የናይጄሪያ ብሔራዊ አየር መንገድን ለማቋቋም አዲስ ከተዋቀረው የናይጄሪያ መንግሥት ጋር በቅርበት እየተሰራ ነው - አቶ መስፍን ጣሰው - ኢዜአ አማርኛ
የናይጄሪያ ብሔራዊ አየር መንገድን ለማቋቋም አዲስ ከተዋቀረው የናይጄሪያ መንግሥት ጋር በቅርበት እየተሰራ ነው - አቶ መስፍን ጣሰው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2016(ኢዜአ)፦የናይጄሪያ ብሔራዊ አየር መንገድን ለማቋቋም አዲስ ከተዋቀረው የናይጄሪያ መንግሥት ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ''ኤር ናይጄሪያ'' የናይጄሪያ ብሔራዊ አየር መንገድን 49 በመቶ ድርሻ ይዞ ለማቋቋም በቂ ዝግጅት ሲያደርግ የቆየ መሆኑ ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎ አየር መንገዱን ለማቋቋም ከናይጄሪያ መንግሥትና ባለድርሻ ከሆኑ የናይጄሪያ ባለኃብቶች ጋር ሥምምነቶች መፈረማቸውም እንዲሁ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የናይጄሪያን ብሔራዊ አየር መንገድ በጋራ ለማቋቋም እየተሰራ ነው።
ይሁንና በቅርቡ በናይጄሪያ አዲስ መንግሥት መዋቀሩን ተከትሎ አየር መንገዱን ወደ ሥራ ለማስገባት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተጨማሪ ውይይቶች ማስፈለጉን ጠቁመዋል።
ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ወደ ናይጄሪያ፤ አቡጃ በማቅናት ከናይጄሪያ መንግሥት ተወካዮች ጋር በጉዳዩ ዙሪያ መነጋገራቸውን ገልጸዋል።
በወይይቱም የናይጄሪያ የመንግሥት አካላት ስለ ብሔራዊ አየር መንገዱ መቋቋም የፕሮጀክት ሂደት ለማወቅ ጥቂት ጊዜ እንዲሰጣቸው ጠይቀው፤ 'እየጠበቅናቸው ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
የናይጄሪያ ብሔራዊ አየር መንገድን ለማቋቋም የተጀመሩ ሥራዎችን ለማስቀጠል አዲስ ከተዋቀረው የናይጄሪያ መንግሥት ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑንም ዋና ሥራ አስፈጻሚው አረጋግጠዋል።