ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም
ይጫኑ

1

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም



2

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም



3



4

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

አድራሻ፦ አራዳ ክፍለ ከተማ

ስልክ ቁጥር +251-11-55-00-11 +251-11-56-39-31 +251-11-56-52-21

ፋክስ ቁጥር +251-11-55-16-09 enanegari@gmail.com

በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በየሁለት ወሩ የምትታተም መጽሔት

ማውጫ

መስከረም 2009 ዓ.ም ተመሰረተች



5

ድረ-ገፅ www.ena.et/web/negari

ውድ አንባቢያን፤ ሰላም ለእናንተ ይሁን! ነጋሪ መፅሔት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ይዛ መጥታለች።

አገራት የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች፣ ግጭቶች እና አለመግባባቶች ዘመን እና ወቅቱን በሚዋጁ ስልቶች ለመፍታትና መፍትሔ ለመስጠት የተለያዩ አማራጮችን ይጠቀማሉ። ችግሮቹን ለመፍታት የሚጠቀሟቸው ዘዴዎች የችግሮቹን ስፋት፣ ዓይነትና አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገቡ ናቸው። ከእነዚህ ዘዴዎች አንዱ እና በበርካታ አገራት ተግባራዊ እየሆነ ያለው አገራዊ ምክክር ነው።

በበርካታ ችግሮችና ስብራቶች ውስጥ ያለፈችው ኢትዮጵያም ከችግሮቿና ከስብራት ታሪኮቿ ለመውጣት ሁነኛ መፍትሄ የሆነውን ምክክር ለማካሄድ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአዋጅ አቋቁሟ ጉዞ ከጀመረች ሰነባብታለች፡፡ የኮሚሽኑ የእስካሁን ሂደት፣ የምክክሩ ዓላማና አጠቃላይ ሂደት የነጋሪ ዐብይ ርዕስ ነው።

. . . ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ባለቤት በነበረችበት ዘመን በቀይ ባሕር ላይ የነገሡ የንግድ እና የጦር መርከቦቿ ባሕሩ ላይ መልህቃቸውን ዘርግተው ዘመናትን ተሻግረዋል፤ ከቀይ ባሕር እስከ ሕንድ ውቅያኖስ ድንበር፤ ከአንደኛው የወደብ መነሻ እስከ ሌላኛው መዳረሻ አስሰዋል። የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው እያውለበለቡ በክብርና በኩራት ቀዝፈዋል። ታሪክ ይህን ይመሰክራል።. . . ኢትዮጵያና የባህር በር የነጋሪ ሌላው ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ቀርቧል።

በሥርዓተ መንግሥታት ለውጥ ያልተናወጠ ወዳጅነታቸውን ማጽናት የቻሉ የሁለት አገራትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት፤ በታሪክ ዑደት ውስጥ ያለፉበት መንገድ ተመሳስሎሽ ይስተዋልበታል። ሁለቱ አገራት ያለፉባቸው ሥርዓተ መንግሥታት ባህሪና ዕጣ ፈንታ ያመሳስላቸዋል። በየዘመናቱ አያሌ ኃይሎች ሁለቱንም አገራት በተደጋጋሚ አጥቅተዋል። ሁለቱም አገራት በጀግንነት ተፋልመው ህልውናቸውን አስጠብቀው ዘልቀዋል። ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው ከተጀመረ ጀምሮ የሚያመሳስላቸው ታሪካዊ ዑደት ያላቸው እነዚህ አገራት . . . የኢትዮጵያ እና የሩሲያን ከአድዋ እስከ ዛሬ የዘለቀ ወዳጅነት ነጋሪ ታስቃኛለች።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥልቅ ወዳጅነትና አክብሮት የተሞላበት ድንቅ ዲፕሎማሲያዊ አቀባበል ምክንያት ግዙፍ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን በዘገባዎቻቸው እማኝነታቸውን የሰጡበት፤ በኢትዮጵያ እና በሕንድ ታሪካዊ ወዳጅነት ጉልህ አሻራ ያኖረው የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሽሪ ናሬንድራ ሞዲ የኢትዮጵያ ጉብኝት፤ የመኪና እና የቡና ዲፕሎማሲ. . . በነጋሪ ይተነተናል።

ነጋሪ በኢትዮጵያ የመስኖ ልማት ያስገኛቸው ትሩፋቶች፣ በዓለም አቀፍ ፋይናንስ ውስጥ ቁልፍ ሚና ያላቸው የኢንቨስትመንት ባንኮች መከፈት ጠቀሜታ እና ጤና ላይ ያተኮሩ ጽሁፎችን ሰንዳ ወደ እናንተ ደርሳለች፤ ዝለቁ!

መልካም ንባብ!

ዋና አዘጋጅ ተስፋዬ ቦካ

ም/ ዋና አዘጋጅ የሺመቤት ደመቀ

ከፍተኛ አዘጋጅ ፍቅርተ ባልቻ

አዘጋጅ መንገሻ ገ/ሚካኤል

አርት ዳይሬክተር ነብዩ መስፍን nebiyou1st@gmail.com

መልዕክት

ኢትዮጵያና የባሕር በር 06

ኢንቨስትመንት ባንክ - የኢኮኖሚ ማሻሻያው

ገፀ በረከት 20

የኢትዮ-ሕንድ የወዳጅነት ማማ

34 ምክክር ለሀገር ክብር

54 ተለምዷዊ የዲፕሎማሲ ብሂልን የለወጠ እጥፋት

74 ሕይወት ለመታደግ -

90 የኢትዮጵያ መስኖ ልማት

ትሩፋቶች 100

የውጤታማነቱ አንዱ ማሳያ. . .

114



6

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያና

ፖለቲካ



7

የባሕር በር

ኢትዮጵያ ከአክሱም ዘመነ መንግሥት አንስቶ የባሕር በር ባለቤት እንደሆነች የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ከሁለት ሺህ ኪሎሜትር ያላነሰ የባሕር ክልል ነበራት። ከዓሰብ እስከ ምጽዋ፣ ከዘይላ እስከ ታጁራ፣ ከአዱሊስ እስከ በርበራ ያሉ ጥንታዊ ወደቦችን በባለቤትነት እና በበላይነት ለዘመናት አስተዳድራለች፤ ተገልግላባቸዋለች።

ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ባለቤት በነበረችበት ዘመን በቀይ ባሕር ላይ የነገሡ የንግድ እና የጦር መርከቦቿ ባሕሩ ላይ መልህቃቸውን ዘርግተው ዘመናትን ተሻግረዋል፤ ከቀይ ባሕር እስከ ሕንድ ውቅያኖስ

በጌታቸው ያለው



8

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

ድንበር፤ ከአንደኛው የወደብ መነሻ እስከ ሌላኛው መዳረሻ አስሰዋል። የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው እያውለበለቡ በክብርና በኩራት ቀዝፈዋል። ታሪክ ይህን ይመሰክራል።

የኢትዮጵያ የኃያልነት ዘመን በነበረው የአክሱም ሥረወ-መንግሥት ማክተሚያ እና የዛጉዌ ሥረወ-መንግሥት ወደ ንግሥነት መምጣት ገደማ ኤርትራ የምትባል አገር ፈጽሞ አልነበረችም። እንዲያውም እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ ዓለምም እንደ አገር አያውቃትም ነበር።

በኋላኛው ዘመን የአክሱም ዘመነ መንግሥት በመሃል አገር በተነሳው የውስጥ የሥልጣን ሽኩቻ ምክንያት መውደቁን ተከትሎ ኢትዮጵያ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት አልነበራትም። እንዲያም ሆኖ እስከ ዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ድረስ ኤርትራ ሐማሴን፣ ሰራዬን እና የአኮሎጉዛይ ደጋማ አካባቢዎችን እንዲሁም የሰሜንና ምዕራብ ቆላማ አካባቢዎችን ጨምሮ በባሕረ ነጋሽ ትታወቅ የነበረች የኢትዮጵያ ሰሜናዊ የግዛት አካል ስለመሆኗ ከታሪክ ባለፈ ዓለም የሚያውቀው ጉዳይ ነው።

ለኤርትራ እንደ አገር ለመቆጠር መደላድሉ የተፈጠረው በኢጣሊያ ቅኝ ግዛት ዘመን እንደሆነ ታሪክ ያስረዳል። ከዚያ ቀደምም ሆነ በኋላ ማለትም በ1993 ዓ.ም ህጋዊ ባልሆነ ምክንያትና ሴራ “ነፃ አገር”



9

ተብላ እስክትገነጠል ድረስ ኤርትራን በኢትዮጵያ የግዛት አካል እንጂ በአገርነት ዓለምም ታሪክም አያውቋትም።

በተለያዩ ዘመናት የነበሩት ታሪኮች እንደተጠበቁ ሆነው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በ1952 ዓ.ም ኤርትራ በኮንፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ጋር ሆና እንድትተዳደር ወስኗል። ከ1962 ዓ.ም በኋላ ግን ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል ሆና ተዋህዳለች። ይህን ተከትሎ ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነቷን ዳግም ማረጋገጥ ችላ ነበር። በ1993 ዓ.ም የኤርትራን ነፃ አገር መሆን ተከትሎ ኢትዮጵያ የባሕር በሯን አጥታ ወደብ አልባ ሆናለች።

ኢትዮጵያ እና ቀይ ባሕር በሦስት ሺህ ዘመን ታሪካቸው ሙሉ በሙሉ ተነጣጥለው የኖሩት ኢጣሊያ የአገሪቱን የሰሜን ክፍል ቅኝ በያዘበትና ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት ብቻ ነው። እናም ኢትዮጵያ ለምን እና እንዴት ከቀይ ባሕር ተገፋች የሚለው ጉዳይ ከመነሻው ማየት የሴራውን ውስብስብነት ለመግለጥ ይረዳል።

ኢትዮጵያዊያን ቀይ ባሕር ለኢትዮጵያ የታሪክ መነሻ ብቻ ሳይሆን የደም ሥር ነው ብለው ያምናሉ። ህልውናቸው የበቀለው፤ ታሪካቸው የተቀዳው ከቀይ ባሕር እና ከዓባይ ሸለቆ ነው የሚል እምነት አላቸው። በእርግጥ የኢትዮጵያ ህልውና እና የሥልጣኔ ታሪክ ከዓባይ እና ከቀይ ባሕር ተነጥሎ የሚታይ አይደለም። የቀይ ባሕርና የዓባይ ሸለቆ ወሰኖች የአገሪቱ የንግድ መግቢያና መውጫ በሮች በመሆን ያገልግሉ እንጂ የውጭ ጠላት ኃይሎች መግቢያና መውጫ በር በመሆን ብሔራዊ የደህንነት ሥጋት ሆነውም ለዘመናት ቆይተዋል።

ኢትዮጵያ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የውጭ ጦርነት የተከፈተባትም በቀይ ባሕር አቅጣጫ ነው። ፋሺስቱ የኢጣሊያ ጦር ኢትዮጵያን ለመውረር የመጣው በቀይ ባሕር በኩል ነው። ግብፆችም ሆኑ ሌሎች የውጭ ጠላቶች የበቀልና የተንኮል ሴራቸውን ለመርጨት አቅደው የመጡትም በዚሁ በኩል ነው። እናም ኢትዮጵያን ከቀይ ባሕር ነጥሎ ማየትም ሆነ ማሰብ ትናንትን የረሳ ነገን አሻግሮ ማየት የተሳነው ተደርጎ የሚቆጠር ነው።

እርግጥ ነው ቅኝ ገዢዎች ሆን ብለውና አስበውበት ያደረጉት የከፋፋይነት አካሄድ አሁን ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ አገራትን ዘመን ለተሻገረ ግጭት ሲዳርግ ቆይቷል። አውሮፓዊያን ቅኝ ገዢዎች በዘመነ ቅኝ ግዛት አፍሪካን ሲቀራመቱ ጥለዋቸው ካለፉ ጥቁር አሻራዎች መካከል በአፍሪካ አገራት የፈጠሯቸው አወዛጋቢ ድንበሮች ተጠቃሾች ናቸው።

ቅኝ ገዢዎች የአፍሪካን የተፈጥሮ ኃብት ለማጋዝ እና አፍሪካዊያንን ሰጥ ለጥ አድርጎ ለመግዛት እንዲያመቻቸው ጎሳዎችን የሚከፋፍሉ ወይም በታሪክ የማይጣጣሙ ድንበሮችን በአንድ ግዛት ሥር አብረው እንዲኖሩ የሚያስገድዱ የዘፈቀደ ድንበሮችን በመፍጠር ለዘመናዊ የድንበር ግጭቶች ቀጥተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል። በዚህም በታሪክ ተወቃሽ ሆነዋል።

ድርጊቱ የወሰን ክፍፍሎችን፣ የጎሳ መከፋፈልን፣ አወዛጋቢ ብሔራዊ ማንነቶችን እና በኃብት ላይ የሚደረጉ ፉክክሮችን ሲያበረታቱ ታይተዋል። ይህ ደግሞ አንድ ወጥ የነበረችን አገር ለመገንጠል አሊያም በድንበር ተጋሪ አገራት መካከል ግጭቶች እንዲፈጠሩ ዋና ምክንያት በመሆን አሁን ድረስ



10

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

ቀጥሏል።

በአፍሪካ በቅኝ ገዢዎች የተሰመሩት አብዛኞቹ የዘፈቀደ ድንበሮች በአውሮፓ ኃያላን መንግሥታት የተሰመሩት እ.አ.አ ከ1884 እስከ 1885 በተካሄደው የበርሊን ኮንፈረንስ እና ያን ተከትለው በተደረጉ ሥምምነቶች መሰረት ነው።

እነዚህ የዘፈቀደ ድንበሮች በዋናነት ለራሳቸው ለቅኝ ገዢዎች የአስተዳደር ምቾት እና ኃብት ዘርፎ ወደ አውሮፓ ለመውሰድ ሲባል፣ ለነባር የአካባቢ የፖለቲካ፣ የጎሳ ወይም የባህል ገጽታዎች ብዙም ደንታ ባልነበራቸው አኳሃን የተሰመሩ ናቸው። በዚህም የአፍሪካ አገራት ከቅኝ ግዛት ነፃ ሲወጡ ቀደም ሲል በአውሮፓዊያን ገዢዎች የተሰመሩት የዘፈቀደ ድንበሮች አገራት አሁን ድረስ ወደ ግጭት እንዲያመሩ አድርጓቸዋል።

በወቅቱ ተቋቁሞ የነበረው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት ቻርተር) አገራት ቀደም ሲል የነበሩትን የቅኝ ግዛት ዘመን ድንበሮችን እንዲያከብሩ በግልጽ ደንግጓል። ቻርተሩ በወቅቱ እንዲጸድቅ የተደረገው በርካታ ድንበሮች በደንብ ያልተለዩ እና የክርክር ምንጭ ስለነበሩ ግጭትን ለማስቀረት ሲባል ቢሆንም ግጭቶችን ግን አሁንም ድረስ ማስቀረት አልቻለም።

ከነፃነት በኋላ የአፍሪካ ኅብረት (AU) ቻርተር አማካኝነት ሰፊ የግዛት ጥያቄዎችንና ሊከሰቱ የሚችሉ አለመረጋጋቶችን ለመከላከል አሁን ያሉትን የቅኝ ግዛት ድንበሮች ማክበር የሚለውን መርህ ተቀብለዋል። ሆኖም ይህ የሕግ ግትርነት ብዙውን ጊዜ ከነባራዊ እውነታዎች ጋር ሳይጣጣም እየቀረ (Legal Inviolability vs. Local Realities) ግጭቶች አሁን ድረስ ሲቀጥሉ ይስተዋላሉ።

በቅኝ ገዢዎች የዘፈቀደ የድንበር ስሪት ምክንያት በአፍሪካ በርካታ ግጭቶች ተከስተዋል። ለማሳያነትም የተወሰኑት ማንሳት ይቻላል፤

የታላላቅ ሐይቆች ቀጣና (Great Lakes Region)

ይህ ቀጣና የቅኝ ግዛት የዘፈቀደ የድንበር ማካለል ሰለባ ከሆኑት የአፍሪካ አካባቢዎች አንዱ ነው። የወቅቱ ቅኝ ገዢ የነበሩት ቤልጂዬም እና ጀርመን በኮንጎ እና ሩዋንዳ መካከል ያሰመሩት የድንበር ወሰን የአካባቢው ማኅበረሰብ የሆኑትን ሁቱ እና ቱትሲን ወዲያና ወዲህ ያዘበራረቀ ሆኗል። የዚህ ጦስ ደግሞ በሁለቱ አገራት መካከል ከፍተኛ የጎሳ ውጥረት በመፍጠር ደም አፋሳሽ የሆነ የሁለት ዙር ጦርነትን አዋልዷል።

ይህን ቀጣና በተለይም ኮንጎን ክፉኛ እያመሳት ያለው በM23 አማፂ የሚደረገው ግጭትም ሩዋንዳን ስቦ አማፂውን እየደገፈች በምስራቅ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ለዓመታት የተሻገረ አለመረጋጋት እና የጅምላ መፈናቀልን ማስከተሉን ቀጥሏል። በቅርቡ የሩዋንዳው ፕሬዚዳነት ፖል ካጋሜ እና የኮንጎው ፕሬዚዳንት ፊሊክሲ ትሼኬዲ በአሜሪካው ፕሬዚዳንት አደራዳሪነት ዋሽንግተን ዲሲ ተገኝተው የሠላም ድርድር የመፈራረማቸውም መነሻው ከኋለኛው ዘመን የቅኝ ገዢዎች የዘፈቀደ ድንበር ማካለል የሚነሳ ነው።

ምዕራብ እና መካከለኛው አፍሪካ

በዚህ ቀጣና ቅኝ ገዢዎች በሰሩት ሴራ ድንበራቸው ለውዝግብና ለግጭት ተጋላጭ ከሆኑት አገራት ካሜሩን እና ናይጄሪያ፣ ሴኔጋል እና ሞሪታኒያ



11

ተጠቃሽ ናቸው። ናይጄሪያ እና ካሜሩን በነዳጅ በበለፀገው የባካሲ ባሕረ ገብ መሬት የይገባኛል ጥያቄ ሳቢያ ወደ ወታደራዊ ግጭት አምርተዋል።

ናይጄሪያ ቅኝ ገዢ በነበሩት እንግሊዝና ጀርመን መካከል ድንበሩን አስመልክቶ እ.አ.አ በ1913 ከተደረሰው ስምምነት በፊት ባካሲ የግዛቴ አንድ አካል ነበር በሚል ትሞግታለች። በአንፃሩ ካሜሩን በአፍሪካ ኅብረት የድንበር ቻርተር መሰረት ባካሲ የራሷ እንደሆነ ትከራከራለች።

ውዝግቡ እ.አ.አ በ1980ዎቹ እና 1990ዎቹ እየከረረ ሄዶ የድንበር ግጭት በኋላም በናይጄሪያ እና በካሜሮን መካከል ጦርነትን ጭሯል። ካሜሩን ውዝግቡን ከጦር ይልቅ በፍርድ ቤት እልባት እንዲያገኝ በሚል እ.አ.አ በ1994 ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፍ የግልግል



12

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

ፍርድ ቤት (ICSJ) አቀረበች።

ጉዳዩን ሲመረምር የቆየው ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤትም ከስምንት ዓመታት በኋላ ባካሲን ለካሜሩን ይገባታል ሲል እንግሊዝ እና ጀርመን ያሰመሩት ወሰን እንዲጸና ወሰነ። እ.አ.አ በ2026 ናይጄሪያ የግሪን-ትሪ ስምምነትን (The Greentree Agreement) በመፈረም የፍርድ ቤቱን ውሳኔ መቀበሏን አሳወቀች። በዚህም ጦሯን ከባካሲ በማስወጣት ግዛቱን ለካሜሩን አስረከበች። ጉዳዩ በዚህ መልኩ የተቋጨ ቢመስልም ራሳቸውን ናይጄሪያዊያን አድርገው በሚቆጥሩ የባካሲ ነዋሪዎች አሁን ድረስ ተቃውሞ ይደመጣል። መፈናቀል እና ጥላቻውም ቀጥሏል።

ሌላው እ.አ.አ ከ1989-1991 የታየው የድንበር ውዝግብ ቀውስ በሴኔጋል እና በሞሪታኒያ መካከል ነበር። ሁለቱን አገራት ቅኝ ስትገዛ የነበረችው ፈረንሣይ ያሰመረቸው ወሰን የኋላ ኋላ ሴኔጋል እና ሞሪታኒያን ወደ ግጭት እንዲያመሩ አድርጓቸዋል። ሁለቱ አገራት የሚጋሩት የሴኔጋል ወንዝ እና በአካባቢው ያለው ሰፊ የግጦሽ መሬት ያልተቃኘ ድንበር ወሰን የይገባኛል ጥያቄ አስነስቶ በርካቶችን ለህልፈት የዳረገ ጦርነት ተካሂዷል። ግጭቱም ከፍተኛ መፈናቀል እና ዲፕሎማሲያዊ ውድቀትን አስከትሏል።

የአፍሪካ ቀንድ

ይህ ቀጣና ከቅኝ ግዛት ማብቃት በኋላ በድንበር ውዝግብ ምክንያት ዋና የግጭት ማዕከል ሆኖ ቆይቷል። እዚህ ላይ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ እንዲሁም የሶማሊያ እና ኬንያ የድንበር ውዝግቦችን ማንሳት ይቻላል።

ኬንያ እና ሶማሊያ በሁለት የድንበር ጉዳዮች በታሪክ ሲወዛገቡ ተስተውለዋል። አንደኛው እ.አ.አ. በ1960ዎቹ ብቅ ያለው “ታላቋ ሶማሊያ”ን የመፍጠር ሥር የሰደደ አባዜ ሲሆን ይህም ሶማሊኛ ተናጋሪዎች የሰፈሩባቸውን የሰሜን ምሥራቅ የኬንያ ግዛቶች ወደ ሶማሊያ የመጠቅለል ፍላጎት የፈጠረው ነው። ይህ ደግሞ እ.አ.አ ከ1963- 1968 በኬንያ እና ሶማሊያ መካከል የተካሄደውን በታሪክ “የሽፍታ ጦርነት” (Shifta War) በመባል የሚታወቀውን ግጭት አስከትሏል።

ጉዳዩ በኬንያ ሳይገታ በኢትዮጵያ እና በጅቡቲ በሚገኙ የሶማሊኛ ተናጋሪዎች ላይ ጭምር ያነጣጠረ ነበር። እዚህ ላይ የ1967ቱ የኢትዮ- ሶማሊያ ጦርነት በወቅቱ በነበረው የሶማሊያ መንግሥት የተስፋፊነት ስሁት እሳቤ ምክንያት የተለኮሰ እንደነበር ታሪክ ከትቦታል።

ሁለተኛው የሶማሊያና የኬንያ የውዝግብ ምንጭ በህንድ ውቅያኖስ ላይ ያለው የባሕር ክልል የይገባኛል ጥያቄ ነው። ይህ አወዛጋቢ የባሕር ክልል ሰፊ የጋዝ ክምችት እንዳለው ይታመናል። እናም ሶማሊያ የባሕር ድንበሩ ከመሬት ወሰን መስመር ጋር በተመሳሳይ ደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ መቀጠል እንዳለበት ትከራከራለች (እኩል ርቀት መርህ በሚል)። በአንፃሩ ኬንያ ድንበሩ በኬንያ የኬክሮስ ሃሳባዊ መስመር (Latitudinal Line) እየሄደ በባሕር ዳርቻው ላይ 45 ዲግሪ መዞር እንዳለበት ትከራከራለች።

ይህ ሁሉ እንግዲህ መንስኤው የቅኝ ገዢዎች የዘፈቀደ የድንበር ማካለል ያስከተለው ቀውስ ነው። አሁን ላይ በሁለቱ አገራት መካከል ለሚነሳው ውዝግብ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ እና እና



13

በ20 ኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ ላይ በእንግሊዞች እና በጣሊያኖች በዘፈቀደ የተሰመሩ የድንበር ወሰኖች ያመጡት ጣጣ ነው። ቅኝ ገዢዎቹ ዘር እና ባህላዊ እውነታዎችን ከትክክለኛ የመልከዓምድራዊ ዕውቀት ጋር ሳያገናዝቡ የፈጸሙት ጥፋት እያመረቀዘ አሁን ድረስ ቀጣናውን የግጭትና የውዝግብ ማዕከል አድርጎታል።

እ.አ.አ ከ1998 እስከ 2000 በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተደረገው የድንበር ጦርነት ቅጽበታዊ መነሻው ምንም ይሁን ምን መሰረታዊ መንስኤው በቅኝ ግዛት ስምምነቶች ውስጥ ከተደረጉ አሻሚ ውሳኔዎች የሚመነጭ ነው። የኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር መገለልም ከዚህ የቅኝ ግዛት ዘመን መልክዓ ምድርንና ሕዝብን ታሳቢ ያላደረገ የዘፈቀደ የድንበር ማካለል አንድ ብሎ የሚጀምር ነው።

በእርግጥ ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን በከፈሉት መስዋዕትነት ኢትዮጵያ በታሪክ በቅኝ ያልተገዛች ብቸኛዋ አፍሪካዊት አገር አድርጓታል። ግን ደግሞ ሰሜናዊ የአገሪቷ ክፍል ለዓመታት በኢጣሊያ ወራሪ ሥር ተይዞ መቆየቱ እና ይህን ተከትሎ ያቆጠቆጠው በውጭ ጠላቶች ሴራና በባንዳዎች አስፈጻሚነት በተቀነቀነ የማንነትና የመገንጠል ጥያቄ ኢትዮጵያን ከሕይወት መስዋዕትነት አንስቶ ከባሕር በር እስከ መገለል ያደረሰ ውድ ዋጋ አስከፍሏታል።

ከቅኝ ገዢዎች ሴራ ባሻገር ኢትዮጵያን ከቀይ ባሕር እንድትገለል ያደረጋት ሌላው ምክንያት ምንድነው የሚለውን ደግሞ እንመልከት። ኢትዮጵያ ከአክሱም ዘመነ መንግሥት አንስቶ የባሕር በር ባለቤት እንደሆነች የታሪክ ድርሳናት በግልጽ ያስረዳሉ። በተለያዩ ዘመናት የነበሩት ታሪኮች ሳይዘነጉ ኢጣሊያ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተሸንፋ ከሰሜናዊ የኢትዮጵያ ግዛት (የአሁን ኤርትራ) ተጠራርጋ ስትወጣ ለተወሰኑ ዓመታት በእንግሊዝ ሞግዚትነት እንድትተዳደር ሆኗል። ኤርትራ ከ1962 ዓ.ም በኋላ የኢትዮጵያ አካል ሆኗ ብትዋሃድም ከኢጣልያ ቅኝ ግዛት ነፃ ከወጣች በኋላ በግብፅ የሚደገፍ የማንነት እና የመገንጠል ጥያቄ በኤርትራ ብቅ ማለት ጀመረ።



14

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ የባሕር በር የማጣት ጉዳይ ግብጽን ጨምሮ ከምዕራባዊያን ሴራ የተያያዘ እንደሆነ የፖለቲካ ተንታኞች ይገልፃሉ። ለሦስት አሥርት ዓመታት ኢትዮጵያን ያደማው ፊት ጀብሃ በኋላ ላይ ደግሞ ሻዕቢያ የግብፆች ሴራ ዋና አስፈፃሚ በመሆን አገሪቷ ከባሕር በር ባለቤትነት ውጭ እንድትሆን ሰርቷል። ኢትዮጵያ የባሕር በር ቢኖራት ተጽዕኖ የመፍጠርና የቀይ ባሕርን ደህንነት የማስጠበቅ አቅሟ የማያጠራጥር ነው። ከዚህ ባለፈ የባሕር በር ለኢትዮጵያ የማደግ ፍላጎት የሚያግዝ በመሆኑ ኢኮኖሚያዊ እምቅ ፋይዳው የላቀ ነው።

ነገር ግን ይህን በሥጋት የሚመለከቱ እንደ ግብጽ ያሉ ኃይሎች ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር እንድትገለል ኤርትራዊያንን በማደራጀትና በማስታጠቅ ወደ ትጥቅ ትግል እንዲገቡ አድርገዋል። ከእነዚህ ኃይሎች ጀርባ ታዝለው ለሦስት አሥርት ዓመታት ኢትዮጵያን በትጥቅ ትግል ያደሙና የሞገቱ የሻዕቢያ ኃይሎች ማስተዋል የጎደላቸው የኢትዮጵያ የቀደሙ መሪዎች የፈጸሙትን ታሪክ ይቅር የማይለው ስህተት ተጠቅመው አገሪቷን የባሕር በር አሳጥተዋታል። በተዛነፈ ሕዝበ ውሳኔ (ሕዝበ ውሳኔ ከተባለ) በ1993 ዓ.ም ኤርትራ



15

ነፃ አገር ተብላ ስትገነጠል ኢትዮጵያ የባሕር በሯን አጥታ ወደብ አልባ ሆናለች።

የቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ ተልዕኮ

የኤርትራ ሕዝበ ውሳኔ (1993 Eritrean Referendum) ሲካሄድ በወቅቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ የነበሩት ግብፃዊው ቡትሮስ ቡትሮስ-ጋሊ ከእናት አገራቸው-ግብጽ የተሰጣቸውን ታላቅ ኃላፊነት ለመወጣት ያሳዩት ከልክ ያለፈ ላይ ታች በዓለም ሕዝብ ፊት ትዝብት ላይ ጥሏቸዋል። በጊዜው ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ ከግብጽ የተሰጣቸው ተልዕኮ ኤርትራን በማስገንጠል ሕጋዊና ዲፕሎማሲያዊ ከለላ እንዲሰጡ ማድረግ ነበር።

ሕዝበ ውሳኔውን በበላይነት በመቆጣጠርና የተባበሩት መንግሥታት የሚከታተልበትን ሁኔታ በማመቻቸት የግብጽን ፍላጎት ዳር ለማድረስ ተግተዋል። በተለይ የሕዝበ ውሳኔው ሂደት ገለልተኝነትና ግልጽነት የጎደለው በመሆኑ ተቃዋሚ የኤርትራ ቡድኖች የሻዕቢያን ኢ-ፍትሃዊ ድርጊቶች በማጋለጥ አካሄዱን ተቃውመዋል።

የቡትሮስ ጋሊ ቁልፍ ሚናዎች

ቡትሮስ ቡትሮስ-ጋሊ የተባበሩት መንግሥታት የታዛቢዎች ልዑክ (UN Observer Mission- UNOVER) ድምጽ አሰጣጡን ማደራጀትን ጨምሮ ሕዝበ ውሳኔውን እንዲታዘቡ ደብዳቤ በመፃፍ እንዲሰማራ የማድረግ ሚና ተጫውተዋል። በዚህም ሕዝበ ውሳኔው ሕጋዊና ዲፕሎማሲያዊ ሽፋን እንዲያገኝ አድርገዋል። የሕዝበ ውሳኔውን ውጤትም በዓለም አቀፍ ደረጃ ፈጥኖ ዕውቅና በመስጠት ኤርትራ ከኢትዮጵያ እንድትገነጠል

በማድረግ ረገድ የጠላትነት ሚና ተጫውተዋል።

ቡትሮስ ጋሊ በሥልጣን ዘመናቸው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ የታዛቢውን ተልዕኮ በውሳኔ 47/114 በኩል ፈቅደው ሂደቱ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዲያገኝ የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት (UNSC) እንዲያጸደቀው አመቻችተዋል።

ሕዝበ ውሳኔውና የውዝግቡ ዓውድ

ኤርትራን ለማስገንጠል የተደረገው ሕዝበ ውሳኔ በሸፍጥ እና በሴራ የታጀበ እንደመሆኑ መጠን በርከት ያሉ ተቃውሞዎችን አስተናግዷል። ሂደቱ ላይ ተቃውሞ ካሰሙት መካከል የኤርትራ ነፃነት ግንባር (ELF-RC) ነበር። እነዚህ የኤርትራ አንጃዎች ሕዝበ ውሳኔው የዴሞክራሲ መርሆዎችን እንደጣሰ በመግለጽ ለቡትሮስ ጋሊ የተባበሩት መንግሥታት ጣልቃ ገብነት ፍትሃዊ ጅምር እንዲኖር አጥብቀው አሳስበዋል።

ሌላው የኤርትራን ዕጣ ፈንታ በወሰነው ሕዝበ ውሳኔው ላይ ሰፊና ጠንካራ ተቃውሞ ያሰማው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነበር። በተለይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በሕዝበ ውሳኔው ዋዜማ ከፍተኛ ተቃውሞ በማስነሳት የሂደቱን ኢ-ፍትሃዊነት ዓለም እንዲገነዘበው ጥረት አድርገዋል። ለተቃውሞ አደባባይ የወጡት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሕዝበ ውሳኔው ኢትዮጵያን የሚከፋፍልና ከባሕር በማራቅ ወደብ አልባ የሚያደርጋት በመሆኑ ጉዳዩ ዳግም እንዲጤን ጩኸታቸውን አሰምተዋል። ዳሩ ምን ያደርጋል ይህን ትውልድ ተሻጋሪ አገራዊ ጥያቄ ላነሱት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከወቅቱ ህወሐት መራሹ መንግሥት የተሰጠው ምላሽ በአፈሙዝ ማፈን



16

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

ነበር። ድርጊቱ አሳዛኝ ብቻ ሳይሆን ታሪክ ይቅር የማይለው ወንጀል ጭምር ሆኖ ተመዝግቧል።

ይህን አጋጣሚ የተጠቀሙት ቡትሮስ ጋሊ ኢትዮጵያን ለማዳከም ከግብጽ የተሰጣቸውን ተልዕኮ ለማሳካት የኤርትራን መገንጠል የሚያፋጥኑ ሥራዎችን በመሥራት የተባበሩት መንግሥታትን ገለልተኛነት ያጠለሸ ተግባር ፈጽመዋል።

ቡትሮስ ጋሊ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሥልጣን ዘመናቸው የኤርትራን መገንጠል አረጋግጠዋል። ሂደቱ አሁን ድረስ በፍትሃዊነት እና በዓለም አቀፍ የፖለቲካ ተጽዕኖ ዙሪያ አወዛጋቢ ሆኖ ቀጥሏል። በመጨረሻም የግብጽን የዘመናት ኢትዮጵያን የማዳከም በተለይም ከቀይ ባሕር የማራቅ ህልም በማሳካት የሴራ ውለታ ሰርተዋል፤ ኢትዮጵያ ላይ ደግሞ ደባ ፈጽመዋል።

አሁንም ቢሆን እነዚህ ኃይሎች ኢትዮጵያ ዳግም ወደ ቀይ ባሕር እንዳትመለስ ለማድረግ ሴራ መሸረባቸውን ገፍተውበታል። በግብጽ ፊታውራሪነት እ.አ.አ በ2020 የተመሰረተው የቀይ ባሕር ምክር ቤት (The Red Sea Council) የቀይ ባሕር እና የኤደን ባሕረ ሰላጤ አዋሳኝ አገራት ኅብረት የዚሁ ተቀጥላነት ማሳያ ነው። በቀይ ባሕር ትብብር፣ ሠላምና ደህንነት ማስፈን የሚል ካባ የደረበው የኅብረቱ እውነተኛ ዓላማ ግን ኢትዮጵያን በማግለል ጂኦፖሊቲካዊ ውጥረትን አባብሷል።

በቀይ ባሕር ፀጥታና ደህንነት ዙሪያ ኢትዮጵያን ያገለለ ኅብረት ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ከጂኦፖለቲካዊ ስትራቴጂ አኳያ ስኬታማ እንደማይሆን የፖለቲካ ተንታኞች ይስማማሉ።

እንዲያም ሆኖ ግብጽ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ስኬት ያደረባትን የመሸነፍ ስሜት ኢትዮጵያን ከቀይ ባሕር በማግለል ለመበቀል ደፋ ቀና እያለች ትገኛለች።

ይህ አልበቃ ብሏት በኢትዮጵያ ጎረቤት አገራት በመቅበዝበዝ አካባቢው እንዲታመስ መውተርተር ላይ ትገኛለች። ከኤርትራ እስከ ሱዳን፣ ከጅቡቲ እስከ ሶማሊያ ‘አለሁ-አለሁ’ እያለች ነው። የሰሞነኛው የጎረቤት አገር መሪ ከካይሮ እስከ ፖርት ሱዳን እና ሪያድ የተደረገው መወራጨትም ይህን ተልዕኮ ለማስፈጸም የሚደረግ ነው።

የጠፋው ዕድል

ሁለት አገራት - ኢትዮጵያ እና ኤርትራ፤ በደም የተሳሰሩ፣ በመልከዓምድር የተቆራኙ፣ በታሪክ የተጋመዱ ቢሆኑም አሁን ላይ ተንታኞች ቀይ ባሕርን ‘በረከተ-መርገም’ ብለው እስከመጥራት ያደረሰ በጣም ጥልቅ በሆነ ፍጥጫ ውስጥ ተዘፍቀዋል። አለመተማመን የወለደው ፍጥጫ።

ይህ ለዓመታት የዘለቀው አለመተማመን ሁለቱን አገራት በቢሊዮን የሚቆጠር በረከተ-ዶላር ያሳጣ ሲሆን በጋራ የመልማት እና የመበልጸግ ዕድልም ያጨለመ ሆኗል። በእርግጥም ያስቆጫል። ኢትዮጵያ ቀይ ባሕር ያስፈልጋታል፤ በአንፃሩ ኤርትራ የኢትዮጵያ ሰፊ ገበያና ኢኮኖሚ ያስፈልጋታል። መተማመኑ ቢኖር እነዚህ አገራት አንድ ላይ ሆነው በአፍሪካ ቀንድ እጅግ ሳቢ የኢኮኖሚ ኮሪደር መገንባት ይችሉ ነበር። ነገር ግን “በጥባጭ ካለ ማን ንጹህ ይጠጣል” እንዲሉ የአንድ ወገን መሻት ብቻ የሚፈለገውን ስኬት አያመጣም። የኤርትራ መንግሥት ከብልጽግና ይልቅ ጥርጣሬን፤ ከኃብት ይልቅ ሴራንና ጦርነትን መምረጡ ይህን የገዘፈ



17

ዕድል አምክኗል። ይህ ዕድል በአፍሪካ ቀንድ ያመለጠ ፀጋ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።

በአንድ ወደብ ላይ መታመን ስትራቴጂካዊ አደጋ እንዳለው ኢትዮጵያ አበክራ ትገነዘባለች። በተለይ የሕዝብ ቁጥሯ በየጊዜው እያሻቀበ መምጣቱ ከፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገቷ ጋር ተዳምሮ አማራጭ ወደቦችን መጠቀም ግድ እያላት መጥቷል። ይህን ጉዳይ ኤርትራ የራሷ የነበረውን ወደብና ባህር የመጠቀም መብት ያላትን ኢትዮጵያን በመግፋት በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረቱ ውይይቶችና ትብብሮች መፍጠር ተስኗት እነዚህን ፀጋዎች የግጭትና የመናቆር መነሻ በማድረግ የመልማት ዕድሎችን እያመከነች ትገኛለች።

የኤርትራ ፖለቲካዊ ሥነ-ልቦና ጫና

የምክክር፣ የጥናት እና የትብብር ማዕከል (Centre

for Dialogue, Research and Cooperation- CDRC) መቀመጫውን ኢትዮጵያ ያደረገ ለትርፍ ያልተቋቋመ ግን ደግሞ በሕዝብ ፖሊሲ ዙሪያ ጠንካራ ጥናትና የትንተና ሥራን የሚሰራ ገለልተኛ ተቋም ነው። በዚህ ተቋም ተመራማሪ የሆኑት እንድሪያስ አማኑኤል በኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት ዙሪያ ባደረጉት ዳሰሳ የሁለቱ አገራት ትልቁ እንቅፋት መልክዓምድራዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ ሥነ-ልቦና (Political Psychology) ነው ሲሉ ይሞግታሉ።

ኢኮኖሚያዊ አቅሟ አናሳ የሆነችው ኤርትራ እምብዛም የማትጠቀምባቸው ጥልቅ የባሕር ወደቦች አሏት። በአንፃሩ በቀንዱ አገራት ግዙፍ የሆነ ኢኮኖሚና ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ ወደብ አልባ አገር ናት። እናም ቀይ ባሕር ያስፈልጋታል። በሌላ



18

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

በኩል ኤርትራ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ትፈልጋለች።

አንደኛው የሌለውን ሰጥቶ በመቀበል መርህ፤ የጎደለውን መሙላት፤ ተባብሮ መሥራት በንግዱ ዓለምም ሆነ በፖለቲካዊ የተለመደ አሠራር ነው። ነገር ግን ኤርትራ ትብብር ሲባል እጅ የመስጠት ያህል ስትፈራ ይስተዋላል። በሕዝብ ቁጥርም፣ በቆዳ ስፋትም፣ በኢኮኖሚም የገዘፈችው ኢትዮጵያ በኤርትራ ዓይን ከትብብር ይልቅ በሥጋትነት ትታያለች። ይህ የተንሸዋረረ የኤርትራ ዕይታ የሁለቱን አገራት ትብብር ለዘመናት ረጅም ርቀት እንዳይሄድ ጋሬጣ ሆኖ ቀጥሏል።

ይህ ሁኔታ ድንበሩን ይዘጋል። ወደቦችን ያቀዘቅዛል። ቀጣናዊ ዲፕሎማሲን ሽባ ያደርጋል። ሁለቱንም አገሮች ለባሕረ ሰላጤ እና ለውጭ ተጽዕኖ ተጋላጭ ያደርጋቸዋል። ይህም በቀይ ባሕር በረከት ላይ የጋራ ልማትና ብልጽግና ለማረጋገጥ የተፈጠረውን ዕድል እንደተዳፈነ እንዲቀር የሚያደርግ ሆኗል።

በነገራችን ላይ ፖለቲካዊ ሥነ-ልቦና የፖለቲካ ባህሪን፣ የውሳኔ አሰጣጥን እና ሥርዓቶችን ለመረዳት የሥነ-ልቦና ንድፈ ሐሳቦችን እና ዘዴዎችን የሚተገብር ሁለገብ የአካዳሚክ መስክ ነው። በግለሰቦች የሥነ-ልቦና ሂደቶች እና በሚኖሩባቸው የፖለቲካ ሁኔታዎች መካከል ያለውን ውስብስብ እና ባለሁለት አቅጣጫ ግንኙነት ይዳስሳል።

በአጭሩ የፖለቲካ ሳይኮሎጂ በሥነ-ልቦና እና በፖለቲካዊ ሂደቶች መካከል ያለውን ግንኙነት ለመተንተን የሚያስችል ሳይንስ ነው። የአመራር ትንተና በመስኩ የመሪዎችን የውሳኔ አሰጣጥ ዘይቤዎች፣ የባህሪ (ለምሣሌ፣ ተቀባይነት- Charisma፣ አምባገነናዊነት፣ ስሜታዊ እና ብልህነት) እንዲሁም እነዚህ ምክንያቶች

አስተዳደርን፣ የፖሊሲ ፈጠራን እና ዓለም አቀፍ ግንኙነቶችን እንዴት እንደሚነኩ የሥነ-ልቦና መሰረት ይመረምራል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ የተዛባ አመለካከት በመያዝ ትልቅ እንቅፋት እየፈጠሩ ያሉት የኤርትራው መሪ እንደሆኑ የፖለቲካ-ኢኮኖሚ ተንታኞች ደጋግመው የገለጹት ጉዳይ ነው። ሰውዬው የተጠናወታቸው እኩይ የመጠራጠር ባህሪይ በፖለቲካዊ ሥነ- ልቦናቸው ውቅራት ላይ አሉታዊ ባህሪይን ያሳደረ ሆኗል።

ይህን መሰሉ የኤርትራ ሥጋት ከተንሻፈፈ ፖለቲካዊ ሥነ-ልቦና የሚመነጭ እንደሆነ ነው የመስኩ ምሁራን የሚገልጹት። የምክክር፣ የጥናት እና የትብብር ማዕከል ተመራማሪው እንድሪያስም ይህንን ይጋሩታል። እንዲህ ዓይነቱ ቅጥ ያጣ አለመተማመን ትልቁ እንቅፋት ፖለቲካዊ ሥነ- ልቦና የሚፈጥረው እንጂ መልክዓምድራዊ አሊያም ኢኮኖሚያዊ ግዝፈት እንዳልሆነ ይሞግታሉ።

የስብዕና ንድፈ ሀሳቦች በሲግመንድ ፍሮይድ እና በሀሮልድ ላስዌል (የፖለቲካ ሳይንቲስት) የተዘጋጁ ሥራዎች የስብዕና ባህሪያትን ከፖለቲካዊ ዓላማዎች እና ባህሪያት ጋር ለማገናኘት የሥነ- ልቦና ትንታኔ አቀራረቦችን ተጠቅመዋል። ከዚህ ሳይንሳዊ አመክንዮ አኳያ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ፖለቲካዊ ሥነ-ልቦና ውቅራት ማየቱ ይጠቅማል። የሰውየው የስብዕና ባህሪያት ከፖለቲካዊ ዓላማቸው እና ባህሪያት ጋር ተገናዝቦ ሲታይ ኢትዮጵያን አስመልክቶ ኤርትራ ያላት የጥርጣሬ መንፈስ ምንጩ ከእርሳቸው ፖለቲካዊ ሥነ-ልቦና ውቅር እንደሚነሳ የሚያሳይ ነው።

ዓለም አቀፍ የፖለቲካዊ ሥነ-ልቦና ማኅበር (ISPP)



19

የኢሳያስ አፈወርቂን ፖለቲካዊ ሥነ-ልቦና በተጋነነ ለራስ የሚሰጥ ግምት ባህሪያት (Narcissism)፣ ሌሎች ሰዎች ጉዳት እያሴሩ ነው በሚል ያልተገባ ጥርጣሬ (Paranoia) እና በፅንፈኝነት እና በርዕዮተ ዓለም ላይ የተመሰረተ የዓለም እይታን በማንሻፈፍ እንደሚታወቅ ይገልፃል። ኢሳያስ ለውጭ ኃይሎች ከፍተኛ ጥርጣሬ ያላቸው ሲሆኑ የግድያ ዒላማ እንደሆኑ በማመን እና ቁጥጥርን ለማስቀጠል “መከፋፈል እና መቆጣጠር” የሚል ስትራቴጂ ይጠቀማሉ።

የሚገርመው ኤርትራና የኤርትራ ሕዝብ በዚህ የተሳከረ ፖለቲካዊ ሥነ-ልቦና ምክንያት ጭቆና እና በደል ደርሶበት ለጦርነት፤ ከጦርነት ካመለጠም ለስደት መዳረግ ከጀመረ እነሆ ከሦስት አሥርት ዓመታት በላይ ሆኖታል። ከኤርትራ ባሻገር እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የጎረቤት አገራት የዚህ የስብዕና ቀውስ ሰለባ በመሆን ጂኦፖለቲካዊ ዕድሎችን ለልማትና ብልጽግና እንዳያውሉ አድርጓቸዋል። አሁን ላይ ታረክን የመቀየር ጊዜው የደረሰ ይመስላል። ታሪክ ቀያሪውም የአሁኑ ትውልድ ነው። በሴራ የጠለሸን የጂኦፖለቲካ ታሪክ ለመቀየር ትውልዱ ሆ ብሎ ተነስቷል።

ይህን ፅሁፍ እያዘጋጀሁ በነበረበት ጊዜ ለዕረፍት ያህል የሞባይል ስልኬን ስነካካ በአንድ የማኅበራዊ ገጽ ላይ የተለቀቀ አጭር ሪልስ ቀልቤን ገዛው። ደጋግሜ ተመለከትኩት። አንድ ነጭ የውጭ አገር ዜጋ በአስመራ ከተማ በርከት ላሉ ኤርትራዊያን አንድ ጥያቄ አነሳላቸው። ኢትዮጵያዊ መሆን ትፈልጋላችህ? የሚል ጥያቄ። የተጠያቂዎቹ ምላሽ ፍጹም የሚገርምና የጠያቂውን ቅንድብ በአግራሞት ከፍ ያደረገ ነበር። ከአንድ በዕድሜ

ገፋ ካሉ ሴት ተጠያቂ በስተቀር ሁሉም ኢትዮጵያዊ መሆን ምርጫቸው እንደሆነ በጋለ ስሜት ሲገልጹ ይታያሉ።

ከኮስማና የኢሳያስ ፖለቲካዊ ሥነ-ልቦና በሚመነጭ ተጠራጣሪነት ምክንያት በብዙ ነገሮች ለተሳሰሩ ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን የተፈጠሩ መልካም ዕድሎች ለጊዜውም ቢሆን ቢዳፈኑም መፋቅ ግን አይቻልም። በጋራ የሚበለጽጉበትን ሂደት እንደሚፈጥሩ ተጠያቂዎቹ የሰጡት ምላሽ ማሳያ ነው። ይህ ምኞት ብቻ ሳይሆን እውነታ ጭምር ነው። ጊዜ ይወሰድ ይሆናል እንጂ እውን መሆኑ አይቀሬ ነው።

ኢትዮጵያ ወደ ባሕር በር የመመለስ ፍላጎቷ የሚመነጨው ከባሕር በር ባለቤትነቷና ከቀይ ባሕር ጋር ባላት ጥልቅ ታሪካዊ ትስስር እና ሕጋዊ መብት መሆኑን መገንዘብ ይገባል። እ.አ.አ በ1993 ኢትዮጵያ የባሕር በሯን ህጋዊ ባልሆነ መንገድና በሴራ ካጣች በኋላ የባሕር በርን እንደገና ለማግኘት ዓለም አቀፍ ድጋፍ መሻቷ ተገቢ ነው። ይህ ጥረት የባሕር በር የሌላቸው አገራት መብቶቻቸውን ለማስጠበቅ የሚጠቀሙባቸውን ታሪካዊ የይገባኛል ጥያቄዎች እና የህግ ማዕቀፎችን ተገቢነትም ያሳያል። የኢትዮጵያ ጥያቄም ይኸው ነው። እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገራት የባሕር መዳረሻን መልሶ ማግኘት የሎጂስቲክስ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የብሔራዊ ማንነታቸው እና የኢኮኖሚ ዕድገታቸው ጉልህ አካል ጭምር በመሆኑ።



20

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

ኢኮኖሚ

ኢንቨስትመንት ባንክ



21

-የኢኮኖሚ ማሻሻያው ገፀ በረከት

አገራዊ ጠቀሜታቸው ጉልህ ሆኖ ሳለ ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጭ አገር ዜጎች ተሳታፊነት ክልከላ ከተደረገባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ ሆኖ ቆይቷል - ስቶክ ማርኬት። ምንም እንኳን ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከሰሃራ በታች ከቀዳሚዎቹ የሚመደብ ምጣኔ ሀብትና የሕዝብ ብዛት ቢኖራትም፤ ስቶክ ማርኬት ከሌላቸው ጥቂት አገራት አንዷ ሆና ቆይታለች። በአፍሪካ 38 አገራት የስቶክ ማርኬት ተጠቃሚዎች ሲሆኑ እነዚህ አገራት የሚገበያዩባቸው 28 ስቶክ ማርኬቶች መኖራቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ።

ስቶክ ማርኬት በአንድ አገር ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል እውን ከማድረግና አማራጭ የፋይናንስ አቅርቦት ከማስፋት አንፃር

በመንገሻ ገ/ሚካኤል



22

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

እንዲሁም አገራዊ ሰላምና ተስፋን ከማሳደግ አኳያ ትልቅ ሚና ቢኖረውም እስከአሁን ተግባራዊ ሳይደረግ የቆየው ከፖለቲካዊ ቁርጠኝነት አለመኖር ጋር በተያያዘ እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል።

ባለፉት ስምንት ዓመታት እየተካሄደ ካለው የኢኮኖሚ ሪፎርም ጋር በተያያዘ መንግሥት የአገሪቷን ምጣኔ ሀብት ለዓለም አቀፍ ውድድር ክፍት ማድረጉና በርካታ የማሻሻያ እርምጃዎችን መውሰዱን ተከትሎ የሰነደ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ተጀምሯል። መንግሥት በኢትዮጵያ ብዝኃ ዘርፍ ተዋንያንን ማስተናገድ የሚያስችል ኢኮኖሚ ለመገንባት በርካታ ማሻሻያዎች ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል። የዚህ ውጤት አንዱ ማሳያ ኢኮኖሚውን ማገዝ የሚችል የሰነደ መዋዕለ ንዋዮች ገበያ መጀመሩ ነው። ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው የሰነደ መዋዕለ ንዋዮች ገበያ ሥራ መጀመር በአብዛኛው የዘርፉ ባለሙያዎች አድናቆት የተቸረው ሲሆን ባንኮች ሊደርሱለት አልቻለም

የተባለውን የፋይናንስ አቅርቦት ችግር በመፍታት የምጣኔ ሀብት ዕድገቱን ያፋጥናል ተብሎም ተስፋ ተጥሎበታል።

ገበያውን እንዲመራ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ሥራውን ለማስጀመር የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች ፍቃድ ሰጥቷል። ይህን ተከትሎም አገልግሎት ሰጪ የኢንቨስትመንት ባንኮች ተቋቁመዋል። በዚህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ንግድ ባንኮች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ እንዳይሰማሩ የሚያግደውን የ2009 ዓ.ም መመሪያ ሽሯል። ሐምሌ 12 ቀን 2016 ዓ.ም ሌላ መመሪያ በማዘጋጀት ባንኮች በተለያዩ ዘርፎች ላይ እንዲሰማሩ ይሁንታውን ሰጥቷል። መመሪያው ንግድ ባንኮች ከብድር ደረጃ አውጭነት ውጭ ባሉ እንደ ኢንቨስትመንት ባንክ ባሉ የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪ ኩባንያዎች ውስጥ ሙሉ ድርሻ ኖሯቸው በባለቤትነት እንዲይዙም ፈቅዷል።

ይህም በካፒታል ገበያ አዋጁ መሰረት የሚፈጸም ሲሆን ባለሥልጣኑ በካፒታል ገበያ አዋጅ ቁጥር 1248/2013 እና አዋጁን



23

ተከትሎ በወጣው የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች ፈቃድ አሰጣጥ እና ቁጥጥር መመሪያ 980/2016 በተቀመጡ ዝርዝር ቅድመ ሁኔታዎች መሰረት ለአራት የኢንቨስትመንት ባንኮች ፈቃድ ሰጥቷል።

የኢንቨስትመንት ባንኮች ለምን?

የኢንቨስትመንት ባንኮች በዓለም አቀፍ ፋይናንስ ውስጥ ቁልፍ ሚና እየተጫወቱ ሲሆን ለግለሰቦች፣ ለድርጅቶች፣ ለመንግሥት እና ለሌሎች ትልልቅ ተቋማት ምክርና የፋይናንስ አገልግሎት በመስጠት ላይ የተመሰረቱ የፋይናንስ ተቋማት ናቸው። ተቀማጭ ገንዘብ በመቀበል ብድር ከሚሰጡ ንግድ ባንኮች የሚለያቸው የኢንቨስትመንት ባንኮች ደንበኞች ካፒታል እንዲያሳድጉ፣ ኢንቨስትመንቶችን እንዲያስተዳድሩ እና ውስብስብ የፋይናንስ ጉዳዮችን እንዲያሳኩ በማድረግ ላይ ያተኩራሉ። በዚህም ግለሰቦች፣ ባለሀብቶች እና ድርጅቶች የፋይናንስ ብሎም የካፒታል አቅማቸውን ለማሳደግ ኢንቨስትመንት ባንኮችን ቀዳሚ ምርጫቸው ያደርጋሉ።

የኢንቨስትመንት ባንክ ተቀዳሚ ግቦች ባለሃብቶችና ድርጅቶች የፋይናንስ ፈተናዎቻቸውን እንዴት መወጣት እንደሚችሉ የምክር አገልግሎት መስጠት፤ ደንበኞቻቸውን በፋይናንስ፣ በምርምር፣ በንግድ እንዲሁም በሽያጭ፣ በሀብት እና በንብረት አስተዳደር ዙሪያ ማማከር ናቸው። በአጠቃላይ ኢንቨስትመንት ባንኮች በትልልቅ ኢንተርፕራይዞች እና ባለሀብቶች መካከል ድልድይ በመሆን ያገለግላሉ። ኢንቨስተሮችን ከገንዘብ ጋር ያገናኛሉ። ኢንቨስት የሚደረግበትን ድርጅት ገበያውን ያጠናሉ።

የኢንቨስትመንት ባንኮች ከመደበኛ (Conventional) የባንክ አገልግሎት በእጅጉ የተለየና ውስብስብ የፋይናንስ ምህንድስናን (Financial Engineering) የሚጠይቅ ነው። ኢንቨስትመንት ባንኮች የካፒታል ገበያን በማሳለጥ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወቱ የሚገልጹት በካፒታል ገበያ ባለሥልጣን የፈቃድ እና ምዝገባ ዳይሬክቶሬት ኃላፊ አቶ እድሪስ ሰልማን የኢንቨስትመንት ባንኮች አምስት ዋና ዋና ተግባራት እንዳሏቸው ይገልጻሉ።

የሰነደ መዋዕለ ንዋይ ደላላ እና ገበያ አከናዋኝ

ኢንቨስትመንት ባንኮች የሰነደ መዋዕለንዋይ ደላላ (Broker) በመሆን ከደንበኞቻቸው የሰነደ መዋዕለንዋዮችን የግዢ ወይም የሽያጭ ትዕዛዞች በመቀበል ግብይቱን ያስፈጽማሉ። በተጨማሪም ገበያ አከናዋኝ (Dealer) በመሆን የሰነደ መዋዕለ ንዋዮችን በራሳቸው ስም መግዛት ወይም መሸጥ ይችላሉ።

የካፒታል ማሰባሰብ (Capital Raising)

ኩባንያዎች እና መንግሥት አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለመጀመር ወይም ለማስፋፋት የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ አክሲዮኖችን (Shares) ወይም የብድር ሰነዶችን (Bonds) ለሕዝብ በመሸጥ እንዲያሰባስቡ ይረዳሉ። እንዲሁም የሰነደ መዋዕለ ንዋይ አውጪዎች (Issuers) እና ኢንቨስት በሚያደርገው ሕዝብ መካከል አገናኝ ድልድይ በመሆን ይሠራሉ።

የምክር አገልግሎት (Advisory Services)

የሰነደ መዋዕለ ንዋይ ኢንቨስትመንትን በተመለከተ ለተቋማት እና ግለሰብ ደንበኞቻቸው የምክር አገልግሎት ይሰጣሉ። በተለይም የሰነደ መዋዕለ ንዋዮቻቸውን ለባልሥልጣኑ የሚያስመዝግቡ



24

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

አክሲዮን ማኅበራትን እንዲሁም ለመጀመሪያ ጊዜ የሚደረግ የሕዝብ ሽያጭ (Initial Public Offering) በግል እና በመንግሥት የልማት ድርጀቶች የሚቀርቡ አክሲዮኖች ወይም የብድር ሰነዶችን የግብይት አማካሪ (Transaction Advisor) በመሆን የደንበኛ ሳቢ መግለጫን (Prospectus) የማዘጋጀት አገልግሎት ይሰጣሉ። ኩባንያዎች እርስ በእርስ ሲዋሃዱ (Mergers) ወይም አንዱ ኩባንያ ሌላውን ሲገዛ (Acquisitions) ሂደቱን በበላይነት ይመራሉ፤ የገበያ ጥናት እና የፋይናንስ ምክርም ይሰጣሉ።

የኮርፖሬት መልሶ ማዋቀር (Corporate Restructuring)

አንድ ድርጅት በዕዳ ሲዘፈቅ ወይም ትርፋማነቱ ሲቀንስ፣ የኢንቨስትመንት ባንኮች የድርጅቱን ንብረት በመሸጥ ወይም የዕዳ አወቃቀሩን በመቀየር ድርጅቱ ከኪሳራ የሚድንበትን መንገድ ያማክራሉ።

የውክልና ሽያጭ (Underwriting)

ኢንቨስትመንት ባንኮች በሁለት መንገዶች የውክልና ሽያጭ ሊያከናውኑ ይችላሉ። የመጀመሪያው የጥብቅ ስምምነት ውክልና ሽያጭ (Firm Commitment Underwriting) በመባል የሚታወቀው ነው። የኢንቨስትመንት ባንኩ (Underwriter) በአንዴና በሙሉ የሚሸጡትን አክሲዮኖች ወይም ቦንዶች በሙሉ ከኩባንያው ይገዛል። ገበያ ላይ ለሕዝብ ከመቅረቡ በፊት የገንዘብ ኃላፊነቱን በራሱ ላይ ይጥላል። በዚህም አውጪው (Issuer) የሚፈልገውን ካፒታል በሙሉ በቅድሚያ ማግኘቱን ያረጋግጣል። አክሲዮኖች ወይም ቦንዶቹ በገበያ ላይ ቢሸጡም ባይሸጡም

አውጪው (Issuer) ኃላፊነት አይወስድም። የሽያጭ ስጋቱን ሙሉ በሙሉ የሚሸከመው የኢንቨስትመንት ባንኩ ነው። ባንኩ ከገዛው በኋላ ለሕዝብ መሸጥ ካልቻለ ያልተሸጠውን አክሲዮን በራሱ መያዝ ወይም በኪሳራ መሸጥ ይኖርበታል።

ሁለተኛው የውክልና ሽያጭ መንገድ የተቻለውን ያህል የመሸጥ ስምምነት (Best Efforts Underwriting) ነው። የኢንቨስትመንት ባንኩ አክሲዮኑን ለመግዛት ቃል አይገባም። ይልቁንም በተሰጠው ጊዜ ውስጥ የተቻለውን ያህል አክሲዮን ለመሸጥ ብቻ ጥረት ያደርጋል። የዚህ ፋይዳ አክሲዮኑ ለሕዝብ ሲሸጥ ብቻ ኮሚሽን ያገኛል። ይህ ስምምነት ባንኩን ከሽያጭ ስጋት ነጻ የሚያደርገው ነው። ዋናው ስጋት የሚወድቀው በአውጪው (Issuer) ላይ ይሆናል። ባንኩ የሚፈለገውን ያህል አክሲዮን መሸጥ ካልቻለ ኩባንያው የሚፈልገውን ሙሉ ካፒታል ላያገኝ ይችላል። በአብዛኛው፣ የተወሰነ ዝቅተኛ የሽያጭ መጠን (Minimum Subscription) ካልተሳካ፣ ሽያጩ ሙሉ በሙሉ ይሰረዛል።

ከንግድ ባንኮች በምን ይለያሉ?

የኢንቨስትመንት ባንኮች እና የንግድ ባንኮች በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ የሚጫወቱት ሚና እና የአሠራር ሞዴል በመሰረታዊነት ይለያያል። የንግድ ባንኮች በዋናነት ገንዘብ በማስቀመጥ እና በማበደር ላይ ያተኮሩ ሲሆኑ፤ የኢንቨስትመንት ባንኮች ደግሞ ገንዘብ በማንቀሳቀስ እና በማሰባሰብ የሰነደ መዋዕለ ንዋይ አውጭዎችን ከባለሃብቶች ጋር በማገናኘት ላይ ትኩረት ያደርጋሉ።

የንግድ ባንኮች ዋና የገንዘብ ምንጭ ከሕዝብ የሚሰበሰበው ተቀማጭ ገንዘብ (Deposits)



25

ነው። በዚህም ምክንያት ዋና አገልግሎታቸው ብድር መስጠት፣ የግል ሂሳቦችን ማስተዳደር እና የክፍያ ሥርዓቶችን ማቀናጀት ነው። የኢንቨስትመንት ባንኮች ግን ተቀማጭ ገንዘብ አይሰበስቡም (non- deposit taking) ናቸው። ይልቁንም ለድርጅቶች የሚያስፈልገውን የረጅም ጊዜ ካፒታል በዋነኛነት የአክሲዮኖች እና ቦንዶች ሽያጮችን ከማማከር ጀምሮ ግብይቱን እስከማስፈፀም (Execute) አውጪዎችን ከኢንቬስተሩ ጋር የማገናኝት ሥራ የሚያከናውኑ ናቸው። ዋና አገልግሎታቸውም የኩባንያዎች ውህደት እና ግዢ፣ የፋይናንስ ምክር እና ካፒታል ማሰባሰብ ነው።

የንግድ ባንኮች ዋና የገቢ ምንጭ ወለድ ነው። ተቀማጭ ገንዘብ በአነስተኛ ወለድ ተቀብለው በከፍተኛ ወለድ ብድር ይሰጣሉ፤ በዚህም በተቀማጭና በአበዳሪ ወለድ መካከል ያለውን ልዩነት ትርፋቸው

ያደርጋሉ። የኢንቨስትመንት ባንኮች በዋናነት የሚያገኙት ገቢ የኮሚሽን እና የአገልግሎት ክፍያ ሲሆን ይህም ከካፒታል ማሰባሰብ፣ ከምክር አገልግሎት እና ግብይት ከማስፈፀም (Trade Execution) የሚመጣ ነው። የንግድ ባንኮች በብሔራዊ ባንክ ፍቃድ የሚሰጣቸው እና ቁጥጥር የሚደረግባቸው ተቋማት ሲሆኑ፤ የኢንቨስትመንት ባንኮች ፍቃድ የሚሰጣቸው እና ቁጥጥር የሚደረግባቸው በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ነው።

የኢንቨስትመንት ባንኮች አገራዊ ጠቀሜታ

የኢንቨስትመንት ባንኮች መኖር ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከነባሩ የባንክ ሥርዓት ውጭ አዲስ የፋይናንስ አማራጭ በመክፈት ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ አላቸው። የመጀመሪያው ጠቀሜታቸው የፋይናንስ ድልድይ (Financial Intermediation) ሆነው የሚያገለግሉ መሆናቸው ነው። በካፒታል ገበያ ባለሥልጣን የፈቃድ እና ምዝገባ ዳይሬክቶሬት ኃላፊ አቶ እድሪስ ሰልማን እንደሚሉት የኢንቨስትመንት ባንኮች በዋናነት ገንዘባቸውን ለረጅም ጊዜ ኢንቨስት ለማድረግ



26

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

በሚፈልጉ ግለሰብ ባለሀብቶች (Retail Investors) እንዲሁም ተቋማዊ ኢንቨስተሮች (Institutional Investors) እና ካፒታል የሚያስፈልጋቸው አውጪዎች (Issuers) መካከል አስተማማኝ ድልድይ ሆነው ያገለግላሉ። ኢንቨስትመንት ባንኮች የካፒታል ፍሰት (Capital Flow) እንዲኖር በማድረግም የላቀ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ። ገንዘብ በባህላዊ የቁጠባ ሂሳቦች ውስጥ ተዘግቶ ከመቀመጥ ይልቅ፣ ወደ ምርትና አገልግሎት ዘርፎች በሚገቡ አክሲዮኖች እና ቦንዶች ውስጥ ፈሰስ እንዲደረግ ያደርጋሉ። ይህ የካፒታል ፍሰት የኢኮኖሚውን ፍጥነት (Velocity of Money) ያሳድገዋል።

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ባንኮች መከፈት በካፒታል እጥረት ምክንያት ወደ ሥራ ያልገቡ የንግድ ሃሳቦች እውን እንዲሆኑ ያስችላል። የንግድ ባንኮች ለበርካታ አዳዲስ እና ፈጠራ ላላቸው የንግድ ሀሳቦች ከፍተኛ ስጋት ስላላቸው ብድር ለመስጠት ይቸገራሉ የሚሉት አቶ እድሪስ፤ የኢንቨስትመንት ባንኮች ግን ለሕዝብ ከማቅረብ ባለፈ በግል ሽያጭ (Private

Placement) በሕጉ ከተፈቀደላቸው ባለሃብቶች ጋር በማገናኘት ለፈጣን ዕድገት የሚያስፈልገውን ፋይናንስ እንዲያገኙ ያስችላሉ። በዚህም የንግድ ሀሳብ ኖሯቸው በካፒታል እጥረት ምክንያት ሃሳቦቻቸውን ተግባራዊ ማድረግ ላልቻሉ ተቋማት እና ግለሰቦች ትልቅ ዕድል ይዘው መጥተዋል።

የኢንቨስትመንት ባንኮች የፕሮጀክት ልማትን በመደገፍም ትልቅ ሚና ይጫወታሉ። አንድ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክት ሲታሰብ፣ የኢንቨስትመንት ባንኮች ፋይናንሱን ከብዙ ምንጮች በማጣመር (ለምሣሌ፡ ከቦንድ ገበያ እና ከአክሲዮን ገበያ) ሀሳቡ እውን እንዲሆን ያስችላሉ። ኢንቨስትመንት ባንኮች በአንድ አገር ሁሉን አቀፍ ዕድገት እንዲመጣ የራሳቸው አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።

የኢንቨስትመንት ባንኮች በአንድ አገር ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል (Equitable Wealth Distribution) እንዲኖር በማድረግ የባለቤትነት መብት እንዲስፋፋ ያደርጋሉ። ቀደም ሲል በአገራችን ትላልቅ እና ትርፋማ ኩባንያዎች ባለቤትነት በጥቂት መስራች ግለሰቦች ወይም



27

አካውንት ለመክፈት ስትራቴጂ ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ይህም በብዙ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን በስቶክ ማርኬት እንዲሳተፉ ያደርጋል ሲሉ አክለዋል።

እንደ አገር ያሉን 30 የንግድ ባንኮች አጠቃላይ ያላቸው የአክሲዮን ባለድርሻዎች ብዛት 400 ሺህ ብቻ ነው። የኢንቨስትመንት ባንኮቹ ወደ ሥራ መግባት የእነዚህን ተቋማት የድርሻ መጠን ያሳድጋል፡። በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች እንደየአቅማቸው የፋይናንስ ተቋማት ድርሻ ለመግዛት የሚያስችላቸው ነው። በአጠቃላይ የኢንቨስትመንት ባንኮች የገቢ ልዩነትን በመቀነስ፣ ኅብረተሰቡ በጋራ የኢኮኖሚው ተጠቃሚ እንዲሆንና በፍትሃዊ መንገድ ሀብት እንዲያፈራ ሰፊ ዕድል ይፈጥራል።

በተጨማሪም የኢንቨስትመንት ባንኮች የንግድ ባንኮችን ጨምሮ የተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት አክሲዮን ለመግዛት ከዚህ ቀደም የነበሩትን አሠራሮች በማሻሻል በዋናነት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ባለድርሻ የሚሆኑበትን

አሠራር ያሰፋሉ።

ኢንቨስትመንት ባንኮች አማራጭ የገንዘብ ምንጭ በማቅረብ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች (SMEs) ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበርክቱ አቶ እድሪስ ይገልጻሉ። አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ለአገሪቷ የሥራ ዕድል ፈጠራ ወሳኝ ቢሆኑም፤ ከንግድ ባንኮች ብድር ለማግኘት የሚከብዳቸው የዋስትና (Collateral) እጥረት አለባቸው። የኢንቨስትመንት ባንኮች ከብድር ውጭ በሆነ መንገድ (ለምሣሌ በዕዳ ሰነዶች ወይም በአክሲዮን ሽያጭ) የፋይናንስ አማራጮችን ስለሚያመቻቹላቸው አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ለፈጣን ዕድገት የሚያስፈልገውን ካፒታል እንዲያገኙ ያግዛሉ።

የአንድ አገር ኢኮኖሚ ጤናማ ዕድገት እንዲኖረው ከሚያደርጉ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ስታርትአፖች፣ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ሚና የላቀ ነው። ለእነዚህ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች መጎልበት የጀርባ አጥንት ሆነው የሚነሱት ደግሞ የኢንቨስትመንት ባንኮች

ቤተሰቦች ላይ ብቻ የተገደበ ነው። የኢንቨስትመንት ባንኮች እነዚህ ኩባንያዎች አክሲዮናቸውን ለሕዝብ እንዲያቀርቡ በማገዝ፣ ማንኛውም ዜጋ በትንሽ ገንዘብ እንኳ ቢሆን በትላልቅ እና ትርፋማ ድርጅቶች ውስጥ የባለቤትነት ድርሻ ማግኝት የሚችልበትን ዕድል ያመቻቻሉ።

በኢትዮጵያ ፍቃድ አግኝተው በቅርቡ ወደ ሥራ ከገቡ የኢንቨስትመንት ባንኮች መካከል አንዱ የሆነውና የ70 በመቶ ድርሻው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሆነውን የሲቢኢ ካፒታል አክሲዮን ኢንቨስትመንት ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ “ኢንቨስትመንት ባንኮች ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር የሚያስችሉ ናቸው“ ሲሉ ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሀብት እየተፈጠረ እንደሆነ የገለፁት አቶ ዘመዴነህ ይህን ሀብት ሕዝቡ እኔም ይመለከተኛል እንዲል ማድረግ የሚቻለው በካፒታል ገበያ በኢንቨስትመንት ባንኮች አማካኝነት ነው። ሲቢኢ ካፒታል በሚቀጥሉት ሁለት ሦስት ዓመታት ውስጥ ወደ 5 ሚሊዮን የሚደርስ የኢንቨስትመንት



28

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

ናቸው። የኢንቨስትመንት ባንኮች ስታርትአፖች እና አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እንዲያድጉ ይደግፏቸዋል።

የኢንቨስትመንት ባንኮች ለስታርትአፖች፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ከሚሰጡት ጉልህ ጥቅሞች መካከል ካፒታል የማሰባሰብ፣ የማማከር አገልግሎት፤ የፋይናንስ ብድሮችን በማመቻቸት ድርጅቶች ለሚሰጡት አገልግሎት የገበያ ዋጋ የማውጣት እና የመተመን፣ የገበያ ሰንሰለት የመፍጠር፤ የአደጋ ቅነሳ አስተዳደር፣ በችግሮች ጊዜ የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ መስጠት ይጠቀሳሉ።

ኢንቨስትመንት ባንኮች አገራዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን (National Economic Growth) ይደግፋሉ። እንደ አቶ እድሪስ ገለፃ፤ የኢንቨስትመንት ባንኮች የሚያሰባስቡት ካፒታል የረጅም ጊዜ ኢንቨስትመንቶችን (Long-Term Investments) የሚደግፍ ነው። ይህ ደግሞ ፋብሪካዎችን ማስፋፋት፣ መሠረተ ልማቶችን ማዘመን እና ምርታማነትን ማሳደግ ስለሚያስችል፣ የአገሪቷን አጠቃላይ ብሔራዊ ምርት ዕድገት በቀጥታ ይደግፋል። እንዲሁም የፋይናንስ ዲሲፕሊን (Financial Discipline) እንዲኖር ለማድረግ ለካፒታል ገበያው ገንዘብ ለማሰባሰብ የሚፈልጉ ኩባንያዎች ግልጽ እና ትክክለኛ የፋይናንስ ሪፖርት የማቅረብ ግዴታ አለባቸው። ይህም በአገሪቷ ያለው የኮርፖሬት አስተዳደር (Corporate Governance) እና የፋይናንስ ዲስፕሊን እንዲሻሻል ያስገድዳል።

በአንድ አገር ተዓማኒነት ያለው ገበያ መፍጠር የሚያስችሉት ኢንቨስትመንት ባንኮች፤ ሙያዊ

አስተዳደር በመዘርጋት በካፒታል ገበያው ሕጎች እና ደንቦች መሰረት ሙያዊ አገልግሎት በመስጠት ይሰራሉ። ይህ ደግሞ በገበያው ላይ የሚደረጉ ግብይቶች ግልጽና ፍትሃዊ መሆናቸውን ያረጋግጣል። እንዲሁም ኢንቨስትመንት ባንኮች የኢንቬስተሮች ጥበቃ ሆነው ስለሚያገልግሉ ባለሃብቶች የሚያደርጉት ኢንቨስትመንት በእውቀት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን የሚያስችል ዝርዝር የሆኑ የደንበኛ ሳቢ መግለጫን ጨምሮ ሌሎች ኃላፊነትን የሚያስከትሉ ይፋ የማድረጊያ ግዴታዎች (dislcosure obligations) በሕዝብ ኩባንያዎች ላይ እንዲሁም የሰነደ መዋዕለ ንዋዮችን ለሕዝብ ሽያጭ የሚያቀርቡ ተቋማት ላይ የሚጥል በመሆኑ ገበያው የኢንቨስተሮችን ጥበቃ ያከበረ ግልጽ እና ተአማኒነት ያለው እንዲሆን ያስችላል። ኢንቨስትመንት ባንኮችም ይህንን መሰረታዊ የገበያውን ዓላማ በማረጋገጥ ረገድ ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ።

ኢንቨስትመንት ባንኮች በአፍሪካ

በ17ኛው ክፍለ ዘመን በእንግሊዝ እንደተጀመረ የሚነገርለት የኢንቨስትመንት ባንክ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለመደ የባንክ ክፍል ሲሆን በበርካታ አገራት ይተገበራል። የእንግሊዙ ባሪንግ ብራዘርስ (Baring brothers) የመጀመሪያው የኢንቨስትመንት ባንክ ሲሆን የአገሪቷን የንግድና የመንግሥት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን ከመደገፍ አኳያ ጉልህ አበርክቶ አለው። የኢንቨስትመንት ባንኮች በ19ኛው እና በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በተለይም በዩናይትድ ስቴትስ በብዛት የተቋቋሙ ሲሆን እንደ ጄፒ ሞርጋን (J.P. Morgan) ያሉ የአሜሪካ ግዙፍ የፋይናንሥ ባንኮች የአሜሪካን



29

ኢንዱስትሪ በመደገፍ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።

እነዚህ ባንኮች ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት አፍሪካን ከዓለም አቀፍ ካፒታል ገበያ ጋር በማገናኘት አስፈላጊ ድልድይ በመሆን በዓለም የፋይናንሥ ምህዳር ያላትን ተሳትፎ በማሳደግ የነበራቸው ሚና ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በአህጉሪቷ ለተመዘገበው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከጀርባ የእነዚህ ባንኮች ሚና የላቀ ሆኖ እናገኘዋለን፡ ፡ በዘመናዊው ዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ የኢንቨስትመንት ባንኮች ካፒታል በማሰባሰብ፣ በኩባንያዎች መዋሃድና ግዥ፣ በመንግሥታዊ የፋይናንሥ አማካሪነት እና በመሰረተ ልማት ፋይናንሥ ውስጥ ዋና ተዋናዮች ሆነዋል።

በዚህም ስታንዳርድ ባንክ ግሩፕ (Standard Bank Group)፣ አብሳ (Absa Group)፣ ራንድ መርቻንት ባንክ Rand Merchant Bank (RMB)፣ ኢኮ ባንክ (Ecobank Transnational Incorporated) እና ሬኒሰንስ ካፒታል (Renaissance Capital) የመሳሳሉት መሰረታቸውን አፍሪካ ያደረጉ

የኢንቨስትመንት ባንኮች በፍጥነት እየተለዋወጠ ባለው የአፍሪካ ኢኮኖሚ ውስጥ የፋይናንሥ መረጋጋትን፣ የኢኮኖሚ ዕድገት እና የዕለት ተዕለት ተግባራትን በማመቻቸት ወሳኝ ሚና በመጫወት የኢኮኖሚ ምሰሶ ሆነዋል፡፡

የኢንቨስትመንት ባንኮቹ የአህጉሪቷን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማፋጠን የሚያስችሉ ታላላቅ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ለመገንባት የሚያስፈልገውን ፋይናንሥ በቦንድና በአክሲዮን ገበያዎች በማሰባሰብ ከፍተኛ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ በባንኮቹ ድጋፍና አማካሪነት በአህጉሪቷ በርካታ የኃይል ማመንጫዎች፣ የባቡር መስመሮች፣ ወደቦች፣ መንገዶች እና የቴሌኮሙኒኬሽን መሠረተ ልማቶች ተገንብተዋል፡፡

አብነት ለመጥቀስ በኬንያ የመሠረተ ልማት ዕድገት ውስጥ የኢንቨስትመንት ባንኮች ወሳኝ ሚና መጫወታቸው በተደጋጋሚ የሚጠቀስ ነው፡፡ የጆሞ ኬንያታ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የማስፋፊያ



30

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

ፕሮጀክትና በጂኦተርማል ኃይል ፕሮጀክቶች ላይ ያላቸው ተሳትፎ ማሳያዎች ተደርገው ይወሰዳሉ። በተመሳሳይ ደቡብ አፍሪካ የታዳሽ ኃይል አቅርቦቷን ለማሳደግ ባደረገችው ጥረት ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ባንኮች ከፍተኛ ድጋፍ በመስጠት ሚናቸውን ተወጥተዋል።

ኢንቨስትመንት ባንኮች አፍሪካ በዓለም አቀፍ ካፒታል ገበያ ጠንካራ ተሳትፎ እንዲኖራት ለማድረግ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ሌላው የባንኮቹ ስኬት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ናይጄሪያ ወደ ዓለም አቀፍ የዩሮቦንድ ገበያ እንድትገባና ተሳትፎዋን አጠናክራ እንድትቀጥል የኢንቨስትመንት ባንኮች ሚና ከፍተኛ ነበር። አገሪቷ በዓለም አቀፍ ካፒታል ገበያ ውስጥ የመንግሥት ዩሮቦንድ ለማቅረብ ከጄፒ ሞርጋን (J.P. Morgan)፣ ሲቲ (Citi) እና ስታንዳርድ ቻርተርድ (Standard Chartered) ያሉ ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ባንኮች ጋር በቅርብ ሰርታለች። ይህም አገሪቷ ከውጭ ገበያዎች በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ካፒታል እንድትሰበስብ አስችሏታል።

በአፍሪካ የሚገኙ



31

የኢንቨስትመንት ባንኮች በአህጉሪቷ የአክሲዮን እና የዕዳ ገበያዎችን በመደገፍ የፋይናንሥ ዘርፉን በመደገፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል። የአፍሪካ ኩባንያዎች በቀላሉ ካፒታል እንዲያገኙ እንዲሁም አሠራራቸውና አስተዳደራቸውን እንዲያሻሽሉም አስችለዋል። በሌላ በኩል ዓለም አቀፍ ባለሐብቶችን በመሳብ ያላትን እምቅ የኢንቨስትመንት ዕድል በበቂ ሁኔታ ለመጠቀም አስችለዋል፡፡ ኢንቨስትመንት ባንኮች ድርጅቶች እንዲዋሃዱ ማማከር አንዱ ሥራቸው ነው፡፡ በዚህም በርካታ የአፍሪካ ኩባንያዎችን ድንበር ተሻጋሪ ውህደት እንዲፈጽሙ አድርገዋል፡፡

በአጠቃላይ ኢንቨስትመንት ባንኮች የመሠረተ ልማት ፋይናንሥ በማሰባሰብ፣መንግሥታትን በማማከር፣ የግሉን ዘርፍ ዕድገት በመደገፍ እንዲሁም የፋይናሥ አማራጮች በማስፋት በአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ውስጥ የማይተካ ሚና ይዘው ይገኛሉ፡፡

የባለሥልጣኑ የክትትልና የቁጥጥር ሥርዓት

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን በኢንቨስትመንት ባንኮች እና በሌሎች አገልግሎት ሰጪዎች ላይ የሚተገብረው ቁጥጥር የገበያውን ፍትሃዊነት፣ ግልጽነት እና የኢንቨስተሮችን ጥበቃ የሚያረጋግጥ ነው። ይህ ሥርዓት በዋናነት በአዋጅ ቁጥር 1248/2013 እና በካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች ፈቃድ አሰጣጥ እና ቁጥጥር መመሪያ ቁጥር 980/2016 ላይ የተመሰረተ ነው። ይህንንም የክትትል እና የቁጥጥር ተግባር በብቃት ለመወጣት ያስችል ዘንድ በባለሥልጣኑ አደረጃጀት ውስጥ ራሱን የቻለ የገበያ ክትትል (Market Supervision) በሚል የሥራ ክፍል በማደራጀት

ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ እንደሚገኝ አቶ እድሪስ ይገልጻሉ።

በዋናነት በባለሥልጣኑ የሚደረጉት ክትትሎች የውስጥ ቁጥጥር እና የህግ ተገዢነት ኦፊሰር፣ ከሥራ ቦታ ውጭ የሚደረግ የሥራ ክትትል፣ በሥራ ቦታው በመገኘት የሚደረግ ቁጥጥር እንዲሁም ህግ የማስከበር እና የቁጥጥር ዘዴዎች (Enforcement Mechanisms) በመጠቀም ነው። ከመደበኛው ቁጥጥር በተጨማሪ ባለሥልጣኑ ጥፋት መፈጸሙን ሲጠራጠር የምርመራ እና የቅጣት እርምጃዎችን የሚወስድ ሲሆን ከሕዝብ፣ ከውስጥ ሠራተኞች ወይም ከሌሎች ተቋማት የሚመጡ ጥቆማዎችን መሰረት በማድረግ ምርመራ ያካሄዳል።

ለምሣሌ አንድ የኢንቨስትመንት ባንክ ደንበኞችን አታሏል ወይም ያለ አግባብ ገንዘብ ሰብስቧል የሚል ቅሬታ ሲቀርብ፣ የባለሥልጣኑ የምርመራ እና ህግ ማስከበር ክፍል ጉዳዩን አጣርቶ ውሳኔ ይሰጣል። በጉዳዩ ላይ የወንጀል ፍሬ ነገር የተገኘ እንደሆነም ጉዳዩን ለሚመለከተው የፖሊስ ወይም የፍትህ ሚኒስቴር ያስተላልፋል። አንድ የኢንቨስትመንት ባንክ ህግ ጥሶ ከተገኘ ባለሥልጣኑ ከማስጠንቀቂያ ጀምሮ እስከ ፍቃድ መሰረዝ እና የገንዘብ መቀጮ የሚደርሱ አስተዳደራዊ እርምጃዎችን የመውሰድ ህጋዊ ሥልጣን ተሰጥቶታል።

ወደ ሥራ የገቡት የኢንቨስትመንት ባንኮች እስከአሁን ባለው ሂደት በተለይም የግብይት አማካሪ በመሆን ኩባንያዎች አክሲዮኖቻቸውን በባልሥልጣኑ ማስመዝገብ እንዲሁም ተጨማሪ ካፒታል መሰብሰብ የሚያስችላቸውን የደንበኛ ሳቢ መግለጫዎች በማዘጋጀት ረገድ ቁልፍ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን አቶ እድሪስ ያነሳሉ። ይህ



32

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

ተግባር ለመገንባት ለሚፈለገው ግልጽ፣ ተዓማኒና ፍትሃዊ ገበያ ትልቅ መሰረት የሚጥል ነው። ከዚህ ባለፈም የሰነደ መዋዕለ ንዋይ ደላላ በመሆን ግብይቶችን እያስፈፀሙ ይገኛሉ። ገበያው ጀማሪ እንደመሆኑ መጠን ወደፊት በርካታ ሥራዎች የሚጠበቁ ቢሆንም በአጭር ጊዜ ውስጥ አመርቂ ተግባራትን ማከናወን እንደቻሉ ነው አቶ እድሪስ ያወሱት።

የዘርፉ ተግዳሮት እና መፍትሔዎቹ

ኢትዮጵያ ወደዚህ አዲስ ምዕራፍ ስትገባ እንደ ጀማሪ በኢንቨስትመንት ባንኮች እንዲሁም በአጠቃላይ በገበያው ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች ይኖራሉ። ዘርፉ ለአገራችን አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በኅብረተሰቡ እና በንግዱ ማኅበረሰብ ዘንድ ስለ ኢንቨስትመንት ባንክ አገልግሎትና ስለ ካፒታል ገበያ በቂ ግንዛቤ አለመፈጠሩ ዋነኛው የዘርፉ ተግዳሮት እንደሆነ አቶ እድሪስ ይናገራሉ። በሌላ በኩል አዲስ ገበያ እንደመሆኑ መጠን የፍሰት መጠኑ በገዢም ይሁን በሻጭ በኩል በቂ የሆነ የገንዘብ ፍሰት (Market Liquidity) ችግር

ሊያጋጥም እንደሚችል ይገመታል።

በዘርፉ ልምድ እና ክህሎት ያለው ባለሙያ በበቂ ሁኔታ አለመገኘት፣ ደካማ የገበያ ባህል መኖር ሌላኛው የባንኮቹ ፈተና ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። አብዛኛው የአገራችን የንግድ ድርጅቶችን የቤተሰብ ንብረት ከመሆን ወደ ሕዝባዊ ኩባንያነት (Public Company) ለመቀየር ያለው ፍላጎት ውስን ሊሆን ይችላል። የኢንቨስትመንት ባንክ ሥራ ጥራት ያለው የሂሳብ ሪፖርት ይፈልጋል።

በኢትዮጵያ ከፋይናንስ ተቋማት ውጭ ያሉ በርካታ ኩባንያዎች ትክክለኛውን ትርፍ እና ኪሳራቸውን በግልጽ የማሳየት እና ለሕዝብ ይፋ የማድርግ ልምድ ስለሌላቸው፣ የኩባንያዎችን ትክክለኛ ዋጋ (Valuation) ለመተመን በጣም አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ያለው የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ለመዘርጋት የሚጠይቀው ከፍተኛ ወጪ እና ጊዜ ሌሎች ፈተናዎች እንደሚሆኑ አያጠያይቅም።

እነዚህ ተግዳሮቶች እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ጀማሪ



33

ገበያዎች ላይ ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ የሚናገሩት በካፒታል ገበያ ባለሥልጣን የፈቃድ እና ምዝገባ ዳይሬክቶሬት ኃላፊ አቶ እድሪስ ሰልማን ባለሥልጣኑ ችግሮቹን አሰቀድሞ ለመቀነስ የሚያስችሉ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል። በዚህም የኅብረተሰቡን የፋይናንሥ ዕውቀት (Financial Literacy) በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች በመገኘት ከተለያዩ የኅብረተሰቡ ክፍል ለተውጣጡ አካላት ተከታታይነት ያላቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን በማዘጋጀት ስለ ካፒታል ገበያ ግንዛቤ እንዲዳብር እየተሠራ ይገኛል።

በዘርፉ የሠለጠነ የሰው ኃይል ከማፍራት አንፃር በርካታ ተግባራት በባለሥልጣኑ እየተከናወኑ ሲሆን በዋናነት ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራበት ያለው የካፒታል ገበያ ኢንስቲትዩት ማቋቋም ይጠቀሳል። የዚህ ኢንስቲትዩት መቋቋም በዘርፉ የሠለጠነ የሰው ኃይል ከማፍራት አንፃር ትልቅ ጥቅም ይኖረዋል። በተጨማሪም በተለይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ በተማሪዎች ዘንድ ስለ ካፒታል ገበያን ያለውን ዕውቀት ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመሥራት ያስችል ዘንድ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እየሠራ ይገኛል። በክረምት መርሃ ግብርም ለዩንቨርሲቲ ተማሪዎቸ ሰፋፊ ሥልጠናዎችን በመስጠት በሥልጠናው ወቅት ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች በካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች ፈቃድ አሰጣጥ እና ቁጥጥር መመሪያ 980/2016 እንደ ብቃት ማረጋገጫ ከሚወሰደው እንግሊዝ አገር ከሚገኝ ዓለም አቀፍ የሥልጠና ማዕከል ነፃ የትምህርት ዕድል በመስጠት በማሠልጠን ላይ ይገኛል።

ሊሎች ገበያው ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችን በተመለከተ የካፒታል ገበያ አዋጁ

የባለሥልጣኑን ዓላማ ሲያስቀምጥ ገበያውን በመቆጣጠር ላይ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ገበያውን የማልማት ኃላፊነት ጥሎበታል። በመሆኑም ባለሥልጣኑ በሚያከናውናቸው ሁለም ተግባራት እና የሕግ ማዕቀፎች ይህንኑ ዓላማ ከግምት ያስገቡ ናቸው። በተለይ በአገራችን የካፒታል ገበያው ከሌሎች አገራት አንፃር ዘግይቶ የተጀመረ እንደመሆኑ አገራት ካጋጠሟቸው ችግሮች ትምህርት በመውሰድ እንዲሁም ምርጥ ተሞክሮዎችን ከአገራዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር በማገናዘብ ችግሮችን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያችል ትልቅ ዕድል እና አቅም መፍጠር ተችሏል።

ማጠቃለያ

የካፒታል ገበያ መስፋፋት የዜጎች ፍትሃዊ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ወሳኝ ሚና አለው። በካፒታል ገበያ ቁልፍ ሚና ያላቸው የኢንቨስትመንት ባንኮች መከፈት ተጨማሪ ፋይናንስ ነክ ተቋማት እንዲከፈቱ በር በመክፈት ተጨማሪ ኢንቨስትመንት እና የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ያስችላል።

የእነዚህ ኢንቨስትመንት ባንኮች የካፒታል ገበያውን መቀላቀል ከዚህ ቀደም በተበጣጠሰ መልኩ ሲከወን የነበረውን አሠራር በማስቀረት መተማመንን በመፍጠር ገንዘባቸውን ፈሰስ የሚያደርጉ ግለሰቦች እና ተቋማትን ከመጭበርበርና ከሀሰተኛ መረጃ ጭምር መከላከል የሚያስችሉ ናቸው።

በአጠቃላይ ኢንቨስትመንት ባንኮች ካላቸው ሰፊ ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት አንጻር በአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ውስጥ ያላቸው ድርሻ የላቀ ነው።



34

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

ፖለቲካ

የኢትዮ-ሕንድ የወዳጅነት ማማ



35

ታሪካዊ ጉብኝት

በአስደማሚ የዲፕሎማሲ እና የወዳጅነት መግለጫ የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሽሪ ናሬንድራ ሞዲ በቅርቡ የኢትዮጵያን ምድር ረግጠዋል። ምድረ ቀደምት የሰው ዘር መገኛ፣ የቡና ምድር. . . በሆነችው ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ጉብኝታቸውን በማድረግ ህያው ታሪክ አስመዝግበዋል። የሞዲ ጉዞ በኢትዮጵያ እና በሕንድ መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነት ከማረጋገጡም በላይ የማንሞሃን ሲንግን

በጌታቸው ያለው



36

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

ፈለግ በመከተል ሁለተኛው የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ስማቸውን በታሪክ መዝገብ ውስጥ አስፍረዋል።

ሞዲ አዲስ አበባ ሲደርሱ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተደረገላቸው ድንቅ ዲፕሎማሲያዊ አቀባበል ብቻ ሳይሆን በመሪዎችም ሆነ በአገሮቻቸው ወዳጅነት ታሪክ ውስጥ የጎላ አሻራ የጣለ ጥልቅ አክብሮትና አድናቆት ስለመሆኑ ግዙፍ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን በዘገባዎቻቸው እማኝነታቸውን ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ ወደ አገራቸው ሲመለሱም ኢትዮጵያዊው አቀባበል ግለቱን እንደጠበቀ አብሯቸው ወደ ሕንድ ስለመጓዙ የአገሪቷ የመገናኛ ብዙኃን ዘገባ አሳብቋል። ጉብኝቱ በዲፕሎማሲና በጋራ መግባባት የተሸመነውን የሁለቱን አገራት የበለፀገ የታሪክ እና የባሕል ትስስር ይበልጥ ያጎላ ሆኗል። ይህ ጉብኝት በኢትዮጵያ እና በሕንድ

መካከል ያለውን ዘላቂ ትስስር ወደ ከፍታ ማማ ያሳደገ ከመሆኑም በላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ እያደገ የመጣውን የአፍሪካን የስበት ማዕከልነት ያጎላ ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ የኢትዮጵያ ጉብኝት ለትብብር መንፈስ ጠንካራ ምስክር ሆኖ ያገለግላል። ጉብኝቱ በጋራ ግቦችና በመከባበር ላይ የተገነባ፤ ስለ ዓለም ሠላም ሁሉም እንዲያስብ የሚጋብዝ ጭምር ነው። በመሆኑም ከአዲስ አበባ የተሰማው የትብብር ዜማ የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኒው ዴልሂ ከደረሱ በኋላም ማስተጋባቱን ቀጥሏል። በእርግጥም የአንድነት የጥንካሬና የዲፕሎማሲ ኃያልነት ነጸብራቅ ሆኖ የተጠናቀቀ ጉብኝት።

የመኪና እና የቡና ዲፕሎማሲ (Car & Cof- fee Diplomacy)

ዲፕሎማሲ ሁሌም ቀላል ጥበብ አይደለም።



37

ይልቁንም የመረዳትና የማሳመን ጥልቅ ነጸብራቅ እንጂ። ብዙውን ጊዜ የድርድር ጥበብ ተብሎ የሚጠራው ዲፕሎማሲ የሰው ልጅ በጣም ስስ እና ተፈላጊ ከሆኑ ክህሎቶች አንዱ ነው። እንደ እጅ መጨባበጥ፣ ግብዣ እና ስምምነቶች ያሉ አካሄዶች የመወዳጀት መገለጫ ተደርገው ቢወሰዱም እውነታው ግን ዲፕሎማሲ ብዙውን ጊዜ በውጥረት፣ በመደራደር እና በተፎካካሪ ፍላጎቶች ጥላ ሥር የሚከናወን ድንቅ ጥበብ ነው።

በዋናነት ዲፕሎማሲ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ማመጣጠን ነው። ብሔራዊ ጥቅሞችን ከዓለም አቀፍ ኃላፊነቶች፤ የአጭር ጊዜ የፖለቲካ ትርፍን ከረጅም ጊዜ ሠላም እና የኃይል ተለዋዋጭነት ከሥነ-ምግባር ግዴታዎች ጋር ማመጣጠን ማለት ነው። የዲፕሎማቶች አንድ የተሳሳተ እርምጃ፣ ሐረግ ወይም ምልክት ወደ አለመግባባት ወይም ግጭት ሊያመራ በሚችልባቸው ጉዳዮች ላይ ያለማቋረጥ አቅጣጫ መቀየር ግድ ይላቸዋል።

ወደ ንዑስ ርዕሱ ስናተኩር የመኪና ዲፕሎማሲ የሚለው ቃል የዓለም መሪዎች የግል መተማመንን፣ ስትራቴጂካዊ ቅርርብን እና መደበኛ ያልሆነ ግንኙነትን ለማመልከት ተሽከርካሪን በጋራ የሚጠቀሙበትና ባለፉት ጥቂት ዓመታት እያደገ የመጣ የዲፕሎማሲ ዘይቤ ነው። በመኪና ዲፕሎማሲ ታሪክ ቀዳሚ ተደርጎ የሚወሰደው በ1970ዎቹ በአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሪቻርድ ኒክሰን እና የቀድሞው ሶቪዬት ኅብረት ኮሚኒስት ፓርቲ ዋና ፀሐፊና የአገሪቷ መሪ ሊዮኒድ ብሬዥኔቭ መካከል የነበረው ነው። ሁለቱ መሪዎች ያደረጉት የመኪና ዲፕሎማሲ መልካም ግንኙነት ለመገንባት ከማገዙም በላይ በዘመኑ የነበረውን የቀዝቃዛውን ጦርነት ውጥረት ለማርገብ (Détente) ዓይነተኛ

ሚና ተጫውቷል።

በወቅቱ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ሪቻርድ ኒክሰን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ለማመቻቸት ሲሉ የምዕራባዊያን ቅንጡ ተሽከርካሪዎች አፍቃሪ ለነበሩት ሊዮኒድ ብሬዥኔቭ ቅንጡ የአሜሪካ ተሽከርካሪዎችን በስጦታ አበርክተውላቸዋል። ለመኪና ዲፕሎማሲ መነሻ እንደሆነ የሚነገርለት ክስተት የተፈጠረው ግን እ.አ.አ በሰኔ 1973 በካምፕ ዴቪድ ነው። ብሬዥኔቭ ‘ሊንከን ኮንቲኔንታል’ የተሰኘች እጅግ ቅንጡ አውቶሞቢል ከፕሬዚዳንት ኒክሰን እጅ ከተረከቡ በኋላ መሞከር እንደሚሹ አጥብቀው ጠየቁ። እናም የፕሬዚዳንቱን ይሁንታ አገኙና ብሬዥኔቭ ራሳቸው ማሽከርከር ጀመሩ። በአውቶሞቢሏ ውስጥ ታዲያ ፕሬዚዳንት ኒክሰን አብረዋቸው ተሳፍረው ነበር።

ብሬዥኔቭ በጠባብ፣ በጠመዝማዛ እና በቂ ብርሃን በሌላቸው መንገዶች ላይ በሠዓት ከ80 ኪሎ ሜትር በላይ በሆነ ፍጥነት ሲያሽከረክሩ ፕሬዚዳንት ኒክሰን የተደናገጠ ገጽታ ይስተዋልባቸው ነበር። ብሬዥኔቭ “በዝግታ ያሽከርክሩ፣ አደገኛ መታጠፊያ አለ” የሚሉ የመንገድ ዳር ምልክቶችን ችላ በማለት በፍጥነት መታጠፋቸው የአውቶሞቢሏ ጎማዎች ለጆሮ የሚሰቀጥጥ ድምፅ እስኪያሰሙ ድረስ ፍሬን እየያዙ፤ በአስደንጋጭ የማሽከርከር ሂደት መጓዛቸው ኒክሰን ዓይናቸውን እንዲያጉረጠርጡ አድርጓቸዋል።

ይህ 30 ደቂቃ ያህል የፈጀው የሁለቱ መሪዎች የጋራ ጉዞ ከደህንነት መረጃዎቻቸው እና ከኒኩሌር ኮዶቻቸው (Nuclear Codes) ለያይቷቸዋል (ሁለቱ አገራት የኒኩሌር ጦር መሣሪያ ባለቤት መሆናቸውን ልብ ይሏል)። ጉዟቸውን አጠናቀው



38

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

ሲመለሱ የፕሬዚዳንት ኒክሰን ፊት ገርጥቶና ላብ ችፍ ብሎበት የታየ ቢሆንም የብሬዥኔቭን የማሽከርከር ብቃት አድንቀው የዲፕሎማሲ ንግግሮቻቸውን ቀጣይ ስኬት ለማረጋገጥ አስችሏቸዋል። ያኔ ለሁለቱ መሪዎች የመኪና ዲፕሎማሲ መጀመር ምክንያት እንደሆነች የሚነገርላት ሊንከን አውቶሞቢል አሁን ላትቪያ በሚገኘው ሪጋ የሞተር ሙዚየም ውስጥ ለሕዝብ እይታ ቀርባ እየተጎበኘች ትገኛለች። ለመኪና ዲፕሎማሲ መጀመር የሁለቱ አገራት መሪዎች እ.አ.አ የ1970ዎቹ ታሪካዊ ሁነት ቢሆንም፤ ጉዳዩ ጎልቶ በስፋት መተግበር የጀመረው ግን ባለፉት ጥቂት ዓመታት ነው።

ይህን ርዕሰ ጉዳይ ለማነሳት ምክንያት የሆነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሕንዱን አቻቸውን ናሬንድራ ሞዲን ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እስከሚያርፉበት ሆቴል ድረስ ራሳቸው እያሽከረከሩ ያደረጉላቸው አቀባበል ነው። እርግጥ ነው ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ፕሬዚዳንት ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ተመሳሳይ አቀባበል ማድረጋቸው ይታወቃል።

በአፍሪካ ኅብረት የሕንድ የቀድሞ አምባሳደር የነበሩትና የሕንድ-አፍሪካ የኢኮኖሚና የልማት አጋርነት ዙሪያ የሚያጠነጥነው ዘ ሃራምቢ ፋክተር (The Harambee Factor) መጽሐፍ ደራሲ ጉርጂት ሲንግ የናሬንድራ ሞዲን አቀባበል ዘ ኢንዲያን ኤክስፕረስ ላይ “PM Modi’s Ethi- opia visit: With car Diplomacy, New Av- enues for Indian investment in Africa” ሲሉ ገልጸውታል። ማለፊያ አገላለጽ። የመኪና

ዲፕሎማሲ ዓለም አቀፍ መሪዎች ግላዊ ግን ደግሞ ሞቅ ያለ ግንኙነትን፣ መተማመን እና ከመደበኛ ውይይቶች ባሻገር ጠንካራ ትስስርን ለማመልከት በጋራ የመኪና ጉዞዎችን የሚያደርጉበት ዘመናዊና የለስላሳ ኃይል (Soft Power) ስልት ነው።

ይህ ስልት ከመደበኛ ውይይቶች በላይ ይሄዳል። መተማመንን የሚያንፀባርቅ፣ የቅርብ ወዳጅነትን የሚፈጥር ነው። እንደ ሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ካሉ መሪዎች ጋር ተሽከርካሪዎችን መጋራት ያሉ የቅርብ ጊዜ አጋጣሚዎች መደበኛ ያልሆኑ ቅርርቦች የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን እንዴት እንደሚያሻሽሉና የወዳጅነት መንፈስን እንደሚያዳብሩ የሚያሳዩ ናቸው። የመኪና ዲፕሎማሲ ተመራጭ የሚያደርገው ጥብቅ ዲፕሎማሲያዊ ፕሮቶኮሎችን ወደ ጎን በመተው በጋራ ወዳጅነት ላይ መመስረቱ ነው። መሪዎች ቀለል ያለ ግን ደግሞ ምቹ ሁኔታን በመምረጥ ከዲፕሎማሲያዊ ፕሮቶኮል መለስ እኩልነትንና የጋራ መከባበርን የሚያንጸባርቁበት ነው።

የጋራ ጉዞዎቹ ዘና ያሉ ውይይቶችን ከመፍጠራቸው ባሻገር መሪዎቹ ለዓለም ሠላምና ለአንድነት ግንባር እንዲፈጥሩ ያስችላቸዋል። ስትራቴጂካዊ ጥምረቶቻቸውን ለዕይታ ተፅዕኖ ባለው መንገድ ያጠናክራሉ። መሪዎች ከመደበኛ ስብሰባዎችና ገደቦች ውጭ እርስ በርስ ሲገናኙ ግንኙነታቸውን ለማጥበቅ ያላቸውን ቁርጠኝነት ያጎላል።

እንዲህ ያሉ የመኪና ዲፕሎማሲዎች የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን የሚያጠናክሩ፣ የሕዝብን ቀልብ የሚስቡና የመሪዎችን ሰብዓዊነት የሚያያንጸባርቁ ተደርገው ይወሰዳሉ። እነዚህ አካሄዶች ከተለመደው ፕሮቶኮል ወጣ ያሉ ሲሆኑ ስትራቴጂካዊ ቅርርብን



39

መደበኛ ባልሆነ፤ ብዙውን ጊዜ በእይታና ገላጭ በሆኑ የገጽታ ምልክቶች ያንጸባርቃሉ። ሰፊ የሕዝብና የመገናኛ ብዙኃን ዕይታን የመሳብ አቅም ያላቸው እነዚህ አስገራሚና ሰፊ እይታዎቸ የሕዝብን አመለካከት በእጅጉ ሊቀይሩ የሚችሉ ናቸው።

መሪዎች የዓለም አቀፍ ፖለቲካን ውስብስብነት ሲቃኙ የመኪና ዲፕሎማሲን እምነትን ለመገንባትና ጠንካራ ትስስር ለመፍጠር እንደ አዲስና ውጤታማ ስትራቴጂ ይጠቀሙበታል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያደረጉትም ይኸው ነው። የኢትዮ-ሕንድን አጋርነት ወደ ስትራቴጂያዊ ከፍታ ማሳደግና ሕንድን ቤተሰብ፤ ጉብኝቱንም ታሪካዊ ማድረግ።

የቡና ዲፕሎማሲ ዓለም አቀፍ ግንኙነቶችን ለመገንባት፣ በጎ ፈቃድን ለማሳደግና ብሔራዊ ጥቅሞችን ለማስጠበቅ ቡና በጋራ መጠጣትን እንደ ስትራቴጂካዊ መሣሪያ መጠቀምን ያመለክታል። ከመጠጥ በላይ ቡና የባሕል ልውውጥና የኢኮኖሚ ተሳትፎ ማጎልበቻ ሆኖ ያገለግላል። ይህም ወዳጅነት በውይይትና

በዲፕሎማሲ ሊያድግ የሚችልበትን ዘና ያለ ግን ደግሞ ጠቃሚ አውድ የሚያስገኝ ነው። በዓለም መሪዎች መካከል በጋራም ሆነ በንግድ ኤክስፖዎች ላይ ቢቀርብም፤ አንድ ስኒ ቡና ግልፅ ውይይትና የጋራ መከባበርን የሚያበረታታ መደበኛ ያልሆነና ሞቅ ያለ የአቀባበል ድባብን ይፈጥራል።

ይህ አካሄድ የባሕል ማንነትን ከኢኮኖሚያዊ ምኞት ጋር በማጣመር አገራት ልዩ ቅርሳቸውን እንዲያሳዩ ያስችላቸዋል፤ ኤክስፖርት እና



40

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

የንግድ ሽርክናዎችንም ያበረታታል። በዚህ ረገድ የቡና መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ ባሕላዊ የቡና ሥነ-ሥርዓቷን የዲፕሎማሲዋ አካል በማድረግ ጥቅሟን እያስጠበቅችበት ትገኛለች። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሕንዱን ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲን ጥዑም ቃና ያለውን ድንቅ ኢትዮጵያዊ ቡና ጋብዘው የአገራቸውን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የሄዱበት መንገድ ልክ እንደ መኪናው ዲፕሎማሲ የብዙዎችን ቀልብ የገዛ ሆኗል።

ሕንድና መሪዎቿ

ሕንድ በጥንታዊ ታሪክ እና በንቃተ ህሊና ባሕል የተሞላች አገር ስትሆን፤ ለረጅም ጊዜ የዴሞክራሲያዊ ሀሳቦችና የለውጥ አመራር ምልክት ሆና ቆይታለች። ከነፃነት ትግሉ ጀምሮ የዓለም ኃያል አገር እስከመሆን ድረስ የሕንድ አመራር ገጽታ በራዕይ፣ በጽናት እና በፈጠራ ክሮች የተሸመነ ነው።

የዘመናዊቷ ሕንድ ታሪክ በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕዝቦችን ባነሳሳው እንደ ታላቁ ማህተመ ጋንዲ ባሉ አስደናቂ



41

መሪዎች የተመሰረተ ነው። የጋንዲ ቅርስ ድንበር አልፎ ጭቆናን በመጋፈጥ ሰላማዊ የመቋቋም ኃይልን ያስታውሰናል። ለነፃ እና ለተባበረችው ሕንድ ያለው ራዕይ በልዩነት ውስጥ አንድነትን ለሚያከብር አገር መሰረት ጥሏል።

የዘመናዊቷ ሕንድ አናፂዎች እንደሆኑ የሚነገርላቸው እንደ ጃዋሃርላል ኔህሩ እና አታል ቢሃሪ ቫጅፓዪ ያሉ መሪዎች ከነፃነት በኋላ ሕንዳዊ ማንነትን የቀረፁበት ታሪክ አገሪቷ አሁን ለደረሰችበት ከፍታ እርሾ ሆኖ አገልግሏል። ኔህሩ ለኢንዱስትሪ ልማትና ለዘመናዊነት የነበራቸው ቁርጠኝነት ለሕንድ የኢኮኖሚ ልማት መንገድ ከፍቷል። አታል ቢሃሪ ቫጅፓዪ በአስተዳደር ብቃታቸው፣ በኢኮኖሚ ማሻሻያዎቻቸው፣ በመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች (The Golden Quadrilateral) እና ሕንድን የኒኩሌር መሣሪያ ባለቤት በማድረጋቸው ምክንያት ከምርጥ መሪዎች አንዱ እንደሆኑ ይታሰባል።

የሕንድ አመራር ጽንሰ-ሀሳብ ጥንታዊ ጥበብን ከዘመናዊ ተግዳሮቶች ጋር በማዋሃድ በአገልግሎት፣ በሥነ ምግባርና በዓለም አቀፍ ራዕይ ላይ ያተኩራል። እንደ ጋንዲ፣ ኔህሩ፣ አምቤድካር እና ሞዲ ባሉ ዘመናዊ መሪዎች ከመንፈሳዊ አመራር (Sadh- guru) እስከ ፖለቲካዊ ለውጥ ድረስ የሕንድን ገጽታ ገንብተዋል። የአገሪቷ የመጀመሪያዋ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ኢንዲራ ጋንዲም መሰናክሎችን ተሻግረው ሕንድን በጥንካሬ መርተዋታል። በተለይ “ድህነትን ማስወገድ- Garibi Hatao” የተሰኘው ታዋቂ መፈክራቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማነቃቃት የተራ ሕንዳዊያንን ሕይወት ለመለወጥ ያስቻለ መሆኑ ይነገርላቸዋል።

በሕንድ ታሪክ ውስጥ እያንዳንዱ መሪ በአገሪቷ እየተለወጠ ላለው ማንነት አስተዋጽኦ አድርጓል። ይህም ለባህል እና ዘመናዊነት ቅይጥ መሰረት ሆኖ ቀጥሏል። የሕንድ አመራር የጋራ ህልም በሂደት፣ በተሳትፎ እና በዓለም አቀፍ ትብብር ላይ የተመሰረተ ነው። ይህም አመራር ስለ ሥልጣን ብቻ ሳይሆን ለመጪው ትውልድ ብሩህ መጻዒ ጊዜን ማመቻቸትን ታሳቢ ያደረገ ስለመሆኑ ያሳያል። በአጭሩ የሕንዳዊያኑ አመራር የአገሪቷ ሕዝብ የጋራ ሕልም ሆኖ ዘልቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ለሕንድ አዲስ ራዕይ በማንጸባረቅ ላይ ይገኛሉ። ፖሊሲዎቻቸው በኢኮኖሚና በቴክኖሎጂ ዕድገት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ጠንካራ መሰረት በመገንባት ላይ ናቸው። “ሕንድ ውስጥ መሥራት” እና “ዲጂታል ሕንድ” ያሉ ተነሳሽነቶች አገሪቷን ወደ ማኑፋክቸሪንግና ቴክኖሎጂ ማዕከልነት ለመቀየር ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያጎሉ ናቸው።

በሞዲ አመራር ሕንድ በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ውስጥ እንደ መሪ ሚናዋን እየተወጣች ትገኛለቸ። ከተለያዩ አገራት ጋር በመተባበር የኢኮኖሚ ግንኙነቶችና ሽርክናዎችን ታበረታታለች። እንደ ታሪካዊው የኢትዮጵያ ጉብኝት ያሉ የቅርብ ጊዜ የአገሪቷ የዲፕሎማሲ ተልዕኮዎች በአፍሪካ እየገነባች ያለችውን ግንኙነት ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያሉ።

የጉብኝቱ አንድምታዎች

ዓለም አቀፍ ትስስር ፈታኝ በሆነበት በዚህ ዘመን የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በኢትዮጵያ ያደረጉትን ታሪካዊ ጉብኝት ያህል ፍሬያማ የዲፕሎማሲ ተልዕኮዎችን ያሳኩት



42

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

ጥቂቶች ናቸው። ጉብኝቱ የፕሮቶኮል ብቻ ሳይሆን የዓላማ ጭምር ነው። ከቀይ ምንጣፍና ከይፋዊ የእጅ መጨባበጦች ባሻገር ይህ ታሪካዊ ጉብኝት ጥንታዊ ትስስርን እንደገና አቀጣጥሏል። ለሁለቱ አገራትም ሆነ ሰፋ ባለው የአፍሪካ አህጉር ጥልቅ አንድምታ የፈጠረ ትልቅ አጋጣሚ ነው ማለት ይቻላል። ጥንታዊ ግንኙነቶችን ወደ ዘመናዊ የትብብርና የአጋርነት ስትራቴጂያዊ ማዕቀፍ ከፍ ያደረገ ድንቅ ጉብኝት።

በኢትዮጵያ እና በሕንድ መካከል ያለው ታሪካዊ ትስስር ሁለት ሺህ ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን ሁለቱ አገራት ከአንደኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ጠንካራ የንግድ ትስስር ማስፋፋት ችለዋል። የሕንድ ነጋዴዎች በ6ኛው ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ ሐር እና ቅመማ ቅመም ይነግዱ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ። ይህ ጊዜ የማይሽረው ትስስር ወደፊት የሚመለከት ስትራቴጂካዊ አጋርነት፣ በጋራ መከባበር፣ በጋራ ፍላጎቶችና በዓለም አቀፍ የደቡብ-ደቡብ የጋራ ራዕይ መለወጡን የሚያሳይ ምልክት ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ ጉብኝት በኢትዮጵያ እና በሕንድ ግንኙነት ውስጥ ጉልህ ምዕራፍ የያዘ ሲሆን ከዘመናት በፊት የነበረውን ግንኙነት እንደገና ያቀጣጠለ ነው። አገራቱ የበለጸጉ ታሪኮችና የተለያዩ ባሕሎች ያሏቸው ናቸው። ሆኖም ብዙውን ጊዜ አካሄዳቸውን ለየብቻ ሲያስሱ ቆይተዋል። የአሁኑ ጉብኝት ግን መልክዓ ምድራዊ ርቀት ሳይገድበው በጋራ እሴቶችና ፍላጎቶች ላይ ጠንካራ ጥምረት ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ያረጋገጠ ነው። የናሬንድራ ሞዲ ጉብኝት በሕንድ በኩል የአፍሪካ ግንኙነት ላይ ላቅ ያለ ፍላጎት ስለመኖሩም ያሳያል። ጉብኝቱ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫና በአፍሪካ ቀንድ

ወሳኝ ሚና በምትጫወተው ኢትዮጵያ ላይ ያተኮረ መሆኑ ደግሞ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ አንድምታው በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ ነው የሚያሳየው።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ኒው ዴልሂ በዓለም አቀፍ አስተዳደር፣ ግንኙነት እና የባሕር ደህንነት ማዕከል በሆነው ቀጣና ውስጥ የፖለቲካ ተሳትፎዋን ለማጠናከርና ስትራቴጂካዊ ሥፍራዋን ለመያዝ ያላትን ፍላጎት የሚጠቁም ነው። ቻይና፣ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ የባሕረ ሰላጤው አገራት እና ቱርኪዬን ጨምሮ የተለያዩ ተዋናይ አገራት አፍሪካ ውስጥ ያላቸውን ተጽዕኖ እያሰፉ ባሉበት ወቅት የሕንድ ግንኙነት ዲፕሎማሲያዊ ቦታን መልሶ ለማግኘትና በዘመናት ውስጥ የተገነቡ መቀራረቦችን ለማጠናከር ያላትን ፍላጎት ያሳያል።

በዚህ ሁሉ ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ከአፍሪካ አገራት ኢትዮጵያን ቁልፍ መዳረሻ ማድረጋቸው በብዙ መልኩ ሊታይ ይችላል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ የባለብዙ ወገን ሥርዓት ውስጥ ያላት የዳበረ የአመራር ሚና እና በቀይ ባሕር እና በኤደን ባሕረ ሰላጤ ወሳኝ የውኃ መስመር ላይ ያላት ቁልፍ መልክዓምድራዊ አቀማመጥ ከ120 ሚሊዮን ከሚልቀው ሕዝቧ ጋር ተዳምሮ ለሕንድ ተፈጥሯዊ የቀጣናው መልህቅ አገር በመሆን ስራቴጂያዊ ተፈላጊነቷ ከፍ እንዲል አድርጎታል።

የሁለቱ አገራት መሪዎች በፓርላማ ግንኙነት፣ በልማት አጋርነትና በአቅም ግንባታ፣ በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በመከላከያ፣ በአይሲቲ፣ በግብርና፣ በወጣቶች ክህሎት እና በሕዝብ ለሕዝብ ትስስር የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ማስፋት በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ መክረዋል። ይህም



43

ቀደም ሲል የነበረው የኢትዮ-ሕንድ ወዳጅነት ወደ ስትራቴጂያዊ አጋርነት እንዲያደግ በማድረግ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፍቷል። የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጉብኝት ዘርዘር ተደርጎ ሲታይ በሚከተለው መልኩ ሊገለጽ ይችላል።

ከንግድና ኢንቨስትመንት አኳያ

በታሪክ ሲታይ ሕንድ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በገንዘብ በመደገፍ፣ የገጠር ኤሌክትሪክ አገልግሎት ማስፋፊያን በመደገፍና የቴክኒክ እና ሙያ ሥልጠናዎችን በመስጠት በኢትዮጵያ ልማት ውስጥ ጠቃሚ ሚና ተጫውታለች።

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የተመዘገቡ 675 የሚደርሱ የሕንድ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በማኑፋክቸሪንግ፣ በጨርቃጨርቅ፣ በመድኃኒት፣ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሸን ቴክኖሎጂ (ICT) እና በአግሮ-ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ተሰማርተው በአጠቃላይ ከስድሥት ቢሊዮን ዶላር በላይ መዋዕለ ነዋያቸውን



44

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

አውጥተዋል። ይህም ሕንድ ከቻይና ቀጥላ በኢትዮጵያ ግዙፍ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ምንጭ እንድትሆን አስችሏታል። እነዚህ ኢንቨስትመንቶች ከ75 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን የሥራ ዕድል ፈጥረዋል።

ሕንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት አጠቃላይ የንግድ ልውውጥ እ.አ.አ ከ2023 እስከ 2024 ባለው ጊዜ 571 ነጥብ 52 ሚሊዮን ዶላር ነበር። በዚህ ወቅት ሕንድ ወደ ኢትዮጵያ የላከችው ምርት 489 ነጥብ 59 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን በአንፃሩ ከኢትዮጵያ የተላኩ ምርቶች ደግሞ 81 ነጥብ 93 ሚሊዮን ዶላር ነበር። ከሕንድ የሚላኩ ምርቶች በዋናነት ያለቀላቸውና በከፊል የተጠናቀቁ የብረታ ብረት፣ የመድኃኒት ምርቶች እና ማሽነሪዎችን ያካትታሉ። ከኢትዮጵያ ወደ ሕንድ የሚላኩ ዋና ዋና ምርቶች ጥራጥሬዎች፣ የከበሩ ድንጋዮች፣ አትክልቶች፣ ቆዳ እና ቅመማ ቅመም ናቸው።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ካላቸው አገራት አንዷ ስትሆን በአህጉሪቱ ሰፊ ገበያ ካላቸው መካከልም ተጠቃሽ ናት። በሌላ መልኩ ኢትዮጵያ ያሏት የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ ከግብርና ወደ ማኑፋክቸሪንግ የሚያመራ ኢኮኖሚና አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ከሕንድ የኢንቨስትመንት ፍላጎቶች ጋር የሚጣጣሙ ናቸው። ይህ ደግሞ የሕንድ በመጠነኛ ዋጋ የማኑፋክቸሪንግ እና የሙያ ሥልጠና ልምድ ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራዎችን በስፋት እንድትፈጥር ሊረዳት ይችላል። ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ ኢትዮጵያን ከጎበኙ በኋላ ከሕንድ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰት እንደሚጠበቅ መጠቆማቸው ሌለው ጠቃሚ አንድምታ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ይህም በቴክኖሎጂ፣ በታዳሽ ኃይል፣ በማዕድንና በሌሎች መስኮች ኢንቨስትመንትን ይበልጥ እንደሚያሳድግ ይጠበቃል።



45

ከዚህ ጋር ተያይዞ ሊታይ የሚችለው ሌላው ጉዳይ የሁለቱ አገራት የመከላከያ ትብብር የሽርክናው ቁልፍ ምሰሶ መሆኑ ነው። ኢትዮጵያ አና ሕንድ ለስትራቴጂካዊ ውይይት፣ የጋራ ልምምዶች፣ የፖሊስ ሥልጠና፣ ወታደራዊ የሕክምና ትብብርና ከሕንድ የመከላከያ መሣሪያ አምራቾች ጋር ሽርክና ለመፍጠር በመደበኛነት አሠራሮችን ፈጥረዋል። ከዚህ ባሻገርም ኢትዮጵያ ሕንድ ባስተናገደችው የተባበሩት መንግሥታት የሠላም አስጠባቂ ኃይል አስተዋጽኦ ያላቸው አገራት ጉባዔ (UN Troop Contributing Countries Chiefs’ Conclave) ላይ መሳተፏ ከንግድና ኢንቨስትመንት ባሻገር የአገራቱን የጋራ ደህንነት ትስስር ያጠናክራል።

ከብሪክስ እና ከቡድን 20 አኳያ

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን መቀመጫ እንዲሁም ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ሦስተኛዋ የግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት በመሆኗ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ቀንድ ያላት ወሳኝ ሚና ሕንድ በአፍሪካ ለሚኖራት የረጅም ጊዜ አጋርነት ተመራጭ ያደርጋታል። በኒው ዴልሂ የሚገኘው የኦብዘርቨር ምርምር ፋውንዴሽን አማካሪ የሆኑት ሳሚር ባታቻሪያ የጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የኢትዮጵያ ጉብኝት ከሕንድ-አፍሪካ ግንኙነት አንፃር ወሳኝ ነው ብለውታል። የሕንድ መንግሥት ቀጣዩን የሕንድ-አፍሪካ ፎረም (India-Africa Forum Summit-IAFS) በኢትዮጵያ ለማካሄድ ፍላጎት እንዳለው ያነሱት ሳሚር ባታቻሪያ ከዚህ አንፃር ጉብኝቱ ምክንያታዊ እንደሆነ ነው የገለጹት።

የሞዲ የኢትዮጵያ ጉብኝት የአፍሪካ ኅብረት በቡድን 20 መንግሥታዊ ፎረም ውስጥ ካለው ሚና አንፃር ሊታይ እንደሚገባውም ያነሳሉ።

ይሁን እንጂ የአፍሪካ ኅብረት አባል የሆነችው ደቡብ አፍሪካ በዚህ ዓመት የቡድን 20 ጉባዔን ባዘጋጀችበት ወቅት አሜሪካ ፕሪቶሪያን በአገሪቱ ውስጥ ባሉ አናሳ የነጮች ማኅበረሰብ ላይ አድልዎ እንዳደረገች በመክሰስ ራሷን ከተሳትፎ ውጭ አድርጋለች። በአንፃሩ አሜሪካ ቀጣዩን የቡድን 20 ጉባዔ ስታስተናግድ ደቡብ አፍሪካ በተጋባዥ አገራት ዝርዝር ውስጥ እንደማትካተት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይፋ አድርገዋል። እናም የአፍሪካ ኅብረት የቡድን 20 ጉበዔ ተሳትፎ ከዚህ አኳያ የሚታይ ይሆናል። ደቡብ አፍሪካ ከቡድን 20 ጉባዔ ላይ ከተገለለች የአፍሪካ ኅብረት ተሳትፎ እንደ አሕጉራዊ ተቋም ጠንካራ አቋም ሊያዝበት ይገባል። “የአፍሪካ ኅብረት በዚህ ጉዳይ ላይ አቋም መውሰድ አለበት፤ ለዚህም ነው የጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ የኢትዮጵያ ጉብኝት አስፈላጊ የሆነው” ሲሉ ትኩረቱን አፍሪካን ባደረገ ጂኦፖለቲካ ላይ ጥናት የሚያካሂዱት ሳሚር ባታቻሪያ የሚሞግቱት።

የኢትዮ-ሕንድ ግንኙነት ከታሪካዊ የንግድና የልማት ድጋፍ ወደ ዘመናዊ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ተሸጋግሯል። ይህም ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል በመሆኗ ያላትን ሚና በመጠቀም የዓለም አቀፉን የደቡብ ደቡብ ድምጽ ለማጉላት፣ ፍትሃዊ ዓለም አቀፍ አስተዳደር፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተግባራዊ እርምጃ፣ ዲጂታል መሠረተ ልማት እና ቴክኖሎጂ ላይ በማተኮር ሁለቱም አገራት እንደ ሰው ሰራሽ አስተውህሎት፣ ታዳሽ ኃይል፣ ጤና እና መከላከያ ባሉ ቁልፍ ዘርፎች ላይ ትብብራቸውን ለማጠናከርና በዓለም መድረኮች ላይ ጠንካራ የጋራ አቋም ለመያዝ ተስማምተዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ



46

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

ገጽታ ውስጥ ልዩ ሥፍራ የያዘች አገር ነች። በአፍሪካ በፍጥነት እያደጉ ካሉ አገራት አንዷ እና ቁልፍ የዲፕሎማሲ ማዕከል እንደመሆኗ መጠን፤ በሕንድ-አፍሪካ የልማት አጋርነት ረገድ ሰፊ ተሳትፎን ትወክላለች። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝትም ሕንድ ለአፍሪካ እንደ ገበያ ብቻ ሳይሆን እንደ ዕድገት አጋር መሆኗን ያሳያል። ይህ አካሄድ ሕንድ በአፍሪካ አገራት ውስጥ ለረጅም ጊዜ ያቆየችውን የአቅም ግንባታ፣ የክህሎት ልማት እና የመሠረተ ልማት ድጋፍ በማሳያነት መጥቀስ ይቻላል።

ከደቡብ ደቡብ ትብብር አኳያ

የኢትዮ-ሕንድ ግንኙነት ባለፉት አሥርት ዓመታት በከፍተኛ ሁኔታ ዕድገት አሳይቷል። ከቀደምት የንግድ ልውውጦችና የልማት ድጋፎች አልፎ ወደ ዘመናዊና ስትራቴጂካዊ አጋርነት እየተሸጋገረ፤ በጋራ እሴቶችና ፍላጎቶች ላይ የተመሠረተ ሆኗል። በታሪክ ሕንድ ለኢትዮጵያ ቁልፍ የልማት አጋር ሆና ቆይታለች። እንደ ትምህርት፣ ግብርና እና የአቅም ግንባታ ባሉ ዘርፎች ትደግፋለች። ከዚህ አልፎ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ እያደገ የመጣው ተጽዕኖ ፈጣሪነቷ ከሕንድ ጋር ሰፊ ጥምረት ለመፍጠር እርሾ ሆኗል።

ኢትዮጵያ በቅርቡ ሕንድ የምትገኝበትን የብሪክስ አባል አገራት ጥምረት በመቀላቀል ሽርክናው አዲስ ገጽታ እንዲላበስ አድርጋለች። ሁለቱም አገራት የዓለም አቀፍ ደቡብ-ደቡብ ድምጽን በማጉላት ረገድ ወሳኝ ሚና እንዲጫወቱ አስችሏል። ኢትዮጵያ እና ሕንድ ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤትና የባለብዙ ወገን የፋይናንሥ ተቋማት ማሻሻያዎችን ጨምሮ የበለጠ ፍትሃዊ

ዓለም አቀፍ ሥርዓት እንዲፈጠር ጥረት እያደረጉ የመምጣታቸው መነሻም ይኸው የጋራ ፍላጎት ነው።

አገራቱ የትብብራቸውን ትኩረት እንደ የአየር ንብረት ለውጥ ያሉ አጣዳፊ ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶች ላይ በማድረግ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ መገንባትና ለሁሉን አቀፍ ዕድገት ቅድሚያ የሚሰጡ ዘላቂ መፍትሄዎችን ይደግፋሉ። እንደ ሰው ሰራሽ አስተውህሎት፣ የጤና አጠባበቅና መከላከያ ባሉ ስትራቴጂካዊ ዘርፎች ትብብርን ለማጠናከር በጋራ እየሠሩ ይገኛሉ። እነዚህ ትብብሮች የጋራ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ አጀንዳዎችን የመቅረጽ የጋራ አቅም እንዲፈጥሩ የሚያስችሉ ናቸው።

አውድ እና ተዛማጅነት

የ21ኛ ክፍለ ዘመን የዓለማችን ጂኦፖሊቲካ በኢንዶ-ፓስፊክ ክልል ውስጥ በሚታየው ክስተት እንደሚወሰን የመስኩ ተንታኞች ያምናሉ። ከዚህ አንፃር እያደገ የመጣው የሕንድ የጂኦ- ኢኮኖሚያዊ፣ የኢንዱስትሪ፣ የባሕር እና ወታደራዊ ኃይል በተለይም ከስትራቴጂካዊ አጋሮቿ ጋር በመተባበር በቀጣናው ጂኦፖሊቲካ ውስጥ ጉልህ ሚና የመጫወት ፍላጎት አላት።

በሌላ በኩል በምዕራብ እስያ፣ በሰሜን እና በምሥራቅ አፍሪካ የተደረቱ እና እርስ በርስ የተቆላለፉ ግጭቶች መብዛት 2024ን በዓለም አቀፍ የፖለቲካ ገጽታ ውስጥ ካሉት እጅግ ፈታኝ ዓመታት አንዱ እንዲሆን አድርጎታል። ይህም የሚሊዮኖችን ሕይወትና ኑሮ ያመሰቃቀለ፣ በቀጣናው እና ከዚያም አልፎ ያለውን ሠላም እና መረጋጋት አደጋ ላይ ሲጥል የተስተዋለ ነው።



47

ይህ ከመካከለኛው ምሥራቅ ውጥረት እስከ ዓለም አቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለቶች (Global Sup- ply Chains) መስተጓጎል ድረስ እየሰፋ ከመጣው ዓለም አቀፍ ቀውስ ጋር ተያይዞ ጥልቅ ትብብርን መፍጠር ይጠይቃል። ግዙፍ ኃያላን አገራት አፍሪካ ውስጥ ያላቸውን ተጽዕኖ እያሳደጉ ባሉበት በዚህ ወቅት የሕንድ ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ በዚህ ረገድ ተገቢ ቦታን መልሶ ለማግኘትና የቆዩ ግንኙነቶችን ለማጠናከር የሚደረገውን ጥረት ያንፀባርቃል።

በምዕራብ እስያ በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል ለረጅም ጊዜ የቆየው ግጭት (ሃማስ እና የፍልስጤም ጂሃዲ ቡድኖችን ያካተተ) መባባሱ

ለቀጣናዊ አለመረጋጋት ምልክት ሆኖ ቆይቷል። ክስተቱ በዓረቡ ዓለም ውጥረትን ከማባባሱ ባሻገር የውጭ (መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ) ተዋናዮችን ወደ ግጭት ስቧል። ለዚህ እንደ ምሣሌ የኢራን-እስራኤል ጥቃት እና የመልሶ ጥቃት፣ የእስራኤል-ሊባኖስ በየጊዜው የሚሰነዘሩ ዒላማ የተደረጉ ጥቃቶችና የመልሶ ጥቃት፣ የሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት፣ የየመን ግጭት፣ የሱዳን የእርስ በርስ ግጭት፣ የሶማሊያ የአል ሸባብ ቀውስና በሞዛምቢክ የካቦ ዴልጋዶን ቀውስ ማንሳት ይቻላል። እነዚህ ሁሉ ቀጣናዊ ፉክክርን ተኪ ባህሪ የሚያሳዩ ሲሆኑ አካባቢያዊና ቀጣናዊ



48

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

ተፅእኗቸው የቱን ያህል የሰፉ መሆኑንም ያሳያል።

በሰፊው የምዕራብ ሕንድ ውቅያኖስ (Western Indian Ocean- WIO) ክልል ውስጥ ያሉት እነዚህና ሌሎች መሰል ውስብስብ እና እርስ በእርስ የተያያዙ ግጭቶች የአገራት የአስተዳደርና የደህንነት መዋቅሮችን ያዳክማሉ፣ ዓለም አቀፍ ሽብርተኝነት፣ የተደራጀ ወንጀል እና ህገ-ወጥ የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ንግድ ያሉ ሰብዓዊ ቀውሶችና ግልጽ ሥጋቶችን ያባብሳሉ። በየብስ ላይ የተቀሰቀሰው ግጭት በሰፊው የምዕራብ ሕንድ ውቅያኖስ የባሕር ክልል ላይ ተጽዕኖ ሲያሳድር የባሕር ንግድን፣ የኃይል አቅርቦትን እና ቀጣናዊ ደህንነትንም ይነካል። በክልሉ ውስጥ የሚያልፉ ወሳኝ የዓለም የባሕር ንግድ መስመሮችን ደህንነት በተደጋጋሚ አደጋ ላይ መጣሉንም ልብ ይሏል።



49

ይህ ለሕንድ የማያቋርጥ ያለመረጋጋት ሥጋት የሚፈጥር በመሆኑ በሰፊው የባሕር መስመር ኢኮኖሚያዊና ጂኦፖለቲካዊ ፍላጎቶቿን ለማዝለቅ ስትራቴጂካዊ ሚዛን የሚያስጠብቁ አገራት እንደሚያስፈልጓት ግልጽ ነው። ምክንያቱም ይህ ክልል ለሕንድ ሠላምና ደህንነት መጠበቅ ወሳኝ በመሆኑ ነው። የሕንድ ብልጽግና በዚህ ክልል ውስጥ ከሚያልፍ የኃይልና የንግድ ልውውጥ ጋር በውስጣዊ መልኩ የተሳሰረ መሆኑ ደግሞ ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል።

ኒው ዴልሂ ይህን “ያለመረጋጋት ቅስት” ተብሎ የሚገለጸውን ቀጣና በቀጥታ ከሚተሳሰሩና ውቅያኖስና ባሕሩን ከሚዋሰኑ አገራት ጋር ግንኙነቷን በጥንቃቄ ማየት እንዳለባት ታምናለች። ምክንያቱም ለሕንድ ሚዛን መጠበቅ ወሳኝ በመሆኑ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ሚዛናዊ አካሄድ ሕንድ እንደ ተመራጭ የደህንነት አጋርና በክልሉና ከዚያም በላይ ሠላምና መረጋጋት ለማስፈን ወሳኝ አጋር ያስፈልጋታል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ በሦስት ጠቃሚ ክፍለ አሕጉሮች በሚገኙ አገራት ጉብኝት ማካሄዳቸው ቀጣይነት ባለው ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ውስጥ ወሳኝ በሆነው ስትራቴጂያዊ አውድ እና ዳራውን የሚያብራራ ወሳኝ መሰረት እንዳለው መገንዘብ ይቻላል።

ከዚህ አኳያ የጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ የኢትዮጵያ ጉብኝት ከላይ በጠተቀሱት አንድምታዎች ብቻ የተገታ አለመሆኑን በርካታ ማሳያዎች ማንሳት ይቻላል። ጉዳዩን ኢትዮጵያ እና ሕንድ ሊያገኙዋቸው ከሚችሏቸው ሦስት የጋራ ጥቅሞች አኳያ መመልከት ይቻላል። ለአብነት የቀይ ባሕር እና የአፍሪካ ቀንድ ለጋራ ደህንነት ጥቅሞች

የመልክዓምድራዊ ጠቀሜታን ወሳኝነት፣ የደቡብ-ደቡብ ትብብርን በማጠናከር የዓለም አቀፍ ደቡብ ድምጾችን ማጠናከር እና የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለጋራ ግቦች ማሳደግ የሚሉትን ማየት ይቻላል።

የአፍሪካ ቀንድ እና የቀይ ባሕር ገጽታና ሚና ከ21ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ጀምሮ በከፍተኛ ሁኔታ ተለውጧል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በቀጣናው ውስብስብ የሆነ የመሠረተ ልማት መተሳሰርና የንግድ ኮሪደሮች ከፍና ዝቅ የማለት አዝማሚያዎች ታይተዋል። አሁንም እንደቀጠሉ ናቸው። ይህ ደግሞ በበርካታ አገራት ውስጥና በአገራት መካከል ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትስስር ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል። በዚህ የተነሳ እንደ ኢትዮጵያ እና ሕንድ ያሉ አገራት ያላቸው ጂኦስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ እንዲጨምር አድርጎታል።

ከዚህም በላይ ሕንድ ከአፍሪካ ቀንድ ጋር ያላት ግንኙነት በሠላም ማስከበር ተልዕኮዎችና በፀረ- የባሕር ላይ ውንብድና መከላከል ብቻ የተገደበ ቢሆንም ከቀጣናው ውጭ ያሉ ኃይሎች ያላቸው ሰፊ እንቅስቃሴ የሕንድ ውቅያኖስን ወደ ስትራቴጂካዊ ማዕከልነት ቀይሮታል። በዚህ ሳቢያ ኢንዶ-ፓስፊክ፣ ቀይ ባሕር እና የአፍሪካ ቀንድ የሚሸፍነው በምዕራባዊ ሕንድ ውቅያኖስ ውስጥ ያሉ ውስብስብና እርስ በእርስ የተያያዙ ግጭቶች የሚፈጥሩትን ሥጋት ለመቀነስ ኢትዮጵያ እና ሕንድ በጋራ እንዲሰሩ የሚያስገድዳቸው ሆኗል።

በእነዚህ ክልሎች ውስጥ ያለው የማያቋርጥ ተለዋዋጭነት ኢትዮጵያ እና ሕንድ በሰፊው የባሕር አካባቢ ኢኮኖሚያዊ እና ጂኦፖለቲካዊ ፍላጎቶቻቸውን ለመጠበቅ ስትራቴጂካዊ ሚዛን



50

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

መጠበቅ እንዳለባቸው ያሳያል። ስለዚህ የጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ የአዲስ አበባ ጉብኝት ሕንድ ለዓለም አቀፍ አስተዳደር፣ ለግንኙነትና ለባሕር ደህንነት ወሳኝ በሆነ ቀጣና ውስጥ የፖለቲካ ተሳትፎን ማጎልበትና ስትራቴጂካዊ ቦታን መልሶ ለማግኘት ያላትን ፍላጎት የሚያመላክት ነው።

እንደሚታወቀው ቀይ ባሕር ወሳኝ የባሕር የንግድ መስመር ነው። በቀጣናው ውስጥ የሚፈጠር ማንኛውም ግጭት በዚህ ወሳኝ ኮሪደር ላይ ሠላምን ብቻ ሳይሆን የባሕር ደህንነትንም አደጋ ላይ ይጥላል። ይህም ቀድሞውኑ በቋፍ የነበረውን የቀጣናውን ሠላም ይበልጥ ያናጋዋል። በተለይ በእስራኤል እና በሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት መካከል የሚከሰተው ግጭት ሁኔታውን እጅጉን ፈታኝ የሚያደርገው በመሆኑ የኢትዮጵያ እና የሕንድ አጋርነት ከዚህ አውድና ተዘማጅነት የሚቆራኝ ጭምር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ያለው አንድምታ ከፍ ያለ ነው።

የሕንድ አለመረጋጋት ቅስት

“የአለመረጋጋት ቅስት” (Arc of Instabili- ty) የሚለው ጽንሰ-ሀሳብ ፕሮፌሰር ፖል ዲብ ለመጀመሪያ ጊዜ እ.አ.አ በ1999 የፓስፊክ ደሴት ሰንሰለትን በአውስትራሊያ የደህንነት አውድ ውስጥ ለመግለጽ የተጠቀሙበት ቃል ነው። ከጊዜ በኋላ ይህ ጽንሰ-ሀሳብ በበርካታ ምሁራንና ስትራቴጂስቶች ለተለያዩ መልክዓምድራዊ እና ጂኦፖለቲካዊ አውዶች መጠቀም ጀመሩ። ቃሉ በአንድ አካባቢ አለመረጋጋት እንዴት ሊስፋፋ እንደሚችልና ዓለም አቀፍ ደህንነትን እንዴት ሊጎዳ እንደሚችል የሚያሳይ የጂኦፖለቲካ ፅንሰ- ሀሳብ ሲሆን ብዙውን ጊዜ ጽንፈኛ ቡድኖች፣

የአየር ንብረት ቀውሶችና የተደራጁ ወንጀሎች የሚፈጥሩትን ሥጋት የሚያካትት ነው። ጽንሰ- ሃሳቡ የቅስቱ አገራት እርስ በእርስ የተሳሰሩ መሆናቸውን ለማሳየትና በአንድ አገር ውስጥ የሚከሰት አለመረጋጋት በአጎራባች አገራት ውስጥ ከፍተኛ የፖለቲካ፣ የወታደራዊና የኢኮኖሚ ተጽዕኖ ሊያስከትል እንደሚችል ያሳያል።

ሕንድ የምዕራባዊ ሕንድ ውቅያኖስን “አለመረጋጋት ቅስት” ቀጣናን የምትመራው ስትራቴጂካዊ ነፃነትን ከተግባራዊ ተሳትፎ ጋር በማመጣጠን፣ የንግድ መስመሮችን፣ የኃይል አቅርቦትን በማስጠበቅ እና ከሌሎች ተቀናቃኝ ኃይሎች ተጽዕኖ ጋር ያላትን ፍጥጫ በበላይነት ለመወጣት ከኢትዮጵያ፣ ከማደጋስካር እና ሌሎች የደሴት አገራት ጋር ጥልቅ ግንኙነት መፍጠርን እንደ ስትራቴጂክ ግብ አስቀምጣለች። በዚህም ቀጣናዊ ደህንነትና ዕድገት ለሁሉም (Security and Growth for All in the Region-SAGAR) እና የኢንዶ-ፓስፊክ ውቅያኖስ ተነሳሽነት (In- do-Pacific Oceans Initiative-IPOI) በሚሉ ማዕቀፎች ሥር ጠንካራ የባሕር ዲፕሎማሲ፣ የባሕር ኃይል ማጠናከርና አስፈላጊ የባሕር መስመሮችን ለመጠበቅ እና በጂኦፖሊቲካዊ ፉክክር ውስጥ እንደ ቁልፍ የኢንዶ-ፓስፊክ ኃይል ለመሆን ያላትን ሚና መጠቀምን ትሻለች።

እ.አ.አ 2015 በጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ እንደተጀመረ የሚነገርለት ቀጣናዊው ደህንነትና ዕድገት ለሁሉም (SAGAR) ኢኒሼቲቭ ጠንካራ ሽርክናዎችን መገንባትና ደህንነቱ የተጠበቀ፣ የተረጋጋና የበለፀገ የባህር ቀጣና መፍጠርን ታሰቢ ያደረገ ነው። ሕንድ በኤደን ባሕረ ሰላጤ እና



51

በሌሎች ወሳኝ የንግድ ኮሪደሮች በሚስተዋለው አለመረጋጋት ምክንያት ከውጭ ለምታስገባው የኢነርጂ አቅርቦት እና ለንግድ ወሳኝ የሆኑ የባሕር መስመሮችን (Sea Lines of Communi- cation-SLOCs) በመጠበቅ ኢኮኖሚያዊ ደህንነቷን ለማረጋገጥ ቅድሚያ ትኩረት ትሰጣለች። በተጨማሪም እንደ ሞሪሺየስ፣ ሲሼልስ እና ማደጋስካር ላሉ የደሴት አገራት በባሕር ፖሊስና ደህንነት ረገድ ድጋፍ በመስጠት ተመራጭ አጋር ለመሆን ትጥራለች።

በሌላ በኩል እንደ ሽብርተኝነት እና የባሕር ላይ ውንብድና ያሉ ሥጋቶችን ለመግታት የጂኦፖለቲካ ፉክክሩን በድል አድራጊነት ለመወጣት ከቀጣናው አገራት ጋር በአጋርነት መሥራትን እንደ አማራጭ ስትራቴጂ ትጠቀምበታለች። ለዚህ ነው ከምዕራብ እስያና ከአፍሪካ ቀንድ አገራት ጋር ጥብቅ አጋርነት መፍጠርን አስልታ የምትንቀሳቀሰው። ይህ እንቅስቃሴ የሕንድ ዋና ዋና የብሔራዊ ጥቅም ዘርፎች በተለይም የፋርስ ባሕረ ሰላጤ፣ የዓረብ ባሕረ ገብ መሬት፣ ቀይ ባሕር እና የምሥራቅ አፍሪካ

የባሕር ዳርቻ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የቅርብ ጊዜ ጉብኝት በኢትዮጵያ፣ ኦማን እና ዮርዳኖስ እንዲሆን የተፈለገውም ለዚህ ይመስላል።

የሕንድ የኢነርጂ ደህንነት፣ ጠንካራ የዳያስፖራ ትስስር እና በምዕራብ እስያና በአፍሪካ ከፍተኛ የንግድና የኢንቨስትመንት አቅም ለኢኮኖሚ ዕድገትና ብልጽግናዋ ወሳኝ ናቸው። ሆኖም ግን እነዚህ ግኝቶች ለደካማ የደህንነት አካባቢና ለጂኦፖሊቲካዊ ተለዋዋጭነት የተጋለጡ ናቸው፣ ይህን ተጋላጭነት ለመቀነስ ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂካዊ አቀራረብን መጠቀምን ይጠይቃል።

በሕንድ ውቅያኖስ ውስጥ የሕንድን ጂኦ-ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ በመንተራስ የባሕር ዘርፍ 95 በመቶ ያህል የአገሪቷን የንግድ እንቅስቃሴ በማመቻቸት እንዲሁም 70 በመቶ የንግድ እሴቷን በመያዝ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ባለፉት አሥርት ዓመታት ሕንድ ከውጭ የምታስገባው የኃይል (Energy) መጠን በባሕር መስመሮች ላይ ያለው ጥገኛነት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። ይህ ማለት ከ40



52

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

በመቶ በላይ የሚሆነው ድፍድፍ ነዳጅ እና 70 በመቶ የሚሆነው የተፈጥሮ ጋዝ አቅርቦት በምዕራባዊ ሕንድ ውቅያኖስ ክልል ውስጥ የሚያልፍ ነው።

ሌላው የሕንድ ዳያስፖራ ወሳኝ የኢኮኖሚ ኃብት ነው። በተለይም በምዕራብ እስያ 8 ነጥብ 7 ሚሊዮን እንዲሁም በአፍሪካ 3 ሚሊዮን ጠንካራ የሕንድ ዳያስፖራዎች በየዓመቱ ከ30 ቢሊዮን በላይ የአሜሪካ ዶላር የገንዘብ ልውውጥ ያካሂዳሉ። ለአብነት በተጠናቀቀው የአውሮፓዊያን ዓመት (2025) ሕንድ ከዜጎቿ ከሪሚታንስ 136 ነጥብ 46 ቢሊዮን ዶላር ማግኘቷን የአገሪቷ ማዕከላዊ ባንክ (Reserve Bank of India-RBI) ባለፈው ጥቅምት ይፋ ያደረገው ዘገባ ያስረዳል። ይህ ደግሞ ኢኮኖሚውን ከማረጋጋት ባለፈ ሕንድ ያለባትን የንግድ ክፍተት ግማሽ ያህሉን በመሙላት ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል። ለዚህ ሕንድ በግጭቶችና በቀውሶች ሳቢያ እንዲህ ያለውን ጥቅሟን አሳልፋ መስጠት ፈጽሞ አትሻም።

እነዚህ ከምዕራብ እስያ እና ከአፍሪካ ጋር የተጠናከሩ የኢኮኖሚ ግንኙነቶች ለሕንድ ያላቸው ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ግልጽ ነው። ሕንድ ኢኮኖሚያዊ እና ጂኦፖለቲካዊ ፍላጎቶቿን ለመጠበቅ የተረጋጋ የደህንነት አካባቢ ያስፈልጋታል። እናም እንደ ኢትዮጵያ ካሉ ወሳኝ አገራት ጋር በአጋርነት መሥራት የአለመረጋጋት ቅስቱን (Arc of Instability) ሥጋት ለመቆጣጠር መተኪያ የሌለው ስልት አድርጋ ትወስዳለች። እነዚህ ጥረቶች ሕንድን በተራዘመ የባሕር ክልል ውስጥ ከሌሎች ጋር በመሆን ውጥረትን ለመግታትና በዚህ ቁልፍ ቀጣና የኢኮኖሚና የደህንነት ትብብር በማሳደግ የመረጋጋት እና የዕድል ቅስት ለመፍጠር

ያስችላታል።

አንድምታው ሲጠቃለል

ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ ወደ ኢትዮጵያ፣ ዮርዳኖስ እና ኦማን ያደረጉት የሦስት ቀጣናዎች ጉብኝት በብዙ የፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ ተንታኞች ዘንድ ጠቃሚ ስትራቴጂያዊ ስኬት እንደሆነ ተገልጿል። ይህም የሕንድን የባለብዙ ወገን ዓለም አቀፍ ተሳትፎ በማሳደግ ረገድ ትልቅ ለውጥ እያመጣ ስለመሆኑ የሚያሳይ ነው። ይህ ከሌሎች የብዙ አገራት ጉብኝት ይልቅ ዓላማ ያለው መልዕክት ያዘለ ሲሆን በየትኛውም መለኪያ ሚዛን የሚደፋ ሆኖ ታይቷል።

ሕንድ ታሪክ፣ ጂኦፖለቲካዊ ስትራቴጂ እና መፃኢው ዓለም በሚገናኙበት ወሳኝ ቀጣና ተጽዕኖዋን እያሰፋች ስለመሆኗ መስካሪ ነው። አገሪቷ በመካከለኛው ምሥራቅና በአፍሪካ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የባሕል ግንኙነቶችን ለማጠናከር ያላት ፍላጎት ከመደበኛ የዲፕሎማሲ ጉብኝት በላይ እየሆነ መምጣቱንም ያመላክታል። ይህ ደግሞ የሕዝብ ለሕዝብ ቅርርብን፣ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታን፣ የረጅም ጊዜ ግቦችን እና ዲፕሎማሲያዊ ተዓማኒነትን አቅፏል። እነዚህ ጉብኝቶች ሕንድ በአፍሪካ ቀንድ፣ በመካከለኛው ምስራቅ እና በኢንዶ-ፓስፊክ ክልል አወዛጋቢ ግን እርስ በእርስ የተያያዙ የጂኦፖለቲካ፣ የጂኦ- ኢኮኖሚ እና የጂኦ-ደህንነት ገጽታዎች ላይ ያላትን ሚና ዓለም ይወቀው እያለች መሆኗንም ጠቋሚ ናቸው።

የጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የኢትዮጵያ ጉብኝት ከፍተኛ የጂኦፖሊቲካ እና የኢኮኖሚ አንድምታ ያለው ሲሆን ይህም በሕንድ እና



53

በአፍሪካ ግንኙነት ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ሆኗል። ጉብኝቱ ሕንድ ከአፍሪካ ቀንድ ጋር ግንኙነቷን ለማጠናከር ያላትን ስትራቴጂካዊ ፍላጎት መሬት ያስያዘ፣ በንግድ፣ በመሠረተ ልማት፣ በጤና፣ በትምህርት እና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያለውን ትብብር የሚያጠናክር ነው። በተጨማሪም ጉብኝቱ ሕንድ ከአፍሪካ ጋር ባላት ሰፊ ግንኙነት ውስጥ ኢትዮጵያ እንደ ቁልፍ አጋር በመሆን ያላትን ሚና ያጎላል። በደቡብ- ደቡብ ትብብር በኩልም የጋራ ልማትን ለማሳለጥ መደላድል የሚፈጥር ይሆናል።

ኢትዮጵያ እና ሕንድ ስምንት የመግባቢያ ሰነዶች ተፈራርመዋል። በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመረጃ ማዕከል ማቋቋም የሥምምነቱ አንድ አካል ነው። በጥቅሉ ሁለቱ አገራት በቡድን-20 የጋራ ማዕቀፍ ሥር የዕዳ መዋቅራዊ ማስተካከያ፣ በንግድ፣ በመከላከያ፣ በዲጂታል መሠረተ ልማት፣

በጤና፣ በባሕላዊ ሕክምና፣ በማዕድን ማውጣት፣ በብሪክስ ማዕቀፍ እና በሌሎች ጉዳዮች ሰፊ ትብብር ለማድረግ ተስማምተዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ከፍ ያለ የዲፕሎማሲ እና ስትራቴጂካዊ አጋርነት መፍጠር ያስቻለና ከባሕላዊ ወዳጅነት ወደ መከላከያ፣ ንግድ እና አስተዳደር ያደገ ጥልቅ የባለብዙ ገጽታ የሽርክና ማማ ተሸጋግሯል።

በአፍሪካ ቀንድ የሚስተዋለው ጂኦፖለቲካዊ ገጽታ በሐብት ክፍፍል ሳቢያ የተፈጠሩ አለመግባባቶች፣ በውክልና ግጭቶች እና በባሕር መሻቶች ምክንያት እየጨመረ ባለው ውጥረት መሃል እንዲህ ዓይነት ያደገ አጋርነት መፍጠር ብሔራዊ ጥቅምን በማስጠበቅ በኩል ጠቃሜታው ላቅ ያለ ነው። የሽርክና ማማው ፋይዳም በዚህ ልክ የሚመነዘር ቁልፍ የዲፕሎማሲ ውጤት ነው።



54

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

ፖለቲካ



55

ምክክር ለሀገር ክብር

አገራት የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች፣ ግጭቶች እና አለመግባባቶች ዘመን እና ወቅቱን በሚዋጁ ስልቶች ለመፍታትና መፍትሔ ለመስጠት የተለያዩ አማራጮችን ይጠቀማሉ። ችግሮቹን ለመፍታት መንግሥታቱ የሚጠቀሟቸው ዘዴዎች የችግሮቹን ስፋት፣ ዓይነት እና አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገቡ ናቸው። እነዚህ የመፍትሔ መንገዶች ታዲያ እንደ ዘመኑ ተለዋዋጭ ናቸው፤ በአንድ ወቅት ችግሮችን ለመፍታት የተሻለ ነው የተባለው በቀጣዮቹ ዓመታት በሌላ የመፍትሔ መንገድ ሊለወጥ ይችላል።

አለመግባባትና ችግሮች ያጋጠሟቸው አገራት መግባባትን ለማምጣት የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ። ከእነዚህ ውስጥ

በፍቅርተ ባልቻ



56

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

አንዱ እና ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በበርካታ አገራት ተግባራዊ እየሆነ የመጣው አገራዊ ምክክር ነው። ምክክር በበርካታ የዓለም አገራት ላይ ግጭት እና አለመግባባቶችን ለመፍታት ተግባራዊ ተደርጓል።

በምስራቅና መካከለኛው አውሮፓ የኮሚኒዝም ሥርዓት ያጋጠመውን ችግር ተከትሎ ፖላንድ፣ ሃንጋሪ፣ ቼኮዝሎቫኪያ፣ ምስራቅ ጀርመን እና ቡልጋሪያ በተከታታይ ለምክክር መቀመጣቸው ይታወሳል። ወደ አፍሪካ መለስ ስንል በርካታ የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ (ፍራንኮፎን-አፍሪካ) አገራት በዜጎች እና ሥልጣን በያዙ መሪዎች መካከል እያደገ የመጣው ልዩነት በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ አገራዊ ምክክር እንዲያደርጉ አስገዳጅ ሁኔታ መፍጠሩን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።

ቀደም ሲል ከተጠቀሱትና ሌሎች አገራትም ላይ ከተካሄዱ ምክክሮች መካከል ስኬታማ የሆኑ እንዳሉ ሁሉ ያልተሳካላቸው አገራትም ይገኛሉ። ለስኬታማነቱም ሆነ ለውጤት አልባነቱ የተለያዩ

ምክንያቶች ይነሳሉ። የምክክሩ ሂደት የሚመራበት መንገድ፣ ገለልተኛ እና አካታችነት ለስኬታማነቱ ጉልህ አስተዋጽኦ ካላቸው ነጥቦች ውስጥ ናቸው። በአንጻሩ የምክክሩን ሂደት በጥንቃቄ ያልመሩና የውጭ ጣልቃ ገብነት በነበረባቸው አገራት ምክክሮቹ ስኬታማ አልነበሩም።

ምክክር በኢትዮጵያ …

ወደ አገራችን መለስ ስንል በኢትዮጵያ ብዝሃነት፣ የተለያየ ባሕል እና የአኗኗር ዘይቤ ያላቸው ብሔር ብሔረሰቦች መገኛ ከመሆኗ አንጻር የተለያዩ እሳቤዎች በፖለቲካ ውስጥ መኖራቸው እርግጥ ነው። እሳቤዎቹና ልዩነቶቹ በአገር ግንባታ ላይ የሚነገረውን የታሪክ አረዳድ የተዛባ ከማድረጋቸው ባሻገር፣ የአገረ መንግሥት መለያ ምልክት በሆነው ሰንደቅ ዓላማ እንዲሁም ሕገ-መንግሥቱ ላይ የጋራ መግባባት እንደሌለ ያመለክታል።

ቀደም ሲል የተመላከቱትን እና ሌሎችንም



57

ልዩነቶች በአገራዊ ምክክር አማካኝነት መግባባት ላይ መድረስ እንደሚገባ በማመን ፈርጀ ብዙ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው። አገሪቷ ለዘመናት እየተንከባለሉ የመጡ ፖለቲካዊ ችግሮቿንና ጫፍ የረገጡ ልዩነቶችን በውይይት በማርገብ ለትውልዱ የምትመች አገር ለመገንባት አገራዊ ምክክር ለማካሄድ ጉዞ ጀምራለች።

ምክክሩን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያገለግሉ የሕግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት አጠቃላይ እንቅስቃሴውን የሚመራ ተቋም ተመስርቷል፤ የኢትዮጵያ ምክክር ኮሚሽን በአዋጅ 1265/2014 መሰረት ተቋቁሟል። የካቲት 2014 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስራ አንድ ኮሚሽነሮች መሰየማቸውን ተከትሎ ኮሚሽኑ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ገብቷል።

በበርካታ ችግሮች ውስጥ እያለፈችና ስብራቶች እየገጠሟት ያለችው ኢትዮጵያ ከችግሮቿና ከስብራት ታሪኮቿ ለመውጣት ሁነኛ መፍትሄ የሆነውን አገራዊ ምክክር ለማካሄድ የጀመረችው ጉዞ በስኬት እንዲጠናቀቅ መንግሥት በምክክሩ መግባባት ላይ የሚደረስባቸውን ድምዳሜዎች ተግባራዊ ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየበት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ኮሚሽኑ በአዋጅ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በተለያዩ ሂደቶቹ ስለ አገራዊ ምክክሩ ዓላማና አስፈላጊነት አንስተዋል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥቅምት 2018 ዓ.ም ስብሰባውን ባካሄደበት ወቅት ይህ አገር አቀፍ አካታች ውይይት ነባር ችግሮቻችንን ለመፍታት እንደሚያግዝ፤ ለተግባራዊነቱም መንግሥት ቁርጠኛ እንደሆነ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመደመር መንግሥት መጽሐፋቸው “በሀገራችን የሚደረገው ሀገራዊ ምክክር የተለያዩ ሐሳቦች በአንድ መድረክ ቀርበው፣ በውይይትና በምክክር ጎልብተው፣ አሰባሳቢና አስማሚ ሆነው የሚወጡበት፤ ሁሉም ስለ ሀገር የሚያገባው አካል በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ አዋጥቶና ተነጋግሮ መግባባት የሚፈጥርበት ምኅዳር ነው። በውይይትና በምክክር ወደ መግባባት የሚደረስበት መንገድ ነው” ሲሉ የአገራዊ ምክክሩን አስፈላጊነት ገልጸዋል።

“በአገራችን የፖለቲካ ታሪክ ከገጠሙን እጥረቶች አንዱ አገራዊ ምክክር ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአገረ መንግሥት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ሕዝብ ተመካክሮ፣ የጋራ መግባባት ላይ ደርሶ፣ መግባባት ላይ የደረሰባቸውን በሕግና በሥርዓት አጽንቶ፣ ያላግባቡትን ጉዳዮች ደግሞ ለወደፊት ምክክሮች አቆይቶ አለመጓዙን ጠቅሰዋል። “. . .በዚህ የተነሣ በየጊዜው ቅሬታ፣ ኩርፊያ፣ አብዮት፣ ዐመጽ ይፈጠራል። ነገሮች በተናጠል እየቀረቡ ለፖለቲካ ነጋዴዎች ምቹ ሁኔታ ይመቻቻል። ሁለንተናዊ ዕይታ ይጠፋል። ሀገራዊ ምክክር ይሄን የዘመናት ስብራት የሚጠግን ነው” በማለት ገልጸዋል።

አገራዊ ምክክሩን በተመለከቱ ንግግሮቻቸው በታሪክ ሂደት ተደጋግሞ የማይገኘውን ይህን ታሪካዊ የምክክር አጋጣሚ በሚገባ መጠቀም ሁላችንንም አሸናፊ ያደርገናል የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከተቃርኖ ይልቅ ተዛምዶን በማጠናከር፣ መጓደልን በመሙላት ኢትዮጵያን ተስፋ ያላት አገር ማድረግ የአገራዊ ምክክሩ ዓላማ እንደሆነ ይጠቁማሉ። በኃይል አማራጭ የሀሳብ ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን ለመፍታት



58

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

የሚደረግ ጥረት ጊዜያዊ አሸናፊና ተሸናፊ ፈጥሮ ከማለፍ በዘለለ ለችግራችን ዘላቂ መፍትሄ እንደማያስገኝ፤ ኢትዮጵያ እያካሄደቸው ባለው ምክክርም የሚከስር እንደሌለና ይልቁንም በሂደቱ አገር አሸናፊ እንደምትሆን ነው የገለጹት።

አሁን አሁን በበርካታ የዓለም አገራት ዘንድ በአገር ውስጥና በተለያዩ አገራት መካከል ግጭቶች፣ አለመግባባቶች እና የሀሳብ ልዩነቶች ሲያጋጥሙ ወደ ስምምነት እንዲመጡ የሚደረግባቸው የተለያዩ አማራጮች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው። ከእነዚህ መካከል ድርድር (Negotiation)፣ ሽምግልና (Mediation)፣ ክርክር (Argument)፣ ውይይት (Discussion)፣ የግልግል ዳኝነት (Arbitration) እንዲሁም ምክክር (Dialogue) ይጠቀሳሉ።

ድርድር ተቀናቃኝ ኃይሎች በቀጥታ የሚሳተፉበት ሂደት ሲሆን ያለ ሦስተኛ ወገን አስማሚነት ከስምምነት ለመድረስ በሚደረገው ጥረት የውሳኔ ሃሳቦችን በማፍለቅ ወደ ስምምነት ለመድረስ የሚደረግ ጥረት ነው። ለድርድሩ የሚቀመጡት ወገኖች ተቀባይነት ያለው ታዛቢ ይሰይማሉ።

ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ግጭት ውስጥ ያሉ ወገኖች በመካከላቸው የተፈጠሩ ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን ለመፍታት በፈቃዳቸው ተቀባይነት ባለው ሦስተኛ ወገን አማካኝነት የሚደረግ የግጭት ወይም የአለመግባባት መፍቻ ሌላው መንገድ ሽምግልና ነው።

ሌላው የግጭት መፍቻ መንገድ በሀሳብ ፉክክር ላይ ትኩረቱን የሚያደርገው ክርክር ነው። ተከራካሪ ወገኖች የሚደግፉት ሀሳብና አቋም አሸናፊ እንዲሆን ለማድረግ በተቃራኒያቸው ያሉ ወገኖች የሚያራምዱት ሀሳብ ስህተት መሆኑን ለማስረዳትና ለማረጋገጥ ጥረት ያደርጋሉ።

ፅንሰ ሀሳቦች ላይ ለመነጋገር ብሎም መረጃና ዕውቀት የማካፈል ዓላማ ያለው የግጭት መፍቻ መንገድ ውይይት ነው። ለተነሱ ጉዳዮች መፍትሔና ምላሽ ለማፈላለግ ጥረት የሚያደርግ ሲሆን ግጭት እና ልዩነት ሊፈጥሩ ወይም ሊያባብሱ የሚችሉ ሁኔታዎችን



59

ለማስወገድ ይሞክራል።

ተቀናቃኝ አካላት ችግራቸውን ለግልግል ዳኞች በማቅረብ ውሳኔ የሚያገኙበት መንገድ ደግሞ የግልግል ዳኝነት የምንለው ነው። ተቀናቃኝ ኃይሎች በጋራ በሚያደርጉት ስምምነት ፍርድ የሚሰጧቸውን ዳኞች ይመርጣሉ። እነዚህ ዳኞች በተቀናቃኞቹ ኃይሎች መካከል ውሳኔ የማሳለፍ ሙሉ ሥልጣን ይኖራቸዋል።

በአንድ አገር ውስጥ በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ እና ስር የሰደዱ ልዩነቶች ሲያጋጥሙ በበርካታ አገራዊ ባለድርሻ አካላት መካከል መግባባት ለመፍጠር በስፋት ተግባራዊ የሚደረገው ሌላው የችግር መፍቻ መንገድ ምክክር ነው። በአብዛኛው የአገራዊ ምክክር ባለቤትም ሆነ ዋነኛ ፈጻሚ ሕዝብ መሆኑ ከሌሎች ግለሰቦች ወይም ውስን ቡድኖች ከሚገኙባቸው የልዩነት ወይም የግጭት መፍቻ መንገዶች የተለየ ያደርገዋል።

አገራዊ ምክክሮች እንደ ሌሎቹ ውጤት ላይ ብቻ ሳይሆን በሂደቱ ላይ ጭምር የሚያተኩሩና ለሂደቱ አካታችነት፣ አሳታፊነት፣ ግልጽነትና ፍትሃዊነት ትኩረትና

ላቅ ያለ ዋጋ የሚሰጡ ናቸው። ከሚያስገኙት ውጤት እኩል ወይም በበለጠ ሁኔታ የሂደታቸው ቅቡልነት፣ አካታችነትና ተዓማኒነት ወሳኝ ነው።

“NATIONAL DIALOGUE Lessons Learned“በሚል ርዕስ በኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት (May 2022) የተዘጋጀው ሰነድ አገራዊ ምክክር የፖለቲካ ቀውስ በሚያጋጥምበት እና በድህረ ጦርነት ወቅት ባለድርሻ አካላትን በስፋት በማሳተፍ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ተግባራዊ የሚደረግ ስለመሆኑ አስፍሯል። የኢንስቲትዩቱ ሰነድ አያይዞ እንደጠቀሰው ምክክሩ ከውጭ አካላት ጣልቃ ገብነት ነጻ በሆነ መልኩ በአንድ አገር ውስጥ ያሉ ዋና ዋና የፖለቲካዊ ውሳኔ ሰጪ አካላትን እንዲሁም ሕዝቡን በስፋት በማሳተፍ ይከወናል።

የፖለቲካ አለመረጋጋት እንዲሁም ቀውሶችን በመከላከል ሊከተል



60

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

የሚችለውን የእርስ በእርስ ጦርነት ማስቀረት ከምክክሮቹ ጥቅሞች መካከል መሆናቸውን፤ ከሂደቱ የሚገኘው ውጤት ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ላሉ ልዩነቶች መፍትሔ በማበጀት የመንግሥት አስተዳደር ሥርዓት ላይ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት የሚያስችሉና ግልጽ በሆነ መንገድ መንግሥት እና ማኅበረሰቡን የሚያስተሳስሩ ውሎችን (new social contract) ወደ አሠራር በማምጣት የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ስለመሆኑም ሰነዱ አብራርቷል።

“Success and Failure of National Dialogue Selected Countries Cases Study: General Lesson to Ethiopia“ በሚል ርዕስ በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና ተመራማሪ በሆኑት አቶ ሱራፌል ጌታሁን የተሠራው ጥናት በበኩሉ “የአገር አቀፍ ምክክሮች ግጭቶችን ከስር መሰረታቸው ለመፍታት፣ ለግጭት መንስኤ የሚሆኑ ክፍተቶችን ከማረም ባሻገር አካታች በሆነ የውይይት ሂደት የዜጎችን መሰረታዊ

ፍላጎቶች ለማሟላት የሚያስችሉ መልካም አጋጣሚዎችን ያበጃሉ“ በማለት ምክክሮቹ ያላቸውን ፋይዳ ያብራራሉ።

አገራዊ ምክክሮችን እንደ አንድ የሰላም መገንቢያ መሣሪያ በመጠቀም ተግባራዊ እየተደረገ ሲሆን በተለይ በእስያ፣ አፍሪካ፣ መካከለኛው ምስራቅ እና ላቲን አሜሪካ አገራት በስፋት ተገልግለውበታል። ይህም በመሆኑ ከዚህ ቀደም ለግጭት አስተዳደር ይቋቋሙ የነበሩት ድርጅቶች በአገራዊ ምክክሮች ተተክተዋል። እነዚህ ምክክሮች በተለይ በማኅበረሰቡ ውስጥ ሰፊ ልዩነት ሲኖር አገራት የሚጠቀሙበት ሁነኛ መፍትሔ መሆኑንም የአቶ ሱራፌል ጥናት አስነብቧል።

ስለሆነም አገራዊ ምክክሮች እንደየአገራቱ ተጨባጭ ሁኔታ የተለያዩ ዓላማዎችን ለማሳካት ሊከናወኑ ይችላሉ። በአንድ አገር የተከሰቱ ከባድ የፖለቲካ ችግሮችን ወይም በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ መሠረታዊና ለአገር ሕልውና አስጊ የሆኑ ልዩነቶችን እንዲሁም ልዩነቶችን ወይም አለመግባባቶችን በዘላቂነት በመፍታት አገራዊ መግባባት መፍጠር ምክክሮች



61

የሚካሄዱባቸው ዓላማዎች ናቸው።

አገራዊ ምክክሮቹ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል መተማመንን ለማስፈን፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማጠናከርና ልዩነቶችን በምክክር የመፍታት ባሕል እንዲዳብር ያስችላሉ። እነዚህ ምክክሮች በዜጎች መካከል የተሻሻለ ማኅበራዊ ግንኙነት እንዲኖር ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር፤ ግጭቶችን በዘላቂነት የመፍታት ጉልህ ፋይዳም አላቸው።

በኢትዮጵያ የምክክር ኮሚሽኑን ለማቋቋም የወጣው አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበበት ወቅት የምክክር ሂደቱን አስፈላጊነት የገለጹት በምክር ቤቱ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) “በአገራችን በተለይ በፖለቲካ ልሂቃን መካከል በአገራዊ ጉዳዮች ላይ እየተፈጠረ የመጣውን ልዩነት መፍታት ለአገራዊ አንድነት መሰረታዊ ጉዳይ ነው። ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ያደረጉ አገራት ተሞክሮ እንደሚያሳው አካታች አገራዊ ምክክሮችን ማድረግ መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የተሻለ መግባባት እንዲኖር ያስችላል፤ ምክክር መተማመን እና በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተቀራርቦ የመሥራት ፖለቲካዊ ባሕልን ለማጎልበት ጠቃሚ ነው” ብለዋል።

ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) መጠነ ሰፊ የፖለቲካ ሽግግር በሚደረግበት ወቅት በብዙ ባለድርሻ አካላት መካከል መግባባትን እና ለችግሮች ዘላቂ መፍትሔን ለመፍጠር፤ እንዲሁም ጠንካራና ተቀባይነት ያለው አገረ መንግሥት ለመገንባት መደላድል የሚሆኑ አገራዊ የምክክር መድረኮች አስፈላጊና ተመራጭ መሆናቸውን፤ በተለያየ ጎራ የተሰለፉ የፖለቲካ ልሂቃንም ሆነ ሕዝቡ መሰረታዊ በሚባሉ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተቀራራቢና ለአገራዊ

ዕድገት ገንቢ የሆነ አቋም እንዲይዙ ማድረግ የምክክሩ ዋና ግብ መሆኑን አመላክተዋል።

ኮሚሽኑ ምን እየሠራ ነው?

ኮሚሽኑ ወደ ሥራ ሲገባ የሚያከናውናቸው ዐበይት ተግባራትና ሊያሳካ የቆመለት ዓላማ በአዋጁ ላይ በግልጽ ተመላክተዋል። የኮሚሽኑ ራዕይ፣ ተልዕኮ እና ስትራቴጂያዊ ዕቅድ መቋቋሚያ አዋጁን በመመስረት ተዘጋጅተዋል። የአዋጁ አንቀፅ ዘጠኝ ሊከወኑ የሚገባቸውን የኮሚሽኑን ዐበይት ተግባራት ይዟል። ስለዚህ ኮሚሽኑ ስትራቴጂያዊ ዕቅዶችን ሲያዘጋጅ እነዚህን ተግባራት በአራት የክዋኔ ጊዜያት ከፋፍሎ አስቀምጧል። እነሱም የቅድመ-ዝግጅት፣ የዝግጅት፣ የሂደት እና የትግበራና ክትትል ምዕራፍ ናቸው።

ኮሚሽኑ በቅደመ-ዝግጅት ምዕራፍ ዓላማውን እንዲያስፈፅም መደላድል የሚሆኑ ተግባራትን አከናውኗል። የተለያዩ ሕጋዊ ማዕቀፎችንና የውስጥ አሠራር ሥርዓቶችን በማዘጋጀት ተቋማዊ አደረጃጀት ተዘርግቷል። በዚህ ምዕራፍ ኮሚሽኑ የፅህፈት ቤት ባለሙያዎችን ቅጥር በመፈፀምና ወደተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ የአገራዊ ምክክርን ምንነት ለባለድርሻ አካላት (የዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡን ጨምሮ) በማስተዋወቅ ገንቢ ውይይቶች ያደረገበት ሂደት ስለመሆኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርዓያ ገልጸዋል።

የዝግጅት ምዕራፍ በአብዛኛው ለአገራዊ ምክክር ጉባዔው ግብዓት የሚሆኑ ተግባራት የሚከናወኑበት ቁልፍ ምዕራፍ ነው። በዚህ ሂደት ሥነ-ዘዴ (Methodology) መቅረፅ፣ የተለያዩ መመሪያዎችን ማዘጋጀት፣ አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት



62

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

ላይ የተሳታፊዎች ልየታ እና አጀንዳን በተለያዩ መንገዶች ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ማሰባሰብ ከዚህ ምዕራፍ ሥራዎች መካከል ናቸው።

በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ ውይይቶችን የሚመሩ አስተባባሪዎች (Moderators) ምልመላና ሥልጠና፣ አጀንዳዎችን ማደራጀት፣ መቅረፅ እንዲሁም ለሕዝብ ይፋ ማድረግ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የሚከወኑ ተግባራት ናቸው። የአገራዊ ምክክር ጉባዔውን የሚመሩ ገለልተኛ እና ሕዝባዊ ቅቡልነት ያላቸው አወያዮች ማስመረጥ የዚህ ሂደት ሌላው ዐብይ ተግባር ነው።

ሦስተኛው የሂደት ምዕራፍ ሲሆን የአገራዊ ምክክር ጉባዔው የሚከናወንበት ነው። በዚህ ምዕራፍ የኢትዮጵያዊያንን ድምፅ የያዙ ወኪሎች ስለ አገራቸው መፃዒ ተስፋ ለመነጋገር የሚሰባሰቡበት ነው። በአራተኛው የትግበራና ክትትል ምዕራፍ ኮሚሽኑ የአገራዊ ምክክር ጉባዔ ውጤቶችን ለሕዝብ ይፋ ያደርጋል። የተገኙ ምክረ-ሀሳቦችን ለሕግ አስፈፃሚው አካል በማቅረብ በፖሊሲ ማዕቀፍ ውስጥ ተካትተው ጥቅም ላይ እንዲውሉ የፖሊሲ መነሻ ሀሳቦችን ያቀርባል።

እንደ ዋና ኮሚሽነሩ ገለጻ፤ ኮሚሽኑ በአገራችን በሚገኙ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት መካከል በሚታዩ የሃሳብ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ምክንያት የተፈጠሩ አገራዊ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት ሲሠራ ቆይቷል። በሁለት ዙሮች ሕዝባዊ ውይይቶችን ያከናወነ ሲሆን በመጀመሪያው ዙር የኮሚሽኑ አባላትና ባለሙያዎች ወደ ሁሉም የክልል ከተሞችና የከተማ አስተዳድሮች በመጓዝ ከሕዝብ ጋር ትውውቅ ያደረጉበት ነው። በሁለተኛው ዙር በክልል እና በዞን ከተሞች ውስጥ በአገራዊ

ምክክሩ ሥነ-ዘዴ (Methodology) ላይ ግብዓት ለማሰባሰብ ያስቻሉ ገንቢ ውይይቶች ተካሂደዋል። ውይይቶቹ በየአካባቢው የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማግኘት ስለ አገራዊ ምክክር ሂደቱ ለማስረዳት ብሎም የሕዝብ አስተያየቶችን ለመቀበል ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውን ኮሚሽነሩ ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በእስካሁን ጉዞው በክልሎች፣ በከተማ አስተዳደሮች፣ በፌዴራል ተቋሟት እንዲሁም በዳያስፖራ ማኅበረሰብ ዘንድ የሚገኙ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ አጀንዳ ማሰባሰብ ችሏል።

የአገራዊ ምክክሩ ዋነኛ ግብ እንደ አገር ያልተግባባንባቸውን መሰረታዊ ጉዳዮች በመለየት፤ መንስኤዎቻቸውን ነቅሶ በማውጣት፤ በመከባበር ተነጋግሮና ተደማምጦ የጋራ መግባባት የሚፈጠርበትን ምቹ ሁኔታ ማመቻቸት እንደመሆኑ በሂደቱ ዜጎች በተወካዮቻቸው አማካኝነት እንዲሳተፉ ለማስቻል እየሠራ መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል።

ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ይረዳ ዘንድ በወረዳዎች (ልዩ ወረዳዎች) ውስጥ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚገኙባቸውን አደረጃጀቶችና ከዚያም ውጪ ያሉትን የኅብረተሰብ ክፍሎች በማሳተፍ ዜጎች ሀሳባችንን ያሰሙልናል የሚሏቸውን ሰዎች እንዲወክሉ መንገዱ ሲመቻች ቆይቷል። ፕሮፌሰር መስፍን “በጥቅሉ በኢትዮጵያ የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ የፖለቲካና የሃሳብ መሪዎች፣ ተቋማትና ማኅበራት እንዲሁም በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ስለ አገር በሚደረገው ምክክር



63

በውክልና ተሳታፊ ሆነዋል” ነው ያሉት።

በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ከሚገኙ ወረዳዎች ተሳታፊዎችን የማስመረጡ ሂደት እጅግ ውጤታማና ተደራሽነታችን ብሎም ተሳትፎን ያረጋገጥንበት ሂደት ነው። የኅብረተሰብ ክፍል ተወካዮችን በወረዳ (ልዩ ወረዳ) የመለየቱ ሂደት ዋና ዓላማ በክልሎች እና ከተማ መስተዳድሮች ሲካሄዱ ለቆዩት አጀንዳ የማሰባሰብ ተግባራት ተወካዮችን ለማስመረጥ ሲሆን ለሂደቱም መሳካት የተለያዩ ተባባሪ አካላት እገዛ ጉልህ ሚና ነበረው” ሲሉም አክለዋል።

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአገራዊ ምክክር ሂደቱ የሚመራበትን ሥነ-ዘዴ ሲቀርፅ የአገራዊ ምክክር ሂደቱ አምሥት ቁልፍ ባለድርሻ

አካላት እንደሚኖሩት አስቀምጧል። እነሱም የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ የፖለቲካና የሃሳብ መሪዎች፣ መንግሥት፣ የተለያዩ ተቋማት እና ማኅበራት እንዲሁም የዲያስፖራ ማኅበረሰብ ናቸው። በእስከ አሁን ሂደት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚናና ድጋፍ እጅግ የሚያበረታታ እና ይበል የሚያሰኝ እንደሆነ ኮሚሽኑ ገልጿል።

የሚያጋጥሙ ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባሕል እንዲጎለብት በምክክር ሂደቱ የታየው ተሳትፎ መጠናከር ይኖርበታል። በኢትዮጵያ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በውይይት እና በምክክር የመፍታት ባሕል እንዲጎለብት ሁሉም በምክክር ሂደቱ የሚያደርገውን የነቃ ተሳትፎ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚጠበቅበትም አስገንዝቧል።



64

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

ሒደቱን አካታች ለማድረግ …

አገራዊ ምክክር በተለያዩ አገሮች የተለያዩ ስያሜዎች ሊኖሩት ቢችሉም የዝግጅት፣ ሂደትና ትግበራ የሚሉ ምዕራፎችን ማለፉ አንድ ያደርገዋል። የተለያዩ የዓለም አገራት ጦርነትና ሌሎች ችግሮችን ካለፉ በኋላ ወደ ግጭት የወሰዷቸውንና አላግባባ ያሏቸውን ጉዳዮች በሠለጠነ መንገድ በንግግር ለመፍታት አገራዊ ውይይት ማካሄዳቸውን የተለያዩ ሰነዶች ያስረዳሉ።

ኢትዮጵያም የፖለቲካ እና የሃሳብ መሪዎች እንዲሁም የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን ልዩነት መፍታት ለአገራዊ አንድነት መሰረት በመሆኑ አካታች ውይይት ለማድረግ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች።

አገራዊ ምክክርን በተመለከተ ዓለም እስካሁን ካለፈችባቸው ሂደቶች የተቀመረና ወጥ የሆነ አካሄድ ስለመኖሩ ባይጠቀስም፤ ኮሚሽኑ ውጤታማ ሊያደርጉ የሚችሉ መሠረታዊ መርሆዎች ላይ መግባባት እንዳለ አመላክቷል። ሕዝባዊ ተቀባይነት፣ የመንግሥት ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት፣ አካታችነት፣ አሳታፊነት፣ ግልጽነት፣ ተዓማኒነት፣ ገለልተኝነትና ተግባራዊነት መሠረታዊ መርሆዎች መሆናቸውንም አብራርቷል።

በአንድ አገር አገራዊ ምክክር ለማካሄድ ቀደም ሲል በውስጥ ከነበሩ ወይንም የሌሎች አገሮችን ልምድ በመውሰድ ስህተቶችን ባለመድገም ውጤታማ ማድረግ ይገባል። የአካታችነትና አሳታፊነት ልክ፣ ውክልና እንዲሁም የአመራረጥ መስፈርቶች፣ ዓላማና ወሰን፣ የተቋማት አቀራረፅና የድጋፍ



65

አወቃቀር እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች በአገራዊ ምክክር ሂደቱ ውስጥ ሊቃኙ ከሚገቡት መካከል ይጠቀሳሉ።

መንግሥት በአገራችን ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮች አካታች አገር አቀፍ ውይይት (inclusive national dialogue) በማካሄድ እንዲፈቱ በቁርጠኝነት እየሠራ ነው። መንግሥትን ጨምሮ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ የፖለቲካ ተዋናዮችና ሌሎች የሚመለከታቸውን ተቋማት በማሳተፍ ለዘመናት ሲንከባለሉ የኖሩትን ችግሮች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት ያልተቆጠበ ጥረት እያደረገ ይገኛል። ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽንን በማቋቋም የተሳካ አገራዊ መግባባት እንዲመጣ ለማስቻል በርካታ ጥረቶችንም እያደረገ ነው።

አዋጁ አካታችነትን የአገራዊ ምክክሩ የመጀመሪያ መርህ ተደርጎ ነው የደነገገው፤ ከዚህ በመነሳት ኮሚሽኑ ለዘለቄታው የሚበጁ የመፍትሔ ሀሳቦችን አካታች በሆነ መንገድ በምክክሮች ለማመንጨት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ሲሠራ ቆይቷል።

ኮሚሽኑ የምክክሩ ሂደት አሳታፊ እንዲሆን ከወሰዳቸው እርምጃዎች መካከል ምክክሩ የሚካሄድባቸው አራት የትኩረት ቦታዎች እንዲሁም የምክክሩን ሂደት ስኬታማነት የሚያሳልጡ ተባባሪ አካላትን ለይቶ መጀመሩ ነው። ይህም ኮሚሽኑ በአገሪቷ የመጀመሪያ የሆነው ብሔራዊ ምክክር ሂደት እንደሚጠበቀው አካታችና ስኬታማ እንዲሆን ብዙ ርቀት መጓዙን ያሳያል።

የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ የሕዝብ ሀሳቦች በአግባቡ በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቶች እንዲወከሉ አድርጓል። ይህን ተከትሎም በተለያዩ ክልላዊ (የከተማ አስተዳደር) መዋቅር ውስጥ የሚገኙ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንዲሁም ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን በማሳተፍ አጀንዳዎችን ከክልሎች እና ከከተማ አስተዳደሮች፣ ከፌዴራል ባለድርሻ አካላት እንዲሁም ከዲያስፖራ ማኀበረሰብ አጀንዳ ማሰባሰብ ችሏል። በዚህ የአካታችነት አውድ ውስጥ ሲሠራ በአገር ጉዳይ ላይ ይመለከተናል ለሚሉ አካላት የአብረን እንስራ ጥሪ ከማቅረቡም በላይ ወደ ጠረጴዛ



66

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

ዙሪያ በመምጣት ስለ አገር የሚመክሩበትን ሂደት ሲያመቻች መቆየቱን፣ አሁንም እያመቻቸ መሆኑን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ አካታችነትን የቁጥር ጉዳይ ብቻ አድርጎ ሳይመለከት የሃሳብ ብዝሃነት የሚስተዋልበት አገራዊ ምክክር ለማድረግ የድርሻውን እየተወጣ ስለመሆኑ መግለጽ ይቻላል። ለዚህም ኮሚሽኑ በተለያየ ደረጃ ለሚገኙ የፖለቲካና የሀሳብ መሪዎች እንዲሁም የኅብረተሰብ ክፍሎች በምክክር ሂደቱ ተሳትፈው ሀሳባቸውን እንዲያሰሙ ጥሪውን አቅርቦ የብዙዎችን አዎንታዊ ምላሽ ማግኘቱን እንደማሳያ ማንሳት ይቻላል።

“ከሚሽኑ አሁን ላይ በአገራዊ ምክክር ሂደቱ ላይ ለመሳተፍ ፈቃደኛ ያልሆኑ ተፅዕኖ ፈጣሪ የፖለቲካ ኃይሎች መኖራቸውን ይገነዘባል” ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ እነዚህ የፖለቲካ ኃይሎች (ፓርቲዎች እና ታጣቂ ቡድኖች) ሀሳቦቻቸውን ወደ ምክክር መድረክ ይዘው እንዲመጡ አሁንም ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ፤ ወደፊትም ይህን ጥረቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የተናገሩት።

በምክክር ሂደቱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ተሳትፎ ይበልጥ ለማጠናከር ኮሚሽኑ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ስለመሆኑ የገለጹት የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ፤ በአገሪቷ ከሚንቀሳቀሱት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል 80 በመቶ ያህሉ በምክክር ሂደቱ ተካተው ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ እንደሆነ አብራርተዋል። የሚካደው አገራዊ ምክክር ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ያካተተና ያሳተፈ እንዲሆን እየተደረገ ባለው ጥረት በሂደቱ ሲሳተፉ ቆይተው ተሳትፏቸውን የቀነሱትንም ሆነ በሂደቱ ለመሳተፍ እስከአሁን ፍቃደኛ ሳይሆኑ ከቆዩ

የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይቶችን ለማድረግ ጥረት እያደረገ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።

በምክክር ሂደቱ የሴቶች ተሳትፎ ትርጉም ያለው እንዲሆን ለማድረግ ኮሚሽኑ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ ነው ያሉት ቃል አቀባዩ በአገራዊ ምክክር ጉባዔው የሴቶች ተካታችነት ከ45 በመቶ በላይ እንዲሆን ከተሳታፊ ልየታ ጀምሮ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ብለዋል። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች ኮከስ አባላት የተሳተፉባቸው ውይይቶች መዘጋጀታቸውንም ጠቅሰዋል።

ውይይቱ የኮከሱ አባላት ግጭት እና ጦርነት በኢትዮጵያ ያስከተሏቸው ችግሮች መፍትሔ የሚኖራቸው በምክክር ብቻ እንደሆነና ሌሎች መንገዶች ሁሉ እጅግ አክሳሪዎች መሆናቸውን ማስገንዘብ እንዲችሉ በተለይም ደግሞ የሴቶች ተሳትፎ ትርጉም ያለው እንዲሆን ለማስቻል እገዛ የነበረው መድረክ እንደነበረ አቶ ጥበቡ አስታውሰዋል።

ቃል አቀባዩ ያነሱት ሌላው ነጥብ በሕግ ጥላ ስር ያሉ ዜጎች በውይይቱ የሚሳተፉበትና ሀሳባቸው የሚደመጥበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ኮሚሽኑ እያደረጋቸው ያሉ ጥረቶችን የተመለከተ ነው። በሕግ ጥላ ስር ያሉ ወገኖች በምክክር ሂደቱ ቢሳተፉ የሂደቱን አካታችነትና አሳታፊነት ይበልጥ ያጠናክራል የሚል እምነት አለ። በማረሚያ ቤት ያሉ ወገኖች የሚሰጡት የአጀንዳ ግብዓት ካሉበት አውድ አኳያ የራሱ መልክ እና እይታ ሊኖረው ስለሚችል ጠቀሜታ ይኖረዋል። ከዚህ አኳያ ኮሚሽኑ በፌዴራል ብቻ ሳይሆን በክልሎች በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች በሕግ ጥላ ስር የሚገኙ ታራሚዎችን ለማሳተፍ እንቅስቃሴ እያደረገ



67

ስለመሆኑ ገልጿል።

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት በኢትዮጵያ ሰላማዊ አማራጮችን ተከትሎ ችግሮችን መፍታት ለአካታች አገራዊ ምክክሩ ውጤታማነት የላቀ ሚና እንዳለው ጠቅሰው እንደ አገር የማያግባቡ ጉዳዮችን በመለየት መምከርና ለችግሮቹ ዘላቂ መፍትሄ ማስቀመጥ የኮሚሽኑ ዓቢይ ተልዕኮ ነው፡፡ ኮሚሽኑ በምክክሩ ማንኛውንም በሰላማዊ መንገድ ለመወያየት ፍላጎት ያላቸውን አካላት ለማሳተፍና ሃሳባቸውን ለማካተት ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ይገኛል፡፡

በዚህም ባለፉት ዓመታት ከመንግሥት፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከአገር ሽማግሌዎችና ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ባከናወናቸው ተግባራት በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል፡፡ የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ አማራጭ መመለስ በአገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት መሰረት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ኮሚሽኑ ለአገራዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት እያካሄደ ያለው የምክክር ሂደት እስከ አሁን ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እንደ አገር ካሉብን ውስብስብ ችግሮች መላቀቅ የምንችለው በሠለጠነ መንገድ መመካከርና መተባበር ስንችል



68

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

እንደሆነም አንስተዋል።

“ኮሚሽኑ የጋራ እሴቶችን ለመገንባት ብሎም አስተማማኝ ሰላምና ዕድገት ለማረጋገጥ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል” ያሉት ኮሚሽነሩ አገራዊ ምክክር የሁሉም ተሳታፊ ድምፅ የሚሰማበት፣ የመፍትሄ ሃሳቦች የሚደመጡበትና አገራዊ መግባባት የሚፈጠርበት እንዲሆን ትኩረት እንደተሰጠው አመላክተዋል። አገራዊ ምክክሩ ዘላቂ ሰላምና ልማት በማረጋገጥ እንዲሁም የጋራ እሴቶችን በማጠናከር የተሻለች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ የሚያስችል መሆኑንም አፅንኦት ሰጥተዋል።

አካታች አገራዊ ምክክር የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት፤ የፖለቲካ ቀውሶችን ለመፍታትና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን፣ የፖለቲካ ሽግግሮችን ለማድረግና ዴሞክራሲን ለማጽናት በመሰረታዊ አገራዊ



69

ጉዳዮችና ቀጣይ ዕጣ ፋንታዋ ላይ አገራዊ መግባባት መፍጠር የሚያስችል፤ እንደ አገር ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ በእጅጉ የሚያስፈልግ ሂደት በመሆኑ ኢትዮጵያዊያን ለአገራዊ ምክክሩ ስኬት ያገኘነውን መልካም አጋጣሚ ልንጠቀምበት ይገባል።

ስለ አገራዊ ምክክሩ …

አገራዊ ምክክሩ ለጋራ ችግሮቻችን የጋራ መፍትሄ የምናመነጭበት ልዩ ታሪካዊ አጋጣሚ በመሆኑ ለስኬቱ በጋራ መሥራት እንደሚገባ አስተያየታቸውን የሰነዘሩ በርካቶች ናቸው። የባሕልና ታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አህመድ ዘከሪያ፤ በአገራዊ ምክክር ሂደቱ ወሳኝ የተባሉና ለአገር ዘላቂ ጥቅምና አንድነት የሚጠቅሙ አጀንዳዎችን የማሰባሰብ ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል። በዚህ ሂደት በአገሪቷ እየታዩ ያሉ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት በውይይት ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት የሚያስችል ተስፋ የተሰነቀበት መሆኑንም አንስተዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ምሁር ዶክተር ደቻሳ አበበ፤ ካለፈው የመበታተንና የግጭት ታሪክ በመማር መስማማትን፣ ለመነጋገር ዝግጁ መሆንን፣ ነገሮችን በሰከነ መንፈስ ማየትን፣ ሃሳቦችን ማክበርን በመላበስ አገራዊ ምክክሩን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ይመክራሉ። አለማዳላት፣ ከራስ ጥቅም ይልቅ የአገር ጥቅምን በማስቀደም በሰከነ መንፈስ መነጋገር ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቀሪ ሥራዎች ስኬታማ ሆነው እንዲጠናቀቁ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ አጠናክረው

እንደሚቀጥሉ እየገለጹ ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ አባል ዶክተር መብራቱ ዓለሙ፤ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሠላምና አንድነት ለማስፈን ከጥላቻና መገፋፋት ፖለቲካ መውጣት እንደሚገባ ገልጸዋል። “በሰንደቅ ዓላማም ሆነ በታሪክ ትርክት ለምን እንጋጫለን?” ያሉት ዶክተር መብራቱ በጉዳዮች ላይ ተከራክረን፣ ተነጋግረን ተወያይተን ለአገር የሚበጅ መፍትሄ ላይ መድረስ አለብን የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል። አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አሰባሳቢ ትርክት ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ቁልፍ ሚና ያለው በመሆኑ ሁሉም ሊሳተፍ ይገባል ብለዋል።

የምክክር ሂደቱ ስኬታማነት ለአገር ሰላምና መረጋጋት ወሳኝ እንደሆነ የገለጹት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ፤ አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የያዛቸው ትልሞች ስኬታማ እንዲሆኑ የጋራ ምክር ቤቱ የበኩሉን ሚና እየተወጣ ነው ብለዋል። የምክክር ኮሚሽኑ ቀሪ ሥራዎቹን በተሳካ ሁኔታ እንዲያጠናቅቅ የጋራ ምክር ቤቱ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር የተመቻቸውን የጠረጴዛ ዙሪያ አገራዊ ምክክር ዕድል መግፋት አዋጭ አለመሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) ሥራ አስፈፃሚ አባል ግርማ ሰይፉ ናቸው። የተመቻቸውን የአገራዊ ምክክር አውድ በመተው መሣሪያ በማንገብ የሚንቀሳቀሱ አካላት የዕውቀት አልባነት መገለጫ መሆኑን በመግለፅ በጽኑ ተችተዋል። ኢዜማ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ በጠረጴዛ ዙሪያ በመምከር



70

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

መፍትሔ ማምጣትን እንደ ቀዳሚ አማራጭ እንደሚቀበል ገልጸው፤ የትጥቅ ትግልን በመተው በሐሳብ የበላይነት መወያየት እንደሚገባ የፓርቲያቸውን ፅኑ አቋም ገልጸዋል፡፡

ለአገራዊ ምክክሩ ስኬት የሃይማኖት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሲቪል ማኅበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሁሉም ዜጎች የሚጠበቅባቸውን ሊወጡ እንደሚገባ በሁሉም ዘንድ የታመነበት ነው። የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የሲቪል ማኅበራት ለአገራዊ ምክክሩ ስኬት የሚጠበቅባቸውን ቁልፍ ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አሳውቋል። በተለይ ምክር ቤቱ በተሰጠው ሥልጣን መሰረት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን በማንቃት በአገራዊ ምክክሩ ላይ ተሳትፏቸው የጎላ እንዲሆን የሚሠራ መሆኑን ገልጿል። ማኅበራቱ የአገራዊ ምክክሩ ባለቤት የሆነው የኅብረተሰብ ክፍል በምክክሩ ላይ በቂ ግንዛቤ በመያዝ ተሳትፎ እንዲያደርግ የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡም ቃል ገብተዋል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ መግባባት ለማስፈን የአገራዊ ምክክሩ ያስገኘውን ወርቃማ ዕድል ሁሉም ዜጋ ሊጠቀምበት እንደሚገባ የገለፁት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አህመድ ሁሴን፤ ኢትዮጵያዊያን ምክክር በማድረግ በጋራ አጀንዳዎች ላይ መግባባት ባለመፍጠራቸው አገር ዋጋ ስትከፍል መቆየቷን አውስተዋል። በዚህ መነሻነት አገራዊ ምክክሩ ለዘመናት ሲንከባለሉ በቆዩ ብሔራዊ አጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር የሚያስችል ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠው ወርቃማ ዕድል ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ በሃሳብ የበላይነት ላይ የተመሠረተ

አገራዊ ምክክር በማካሄድ ብሔራዊ መግባባትን ማጠናከር የሚያስችል የዳበረ የዴሞክራሲ ሥርዓትና የፖለቲካ ምኅዳር መፍጠር ያስፈልጋል። የኢትዮጵያን አገራዊ ምክክር አሳታፊ፣ አካታችና ተዓማኒነት ለማስጠበቅ፤ ብሔራዊ መግባባትን ለማጠናከርና አንድነትን ለማጽናት አገራዊ ምክክር ትልቅ ዕድል መሆኑን በመግለጽ ብሔራዊ መግባባት የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመገንባት የተፈጠረውን የአገራዊ ምክክር ዕድል ሁሉም ዜጋ ሊጠቀምበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

መንግሥት ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እና ውይይትን እንደ መርህ በመውሰድ ለአገር ዘላቂ ብልፅግና በትጋት እየሠራ እንደሆነ የገለጹት የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ፤ ጠንካራ አገር የሚገነባው በሕዝቦች አብሮነትና በመመካከር እንደሆነ መንግሥት ጽኑ አቋም እንዳለውና በኢትዮጵያ ለዘመናት ስር ሰደው የቆዩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትና በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱም የዚሁ ቁርጠኝነት ማሳያ መሆኑን እንዲሁም በተለያዩ ክልሎች በርካታ የቀድሞ ታጣቂዎች የመንግሥትን የሠላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ሰላማዊ ሕይወት በመመለስ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በሕዝቦች መካከል መቀራረብ እንዲኖር፣ የጋራ ትርክት እንዲገነባና አገር በቀል የችግር መፍቻ ሥርዓቶች እንዲዳብሩ በትኩረት እየተሠራ ሲሆን፤ ይህም ዜጎች በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ ተመሳሳይ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና ለሰላም ግንባታ የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማስቻል ያለመ እንደሆነ አክለዋል።



71

አገራችን ከገጠሟት ችግሮችና ፈተናዎች ትወጣ ዘንድ ኢትዮጵያዊያን በመተባበር፣ በመስማማትና በመከባበር እንደ ስሟ ትልቅ አገር መገንባት የሚቻለው እንዴት ነው? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የሚገኘው ከአገራዊ ምክክሩ ነው። በመሆኑም ያለፉ ስህተቶችን ላለመድገም ቃል በመግባባት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ መጀመር፤ የጸናችና የበለጸገች አገር ባለቤት ለመሆን የተገኘውን መልካም አጋጣሚና ዕድልም መጠቀም ይገባል።

ተጠቃሽ ችግሮች እና ቀጣይ ሥራዎች

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሥራ ላይ በነበረባቸው ጊዜያት በርካታ ችግሮችን ያሳለፈ ቢሆንም ፕሮፌሰር መስፍን ከችግሮቹ መካከል ሁለቱን አንስተዋል። የመጀመሪያው ችግር አንዳንድ ባለድርሻ አካላት በሂደቱ ለመሳተፍ ያሳዩት ተነሳሽነት ዝቅተኛ መሆን ነው።



72

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ወደሆነ የምክክር ሂደት ከገባችበት ጊዜ አንስቶ አንዳንድ የፖለቲካ ኃይሎች (ፓርቲዎች እና ታጣቂ ቡድኖች) በሂደቱ ተሳትፎ ለማድረግ ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውን አንስተዋል። ይሁንና ከእነዚህ ኃይሎች መካከል የኮሚሽኑን ሥራዎች በመመልከት በሂደቱ ተሳትፎ ማድረግ የጀመሩ ኃይሎች ስለመኖራቸው ጠቅሰዋል።

በቀጣይ ስለሚደረጉ ጥረቶች፤ “ኮሚሽኑ የእነዚህን ወገኖች ተሳትፎና የሃሳብ ውክልና ትልቅ ቦታ ስለሚሰጠው እነዚህ አካላት ወደ ምክክሩ እንዲመጡ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል፤ ወደፊትም ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበትን የምክክር መድረክ ለማካሄድ እስከ መጨረሻው ርቀት እንጓዛለን” በማለት ነው የገለጹት።

ዋና ኮሚሽነሩ በሁለተኛ ደረጃ እንደ ችግር ያነሱት ነጥብ ኅብረተሰቡ በሂደቱ ላይ ያለው

የግንዛቤ ክፍተት ነው። ኮሚሽኑ የመገናኛ ብዙሃን አማራጮችን ተጠቅሞ ሥራዎችን ለሕዝቡ ተደራሽ ሲያደርግ የቆየ ቢሆንም ግንዛቤ ከመፍጠር አንፃር ክፍተቶች እንዳሉ ተለይቷል።

“የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ብቻውን ስለ ሥራዎቹ እየተናገረና ስለ አገራዊ ምክክር ምንነት ግንዛቤ ለመፍጠር ጥረት እያደረገ እንብዛም ውጤታማ እንደማይሆን ትምህርት ወስደናል” ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን፤ ይህን ክፍተት ለማረም የትብብር አድማሳችንን በማስፋት በዙሪያችን ከሚገኙ አጋር አካላት ጋር በመተባበር በሠራነው ሥራ ውጤት እያገኘን ነው ሲሉ አክለዋል።

ኮሚሽኑ በቀጣይ የሚያከናውናቸው አራት ዐበይት ተግባራት አሉት። የመጀመሪያውና በቅርብ ቀናት ውስጥ ሊጀመር የታሰበው የትግራይ ክልል የምክክር ሂደት ነው። ይህን ተከትሎ ከሁሉም የምክክሩ ባለድርሻ አካላት በተለያዩ መንገዶች



73

የተሰበሰቡ አጀንዳዎችን በማደራጀትና በመቅረፅ የአገራዊ ምክክር ጉባዔውን አጀንዳዎች ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ይጠበቃል። ከዚህ ጎን ለጎን የአገራዊ ምክክር ጉባዔውን ውይይቶች የሚመሩ ገለልተኛ አወያዮች ተመልምለውና ሥልጠና ወስደው ለሥራው ዝግጁ እንዲሆኑ ይደረጋል። በአጠቃላይ ኮሚሽኑ ቀደም ሲል የተመላከቱትና ሌሎች ጉዳዮች መጠናቀቃቸውን ካረጋገጠ በኋላ የአገራዊ ምክክር ጉባዔው እንደሚካሄድ አሳውቋል።

ኢትዮጵያ ከምክክሩ ምን ትጠቀማለች?

በአገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ያለፉ አገራት ሂደቱ የተለያዩ ውጤቶች እና መልካም አጋጣሚዎችን አስገኝቶላቸዋል። አገራዊ ምክክሮቹ የተወጠኑበት ምክንያት ከአገር አገር የሚለያይ ቢሆንም ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆኑ ውጤቶችን እንዳስመዘገቡ በዚሁ ዙሪያ የተዘጋጁ ሰነዶች ያስረዳሉ።

ቀጥተኛ ተብለው የተመዘገቡት ውጤቶች ስር- ነቀል የሆኑ ለውጦችን የሚያጠቃልሉ ሲሆኑ የፓለቲካ ሥርዓት ማሻሻያዎች፣ የሕገ-መንግሥት ማሻሻያዎች፣ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት ማሻሻያዎች፣ የሰብዓዊ መብት አያያዝ፣ ወዘተ... ላይ የሚደረጉ ማሻሻያዎችን እንደ ምሣሌ መጥቀስ ይቻላል።

በሌላ በኩል ቀጥተኛ ያልሆኑና ምናልባትም በአገራዊ ምክክር ሂደቶች እንደ ዓላማ ያልተያዙ ውጤቶች እንደተገኙ የተለያዩ አገራት ተሞክሮዎች ያሳያሉ።

ነገር ግን በእኛ ምልከታ ላለፉት 46 ወራት ስናከናውነው በቆየነው የምክክር ሂደት ዜጎች

ሀሳቦቻቸው እና አመለካከቶቻቸው ላይ ያለምንም ተፅዕኖ በነፃነት ተወያይተዋል። ይህም ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን የሚያጎለብት በመሆኑ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መዳበር ጉልህ ሚና ይጫወታል።

“አገራዊ ምክክር በፖለቲከኞች፣ በልሂቃን፣ በምሁራን ሳይወሰን ዋናው የአገራችን ምሰሶና ማገር የሆኑትን የዳር አገር ሕዝቦች ከመሀሉ ጋር ባማከለ መልኩ አካታችና አሳታፊ ሆኖ መካሄዱ በኢትዮጵያ ለበሳል ዴሞክራሲ ጅማሮ እርሾ ይሆናል የሚል ፅኑ እምነት አለኝ” የሚል መልዕክታቸውን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ አስተላልፈዋል።

ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት አላግባባ ያሏቸው ልዩነቶች ላይ በጠረጴዛ ዙሪያ በመምከርና የጋራ አቋም በመያዝ በአገራዊ ምክክሩ ዘላቂ መፍትሄ እንደሚያመጡ ይጠበቃል። ችግሯን በውይይት በመፍታት የበለጸገች፣ ያደገች፣ ለዜጎች የምትመችና ሌሎች አገሮች በምሣሌነት የሚጠቅሷት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ አይተኬ ሚና አለው፡፡

ሲጠቃለል የሃሳብ መድረክ ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ ዴሞክራሲና ሰላም እንዲያብቡ በእጅጉ የሚጠቅም ነው። በአገራችን አገር አቀፍ ምክክር እንዲካሄድ እየተሠራ ያለውም በዚህ መነሻነት ነው። ከምክክሩ የሚገኘው ውጤት (ዴሞክራሲ፣ ሰላም፣ ወዘተ...) የጋራ ነውና ሂደቱ ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅበታል።



74

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

ፖለቲካ

ተለምዷዊ የዲፕሎማሲ



75

ብሂልን የለወጠ እጥፋት

ጭላፊ…

ሩሲያዎች ወደ አውሮፓ መዛለቂያ ’ደጅ-አፍ’ ይሏታል። የታሪክ፣ የባህልና የአገረ መንግሥት ምስረታ ትናንታቸው ትዕምርት አድርገውም ይቆጥሯታል። ከተማዋ ዕልቆ ቢስ የሚመስሉ ቅርሶች ሙዳይ ናትና “ጣሪያ አልባዋ አብያተ-መዘከር” ትሰኛለች። ለአያሌ ምዕተ ዓመታት የሩሲያ ርዕሰ መዲና ሆና ያገለገለችውን ሴንት ፒተርስበርግ ከተማ።

ከሁለት ዓመት በፊት በሥራ አጋጣሚ ወደ ከተማዋ ባቀናሁበት ወቅት የዓለም ቱሪስቶች ለማየት ከሚቋምጡላቸው የከተማዋ

በአየለ ያረጋል



76

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

ድንቅና ብርቅ ተጎብኚ አብያተ-መዘክሮች መካከል ጥቂቶችን የመጎብኘት ዕድል አገኘሁ። ለምሣሌ ፒተርሆፍ፣ ሔርሚታዥ እና የሩሲያ ምድረ ፅፋዊ ማኅበር (ጂኦግራፊያዊ ሶሳይቲ)። እነዚህን የጠቀስኩት የኢትዮ-ሩሲያ ታሪካዊ ወዳጅነት እርሾ የተቦካባቸው ቋሚ ቅርሶችና ተቋማት ስለሆኑ ነው።

በአውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር በ1990 በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት ከተመዘገበው ፒተርሆፍ (ከቀዳማዊ ፒተር እስከ ዳግማዊ ኒኮላስ ቤተ መንግሥት የነበረ) ደጅ ላይ ቆሜ የአድዋውን ሰማዕት ፊታውራሪ ዳምጠው ከተማ የወጠኑትን

የኢትዮ-ሩሲያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ጅማሮ አሰብኩ።

ይኸውም ከአድዋ ድል አንድ ዓመት ቀደም ብሎ በ1887 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ በፊታውራሪ ዳምጠው ከተማ (የራስ ደስታ አባት) የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ ሩሲያን ሲረግጥ ደማቅ አቀባበል የተደረገለት በፒተርሆፍ ቤተ መንግሥት ነበር። ፊታውራሪ ዳምጠው ከተማ ከአጼ ምኒልክና ከእቴጌ ጣይቱ የተላኩ ስጦታዎችን ለቄሳር ኒኮላስ ዳግማዊ እና ለባለቤታቸው ቀዳማዊት አሌክሳንድራ ያስረከቡት ፒተርሆፍ ቤተ መንግሥት ነበር። ከሩሲያ ሲመለሱም ለአድዋ ጦርነት ስንቅ የሆኑ

ፊታውራሪ ዳምጠው ከተማና ልዑካቸው



77

የጦር መሣሪያዎች እና የቀይ መስቀል አባላትን አስከትለው ተመልሰዋል። የኢትዮ-ሩሲያ ወዳጅነት መተሳሰሪያ ታሪካዊ የዲፕሎማሲ ገመድ የተፈተለበት ስፍራ ነው-ፒተርሆፍ።

ከሶስት ሚለዮን በላይ ቅርሶች ሙዳይ እንደሆነ የሚነገርለት የሩሲያ የኢትኖግራፊና አንትሮፖሎጂ ሙዚየም ወይም ሔርሚታዥ (የበጋ ቤተ መንግሥት) ከአፍሪካ ወካይ ቅርሶች መካከል (የኢትዮጵያው ንጉሥ የሚል ቅርጽ እና የእቴጌ ጣይቱ ስዕልን ጨምሮ) በርካታ የኢትዮጵያ ስብስቦች ይገኛሉ።

ሌላው በወቅቱ ያስደነቀኝ በታዋቂው የሩሲያ ምድረ ፅፋዊ ማኅበር (ጂኦግራፊያዊ ሶሳይቲ) ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ ያጋጠመኝ ነገር ነው። በወቅቱ ሁለተኛውን የአፍሪካ-ሩሲያን ጉባዔ ምክንያት በማድረግ ለአንድ ሣምንት በተከፈተ ዐውደ ርዕይ ሩሲያዊያን አሳሾች በኢትዮጵያ ያደረጓቸው የምድረ ፅፋዊ ሥራዎች አፍሪካን በመወከል በብቸኝነት በዐውደ ርዕይ መቅረቡ ነው። ይህ አጋጣሚ ለሩሲያ የኢትዮ¬ጵያን ያህል የጥንት ወዳጅነት የሚዘክር

ስብስብ ያለው አፍሪካዊ አገር እንደሌለ ሁነኛ ምስክር ነበር።

በተለያዩ ዘመናት ሩሲያዊያን አሳሾችና የኢትኖግራፊ ተመራማሪዎች በኢትዮጵያ ያደረጉትን የምድረ ፅፋዊ (የሥነ መልክዓ ምድራዊ) ሥራዎችን ለዐውደ ርዕይ መቅረባቸው ብቻ አይደለም ያስደነቀኝ። በድርጅቱ ሳይንሳዊ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ የአማርኛ ጽሁፎችን ጨምሮ አያሌ ኢትዮጵያ ነክ ሰነዶች መገኘታቸው ጭምር ነው። በነገራችን ላይ በቤተ መጻሕፍቱ ከሚገኙ ካርታዎች መካከል በ1820 ኒኮላይ ባቢሎ በተሰኘው ተጓዥ የተዘጋጀው ‘የኢትዮጵያ (የአቢሲኒያ) ካርታ’ የተሰኘው ካርታ ከየትኛውም የዓለም ክፍል ካርታዎች በግልጽ የተቀመጠ እንደሆነ አስጎብኚዎች ነግረውናል።

ከዐውደ ርዕዩ ይዘቶች መካከል በ19ኛው እና በ20ኛው ክፍለ ዘመን ዕውቅ የሩሲያ የመልክዓ ምድር አሳሾችና የምድረ ፅፋዊ ሊቃውንት የካርታ ሥራዎችና በዘመኑ የኢትዮጵያን የሥነ ምህዳር መልክ የሚያስቃኙ ፎቶግራፎቾ ይገኙበታል። በሩሲያው ቄሳር ቀዳሚዊ ኒኮላስ ትዕዛዝ በ1845 የተቋቋመው ይህ ማኅበር ከተቋቋመ 175ኛ ዓመቱን አስቆጥሯል። የሩሲያ ጆግራፊካል ሶሳይቲ የሳይንስ ቤተ

“በአድዋ ድል በዓመቱ (በ1989 ዓ.ም) የመጀመሪያው የሩሲያ ዲፕሎማቲክ ልዑክ ወደ ኢትዮጵያ ገባ፤ ከቀይ ባሕር ጀምሮ እስከ አዲስ አበባ በጥሩ መስተንግዶ አቀባበል ተደረገለት። በወርሃ የካቲት 1890 ዓ.ም የመጀመሪያው የሩሲያ ጉዳይ አስፈጻሚ ፒዮተር ቫስሎቭ ለዳግማዊ ምኒልክ የሹመት ደብዳቤውን አቀረበ”



78

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

መጻሕፍት በዓለማችን ከሚገኙ የምድረ ፅፋዊ አብያተ መጻሕፍት በይዘት ግዝፈቱ ቀዳሚ እንደሆነ ይነገርለታል። ቤተ መጻሕፍቱ የተመራማሪዎች ሳይንሳዊ ሥራዎችን፣ የጉዞ ዘገባዎችን፣ ማጣቀሻዎችን እና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቁሳቁሶችን ያቀፈ ነው።

በአድዋ ዋዜማ የተጀመረ የወዳጅነት ጥንስስ

በእርግጥ የኢትዮ-ሩሲያ ወዳጅነት በይፋ የተጀመረው በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ቢሆንም ቅሉ ቀደም ብሎም የሁለቱ አገራት ነገሥታት ግንኙነት ለመመስረት ፅኑ መሻት እንደነበራቸው ይነገራል። ለምሣሌ የሩሲያ አገረ መንግሥት ቁልፉ ሰው ቀዳማዊ ፒተር ወደ ኢትዮጵያ መልዕክተኛ ለመላክ ሞክሮ እንዳልተሳካለት ይወሳል። ከኢትዮጵያ ወገንም ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ታሪካዊውን የ’ሴባስቶፖል’ መድፍ ስያሜ የሰጠው በክርሚያ ጦርነት መነሻ ነበር።

አጼ ዮሐንስ አራተኛ በተመሳሳይ በተለይም ከክርስትና እምነት ጋር በተያያዝ ከሩሲያ ጋር ጥብቅ ወዳጅነት ለመመስረት ፍላጎት እንደነበራቸው ይወሳል። ዳሩ በጭላፊው መንደርደሪያ እንደተጠቆመው የኢትዮ-ሩሲያ ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አሀዱ ብሎ የጀመረው በሰኔ 1987 ዓ.ም በፊታውራሪ ዳምጠው ከተማ የተመራው ልዑክ ወደ ሴንት ፒተርስበርግ ባቀናበት አጋጣሚ ነበር።

ልዑኩ የሁለቱን አገራት ዘመን ተሻጋሪ ጽኑ ወዳጅነት መሰረት አስይዟል። በወቅቱ ቅኝ ግዛትን ስለመከላከል ከመምከር የተሻለ ተግባራዊ እርምጃው ተወስዷል። ልዑኩ ከዳግማዊ አጼ ምኒልክ የተላከውን የሰለሞን የክብር ኒሻን ሲያበረክት በተመሳሳይ ከእቴጌ ጣይቱ ብጡል ለዳግማዊ ኒኮላይ ባለቤት እቴጌ ቀዳማዊት አሌክሳንደሪያ እንዲሁም እና ለንጉሠ ነገሥቱ እናት ማሪያ ፊዎዶሮቭና የአንገት ሀብል፣ የእጅ አምባር እና ሌሎች ውድ ስጦታዎችን አበርክቷል።

የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ልዑክ ለአንድ ወር ቆይተው ከምክክር ተሻግሮ ለአድዋ ጦርነት የዋሉ ቁሳቁሶችና ሐኪሞችን ያካተተ የሩሲያዎች ልዑክ በፍጥነት ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ ያደረገ ፍሬያማ ተልዕኮ ነበር። በኒኮላይ ሌዎንቴፍ (በኋላ ደጃዝማች) መሪነት አድዋ ጦርነት ላይ አይተኬ ሚና የተጫወቱ ከ40 በላይ የቀይ መስቀል በጎ ፈቃደኞች እንዲመጡ አስችሏል። ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰው ቀደም ብለው ወደ ኢትዮጵያ የዘለቁ የመልክዓ ምድር አሳሾችም ሥራቸውን አጠናከረው ቀጥለዋል። ከስመጥር



79

የኢትዮጵያ አሳሾችና የኢትዮጵያ ወዳጆች መካከል ኒኮላይ ሊዎንቴፍ (ደጃዝማች) እና አሌክሳንደር ቪላቶቪችን ጨምሮ ከ1880ዎቹ ጀምሮ በርካታ ተጓዦችና የሥነ መልክዓ ምድር አጥኚዎች ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የአገራቱን ግንኙነት ፈር አስይዟል። የኢትዮጵያና የሩሲያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ትብብርም ከ1880ዎቹ ጀምሮ እየተጠናከረ መምጣት ለባህል ዲፕሎማሲው የማይናቅ ሚና እንደነበረው ይወሳል።

“በአድዋ ድል በዓመቱ (በ1989 ዓ.ም) የመጀመሪያው የሩሲያ ዲፕሎማቲክ ልዑክ ወደ ኢትዮጵያ ገባ፤ ከቀይ ባሕር ጀምሮ እስከ አዲስ አበባ በጥሩ መስተንግዶ አቀባበል ተደረገለት። በወርሃ የካቲት 1890 ዓ.ም የመጀመሪያው የሩሲያ ጉዳይ አስፈጻሚ ፒዮተር ቫስሎቭ ለዳግማዊ ምኒልክ የሹመት ደብዳቤውን አቀረበ።”

ከአምሥት ዓመታት በኋላ መጋቢት 1895 የሩሲያ ቋሚ ጉዳይ አስፈጻሚ ቢሮ በአዲስ አበባ ተከፈተ። ጄኔራል ኮንስታንቲን ሊሸን የተባሉት በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሩሲያ አምባሳደር (በወቅቱ ካውንስለር) አዲስ አበባ ውስጥ ሕይወታቸው እስካለፈ ድረስ የሁለቱን አገራት ግንኙነት በጸና መሰረት ላይ እንዲቀጥል አይተኬ ሚና ተጫውተዋል። መካነ ቀብራቸው በአዲስ አበባ ይገኛል።

በበርሊኑ ጉባዔ መላው የአውሮፓ ኃያላን አፍሪካን ለመቀራመት ሜዲትራኒያን ባህርን ሲያቋርጡ ሩሲያ ግን በተዘዋዋሪም ቢሆን ከኢትዮጵያ ጎን ቆማ ነበር። ጥያቄው ከሌሎች የአውሮፓ አገራት የተለየ የሩሲያ መንግሥት በኢትዮጵያ የነበረው ፖሊሲ ምን ነበር? የሚለው ነው። አምባቸው

ከበደ የተባሉ ጸሀፊ የአሌክሳንደር ቡላቶቪችን “ከእንጦጦ እስከ ባሮ፤ ከዳግማዊ ምኒልክ ሠራዊት ጋር (From Entotto to the River Baro, and With the Armies of Menelik II) በሚል ርዕስ በተረጎሙበት መፅሐፍ ማስታወሻ ላይ ያሰፈሩት ሃሳብ ጥያቄውን በቅጡ ይመልሳል።

“የሩሲያ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ይከተለው የነበረው ፖሊሲ ከራስ ዓላማ ጋር የተሳሰረ ነው ማለት ይቻላል። ነገር ግን ሌሎች ኤምፔሪያሊስት አገሮች በተለይም ኢትዮጵያን የከበቧት አገሮችና ሩሲያ የነበራቸው ዓላማ አንድ አልነበረም። በኢትዮጵያ ዙሪያ የነበሩ አገሮች ዓላማ አመቺ አጋጣሚ ጠብቆ ይህችን አገር በቁጥጥራቸው ስር ማድረግ ነበር። የቄሳሩ መንግሥት ዋና ዓላማ ግን ሌሎች ቅኝ ገዥዎችን በተለይም እንግሊዝን መቋቋም የምትችል ራሷን የቻለችና ነጻ ወዳጅ አገር በቀይ ባሕር ዳርቻ እንድትሆን ለማድረግ ነው። ይህ አይነቱ የሩሲያ መንግሥት አቋም በሁለቱ አገራት መካከል የአቋም አንድነት እንዲፈጠር አድርጓል። ለዚህም የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች ኢትዮጵያን በቁጥጥራቸው ስር ለማድረግ የሚያደርጉትን ሙከራ ሁሉ የቄሳር መንግሥት በጥብቅ ተቃውሟል”

የኢትየ-ሩሲያ ወዳጅነት ታሪካዊ ተብሎ የሚገለጽ ብቻ አይደለም። ለምሣሌ ከአድዋ ጦርነት ቀደም ብሎ የውጫሌውን ውል አንቀጽ 17 በዓለም መድረክ የተቃወመ የቄሳሩ መንግሥት ብቻ ነበር። ከአድዋ ጦርነት በኋላ የቀይ መስቀል ቡድን በመላክ ታድጓል። በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኤቭጌኒ ተርክሂን ብዙ ጊዜ የሁለቱን አገራት ወዳጅነት “የመንፈስ መተሳሰር” ሲሉ ይገልጹታል። በርግጥም



80

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

የኢትዮ-ሩሲያ ወዳጅነት የክፉ ቀን ጓድ ‘A friend in need is a friend indeed’ ይሉት የነጮች አባባል የሚገልጸው ነው። በየዘመኑ የነበራቸው ወዳጅነትና መተሳሰብ በተግባር የተገለጠ ነውና!

ሩሲያ በአፍሪካ ውስጥ ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙት የጀመረችው ከኢትዮጵያ ጋር ነው። በአፍሪካ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ኤምባሲ የከፈተችው አዲስ አበባ ውስጥ ነው። ለሩሲያና ለአፍሪካ ቀጣይነት ያለው ትብብርና ግንኙነትም ኢትዮጵያ ያላት ሚና ከፍተኛ ነው።

“በመንግሥታቱ ድርጅት የነበሩ ፀረ-ኢትዮጵያ ውሳኔዎችን በመቃወምም ሩሲያ ወሳኝ ውለታ ነበራት። በአድዋ ጦርነት ዋዜማ የነበረው የዲፕሎማሲ ጥንስስ ዛሬ እስከ ኢትዮጵያ የኒውክሌር ልማት ፕሮግራም የአጋርነት ከፍታ

በመንግሥታቱ ድርጅት የነበሩ ፀረ- ኢትዮጵያ ውሳኔዎችን በመቃወምም ሩሲያ ወሳኝ ውለታ ነበራት። በአድዋ ጦርነት ዋዜማ የነበረው የዲፕሎማሲ ጥንስስ ዛሬ እስከ ኢትዮጵያ የኒውክሌር ልማት ፕሮግራም

የአጋርነት ከፍታ ደርሷል።

ደርሷል።”

ሩሲያ እና ሩሲያዊያን ለኢትዮጵያ በበጎም፣ በክፉም ዘመናት ውለታ ውለዋል። ከአንድ ምዕተ ዓመት በፊት ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ለሩሲያው ንጉሥ (ቄሳር) ዳግማዊ ኒኮላስ በፃፉት ደብዳቤ “ኢትዮጵያ ከእግዚአብሄር እና ከሞስኮ መንግሥት በቀር ሁነኛ ወዳጅ የላትም” ያሉትም የሁለቱን አገራት እውነተኛ ወዳጅነት በቅጡ ይገልጣል። በአድዋ ጦርነት አይተኬ ሚና የተጫወተውን የሩሲያን ቀይ መስቀል ድጋፍ ጨምሮ ሩሲያ በየዘመናቱ ኢትዮጵያ የሉዓላዊነት ስጋትና ዓለም አቀፍ ጫና ሲጋረጥባት ከጎኗ ነበረች። በኢትዮጵያ ውስጥ የጤናና የትምህርት ተቋማት እንዲስፋፉ ውሳኝ ሚና ተጫውታለች። በመንግሥታቱ ድርጅት የነበሩ ፀረ-ኢትዮጵያ ውሳኔዎችን በመቃወምም ሩሲያ ወሳኝ ውለታ ነበራት። በአድዋ ጦርነት ዋዜማ የነበረው የዲፕሎማሲ ጥንስስ ዛሬ እስከ ኢትዮጵያ የኒውክሌር ልማት ፕሮግራም የአጋርነት ከፍታ ደርሷል።

በሥርዓተ መንግሥታት ለውጥ የማይናወጥ ወዳጅነት

ኢትዮጵያ እና ሩሲያ በታሪክ ዑደት ውስጥ ያለፉበት መንገድ ተመሳስሎሽ ይስተዋልበታል። ለምሣሌ ሁለቱ አገራት ያለፉባቸው ሥርዓተ መንግሥታት ባህሪና ዕጣ ፈንታ ያመሳስላቸዋል። በየዘመናቱ አያሌ ኃይሎች ሁለቱንም አገራት በተደጋጋሚ አጥቅተዋል። ሁለቱም አገራት በጀግንነት ተፋልመው ህልውናቸውን አስጠብቀው ዘልቀዋል። ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው ከተጀመረ ጀምሮ የሚያመሳስላቸው ታሪካዊ ዑደት ያላቸው እነዚህ አገራት፤ ኢትዮጵያ ፋሺዝምን ስታሸንፍ፣



81

ሩሲያ ናዚዝምን ድል ነስታለች።

በአንድ ክፍለ ዘመን ውስጥ (ዓመቱ ቢለያይም) የሁለቱ አገራት ባላባታዊ ሥርዓት በስር ነቀል አብዮት ተገርስሷል። አብዮቱ የንጉሣዊያን ቤተሰቦችን ለስደትና ለጉዳት በመዳረግ ተመሳሳይ ዕጣ ፈንታ አድርሷል። ድህረ አብዮት የእርስ በእርስ ደም አፋሳሽ ዕልቂት ሩሲያ በቦልሸቪክ እና መንሸቪክ (Bolshevik and Menshe- vik)፤ ኢትዮጵያ ደግሞ በቀይ እና ነጭ ሽብር መልከ ብዙ ግፎች አስተናግደዋል። ያም ሆኖ በየትኛውም ሥርዓተ መንግሥት ውስጥ የኢትዮ- ሩሲያ ወዳጅነት የሻከረበት ወይም አሉታዊ መልክ የያዘበት ጊዜ አልነበረም።

እንደሚታወቀው በፈረንጆቹ 1917 በሩሲያ የቄሳሮች ሥርዓተ መንግሥት ተገርስሶ የእነ ቭላድሚር ሌኒን አብዮት ሶሻሊስታዊ መንግሥት ሲያቋቁም በኢትዮጵያ የነበረው የሩሲያ ቆንስላ እስከ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ድረስ ተዘግቶ ቆይቷል። ያም ሆኖ ኢትዮጵያ በጠላት በተወረረችበት በሁለተኛው የፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ዘመን ሳይቀር ሩሲያ (ሶቪየት ሕብረት) በዓለም መድረክ ለኢትዮጵያ በመወገን አጋርነቷን

አሳይታለች። ለምሣሌ በሁለተኛው የፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ሲጣል የተቃወመችው ሩሲያ (የወቅቱ ሶቪየት ሕብረት) ነበረች። ይህ ወዳጅነት በዲፕሎማሲው ዓለም “ቋሚ ወዳጅና ቋሚ ጠላት የለም” የሚለውን ዲሎማሲያዊ ብሂል የሰበረ ነበር ማለት ይቻላል።

የዳግማዊ ምኒልክ እና የዳግማዊ ኒኮላስ ግንኙነት ሙሉ መተማመንና ልባዊ ወዳጅነት እንደነበረው የተለዋወጧቸው ደብዳቤዎች ዋቢ ናቸው። የደስታና የሀዘን ስሜቶችን ተጋርተዋል። ለአብነትም ዳግማዊ ኒኮላስ በራስ መኮንን ድንገተኛ ሕልፈት ማዘናቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ልከዋል። በተመሳሳይ ዳግማዊ ምኒልክ በጦርነት በሩሲያዊያን ላይ የደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ በጄኔራል ሊሸን በኩል የማጽናኛ ሀዘናቸውን ልከዋል። ሀዘን ብቻም ሳይሆን ተጎጂዎችን ለመደገፍ በሚል ለሩሲያ ቀይ መስቀል የገንዘብ ድጋፍ ልከዋል። ‘የአጼ ምኒልክ የውጭ አገር ደብዳቤዎች’ በተሰኘው የጳውሎስ ኞኞ መጽሐፍ እንደተጠቆመው ዋና ፍሬ ነገሩ እንዲህ ይነበባል።

“ሰላም ላንተ ይሁን፡፡ በሩቅ አገር የመስኮብ

ሔርሚታዥ ውስጥ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ወካይ ስዕላት መካከል



82

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

መንግሥት ልጆች ለንጉሣቸውና ለአገራቸው ደማቸውን በማፍሰሳቸው ብዙ አሳዘኑኝ፡፡ ጥቂትም እንኳን ቢሆን ለእነዚያ ለተጐዱት ልጆች ለመርዳት ብዬ ከዚህ ደብዳቤ ጋር አንድ አክሬዲልዩን ቼክ ስለመቶ ሺ ፍራንክ ልኬልሃለሁና ይህንን ቼክ ከመልካም ምኞቴ ጋር ለመስኮብ የቀይ መስቀል አለቃ እንድታደርስልኝ ይሁን።ይህን አሁን በመስኮብ መንግሥት የተነሳውን ጦር ጠላታቸውን አሸንፈው በቶሉ እንዲያልቅ እጅግ የከበሩ ታላቅ ወዳጃችን የመስኮብ መንግሥት ንጉሠ ነገሥት በጤና በሀብት እንዲያኖራቸው፣ ለመስኮብ መንግሥት ሰላምና ረፍት እንዲሰጥ እግዚአብሔርን እንለምናለን”፡፡

በነገራችን ላይ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ለዳግማዊ ኒኮላስ ቄሳር የፃፋት ደብዳቤ ኢትዮጵያ በዩኔስኮ ካስመዘገበቻቸው የሥነ-ጽሁፍ ቅርሶች መካከል ይጠቀሳል። የሁለቱን አገራት መልክዓ ምድራዊ ርቀት ያልገደበው የመተሳሰብ ስሜት ያንጸባረቀ፤ የጋራ ዕጣ ፈንታ እንዳላቸውም የሚያመላከት ይመስላል። አጼ ምኒልክ ከሩሲያ በስተቀር ኢትዮጵያ ሁነኛ ወዳጅ እንደሌላት እስከ መግለጽ ደርሰው

ነበር። ይህ የኢትዮ-ሩሲያ ወዳጅነት እስከዛሬ ሳይዛነፍ በመልካም ትብብርና መደጋገፍ ቀጥሏል።

ሩሲያዊያን የደጃዝማች ባልቻ መታሰቢያ ሆስፒታልን ጨምሮ በተቋማት ግንባታ አሻራቸውን አሳርፈዋል። የሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩም እያደገ ቀጥሏል። ቀደም ብሎ በታላቁ ቀዳማዊ ፒተር ዘመን በኢትዮጵያዊው አብርሃም ሃኒባል (የታላቁ የሩሲያ ባለቅኔ አሌክሳንደር ፑሽኪን ቅደመ አያት) በኩል የተጀመረው የደም ትስስርም በ20ኛው ክፍለ ዘመን በስፋት ተስተውሏል። በርካታ ሩሲያዊያን ከኢትዮጵዊያን ጋር በደም ተሳስረዋል። ከሁለቱ አገራት የተወለዱ ዜጎችም ለኢትዮጵያ ውለታ ውለዋል። ለምሣሌ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ አየር ኃይል አዛዥና አብራሪ ሚሽካ ባብቼፍ በአባቱ ሩሲያዊ መሆኑን ልብ ይሏል።

ከነጻነት በኋላም የኢትዮጵያ እና የሩሲያ ወዳጅነት ዳግም ተጠናክሯል። በአውሮፓዊያኑ 1937 ሩሲያ ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ ዳግም ከፍታለች። በዚህም በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ



83

መንግሥት በሰው ሀብት ልማትና መሰረተ ልማት ላይ መልካም የትብብር ጅምሮች ነበሩ።

በ1937 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሩሲያ ባህል ማዕከል (ፑሽኪን አዳራሽ) ሲመረቅ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ድልን የተመለከተ ኤግዚቢሽን ተካሂዶ ነበር። ዐውደ ርዕዩን የከፈቱት አጼ ኃይለሥላሴ “ጀግኖች የሶቪየት የጦር ሠራዊቶችና ሕዝቦቹም በጦርነቱ ውስጥ የሠሩትን ብዙ የሆነ የመታገልና የጦርነት ሥራ ዝርዝር የሚያሳይ ውብ የሆነው ይህ ኤክስፓዚሲዮን ቤት በሚመረቅበት ጊዜ ፈቃደኞች ሆነን የመጣነው በጣም ደስ እያለን ነው። ደግሞም ይህ ኤክስፓዚሲዮን በሁለቱ አገሮች መካከል ያሉትን የፍቅር ማሠሪያዎች ይበልጥ የጠበቀ አድርጎ ለማኖር እንዲረዳን እመኛለሁ” ብለዋል። ይህ መልዕክታቸው የጸረ ፋሺዝምን ትግል ዕውቅና የመስጠትና የቀጣይ ትብብር ማጠናከር በአጽንኦት የተናገሩበት ነበር።

በተመሳሳይ ንጉሠ ነገሥቱ በግንቦት 1952 ዓ.ም በሶቪየት ሕብረት መንግሥት በአዲስ አበባ የተከፈተውን የኢንዱስትሪ ኤክስፖ በጎበኙበት ወቅት “እስከዛሬ በአገራችን እንደዚህ ባለ ሁናቴ ተዘጋጅቶ አላየንም። ስለዚህ ይህ ኤክስፓዚሲዮን ትልቅ ግምት የምንሰጠው ነው” በማለት አድንቀዋል። ይህ ማለት በወቅቱ የሁለቱን አገራት በኢኮኖሚ የመተሳሰር ፍላጎት ጉልህ ማሳያ ነው።

በ1950ዎቹ መባቻ ላይ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ወደ ሩሲያ ባቀኑበት የመጀመሪያው ጉብኝት በርካታ ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮ የፈጸሙበት እንደሆነ ይወሳል። ሁለቱ አገራት የነበራቸውን ወዳጅነት ዕውቅና የተሰጣጡበት፣ የተመሰጋገኑበትና የቀጣይ ዘመን ወዳጅነትን ለማጎልበት ተጨማሪ

ስንቅ የቋጠሩበት ነበር። ንጉሠ ነገሥቱ ከሶቪየት መንግሥት በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማና በዘውዳዊ መንግሥት ትዕምርት ያሸበረቀ የአውሮፕላን ስጦታ ተበርክቶላቸው ነበር። በወቅቱ የንግድና ኢኮኖሚ ስምምነቶች ተፈርመዋል። በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪና ግብርና ልማት የሚውል በተራዘመና በአነስተኛ ወለድ የሚከፈል የ90 ሚሊዮን ዶላር ብድርም ለኢትዮጵያ እንዲመቻች ተደርጓል። በአጠቃላይ በሁለቱ አገራት ወዳጅነት መሰረት የተጣለበት ጉዞ እንደሆነ በታሪክ ይወሳል። የሞስኮ ሬዲዮ በአማርኛ ቋንቋ ስርጭት መጀመሩና የሩሲያ ሥነ ጽሁፍ ወደ አማርኛ መተርጎም የጀመሩበት ጊዜ ነበር። የባሕርዳሩ ፖሊቴክኒክ ትምህርት ቤት (አሁን ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ) እንዲገነባ ድጋፍ የተገኘው በዚህ ጉዞ መነሻ ስለመሆኑም ይነገራል።

በዚህ ዘመን ሊጠቀስ የሚገባው ወቅቱ የምዕራብና የኮሚኒስቶች ፉክክር ያየለበት መሆኑ ነው። በተለይም ኢትዮጵያ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያላት ወዳጅነት ጠንካራ ሲሆን ወደ ሶቪየት መንግሥት የነበራት ዲፕሎማሲ በአሜሪካ አልወተደደም ነበር። በወቅቱ መጀመሪያ በሞስኮ ቀጥሎ በዋሸንግተን የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት ቢትወደድ ዘውዴ ገብረ ሕይወት ባሰፈሩት ግለ ታሪክ (የሕይወት ውጣ ውረድ) በወቅቱ አሜሪካኖች የኢትዮጵያ እና የሩሲያን ወዳጅነት አልወደዱትም ነበር። በጉዳዩ ላይ ንጉሠ ነገሥቱና አምባሳደር ዘውዴ ከተለዋወጡት ደብዳቤ ውስጥ አጼ ኃይለሥላሴ ለአምባሳደር ዘውዴ የላኩት ተከታዩ የደብዳቤ አንቀጽ ይገኝበታል።

“ከሞስኮቦች የተደረገልን ችሮታና ያስቀደሙልን ክሬዲት ያላንዳች ኮንዴሲዮን መሆኑን እንዴት



84

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

ሳይረዱት ቀሩ? ከዚህም ክሬዲት ታላላቅ ጉዳይ ላይ የሚውለውን የወርቅ ማዕድን ለማውጣትና ለማምጣት እንዲቻል፣ በአሰብ በር ላይ የዘይት ማጣሪያ ለማቋቋም፣ ኮስቲክ ሶዳ የተባለውን ለማደራጀትና ዋጋ ለመስጠት እነዚህን ሁሉ ጨርሰው ለማስረከብ ዋና ዋናዎቹ እነዚህን ሲሆን በችሮታ ደግሞ ለአንድ ሺህ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ቤቱን ሰርተው አስፈላጊውን አሟልተው ከሰጡ በኋላ ኢትዮጵያዊያን እንዲረከቡት ስለተማመንን እነዚህ ኢትዮጵያን አስተማሪዎች በማደራጀት ላይ ነን” ይላል።

ይህ ደብዳቤ የሚያሳየው በወቅቱ ሩሲያ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለኢትዮጵያ ዕድገት የሚበጁ ወሳኝ ድጋፎች በማድረግ ለይ መሆኗን በፅኑ መተማመን ላይ የተመሰረተ ወዳጅነት እንደሆነ በአንጻሩ የምዕራባዊያን ግንኙነት በቅድመ ሁኔታና ጣልቃገብነት ላይ ያተኮረ እንደነበር አምባሳደር ቢትወደድ ዘውዴ በግልጽ አስፍረውታል።

በዘመነ ደርግ ደግሞ ከፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ጋር ተዳምሮ ሁሉን አቀፍ ትብብር ነበር። በዘመኑ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መጠበቅ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። ቀደም ብሎ በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን የጀመረው የጥቂት ኢትዮጵያዊያን የትምህርት ዕድል በደርግ ዘመን በከፍተኛ ደረጃ አድጓል። በሁሉም የትምህርት መስኮች ከ20 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ዘመን የነጻ ትምህርት ዕድል አግኝተው ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።

በየዘመናቱ በሩሲያ የተማሩ ኢትዮጵያዊያን ስለ አገሪቷ የሚሰጡት ፍቅርና አክብሮትም የዚህ ማሳያ ይመስላል። ለምሣሌ ፊታውራሪ ተክለሐዋርያት

ተክለማርያምን በዋቢነት እንጥቀስ። በራስ መኮንን ቤት ያደጉት ፊታውራሪ ተክለሐዋርያት ገና በልጅነታቸው (በ19ኛው ክፍል ዘመን መጨረሻ) በራስ መኮንን አደራነት እንዲማሩ በሚል ከአንድ ሩሲያዊ ጋር ወደ ሴንት ፒተርስበርግ አቅንተው ያደጉ፣ የተማሩና የኖሩ እንዲሁም በኋላ በዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካና አገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ትልቅ ሚና የነበራቸው፣ ከቀደምት ዘመናዊ ትምህርት ፈር ቀዳጆች መካከል የሚጠቀሱ ጉምቱ አሰላሳይ ምሁር ሰው ናቸው። በሩሲያ እናቶች ቤት ያደጉት እኒሁ ሰው ‘አውቶባዮግራፊ’ በተሰኘው ግለ ታሪክ መፅሐፋቸው እንደከተቡት ስለ ሩሲያ ሕዝብ ፍቅርና የአገሩ ኃያልነት አንስተው አይጠግቡም። “ሩሲያ ሁለኛ አገሬ ናት። ለእኔ የዋሉልኝን ውለታ መቼም ልረሳው አልችልም። ሩሲያኖች ሐሳባቸው ሰፊ፣ ሥራቸው ጠንካራ ነው። በማንኛውም ሙያ የሚያሽንፋቸው ኃይል ሊኖር አይችልም” ብለዋል።

የቀድሞ ተማሪዎችም ቢሆኑ ስለ ሩሲያ ሕዝብ ያላቸው አክብሮት ልዩ ነው። በሩሲያ አይረሴ ትዝታ የቋጠሩበት፣ ወጣትነታቸውን ያጣጣሙበት፣ የታሪክ፣ የሥነ ጥበብና የሥነ ፅሁፍ ከፍታቸው የሚደንቃቸው፣ የአገር ፍቅር ስሜታቸው የሚያስቀናቸው ናቸው። በተለያዩ ጊዜያት ካነጋገርኳቸው የሩሲያ ተማሪዎች መካከል ደራሲና ሃያሲ አያልነህ ሙላቱ፣ አንጋፋው ዲፕሎማት በላይ ግርማይ፣ የእርሻ ባለሙያው አለማየሁ ዓሊ እና ዕውቁ ሠዓሊ መዝገቡ ተሰማ የሩሲያዊያንን ፍቅር፣ የአገሩን ጥበብና ኃያልነት አውስተው አይጠግቡም። ዛሬም ይናፍቃቸዋል።

የቀድሞ ተማሪዎች እንደሚሉት በቀዳማዊ ፒተር ዘመን መሰረት የተጣለው የዘመናዊት ሩሲያ



85

ሥነ-ፅሁፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅጉን ተቀባይነት አግኝቷል። አቶ አለማየሁ ዓሊ በዘመነ ደርግ ለግብርና ሙያ ትምህርት ቢላኩም ከግብርና ሙያቸው ጎን ለጎን በሩሲያ ሥነ-ጽሁፍ ፍቅር መለከፋቸውን ይናገራሉ፡ ፡ የሩሲያ ሥነ-ፅሁፍ ነገረ- አመክንዮ፣ ፍልስፍና፣ ሥነ-ልቦና፣ የሳይንስ ዕውቀቶችን መያዙን ገልጸው፤ በርካታ የኢትዮጵያ ሥነ-ፅሁፍ ሀብቶችም ወደ ሩሲያኛ ቋንቋ መተርጎማቸውንና የሞስኮቭኛ መጻህፍትንም ወደ አማርኛ እንደተረጎሙ ይናገራሉ።

በተመሳሳይ በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ሕግ ተምረው በሩሲያ የኢትዮጵያ ኤምባሲና በሌሎች አገራት ያገለገሉትና ለቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም የሩሲያኛ ቋንቋ አስተርጓሚ የነበሩት አቶ በላይ ግርማይ ሩሲያን “ሁለተኛ አገሬ” ይሏታል። ሩሲያ በሺህዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን በነጻ ያስተማረች፣ ኢትዮጵያ በየዘመኑ የገጠማትን ውጫዊ ወረራዎች ስትመክት ከጎኗ በመቆም የነበራትን ውለታ ያነሳሉ።

መርህ ተኮር የሆነውን

ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ተከትሎ የሩሲያ ቱሪስቶችም በኢትዮጵያ ጉብኘት የማድረግ ፍላጎታቸው ጨምሯል። በባለብዙ ወገን መድረኮችም ላይ ትብብራቸው አድጓል።

የደርጉ ሊቀመንበርና የአገሪቷ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም (ሌ/ኮ) በአውሮፓዊያኑ 1969 በሞስኮ ያደረጉት ጉብኝት የኢትዮ- ሩሲያን ግንኙነት ደረጃ ፍጹም ለወጠው። የደርግ መንግሥት የሕብረተሰባዊነት ርዕዮተ ዓለም መከተሉ ደግሞ ከወትሮው በተለየ የኢትዮጵያና የሶቪየት ኅብረት ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ አድጓል። በ1969 ዓ.ም የሶማሊያው የዜያድ ባሬ መንግሥት ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ሶቪየት ኀብረት አሰላለፏን በፍጥነት በመቀየር ወደ ኢትዮጵያ በመወገን የማይተካ ወታደራዊ ድጋፍ በማድረግ ትልቅ ውለታ ዋለች። መረጃዎች እንደሚያሳዩት በወቅቱ ሶቪየት ኅብረት የቁሳቁስና አንድ ሺህ ገደማ የሰው ኃይል በመላክ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እንዲከበር የክፉ ቀን አጋርነቷን አሳይታለች። ከዚያም በኋላ የኢትዮጵያ የግዛት አንድነት መከበርና ውስጣዊ ሰላም እንዲሰፍን በተደረጉ የትብብር ስምምነቶች ሶቪየት ኅብረት ትልቅ



86

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

ሚና ተጫውታለች። በወቅቱ ያደረገችው ድጋፍ ከሰሃራ በታች ላሉ አገራት ትልቁ እንደነበር ይወሳል።

የደርግ መንግሥት ውድቀትና የሶቪየት ኅብረት መበታተን በተመሳሳይ ወቅት መከሰቱ ይታወሳል። የደርግን ውድቀት ተከትሎ ወደ ሥልጣን በመጣው የኢሕአዴግ መንግሥት በርዕዮተ ዓለም መለያየትን ተከትሎ በደርግ የነበረው የትብብር መልክ በተወሰነ መልኩ ተቀይሯል። ያም ሆኖ ሩሲያ ለኢትዮጵያ የነበራት ወዳጅነትና ድጋፍ ቀጥሏል። የኢትዮ-ኤርትራን ጦርነት ተከትሎ ሩሲያ የኢትዮጵያን ወታደራዊ አቅም ማጠናክር የሚያስችላትን ትብብር አድርገዋል። በፈረንጆቹ ታህሳስ 2001 የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በሞስኮ ባደረጉት ይፋዊ ጉብኝት ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር የወዳጅነት ግንኙነት መርሆች ስምምነትን (Declaration on Principles of Friendly Relations and Part- nership) ተፈራርመዋል። ስምምነቱም በንግድ፣ በሳይንስ፣ በባህልና በጸጥታ ጉዳዮች ላይ ያተኮረና ያጋራ ሉዓላዊነት መጠበቅን ያረጋገጠ ነበር።

በኋላም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በፈረንጆቹ 2013 ለቡድን 20 አገራት ስብሰባ ወደ ሴንት ፒተርስበርግ ባቀኑበት ወቅት ኢኮኖሚያዊ ትብብርን ማሳደግ በሚቻልባቸው ሁነታዎች ላይ መክረዋል። በተመሳሳይ ከአንድ ዓመት በኋላ በ2014 (እ.አ.አ) የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ አዲስ አበባን የጎበኙ ሲሆን በኃይል፣ በሥነ ምድርና በከፍተኛ ትምህርት መስኮች ትብብር ማሳደግ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ከኢትዮጵያ መሪዎች ጋር ተወያይተዋል። ያም ሆኖ እስከ አገራዊ ለውጡ ድረስ በኢሕአዴግ

መንግሥት የነበረው የኢትዮ-ሩሲያ ወዳጅነት የተጠበቀውን ያህል ጠንካራ እንዳልነበር የሚያነሱ ተንታኞች አሉ።

በተለያዩ ሥርዓተ መንግሥታት የተለያየ መልክ ቢኖረውም ቅሉ በሁለቱ አገራት መካከል ጥልቅ ታሪካዊና መንፈሳዊ ትስስሮች አሉ። በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢያቭገኒ ተርክኺን ‘በኢትዮጵያና በሩሲያ ሕዝቦች መካከል የባህል፣ የመንፈስና የስሜት ቅርበት አለ’ ባይ ናቸው።

የኢትዮ-ሩሲያ ወዳጅነት አዲስ እጥፋት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ መንበረ ሥልጣን ከመጠቡት መጋቢት 2010 ዓ.ም ጀምሮ የነበሩ ውስጣዊ ሪፎርምች የውጭ ግንኙነትም አዲስ መልክ እንዲይዝ አድርገዋል። ታሪካዊው የኢትዮ-ሩሲያ ወዳጅነትና ትብብርም በአዲስ ምዕራፍ እንዲታደስ አስችሏል። ብዙዎች ይህን የዲፕሎማሲው አዲስ ዕይታ ታሪካዊ እጥፋት ነው ይሉታል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚመራው የኢትዮጵያ ልዑክ በጥቅምት 2012 ዓ.ም በመጀመሪያው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባዔ ተሳትፏል። ከጉባዔው በተጓዳኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እና የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በቅርበት መክረዋል። መሪዎቹ በውይይታቸው በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በቴክኖሎጂ ሽግግር በተለይም በግብርና፣ በታዳሽ ኃይልና መሰረተ ልማት እንዲሁም በትምህርት መስክ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ ትብብራቸውን በአዲስ ምዕራፍ ለማላቅ ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋገጠዋል።



87

ይህ ታሪካዊ ውይይት በሁለቱ አገራት ቀጣይ ጉዞ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ስምምነት እንዲፈራረሙ አስችሏል። የኒውክሌር ኃይልን ለሰላማዊ ዓላማ ለመጠቀምና ኢትዮጵያ በሩሲያ የቴክኒክ ድጋፍ በኩል የራሷን የኒውክሌር ኃይል ልማት ለመጀመር መሰረት የተጣለበት ስምምነት ሲሆን፤ በዚህም የሩሲያ አቶሚክ ኢነርጂ ኮርፖሬሽን (Rosatom) እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሰላማዊ የኒውክሌር ኃይል ልማት የትብብር ፍኖተ ካርታ የተፈራረሙበት ነው።

በታኅሣስ 2012 ዓ.ም የሩሲያ-ኢትዮጵያ ወታደራዊ-የቴክኒክ ትብብር የሥራ ቡድን 10ኛ ስብሰባውን ያካሄደ ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮም በተለያዩ ጊዜያት በአዲስ አበባ የተለያዩ ወታደራዊ የቴክኒክ ቡድኖች ስብሰባዎች ተካሂደዋል።

በ2013 ዓ.ም ኢትዮጵያ እና ሩሲያ በተመሳሳይ ወታደራዊ ትብብር ላይ ያተኮረ ስምምነት ተፈራርመዋል። በሀምሌ 2014 ዓ.ም የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሴርጌይ ላቭሮፍ ኢትዮጵያን የጎበኙ ሲሆን በወታደራዊ ቴክኒካል ድጋፍ፣ በጸረ ሽብርተኝነትና በአፍሪካ ቀንድ ሰላም ማስጠበቅ ዙሪያ ምክክሮች ተደርገዋል። ኢትዮጵያና ሩሲያ ከፖለቲካዊ ባሻገር ኢኮኖሚያ ትብብራቸውን ወደላቀ ደረጃ ለማሳደግ አመርቂ ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎች ተከናውነዋል።

በ2022 በሩሲያ ድጋፍ የታደሰው የደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል ከሩሲያ ቀይ መስቀል (RRC) ጋር በትብብር እንዲሠሩ በኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር በኩል ስምምነት ተፈርሟል። የሩሲያ የሳይንስ እና ባህል ማዕከል፣ የሩሲያ ቀይ መስቀል፣ በባህል እና ትምህርት ዕድል ላይ የሚሠራው (Rossotrud-

nichestvo)፣ የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር፣ የሩሲያ ቴሌኮም ኮርፖሬሽን (FSMTC)፣ የከፍተኛ ማሽነሪዎች እና ቴክኖሎጂዎች አምራች የሆነው ‘Rostec’፣ እና የኢትዮጵያ-ሩሲያ ሥነ-ሕይወት ኢንስቲትዩት በአዲስ አበባ ቢሮዎቻቸውን ከፍተው እየሠሩ ይገኛሉ። በ1987 ዓ.ም የጀመረው የኢትዮጵያ-ሩሲያ የጋራ የሥነ-ሕይወት ምርምር ማዕከልም ሥራውን እንዲቀጥል ተደርጓል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዓለም አቀፍ የአቶሚክ ፎረም ላይ ለመሳተፍ ወደ ሩሲያ አቅንተው ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ጋር መክረዋል። በዚሁ ጊዜም የ‘ሮሳቶም’ ዋና ዳይሬክተር አሌክሲ ሊካቼቭ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ቀደም ብሎ በተፈረመው የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የድርጊት መርሐ-ግብር ተለዋውጠዋል።

“ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን “ኢትዮጵያ በአፍሪካ የረዥም ጊዜ አስተማማኝ አጋራችን ነች፤ በ1898 በአገራቱ መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተመሥርቷል” ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው የአገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት በጣም ጠንካራ መሆኑን፣ አገራቱ የጋራ ታሪክ እና ሃይማኖት እንዲሁም ብዙ የሚጋሯቸው ፖሊሲዎች እንዳሏቸው ተናግረዋል።”

ሩሲያ እንደቀደመ ታሪኳ ሁሉ በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን ግጭት ተከትሎ በዓለም አቀፍ መድረክ በተለይም በፀጥታው ምክር ቤት ያላትን ድምጽ በመጠቀም በአንዳንድ ምዕራባዊያን አገራት ዘንድ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን ጣልቃገብነትና ዲፕሎማሲያዊ ጫና በመቃወም የምንጊዜም የኢትዮጵያ ወዳጅነቷን አረጋግጣለች። የኢትዮ-



88

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

ሩሲያ የሁለትዮሽ ግንኙነት ምንም የዓለም መልክ ቢለዋወጥና ተናጠላዊ ማዕቀቦች ቢበረቱም መልኩን ሳይቀይር እያበበ ቀጥሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሐምሌ 2015 ዓ.ም በሴንት ፒተርስበርግ ከተካሄደው ሁለተኛው የሩሲያ አፍሪካ ጉባዔ ጎን ለጎን ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር በኒውክሌር ኃይል ትብብርና ስትራቴጂክ ትብብር ሂደት ላይ መክረዋል።

በተለይም ጥር 2016 ዓ.ም ኢትዮጵያ በይፋ የብሪክስ አባልነት መቀላቀሏን ተከትሎ የኢትዮ- ሩሲያ ትብብርና አጋርነት አድማሱን እንዲያሰፋ አስችሏል። የሁለቱ ወዳጅ ሀገራት ትብብር ከሁለትዮሽ ብቻ ሳይሆን በባለ ብዙ ወገን ዓለም አቀፍ መድረክም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ዕድል ፈጥሯል።

“ከድህረ ሶቪየት ኅብረት በኃላ `በነበረው ሁኔታ ላልቶ የቆየው የኢትዮ-ሩሲያ ኢኮኖሚያዊ ትብብር ከአገራዊ ለውጡ ወዲህ ግን በአዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሯል። አሃዛዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የሁለትዮሽ የንግድ ልውውጥ ምጣኔ በፍጥነት እያደገ ነው። ለአብነትም በፈረንጆቹ 2024 የመጀመሪያ 10 ወራት የንግድ ልውውጥ 40 በመቶ ያደገ ሲሆን በ2025 ደግሞ በሁለት እጥፍ ከፍ ብሏል”።

መስከረም 15 ቀን 2018 ዓ.ም በሩሲያ አቶሚክ ኢነርጂ ኮርፖሬሽን (ሮሳቶም) ዋና ዳይሬክተር አሌክሲ ሊካቼቭ እና በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) መካከል የተፈረመው ስምምነት ሮሳቶም እና የኢትዮጵያ

ኤሌክትሪክ ኃይል በኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ለመገንባት ለሚያደርጉት ትብብር ተግባራዊ እርምጃን የሚያስቀምጥ ነው። እነሆ በያዝነው ታህሳስ 2018 ዓ.ም ደግሞ ኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ኮሚሽን አቋቁማ በይፋ ሥራ ያስጀመረች ሲሆን የኢትዮጵያ የኒውክሌር ልማት ፕሮግራም ላይ የመከረ መድረክም ተካሂዷል።

የቅርብ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ለትምህርት ወደ ሩሲያ አቅንተዋል። የሩሲያ መንግሥትም የኢትዮጵያን ተማሪዎች የመቀበል ምጣኔን ለማሳደግ ወስኗል። በኢትዮጵያም ከ400 ያላነሱ የሩሲያ ዜጎች በተለያዩ ፕሮጀክቶችና የዲፕሎማሲ ተልዕኮ ኢትዮጵያ ውስጥ ይኖራሉ። በአዲስ አበባ እና በሞስክ ለሁለቱ አገራት ቋንቋና ባህል ዕድገት የሚበጁ ሥራዎች እየተከናወኑ ቀጥለዋል። በቅርቡ የኢትዮጵያ የባህል ልዑክ ወደ ሩሲያ ማቅናቱ የሚታወስ ሲሆን በአዲስ አበባው የሩሲያ የባህልና ቋንቋ ማዕከልም በተለያዩ ጊዜያት የሁለትዮሽ የባህልና ጥበብ ትስስርን ለማጠናከር ያለሙ መድረኮች ይካሄዳሉ።

በፖለቲካው መስክም የኢትዮጵያና የሩሲያ ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ ተሸጋግሯል። ባሳለፍነው ዓመት ለብልጽግና ፓርቲ ጉባዔ በአዲስ አበባ የተገኙት የዩናይትድ ሩሲያ ፓርቲ ሱፕሪም ካውንስል ቢሮ አባልና የሩሲያ ፌዴሬሽን ሴናተር አንድሬ ክሊሞቭ “ኢትዮጵያና ሩሲያ አያሌ ዓመታት ያስቆጠረ ታሪካዊ ወዳጅነት አላቸው። በንግድ፣ በሰብዓዊ እርዳታ፣ በተለያዩ መስኮች ላይ የተመሰረተ ግንኙነታቸውም እያደገ መጥቷል። የኢትዮ-ሩሲያ ትብብር በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን በተለይም ብሪክስ እና የአፍሪካ-ሩሲያ የትብብር ማዕቀፍ



89

ተጠናክሮ ይቀጥላል። የዩናይትድ ሩሲያ ፓርቲ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ያለው ግንኙነት የበለጠ እንዲጠናከር ይሰራል” ብለዋል።

“የኢትዮ-ሩሲያ የባህል፣ የፖለቲካ፣ የታሪክ እና የዲፕሎማሲ ወዳጅነት ጥልቅና ታሪካዊ ቢሆንም በኢኮኖሚው መስክ ያላቸውን አቅም በቅጡ እንዳልተጠቀሙ ይወሳል። ባለፉት ቅርብ ዓመታት ግን ይህን ዕድል በአግባቡ ለመጠቀም በቁጭት የተነሱ ይመስላል”።

አሁናዊ የኢትዮ-ሩሲያ ወዳጅነትና ትብብር ከፖለቲካ ወደ ኢኮኖሚም ተሸጋግሯል። የብሪክስ ማዕቀፍ ደግሞ ሌላ መሰረት ጥሏል። ይህ ደግሞ በሁለቱ አገራት መሪዎችም ተረጋግጧል። ገራቱ በኢነርጂ፣ በኢንፎርሜሽን ደህንነት፣ በአየር ትራፊክ፣ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂዎችና በአቶሚክ ኢነርጂ አጠቃቀም ረገድ ስምምነቶችን አድርገዋል።

መውጫ

የኢትዮ-ሩሲያ የትብብር መልኮች በተለዋዋጭ የዓለም ሁኔታ ውስጥ የማይናወጥ ግንኙነት እንዳላቸው ታሪክና ሁኔታ ገልጦታል። ይህ የወዳጅነት እሴትና ቅርስ አድማስ ይሰፋ ዘንድ የዲፕሎማሲው በር ሰፍቷል። በአድዋ ጦርነት ዋዜማ ጀምሮ 130 ዓመታት የዘለቀው የዲፕሎማሲ ጉዞ እስከ ኒውክሌር ልማት ፕሮግራም የአጋርነት ከፍታ ደርሷል።

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በ2012 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር ሲገናኙ የኢትዮጵያና የሩሲያን ጥንተ ታሪክ ትስስርና ወዳጅነት በአጽንኦት

ጠቅሰው ነበር። በተመሳሳይ ባሳለፍነው ወርሃ መስከረም ወደ ሞስኮ ካቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር በነበራቸው ውይይት ኢትዮጵያን “የረጅም ዘመን አስተማማኝና ቁልፍ አፍሪካዊት አጋራችን ናት” ብለዋታል።

ኢትዮጵያና ሩሲያ የትናንትና እና የዛሬ በተለዋዋጭ ዓለም ውስጥ የማይለዋወጥ ወዳጅነታቸውን ይበልጥ የሚያሳድግ የኒውክሌር ኃይል ልማትን ጨምሮ በብዝሃ ኢኮኖሚ መስኮች ትብብራቸውን የሚያጠነክር መሆኑን አንስተዋል። ከሁለትዮሽ የትብብር ልህቀት ባሻገር ብሪክስን በመሰሉ የባለብዙ ወገን መድረኮች የሁለቱን አገራት ነገ ብሩህ ለማድረግ የሚኖረውን ወሳኝ ሚና አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው ሩሲያ ለዘመናት ለኢትዮጵያ ክብርና ሉዓላዊነቷን መጠበቅ ላበረከተችው የታሪክ ዑደት ሁሉ ሩሲያ ለነበራት አጋርነትና ድጋፍ ዕውቅና በመስጠት በቀጣይም ትብብራቸው መጠናከር እንደሚገባው አጽንኦት ሰጥተዋል። “ሩሲያ በዓለም ላይ ቁልፍ አጋራችን እንደሆነች እናምናለን፤ ይህ ትብብር እንዲልቅም እንሻለን” ብለዋል።

የሁለቱ አገራት መሪዎች እንዳሉትም የዲፕሎማሲ ይትባህልን የለወጠው የኢትዮ-ሩሲያ ወዳጅነት አድማሱን እያሰፋና ፍሬያማነቱን እያረጋገጠ መቀጠሉ እሙን ነው!



90

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

ማኅበራዊ

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ እና በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ትብብር የተዘጋጀ

ሕይወት ለመታደግ



91

ሕይወት ለመታደግ

በፍቅርተ ባልቻ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመላክተው በዓለማችን ከስምንት ሴቶች መካከል አንዷ በሕይወት ዘመኗ የጡት ካንሰር ያጋጥማታል። የጡት ካንሰር በሽታ በተለይ በ157 አገራት እያስከተለ ያለው ችግር ሰፊ ነው። በዓለም ላይ ከሚከሰተው የጡት ካንሰር መካከል አንድ በመቶው የሚሆነው በወንዶች ላይ የሚከሰት ስለመሆኑም መረጃዎች ያሳያሉ።

በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር 2020 ዓ.ም የተካሄደ ዓለም አቀፍ ጥናት በአንድ ዓመት ጊዜ ብቻ 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን አዲስ የጡት ካንሰር ታማሚዎች መገኘታቸውን አረጋግጧል። ‘Globacon‘ ካንሰርን የተመለከቱ ዓለም አቀፍ መረጃዎችን ይፋ የሚያደርግ



92

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

ድረገጽ ሲሆን በተጠቀሰው 2020 ዓ.ም 685 ሺህ ሰዎች በጡት ካንሰር ምክንያት ሕይወታቸው ማለፉንም ጠቅሷል።

የካንሰር በሽታ እና ሞት በብዛት እየተከሰተ ያለው ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት ውስጥ ነው። በእነዚህ አገራት የታማሚዎች እና የሟቾች ቁጥር የጨመረው ዘመናዊ እና ሁሉን አቀፍ (com- parhensive) ህክምና እና እንክብካቤ ባለመኖሩ እንዲሁም ታማሚዎች ወደ ህክምና የሚሄዱት ዘግይተው በመሆኑ ነው።

እ.አ.አ 2040 ዓ.ም የካንሰር ታማሚዎች ቁጥር 28 ነጥብ 4 ሚሊየን እንደሚደርስ እየተተነበየ ነው፤ ይህ አሃዝ የሚያሳየው በ2020 ዓ.ም ከነበረበት የ47 በመቶ የታማሚዎች ቁጥር እንደሚጨምር ነው። ተገቢ እና ጤናማ ያልሆኑ የኑሮ ዘይቤዎችና ልማዶች ለቁጥሩ መጨመር አበይት ምክንያቶች መሆናቸው ተገልጿል።

ወደ አገራችን መለስ ስንል በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የጡት ካንሰር ታማሚዎች ለህልፈተ ሕይወት እንደሚዳረጉ መረጃዎች ያሳያሉ። የጡት ካንሰር በአገራችን ለከፋ ህመም እና ለሞት ከሚዳርጉ በሽታዎች እንዲሁም የካንሰር ዓይነቶች

መካከል ቀዳሚው ነው።

NATIONAL GUIDELINE FOR BREAST HEALTH, EARLY DIAGNOSIS AND TIMELY BREAST CANCER MANAGEMENT IN ETHI- OPIA (2024-2028) በሚል ርዕስ የጤና ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው ሰነድ እንዳስነበበው አዳዲስ የጡት ካንሰር ታማሚዎች ቁጥር 16 ሺህ 133 (እ.አ.አ በ2020 ዓ.ም) ነበር። ሰነዱ አያይዞ እንደጠቀሰው በአገራችን በካንሰር ከሚያዙ ሴቶች መካከል አንድ ሦስተኛው የጡት ካንሰር ታማሚዎች ናቸው።

በአዲስ አበባ በሴቶች ላይ ከሚያጋጥሙ የካንሰር ዓይነቶች ውስጥ 35 በመቶውን የሚሆነው የጡት ካንሰር ነው፤ ይህ አሃዝ የሚያሳየው በከተማዋ የካንሰር ምርመራ ከሚያደርጉ ሴቶች መካከል የጡት ካንሰር የሚገኝባቸው ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ነው።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ሌላው ነጥብ በሽታው ከተስፋፋ በኋላ ወደ ህክምና ተቋማት መምጣት ችግሩን ይበልጥ እያባባሰው የመገኘቱ ሁኔታ ነው። በዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት በርካታ ሰዎች ሕይወታቸውን የሚያጡበት አንደኛው ምክንያት ስለበሽታው በቂ ግንዛቤ



93

አለመፈጠሩ እንደሆነ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ መምህርና የካንሰር ህክምና ስፔሻሊስትና የትምህርት ክፍሉ አስተባባሪ ዶ/ር መሀመድ ኢብራሂም ይጠቅሳሉ።

በኢትዮጵያ 71 በመቶ የሚሆኑት የጡት ካንሰር ታማሚዎች በጣም ዘግይተው (ማለትም ህመሙ ሦስት እና አራተኛ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ) ወደ ህክምና ተቋማት የሚሄዱ በመሆኑ የመዳን ዕድላቸውን በጣም ዝቅተኛ እንደሚያደርገው በአጽንኦት ገልፀዋል።

የጡት ካንሰር ምንድን ነው?

በሰውነታችን ውስጥ ያሉ ሕዋሳት ከተለመደው አሰራር ወጣ ባለ እና ከቁጥጥር ውጭ በሆነ መልኩ ሲያድጉ እንዲሁም ለአሰራር ሳይመቹ ሲቀሩ፣ በአግባቡ እየሰሩ ያሉትን ሌሎች ሕዋሳት በማጥቃት ጉዳት ሲያደርሱ የሚከሰት በሽታ ነው - ካንሰር።

በጤናማ ሰውነት ውስጥ የሕብረ ሕዋሶች እና የአካል ክፍሎች መደበኛ ሥራን ለመጠበቅ ሕዋሳት ያድጋሉ፣ ይሞታሉ። ይህ ሥርዓታማ ሂደት ሲስተጓጎል የካንሰር በሽታ ይከሰታል፤ የካንሰር ዕጢ ይፈጠራል። በአጠቃላይ ካንሰር በሰው አካል ውስጥ ከቁጥጥር ውጭ በሆነ እና ባልተለመደ የሕዋሳት መባዛት ምክንያት የሚከሰት በሽታ ነው። ካንሰሩ ካጠቃው የአካል ክፍል በመነሳት በአቅራቢያው ወደሚገኙና ወደ ሌሎች የአካል ክፍሎች ይሰራጫል። “በሰውነታችን ውስጥ ያሉ ሕብረ ሕዋሳት ያድጋሉ፣ ይሞታሉ፤ ይህ ሂደት ተፈጥሯዊ እና ትክክለኛ ነው። ካንሰር የሚሆነው ይህ ተፈጥሯዊ ሂደት ሲዛባ ነው።“ ሲሉ የካንሰርን ምንነት ያብራሩት ዶ/ር መሀመድ ናቸው።

የጡት ካንሰር በአብዛኛው በሴቶች ላይ የሚከሰት ቢሆንም ወንዶችንም የሚያጠቃ የካንሰር ዓይነት ነው። ከቁጥጥር ውጭ በሆነ ሁኔታ ማደጉና በአጭር ጊዜ ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች በመዛመት የከፋ ችግር ሊያስከትል የሚችል በሽታ መሆኑ ባህሪይውን ልዩ ያደርገዋል።

ጡት በተፈጥሮው ወተት ለማመንጨት የሚያስችሉ በርካታ ከረጢት መሰል ነገሮች እንዲሁም እነዚህን ከጡት ጫፍ ጋር የሚያገናኙ ቱቦዎች አሉት። እነዚህ ቱቦዎች በእርግዝና ወቅት



94

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

ወተት ለማመንጨት ትልቅ ሚና ይጫወታሉ። ታዲያ የጡት ካንሰር በአብዛኛው ማደግ የሚጀምረው በእነዚህ ቱቦዎች ውስጥ ነው። የጡት ካንሰር ተፈጠረ የሚባለው አንድ ጤነኛ ያልሆነ ሕዋስ በሰውነት ውስጥ ተፈጥሮ ከገደብ በላይ መራባት ሲጀምር ነው። የሚራባው ሕዋስም በጊዜ ሂደት ጤናማ የነበሩ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ህብረ ሕዋሳትን በማጥቃት በሽተኛ ያደርጋቸዋል።

ተጋላጮች እና ምልክቶቹ …

በአብዛኛው ሴቶችን የሚያጠቃው የጡት ካንሰር በሽታ የሚመጣበት ምክንያት በውል አይታወቅም። ሆኖም ተጋላጭ እንደሚያደርጉ የተለዩ ነጥቦች አሉ። ለዚህ ከሚጠቀሱና ለጡት ካንሰር በሽታ ተጋላጭ ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል አንደኛው ዕድሜ ነው፤ ዕድሜያቸው ከ40 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች ለካንሰር ተጋላጭ ናቸው። በጡት ካንሰር የተያዘ ቤተሰብ ያላቸው ሰዎች ለካንሰር ያላቸው ተጋላጭነት ይጨምራል። የወር አበባቸውን ቀድመው በልጅነት ያዩ፣ ከ30 ዓመት በኋላ ልጅ የሚወልዱ ወይም ልጅ ያልወለዱ፣ ዘግይተው ያረጡ ሴቶችም ለጡት ካንሰር ተጋላጮች ናቸው።

እንደ ዶ/ር መሀመድ ማብራሪያ ለጡት ካንሰር ተጋላጭ የሚያደርጉ ምክንያቶችን በአራት ከፍሎ ማየት ይቻላል። የመጀመሪያው በሽታው ከኤስትሮጂን ሆርሞን ጋር የተያያዘ ስለሆነና ይህ ሆርሞን በሴቶች ላይ በብዛት ስለሚገኝ ሴት መሆን በራሱ ተጋላጭ ያደርጋል። በሌላ በኩል በእርግዝናና በጡት ማጥባት ወቅት የኢስትሮጂን ሆርሞን መጠን ስለሚቀንስ ለካንሰር የመጋለጥ ዕድል ዝቅ ይላል።

በሣምንት ውስጥ ከ150 እስከ 300 ደቂቃዎች የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ ለካንሰር የመጋለጥ ዕድልን ከ10 እስከ 20 በመቶ ለመቀነስ ይረዳል። አመጋገብን ጤናማ እና የተመጣጠነ ማድረግም ተጋላጭነትን ለመቀነስ ይጠቅማል።

አንዲት ሴት በቤተሰቧ ውስጥ እናቷ፣ ወይንም እህቷ በካንሰር የተጠቁ እንደሆነ የመጀመሪያ ደረጃ ስጋት ውስጥ ነው የምትሆነው፤ ይህም ሁለተኛው ለካንሰር ተጋላጭ የሚያደርግ ምክንያት ነው። ሦስተኛው ምክንያት ለጨረር የመጋለጥ ሁኔታ መኖሩ ሲሆን፤ አራተኛው



95

አጋላጭ ምክንያት የወር አበባን ቀደም ብሎ ማየት መጀመር እና ከ50 እስከ 55 ዓመት ዕድሜ ድረስ መዘግየት ነው።

የመጋለጥ ዕድላቸው ሰፊ እንደሆነ የተለዩ ሴቶች ከሦስት እስከ አራት በመቶ ተጋላጭነታቸው እንደሚጨምር ዶ/ር መሀመድ ጠቅሰዋል። የሰውነት ክብደት መጨመር፣ እንቅስቃሴ አለማድረግ (የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ የእግር ጉዞ፣ ወዘተ … )፣ ሲጋራ ማጤስ፣ የአልኮል መጠጥ ማዘውተር፣ የተመጣጠነ ምግብ አለመመገብ፣ አለመውለድ እና አለማጥባት ተጋላጭነት ከሚጨምሩ ምክንያቶች መካከል ናቸው።

የጡት ካንሰር ሲጀምር ህመምም ሆነ ምልክቶች የሉትም።

ምልክቶቹን ማወቅ በሽታውን በመረዳት ወደ ምርመራና ህክምና በማምራት ሕይወትን ለመታደግ ያስችላል። ሁሉም ዓይነት ጡት ላይ የሚወጡ እብጠቶች ካንሰር ባይሆኑም አንደኛው የጡት ካንሰር ምልክት በጡት ላይ የሚከሰት ጠጣር እብጠት ነው።

ከጡት ጫፍ ደም የቀላቀለ ፈሳሽ መውጣት፣ የጡት ጫፍ አካባቢዎች መቅላትና ወደ ውስጥ መሰርጎድ፣ በጡት ጫፍ አካባቢና በብብት ውስጥ እብጠት መከሰትና ሙቀት ያለው መሆን፣ የጡት ቆዳ መሸብሸብ ወደ ውስጥ መግባት ወይም እንደ ብርቱካን ልጣጭ ዓይን ማውጣት ካንሰር ስለመከሰቱ ጠቋሚ ምልክቶች ናቸው።

ዶ/ር መሀመድ እነዚህ ምልክቶች ሲታዩ ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ አስፈላጊውን ህክምናና ምርመራ ማድረግ እንደሚገባ ያሳስባሉ። ጡት ላይ የሚከሰትን ችግር በጊዜው ለማወቅ ሴቶች የዘርፉ የጤና ባለሙያዎች በሚሰጡት ምክር በመታገዝ ቢያንስ በሣምንት ሁለት ጊዜ የጡታቸውን ሁኔታ በራሳቸው እንዲመረምሩ ይመከራል።



96

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

የኮሌጁ እንቅስቃሴዎች…

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ የህክምና እና የማስተማሩን ስራ በአንድነት አጣምሮ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ተቋም ነው። የጡት ካንሰር ልየታ እና ህክምና በህክምና ኮሌጁ እየተሰጡ ካሉ አገልግሎቶች መካከል አንዱ ነው። በተቋሙ እንደ አስፈላጊነቱና እንደ በሽታው ደረጃ በተናጠል ወይም በአንድ ላይ የሚሰጡ የተለያዩ ዓይነት ህክምናዎች አሉ። የቀዶ ህክምና፣ የኬሞ እና የሆርሞናል ቴራፒ ዋናዎቹ ናቸው።

እነዚህና ሌሎች የጡት ካንሰርን ለመለየትና ለማከም ተግባራዊ መደረግ ያለባቸው ህክምናዎች (ከጨረር ህክምና በስተቀር) እየተሰጡ ስለመሆኑ ዶ/ር መሀመድ ገልጸዋል። ከህክምናው ባሻገር



97

የሥነልቦና ድጋፍ፣ የቤተሰብ እና የማኅበረሰብ እገዛ ለታማሚው እጅግ ጠቃሚ በመሆኑ በህክምና ኮሌጁ የታማሚ ቤተሰቦችን ጭምር የማማከር ሥራ እንደሚሰራ ዶ/ር መሀመድ ይናገራሉ።

ዶ/ር መሀመድ ካንሰርን ቀድሞ ለመለየት የሚረዱ ዘዴዎችን በሦስት ከፍለው አብራርተዋቸዋል። በተቋሙ ሰዎች ጤንነታቸውን በራሳቸው እንዲከታተሉ ለማስቻል የጡት ካንሰር ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ (breast selfaware- ness)፣ ሁለተኛ በባለሙያ አማካኝነት የሚደረግ ምርመራ (clinical breast exam)፣ የማሞግራፊ (mammography) ምርመራ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ነው።

ማሞግራፊ በጡት ላይ ካንሰር መኖር አለመኖሩን ለይቶ ሊያሳይ የሚችል መሣሪያ ነው። ይህ ጡትን ራጅ በማንሳት የሚደረግ አስተማማኝ የጡት ካንሰር ምርመራ ዘዴ ነው። ማሞግራፊ ከሌሎች መመርመሪያ መሳሪያዎች በተሻለ ስለ ካንሰር መረጃ የሚሰጥ ስለመሆኑ የመስኩ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ከ40 እስከ 50 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሴቶች በዚህ መሳሪያ በዓመት አንድ ጊዜ እንዲመረመሩ ይመከራል፤ በተለይ ምልክቶች ካሉ እና ተጋላጭ ከሆኑ ሰዎች መካከል የሆነች ሴት በዚህ መሳሪያ ምርመራ ማድረግ ይኖርባታል።

እነዚህን ህክምናዎች በስፋት እና ዘመኑን በዋጀ መልኩ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተንቀሳቀሰ በሚገኘው በህክምና ኮሌጁ በቅርቡ ከዚህ ቀደም ከነበሩት በተጨማሪ አዲስ እና ዘመናዊ የካንሰር መመርመሪያ መሳሪያዎች መምጣታቸውና ለአገልግሎት ዝግጁ መሆናቸው ተበስሯል። ሆስፒታሉ የጡት ካንሰርን በማከም እና

በመለየት ሂደት የላቀ አስተዋጽኦ ያላቸውን ሁለት የማሞግራፊ መሳሪያዎች ሥራ አስጀምሯል። እነዚህን የማሞግራፊ መሳሪያዎች መጠቀሙ የጡት ካንሰር ያለባቸውን ሰዎች አስቀድሞ ለማወቅና በሽታው ከመሰራጨቱና የከፋ ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት አስፈላጊውን ህክምና ለመስጠት በእጅጉ ይጠቅማል።

በበጎ አድራጊዎች እገዛ በ120 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገዙት ማሽኖቹ የሴቶችን የጡት ካንሰር ተጋላጭነት ለመቀነስ ብሎም ካንሰሩን አስቀድሞ በመለየት አስፈላጊውን ህክምና በወቅቱ ለመስጠት ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖራቸው ተመላክቷል። ቀልጣፋና ታማሚውን ማዕከል ያደረገ አገልግሎት ለመስጠት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እንደሚያግዙም ተገልጿል።

በህክምና ኮሌጁ ካንሰር ላይ የሚሰራ በቂ የሰው ኃይል እና ግብዓት መኖሩን የጠቀሱት ዶ/ር መሀመድ በተቋሙ ያለውን ተሞክሮ ወደ ሌሎች ለማስፋት እየተሠራ እንደሆነና በተለያዩ ተቋማት በልዩ ሁኔታ የካንሰር ምርመራና ልየታ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ክሊኒኮች እንዲኖሩ እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ እንደማሳያ አንስተዋል።

ኮሌጁ ዓመቱን ሙሉ በመደበኛነት ከሚሰጠው አገልግሎት ጎን ለጎን በጥቅምት ወር በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው የካንሰር ንቅናቄ አካል በመሆን የተለያዩ ተግባራትን አከናውኗል። በወርሃ ጥቅምት 2018 ዓ.ም ቁጥራቸው ከሁለት ሺህ ሁለት መቶ ዘጠና በላይ የሚሆኑ ሰዎች የተሳተፉባቸውን የተለያዩ መድረኮች በማዘጋጀት ግንዛቤ ለማስጨበጥ ተንቀሳቅሷል። ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች የጡት ካንሰር ምርመራ (Clinical breast



98

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

exam) ተደርጎላቸዋል።

ቀደም ሲል በተጠቀሱትን መመዘኛዎች መነሻ በማድረግ ለጡት ካንሰር ይበልጥ ተጋላጭ እንደሚሆኑ የተገመቱ አራት መቶ ሃምሳ በላይ ሴቶች በአልትራሳውንድ የታገዘ ምርምራ የተደረገላቸው ሲሆን ለሁለት መቶ ሃምሳ ሴቶች የማሞግራፊ ምርመራ አገልግሎት ተሰጥቷል። በተጨማሪም የጡት ላይ ናሙና (FNAC) በመውሰድ ምርመራ የተደረገላቸው ተገልጋዮች ሃያ አምስት ናቸው።

ካንሰር መኖሩ ከተረጋገጠ በኋላ ህክምናው ሁሉም ዓይነት የካንሰር ህክምናዎች በሚሰጥባቸው ተቋማት እንዲጀመር ይመከራል። የዚህ ምክንያቱ ህክምናው ከተጀመረ በኋላ የተለያዩ የህክምና ዘዴዎችን መጠቀም ሊያስፈልግ ስለሚችል ነው። ዶ/ር መሀመድ “ካንሰር አለ ሲባል ቶሎ ወደ ህክምና ለመግባት መቸኮል ተገቢ አይደለም፤ የተለያዩ የዘርፉ የህክምና ባለሙያዎች ጉባዔ በታማሚው ላይ ስለታየው የካንሰር ሁኔታ በመወያየት የተሻለ የሚባለውን የመጨረሻ አማራጭ ይሰጣሉ“ ይላሉ፡፡

ጉዳቱን ለመቀነስ …

የጡት ካንሰር ተሰራጭቶ ወደ ሌላ የሰውነት አካል ከመድረሱና ከመዛመቱ በፊት ከተደረሰበት ሙሉ በሙሉ ሊድን ይችላል። በማኅበረሰቡ ዘንድ በካንሰር የተያዘ ሰው ይሞታል የሚል አመለካከት የሰረጸ ቢሆንም ነገር ግን ቀድመው ወደ ህክምና ተቋም ከመጡ 99 በመቶውን ማዳን ይቻላል በማለት ሙያዊ አስተያየታቸውን የሰነዘሩት ዶ/ር መሀመድ የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ከጡት ካንሰር ህመም የተለያዩ ደረጃዎች መካከል የመጀመሪያው ደረጃ ዜሮ የሚሰኘው ሲሆን በዚህ ወቅት በሚሰጡ ህክምናዎች በሽታውን መቶ በመቶ ማዳን ይቻላል። በዚህ ደረጃ ላይ ለሚገኝ የጡት ካንሰር የሚሰጠው ህክምና ቀለል ያለ እና ጡት ሳይቆረጥ የሚሰራ ቀዶ ህክምና ነው። በዚህ ደረጃ ላይ የሚገኝ ካንሰር አብዛኛውን ጊዜ የሚታወቀው የማሞግራፊ መሳሪያን በመጠቀም ነው። ደረጃ አንድ ላይ የደረሰን ካንሰርም በህክምና 99 በመቶ ማዳን ይቻላል።

ደረጃ ሁለት ላይ የደረሰ ካንሰር ማዳን የሚቻለው 90 በመቶውን ነው፤ ሰዎች በየዓመቱ የመመርመር ልምድን ካዳበሩ በዚህ ደረጃ ላይ እያለ ካንሰሩን መለየት ይቻላል። ደረጃ ሦስት ካንሰርን ማዳን የሚቻለው ከ50 እስከ 60 በመቶ ብቻ ሲሆን፤ ደረጃ አራት ላይ የደረሰ ካንሰር የመዳን ዕድሉ ከ20 እስከ 30 በመቶ ብቻ ነው።

“ኅብረተሰቡ ያለው እሳቤ እና እምነት ካንሰር የአዛውንቶች በሽታ እንደሆነ ነው። የህክምና ዝግጅታችን አስቀድሞ ማከም ላይ መሆን አለበት የምንለው በዚህ ምክንያት ነው” የሚሉት ዶ/ር መሀመድ በተለይ በአዲስ አበባ 43 በመቶ የሚሆኑ የጡት ካንሰር ታማሚዎች ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በታች መሆኑን ጥናቶች እንደሚያሳዩና በህክምና ተቋማትም በ30ዎቹ እና በ40ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ በርካታ ታማሚዎች እየተገኙ መሆኑን ገልፀዋል። በቂ ግንዛቤ ባለመፈጠሩ ታማሚዎቹ ካንሰሩ ከመሰራጨቱ በፊት ወደ ህክምና ተቋማት አለመምጣታቸው የመዳን ዕድላቸውን የጠበበ እያደረገው በመሆኑ በጡት ካንሰር ምክንያት የሚከሰተውን ሞት የመቀነስ ግብ ተይዞ እየተሠራ ስለመሆኑም አክለዋል።



99

አገራዊው የካንሰር እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን የመከላከል እና የመቆጣጠር ዕቅድ የጡት ካንሰርን አስመልክቶ ግንዛቤ የመፍጠር፣ የቅድመ ልየታ ማድረግ፣ የከፋ ደረጃ ከመድረሱ አስቀድሞ ለታማሚዎች ህክምናና እንክብካቤ ለመስጠት በተለየ ሁኔታ በመስራት የሞት ምጣኔውን እ.አ.አ በ2025 ዓ.ም በ25 በመቶ መቀነስ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

ከዚህ አንጻር የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማድረግ የሚያግዘውንና ዓመቱን ሙሉ አገልግሎት የሚሰጥ ክሊኒክ አቋቁሟል። በመደበኛነት ከሚሰጡት አገልግሎቶች ባሻገር በየዓመቱ በጥቅምት ወር የሚያከናወነው የጡት ካንሰር ምርመራ የዘመቻ እንቅስቃሴ ግንዛቤ በመፍጠር፣ የምርመራ ባህልን በማሳደግ እንዲሁም ካንሰር ያለባቸውን ሰዎች በማግኘት ህክምና እንዲሰጣቸው ትልቅ እገዛ እያደረገ ነው። ይህም በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚከናወነው እንቅስቃሴ የራሱ አበርክቶ እንደሚኖረው እሙን ነው።

የሰው ኃይል እና የግብዓት

አቅሙንም በማሳደግ መጠነ ሰፊ አገልግሎት ለመስጠት በትኩረት እየሰራ ስለመሆኑ የተቋሙ እንቅስቃሴ ያመላክታል። ይህን እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ የጡት ካንሰርን ከመለየት ጀምሮ የሚሰጡ የህክምና አገልግሎቶችን የመጠቀም ባህልን ማሳደግ ከማኅበረሰቡ ይጠበቃል።

በአጠቃላይ በጡት ካንሰር መያዝ ለዘላቂና ለህይወት ዘመን የጡት ካንሰር ህክምና ክትትል ይዳርጋል፤ በዋናነት ራስን ለበሽታው አጋላጭ ከሆኑ ነገሮች በመከላከል እንዲሁም የበሽታው ምልክት ሲታይ በፍጥነት ወደ ጤና ተቋም መሄድ ያስፈልጋል።

ካንሰር የከፋ ደረጃ ከመድረሱ አስቀድሞ ማወቅ ሕይወትን የመታደግ ትልቅ ውሳኔ ነውና የተጋላጭነትን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት በቋሚነት የካንሰር ምርመራ ማድረግ ይመከራል። ወደ ሀኪም በመቅረብ የሚሰማን ስሜት መግለጽ፣ ጡትን መዳሰስና ሌሎች ምርመራዎችን በየጊዜው ማድረግ ተገቢ ነው። የራስን ጡት በራስ መመርመር በጡት ላይ የሚከሰት ማንኛውንም ለውጥ ለማወቅ ስለሚረዳ ራስን ከሞት ለመታደግ ያስችላል።



100

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ መስኖ ልማት ትሩፋቶች

ኢኮኖሚ



101

መግቢያ

ጥንታዊነትቱን የተለያዩ ሰነዶች የሚናገሩለት የመስኖ ሥራ የተጀመረው ቀደምት የሥልጣኔ አሻራ እንዳላቸው ከሚተረክላቸው አገራት መካከል ሱመር፣ ሜሶፖታሚያ (ያሁኗ ኢራቅ፣ ሶሪያ እና ኩዌት አካባቢ ነው። በዚያን ጊዜ የኤፍራጠስና የጤግሮስ ወንዞችን ለመቆጣጠር እና ለማልማት ታሰቦ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ከ6000-5000 ገደማ የመስኖ መፍሰሻ ቦይ በመቆፈር ውሃውን ከወንዞች በመጥለፍ ለሰብል ልማት መዋል ተጀመረ። የሜሶፖታሚያን ዳና ተከትላ በእኛው ዓባይ ውሃ ላይ ተመስርታ በቅድመ ልደተ ክርስቶስ 5000 ገደማ የመስኖ ልማት

በአዲሱ ዘገየ



102

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

የተገበረች አገር ግብጽ ነች። ከዚያ በማስከተል ሕንድ እና ፓኪስታን በዘመነ ኢንዱስ ቫሊ ሲቪላይዜሽን (Indus Valley Civilization) ፣ ጥንታዊት ቻይና (Yellow River region) የመስኖ ልማት ተቋዳሽ ሆኑ።

በኢትዮጵያ ታሪካዊውን የመስኖ አጀማመር በተመለከተ በዘመነ አክሱም ሥርወ-መንግሥት ቅድመ ልደተ ክርስቶስ 1000-700 በትግራይ እና በአማራ አካባቢ መታየቱንና ይኸውም በጥቃቅንና አነስተኛ ደረጃ ወራጅ ወንዞችን በማስቀየስ ቦይ በመቆፈር ወደ እርሻ ማሳዎች ማስገባት መጀመሩን ሰነዶች ያወሳሉ።

በዘመናዊ ብሎም በተቀናጀ መልኩ ታላላቅ የመስኖ ሥራ ደረጃ በአገራችን መስፋፋት የጀመረው በ14ኛው እና 19ኛው ክፍለ ዘመን ነው። ይህ 14ኛው ክፍለ ዘመን ሲወሳ መዘከር ያለባቸው አፄ ዳዊት



103

(1380-1412) ግንባር ቀደሙ ናቸው፤ በተለይም የዓባይ ወንዝ ላይ ግብጾች አዛዥና ተጠቃሚነታቸውን ለማጉላት ሲሯሯጡ የንጉሡ መልስ የዓባይን ምንጭ መዝጋት አልያም መፍሰሻ/መውረጃ መስመሩን መቀየር እንደሚችሉ የማስፈራሪያ መልዕክት ይልኩ ነበር። ልዑካኖችን ሲልኩም የሚያያይዙት መልዕክት “የዓባይን መውረጃ አቅጣጫ መለወጥና ግብጽን ሙሉ ማስራብ ለእኔ ቀላል ነው!” የሚለውን ነው።

የመስኖ ልማት መሠረታዊያን

የመስኖ ምንነት፡- የአማርኛ መዝገበ ቃላቱ መስኖ ለሚለው ቃል የሰጡት ፍቺ “መመሰን፣ ውሃን ማውጣት፣ ውሃን ግመልና በሬ በሚያዞረው በታላቅ መዘውር ከጉድጓድ ከአዘቅት እያወጡ ማፍሰስ ማውጣት ወደ ቡቃያና ወደ አትክልት መውሰድ፣ ማግባት፣ መሳብ፣



104

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

መጎተት ምሣሌ እንደ ግብጦች። በቁሙ የቦይ ውሃ ወደ መሩት ወደ ወሰዱት የሚሄድ” ይላል።

የእንግሊዝኛው ፍች እንደሚያሳየን ከሆነ Irrigate ማለት ማለስለስ፣ ማረስረስ፣ ማራስ፣ ርጥበትን ማደል ማርጠብ፣ ማለት ነው። ይኸውም በፍሳሽ ማጓጓዣ ቦይ፣ በቧንቧ፣ በርጭት፣ በንጥበት መልክ የማዳረስ ዘዴ ሲሆን ለተክልና ዕፅዋት ምግብነትና ዕድገት፣ ተክሎችን መጋቢ ለሆነው አፈር ማለሳለሻነት ያገለግላል። ውሃ የሚለው ቃል ፍቺ ደግሞ “ካራቱ ባህርያት አንዱ የርጥበት፣ የልምላሜ ሥር መሰረት፣ በቀን ብዛት ሜዳውን ገደል የሚያደርግ ፈሳሽ ባህርይ፣ ይዞ ኺያጅ፤ ቦይ ለውሃ ጎመን ለ. . .!” እንዲሉ። ከፍቺዎቹ መረዳት የሚቻለው አንደኛው በሌላው እንደሚገለጽ (መስኖ በውሃ፣ ውሃ በመስኖ) ተወራራሽ ሚና መያዛቸውን ነው።

ስለዚህ በዚህ ስሌታችን ተመርተን “የዓባይን ልጅ

መስኖ ጠማው!” እንበል። ይህን አባባል መቀመር ያስፈለገበት ምክንያት ከሰብ ሰሐራ አፍሪካ አገራት መካከል 122 ቢሊዮን ኪውቢክ ሜትር የገጸ- ምድር ውሃ ያላት (በወንዞችና በሐይቆች ያለውን ብቻ)፣ በውሃ ሀብቷ አንደኛ እና የአፍሪካ የውሃ ማማ የሚል ስያሜ የተቀጸለላት አገር በመስኖ እንዴት እንደተጠማች ለማሳየት ነው።

የመስኖ እንዴትነት፡- ስለ መስኖ ጥንታዊነትና አጀማመሩ ስናወጋ ውሃ ከመገኛ ምንጩ ከወንዝ/ ሐይቅ/ግድብ/ማቋቻ በመጥለፍ ጥንታዊያኑ የተጠቀሙት ቀዳሚ ዘዴ መሬቱን ለመፍሰሻ ያህል በመቆፈር ክፍት ቦይ ማዘጋጀት ነበር። ይህ ክፍት ቦይ (Open Canal) ሲባል፣ አንደኛ አፈሩን በመማስ ቦይ በመቅደድ ብቻ፣ ሁለተኛ ኮንክሪት በመገንባት ነው። አፈር በመቆፈር ብቻ የሚዘጋጀው ቦይ በቦዩ ወለልና ግድግዳ አማካይነት ውሃን በማስረግ እና በማትነን ለብክነት ይዳርጋል።



105

ስርገትም ሆነ ትነት ውሃው ለተፈለገው ተግባር እንዳይውል ከማድረጉ በላይ በቀላሉ መስመሩን በመጥለፍ ወይም ወደ ሌላ መስመር ለማስቀየስ የተጋለጠ በመሆኑ ከፍተኛ የውሃ ብክነትና ጥፋት ያስከትላል። የኮንክሪት ግንብ መገንባት ግን የውሃ ስርገትን ሲያስቀር የውሃ ትነትን ግን አያግድም።

ዛሬ ዛሬ ዘመን በተራቀቀበት ጊዜ ጥንታዊውን የአፈር ቦይ ለመስኖ ማዋል ካልቸገረ በቀር አይመከርም። አርሶ አደሩ ዝናብ ጠባቂ ብቻ እንዳይሆን የሚያደርገው ሌላው ዘዴ (የገንዘብ አቅም ቢጠይቅም) የመሬት አቀማመጥንና አካባቢያዊ ሥነ ምህዳርን መሰረት ባደረገ መልኩ ውሃውን በሙሉ በቧንቧ (ቱቦ) የሚያደርስ ነው። ይህም ውሃ ቆጣቢ የማጓጓዣ ዘዴ ነው። ቢሆንም ቅሉ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ አገራት ኢኮኖሚ የማይቀመስ ግን ደግሞ የተሻለ ውጤት የሚያስገኝ ነው።

በሂደት ዘመኑ ሲሠለጥን የመስኖ ሥራ ዘመናዊ መልክ መያዙ አልቀረም። በዚህ የተነሳ በየማሳው በመስኖ ልማት ለየሰብል ቅንጣቶች፣ ፍሬዎች ወዘተ ማጠጫነት የተበረከቱ የዘመን ትሩፋቶች የሚከተሉት ናቸው። ውሃውን በተለያዩ የማጠጫ ቁሶች ቀድቶ የማጠጣት ዘዴ፣ በማጥለቅለቅ የማጠጣት ዘዴ (Flood Irrigation)፣ የቤዚን/ ተፋሰስ መስኖ (Basin Irrigation) ማለትም መሬቱን በገበቴ መልክ በመቆፈር ማቋቻ በመፍጠር የማጠጫ ዘዴ፣ የድንበር መስኖ (ማሳውን በማጠር የማጠጣት) ዘዴ (Border Irrigation)፣ በትልም (ቦይ) መስኖ የማጠጣት ዘዴ (Furrow Irrigation)፣ በጠብታ መስኖ የማጠጣት ዘዴ (Drip Irrigation)፣ በዝናብ መሰል

ርጭት የማጠጣት ዘዴ (Sprinkler Irrigation) ይጠቀሳሉ።

ኢትዮጵያ እና ለም መሬቷ

የዘርፉ ባለሙያዎች ለግብርና ልማት አመቺ የሆነው የኢትዮጵያ ለም መሬት ከ40 እስከ 80 ሚሊዮን ሔክታር ማሳ መሆኑን ይናገራሉ። ነገር ግን ዓመታዊ የግብርና ምርት እየታፈሰባቸው የሚገኙ የእርሻ ማሳዎች መጠን ከ15 ሚሊዮን ሔክታር አይበልጥም። ከዚህ ውስጥ ደግሞ በመስኖ ውሃ መልማት እንደሚችል የተገመተው የመሬት ስፋት ከ5 ነጥብ 8 እስከ 8 ሚሊዮን ሔክታር የሚሸፍነው ነው። ነገር ግን እየታረሰ ካለው 15 ሚሊዮን ሔክታር መሬት እና በመስኖ አለኝታ እንደሚለማ ከተገመተው 8 ሚሊዮን ሔክታር ከሚጠጋ መሬት ውስጥ የመስኖ ውሃ ተደራሽ የሆነው ከ20 በመቶ አይበልጥም።

በኢትዮጵያ በመስኖ ውሃ ተደራሽ የሆነውን የመሬት ስፋትና ርዝመት በተመለከተ ትክክለኛውን ሽፋኑን መገመት ያዳግታል። ምሣሌ ለመጥቀስ ያህል በበጋ መስኖ ለስንዴ ልማት ተደራሽ የሆነው መሬት 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሔክታር መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ሪፖርት ያሳያል።

በመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር መረጃ መሠረት መልማት ከሚችለው መሬት 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሔክታር ብቻ የመስኖ ተጠቃሚ መሆኑንና ከዚህ መካከል ደግሞ 70 በመቶ ያህሉ በአነስተኛ አርሶና አርብቶ አደሮች አማካይነት በባህላዊ መንገድ የተከናወነ ነው። በመስኖ ውሃ ሰብልን የማምረት ተሞክሯችን አነስተኛ መሆኑን የሚጠቁመው ጥናት እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በ2023 በመስኖ የመልማት ዕድል ካለው ከጠቅላላው



106

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

የአገሪቷ መሬት መካከል ከ10 እስከ 15 በመቶ ያህል ብቻ በመስኖ ማልማት እንደተቻለ ይናገራል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ መስኖ ለብሔራዊው ምጣኔ ሀብት ያለው አበርክቶ በባለሙያዎች ሲገለጽ የሚከተለውን ይመስላል። በአገር ደረጃ የሚተገበረው የመስኖ ልማት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። የአነስተኛ መስኖ ልማት ድርሻ ከጠቅላላው የአገር ውስጥ ምርት (Gross Dometic Product/GDP) 4 ነጥብ 46 በመቶ ሲገመት፣ ለአጠቃላይ የአገሪቷ ኢኮኖሚ ደግሞ 1 ነጥብ 97 በመቶ ያበረክታል። መካከለኛና ትላልቅ የመስኖ ዓይነቶች ደግሞ ከጠቅላላው የአገር ውስጥ ምርት 1 ነጥብ 26 በመቶ እና ለአጠቃላይ የአገሪቷ ኢኮኖሚ ደግሞ 0 ነጥብ 5 በመቶ ድረስ አስተዋጽኦ አላቸው። በአጠቃላይ የመስኖ ልማት ለአገር ውስጥ ምርት ያለው አበርክቶ 5 ነጥብ 7 በመቶ ሲሆን እንደ ሴክተር ደግሞ የመስኖ ልማት ለአገሬው ኢኮኖሚ ግንባታ ድርሻው 2 ነጥብ 5 በመቶ ነው።

የኢትዮጵያ መስኖ ልማት አሁናዊ ገጽታ

የመስኖ ልማት ውሃ አጠር በሆኑ የመልክዓምድር ወሰኖች፣ ቆላማ የአየር ጠባይ በሚያዘወትርባቸው አካባቢዎች ትኩረቱን ሲያደርግ፤ በአብዛኛው ሜዳማ የመሬት አቀማመጥ ይመርጣል። ለዚህም ሲባል በአንዲት አገር ውስጥ የመስኖ ልማት መተግበር ሲታሰብ የፕሮጀክት አስፈጻሚዎች ዝንባሌ የሚያመዝነው በቆላማ አካባቢ ለሚገኙ አርብቶ እና ከፊል አርብቶ አደር የማኅበረሰብ ክፍል ይሆናል። በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚተገበሩ የመስኖ ልማት ሥራዎች ለውሃ አጠር አካባቢዎች ቅድሚያ በመስጠት ነው። በአገራችን ኢትዮጵያም

ይህ ነባራዊ እውነታ ያመዝናልና ከእርሻ ማሳው አመቺነት፣ ከአፈሩ ለምነት፣ ከሰብል ዓይነቶች የውሃ ፍጆታና አቅርቦት አንጻር ታሳቢ በማድረግ የመስኖ ውሃ አብዛኛውን ጊዜ በቆላማ አካባቢዎች የሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ትኩረት ያደርጋል። በኢትዮጵያ በውሃ ዕጥረት ወይም በውሃ አቅርቦት የተደራሽነት ችግር የተነሳ በምግብ ሰብል ራስን የመቻል ጉዳይ የማይታሰብ የሆኑባቸው ክልሎች፣ ዞኖችና ወረዳዎች አያሌ ናቸው። በነዚህ አካባቢዎች የሚኖረው የሕዝብ ቁጥርም 15 ሚሊዮን መድረሱ ይነገራል።

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር በአገር አቀፍ ደረጃ እያከናወናቸው ከሚገኙ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች መካከል በየክልሉ ያሉ ወንዞችና ሐይቆችን መሰረት ያደረገ የግድቦች ግንባታ ይጠቀሳል። ከዚህ ጎን ለጎን የመስኖ ልማት አስተዳደር፣ ቁጥጥርና አመራር ሒደት በፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና የአፈጻጸም መመሪያዎች መምራት ስለሚገባ በአገር አቀፍ ደረጃ ከተከናወኑ ሥራዎች መካከል የመስኖ ፕሮጀክቶችን ጥራት የሚያስጠብቅ የመስኖ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ስታንዳርድ አዘጋጅቶ ሥራ ማስጀመሩ እንደ አዎንታዊ ርምጃ ይቆጠራል።

ከዚህ ቀደም የመስኖ ልማትና ሀብት አጠቃቀምን በተመለከተ ሁሉም እንዳሻውና እንዳመቸው የሚተገብረው እንጂ በአገር ደረጃ የአጠቃቀም ፍትሐዊነትን የሚያረጋግጥ አሠራር አልነበረም፤ በዚህ የተነሳ በየቦታው ያሉ አፈጻጸሞች ወጥና ዘላቂ አለመሆናቸው ዘርፉን ጎድቶታል። ስለዚህም ፍትሐዊ የሀብት ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ስታንዳርድ መውጣቱ ለዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት ማሳያ ይሆናል። ከስትራቴጂያዊ ዕቅዶቹ ውስጥ



107

በመስኖ ልማት የግብርና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ በመስኖ ዘርፍ የሥራ ዕድል መፍጠር፣ የመንግሥት የወጪ ቅነሳ እና አማራጭ የፋይናንስ ምንጮች ማሳደግ፣ ተቋማዊ አቅምና የሰው ሀብት ልማት ማሳደግ፣ በመስኖ ልማት የሥርዓተ ጾታና አካል ጉዳተኞች አካታችነትን ማረጋገጥ ይገኙበታል።

የመስኖ ልማት ብሔራዊ ትሩፋቶች

ከስንዴ አስመጪነት ወደ ስንዴ ላኪነት ብሎም ለኢንዱስትሪ ግብዓት አቅራቢነት፡ - ባለፉት ስድስት ዓመታት፣ በኢትዮጵያ የመስኖ ሥርዓት ተጠቃሚዎች ዘንድ የታዩ ለውጦች

በተለይም በገጠር አካባቢዎች የአልሚዎችን የአኗኗር ሁኔታ ለማሻሻል ድርሻ ነበረው። አብነት ለመጥቀስ ያህል በአገሪቷ ውስጥ የበጋ መስኖ የስንዴ ምርት ተነሳሽነት በመስኖ፣ በሜካናይዜሽን የጋራ አጠቃቀም፣ በግብርና ግብዓቶች አቅርቦት እና በሌሎች የግብርና አስተዳደር ተቋማት አማካይነት ቀድሞ ያልነበረ ምርትና ምርታማነት አሳድጓል።

የመስኖ ስንዴ ቴክኖሎጂ ከምርምር ማዕከል ወጥቶ ወደ ተጠቃሚዎች መድረስ የጀመረው በ2004 ዓ.ም በአፋር ክልል በአንድ ከፊል አርብቶ አደር ማሳ ሲሆን በወቅቱ የተሰበሰበው የምርት መጠን 29 ኩንታል በሔክታር ነበር። በወቅቱ የተዘራው የስንዴ ዝርያ በመስኖ ለሚለሙ ቆላማ



108

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

አካባቢዎች የተለቀቀ ሲሆን የተዘራውም በአንድ ሔክታር ማሳ በመሆኑ ቴክኖሎጂውን ለአካባቢው ማኅበረሰብ የማስተዋወቅ ዕድል ፈጠረ። በዚያ ቦታ የተገኘው ምርት በወቅቱ ከነበረው የመኸር አማካይ አገር አቀፍ የስንዴ ምርት መጠን (24 ኩንታል በሔክታር) የተሻለና ተስፋ እንዲጣልበት ያደረገ ሆነ። ከዚያ በመቀጠል የመስኖ ስንዴ ልማቱ በዋነኛነት በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በአማራና ሌሎች ክልሎች ተጠናክሮ ቀጠለ። በ2015 ዓ.ም የምርት ዘመን 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሔክታር ማሳ በመሸፈን አማካይ አገራዊ የምርት መጠኑ ወደ 36 ኩንታል በሔክታር ከፍ ሲል በጠቅላላው ዓመታዊ የስንዴ ምርት መጠን 47 ሚልዮን ኩንታል ደረሰ።

በመስኖ ስንዴ የሚሸፈነው የመሬት ስፋት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ከመምጣቱ ጎን ለጎን አገራዊ የመስኖ ስንዴ ልማት ንቅናቄ በጅማ ከተማ መጀመሩ ሲነገር፤ በተያዘው ዓመት (በ2016 ዓ.ም) ሦስት ሚሊዮን ሔክታር በመስኖ ስንዴ ለማልማት ያቀደ ነበር። በመጨረሻም አዝመራው ተሰብስቦ ሲመዘን በምርት ዘመኑ ከአነስተኛ ማሳ ተጠቃሚ አርሶ አደሮች 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሔክታር ላይ 123 ሚሊዮን ኩንታል እንዲሁም በመስኖ ከለማው 2 ነጥብ 9 ሔክታር መሬት ላይ የታፈሰው ምርት 107 ነጥብ 7 ሚሊዮን



109

ኩንታል በመድረሱ በጠቅላላው በአገር ደረጃ 230 ሚሊዮን ኩንታል ማምረት ተቻለ።

የመስኖ ስንዴ ልማት ተሞክሮ እንደሚያመላክተው ከዓመት ዓመት የምርቱ መጠን እያደገ መሄዱን ነው። በ2016 ዓ.ም ክረምትና በ2017 ዓ.ም በጋ በመስኖ የለማው የስንዴ ምርት መጠን 290 ሚልዮን ኩንታል ሲሆን ከአምናው ምርት አንጻር የ60 ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ አሳይቷል።

በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በኢትዮጵያ የመስኖ ልማት

የሰው ልጆችን አሁናዊ የምግብ ፍላጎት ከመሙላት በላይ፣ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ የጥሬ ዕቃ ግብዓት ከ40 እስከ 50 በመቶ ድረስ ለመሸፈን ይሠራል። ከስንዴ ምርት በተገኘው ተሞክሮ በመደገፍ ደግሞ ከውጭ አገር የሚገባውን የቢራ ገብስ በአገር ውስጥ ማምረት መቻሉን፣ በአገር ደረጃ በ30 ሺህ ሔክታር ማሳ ላይ በማምረት ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሔክታር ወደ 63 ሚሊዮን ኩንታል የሩዝ ምርት መሰብሰብ ተችሏል። መስኖ ከስንዴ ወደ ገብስ፣ ሩዝ ብሎም ወደ ቅባት እህሎች እየተሻገረ



110

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

በመተግበሩ የምርት መጠን ላይ ዕድገት አሳይቷል።

አሳታፊ መስኖ ልማትና የመስኖ ኤክስቴንሽን፡ - ኢትዮጵያ የግብርና ምርትን ለማሳደግና የዜጎቿን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ከ ም ት ን ቀ ሳ ቀ ስ ባ ቸ ው ስትራቴጂያዊ ዕቅዶች መካከል የመስኖ ልማት ማስፋፊያ ተጠቃሽ ነው። በዚህም ለውጥ እንደሚያመጡ ከታመነባቸው የመስኖ ልማት መርሃግብሮች አንዱ “አሳታፊ አነስተኛ የመስኖ ልማት ፕሮግራም” ሲሆን ፕሮግራሙ የተቀረጸው በአገሪቷ የምግብ ዋስትና በተመናመነባቸው አካባቢዎች በአነስተኛ ማሳ የሚያመርቱ አርሶ አደሮችን በመስኖ ልማት ተጠቃሚ ያደረገ ነው። በመስኖ ተጠቃሚነታቸው በምግብ ራሳቸውን ከመቻል ባሻገር የገበያ ትስስር ተፈጥሮላቸው የተሻለ ገቢ አግኝተው ኑሯቸው እንዲሻሻል ያለመ ነው።

ስለሆነም ለመስኖ አመቺ የሆኑ ለም መሬቶች ከመለየት አንስቶ የመስኖ ልማት ዲዛይንና ግንባታ፣ አተገባበር (Operation) እና ጥገና (Maintenance) ሥራ

ላይ አርሶ አደሩን በማሳተፍ ተጠቃሚ አድርጓል። በተለይ ገጠርን ማዕከል ያደረገ ዘላቂነት ያለው የኢኮኖሚ ልማት ዕውን ለማድረግ የላቀ አስተዋጽኦ አለው። በመንግሥትና በልማት አጋሮች ከፍተኛ ቅንጅትና ትብብር አማካኝነት መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ የሚገነቡ የመስኖ መሰረተ ልማቶች ዘመናዊ የእርሻ ዘዴን በማስፋፋት፣ ጥራት ያለው ምርት በማምረትና በወቅቱ ለገበያ በማቅረብ አርሶ አደሩና ኀብረት ሥራ ማኅበራት ሀብት የሚያፈሩበትን ዕድል ፈጥሯል። በመርሃግብሩ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑ አባዎራዎችን፣ እማዎራዎችንና የልማት ሠራተኞችን አቅም የሚያሳድግ ሥልጠና በዘለቄታዊነት እንዲያገኙ ያደረገ መርሃ ግብር ነው። የመስኖ ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ምርታማነትን የሚያሳድጉ አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂ ውጤቶች በብቃት የተተገበሩበት የሥራ ክፍል ነው። ለአርሶና አርብቶ አደሩ ማኅበረሰብ ተደራሽ በመሆን፣ የአገልግሎት አቅርቦት ሂደትን በማሳለጥ፣ የግብርና ልማትን በማዘመን ምርትና ምርታማነት



111

የማሳደግ ኃላፊነት ከመስኖ ኤክስቴንሽን ይጠበቃል።

የአረንጓዴ አሻራና የሌማት ትሩፋት፤ የተፋሰስ ልማት እና የአካባቢ ሥነ ምሕዳር ጥበቃ፡ - የተለያዩ የሚመስሉ ነገር ግን እርስ በእርስ የተጋመዱ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ውጤቶች ናቸው። ኢትዮጵያም እንደ አገር የአረንጓዴ ልማት ንቅናቄ በማወጅ በተከታታይ ዓመታት በርካታ ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል በቅታለች። አገሪቷ በራሷ ብቻ ሳትወሰን ለጎረቤት አገራት ልምዷንና ችግኞችን በመለገስ እንዲለሙ ሠርታለች። ከዚህ ጎን ለጎን የቆሻሻ መጣያ የነበሩ ወንዞችን በማስዋብ አረንጓዴ የልምላሜ አሻራ እንዲያብብና እንዲናበብ አድርጋለች።

ጎን ለጎንም ገበታ ለአገር እና የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብሮችን ዐውጃ በተፈጥሮ ሀብታቸው የታደሉ መልክዓ ምድሮችን በማልማት አገር ከጭስ አልባው ኢንዱሰትሪ እንድትጠቀም የሚያስችሉ ሥራዎችን ሰርታለች። አረንጓዴ አሻራ ከተፋሰስ ልማት፣ ከወንዝ ዳር ጽዳትና ልማት፣ አረንጓዴ አሻራ ከተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት ወዘተ ጋር እየተሳሰሩ ለበረሃማነትና ለአካባቢ ብክለት የሚዳርጉ መንስኤዎችን ከሥሩ ለማድረቅ የሚደረገውን ዓለም አቀፋዊ ንቅናቄ በፊታውራሪነት መምራት ችላለች። ይህም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) መሪነት ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት መመናመንና የአየር ንብረት ለውጥ የሚያደርሱትን ማኅበረ- ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለመቋቋም የወሰደችው ሁነኛ ርምጃ ነው።

በመስኖ ልማት የበለጸጉ አገራት ተሞክሮ

በመስኖ ልማት ዓርአያ ከሆኑ አገራት መካከል ሕንድና ቻይና የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ። “ችግር በቅቤ ያስበላል” እንዲሉ የሕዝብ ቁጥራቸው ከፍተኛ በመሆኑ የዝናብ ወቅትን ጠብቆ መመገብ ማለት አብዛኛውን ሕዝባቸውን በረሃብ አለንጋ እንደመግረፍ ቆጥረው መላ ዘይደዋል።

በአሁኑ ወቅት በቻይና ከ71 ሚሊዮን ሔክታር በላይ መሬቷ በመስኖ ውሃ መልማት ችሏል። በአገረ-ሕንድ ደግሞ ወደ 82 ሚሊዮን ሔክታር ድረስ በመስኖ ተደራሽ ሆኗል። ሕንድና ቻይና የመስኖ ልማትን ሲመርጡ በአንጻሩ የሰብል ዓይነቱንም ከግምት በማስገባት ሲሆን በዚህም በብዛት ሩዝ፣ በቆሎና ስንዴ ሰብሎችን ተመራጭ ማድረጋቸው ተሰንዷል። ከእነዚህ ዐበይት የሰብል ዓይነቶች በተጨማሪም የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎችን አልምተው ለውጭ ገበያ በማቅረብ የገቢ ምንጫቸውን አዳብረዋል። ከእነዚህ ሥራዎች አንዱ ለአርሶ አደሮቻቸው እና ከፊል አርብቶ አደሮቻቸው በቅርበት ሆነው የሙያ ድጋፍ በመስጠት አንድም አምራቾችን፣ ሁለትም አገራቸውን ተጠቃሚ ማድረጋቸውን ምሁራኖቻቸው ይመሰክሩላቸዋል። ሕንድ እና ቻይና የመስኖ ውሃ ላይ የተራቀቁ አገራት ናቸው፤ ምክንያቱም ያገኙትን ማናቸውም የውሃ ሀብት ካሰቡትና ካለሙት ማሳ ደርሶ ለአትክልትና ዕፅዋቱ ይደርስ ዘንድ የመስኖ ልማትን የሚያግዙ (State of the Art Technology) ቴክኖሎጂዎችን በተግባር በማዋል ጭምር ነው። ይህ ችግራቸው መላ አስገኝቶላቸው በቅቤ እንዲበሉ አላደረጋቸውም?

በሌላ ወገን መሬታቸው ለእርሻ የማይመች፣ ውሃ አጠር በረሃማና ከፊል በረሃማ የአየር ጠባይ የሚያመዝንባቸው አገራት ያላቸውን አነስተኛ



112

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

የውሃ ሀብት ለማብቃቃት ከፍተኛ ጥናትና ምርምር በማድረግ በምሁራኖቻቸውና አርሶ አደሮቻቸው ብርቱ ትግል ዘመን አመጣሽ ዘዴዎችን አክለው በመጠቀም የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጣቸው አልፈው ምርቶቻቸውን ለዓለም ገበያ በማቅረብ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር እያገኙ ነው። የመስኖ ሥራ ቴክኖሎጂ ከፍተኛ እመርታ በማሳየቱ የተነሳ በአንድ የመስኖ ማጠጫ መሣሪያ በመታገዝ እስከ 800 ሔክታር የሚሸፍን ማሳ ላይ ሰብል ማምረት መቻላቸው ተዘግቧል።

ውሃ አጠር ሆና ሳለ በመስኖ ልማት ከተራቀቁት አገራት መካከል ቀድማ የምትጠራዋ እስራኤል ናት። እስራኤል እንደ አገር ያላት የውሃ ሀብት በጣም አነስተኛ ነው። ቢሆንም ቅሉ የውሃ ሀብት መሐንዲሶቿ የገጠማቸውን የውሃ ችግርና ተግዳሮት እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ አገራቸው ያላትን ውስን የውሃ ሀብት አብቃቅታ እንድትለማ የሚያስችል የጠብታ መስኖ ዘዴ በተግባር አውለዋል።

እስራኤል ያላትን ውስን/ጥቂት የውሃ ሀብት በጥንቃቄ መጠቀሟን የሚያሳየውን አሰራር ለማውሳት ያህል ከአንድ ምንጭ የተገኘውን ውሃ በተደጋጋሚ ቢያንስ ለሶስት ዙር ያህል ለተለያዩ ሚናዎች ትገለገላለች። ከአንድ ምንጭ ያገኘችውን ውሃ ለሶስት ጊዜ ያህል ጥቅም ላይ ስታውልም ውሃውን በተለያዩ ስልቶች በማከም፣ በማጣራት፣ በማደስ ወዘተ ነው።

በግብርና ልማት ግንባር ቀደም ከሆኑ አገራት መማር እንደሚቻለው ለምሣሌ እስራኤል ከፍተኛ የውሃ ዕጥረት ቢኖርባትም ዕጥረቱ በግብርና ምርቶቿ ላይ ተጽዕኖ አልፈጠረም። ለችግሯ

የፈጠረችው መላ የነጠብጣብ መስኖ (Drip Irrigation)፣ የቆሸሸ ውሃን ዳግም በማከም መጠቀም (Recycled Wastewater) እና ስማርት መስኖ (Sensor እና AI መቆጣጠር) ዘዴዎችን በመተግበር ምርታማነቷ እንዲያድግ ሠርታለች።

ኔዘርላንድ (Netherlands) በበኩሏ አነስተኛ የእርሻ ማሳ ቢኖራትም ስንዝር በማትሞላ ማሳ ላይ ከፍተኛ ምርት ከማምረት አልተገታችም። ኔዘርላንድ በአትክልትና በአበባ ልማት ታዋቂ ስትሆን በተግባር ካዋለቻቸው የመስኖ ልማት ዘዴዎች መካከል የግሪንሃውስ መስኖ፣ የተዘጋ የውሃ ሥርዓት መስኖ (Closed-loop irrigation)፣ የነጠብጣብ እና የርጭት መስኖ ዘዴዎቿ ምርታማነቷን አሳድገውላታል።

ሕንድ ከዓለም አገራት መካከል ሰፋፊ የመስኖ መሬት ያላት ስትሆን የምግብ ደህንነቷን ለማረጋገጥ ካበቋት የመስኖ ዓይነቶች መካከል የካናል (Canal Irrigation)፣ የጉድጓድ መስኖ (Tube wells)፣ ነጠብጣብ እና ርጭት የመስኖ ስልት በመጠቀም የግብርና ሥርዓቷን አዘምናለች።

አገረ ቻይና ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ ትላልቅና ግዙፍ የውሃ መቆጣጠሪያ ፕሮጀክቶችን ስታስተዳድር ምርታማነቷን ለማሳደግ የምትጠቀማቸው ዘዴዎች የካናል መስኖ፣ ዘመናዊ ነጠብጣብ እና ርጭት እንዲሁም ዘመናዊ የውሃ መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂ (Smart water management) ሥርዓቶችን ተግብራለች። ።

ወደ አውስትራሊያ ጎራ ስንል በተወሰኑ አካባቢዎቿ ከፍተኛ የውሃ ዕጥረት ቢገጥማትም ያላትን አነስተኛ የውሃ ሀብት በብቃት በመጠቀም ዕውቅናን አትርፋለች። በመረጠችው የመስኖ



113

ልማት የነጠብጣብ መስኖ፣ የርጭት እና ውሃን አመጣጥኖና አብቃቅቶ የመጠቀም (Water allocation systems) ሥርዓት ተጠቃሚ ሆና ግብርናዋን አዘምናለች።

ከወደ ሕንድ የተገኘው የመስኖ ልምድ እንደሚያሳየው ለአነስተኛ አርሶ አደሮች ቀላልና አመቺ መፍትሄ ሳይሆን አይቀርም። ይህ ጉዳይ በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ጅምሩ እንደሚታይ እማኝ መጥራት አያሻም። አርሶ አደሮችን በማኅበርና በዩኒየን በማጣመር የተቀናጀ የመስኖ አጠቃቀም (cooperative-based irrigation) ወይም (Water User Associations) ሥርዓትን መተግበር፣ እንዲሁም በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ ፓምፖችን ተደራሽ በማድረግ የዘመናዊ መስኖ ልማት በረከቱ ተቋዳሽ ማድረግ ይቻላል።

በአነስተኛ ደረጃ ለሚያለሙ አርሶ አደሮች ቀላልና ምቹ ሆኖ ከሚጠቀሱት ቀላሉ የመስኖ ዘዴ የውሃ ማጠጫ ባልዲ መስኖ (Bucket Irrigation) ሲሆን ይህም አነስተኛ ወጪ የሚጠይቅ፣ ለትናንሽና አነስተኛ ማሳዎች የሚበጅ ነገር ግን ከፍተኛ የሰው ኃይል በማሰማራት ውጤታማ የሚያደርግ ሆኖ ይመረጣል። ለአትክልትና ፍራፍሬ ምርት የሚመከረው የመስኖ ዓይነት በፕላስቲክ ቱቦ (gravity-fed drip) አማካይነት የነጠብጣብ መስኖ ነው። ይህም የውሃ ብክነትን ከ30 እስከ 60 በመቶ በመቀነሱ ይመረጣል።

ወደ አገራችን ስናመጣው የርጭት መስኖ ዘዴ በመካከለኛ ደረጃ ወጪ የሚጠይቅ ቢሆንም ለስንዴ፣ ለሩዝ፣ ለገብስ እና ተዛማጅ የሰብል ዝርያዎች ምቹ ነው። ከመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በፀሐይ

ኃይል የሚሰራ ፓምፕ የነዳጅ ወጪን የሚቀንስና በርቀት ላሉ ገጠራማ አካባቢዎችም በቀላሉ ተደራሽ ማድረግ እንደተቻለ ነው። ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ የመስኖ ዓይነቶችን በአርሶ አደሩ ዘንድ ተደራሽ ማድረግ የሚቻለው አንድም ለአርሶ አደሩ ድጎማ ወይም የተለየ የብድር አቅርቦት (Subsidy/ Credit) በማመቻቸት ቢተገበር ያዋጣል።

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴርም ሆነ በግብርና ዘርፍ የተሰማሩ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከዓለም አገራት አልሚውን ልምድ መቅሰም፣ ማላመድና መተግበር ይጠበቅባቸዋል። ከእነዚህም መካከል የመሬት ማጥለቅለቅ (Surface irrigation) በኢትዮጵያ በስፋት እየተተገበረ ያለ ቀላል ግን ደግሞ የውሃ ሀብትን ለጥፋትና ለብክነት የሚዳርግ ዘዴ ነው። ቢሆንም ቅሉ የውሃ ሀብትን በቁጠባ ለመጠቀም ሲባል አማራጭ ዘዴ መጠቀም ያሻል። የርጭት መስኖ ከአፈር ቦይ መስኖ በተሻለ መልኩ ውሃን ከመቆጠቡ ባሻገር በመካከለኛ ደረጃ ብቃቱ ተመራጭ አድርጎታል። ይህ ዘዴ በአገራችን ባሉ ሰፋፊ እርሻዎች ላይ አገልግሎት ሲሰጥ ይታያል፤ ነገር ግን በአነስተኛ ማሳ ለሚያለሙ አርሶ አደሮች ተደራሽነቱ ሩቅ ይመስላል። የነጠብጣብ መስኖ ዘዴ በከፍተኛ ደረጃ ውሃን ለመቆጠብ የሚመረጥ፣ የአፈር መከላትን የሚከላከል፣ ለሰብል ዕድገት በቂና የተመጠነ ውሃ የሚያደርስ ሆኖ ይመረጣል። በተለይም በቆላማው የአገራችን ክፍል ደረቅ የአየር ጠባይና ከፍተኛ ሙቀት በመኖሩ የነጠብጣብ መስኖ ለአፋር፣ ለሶማሌ እና ለስምጥ ሸለቆ ስፍራዎች ተመራጭ ነው።



114

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

ማኅበራዊ

የውጤታማነቱ

(በአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እና በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ትብብር የተዘጋጀ)



115

አንዱ ማሳያ. . .

የጤና ተቋማት ዓለምአቀፋዊ ተልዕኮ ሰብዓዊነትን መሠረት ያደረገ፣ ተደራሽ፣ ፍትሃዊ እና ጥራቱን የጠበቀ የሕክምና አገልግሎት መስጠት ነው። በዚህ አውድ ውስጥ፣ በአዲስ አበባ የሚገኘው የአለርት (ALERT) ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ደረጃ ጠንካራ ታሪክ፣ የተረጋገጠ ተልዕኮ እና ዘርፈ- ብዙ አስተዋጽኦ ያለው ተቋም ነው።

አለርት ሲመሰረት ዋና ተልዕኮው በወቅቱ የማይድንና ከፍተኛ ፍርሃት ያሳድር የነበረውን የስጋደዌ (Leprosy) በሽታ መከላከል፣ ታካሚዎችን መንከባከብ እና የሰው ልጅን ክብር መጠበቅ ነበር። ዛሬ ግን ተቋሙ ያንን ታሪካዊ መነሻ በማጠናከር፣ የሰውን ልጅ አካላዊ፣

በመንገሻ ገ/ሚካኤል



116

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

ሥነ-ልቦናዊ እና ማኅበራዊ ጤና በሙሉ የሚመልሱ ውስብስብ እና ዘመናዊ የሕክምና አገልግሎቶች ማዕከል ሆኗል።

አለርት ከዓለምአቀፍ የጤና ተልዕኮዎች (Global Health Missions) ጋር ተጣጣሚ በሆነ መንገድ ቁልፍ ተግባራትን እያከናወነ ሲሆን ከእነዚህ ተግባራት መካከል የመልሶ ማቋቋም ሕክምና (Rehabil- itation) ይገኝበታል፡፡ በአደጋ ወይም በበሽታ ምክንያት የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ሰው ሰራሽ አካላት መገጣጠም፣ ፊዚዮቴራፒ እና አጠቃላይ የመመለሻ እንክብካቤ በመስጠት ወደ ሙሉ እና ንቁ ሕይወት እንዲመለሱ በግንባር ቀደምነት ይሠራል።

የቆዳ ሕክምናና ቀዶ ሕክምና ሌላው ሆስፒታሉ በዋናነት የሚታወቅበት አገልግሎት ነው፡፡ ሆስፒታሉ በቆዳ ሕክምና (Der- matology) እና በፕላስቲክና መልሶ ማቋቋም ቀዶ ሕክምና (Plastic & Reconstructive Surgery) ዘርፍ የአገሪቷ ዋነኛ እና የተመረጠ የሪፈራል ማዕከል ነው።

አለርት ከሕክምናው ባሻገር



117

ከአርማወር ሃንሰን ሪሰርች ኢንስቲትዩት (Armauer Hansen Re- search Institute – AHRI) ጋር በቅርብ ትብብር በዓለምአቀፍ ደረጃ እውቅና ያላቸው የምርምር ሥራዎችን በማካሄድ ለሳይንሳዊ ዕድገት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

እንደ ትልቅ የጤና ተቋም አለርት፤ በቴክኖሎጂ አቅርቦት፣ በሰው ኃይል ልማት እና በዘላቂ ፋይናንስ ረገድ ያሉ ፈተናዎችን በመቋቋም በተለይ ለድሃና ለተጋላጭ የማኅበረብ ክፍሎች ተደራሽና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት በቁርጠኝነት እየሠራ ይገኛል። “ማንንም ወደ ኋላ አለማስቀረት” (Leaving No One Behind) የሚለውን ዓለምአቀፋዊ መርህ በተግባር የሚያሳይ ተቋም ነው። የአለርት ሆስፒታል ጉዞ ከበሽታ መከላከል በላይ ተሻግሮ የሰውን ልጅ ሙሉ ጤና፣ ክብር እና ራስን መቻል ወደ መመለስ አድጓል።

ሆስፒታሉ አሁንም በቆይታው ያካበተውን ልምድ፣ ያዳበረውን አቅምና የፈጠረውን በጎ ተፅዕኖ በመጠቀም ራሱን ወደ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ የሚያሸጋግርበት ሂደት ውስጥ ገብቷል። በጤናው ዘርፍ እጅግ ዘመናዊ የልህቀት ማዕከል ለመሆን የሚያስችሉትን



118

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

ሥራዎች በስፋት በማከናወን ላይ ይገኛል። የአገልግሎት አድማሱን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሰፋ የመጣው አለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በአገራችን የግል ሕክምና አገልግሎት ከጀመሩ የመንግሥት ሆስፒታሎች ግንባር ቀደም ነው።

የሆስፒታሉ የግል ሕክምና አገልግሎት

የጤና ባለሙያዎችን የሥራ ተነሳሽነት በማሳደግ ባሉበት ሆስፒታል ውስጥ የሚያገለግሉበትን ሠዓት ለመጨመር እንዲሁም ኅብረተሰቡ አማራጭ

የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኝ ለማድረግ ታስቦ በመንግሥት ሆስፒታሎች የግል ሕክምና አገልግሎት ከተጀመረ ሰንበትበት ብሏል። በአገር አቀፍ ደረጃ የመንግሥት ሆስፒታሎችን የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ደረጃውን የጠበቀና በሥርዓት የሚመራ እንዲሆን ለማስቻል የሚኒስትሮች ምክር ቤት የፌዴራል ሆስፒታሎች አስተዳደር ደንብ ቁጥር 167/2001 ማጽደቁ ይታወቃል።

የጤና ሚኒስቴር በመንግሥት ሆስፒታሎች የግል ሕክምና ክፍል አገልግሎት የአሠራርና የአደረጃጀት መመሪያ ማዘጋጀቱን ተከትሎ በ2007 ዓ.ም



119

ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተገብቷል። የአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልም ይህንኑ አገልግሎት ከጀመሩት የመንግሥት የጤና ተቋማት መካከል አንዱ ነው።

በመንግሥት ሆስፒታሎች የግል ሕክምና አገልግሎት የምንለው ከድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት በስተቀር ከመደበኛ የሕክምና አገልግሎት ጎን ለጎን ባለሙያዎች ከሥራ ሠዓት ውጪ፣ ቅዳሜ እና እሁድ እንዲሁም በበዓላት ቀን በተመጣጣኝ ክፍያ የሚሰጠውን የተመላላሽ እና የተኝቶ ሕክምና አገልግሎት ነው።

ይህ የግል ሕክምና አገልግሎት ከመደበኛው የሕክምና አገልግሎት የሚለይበት ሌላው ጉዳይ ለጤና መድህን ተጠቃሚዎች አገልግሎት የማይሰጥ መሆኑ እና በክፍያ ብቻ የሚያስተናግድ መሆኑ ነው።

አለርት የግል ሕክምና አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ከ10 ዓመት በላይ ማስቆጠሩን የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር እና የቆዳና አባላዘር ስፔሻሊስት ሐኪም ዶክተር አብዱልናስር ሀምዛ ይናገራሉ። በጥቂት የሕክምና ዓይነቶች የተጀመረው የግል ሕክምና አገልግሎት በሂደት በተለይም ከኮቪድ- 19 ወረርሽኝ መከሰት ጋር ተያይዞ መቆራረጥ አጋጥሞት እንደነበረ ያስታውሳሉ።

ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ሆስፒታሉን በአዲስ መልኩ በማደራጀት ከድንገተኛ፣ ከማዋለጃ እና ከጽኑ ሕክምና አገልግሎት በስተቀር በሆስፒታሉ በመደበኛነት የሚሰጡ ሁሉንም ዓይነት ሕክምናዎች ያካተተ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

በተቋሙ በመደበኛ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ

የሕክምና ዓይነቶች በተመሳሳይ በግል ሕክምና እንደሚሰጡ የገለፁት ዶክተር አብዱልናስር፤ በዚህም በዓመት እስከ መቶ ሺህ ታካሚዎችን እያስተናገደ ይገኛል ብለዋል።

የዓይን፣ የቆዳ፣ የጥርስ፣ የአዕምሮ እና ህብለ ሰረሰር፣ የአጥንት፣ የፕላስቲክና ሪኮንስትራክቲቭ፣ የአጠቃላይ ቀዶ ጥገና፣ የአዕምሮ ሳይካትሪ፣ የውስጥ ደዌ፣ የሕፃናት፣ የጽንስና የማህጸን ሕክምናዎች እንዲሁም አጠቃላይ የጤና ምርመራ አገልግሎት በግል የሕክምና አገልግሎቱ እየተሰጡ ከሚገኙት መካከል ይጠቀሳሉ።

አገልግሎቱ ምን ውጤት አስገኘ?

የግል ሕክምና አገልግሎቱ ሲጀመር ከተያዙ ዓላማዎች መካከል የጤና ባለሙያዎችን በመንግሥት የጤና ተቋም ውስጥ ማቆየት፣ የታካሚውን ፍላጎት በመጠነኛ ገንዘብ ማሟላት እና የጤና ተቋማቱ የራሳቸውን ገቢ በማስገኘት አገልግሎታቸውን ማዘመን የሚሉት ይገኙበታል። ከዚህ አንጻር የአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የግል ሕክምና አገልግሎት በመጀመሩ ተጠቃሚ መሆኑን ዶክተር አብዱልናስር ይገልጻሉ።

የተቋሙ ባለሙያዎች በተለይም ስፔሻሊስት ሐኪሞች ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ በማድረግ በሆስፒታሉ ውስጥ በሥራ ላይ እንዲቆዩ አድርጓል ይላሉ። የግል ሕክምና አገልግሎት ከተጀመረ ወዲህ የባለሙያዎችን ፍልሰት በከፍተኛ ሁኔታ ማስቀረቱን ገልጸዋል። በዚህም የባለሙያዎችን የሥራ ተነሳሽነት በመጨመር በተቋሙ እንዲሠሩ እና የባለቤትነት ስሜት እንዲኖራቸው አድርጓል። የግል ሕክምና አገልግሎቱ ለሠራተኞቹ ብቻ ሳይሆን ለሆስፒታሉም ተጨማሪ የገቢ ምንጭ



120

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም

እያስገኘላቸው ነው።

በመንግሥት ሆስፒታሎች የሚሰጠው የግል ሕክምና አገልግሎት ማኅበረሰቡ አማራጭ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኝ አስችሏል። የግል ሕክምና አገልግሎት በትርፍ ሠዓት የሚሰጥ በመሆኑ በሥራ ሠዓት የሕክምና ክትትል ማድረግ የማይችሉ ታካሚዎች በትርፍ ጊዜያቸው ሕክምና እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።

ይህም ብቻ ሳይሆን በመንግሥት ሆስፒታሎች የሚሰጠው የግል ሕክምና አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ የሚሰጥ በመሆኑ በብዙዎች ዘንድ ተመራጭ እየሆነ ነው። በግል የሕክምና ተቋማት የሚጠየቀውንና በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን የሕክምና ዋጋ ለማረጋጋትም የራሱን ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

በመንግሥት ሆስፒታሎች በመደበኛ ሠዓት የሚሰጠው የሕክምና አገልግሎት በሪፈራል ቅብብሎሽ ሲሆን በግል ሕክምናው ግን ማንኛውም ታካሚ በቀጥታ አገልግሎት የሚያገኝ በመሆኑ ለማኅበረሰቡ ያለውን ተደራሽነት ቀላል አድርጎታል።

በአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የግል ሕክምና አገልግሎት የራሱ አደረጃጀት የተፈጠረለት እና አስተዳደራዊ ሥራውም ከመደበኛው ጋር በተለየ እንዲከናወን መደረጉ አገልግሎቱን ውጤታማ አድርጎታል።

ከሆስፒታሉ የተለያዩ ክፍሎች የተውጣጡ ባለሙያዎች የተካተቱበት የግል ሕክምና አገልግሎት ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን ይህም በየዕለቱ በመገናኘት በመደበኛ እና በግል ሕክምና

አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ክትትል እና ቁጥጥር ያደርጋል።

ማጠቃለያ

የአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን ጨምሮ ሁሉም የመንግሥት ሆስፒታሎች በተመሳሳይ ጊዜ የግል ሕክምና አገልግሎት መስጠት የጀመሩ ቢሆንም አብዛኞቹ ሆስፒታሎች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት፣ በአንዳንድ ተቋማትም ከሕክምናው የሚገኘው ገንዘብ አነስተኛ ነው በሚል አገልግሎቱን ያቋረጡ ሲሆን፤ የአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ግን አገልግሎቱን አጠናክሮ በማስቀጠል በዘርፉ ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ ችሏል።

በአሁኑ ወቅት በግል የሕክምና ተቋማት የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት የሚጠየቀው ዋጋ በፍጥነት እየጨመረ መምጣቱ እንዲሁም በመደበኛው የመንግሥት የጤና ተቋማት ያለው ፍላጎት እና እቅርቦት አለመጣጣም ዜጎችን ለከፍተኛ ወጪ እና ለእንግልት ይዳርጋል፡፡ በመሆኑም መንግሥት የጀመረውን የጤና አገልግሎት በጥራት እና በፍትሃዊነት ተደራሽ የማድረግ ጥረት ከግብ ለማድረስ በመንግሥት ሆስፒታሎች የሚሰጠው የግል ሕክምና አገልግሎት አስተዋጽኦ የላቀ በመሆኑ ሌሎች ሆስፒሎችም የአለርትን ተሞክሮ በመውሰድ የግል ሕክምና አገልግሎትን የተደራጀ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት ማስቀጠል ይጠበቅባቸዋል።



121



122

ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 32 የካቲት 2018 ዓ.ም


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም