር ከተማ ትላንት በተጀመረውና ለቀጣይ ለአራት ቀናት በሚቆየው የተወካዮች ልየታም 1ሺህ 80  በአጀንዳ ማሰባሰብ ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችና ተጠባባቂዎች እንደሚመረጡ ጠቅሰዋል።

በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ተወካዮች ልየታ ላይ ለመሳተፍ ከምስራቅ ሐረርጌ ዞን ባቢሌ ወረዳ እንደመጡ የገለጹት ሃጂ አሚን አብዲ፣ ሀገራዊ ምክክሩ ሰላም፣ ልማትና አብሮነትን ለማጠናከርና የብሔር ብሔረሰቦችን  አንድነትን ለማጎልበት ወሳኝ ነው ብለዋል።


 

በአጀንዳ ማሰባሰብ ተወካዮች ልየታ ከተለያዩ ማህበራዊ መሠረቶች እንደመምጣታችን ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በቅርበት ለመስራት ዝግጁ ነን ያሉት አቶ አሚን፤ ለስኬታማነቱ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል። 

ከምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ኮምቦልቻ ወረዳ የመጡት አቶ ታመነ ፍቃዴ ወደ አንድ የጋራ ትርክት ለማምጣት የምክክር ሂደቱ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።


 

አለመግባባቶችን ተወያይቶ በጋራ ለመፍታት የሚያስችል የመፍትሔ ሀሳብ በማምጣት ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን የበኩላቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን የገለጹት አቶ ታመነ በአሁኑ ወቅትም ሁሉንም የማህበረሰብ  ክፍል ያሳተፈ ልየታ እያከናወኑ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

ኮሚሽኑ በሚያካሂደው ስራዎች ላይ በንቃት በመሳተፍና አገራዊ መግባባት በመፍጠር ረገድ ተሳትፏችውን እንደሚያጠናክሩም ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም