ቀጥታ፡

አንድ ሺህ 439ኛው የኢድ አልፈጥር በአል በመላ ሀገሪቱ ተከበረ

ሰኔ 8/2010 ጨረቃ ትናንት አመሻሹ ላይ በመታየቷ  በዛሬው እለት አንድ ሺህ 439ኛው የኢድ አልፈጥር በአል በመላ ሀገሪቱ እየተከበረ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ስታዲየም በተከበረው በአል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ድሪባ ኩማን ጨምሮ የሃይማኖት አባቶችና የእምነቱ ተከታዮች ተገኝተዋል፡፡ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት  ፕሬዝዳንት ሼህ መሐመድ አሚን ጀማል በበዓሉ ዋዜማ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ሕዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ወር ያዳበራቸውን መልካም ስራዎች ማስቀጠል  እንዳለበት  አሳስበዋል፡፡ መንግስት በኢትዮጵያ መረጋጋትንና ብሄራዊ መግባባትን ለማምጣት የጀመረው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፣  ጥረቱ ለፍሬ እንዲበቃ ሕዝበ ሙስሊሙም  ከመንግሥት ጎን  እንደሚቆም አረጋግጠዋል። “እንደ አገር ያጋጠሙንን ችግሮች ለመሻገር ሙስሊምና ክርስቲያኑ ለዘመናት በአብሮነት መኖራቸው ትልቁን አስተዋጽኦ አበርክቷል” ብለዋል። የአገሪቷ አንድነትና ሰላም ተጠብቆ እንዲዘልቅ ሁሉም ሕብረተሰብ በየኃይማኖቱ ፀሎት እንዲያደርግና በተለይም ወጣቶች ለአገሪቷ ሰላም ዘብ እንዲቆሙም ጥሪ አቅርበዋል። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድና የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔም ለመላ የእስልምና እምነት ተከታዮት የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም