1 ሺህ 439ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል ነገ ይከበራል

865

አዲስ አበባ  ሰኔ 7/2010 ጨረቃ ዛሬ ምሽት በመታየቷ 1 ሺህ 439ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በነገው እለት ተከብሮ እንደሚውል ተገለጸ፡፡

የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት  ፕሬዝዳንት ሼህ መሐመድ አሚን ጀማል በዓሉን ምክንያት በማድረግ ለሙስሊሙ ማህበረሰብ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ሕዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ወር ያዳበራቸውን የተቸገሩ ወገኖችን የመርዳትና መሰል መልካም ስራዎችን ማስቀጠል  እንዳለበትም ፕሬዝዳንቱ አሳስበዋል፡፡

መንግስት በኢትዮጵያ መረጋጋትና ብሄራዊ መግባባት ለማምጣት የጀመረው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፣  ጥረቱ ለፍሬ እንዲበቃ ሕዝበ ሙስሊሙም  ከመንግሥት ጎን  እንደሚቆም አረጋግጠዋል።

“የኢትዮጵያ ህዝቦች እንደ አገር ያጋጠሙንን ችግሮች ለመሻገር ሙስሊምና ክርስትያኑ ለዘመናት በአብሮነት መኖራቸው ትልቁን አስተዋጽኦ አበርክቷል” ብለዋል።

የሰላም ዋጋ ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ በጥንቃቄና በትዕግስት መያዝ አንደሚገባም አሳስበዋል።

የአገሪቷ አንድነትና ሰላም ተጠብቆ እንዲዘልቅ ሁሉም ሕብረተሰብ በየኃይማኖቱ ፀሎት እንዲያደርግና በተለይም ወጣቶች ለአገሪቷ ሰላም ዘብ እንዲቆሙም ጥሪ አቅርበዋል።

በሌላ በኩል የሀጂ ጎዞ በረራ ክፍያ ላይ የተከሰተውን የዋጋ ንረት ለማሰተካከል በተደረገው ጥረት የ32 ዶላር ቅናሽ እንዲደረግ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በተደረገው ስምምነት መሰረት ምዝገባው እየተካሄደ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ለመላው የእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች ለኢድ አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል።

ሙስሊሙ ሕብረተሰብ ከሌሎች የእምነት ተከታዮች ጋር ለዘመናት የዘለቀውን የመከባበርና አብሮ የመኖር ዕሴቱን ጠብቆ ሊቀጥል እንደሚገባም ጉባዔው አሳስቧል።

ቀደም ሲል በአገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች ከብሄርና ከማንነት ጋር በተያያዘ  የተከሰቱ ችግሮች የቀነሱ ቢሆንም ችግሩ አሁንም በተወሰኑ አካባቢዎች የቀጠለ በመሆኑ “የዚህ መሰሉ ድርጊት በሁሉም ኃይማኖቶች የተወገዘ ነው” ብሏል ጉባዔው።

በመሆኑም ሕዝበ ሙስሊሙ ችግሩ በዘላቂነት እንዲፈታ በሚደረገው እንቅስቃሴ መንፈሳዊ ኃላፊነቱን መወጣት እንደሚጠበቅበትም ተጠቅሷል።

በግጭቱ ሳቢያ ለተፈናቀሉና በጊዜያዊ መጠለያዎች ለሚገኙ ወገኖች ሕዝበ ሙስሊሙ ድጋፍ እንዲያደርግም ጉባዔው ጥሪ አቅርቧል።