ቀጥታ፡

አየር መንገዱ በኢትዮጵያ የኤሮስፔስ ቴክኖሎጂዎች ማምረቻ ኢንዱስትሪን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ገለጸ

አዲስ አበባ ፤ጥቅምት 8/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሀገሪቱ የኤሮስፔስ ቴክኖሎጂዎች ማምረቻ ኢንዱስትሪን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን  የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።

አየር መንገዱ የተለያዩ የአውሮፕላን አካል መለዋወጫ እቃዎችን በሀገር ውስጥ በስፋት ለማምረት ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኤሮስፔስ ምህንድስና ዘርፍ የአውሮፕላን፣ የጠፈር መንኮራኩር እንዲሁም ከነዚህ ጋር ተጓዳኝ የሆኑ ስርዓቶችና መሳሪያዎች ንድፍ፣ ፈጠራ፣ ማምረትና ፍተሻ ላይ የሚያተኩር የምህንድስና ዘርፍ ነው።

እ.አ.አ በ2020 የኤሮስፔስ ዓለም አቀፍ የገበያ መጠን 328 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የደረሰ ሲሆን፤ እ.አ.አ በ2028 ወደ 430 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የዘርፉ ጥናቶች ያመለክታሉ።

በኤሮስፔስ የማምረቻ ኢንዱስትሪ  የአውሮፕላን የውስጥ አካላት ምርት ዓለም አቀፍ ሽያጭ እ.አ.አ 2019 19 ነጥብ 7 ቢሊዮን መድረሱንና እ.አ.አ እስከ 2027 በየዓመቱ የ3 ነጥብ 5 እድገት እንደሚያስመዘግብ ይገመታል።

የናይጄሪያ ብሔራዊ አየር መንገድን ለማቋቋም አዲስ ከተዋቀረው የናይጄሪያ መንግሥት ጋር በቅርበት እየተሰራ ነው - አቶ መስፍን ጣሰው

በዘርፉ የሚመረቱ የአውሮፕላን ቴክኖሎጂዎች ለአቪዬሽን ኢንዱስትሪው እድገት ቁልፍ ሚና እየተጫወቱ መሆናቸውም ይነገራል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ የአውሮፕላን የውስጥ አካላትን ማምረት የሚያስችለውን ስምምነት በነሐሴ ወር 2015  ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና ከኢንዱስትሪ  ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር መፈራረሙ ይታወቃል።

የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው በኢትዮጵያ የኤሮስፔስ ቴክኖሎጂዎች የማምረቻ ኢንዱስትሪ በሚፈለገው ደረጃ አለማደጉን ለኢዜአ ገልጸዋል።

እንደ ሞሮኮና ደቡብ አፍሪካ ያሉ አገራት የኤሮስፔስ ቴክኖሎጂዎችን በአገራቸው በስፋት በማምረት በአህጉሪቱ ተጠቃሽ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድም በመንገደኞችና በእቃ ጭነት በዓለም ላይ እያሰፋ ካለው አገልግሎቱ ባሻገር የአውሮፕላን አካል መለዋወጫ እቃዎችን ለማምረት ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው ብለዋል።


 

የአውሮፕላን የውስጥ አካልን በአገር ውስጥ በስፋት ለማምረት የጀመረው እንቅስቃሴ ለኢትዮጵያ ኤሮስፔስ የማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፍ መጎልበት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረውም ነው ያብራሩት።

የአውሮፕላን የውስጥ አካል መለዋወጫዎች በሀገር ውስጥ መመረት የውጭ ምንዛሬ ለማስገባት፣ የስራ እድል ለመፍጠርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማምጣት እንደሚያስችልም ዋና ስራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል።

ከዚህ ቀደም አየር መንገዱ ለረዥም ጊዜ ሁለት አይነት የአውሮፕላን እቃዎችን በጥገና ማዕከሉ ውስጥ እያመረተ ለቦይንግ ኩባንያ ሲያቀርብ የቆየ መሆኑን በማንሳት፤ አሁን ላይ የተጀመረው እንቅስቃሴም ይህን የማስፋት እንደሆነ አመልክተዋል። 

አየር መንገዱ ለአውሮፕላን አካል የሚሆኑ እቃዎችን ለማምረት በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ  ውስጥ ቦታ መረከቡንና ለዚሁ የሚሆን ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ከዓለም አቀፍ የአውሮፕላን አምራች ኩባንያዎች ጋር የሚመረትላቸውን የእቃ አይነቶች አስመልክቶ ንግግር እያደረገ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከ810 ሚሊዮን ብር በላይ መዋዕለ ነዋይ በማፍሰስ አራት ሄክታር የለማ መሬት በመውሰድ የተለያዩ የአውሮፕላን የውስጥ አካላትን ለቦይንግ፣ ለኤርባስ እና ጣሊያን አገር ለሚገኝ የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ ለማቅረብ እየሰራ ይገኛል።

አየር መንገዱ ለቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን የሚሆኑ "ኢንሱሌሽን ብላንኬት" የተሰኙ የአውሮፕላን የውስጥ ምቾት የሚያሻሽሉ ቁሶች የሚያመርትበት ፋብሪካ በ2014 ዓ.ም በስድስት ሚሊዬን ዶላር ወጪ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ መመረቁ የሚታወስ ነው።

'ኢንሱሌሽን ብላንኬት' አውሮፕላኑ ከፍታውን እየጨመረ በሚሄድበት ወቅት የበረራ አስተናጋጆችና መንገደኞችን ከከፍተኛ ቅዝቃዜና ከሞተር ድምፅ የሚከላከል ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም