የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ለ2ኛ ዙር አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ እያሰራጨ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ለ2ኛ ዙር አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ እያሰራጨ ነው
አዳማ ፤ መስከረም 21/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ለ2ኛ ዙር አስቸኳይ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ስርጭት መጀመሩን ገለፀ።
ኮሚሽኑ አዳማ የሰብዓዊ ድጋፍ እርዳታ ማስተባበሪያ ቅርንጫፍን ጨምሮ በሀገሪቷ ከሚገኙ ስምንት ማዕከላት ስንዴና በቆሎ እንዲሁም የዳቦ ዱቄትና አልሚ ምግቦችን ለ2ኛ ዙር ስርጭት ዛሬ በይፋ የማጓጓዝ ስራ ጀምሯል።
በኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የሎጀስቲክስ ኦፕሬሽን ስራ አመራር ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ደምሴ እንደገለፁት ኮሚሽኑ በሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ተፈናቅለው በመጠለያ ለሚገኙ ዜጎች ነው የአስቸኳይ ድጋፍ እያደረገ ያለው።
በመጀመሪያው ዙር ተመሳሳይ ድጋፍ ለሁሉም ክልሎች መሰጠቱን ጠቅሰው አሁንም መንግሥት ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች ተደራሽ እያደረገ ነው ብለዋል።
በዚህም በዛሬው ዕለት ከ600 ሺህ ኩንታል በላይ ስንዴና በቆሎ፣ የዳቦና የበቆሎ ዱቄት፣ ሩዝ እንዲሁም ከ10 ሺህ ኩንታል በላይ አልሚ ምግቦችና ከ1 ሚሊዮን ሊትር በላይ የምግብ ዘይት ለሁለተኛ ዙር ተደራሽ የማድረግ ስራ ጀምረናል ብለዋል።
ሰብዓዊ ድጋፉ ትግራይ ክልልን ጨምሮ ለተለያዩ ክልሎች አስቸኳይ እርዳታ ለሚሹ ከ4 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተደራሽ ለማድረግ ነው ብለዋል።
ድጋፉ የሚሰራጨው ከአዳማ፣ ወላይታ፣ ሻሸመኔ፣ ሽንሌ፣ ኮምቦልቻና ድሬ ደዋ ካሉት የኮሚሽኑ መጋዘኖች ካለው ክምችት መሆኑን ገልጸዋል።
ድጋፉ ከመጀመሪያው ዙር በመጠንና በአይነት መጨመሩን የገለፁት ዳይሬክተሩ፤ ይህም የሀገሪቷ የእህል ክምችት መጨመሩን የሚያሳይ መሆኑን አመልክተዋል።
ዳይሬክተሩ አክለውም መንግስት ከሚያደርገው ድጋፍ በተጓዳኝ ህብረተሰቡ ባለው የመደጋገፍ ባህሉ ችግሮቹን በጋራ ማለፍ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በኮሚሽኑ የአዳማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ወንደወሰን ፍቃዱ በበኩላቸው ከአዳማ ቅርንጫፍ መጋዘኖች በሁለተኛው ዙር ለትግራይ ክልል ብቻ ከ60 ሺህ ኩንታል በላይ ያልተፈጨ ስንዴና የስንዴ ዱቄት እንዲሁም 8 ሺህ 637 ኩንታል አልሚ ምግብ መላኩን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ በድርቅና ጎርፍ ለተጎዱ የኦሮሚያና ጋምቤላ ክልሎች በተለይም ለቦረና፣ ጉጂ፣ አርሲ፣ ባሌና ጋምቤላ 200 ተሽከርካሪዎች የዕርዳታ እህልና አልሚ ምግብ ከአዳማ መጋዘን እያጓጓዙ መሆኑን ጨምሮ ገልጸዋል።