በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ጉዳት እንዳይደርስ በቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራ ላይ በቅንጅት እየተሰራ ነው - የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ጉዳት እንዳይደርስ በቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራ ላይ በቅንጅት እየተሰራ ነው - የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን
አዳማ ፤ መስከረም 23/2016 (ኢዜአ)፡- በአየር ንብረት ለውጥ ሊኖር በሚችለው ድርቅና ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ በሚከሰተው ጎርፍ ጉዳት እንዳይደርስ በቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ገለፀ።
በኮሚሽኑ የሎጀስቲክስ ኦፕሬሽን ስራ አመራር ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ደምሴ ለኢዜአ እንደገለፁት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራዎች ሊከሰቱ የሚችሉትን ጉዳቶች ከመቀነስ አንፃር ወሳኝ ሚና አላቸው።
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ለ2ኛ ዙር አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ እያሰራጨ ነው
ኮሚሽኑ ከክልሎች፣ ከብሔራዊ ሜትሪዎሎጂ ኢንስቲትዩትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራዎች ላይ በትብብር እየሰራ መሆኑን ነው ያነሱት።
በተለይም በአየር ሁኔታ መለወጥ ምክንያት ሊኖር የሚችለው ጎርፍና ድርቅ በዜጎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራ ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
አሁን በሀገሪቷ በተለያዩ አካባቢዎች ሊኖር በሚችለው ዝናብ በሚከሰተው ጎርፍም ጉዳት እንዳይደርስ ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግና ከቦታው መነሳትም ካለበት እንዲነሳ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራ እየተሰራ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ድርቅ እንዲሁም በደቡብና ደቡብ ምስራቅ የሀገሪቷ አካባቢዎች ደግሞ ጎርፍ ሊያስከትል የሚችል ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ትንበያዎች መኖራቸውንም አክለዋል።
በመሆኑም ከግብርና፣ ጤና፣ የእንስሳት ሀብትና ትምህርት ሴክተሮች ጋር የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራዎችን ተከትለን በቅንጅት መስራት ይገባናል ሲሉም አስገንዝበዋል ዳይሬክተሩ።
ችግሮቹ ከተከሰቱም የከፋ ጉዳት እንዳያደርሱ መስራት አለብን ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ለአብነትም ባሮና አዋሽ ወንዞች ሞልተው የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የተፈናቀሉ ቢሆንም ፈጣን የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደርሳቸው መደረጉን አንስተዋል።
ለሚከሰቱት ችግሮች የሚሰጠው የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራን ወስዶ በአግባቡ ካለመተግበር የሚታዩ ችግሮችን እንደ ክፍተት አንስተው፤ በቀጣይ ህብረተሰቡ ሰፊ ግንዛቤ እንዲያገኝ በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት በትብብር መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።
ጎርፍና ድርቅ የተከሰተባቸው የአገሪቷ አካባቢዎች የምግብ እህልና አልሚ ምግቦች በአስቸኳይ ድጋፍ መልክ እንዲደርሱ ኮሚሽኑ ሁለተኛውን ዙር የስርጭት ስራ እያከናወነ መሆኑንም አስታውሰዋል።
በዚህም ከ600ሺህ ኩንታል በላይ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ሩዝ፣ አልሚ ምግብና ከ1 ሚሊዮን ሊትር በላይ የምግብ ዘይት በአሁኑ ወቅት እየተሰራጨ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል።