የአውሮፓ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያላቸው የኢንቨስትመንት ተሳትፎ እንዲጨምር ኅብረቱ ድጋፍ ያደርጋል- ጁታ ኡርፒላይነን - ኢዜአ አማርኛ
የአውሮፓ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያላቸው የኢንቨስትመንት ተሳትፎ እንዲጨምር ኅብረቱ ድጋፍ ያደርጋል- ጁታ ኡርፒላይነን
አዲስ አበባ፤ መስከረም 23/2016 (ኢዜአ)፦ የአውሮፓ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ተሳትፏቸው እንዲጨምር ድጋፍ እንደሚደረግ የአውሮፓ ኅብረት ዓለም አቀፍ የትብብር ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይነን ገለጹ።
ኮሚሽነሯ በኢትዮጵያ የነበራቸው የሁለት ቀናት የስራ ጉብኝት ፍሬያማ እንደነበር ገልጸዋል።
በጉብኝቱ ከኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ ከአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋቂ ማህማትና ከቀጣናዊ ልዑካን ጋር መወያየታቸውን ኮሚሽነር ጁታ ለኢዜአ ተናግረዋል።
በተጨማሪም በኢትዮጵያ ከሚገኙ የአውሮፓ ኩባንያዎች አመራሮች ጋር ምክክር ማድረጋቸውን አመልክተዋል።
የአውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያ ጋር የሚያደርጋቸውን የትብብር ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋገጠ
ውይይቱ ኩባንያዎቹን ጨምሮ የአውሮፓ የግሉ ዘርፍ ተዋናዮች በኢትዮጵያ ያላቸውን ተሳትፎ ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአውሮፓ የግል ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ኅብረቱ እንደሚያበረታታና ድጋፍ እንደሚያደርግ ነው ኮሚሽነሯ የተናገሩት።
ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ለመሳብና ለንግድ ስራ የተመቸ አውድ ለመፍጠር ለጀመረችው ስራ ኅብረቱ አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል ሕብረቱ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(አይኤምኤፍ) ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር አዲስ የፋይናንስ ድጋፍ ማዕቀፍ ይፋ ለማድረግ እያደረገ ያለው ድርድር ስኬታማ እንዲሆን ይደግፋል ነው ያሉት።
የአውሮፓ ኅብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማደስ እንደሚፈልግ ገልጸው፤ ትናንት ይፋ የተደረገው የ650 ሚሊዮን ዩሮ የድጋፍ ማዕቀፍ የዚሁ ማሳያ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የኅብረቱ ስትራቴጂካዊ አጋር ናት ያሉት ኮሚሽነሯ፤ ለኢትዮጵያ በምግብ ዋስትና፣ ጤና፣ ትምህርትና የተለያዩ መስኮች ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
ኮሚሽነሯ ኅብረቱ በኢትዮጵያ እየተገበረ ባለው የቴክኒክና ሙያ የስልጠና መርሐ-ግብሮች አንዱ በሆነው "የፈጠራ ልማት ማዕከል" ፕሮጀክት ተጠቃሚ ከሆኑ ወጣቶች ጋር መወያየታቸውን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ የነበራቸው አጠቃላይ ቆይታ ስኬታማና ፍሬያማ እንደነበርም ገልጸዋል።
ኮሚሽነሯ ትናንት በአዲስ አበባ በተካሄደው 18ኛው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ የገንዘብ ሚኒስትሮች ስብስባ ላይ መሳተፋቸው ይታወቃል።
የአውሮፓ ሕብረት ከኢትዮጵያ ጋር ካለው የኢኮኖሚ ትብብር ማዕቀፍ አንዱ የግሉ ዘርፍ ልማት እና በኢትዮጵያ የንግድ ስራ አመቺነት እንዲሻሻል ድጋፍ ማድረግ ነው።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ተዋዳዳሪና ምርታማ እንዲሆን የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን አቅም የማጎልበትና የሰው ኃይል ልማት ላይ የተለያዩ ድጋፎችን ያደርጋል።
እ.አ.አ በ2022 በቤልጂየም ብራስልስ በተካሄደው የአውሮፓ ኅብረትና የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ይፋ የሆነውና በመተግበር ላይ ያለው የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ስትራቴጂ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች አባል አገራት ያለውን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ማሳደግ ላይ ያተኮረ ነው።
ኢትዮጵያና የአውሮፓ ሕብረት ከ40 ዓመታት በላይ የቆየ የሁለትዮሽ ትብብር እንዳላቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።
ሁለቱ ወገኖች ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለመመስረት የሚያስችላቸውን ስምምነት እ.አ.አ በ2016 በቤልጂየም ብራሰልስ መፈራረማቸው የሚታወስ ነው።