ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከሶማሌ ላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት የሚደገፍና ጠቀሜታው የጎላ ነው

ሰመራ፤ ጥር 7/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከሶማሌ ላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት ጠቀሜታው የጎላ ነው ሲሉ በአፋር ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና የሶማሌላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ በቅርቡ በአዲስ አበባ ታሪካዊ የሆነ የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ይታወሳል።

በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ መንግስት እና የሶማሌላንድ መንግስት የተፈራረሙት የትብብር እና የአጋርነት መግባቢያ ሰነድ በተለያዩ ዘርፎች በቀጣይ ለሚኖር ግንኙነቶች ማዕቀፍ እንደሚሆን ጠቅሰዋል።

የመግባቢያ ስምምነት ሰነዱ የሁለቱን ወገኖች የፖለቲካ፣ የዲፕሎማሲ፣ የፀጥታ እና የኢኮኖሚ ትብብርን የሚያጠናከር መሆኑንም ተናግረዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው በአፋር ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እንዳሉት፤ የመግባቢያ ስምምነቱ የሚደገፍና ወቅታዊ ነው።

የአፋር ነፃ አውጭ ግንባር ፓርቲ ሊቀመንበር ሐሰን ዳውድ ስምምነቱ ሊደገፍ የሚገባው ነው ሲሉ ገልጸዋል።

 

ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ የተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት የቀጣናውን ሁለንተናዊ እድገት የሚያፋጥን ነው-- የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት

የመግባቢያ ስምምነቱ አገራችን በዲፕሎማሲ ጉዞ ላይ ያላትን ከፍታ ያሳየ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነቶች ቢኖርም እንኳ ለአገር የሚጠቅም እስከሆነ ድረስ የሚደገፍ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሁሉን አቀፍ ድጋፋቸውን እንደሚያደርጉ ሊቀመንበሩ ተናግረዋል።

የአርጎባ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት(አህዴድ)ሊቀ መንበር አሊ ዘይኑ በበኩላቸው፤ ከሶማሌ ላንድ ጋር የተደረገው የመግባቢያ ስምምነት በሙሉ የሚደግፉ መሆኑን ገልጸዋል።

የመግባቢያ ስምምነቱ ሁሉን ዓቀፍ  ተጠቃሚ ያለው  በመሆኑ ለተግባራዊነቱ አንድ የምንሆንበት ነው ብለዋል።

የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር(አርዱፍ) ምክትል ሊቀመንበር መሐመድ አወል ወግሪስ በበኩላቸው፤ ከሶማሌ ላንድ ጋር የተደረገውን ስምምነት ፓርቲያቸው እንደሚደግፈው ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ ከ30 ዓመታት በላይ ያለባህር በር መቆየቷን ያወሱት ምክትል ሊቀ መንበሩ፤ ለስምምነቱ ተግባራዊነት በትብብር መሠራት እንዳለበት ጠቅሰዋል።

ለዚህም ኢትዮጵያ ያደረገችው ስምምነት ዕውን እንዲሆን ከመንግስት ጎን መሆናቸውን ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም