ቀጥታ፡

በሰኔ 16 የድጋፍ ሰልፍ ወቅት በደረሰው ፍንዳታ ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ሊመሰረት ነው

አዲስ አበባ ሀምሌ 27/2010 ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም የድጋፍ ሰልፍ ሲካሄድ በደረሰው የቦንብ ፍንዳታ የተጠረጠሩ አምስት ግለሰቦች ላይ ዐቃቤ ሕግ ክስ ሊመሰርት ነው። ጉዳዩን የያዘው መርማሪ ፖሊስ ልደታ በሚገኘው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት 10ኛ ወንጀል ችሎት እንዳስረዳው፤ በተጠረጣሪዎች ላይ እስካሁን ሲያካሂድ የነበረውን ምርመራ አጠናቆ የምርመራ ሰነዱን ለጠቅላይ ዐቃቤ ሐግ አስረክቧል። ተጠርጣሪዎች 1ኛ አብዲሳ ቀነኔ፣ 2ኛ ደሳለኝ ተስፋዬ፣ 3ኛ ጌቱ ግርማ፣ 4ኛ ሕይወት ገዳ፣ 5ኛ ባህሩ ቶላ ሲሆኑ በጤና እክል ምክንያት አማኑኤል ሆስፒታል ከሚገኙት 4ኛ ተጠርጣሪ በቀር ሌሎቹ ችሎት ቀርበዋል። ዐቃቢያነ ሕጎች በበኩላቸው በዛሬው ዕለት ከመርማሪ ፖሊስ የምርመራ ሰነዱን መረከባቸውን ለችሎቱ አስረድተው በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ሰርዓት ሕጉ አንቀጽ 109 (1) መሰረት በቀረበው ሰነድ ላይ የውሳኔ ሃሳብ አሳልፎ ክስ ለመመስረት የክስ መመስረቻ 15 ቀናት እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል። ችሎቱም የምርመራ ሰነዱ ለዐቃቤ ሕግ የቀረበበትን ዕለትና ወንጀሉ ለሰው ሕይወት ህልፈት፣ የበርካታ ሰዎችም ቀላልና ከባድ ጉዳት የደረሰበት መሆኑን በመጥቀስ ዐቃቤ ሕግ የጠየቀውን የ15 ቀናት የክስ መመስረቻ ጊዜያት ፈቅዷል። ስለሆነም ፍርድ ቤቱ በነሐሴ 11 ቀን 2010 ዓ.ም ከጠዋቱ 3 ሰዓት ላይ የአቃቤ ሕግን ክስ ለመስማት ቀጠሮ ይዟል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም