ከሰኔ 16ቱ የቦምብ ጥቃት ጋር በተያያዘ በሁለት ተጨማሪ ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ሊመሰረት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ከሰኔ 16ቱ የቦምብ ጥቃት ጋር በተያያዘ በሁለት ተጨማሪ ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ሊመሰረት ነው
አዲስ አበባ ነሓሴ 2/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድን ለመደገፍ ሰኔ 16 በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ላይ የተፈጸመውን የቦንብ ጥቃት አስመልክቶ በተጨማሪ ሁለት ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ሊመሰረት ነው። በሌላ በኩል በተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት በተጠረጠሩት በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል ማስተባበርያ መምሪያ ኃላፊ በነበሩት በአቶ ተስፋዬ ዑርጌ ላይ ተጨማሪ የሰባት ቀናት የምርመራ የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል። ጉዳዩን የያዘው መርማሪ ፖሊስ በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት 10ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ እንዳስረዳው፤ በመዝገብ ቁጥር 265191 የተጠረጠሩ አቶ በየነ ሩዳና አቶ አብዲሳ መገርሳ በተባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ ሲያካሂድ የነበረውን ምርመራ አጠናቆ ለጠቅላይ አቃቤ ሕግ አስረክቧል። ጠቅላይ አቃቤ ሕግም ሓምሌ 27 ቀን 2010 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ የምርመራ ሰነዱን ከመርማሪ ቡድኑ ተረክቦ በሰነዱ ላይ ምርመራ ሲያካሂድ መቆየቱን ገልጿል። ይሁንና ሰኔ 16 ቀን የተፈጸመው ወንጀል ውስብስብና በርካታ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች በመኖራቸው ሰነዱን መርምሮ ለማጠናቀቅና ውሳኔ ለማሳለፍ አለመቻሉን በመግለጽ፣ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩ በመደበኛ ፍርድ ቤት እንዲታይ የክስ መመስረቻ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል። ከወንጀሉ ክብደትና ውስብስብ ባህሪ አኳያም ዋስትና ስለሚከለክል ተጠርጣሪዎች በማረፊያ ቤት እንዲቆዩ ትዕዛዝ እንዲሰጠውም ለችሎቱ አቅርቧል። አንደኛ ተጠርጣሪ አቶ በየነ ሩዳ "ከተያዝኩ ወር አልፎኛል፣ ቤተሰቤ በቅርብ የለም፣ ሽንት ቤት ነው የታሰርኩት፤ ፖሊስ ቃሌን ከተቀበለ አስር ቀን አልፎታል፤ እስካሁን ክስ መመስረት ነበረበት" ሲሉ የክስ መመስረቻ ጊዜውን ተቃውመዋል። የሁለተኛ ተጠርጣሪ ጠበቃ በበኩላቸው ደንበኛቸው ለተጠርጣሪዎች ፋይናንስ በማድረግ ወንጀል መጠርጠራቸውን በመግለጽ፤ ወንጀሉ "ዋስትናን አይከለክልም" በማለት ተከራክረዋል። አቃቤ ሕግ በበኩሉ በተመሳሳይ ድርጊት የተጠረጠሩ ሌሎች ግለሰቦች በመኖራቸው በእያንዳንዱ ተጠርጣሪ ላይ የወንጀል ተሳትፎ ለመደበኛ ፍርድ ቤት ለማቅረብ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል። ግራ ቀኙን የተመለከተው ችሎቱም ከወንጀሉ ውስብስብነትና ክስ ለመመስረት ቀጠሮ የተያዘላቸውን ሌሎች ተጠርጣሪዎችን ጉዳይ ከግምት ውስጥ በማስገባት የ10 ቀናት ክስ መመስረቻ የጊዜ ቀጠሮ ፈቅዷል። በሌላ በኩል በተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት በመዝገብ ቁጥር 265044 ጉዳያቸው እየታየ ያሉት የቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል ማስተባበሪያ መምሪያ ኃላፊ የነበሩት አቶ ተስፋዬ ዑርጌ ችሎት ቀርበዋል። መርማሪ ፖሊስም ከዚህ በፊት በተሰጠው የምርመራ ጊዜ ቀጠሮዎች በተጠርጣሪው ላይ የምስክር ቃል መቀበል፣ በገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል በተባሉ ግለሰቦች ጉዳይ ከባንክ ምላሽ መቀበሉን፣ በጥቃቱ ተጎጂዎችና አስከሬን ምርመራ መረጃዎችን ከሆስፒታል መቀበሉን፣ ከኢትዮ ቴሌኮም የስልክ መረጃዎችን መቀበልና ሌሎች መሰል ተግባራትን ማከናወኑን አመልክቷል። ነገር ግን ተጠርጣሪው በአገር ውስጥና በውጭ የሽብር ቡድኖች ስለነበራቸው ግንኙነት ማጣራት፣ ተጨማሪ የምስክር ቃል መቀበል፣ የሃብት ማጣራት፣ የሰነድና ቴክኒክ ምርመራዎች ውጤት መጠባበቅና ሌሎች ቀሪ ስራዎች እንዳሉት ገልጿል። ግለሰቡ ቢለቀቅ በሰውና ሰነድ ማስረጃዎች ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር በመግለጽም የዋስትና ጥያቄው ውድቅ ተደርጎ ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል። የተጠርጣሪ ጠበቃ በበኩላቸው በተመሳሳይ ድርጊት ተጠርጣሪዎች ምርመራ ተጠናቆ ለአቃቤ ሕግ በተሰጠበት ሁኔታ ለደንበኛቸው በተለየ መንገድ ተጨማሪ ጊዜ ሊሰጥ አይገባም፤ የፖሊስ ማስረጃዎችም ከመንግስት መሥሪያ ቤት ስለሚሰበሰቡ ደንበኛቸው በዋስ ቢለቀቁ የሚያሳድሩት ተዕጽኖ እንደማይኖር ተናግረዋል። መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ ተጠርጣሪው በዋስ ቢለቀቁ በሚሰሩበት መስሪያ ቤት በዳሬክተር ደረጃ ስለነበሩ በስራቸው ከነበሩ ሰራተኞች ጋር በመመሳጠር "ሰነድ ያበላሻሉ፣ ያሸሻሉ የሚል ስጋት አለን" ብላል። ከዚህም በተጨማሪ ከምስክሮች ጋርም ግንኙነት ፈጥረው በስራችን ላይ ተጽዕኖ ስለሚያሳድሩ ዋስትናው መፈቀድ እንደሌለበት ገልጿል። ግራ ቀኙን የተመለከተው ችሎቱም ፖሊስ ከጠየቀው የ14 ቀናት ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ወስጥ 7 ቀናት ብቻ ፈቅዷል። በዚህም ችሎቱ በመጀመሪያው መዝገብ የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦችን ክስ ለመስማት ለነሐሴ 12 ቀን፤ በተጠርጣሪ አቶ ተስፋዬ ላይ ፖሊስ ምርመራውን አጠናቆ እንዲቀርብ ደግሞ ለነሐሴ 9 ቀን 2010 ዓ.ም ቀጠሮ ይዟል።
በመስቀል አደባባይ በተፈጸመው ጥቃት የሁለት ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን፤ ከ150 በላይ በሚሆኑት ላይ ደግሞ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱ ይታወሳል።