ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም - ኢዜአ ነጋሪ
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
ማውጫ
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በየሁለት ወሩ የምትታተም መጽሔት
መስከረም 2009 ዓ.ም ተመሰረተች
አድራሻ፦ አራዳ ክፍለ ከተማ
ስልክ ቁጥር +251-11-55-00-11 +251-11-56-39-31 +251-11-56-52-21
ፋክስ ቁጥር +251-11-55-16-09 enanegari@gmail.com
የናይል ተፋሰስ ትብብር የትይዩ ጎዳና ጉዞ. . .
06
ትናንት ዛሬ እና ነገን ለማስታረቅ. . .
40
ውድድሩን የማሸነፍ ምርጫ …
56
የገንዘብ ወንጀሎችና የዓለም ሥጋት
70
የሰቆጣ ቃልኪዳን የትውልድ ተስፋ
88
ከምቹ እስከ ልህቀት ማዕከልነት
104
አስተማማኙ መንገድ
112
የቆዳ ሕክምናው የስኬት ጉዞ …
122
መልዕክት
ሰላም! ውድ አንባቢያን፤ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች የተዳሰሱባት ነጋሪ መፅሔት እነሆ ወደ እናንተ ደርሳለች።
የቀደመ ሥልጣኔ ያላት ኢትዮጵያ፤ ያን ሥልጣኔ እና ታሪኳን ስለምን አጽንታ መዝለቅ አልቻለችም፤ በተለያዩ ጊዜያት የነበሩ መንግሥታት ወደ ቀደመ ሥልጣኔዋ ለመመለስ እና ከከፍታ ማማ ላይ እንድትወጣ ለማድረግ ያደረጓቸው በርካታ ጥረቶችስ ስለምን እስከ አሁን እውን አልሆን አሉ? ታሪክና ትርክት፣ ሥልጣኔ እና ትርክት፣ አገረ መንግሥት እና ትርክት እነዚህ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በማንሳት የትናንት ታሪኮችን እንደ እርሾ በመጠቀም ዛሬ ለምንፈልገው አሉታዊም ይሁን አዎንታዊ ፍላጎቶቻችን ማስፈጸሚያነት የሚውለውን “ትርክት”ንዐብይ ጉዳይዋ አድርጋለች - ነጋሪ።
የተለያዩ የመልክዓ ምድር አቀማመጦችን፣ በርካታ ሥነ-ምህዳሮችን እና የአየር ጠባያትን ያካተተ በመሆኑ ተፈጥሮውን ምሥጢራዊ፣ ውስብስብ፣ አስደናቂ እና አወዛጋቢ ግን ደግሞ በጣም አስፈላጊ ስለሆነው ናይል እና የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ድርድር ከመነሻው እስከ አሁን ያለውን ጉዞም ታስቃኛለች።
ዓለም በሉላዊነት አንድ በሆነችበት በዚህ ዘመን በአንዱ የዓለም ክፍል የሚከናወን ተግባር፣ ምርት እና አገልግሎት ወደ ሌላው ተደራሽ ለማድረግ በርካታ ምቹ ሁኔታዎች አሉ። ይህ የሉላዊነት በጎ አስተዋጽኦ እንዳለ ሆኖ በተቃራኒው ተግዳሮቶችም ያጋጥማሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳው አንደኛው ነጥብ በዓለም ምርትና የአቅርቦት ሰንሰለት እንዲሁም አገልግሎት አሰጣጥ በጥራትና ቅልጥፍና ተወዳዳሪ ሆነው ባልተገኙት ላይ የሚፈጥረው አሉታዊ ተጽዕኖ ነው። ይህን በቅጡ የተገነዘቡ አካላት ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን በማዘጋጀት ብቁ ሆነው ለሚገኙ እውቅና በመስጠት በዓለም መድረክ ላይ ንቁ ተሳታፊ ሆነው እንዲዘልቁ የሚያስችል ሁነኛ መፍትሔ አበጅተዋል። የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት (ISO 9001) ምንድን ነው? ምላሹ በነጋሪ ተካቷል።
በሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ በማጭበርበር እና በሙስና ሕገ-ወጥ ድርጊቶች ዓለማችን በየዓመቱ በትሪሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ገንዘብ ትዘረፋለች። ይህም በፋይናንሺያል ሥርዓቱ ላይ እምነትን የሚሸረሽር ተግባር ሆኖ ሕዝብና አገራትን ለጉዳት ሲዳርግ ይስተዋላል። የፋይናንስ ሥርዓቶችን ለሕገ-ወጥ ጥቅም የሚያውሉ ሕገ-ወጥ ተግባራትን የሚያካትተው ዓለም አቀፍ የገንዘብ ወንጀሎች ሥጋት የነጋሪ ሌላው ርዕሰ ጉዳይ ነው።
የሕጻናትን ሰውነት ቀስ በቀስ እየጎዳ አዕምሮ እና የመፍጠር አቅማቸውን እያዳከመ በመሄድ፣ በድምፅ አልባነት ውስጥ ውስጡን ዘላቂ መዘዝ እያመጣ ይገኛል - መቀንጨር። ሕጻናትን በለጋ ዕድሜያቸው ብቻ ጎድቶ የሚያበቃ ሳይሆን ዳፋው እስከ ሕይወታቸው መጨረሻ የሚከተላቸውም ነው። ሕጻናት ከተወለዱ እስከ ሁለት ዓመት ባለው ዕድሜያቸው የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት ሲገባቸው በምግብ እጦት ምክንያት ዕድገታቸው አሉታዊ ተጽዕኖ ይደርስበታል. . . መቀንጨርን ታሪክ ለማድረግ ቆርጦ የተነሳው የሰቆጣ ቃል ኪዳን ትግበራን የተመለከተ ፅሁፍ በነጋሪ በስፋት ተዳሷል።
ነጋሪ ትኩረታቸውን ለውጭ አገር ሥራ ስምሪት አስተማማኙ መንገድ፣ ምቹ የሕክምና ማዕከል፣ የቆዳ ሕክምና የስኬት ጉዞ በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያደረጉ ፅሁፎችንም ይዛለች።
መልካም ንባብ!
ዋና አዘጋጅ ፈለቀ ሽኩር
ም/ ዋና አዘጋጅ የሺመቤት ደመቀ
ከፍተኛ አዘጋጅ ፍቅርተ ባልቻ
አዘጋጅ መንገሻ ገ/ሚካኤል
አርት ዳይሬክተር ነብዩ መስፍን nebiyou1st@gmail.com
ድረ-ገፅ www.ena.et/web/negari
ፖለቲካ
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
የናይል ተፋሰስ ትብብር
የትይዩ ጎዳና ጉዞ. . .
ፈቅአህመድ ነጋሽ (የውኃ ሐብት አስተዳደር ከፍተኛ አማካሪ)
መግቢያ
የናይል ተፋሰስ በዓለማችን ከሚገኙ በጣም ውስብስብ፣ አስደናቂ፣ አወዛጋቢ ግን ደግሞ በጣም አስፈላጊ ተፋሰሶች አንዱ ነው። ተፋሰሱ የተለያዩ የመልክዓ ምድር አቀማመጦችን፣ በርካታ ሥነ¬¬-ምህዳሮችንና የአየር ጠባያትን ያካተተ በመሆኑ ተፈጥሮውን ምስጢራዊ፣ ውስብስብ እና አስደናቂ አድርገውታል። የናይል ወንዝ በተፋሰሱ ውስጥ በስፋት አነስተኛ ከሆኑ የኢትዮጵያ ደጋማ አካባቢዎች እና የናይል ታላላቅ ሐይቆች
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
አካባቢ ተራሮች በመንደርደር ጥቅጥቅ ደኖችን፣ በርካታ ሐይቆችን፣ ረግረጋማ ቦታዎችን፣ ሰፋፊ የሣር መሬቶችን፣ ደረቃማ አካባቢዎችና በረሃ በማቋረጥ ወደ ጉዞው ማብቂያ የሜዲትራኒያን ባህር ይገባል። ይህንን ረዥም ጉዞ ሲያደርግ የተለያየ ቋንቋ፣ ባህል፣ ሃይማኖት፣ የቆዳ ቀለም፣ ርዕዮተ ዓለም እና የኑሮ ዘይቤ ያላቸውን ሕዝቦች በማስተሳሰርና የኑሯቸው፣ የዕድገታቸው፣ የክብርና የልዕልና በጠቅላላው ሁለንተናዊ ዋስትናነቱን በማረጋገጥ ነው።
የናይል ወንዝ ከምድር ወገብ አካባቢ ተነስቶ ወደ ሰሜን አቅጣጫ የሚፈስ ብቸኛው የዓለማችን ወንዝ ነው። በዚህም የተነሳ ካርታ ላይ ሲታይ ወንዙ የተፈጥሮ ዑደትን በመጻረር ሽቅብ የሚፈስ ይመስላል። ናይል የዓለማችን ረዥም ወንዝ ነው። መነሻ ነው ተብሎ በአብዛኛው ከሚታመንበት የቡሩንዲ እና ሩዋንዳ ተራሮች ከምትመነጨዉ ሩቪሮይንዛ ወንዝ ተነስቶ ሜዲትራኒያን ባህር እስኪገባ ድረስ 6 ሺህ 695 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ርቀት ይጓዛል። ይሁን እንጂ የናይል ወንዝ በሚያመነጨው የውኃ መጠን
ከዓለማችን ታላላቅ ወንዞች አኳያ ሲታይ በጣም ዝቅተኛ ነው። የዓለማችን ትልቁ የአማዞን ወንዝ የናይል ወንዝን 65 ጊዜ ይገዝፋል ወይንም የናይል ወንዝ ውኃ የአማዞንን 1 ነጥብ 5 በመቶኛ ይሆናል ማለት ነው።
በተመሳሳይ የዓለማችን ሁለተኛ ግዙፍ የሆነው ኮንጎ የናይልን 15 እጥፍ የሚተልቅ ሲሆን በመቶኛ ሲሰላ ናይል የኮንጎ ወንዝ 6 ነጥብ 7 በመቶኛ ይሆናል። ለዚህም ዋናው ምክንያት ወንዙ የሚመነጨው በጣም አነስተኛ ከሆነ የተፋሰሱ አከባቢ መሆኑ፤ የተለያዩ ሥነ¬-ምህዳሮችን አቋርጦ ረዥም ርቀት መጓዙ እና በአብዛኛው ከፍተኛ ሙቀት ያለው በረሃማ አካባቢ እያቆራረጠ መፍሰሱ ናቸው።
የናይል ወንዝ ሁለት ዋና ዋና ምንጮች ሲኖሩት እነሱም የናይል ታላላቅ ሐይቆች እና የኢትዮጵያ ደጋማ አካባቢዎች ናቸው። ዓባይ፣ ተከዜ፣ መረብ እና ባሮ አኮቦ ከኢትዮጵያ ወደ ናይል የሚገቡ ወንዞች ናቸው። እነኚህ ከአራት ተፋሰሶች የሚነሱ ወንዞች የናይልን 84 በመቶ ፍሰት ያዋጣሉ። ከናይል ታላላቅ ሐይቆች አካባቢ የሚመጡ ወንዞች ቀሪውን 16 በመቶ ፍሰት ያበረክታሉ። ከኢትዮጵያ ወደ ናይል የሚፈሱ ወንዞች ፍሰታቸው በወቅት የተዛባ ሲሆን ከፍተኛ ደለል ተሸክመዉ ይጓዛሉ። በአንጻሩ ከናይል ታላላቅ ሐይቆች አካባቢ የሚመጡ ወንዞች ፍሰታቸው የተረጋጋና የሚኖራቸው የደለል መጠንም አነስተኛ ነው።
የናይል ተፋሰስ አስር በመቶ የአፍሪካ የሕዝብ ብዛትና አስር በመቶ የአፍሪካን የቆዳ ስፋት ይይዛል። ተፋሰሱ 11 አገራትን የሚያካልል ሲሆን በአገራቱ ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦች ቁጥር ወደ 600 ሚሊዮን ይጠጋል። በተፋሰሱ ውስጥም ቁጥራቸው ከ260
ሚሊዮን የሚልቅ ሕዝቦች ይኖራሉ። ይህ የሕዝብ ብዛት በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ የሚገኝ በመሆኑ እ.አ.አ በ2050 ቁጥሩ አንድ ቢሊዮን እንደሚደርስ ይጠበቃል። ይህ በከፍተኛ ፍጥነት በመጨመር ላይ ያለው የሕዝብ ቁጥር ተፋሰሱ ካለው አነስተኛ የውኃ መጠን ጋር ተዳምሮ ናይልን ከፍተኛ የውኃ እጥረት የሚታይበት ተፋሰስ አድርጎታል። የከባቢ አየር ለውጥ የሚያስከትለው ተጽዕኖ፣ የከተሞች፣ የኢንደስትሪዎች እና የመስኖ እርሻዎች መስፋፋት የሚፈጥሩት ብክለት የውኃ ሀብት አጠቃቀሙን አወሳስበውታል። በርካታ አገራት ተንሰራፍቶ ከሚገኘው ድህነት፣ ኋላ ቀርነትና ያለመረጋጋት ለመላቀቅ የወንዙን ውኃ አጠቃቀም ማሳደግን እንደ ዋነኛ አማራጭ መያዛቸውም በአገራት መከከል ያለው ግንኙነት በጥርጣሬና ስጋት ላይ እንዲመሰረት አድርጎታል።
እንደ ናይል ያሉ ውስብስብና ከፍተኛ የውኃ እጥረት ያለባቸው ተፋሰሶች የውኃ ሀብቱን ፍትሃዊ፣ ምክንያታዊ እና ዘላቂ በሆነ መልኩ ለመጠቀም የተፋሰሱ አገራት ሉዓላዊ እኩልነታቸውና ግዛታዊ አንድነታቸውን በጠበቀ መልኩ ግልጽ፣ ቀነኣዊ እና አሳታፊ የሆነ ትብብር መካሂዱ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። ይህም ትብብር ህጋዊ እና ተቋማዊ ማዕቀፍ ላይ የተመሰረተ ቢሆን ዘላቂነቱ አስተማማኝ ይሆናል። ጎን ለጎንም የቴክኒክ ትብብር ማድረጉ ለህጋዊ እና ተቋማዊ ትብብር ድጋፍ ከመስጠቱም በላይ የትብብሩን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ብሎም ከትብብር የሚገኙ ጥቅሞች እንዲሰፉ በማድረግ በወቅቱ ጥቅሞቹን በተግባር በማሳየት አገራቱ በትብብር ላይ ያለቸውን እምነት እንዲያጎለብቱ ይረዳል።
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
አሥሩ የናይል ተፋሰስ አገራት፡- ኢትዮጵያ፣ ቡሩንዲ፣ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ ግብጽ፣ ኤርትራ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ታንዛኒያ እና ኡጋንዳ
የቅኝ ግዛት
የናይል ተፋሰስ አገራት በ1980 ጀርመን በርሊን ላይ ከተካሄደው አፍሪካን የመቀራመት ስምምነት አንስቶ እስከ አንደኛው የዓለም ጦርነት ድረስ በዘለቀው የቅኝ ግዛት ቀንበር ስር ወድቀው ቆይተዋል። በዚህ የአፍሪካ አገራትን የመውረር፣ የመያዝ እና በቅኝ ግዛት ስር የማዋል ዓላማን ያዘለ ዘመቻ ሰባት የምዕራብ አውሮፓ አገራት ተሳትፈውበታል። በናይል ተፋሰስ ውስጥ ከኢትዮጵያ በስተቀር ሁሉም የተፋሰሱ አገራት በቅኝ ግዛት የተያዙ ሲሆን እንግሊዝ፣ ፈረንሣይ፣ ቤልጅየም፣ ጀርመን እና ኢጣሊያ ዋናዎቹ ቅኝ ገዥዎች ናቸው። ከዚህ አፍሪካን የመቀራመት ዘመቻ ቀደም ብሎም ግብጽ በፋርስ፣ በግሪክ፣ በሮማን፣ በዓረቦች እና በቱርኮች ተገዝታ እንደነበር ይታወቃል። በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይም እንግሊዝ በላንካሻይር የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎቿ የገጠማትን የጥጥ ግብዓት እጥረት ለመቅረፍ፣ የስዊዝ ቦይን በቅርብ ለመቆጣጠር እንዲሁም የቅኝ ግዛት ፍላጎቷን
የናይል ተፋሰስ ትብብርን የወሰኑ ቁልፍ ተግባራት ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ለማሸጋገር ግብጽን በቅኝ ግዛት ያዘች። በመቀጠልም ሱዳንን፣ ኬንያን፣ ኡጋንዳ እና ታንጋኒካ (የአሁኗን ታንዛንያን) ተቆጣጠረች። ኢጣሊያ ኤርትራን፤ ጀርመን ታንዛኒያን፤ ቤልጅየም ሩዋንዳን፣ ቡሩንዲን እና ኮንጎን እንዲሁም ፈረንሣይ የናይል ተፋሰስ አጎራባች አገራትን በቅኝ ግዛቶቻቸው ስር አኖሩ።
በቅኝ ግዛት መያዝ ብቻ ሳይሆን፤ የቅኝ ግዛት ምኞት ያላቸው አገራት መሸጋገሪያ የሆነችው ግብጽ ራሷም ቅኝ ገዥ በመሆን ከእንግሊዝ ጋር ሱዳንን እስከ 1956ቱ የሱዳን ነጻነት ድረስ ገዝታለች። ግብፅ ቀደም ብሎ በኦቶማን ቱርክ ቁጥጥር ስር በነበረችበት ወቅት በተስፋፊዋ ኸዲቭ እስማኢል እየተመራች የናይል ግዛታዊ አሃዳዊነትን ዕቅድ ለማሳካት የነበራትን ምኞት እውን ለማድረግ ያካሄደችው የመስፋፋት ሙከራ የአፄ ዮሐንስ ጦር ጉንደት (1875) እና ጉራ (1976) ላይ ባደረሱባቸው ካባድ ሽንፈት ተገቷል።
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
የቅኝ ገዥ አገራት ግብጽ ውስጥ ያላቸውን የመስኖ እርሻና ሌሎች ኢንቨስትመንቶች ውጤታማነት ለማረጋገጥ የናይል ውኃን ለግብጽ ጥቅም ብቻ ለማዋል የተለያዩ ተግባራትን አከናውነዋል። ይህንኑ ለማረጋገጥም በርካታ ስምምነቶችን እርስ በእርሳቸው፣ ከቅኝ ግዛቶቻቸውና ከነጻ አገራት ጋር ተፈራርመዋል። የውኃ ሀብቱን ለመቆጣጠር የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን የገነቡ ሲሆን የላይኛው ተፋሰስ አገራት ውኃውን ለማልማት የሚያስፈልጋቸውን ፋይናንስ እንዳያገኙ የሚያግዱ አሰራሮችንም ተግብረዋል። ይህም የናይል ተፋሰስ ትብብርን እስከ አሁን ድረስ አወሳስቦታል።
የቀዝቃዛው ጦርነት በናይል ተፋሰስ ውስጥ
እ.አ.አ በ1952 በሙሐመድ ናግብ እና ጀማል አብዱልናስር የሚመራ የግብጽ ነጻ መኮንኖች ንቅናቄ የንጉሥ ፋሩቅን መንግሥት በመገልበጥ ሥልጣን ያዘ። በንጉሡ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ በማስታከክ የተጀመረው ይህ የግብጽ አብዮት አገሪቷን ከታላቋ ብሪታንያ፤ ሱዳንን ከግብጽ እና ታላቋ ብሪታንያ የጥምር ቅኝ ግዛት ነጻ የማውጣት፤
ግብጽ ትመራበት የነበረውን ሕገ መንግሥታዊ የዙፋን ሥርዓት የመገርሰስና የዓረብ ሪፐብሊክ የማቋቋም ዓላማ የያዘ ሲሆን ጽንፈኛ ብሔረተኝነትና ፀረ ኢምፔሪያሊዝምን እንደ መርህ በመያዝ የዓረብ ብሔረተኝነትና ዓለም አቀፋዊ ገለልተኛነትን የማራመድ አቅጣጫ የያዘ ነው። ይህ አቋም ግብጽ በሶቪዬት ህብረት ወደሚመራው የምስራቁ ዓለም እንድታጋድል ያደርጋታል።
አፄ ኃይለሥላሴ የአሜሪካ ወዳጅ መሆናቸው ይታወቃል። አሜሪካኖችም ለንጉሡ የጠነከረ ከበሬታ ነበራቸው። ንጉሡ ከ1954 ጀምሮ በአይዘንሀወር፣ በኬኔዲ፣ በኒክሰን እና ጆንሰን ዘመን ስድስት ጊዜ አሜሪካን ጎብኝተዋል። እንግሊዞች ጣና ሐይቅ ላይ ግድብ ለመገንባት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴም ለማኮላሸት ንጉሡ ከአሜሪካ ጋር ያላቸውን መቀራረብ እንደ አንድ ስልት ተጠቅመዋል። እ.አ.አ ከ1956 እስከ 1964 የተካሄደውን የዓባይ የመሬት እና የውኃ ጥናት ቢሮ (Bureau Of Reclamation) የተባለ የአሜሪካ ኩባንያ እንዲያጠና አድርገዋል። ይህ የዓባይ ወንዝ
ተፋሰስን የሸፈነ ጥናት እንዲካሄድ አፄ ኃይለስላሴ አሥር ሚሊዮን ዶላር የከፈሉ ሲሆን የአሜሪካ መንግሥት አስተዋጽኦም ከፍተኛ ነበር።
በ1950 መጀመሪያ አካባቢ ግብጽ ታላቁን የአስዋን ግድን ለመገንባት ስታቅድ የአሜሪካ መንግሥት፤ እንግሊዝ እና የዓለም ባንክ የግድቡን ግንባታ በፋይናንስ ለመደገፍ አቅደው የነበረ ቢሆንም ግብጽ በወቅቱ ስታራምደው የነበረውን የብሔርተኝነት አስተሳሰብና የምትከተለው ጸረ ምዕራብ አገራት ፖሊሲ ያልተመቻቸው አሜሪካና እንግሊዝ ከግድቡ ድጋፍ ላይ እጃቸውን አውጥተዋል። አገራቱ የፋይናንስ ድጋፉን መሰረዛቸውን ሲያሳውቁ ጀማል አብዱልናስር አጋጣሚውን በመጠቀም ለግድቡ ግንባታ የፋይናንስ ምንጭ ይሆናል በሚል በ1956 የእንግሊዝና የፈረንሳይ ባለሀብቶች ንብረት የነበረውን የስዊዝ ቦይ ወርሰዋል። ይህንንም ተከትሎ የእንግሊዝ፣ የፈረንሳይ እና የእስራኤል ጦር ግብጽ ላይ ጥቃት ፈፅመዋል። ይህንን ጥቃት ምንም እንኳን አሜሪካ ያስቆመችው ቢሆንም በወቅቱ ተቃውሞዋን ያሰማችው ሶቪየት ህብረት የግድቡ ግንባታ የፋይናንስ ድጋፍ መሰረዝን እንደ አጋጣሚ በመጠቀም ለግብጽ አንድ ቢሊዮን ዶላር ለዚሁ አገልግሎት በብድር ያቀረበች ሲሆን የቴክኒክ ድጋፍም አድርጋለች። በመቀጠልም ጀማል አብዱልናስር ለወደፊት የግብጽ የማደግ ዕድልም ሆነ ከእስራኤል ጋር ባለው ግጭት የሶቪየት ህብረትን የጦር መሣሪያ ድጋፍ በመፈለጋቸው ግብጽ ከምስራቁ አገራት ጎራ በግልጽ እንድትቀላቀል አድርገዋል።
እ.አ.አ በ1974 ኢትዮጵያ ውስጥ በተካሄደው አብዮት የአፄ ኃይለሥላሴን መንግሥት በመገርሰስ
ሥልጣን የተቆጣጠረው ወታደራዊ መንግሥትም ኢትዮጵያ የሶሻሊስት ሥርዓት እንደምትከተል በማወጅ አሜሪካኖች ከኢትዮጵያ እንዲወጡ አድርጓል። በመቀጠልም ኢትዮጵያ የወሰደቻቸው ተከታታይ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እርምጃዎች የምዕራቡን ዓለም ያስኮረፈ ሲሆን የሶቪየት ህብረት በኢትዮጵያና ሶማሊያ ጦርነት ወቅት ለኢትዮጵያ ያደረገችው የጦር መሣሪያ አቅርቦትና የማማከር አገልግሎት፤ የኩባ እና የሰሜን የመን ከኢትዮጵያ ጎን መሰለፍ አገሪቷ ወደ ምስራቁ ጎራ ጠቅላላ እንድትገባ አድርጓል።
ፕሬዚደንት ጀማል አብዱልናስር እ.አ.አ በ1970 ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ በእርሳቸው ቦታ የተተኩት አንዋር ሳዳት በግብጽ ኢኮኖሚዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ቀጣናዊ ሁኔታዎች ላይ መሰረታዊ ለውጥ አሳይተዋል። ሥልጣን በያዙ በአንድ ዓመት ውስጥ በ1967ቱ የግብጽ-እስራኤል ጦርነት ግብጽ የደረሰባትን ሽንፈት ለመበቀል ሲሉ እስራኤልን ለመውጋት ያላቸውን ዕቅድ ለማሳካት ከሶቪየት ኅብረት መሣሪያ ለማግኘት ያደረጉት ጥረት ባለመሳካቱ ከሰቪየት ህብረት ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማቋረጥ ቀስ በቀስ ወደ ምዕራቡ ጎራ ተመልሰዋል።
በዚህ ሁኔታ ኢትዮጵያና ግብጽ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ከምዕራቡ እና ከምስራቁ ዓለም ጋር ያላቸውን ግንኙነት ከአንዱ ፅንፍ ወደ ሌላኛው ሲለዋውጡ ግብጽ ዕድሉን በመጠቀም የታላቁን የአስዋን ግድብ በመገንባት የናይልን ውኃ መቆጣጠር ብቻ ሳይሆን ኤኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ አቅሟን በከፍተኛ ደረጃ ስታሳድግ ኢትዮጵያ ዓባይ ላይ ያስጠናችውን
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
ጥናት በአግባቡ ወደ ትግበራ ሳታስገባ ቆይታለች።
ቀደምት የናይል ተፋሰስ የትብብር ሂደቶች፤ የቅኝ ግዛትና ድህረ ቅኝ ግዛት ስምምነቶች
ግብጽና አጋሮቿ ናይልን በቅኝ ግዛት በመያዝ፣ የናይል ተፋሰስን ግዛታዊ አሃዳዊነት ለግብጽ ጥቅም በማረጋገጥ ወንዙን ከምንጩ ለመቆጣጠር ያደረጉት ሴራ ሳይሳካ ሲቀር ስልታቸውን በመቀየር የተፋሰሱን አገራት በተለያዩ ህጋዊ ስምምነቶች በመቀፍደድ ውኃው ያለምንም እንቅፋት ወደ ግብጽ እንዲፈስ ለማድረግ ተዘጋጁ። ይህንንም ለማሳካት ተፋሰሱን በበርካታ ህጋዊ ስምምነቶች እንዲታጠር አድርገውታል። እነዚህ ስምምነቶች በቅኝ ገዥዎች መካከል፣ በቅኝ ገዥዎች እና ነፃ መንግሥታት፣ በቅኝ ገዥዎች እና በቅኝ ግዛት ስር ባሉ መንግሥታት እንዲሁም በድህረ ቅኝ ግዛት መንግሥታት የተገቡ ስምምነቶች ናቸው።
በቅኝ ገዥዎች መካከል የተፈጸሙ ስምምነቶች
በቅኝ ገዥዎች መካከል ከተፈጸሙ ስምምነቶች ውስጥ ከሚመደቡት ውሎች አንዱ እንግሊዝ የተከዜን ወንዝ ከላይ እንድትቆጣጠር የፈቀደው የ1991 የእንግሊዝ እና የኢጣሊያ ስምምነት ሲሆን ሌላው ስምምነት የአፄ ምኒልክን መታመም ተክትሎ የኢትዮጵያን ሎዓላዊነት ለማረጋገጥና የየራሳቸውን የግዛት ክልል ለመወሰን ሲባል በእንግሊዝ፣ በፈረንሳይና በኢጣሊያ መካከል የተፈጸመው የ1906ቱ ስምምነት፣ እንዲሁም በዚሁ ዓመት በቤልጅየም እና በእንግሊዝ መንግሥታት መካከል የተገባውና ኮንጎ ወደ ናይል በሚገቡት የሲሚሊክ እና ኢሳንጎ ወንዞች ላይ ምንም ግድብ እንዳትገነባ የሚደነግጉ ስምምቶች ናቸው።
በ1925 እንግሊዝ እና ኢጣሊያ ኢትዮጵያ በዓባይ፣ በነጭ ዓባይ እና የእነዚህ ወንዞች ገባሮች ላይ ምንም ግድብ እንዳትገነባ የሚደነግገው ስምምነት፤ በ1949 እንግሊዝ እና ግብጽ ኡጋንዳ ውስጥ በግብጽና በኡጋንዳ የሚገነባውን የኦዌንስ ፏፏቴ ግድብ በተመለከተ የገቧችው ስምምነቶች በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ይገባሉ።
በቅኝ ገዥዎች እና ነጻ አገራት መካከል የተገቡ ስምምነቶች
እ.አ.አ በ1902 በኢትዮጵያና በእንግሊዝ መካከል የተገባውና በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ድንበር ለመከለል የተፈረመው ይህ ስምምነት በቅኝ ገዥዎች እና በነጻ መንግሥታት መካከል የተገባ ብቸኛ ስምምነት ነው። ምንም እንኳን ይህ ስምምነት በኢትዮጵያና በሱዳን መከከል ያለውን ድንበር ለመከለል እንግሊዝ ቅኝ ግዛቷን ሱዳንን በመወከል የፈረመችው ውል ቢሆንም በዚህ ስምምነት አንቀጽ 3 ላይ አፄ ምኒልክ በዓባይ ወንዝ፣ በጣና ሐይቅ እና በሶባት ወንዝ ላይ ወንዙን ከዳር ዳር የሚደፍን ምንም ሥራ ላለመሥራት ወይንም እንዲሠራ ላለመፍቀድ የተስማሙበት ነው። ይህ ስምምነት በኢትዮጵያ በኩል የተገባበት አስገዳጅ ሁኔታ፣ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቅጅ መካከል የታየው ልዩነት፣ ለሁለቱ ተፈራራሚዎች የሰጠው የተዛባ መብትና የጣለባቸው ግዴታ፣ ከተፈረመ በኋላ በአገራቱ ዘንድ የታየው መሰረታዊ ለውጥ፣ በሁለቱ ተፈራራሚ አገራት መንግሥታት ያለመፅደቁ እና በሌሎች በርካት ምክንያቶች የተነሳ በኢትዮጵያ ላይ አስገዳጅነት የሌለው መሆኑ ይታወቃል።
በቅኝ ገዥዎች እና በቅኝ ግዛት ስር ባሉ አገራት
መካከል የተፈረሙ ስምምነቶች
በቅኝ ገዥዎችና በቅኝ ግዛት ስር በሚገኝ አገር መካከል የተፈረመው ስምምነት የ1929 የናይል ውኃ ውል ነው። ይህ በማስታወሻ ልውውጥ መልክ በታላቋ ብሪታንያ እና በቅኝ ግዛቷ ግብጽ መካከል የተገባው ስምምነት በናይል ከተደረጉ ዋና ዋና ስምምነቶች ተርታ የሚሰለፍ ነው። በናይል ተፋሰስ ውስጥ እስከ አሁን ድረስ ሁሉን አቀፍ የውኃ አጠቃቀም ህጋዊ ማዕቀፍ እና ተቋማዊ አደረጃጀት እንዳይኖር ካደረጉ ተግዳሮቶች ውስጥ አንዱ የዚህ የ1929 ስምምነትና እሱን ተከትለው የመጡ መዘዞች ናቸው።
ታላቋ ብሪታንያ ስምምነቱን የፈረመችው በወቅቱ በቅኝ ግዛቷ ስር የነበሩትን ሱዳንን፣ ኬንያን፣ ኡጋንዳ እና ታንጋኒካን (የአሁኗን ታንዛንያ) በመወከል ነው። ስምምነቱ ሦስት ዋና ዋና ዓላማዎች ሲኖሩት የመጀመሪያው ከውኃ አጠቃቀም ጋር የተያያዘውና ታላቋ ብሪታንያ ግብጽ ውስጥ ላላት የጥጥ መስኖ እርሻና በስሯ ለሚተዳደሩ
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
የግብጽ አርሶ አደሮች በቂ ውኃ እንዲኖር ለማድረግ የገባችው ውል ነው። ሁለተኛው ዓላማ ፖለቲካዊ ሲሆን ከ1919 ጀምሮ ግብጽ ውስጥ እየተጠናከረ የመጣውንና በሳዕድ ዛግሉል የሚመራውን የጸረ ቅኝ ግዛት ንቅናቄና የብሔርተኝነትን ስሜት ለማዳከም፤ የግብጽ ሕዝብ በቅኝ ግዛት ላይ እምነት እንዲኖረው በማድረግ የቅኝ ግዛት ዘመናቸውን ለማራዘምና ግብጽን በቅኝ ግዛት ቀንበር ለዝንተ ዓመት ለማቆየት የታለመ ሲሆን፤ ሶስተኛው የዚህ ስምምነት ዓላማ ስትራቴጂካዊና ታላቋ ብሪታንያ በወቅቱ ግብጽ ውስጥ ይታይ የነበረው የጸረ ቅኝ ግዛትና የብሔረተኝነት ንቅናቄ ተንሰራፍቶ አገሪቷን ለቀው እንዲወጡ የሚያስገድዳቸው ከሆነ በግብጽ ያላቸውን ኢንቨስትመንት ወደ ሱዳን ለማሸጋገር እና ራሳቸውም ወደዚያው የማፈግፈግ ዕቅድ ነበር።
ስምምነቱ በወቅቱ ባሉት መሰረተ ልማቶችና የውኃ አጠቃቀም መቆጣጠር ከሚቻለው 52 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ የናይል ውኃ ውስጥ 48 ቢሊዮን ሜ.ኩ ለግብጽ እንዲሁም ቀሪውን አራት ቢሊዮን ሜ.ኪ ለሱዳን መድቧል። በተጨማሪም ይህ ስምምነት ግብጽ በናይል ውኃ ላይ ታሪካዊ መብት እንዳላት የደነገገና የላይኛው ተፋሰስ አገራት በሚያደርጉት የውኃ አጠቃቀም ላይ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ከመስጠት በላይ አስፈላጊ ሆኖ ካገኘችው በላይኛው ተፋሰስ አገራት ውስጥ የውኃ መሰረተ ልማት የመገንባት ሥልጣንም የሰጠ ነው። ይህ ስምምነት ኢትዮጵያ ሉዓላዊት አገር ሆና ሳለ እሷን ሳያካትት የተገባ በመሆኑ በኢትዮጵያ ላይ ምንም አይነት ተፈጻሚነት የሌለው ሲሆን ውሉ ለአገራቱ ለሰጠው የውኃ ድርሻም ኢትዮጵያ ምንም እውቅና አልሰጠችም።
የ1929ኙ ስምምነት በስማቸው የተፈረመላቸው የላይኛው ተፋሰስ አገራትም ተራ በተራ ከቅኝ ግዛት ቀንበር ነጻ ሲወጡ ውድቅ አድርገውታል። በተለይ ታንዛኒያ ስምምነቱን ውድቅ ለማድረግ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ጁሊዬስ ኔሬሬ ያወጡትን የኔሬሬ ድንጋጌ ተጠቅመዋል። ይህም ድንጋጌ አንድ በቅኝ ግዛት ስር የነበረ አገር ከቅኝ ግዛት ነጻ ሲወጣ በቅኝ ግዛት ስር በነበረበት ወቅት ቅኝ ገዥዎች በስሙ የገቡትን ስምምነት ማክበር ያለበት ቢበዛ ለሁለት ዓመት ብቻ ነው ሲል ይደነግጋል። ኬንያ እና ኡጋንዳም ይህንኑ ድንጋጌ ተጠቅመው ውሉን ውድቅ አድርገውታል። በስምምነቱ የተካተተውና ግብጾች በሰፊው ሊጠቀሙበት የሚሞክሩት ታሪካዊ መብት የሚባለው ትርክትም ህጋዊነት የሌለው፣ እንደ ውኃ ባለ ተንቀሳቃሽ ሀብት ላይ ተፈጻሚ መሆን የማይችል፣ የማንንም አገር ወይንም ተቋም ድጋፍ ያላገኘ ኋላቀር አስተሳስብ መሆኑ ይታወቃል።
የድህረ ቅኝ ግዛት ስምምነቶች
የድህረ ቅኝ ግዛት ስምምነት ተብሎ የሚታወቀውና በሁለት ከቅኝ ግዛት ነጻ በወጡ አገራት መካከል የተገባው ውል በግብጽ እና በሱዳን መካከል የናይልን ውኃ ሙሉ በሙሉ ጥቅም ላይ ለማዋል የተፈረመው የ1959 የናይል ውኃ ስምምነት ነው። ይህ ስምምነት ከቅኝ ግዛት ነጻ በወጡ ሁለት ነጻ አገራት መካከል የተገባ ይሁን እንጂ መሰረቱ የ1929ኙ ስምምነት በመሆኑ ከቅኝ ግዛት ስምምነት ተጽዕኖ የነጻ አይደለም።
ይህንን ስምምነት ለመፈራረም መነሻ የሆነው በ1952 መፈንቅለ መንግሥት ወደ ሥልጣን የመጡት ጀማል አብዱልናስር የግብጽን ሕዝብ
ድጋፍ በመፈልግ የአስዋንን ግድብ ለመገንባት በማቀዳቸውና ግድቡ ሲገነባ የሚፈጠረው ሐይቅ ሱዳን ውስጥ 250 ኪ.ሜ ዘልቆ ስለሚገባ የሱዳን ስምምነት ወሳኝ በመሆኑ ነው። ግብጽና ሱዳን በዚሁ ጉዳይ ከ1954 ጀምሮ የተደራደሩ ሲሆን ሂደቱም አስቸጋሪ እንደነበር ይታወቃል። በተጨማሪም ሱዳን በ1956 ከእንግሊዝ እና ከግብጽ የጥምር ቅኝ ግዛት ነጻ ስትወጣ የ1929ኙን ስምምነት ውድቅ ማድረጓ ሁኔታውን አሳሳቢ አድርጎታል። የሱዳን ተደራዳሪዎችም የውኃው ክፍፍል ፍትሃዊ እንዲሆን፣ ግብጽ በላይኛው ተፋሰስ ፕሮጀክቶች ላይ ያላት ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት እንዲሻርና ሱዳን ውስጥ በአስዋን ግድብ የተነሳ ለሚፈናቀሉ ዜጎች አስፈላጊው ካሳ እንዲከፈል አበክረው ሞግተዋል።
ድርድሩ አስቸጋሪ ደረጃ ላይ ባለበት ወቅት ሱዳን ውስጥ በሕዝብ የተመረጠው መንግሥት በጄኔራል ኢብራሂም አቡድ በተመራ መፈንቅለ መንግሥት በ1958 እንዲገረሰስ ሆኗል። ከዚህ መፈንቅለ መንግሥት ጀርባ የግብጽ እጅ አለበት የሚል ሀሜት በሰፊው ይነገራል። ግብጽም ወዲያው ለሱዳን ነጻነትና ለጄኔራል ኢብራሂም አቡድ መንግሥት እውቅና የሰጠች ሲሆን አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ተቋርጦ የነበረው ስምምነት ተጠናቆ እንዲፈረም ተደርጓል።
በ1959ኙ የናይል ውኃ ስምምነት አማካኝነት የአስዋን ግድብ በመገንባቱ የተነሳ የናይልን ውኃ ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር አስችሏል። በዚሁ መሰረትም የናይል ወንዝ ፍሰት አስዋን ላይ ሲለካ 84 ቢሊዮን ሜ.ኪ መሆኑ በመታወቁ የ1929 ስምምነት ለሁለቱ አገራት ከመደበው
ተጨማሪ 32 ቢሊዮን ሜ.ኪ ውኃ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚቻል ታውቋል። ከዚህ ተጨማሪ ውኃ ውስጥም 10 ቢሊዮን ሜ.ኪ ለአስዋን ግድብ በትነት ለሚጠፋ ውኃ፣ 14 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሜ.ኪ ለሱዳን እና ቀሪው 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሜ.ኪ ለግብጽ በተጨማሪነት ተመድቧል።
ሲጠቃለልም አስዋን ከሚደርሰው 84 ቢሊዮን ሜ.ኪ ውኃ ውስጥ 55 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሜ.ኪ ለግብጽ፣ 18 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሜ.ኪ ለሱዳን እና ቀሪው 10 ቢሊዮን ሜ.ኪ ውኃ ለአስዋን ግድብ (ናስር ሐይቅ) ለትነት ተመድቧል። ኢትዮጵያን ጨምሮ ለላይኛው ተፋሰስ አገራት ምንም ውኃ አልተመደበም። በስምምነቱ መሰረት ግብጽ የአስዋንን ግድብ ሱዳን ደግሞ ዓባይ ወንዝ ላይ የሮዚርዬስ ግድብን ትገነባለች። እንደ ማስተዛዘኛም የላይኛው ተፋሰስ አገራት ለሚያነሱት የውኃ ጥያቄ ሁለቱ አገራት የጋራ ምላሽ ለመስጠት ተስማምተዋል።
ይህ የ1959 ስምምነት ሲፈረም ሁለቱ አገራት ሉዓላዊነቷን ጠብቃ የቆየችውን ኢትዮጵያን ለማሳተፍ ፍቃደኛ ባለመሆናቸው አገራችን ስምምነቱን ውድቅ በማድረግ ለሚመለከታቸው አካላት አሳውቃለች። ስምምነቱ ለሁለቱ አገራት የሰጠውን የውኃ ድርሻም ሆነ ስምምነቱን መሰረት በማድረግ ለተገነቡ መሰረተ ልማትና የውኃ አጠቃቀሞች ኢትዮጵያ ምንም አይነት እውቅና አልሰጠችም። ስምምነቱም ተፈጻሚ የሚሆነው በሁለቱ የስምምነቱ አካላት ላይና ድንበራቸው ውስጥ የገባ ውኃ ላይ ብቻ ይሆናል። ይህ ድርጊታቸው ሁለቱን አገራት ከፍተኛ ጸጸት ውስጥ እንደከተታቸው ይታመናል።
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
የይስሙላ የትብብር መድረኮች
ግብጽና አጋሮቿ የላይኛውን ተፋሰስ አገራት በህጋዊ ስምምነት ቀፍድደው በመያዝ በድንበራቸው የሚፈሰውን ውኃ እንዳይጠቀሙ ለማድረግ የሸረቡት ሴራ አገራቱ ከቅኝ ግዛት ነጻ እንደወጡ ስምምነቶቹን ውድቅ በማድረጋቸው ሳይሳካ ቀርቷል። በመቀጠልም ግብጽ የአስዋንን ግድብ በመገንባት ለውኃ ፍላጎታቸው በላይኛው ተፋሰስ ላይ ያላቸውን ጥገኝነት ለመቅረፍ ቢሞክሩም ይህ ስልት የላይኛው ተፋሰስ አገራት ግድብ መገንባት ከጀመሩ መፍትሄ እንደማይሆን ተረድተዋል።
ለዚህም እንደ መፍትሄ ግብጽ የተከተለችው የላይኛው ተፋሰስ አገራትን በይስሙላ የትብብር መድረኮች በማጥመድና መጨረሻ የሌለው አዙሪት ውስጥ በመክተት ትኩረታቸውን ወደ ውኃ አጠቃቀም እንዳይመልሱ ማድረግ ነው። ግብፅ እና አጋሮቿ ተግባራዊ ያደረጓቸው ሦስት የይስሙላ ስምምነቶች የሚከተሉት ናቸው።
የኃይድሮሜት ልኬት (Hydromet)
ይህ የኃይድሮሜት ልኬት ስምምነት በ1967 የተጀመረ ሲሆን ዋና ዓላማው በናይል ታላላቅ
ሐይቆች አካባቢ በሚገኙ ዋና ዋና ሐይቆች እና የውኃ አካላት ላይ የፍሰት መለኪያ መትከል፣ መረጃ መሰብሰብና ለታችኛው ተፋሰስ አገራት ጥቅም ማዋል ነው። ኢትዮጵያ በዚህ ትብብር ላይ ከ1971 ጀምራ በታዛቢነት ተሳትፋለች።
ኡንዱጉ (በክስዋሂሊ ወንድማማችነት) - Un- dugu
ይህ ኡንዱጉ የተባለው የትብብር መድረክ በግብጽና በአጋሮቿ ከ1983 – 1993 ከተመሩ ስምምነቶች ውስጥ አንዱ ሲሆን ዓላማውም በአብዛኛው ከውኃ አጠቃቀም ጋር ምንም ግንኙነት በሌላቸው እንደ ባህል፣ ትምህርት፣ ጤና፣ የኃይል ንግድ እና መሰረተ ልማት ላይ ያተኮረ ነው። ይህም የትብብር መድረክ መሰረታዊውን የናይል አጀንዳ ስለማይነካ ኢትዮጵያ ታዛቢ መሆንን መርጣለች።
ቴኮናይል (TECONNILE)
ይህ የናይል ተፋሰስን ለማልማት እና ለመንከባከብ ታልሞ የተቀረጸው የቴክኒክ ትብብር መድረክ የተጀመረው በ1993 ነው። የዚህ የትብብር መድረክ የረዥም ጊዜ ዓላማ የናይል ተፋሰስ አገራት የናይልን ውኃ በዘላቂነት እንዲያለሙ፣ እንዲንከባከቡ እንዲጠቀሙ መርዳት ሲሆን የአጭር ጊዜ ዓላማውም በትብብሩ የሚሳተፉ አገራት የየራሳቸውን መሪ ዕቅድ እንዲያዘጋጁና የናይል ተፋሰስ የልማት ዕቅድ አካል እንዲያደርጉ ማገዝ፣ በመሰረተ ልማት እና በአቅም ግንባታ እንዲሁም በውኃ ሀብት አስተዳደር ላይ ማገዝ ነው። ቴኮናይ እንደ ናይል ተፋሰስ አትላስ፣ የናይል ተፋሰስ የድርጊት መርሃ ግብር ያሉ ውጤቶችን ያስገኘ ሲሆን የናይል 2002 የተሰኙ አውደ ጥናቶችንም አስተባብሯል። ይህ የትብብር መድረክ
እንደ ቀደምት የትብብር ተግባራት ሁሉ ዋነኛውንና ወሳኙን የውኃ አጠቃቀም ጉዳይ በዝምታ ያለፈው ቢሆንም ለናይል የትብብር መድረክ መፈጠር አይነተኛ ሚና ተጫውቷል። ኢትዮጵያ በዚህኛውም መድረክ ታዛቢ ብትሆንም መድረኩን የላይኛው ተፋሰስ አገራትን ለማስተባበር ተጠቅማበታለች።
በጠቅላላው ከላይ የተዘረዘሩት የይስሙላ ስምምነቶች ከተወሰኑት በስተቀር ሁሉም አገራት ያልተሳተፉባቸው በመሆናቸው አካታች ያልነበሩ፣ መሰረታዊውን የውኃ አጠቃቀም አጀንዳ በዝምታ ያለፉ፣ ጥቃቅን ጉዳዮች ላይ ብቻ ያተኮሩ በመሆናቸው አግባብነት እና ሁለገብነት የላቸውም። ይሁን እንጂ ሶስተኛው የትብብር መድረክ ማለትም ቴኮናይል (TECONNILE) በሚተገበርበት ወቅት ኢትዮጵያ መድረኩን በአግባቡ ተጠቅማ የላይኛው ተፋሰስ አገራትንና አንዳንድ የልማት አጋሮችን የይስሙላ መድረኮቹ መሰረታዊውን የናይል ተፋሰስ ችግር የማይፈቱ የማዘናጊያ አጀንዳዎች መሆናቸውን አበክራ በማስገንዘብና በማሳመን ዘላቂ የትብብር መድረክ እንዲጠነሰስ አድርጋለች።
የናይል ተፋሰስ ትብብር፣ የትይዩ ጉዞ (Paral- lel Track)
ከላይ እንደተጠቀሰው ቴኮናይል የተሰኘው የይስሙላ ስምምነት ሊጠናቀቅ አካባቢ ኢትዮጵያ ለላይኛው ተፋሰስ አገራትና ለአንዳንድ የልማት አጋሮች ሂደቱ ወደሚፈለገው ፍትሃዊና ምክንያታዊ የውኃ አጠቃቀም የማያደርስ መሆኑን በመግለጽ ያደረገችው ውትወታ ጆሮ ሊያገኝ ችሏል። ቴኮናይል ሲጠናቀቅ የናይል ተፋሰስ የድርጊት መርሃ ግብርን እንደ አንድ ውጤት አዘጋጅቷል። ይህም መርሃ
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
ግብር ወደ 25 ፕሮጀክቶችን በውስጡ አካቷል። ፕሮጀክቶቹ በባለ አምስት በአምስት ረድፍ እና ወርድ ሰንጠረዥ የተዘረዘረ እና ረድፉ በእንግሊዝኛ ፊደላት (A,B,C,D,E)፤ ወርዱ ደግሞ በቁጥር (1,2,3,4,5) የተሰየመ ነው።
በ1995 የናይል ተፋሰስ አገራት የተፋሰሱን የድርጊት መርሃ ግብር ሲያጸድቁ በመርሃ ግብሩ ውስጥ ከተዘረዘሩ ፕሮጀክቶች በረድፍ አራት ማለትም D እና በወርድ 3 ላይ የተቀመጠው ፕሮጀክት ቅድሚያ እንዲሰጠው ተስማምተዋል። ፕሮጀክቱም D3 በመባል የተሰየመ ሲሆን በዚሁ ጊዜ አሩሻ ታንዛኒያ ላይ የተሰበሰበው የናይል የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሙሉ ድምጽ ወደ ትግበራ እንዲገባ አጽድቆታል። የዚህ ፕሮጀክት የአጭር ጊዜ ዓላማ አገራቱ ሊስማሙበት የሚችሉ ሁሉን አቀፍ ስምምነት ማዘጋጀት፤ የረዥም ጊዜ ዓላማው ደግሞ የናይል ተፋሰስ አገራት ለሕዝባቸው ዘላቂ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚያስገኝ የውኃ አጠቃቀሞ ይኖራቸው ዘንድ መሰረታዊ የሆነውን ፍትሃዊ የውሃ ክፍፍል ለመወሰን ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነው። የዚህ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ውጤት የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት (Nile Basin Cooperative Framework Agreement, CFA) ነW። የD3 ፕሮጀክት ትግበራ በ1997 የተጀመረ ሲሆን የትብብር ማዕቀፉን ለማዘጋጀት በተፋሰሱ አገራት መካከል ረጅም እና እልህ አስጨራሽ ድርድር ተካሂዷል። ይህም አንደኛው የትብብር መድረክ ጎዳና ነው።
የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን ለመቅረጽ ድርድር ሲጀመር ጎን ለጎን የሽግግር ጊዜ ተቋም አስፈላጊነት የታመነበት ቢሆንም በፋይናንስ
እጥረት የተነሳ በወቅቱ ሳይቋቋም ቀርቷል። ድርድሩ እንደተጀመረ ግን በርካታ ችግሮች ይታዩ ጀመር።
በድርድሩ ወቅት በተደራዳሪዎች ዘንድም ሆነ በሚኒስትሮች መካከል የመተማመን ችግር ነበር። ውይይቶችን በግልጽ ማካሄድ አልተቻለም። አገራት አቋማቸውን፣ ፍላጎቶቻቸውንና መረጃዎቻቸውን ምስጢር ማድረግ ይቀናቸው ነበር። መተማመን ከሌለ ውጤታማ ድርድር ማካሄድ አስቸጋሪ ይሆናል።
ሌለው ችግር የአቅም ልዩነት ነበር። በናይል ተፋሰስ አገራት መካከል ከፍተኛ የሰው ኃይልና የተቋማዊ አቅም፣ የመሰረተ ልማት፣ የመረጃና መረጃን የመተንተን ሥርዓትን በተመለከት የአቅም ልዩነት ይታይ ነበር። እንዲህ አይነት የአቅም ልዩነት በድርድር ወቅት ወደ ውጤት ለመምጣት አያስችልም። አቅም የለኝም ብሎ የሚያስብ ተደራዳሪ ሁሉንም ሀሳብ ያለመቀበልን ሊመርጥ ይችላል።
የፖሊሲዎች ያለመጣጣም ሦስተኛው ችግር ነው። ሁሉም አገራት የየራሳቸው የውኃ ፖሊሲ ያላቸው ሲሆን የፖሊሲዎቹ ይዘት በፍጹም የማይጣጣም እንዲሁም እርስ በእርሱ የሚቃረን ሆኖ ተገኝቷል። ድርድሩንም ሆነ ሌሎች ትብብሮችን ውጤታማ ለማድረግ ፖሊሲ ማጣጣም አስቸጋሪ ቢሆንም እንኳ እርስ በእርሳቸው እንዲናበቡ ማድረጉ አስፈላጊ ነበር።
የናይል ተፋሰስ አገራት የነበራቸው የመረጃ አሰባሰብና አተናተን ሥርዓትም በጣም የተለያየ ሆኖ ተገኝቷል። በተፋሰስ ደረጃ በጋራ ለሚደረስባቸው ውሳኔዎች የሚፈለገው መረጃና መረጃውን ወደ ዕውቀት ለመለወጥ የሚደረገው
ትንተና ወጥ መሆን ይኖርበታል። ያለበለዚያ መተማመን አይኖርም።
የትብብርን ጥቅም በተግባር ማሳየት አስፈላጊ መሆኑ፤ ትብብር በፍጥነት ግልጽ ጥቅም ካልሰጠ ጽንሰ ሃሳብ ሆኖ ይቀራል። ድርድር በባህሪው ረጅም ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ በተግባር የትብብር ጥቅም ካልታየ አሰልቺና ተስፋ አስቆራጭ ሊሆን ይችላል። ይህንንም እውን ለማድረግ የጋር ፕሮጀክቶችን እያዘጋጁ ለትግበራ ማዘጋጀቱ እንደ አንድ መፍትሄ ሊወሰድ ይችላል።
ለድርድር ሂደቱ ሴክሬታሪያት ማስፈለጉ፣ ድርድሩ ሲካሄድ የድርድር ሂደቱን ለማስተባበር፣ ቦታዎችን ለማዘጋጀት፣ የተደራዳሪዎችን ጉዞ ለማስተካከል፣ ቃለ ጉባዔ ለመያዝና ሰነዶችን ለማስተዳደር ሴክሬታሪያት አስፈላጊ ሆኗል።
ከላይ የተዘረዘሩትን ችግሮች ለመቅረፍ ሲባልም የናይል የትብብር ማዕቀፍ (Nile Basin Ini- tiative, NBI) እንዲመሰረት የተፋሰሱ አገራት በፌብሩዋሪ 22/1999 ዳሬሰላም ታንዛንያ ላይ ከስምምነት ደርሰዋል። የናይል የትብብር መድረክ ቅድሚያ ትኩረት የሰጣቸው ጉዳዮችም በአገራቱ መካከል የጠነከረ ትብብር እንዲኖር መተማመንን ማጎልበት፣ የተለያዩ ሥልጠናዎችንና ድጋፎችን በመስጠት የአቅም ልዩነትን ማጥበብ፣ የየአገራቱ የውኃ ፖሊሲዎች እርስ በእርሳቸው እንዲናበቡ ማድረግ፣ የመረጃ አሰባሰብ፣ አተናተን እና የውሳኔ መስጫ ዘዴዎች ወጥ እንዲሆኑ ማገዝ፣ የጋራ የትብብር ፕሮጀክቶችን በማዘጋጀት አገራቱ እንዲተገብሩና የትብብርን ጥቅም በተግባር እንዲረዱ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንዲሁም ለድርድር ሂደቱ የሴክሬታሪያት አገልግሎት
መስጠት ናቸው።
በናይል ወንዝ ላይ የሚካሄዱት የድርድር እና የትብብር ሥራዎች እርስ በእርሳቸው ተመጋጋቢ ቢሆኑም በተለያየ የትይዩ ጎዳና (parallel track) ላይ እንዲጓዙ ታቅዷል። ድርድሩ በአገራቱ መካከል የሚካሄድ ሲሆን ትብብሩን የሚመራው የናይል የትብብር መድረክ ነው። የናይል የትብብር መድረክ በድርድሩ ላይ የሴክሬታሪያት አገልግሎት ከመስጠት ውጪ ሌላ ሚና አልነበረውም። እነዚህ ሁለት የትብብር ጎዳናዎች በትይዩ አቅጣጫ አንዱ ሌላኛውን ሳያቋርጥ እንዲጓዝ የተፈለገው ምናልባትም አንደኛው የትብብር ጎዳና (በተለይም የድርድር ሂደቱ) እንቅፋት ቢገጥመው ትብብሩ ሙሉ በሙሉ ሳይቋረጥ በቀሪው መስመር ላይ እንዲቀጥልና እንቅፋት የገጠመውን መንገድ በሂደት ለማስቀጠል ሲባል ነው። ትይዩ የትብብር መንገዶች ድርድሩ አልቆ፣ ስምምነቱ ጸድቆ ተግባራዊ ሲደረግ በስምምነቱ አማካኝነት የሚቋቋመውን ተቋም ለመመስረት እንደሚገናኙ ተገምቶ ነበር።
የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን ለማዘጋጀት የተደረገው ድርድርና ስምምነቱን የመፈረምና የማጽደቅ ሂደቶች ከናይል የትብብር መድረክ ሂደት ጋር ለረጅም ዓመታት በትይዩ የተጓዙ በመሆናቸው የታለፈባቸውን ውስብስብ ደረጃዎች መረዳት እንዲቻል ሁለቱንም ሂደቶች በተመሳሳይ የጊዜ ምዕራፎች ከፋፍሎ ማየቱ የተሻለ ይሆናል። በእነዚህ አራት ምዕራፎች ስር ሁለቱ ትይዩ ሂደቶች ያከናወኗቸው ዋና ዋና ተግባራትና የደርሱባቸው ደረጃዎች ይተነተናሉ።
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
ምዕራፍ አንድ - ከጅማሮ እስከ 2005
የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ድርድር (Negotiation for Cooperative Framework Agreement)
የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ድርድር ላይ ሁሉም የናይል ተፋሰስ አገራት በፈቃደኝነት የተሳተፉ ሲሆን ኤርትራ በራሷ ፍላጎት በታዛቢነት ለመቆየት ወስናለች። ደቡብ ሱዳን ድርድሩ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ነጻ አገር ስላልነበረች እንደ አንድ ሱዳን ነው የተደራደረችው። በ1995 አሩሻ ታንዛኒያ ላይ የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ድርድርን ለመጀመር ከስምምነት ሲደረስ የድርድር ሰነድ የሚያዘጋጅ የኤክስፐርቶች ፓናል
(Panel of Experts) እንዲቋቋም ተወስኖ ነበር። በዚሁ መሰረት ከየአገራቱ ሦስት ሦስት አባላት ያሉበት የኤክስፐርቶች ፓናል በ1996 ተመሰረተ። የኤክስፐርቶቹ ፓናል እ.አ.አ ጃንዋሪ 1997 ሥራውን ጀመረ። የፓናሉ ዋና ዓላማ የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ረቂቅ ሰነድ ማዘጋጀት ነው። የኤክስፐርቶች ፓናሉ በተዘጋጀው ረቂቅ ላይ ድርድር አድርጎ ልዩነቶችን ካጠበበ በኋላ ከልዩነት ነጥቦች ጋር የተሻሻለ ረቂቅ ካርቱም ሱዳን ላይ እ.አ.አ ኦገስት 2000 ለተደረገው የሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅርቧል።
የኤስፐርቶች ፓናል ያቀረበው ረቂቅ ሰንድ ውስጥ ስምምነት ያልተደረሰባቸው በርካታ ጉዳዮች
መኖራቸውን፣ የተሻሻለ የስምምነት ሰንድ እንዲዘጋጅ ያለውን ፍላጎት ትኩረት ውስጥ በማስገባት እ.አ.አ ከ2001–2002 ተጨማሪ ሥራዎችን በመሥራት የተጠናቀቀ ሰነድ የሚያቀርብ ከየአገሩ ሁለት ሁለት አባላት ያሉበት የሽግግር ጊዜ ኮሚቴ (Transitional Committee) ተቋቋመ። የሽግግር ኮሚቴው ተልዕኮም ወደ ስምምነት ለመድረስ አስቸጋሪ ለሆኑ ጉዳዮች መፍትሔ መስጠትና የትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱን ሰነድ በተሻለ መልኩ ማደራጀት ነው። ኮሚቴውም የትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱን የመጀመሪያ ደረጃ ረቂቅ እ.አ.አ በኦገስት 2001 አዘጋጅቷል። ይህ ሰነድ የድርድር ኮሚቴውን በዋና ዋና የልዩነት ነጥብ ላይ ወደ አንድ አቅጣጫ ለማምጣትና ሰንዱንም የተሟላ ቅርጽ ለመስጠት ነው።
በቀጣይ ሥራውን የተረከበው በ2003 የተቋቋመው የድርድር ኮሚቴ (Negotiation Commit- tee) ነው። የድርድር ኮሚቴው የሽግግር ኮሚቴ ያዘጋጀውና የቴክኒክ አማካሪ (Technical Ad- visory Committee) ኮሚቴ መለስተኛ ማሻሻያ ያከለበትን ሰነድ በመረከብና አስቸጋሪ ድርድሮችን በማካሄድ ብሎም በልዩነት በተያዙ ጉዳዮች ላይ እልባት በመፈለግ እ.አ.አ ዲሴምበር 2005 ሪፖርቱን አቅርቧል። በማርች 2005 አዲስ አባባ ላይ የተሰበሰበው የናይል ተፋሰስ የሚኒስትሮች ምክር ቤት መፍትሄ ባልተገኘባቸው ጉዳዮች ላይ የስምምነት ውሳኔ ሳይሰጥ ተለያይቷል።
ድርድሩ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ልዩነት የተመዘገበ ቢሆንም አብዛኛዎቹ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት መድረስ ተችሏል። እስከ መጨረሻው ስምምነት ያልተደረሰበት የነባር
ስምምነቶችን ዕጣ ፋንታ በተመለከተ የተቀመጠው አንቀጽ ነው። ነባር ስምምነቶችን በተመለከት የላይኛው ተፋሰስ አገራት ስምምነቶች ከትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ጋር እስካልተጣጣሙ ድረስ ውድቅና ጠፊ እንዲደረጉ የሞገቱ ሲሆን የታችኛው ተፋሰስ አገራት በበኩላቸው የማዕቀፍ ስምምነቱ ነባር ስምምነቶችን ማክበር እንዳለበት አስከ መጨረሻው ተከራክረዋል። ይህ ደግሞ የቅኝ ግዛት ስምምነትን እውቅና ሰጥቶ እንደመቀበል ስለሚቆጠር ልዩነቱን ማጥበብ አልተቻለም። ይህንን የተደራዳሪ ኮሚቴው ሊፈታው ያልቻለውን ጉዳይ እንዲፈቱት ለሚኒስትሮች ተላልፏል።
የናይል የትብብር መድረክ (Nile Basin Ini- tiative)
የናይል የትብብር መድረክ በናይል ተፋሰስ ውስጥ የውኃ ሀብቱን በትብብር በማልማት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ለመጋራት እንዲሁም ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን በማለም በናይል ተፋሰስ አገራት የተቋቋመ ብቸኛና ሁሉን አቀፍ መድረክ ነው። አገራቱ በውይይት ያስቀመጡት የጋራ ራዕያቸውም በናይል ተፋሰስ ውስጥ ፍትሃዊና ምክንያታዊ የውኃ አጠቃቀም በማስፈንና ተጠቃሚ በመሆን ዘላቂ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማረጋገጥ የሚል ነው። የናይል ተፋሰስ የትብብር መድረክ የሽግግር ጊዜ ተቋም ነው። መድረኩ በሥራ ላይ የሚቆየው የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ተጠናቆ እስከሚጸድቅና ቋሚ የተፋሰስ ኮሚሽን እስከሚቋቋም ድረስ ብቻ ነው።
የናይል ተፋሰስ የፓሊሲ ማዕቀፍ የመድረኩን አደረጃጀት የወሰነ ሰነድ ነው። መድረኩም በሁለት
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
ፕሮግራሞች የተከፈለ ስትራቴጂያዊ የድርጊት መርሃ ግብር ያዘጋጀ ሲሆን የመጀመሪያው የጋራ ራዕይ ፕሮግራም (Share Vission Program, SVP) ሲሆን በሁሉም አገራት ውስጥ ተፋሰሱን አካሎ የተተገበረ ፕሮግራም ነው። ሁለተኛው የንዑስ ተፋሰስ የድርጊት መርሃ ግብር (Sub- sidiary Action Program, SAP) የሚባል ሲሆን በልማት ዕድልና ተግዳሮቶች ተመሳሳይነት ያላቸውን አገራትን በቡድን በማድረግ ተፋሰሱን ሁለት ቦታ በመክፈል የተዘጋጀ ነው። እነዚህ ሁለት የድርጊት መርሃ ግብሮች የምስራቅ ናይል የድርጊት መርሃ ግብር (Eastern Nile Subsidiary Action Program, ENSAP) እና የናይል ታላላቅ ሐይቆች የድርጊት መርሃ ግብር (Nile Equatorial Lakes Subsidiary Action Program, NELSAP) ተብለው ተለይተዋል። የምስራቅ ናይል የድርጊት መርሃ ግብር ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን ያቋቋሙት ሲሆን ደቡብ ሱዳን በ2013 ተቀላቅላለች። የናይል ታላላቅ ሐይቆች አካባቢ የድርጊት መርሃ ግብር ሁሉንም የተፋሰሱን አገራት ያካተተ ነው።
የናይል የትብብር መድረክ ሦስት ማዕከላት ያለሁት ሲሆን አንደኛው መቀመጫውን ኢንቴቤ ኡጋንዳ ላይ ያደረገና በተፋሰሱ ውስጥ ትብብርን የማመቻቸትና የውኃ ሀብት አስተዳደርን የማጠናከር ኃላፊነት የተሰጠው የናይል ተፋሰስ መድረክ ሴክሬታሪያት (NBI Secretariate) ነው። መቀመጫው አዲስ አበባ የሆነው ሁለተኛው ማዕከል የምስራቅ ናይል የቴክኒክ አህጉራዊ ጽ/ቤት (ENTRO) ሲሆን፤ ሶስተኛውና መቀመጫውን ኪጋሊ-ሩዋንዳ ያደረገው የናይል ታላላቅ ሐይቆች አካባቢ የድርጊት መርሃ ግብር ማስተባበሪያ ዩኒት (NELSAP-CU) ናቸው። በመጨረሻ የተጠቀሱት
ሁለት ማዕከላት ትብብርን ከማመቻቸትና የውኃ ሀብት አስተዳደሩን ከማጠናከር በተጨማሪ በሚሸፍኑት የተፋሰሱ አከባቢ ድንበር ተሻጋሪ የትብብር ፕሮጀክቶችን የማዘጋጀትና አተገባበራቸውን የማቀናጀት ኃላፊነት አላቸው።
ሶስቱም የናይል ተፋሰስ የትብብር መድረክ ማዕከላት የየራሳቸው የውሳኔ ሰጪ እና የቴክኒክ አማካሪ ቡድን አላቸው። መቀመጫውን ኢንቴቤ ላደረገው የናይል የትብብር መድረክ ሴክሬታሪያት የናይል የሚኒስትሮች ም/ቤት (Nile COM) እንደ ዋና ውሳኔ ሰጪ አካልና የናይል የቴክኒክ አማካሪ ኮሚቴ (Nile TAC) እንደ አማካሪ ቡድን ተደራጅቶለታል። አዲስ አበባ ላይ ለተቋቋመው የምስራቅ ናይል የቴክኒክ አህጉራዊ ጽ/ቤት በውሳኔ ሰጪነት የሶስቱ አገራት ሚኒስትሮች በአባልነት የሚሳተፉበት የምስራቅ ናይል የሚኒስትሮች ም/ ቤት (ENCOM) የተደራጀ ሲሆን ሚኒስትሮቹን ለማማከርና ጽ/ቤቱን በቴክኒክ ለመርዳት የምስራቅ ናይል የድርጊት መርሃ ግብር የቴክኒክ ቡድን (ENSAPT) ተመስርቷል። በተመሳሳይ የናይል ታላላቅ ሐይቆች የድርጊት መርሃ ግብር ማስተባበሪያ ዩኒትን ለመምራት የመርሃ ግብሩ የሚኒስትሮች ምክር ቤት (NELCOM) እና የቴክኒክ ኮሚቴ (NELTAC) ተቋቁሟል።
በናይል ተፋሰስ የትብብር መድረክ ተፋሰሱን ሙሉ ባካለለ መልኩ የተተገበረው የጋራ ራዕይ ፕሮግራም ያተኮረው የናይል የትብብር ጉዞ አጀማመሩ ላይ የገጠመውንና ከላይ የተዘረዘሩ ተግዳሮቶችን መቅረፍ ላይ ነው። ፕሮግራሙ ሰባት ፕሮጀክቶችን የተገበረ ሲሆን እነሱም በተፋሰሱ ውስጥ ተንሰራፍቶ የነበረውን ያለመተማመን ለመቅረፍ የሚችሉ የመተማመን ማጎልበቻና
የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ የተመለከቱ፤ በወቅቱ ከፍተኛ የነበረውን በአባል አገራት መካከል የነበረ የአቅም ልዩነት ለማጥበብ የሚያስችሉ የአቅም ግንባታ ሥራዎች፣ የመረጃ አሰባሰብ፣ አተናተን እና የፖሊሲ ያለመጣጣምን ለማስተካከል የተዘጋጁ ፕሮጀክቶች ናቸው። እነኚህ በተለያዩ የተፋሰሱ አገራት ውስጥ የተተገበሩ የጋራ ራዕይ ፕሮጀክቶች የመድረኩን እውቅና ከፍ ከማድረጋቸውም በላይ በአባል አገራቱ ዘንድ የነበረውን የባለቤትነት ስሜትም አጎልብተዋል።
በንዑስ ተፋሰስ ደረጃ የተተገበረው የድርጊት መርሃ ግብር በማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ውጤት በማሳየት የጋራ ራዕይ ፕሮግራሞቹ ያስገኙትን ለውጥ ለማጉላት ችሏል። ከድርጊት መርሃ ግብሮቹ መካከል በተለይ በምስራቅ ናይል ፕሮጀክቶችን ለማዘጋጀትም ሆነ በየአገራቱ ወደ ትግበራ ለማስገባት ጊዜ አልፈጀም ነበር። ፕሮጀክቶቹ የመስኖ ልማትን፣ የኃይል ማመንጫና ንግድን፣ የኃይል ግንኙነትን፣ የተፋሰስ እንክብካቤ ፕሮጀክቶችን፣ የጎርፍ ትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራዎችን፣ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማትና በልማቱ ዙሪያ የሚያስፈልጉ የመረጃ አሰባሰብና አተናተን የሚያጎለብቱ ናቸው። በየዘርፉ የተዘጋጁት ፕሮጀክቶች ሁለት ወይንም ከዚያ በላይ አገራትን የሚነኩ በመሆናቸው ዋና ዓላማቸውም የመሰረተ ልማት ግንባታን በጋራ በማዘጋጀት በርካታ ጥቅሞችን ለተሳታፊ አገራት እንደሚያስገኝና ጉልህ ተጽዕኖ እንዳይደርስ ማድረግ እንደሚቻል በተግባር ለማሳየት ነው። ፕሮጀክቶቹን በመተግበር የሚገኘው ጥቅም ሲደጋገም ወይንም ትብብሩ ከፍ ያለና በርካታ ጥቅሞች ወደሚሰጥ የጋራ ልማት ፕሮጀክት ከተሸጋገረ የድንበር ተሻጋሪ
ውኃዎች ላይ የመተባበርን አስፈላጊነት በግልጽ እንደሚያሳይ ታምኖባቸዋል። አገራቱም የተናጠል እርምጃ ላይ ከማተኮር ወደጋራ ፕሮጀክቶች እንዲያዘነብሉ የታቀዱ ፕሮጀክቶች ነበሩ። በ2005 የምስራቅ ናይል የቴክኒክ አህጉራዊ ጽ/ ቤት አብዛኛዎቹን ፕሮጀክቶች አዘጋጅቶ ያጠናቀቀ ሲሆን አገራቱ ከራሳቸው ፋይናንስ፣ በዕርዳታ እና በብድር ብዙዎቹን ወደ ትግበራ አስገብተዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ በዚህ መልክ ከተተገበሩ ፕሮጀክቶች መካከል የኢትዮጵያ ሱዳን የኃይል ግንኙነት መስመርና የኃይል ንግድ፣ ጣና በለስ ንዑስ ተፋሰስ ውስጥ የተከናወኑ የተፋሰስ እንክብካቤ፣ የጎርፍ መከላከልና የውኃ ሀብት አስተዳደር ሥራዎች፣ ጣና ዙሪያ የለሙ የመስኖ እርሻዎች፣ በተለያዩ የኢትዮጵያ ተፋሰሶች የሚካሄዱ የጎርፍ ትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራዎችን መጥቀስ ይቻላል። በተጨማሪም የምስራቅ ናይል የኃይል ንግድ ፕሮጀክት ተጠንቶ በኢትዮጵያ፣ በግብጽ እና በሱዳን መካከል እስከ 3 ሺህ 200 ሜጋ ዋት ኃይል መነገድ አዋጭነቱ ስለተረጋገጠና አገራቱም ስለተስማሙ ይህንኑ ዓላማ ለማሳካት አንድ ከፍተኛ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን በቅድመ ዝርዝር ደረጃ ማስጠናቱ አስፈላጊ በመሆኑ ኤሌክትሪክ ዲ ፍራንስ የተሰኘን የፈረንሳይ ኩባንያ በጋራ በመቅጠር በወቅቱ የድንበር ግድብ የሚባለውንና በቅርቡ ግንባታው ተጠናቆ ለምረቃ የበቃውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስጠንተዋል።
ምዕራፍ ሁለት ከ 2005 – 2010
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ድርድር
እ.አ.አ ከ2005 ጀምሮ በናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ሂደት ውስጥ የተደራዳሪ ኮሚቴው ያልቋጫቸውን ጉዳዮች ለመቋጨት ድርድሩ በሚኒስትሮች ደረጃ መካሄድ ጀመረ። በተለይም በጣም አስቸጋሪ፣ እልህ አስጨራሽና ረዥም ጊዜ የፈጀው የቅኝ ግዛት ስምምነቶችን ዕጣ ፋንታ በመወሰኑ ጉዳይ ከስምምነት መድረስ አልተቻለም። የላይኛው ተፋሰስ አገራት የቅኝ ግዛት ስምምነቶች ከትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ጋር እስካልተጣጣሙ ድረስ ውድቅና ጠፊ መደረግ አለባቸው ሲሉ ግብጽና ሱዳን ግን የትብብር ስምምነቱ ነባር ስምምነቶችን ማክበር አለበት በማለት ዓይናቸውን በጨው አጥበው ተከራከሩ። ድርድሩ በዚህ ሁኔታ በዘጠኝ አገራት መካከል መሆኑ ቀርቶ በላይኛው እና በታችኛው ተፋሰስ አገራት መካከል ሆነ። የላይኛው ተፋሰስ አገራት ቡድን በኢትዮጵያ፤ የታችኛው ተፋሰስ አገራት ቡድን ደግሞ በግብጽ መመራት ጀመረ። በዚህም የተነሳ ድርድሩ ለተወሰነ ጊዜ የተቋረጠ ሲሆን በወቅቱ ድርድሩን ያመቻች የነበረው የዓለም ባንክ አንድ አወዛጋቢ ጽንሰ ሀሳብ ይዞ ብቅ አለ። ድርድር ሲቋረጥ አደራዳሪዎች አወዛጋቢ ሀሳብ ይዘው በመቅረብ ድርድሩን እንደገና ለማስጀመር የሚያደርጉት ጥረት የተለመደ አሠራር ነው። ይህ አደራዳሪዎች የሚያመጡት አወዛጋቢ ሀሳብ ገንቢ ማወዛገቢያ (Constructive Ambiguity) በመባል ይታወቃል። የዓለም ባንክ አደራዳሪው ያቀረቡት ጽንሰ ሀሳብም የውኃ ዋስትና የሚባል ሲሆን
በውኃ ህግ ከአሁን በፊት ያልተካተተና ያልተሞከረ በመሆኑ ህጋዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ ጽንሰ ሀሳብ ነው የሚል ትችት ይቀርብበታል።
በስምምነት ማዕቀፉም ውስጥ የውኃ ዋስትና የናይል ተፋሰስ አገራት ለጤና፣ ለግብርና፣ ለመተዳደሪያ፣ ለልማት እና ለአካባቢ ጥበቃ የሚያስፈልጋቸውን አስተማማኝ የውኃ አቅርቦትና ጥቅም ከናይል ወንዝ ሥርዓት የማግኘት መብት በማለት ተርጉመውታል። አገራቱ ከትንሽ ውጣ ውረድ በኋላ የውኃ ዋስትናን እንደ ጽንሰ ሀሳብ የተቀበሉት ሲሆን ይህም ከፍትሃዊና ምክንያታዊ የውኃ አጠቃቀም ጋር ተጣምሮ እንዲታይ ተስማምተዋል። ይሁን እንጂ ወደ ህጋዊ ማዕቀፉ ሲመጡ በላይኛውና በታችኛው ተፋሰስ አገራት መካከል ስምምነት መፍጠር አልተቻለም።
ይህ የውኃ ዋስትና ጽንሰ ሀሳብ በስምምነቱ አንቀጽ 14 ላይ የተቀመጠ ሲሆን ንዑስ አንቀጽ 14b ላይ ልዩነትን ማጥበብ አልተቻለም። የላይኛው ተፋሰስ አገራት አንቀጽ 14b “የናይል ተፋሰስ አገራት የሌላኛው የተፋሰስ አገር የውኃ ዋስትና ላይ ጉልህ ተጽዕኖ ላለማድረስ ተስማምተዋል” የሚል አቋም የያዙ ሲሆን በተቃራኒው የታችኛው ተፋሰስ አገር የሆኑት ግብጽና ሱዳን የናይል ተፋሰስ አገራት የሌላኛውን የተፋሰስ አገር የውኃ ዋስትና፣ የአሁን አጠቃቀምና መብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ላለማሳደር ተስማምተዋል የሚል እንዲሆን ሀሳብ አቅርበዋል።
በተጨማሪም ወደፊት የሚቋቋመው ኮሚሽን መቀመጫ የት ይሁን በሚለው ላይ ኢትዮጵያ አዲስ አበባ እንዲሆን በዕጩነት አቅርባ ነበር።
ዋናው መከራከሪያዋም ኢትዮጵያ ዋናው የናይል ውኃ መነሻ አገር መሆኗ፣ አዲስ አበባም በርካታ ዲፕሎማቶችና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚገኙባት በመሆኗ ለኮሚሽኑ ሥራ አመቺ ይሆናል በሚልና ኢትዮጵያ ከሁሉም የተፋሰሱ አገራት ጋር ያላት ርቀት አማካይ ስለሆነ የሚል ነበር። ሌላዋ በዕጩነት የቀረበችው የኡጋንዳዋ ከተማ ኢንቴቤ ነበረች። ሁሉም አገራት ኢንቴቤ እንዲሆን ፍላጎት በማሳየታቸውና በተለይ ግብጽ ይህንን የሀሳብ ልዩነት እንደ አጋጣሚ በመጠቀም በኢትዮጵያና ኡጋንዳ መካከል የእርስ በእርስ መጠራጠርን ለመፍጠር መሞከሯ ስለታወቀ ኢትዮጵያ በኮሚሽኑ ኢንተቤ መቀመጥ በመስማማት በአጸፋው የላይኛው ተፋሰስ አገራት ኢትዮጵያ በምትፈልጋቸው ሌሎች ጉዳዮች እንዲደግፏት አድርጋለች።
ሌላው በቀላሉ ስምምነት ያልተደረሰበት ጉዳይ የድርድሩ መሰረታዊ አሃድ ምን ይሁን የሚለው ነበር። ግብጽና ሱዳን የድርድሩ መሰረታዊ አሃድ ተፋሰስ እንዲሆን ሀሳብ ያቀረቡ ሲሆን ይህንን ኢትዮጵያ አልገዛችውም። ተፋሰስ ወንዝ ውስጥ የሚፈስ ውኃ ብቻ ሳይሆን መሬትን፣ ደንን፣ ከተማን፣ ዝናብን፣ የከርሰ ምድር ውኃን እና በተፋሰስ ውስጥ የሚገኘውን ሀብት በሙሉ ስለሚያካትት ይህንኑ በመግለጽ የላይኛው ተፋሰስ አገራትን ድጋፍ ካገኘች በኋላ የውኃ አጠቃቀምና ክፍፍልን በተመለከት የድርድር አሃድ የወንዝ ሥርዓት (ወንዝ ውስጥ ያሚፈሰው ውኃ እና ከወንዙ ጋር የተገናኘ የከርሰምድር ውኃ) እንዲሆን እንዲሁም ልማትን፣ እንክብካቤንና ጥበቃን በተመለከት ተፋሰስ እንዲሆን ከስምምነት ተደርሷል።
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
ግብጾች በፍጹም ላለመቀበል እስከመጨረሻው የሞገቱትና ከተስማሙ በኋላ ተጸጽተው ወደኋላ ሊመልሱት የሞከሩት ጉዳይ ደግሞ የታቀዱ ፕሮጀክቶችን ቀድሞ ማሳወቅ የሚለውን ድንጋጌ ነው። ይህ የታቀዱ ፕሮጀክቶችን ቀድሞ ማሳወቅ የሚለው ድንጋጌ እንዲሁ እንዳለ ስናየው ገራም ይመስላል። ዝርዝር ጉዳዮች ውስጥ ሲገባ ግን ወደ ይሁንታን መጠየቅ የሚጠጋ፣ የግብጽን መንግሥት ባህሪ ለሚያውቅ ደግሞ በፕሮጀክቶች ዕጣ ፋንታ ላይ ለግብጽ ድምጽን በድምጽ የመሻር ያክል መብት የሚሰጥ ስለሆነ እንዲሁም ድንጋጌው ግብጽ ፕሮጀክቱን በጸጥታ እንድትገድል ዕድል የሚሰጣት በመሆኑ በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት አላገኘም። ይህንንም ችግር በተደጋጋሚ በመወትወት ኢትዮጵያ የላይኛው ተፋሰስ አገራትን እምነት በማግኘቷ ይህ አንቀጽ የታቀዱ ፕሮጀክቶች ላይ በናይል ተፋሰስ ኮሚሽን አማካኝነት መረጃ መለዋወጥ በሚል እንዲተካ ተደርጓል።
በሰኔ 2007 የናይል ተፋሰስ የሚኒስትሮች ም/ ቤት በጣም አስቸጋሪና አሰልቺ ድርድሮችን ካካሄደ በኋላ በስምምነቱ ውስጥ በተካተቱት ሁሉም መሰረታዊ እና የአፈጸጸም አንቀጾች ላይ ከአንድ ንዑስ አንቀጽ ማለትም ንዑስ አንቅጽ 14b በስተቀር መስማማቱንና ድርድሩም በስኬት መቋጨቱን አበሰረ። ይህችንም ንዑስ አንቀጽ የአገራቱ መሪዎች እንዲፈቷት ተወስኖ ድርድሩ ላልተወሰነ ጊዜ ተቋረጠ።
በስተመጨረሻም የላይኛው ተፋሰስ አገራት ባደረጉት ጥረት በ2008 ድርድሩ እንደገና ተጀምሮ ግብጽና ሱዳን ስምምነቱን እንዲቀበሉ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት መደረግ ጀመረ። እ.አ.አ ግንቦት
2009 ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኪንሻሳ ላይ በተካሄደ የሚኒስትሮች ም/ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ሰባት የላይኛው ተፋሰስ አገራት ስምምነቱ ለፊርማ ክፍት እንዲደረግ ተስማሙ። ግብጽና ሱዳንንም አካቶ መፈረም እንዲቻል የላይኛውና የታችኛው የተፋሰስ አገራት ያልተስማሙበት ንዑስ አንቀጽ 14b ከስምምነቱ ውጪ እንዲደረግና ኮሚሽኑ ከተቋቋመ በኋላ ለድርድር ለመክፈትና በስድስት ወር ውስጥ እልባት ለመስጠት ወሰኑ።
ግብጽና ሱዳንን የማግባባቱ ሁኔታ ተጠናክሮ በቀጠለበት ወቅት ግብጽ ዋናዋ ተደራዳሪዋን የውኃ ሀብትና መስኖ ሚኒስትር ዶ/ር ማህሙድ አቡዘይድን ከኃላፊነታቸው በማንሳት በእርሳቸው ቦታ የካይሮ ዩኒቨርሲት መምህር የሆኑትን ዶ/ር ነስር አላምን ተካች። አዲሱ የግብጽ ሚኒስትርም ሥራቸውን እንደጀመሩ በርካታ ስምምነት የተደረሰባቸው የትብብር ማዕቀፉ አንቀጾች እንደገና ለድርድር እንዲቀርቡ ጥያቄ አቀረቡ። ይህ ጥያቄያቸው በአንድ አንቀጽ ላይ ስምምነት ከተደረሰ ስምምነቱ ተፈጻሚ እስከሚሆን ድረስ እንደገና ለድርድር ክፍት አይደረግም የሚለውን የተደራዳሪ ኮሚቴ መተዳደሪያ ደንብ ስለሚቃረን ተቀባይነት አላገኘም። በዚህ ደረጃ የላይኛው ተፋሰስ አገራት ግብጽና ሱዳንን ለማሳመን የታለመ ምንም አይነት ተጨማሪ ሥራ ቢሰሩም ምንም ውጤት እንደማያመጡ አመኑ።
የትብብር ስምምነቱ ሰነድ በተደጋጋሚ በተደረጉ የናይል ተፋሰስ የሚኒስትሮች ም/ቤት፣ የተደራዳሪ ኮሚቴ እና የናይል ቴክኒክ አማካሪ ኮሚቴ ስብሰባቸው እንዲጠራ ተደርጎ ተዘጋጀ። በኤፕሪል 2010 ግብጽ ሻርም አል ሼክ በተካሄደው አስቸኳይ
የሚኒስትሮች ም/ቤት ስብሰባ ላይ ስምምነቱ እ.አ.አ ከሜይ 14 ቀን 2010 ጀምሮ ለአንድ ዓመት በሚቆይ ለፊርማ ክፍት እንዲደረግ ተወሰነ።
የናይል ተፋሰስ የትብብር መድረክ
በምስራቅ ናይል የድርጊት መርሃ ግብር ስር ዝግጅታቸው ሲከናወን የነበሩት የጋራ ፕሮጀክቶች በ2005 በአብዛኛው ተጠናቀው ወደ ትግበራ ገብተዋል። ይህንን የተረዳው የምስራቅ ናይል የሚኒስትሮች ም/ቤት እስከ አሁን የተከተሉትን አቅጣጫ በመቀየር የወደፊት ፕሮጀክቶች ግዙፍ ዘርፈ ብዙ የጋራ ፕሮጀክቶች እንዲሆኑ ተስማሙ። በዚህ ስምምነት መነሻ የጋራ ዘርፈ ብዙ ፕሮጀክት (Joint Multipurpose Project, JMP) እንዲቀረጽ ተወሰነ። የጋራ ዘርፈ ብዙ ፕሮጀክት በምስራቅ ናይል ንዑስ ተፋሰስ ውስጥ ዘላቂ የውኃ ልማትና አስተዳደርን ለማመቻቸት የተቀናጁ ኢንቨስትመንቶችና የማስቻያ ሁኔታዎችን በማጠቃለል ሰፋፊ ልማቶችንና የልማት ትሩፋቶችን ለአገራት የሚያዳርስ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው።
የምስራቅ ናይል አህጉራዊ ጽ/ቤት እስከ 2008 ድረስ በአገራቱ መካከል በፕሮጀክቱ ላይ ለመነጋገር የሚረዱ በርካታ ዝርዝር ጥናቶችን አካሂዷል። የጋራ ዘርፈ ብዙ ፕሮጀክት ለመጀመር የሚያስችሉ ሁኔታዎችም ተሟልተዋል። የምስራቅ ናይል የቴክኒክ አህጉራዊ ጽ/ቤትም የፕሮጀክት ጅማሮ ምዕራፍ በመክፈት የመጀመሪያ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ለመለየትና ለማዘጋጀት እንቅስቃሴ ጀመረ። የዘርፈ ብዙ ፕሮጀክቱም የኃይል ማመንጫን፣ የመስኖ ልማትን፣ የጎርፍ መከላከልንና የተፋሰስ እንክብካቤን በማቀናጀት የያዘ ግዙፍ ግድብ ታቀደ። ለፕሮጀክት መረጣ
የተቀመጡት ሦስት መመዘኛዎችም ሦስቱንም አገራት መጥቀም፣ ዘርፈ ብዙ መሆን እና በማንም አገር ላይ ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ የሚሉ ናቸው። ሦስቱን አገራት የሚጠቅም ፕሮጀክት በተፈጥሮ መመረጥ ያለበት ከኢትዮጵያ ብቻ መሆኑን አገራቱ ተገንዝበዋል።
የዝግጅት ጥናቶቹን መሰረት በማድረግ በመጀመሪያ ደረጃ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቱ ከየትኛው የምስራቅ ናይል ንዑስ ተፋሰስ ውስጥ ቢመረጥ ይሻላል የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ሦስቱ ንዑስ ተፋሰሶች ማለትም ተከዜ፣ ዓባይ እና ባሮ አኮቦ ተወዳድረው ዓባይ ተፋሰስ ተመረጠ። ዓባይ ተፋሰስ ውስጥ ከሚገኙ ግዙፍ ግድቦች ውስጥ ኢትዮጵያ በኖርዌይ መንግሥት ዕርዳታ ዝርዝር ጥናት ለማስጠናት አዘጋጅታቸው የነበሩ ሦስት ፕሮጀክቶችን በጋራ በትብብር ለማዘጋጀት በዕጩነት አቀረበች። ቤኮ አቦ፣ ማንዳያ እና የድንበር ግድቦች ይባላሉ።
ሦስቱ አገራት በጋራ አማካሪ ድርጅት በመቅጠር በ2010 የመጀመሪያውን የጋራ ዘርፈ ብዙ ፕሮጀክት ለማዘጋጀት እንቅስቃሴ ጀመሩ። ፕሮጀክቱም በጋራ ተለይቶ፣ በጋራ ተዘጋጅቶ፣ በጋራ ከለማ በአገራቱ መካከል ያለውን ትብብር ወደ ከፍተኛ ደረጃ ያሳድጋል። ዜጎችም ከትብብር የሚገኘውን ከፍተኛ ጥቅም በማጣጣም የተሻሉ የጋራ የትብብር ፕሮጀክቶች ወደ ሥርዓቱ እንዲገቡ ጫና ይፈጥራሉ ተብሎ ተጠብቋል። ይህም ፕሮጀከት በምስራቅ ናይል ውስጥ በኢትዮጵያ፣ በግብጽ እና በሱዳን መካከል ዘላቂ ትብብርን፣ ግልጽ አሠራርንና መተሳሰርን እንደሚፈጥር ከፍተኛ ተስፋ ተጥሎበታል።
ምዕራፍ ሦስት ከ 2010 – 2013
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት
እ.አ.አ ሜይ 14 ቀን 2010 የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ኡጋንዳ ኢንተቤ ላይ ለፊርማ ክፍት ተደረገ። ኢትዮጵያም በዚሁ የመጀመሪያ ዕለት ፊርማዋን በማኖር በድርድሩ ወቅት የላይኛው ተፋሰስ አገራትን እንደመራች ሁሉ ፊርማውንም መራች። ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ እና ታንዛኒያም በዚሁ ዕለት ስምምነቱን በመፈረም በናይል ተፋሰስ የትብብር ሂደት ውስጥ ፍትሃዊና ምክንያታዊ የውኃ አጠቃቀም ለማስፈን የተደረገው ረዥም እና ትዕግስት አስጨራሽ ጉዞ ውስጥ የወሳኝ ምዕራፍ አካል መሆናቸውን አረጋገጡ። በአምስተኛው ቀን ማለትም ሜይ 19 ቀን 2010 ኬንያ ስምምነቱን በፊርማዋ በማድመቅ አምሥተኛ አገር ሆነች። የላይኛው ተፋሰስ አገራት ስምምነቱን ወደማጽደቅ ሂደት ለማሸጋገር የሚያስፈልገውን ስድስት ፊርማ ለማግኘት የተለያዩ የዲፕሎማሲ ሥራዎች መከናወን ጀመሩ።
ግብጽና ሱዳን ስምምነቱ ያልተጠናቀቀ፣ ሁለንተናዊ ስምምነት ያልተቸረው እንዲሁም ህገወጥ ነው ብለው አጣጣሉት። ሙሉ በሙሉም ስምምነቱን እንደማይቀበሉ በማሳወቅ ውድቅ አደረጉት። ስምምነቱ በተፈረመ ማግስት ግብጾች የማዳከም ሥራቸውን በይፋ ጀምረዋል። ይህንንም ያደረጉት ኬንያ ስምምነቱን ከመፈረሟ ቀድመው እንዳትፈርም ጥረት በማድረግ ነበር። ለዚህም የኬንያ የወቅቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ እና የውኃ ሚኒስትሯን ወደ አገራቸው በመጋበዝና በማግባባት ኬንያ የስምምነቱን
ፈራሚዎች እንዳትቀላቀል ለማድረግ ሞክረዋል። ይህንንም ሴራ በአግባቡ የተረዳው የኬንያ ልዑክ ወደ ካይሮ ከማቅናቱ በፊት ስምምነቱን ፈርሟል። በተመሳሳይ ጊዜ ሌላኛዋ ያልፈረመችው አገር የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ፕሬዚደንት ጆሴፍ ካቢላም ወደ ካይሮ ተጋብዘው ነበር። ሁለቱንም መሪዎች ያናገሩት ፕሬዚደንት ሆስኒ ሙባረክ የናይል ውኃን በተመለከተ የግብጽን አቋም አበክረው አስገንዝበዋል።
በመቀጠልም ግብጽ ስምምነቱን ያልፈረሙ አገራት እንዳይፈርሙ፣ የፈረሙ አገራት ስምምነቱን እንዳያጸድቁ ከፍተኛ ሩጫ ማድረግ ጀመረች። የተፋሰሱን አገራት የተለያዩ ፓኬጆች በመያዝ ለማነሁለል ሞከረች። ይህም ዘመቻ በተቀናጀ መልኩ በአገሪቷ ርዕሰ ብሔር፣ በጠቅላይ ሚኒስትራቸው፣ በውጭ ጉዳይ እና በውኃ ሚኒስትሮችና በሌሎች ዲፕሎማቶች አማካኝነት ይፈጸም ነበር። ግብጽ ስምምነቱን ለማክሰምና የናይል የትብብር መድረክን ለማዳከም በየዓመቱ እስከ 10 ሚሊዮን ዶላር እንደምትመድብ ይታማል። የግብጽ ልዑክ ለዚህ ዓላማ ያልጎበኘው አገር ቢኖር ኢትዮጵያ ብቻ ነች።
እ.አ.አ ፌብሩዋሪ 2011 ቡሩንዲ የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን በመፈረም ስድስተኛ አገር ሆነች። ቡሩንዲ የትብብር ማዕቀፉን ስምምነት የፈረመችው የፊርማ መርሃ ግብር የሚዘጋበት ሜይ 13 2011 ሊደርስ ሦስት ወራት ብቻ ሲቀሩት ነው። በአንድ በኩል ግብጾች ቡሩንዲ ስምምነቱን እንዳትፈርም በየቀኑ በሯን ሲያንኳኩ
በሌላ በኩል የላይኛው ተፋሰስ አገራት በተለያዩ እርከኖች ባሉ መሪዎቻቸው እንድትፈርም የማበረታታት ሥራ ሠርተዋል። የቡሩንዲ ስምምነቱን ስድስተኛ አገር ሆኖ መፈረም ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ውጤት ሲሆን፤ አገራቱ ስምምነቱን የማጽደቅ ሂደት እንዲጀምሩ የሚያስችል ነው።
ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ስምምነቱን መቀበል ብቻ ሳይሆን እንዲፈረም ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች። ሰባቱ የላይኛው ተፋሰስ አገራት ስምምነቱን ለፊርማ ክፍት ለማድረግ ከውሳኔ
የደረሱት በ2009 በኮንጎ ኪንሻሳ በተካሄደው የሚኒስትሮች ም/ቤት ስብሰባ ላይ መሆኑ ይታወሳል። ይሁን እንጂ ኮንጎ ግብጽና ሱዳን ካልፈረሙ አልፈርምም የሚል አቋም ይዛለች። ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ የኮንጎ ወንዝ ባለቤት እንደመሆኗ ይህንን ግዙፍ ወንዝ ይዛ የናይል የውኃ ጭቅጭቅ አካል መሆን አልፈለገችም። ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ከኮንጎ ተነስተው ናይል የሚገቡ ወንዞች ሲሚሊክ እና አሳንጎ የሚባሉ ጅረቶች በመሆናቸው ለዚህች አነስተኛ ውኃ ብለው ፍጥጫ ውስጥ መግባትም እንዲሁ። ሶስተኛው ምክንያት
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
ደግሞ ኮንጎ ውስጥ የተሰማራው የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ጦር ከፍተኛ ቁጥር የያዙት ግብጻዊያን በመሆናቸው ለእነዚህ ትናንሽ ዥረቶች ብላ ከግብጽ ጋር መቃቃር አልፈለገችም።
እ.አ.አ ሰኔ 9 ቀን 2011 ደቡብ ሱዳን ሉዓላዊ አገር ሆና ብቅ አለች። በነሐሴ 2012 የናይል ተፋሰስ የትብብር መድረክ አባል ስትሆን የቅኝ ግዛት ስምምነቶችን ውድቅ ማድረጓንና የትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱን እንደምትደግፍ አሳወቀች። ይህም ደቡብ ሱዳን በዋናነት ከጥቅሟ እና መሰረታዊ ፍላጎቶቿ አኳያ ከላይኛው ተፋሰስ አገራት ጎን መቆሟን ያሳያል።
እ.አ.አ በ2011 ኢትዮጵያ የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን የማፅደቁን ሂደት እንድትመራ በተጠየቀችው መሰረት አስፈላጊውን ሰንድ አዘጋጅታ ወደ ሚኒስትሮች ም/ቤት ላከች። ይሁን እንጂ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ስጋት ላይ እንደጣላቸው ያሳወቁት ግብጽና እና ሱዳን ለስጋት መቅረፊያ ተብሎ የግድቡን መረጃ ኢትዮጵያ ለመስጠት ቃል መግብቷን ተከትሎ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱንም የማጽደቅ እንቅስቃሴ እንድታዘገይ ስለጠየቁ ሂደቱ እንዲዘገይ ሆነ።
የናይል ተፋሰስ የትብብር መድረክ
የምስራቅ ናይል ንዑስ ተፋሰስ የድርጊት መርሃ ግብር አካል የሆነውን ሁሉን አቀፍ የጋራ ፕሮጀክት እውን ለማድረግ ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን በጋራ አማካሪ ቀጥረው የመጀመሪያውን ፕሮጀክት የማዘጋጀት ሥራ ጀምረዋል። ቀድመው የተዘጋጁ ፕሮጀክቶች ትግበራ በመጠናቀቅ ላይ መገኘቱ በመዘጋጀት ላይ ላለው ግዙፍ ዘርፈ ብዙ ፕሮጀክት
ወደ ትግበራ መለወጥ ዋስትና ሆኗል። የዚህ ፕሮጀክት በጋራ ወደ ልማት መግባት ባለመግባባት፣ ባለመተማመን እና በፍጥጫ የሚታወቀውን የምስራቅ ናይል የውኃ ፖለቲካ ወደ ከፍተኛ ትብብር ያሸጋግራል ተብሎ እምነት ተጥሎበታል። ለፕሮጀክቱ ትግበራ የሚያስፈልገውን ፋይናንስ የዓለም ባንክ እና ሌሎች የፋይናንስ ድርጅቶች እንደሚሸፍኑ ከወዲሁ አስታውቀዋል።
ይህ በእንዲህ እያለ እ.አ.አ ሜይ 2010 የላይኛው ተፋሰስ አገራት የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት መፈረማቸው ተሰማ። ግብጽና ሱዳን ስምምነቱን ህገወጥ፣ ያላለቀ እና ሁሉን አሳታፊ ያልሆነ በማለት ውድቅ ቢያደርጉትም። እ.አ.አ ጁን 2010 በአዲስ አበባ በተካሄደው የናይል ተፋሰስ የሚኒስትሮች ም/ቤት ስብሰባ ሱዳንና ግብጽ በናይል የትብብር መድረክ ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ ማቋረጣቸውን አሳወቁ። ይህ ውሳኔያቸው የናይል ተፋሰስ ትብብርን ዘላቂ ለማድረግ ሁለቱ የትብብር ተግባራት በትይዩ እንዲጓዙ እና አንደኛው የትብብር መስመር ቢቋረጥ በሌላኛው አብሮ ለመቀጠል ታስቦ የነበረውን ፅንሰ ሀሳብ ከሥራ ውጭ አደረገው። በምስራቅ ናይል ንዑስ ተፋሰስ ውስጥ ዘላቂ ትብብር እንደሚያመጣ የታመነበት የጋራ ዘርፈ ብዙ ፕሮጀክት ላይ ቀዝቃዛ ውኃ ተቸለሰበት። በተለይ ሦስት አገራዊ ፕሮጀክቷን በዝርዝር ጥናት ደረጃ ለማስጠናት እየተዘጋጀች የነበረችው ኢትዮጵያ የጋራ ዘርፈ ብዙ ፕሮጀክት ሀሳብ ሲነሳ ፕሮጀክቶቹን በጋራ ለማልማት ስትል የጀመረችውን ጥናት በማቋረጥ ከነፋይናንሱ በዕጩነት ካቀረበች በኋላ ፕሮጀክቱን መሀል መንገድ ላይ ጥለውት መሄዳቸው ተስፋ አስቆራጭ ተግባር ነበር።
በኢትዮጵያ፣ በግብጽ እና በሱዳን በጋራ የተቋቋመውንና መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገውን የምስራቅ ናይል የቴክኒክ አህጉራዊ ጽ/ቤት ኢትዮጵያ ብቻዋን ታቅፋ ቀረች። የናይል የትብብር መድረክ ለሥራው የሚያስፈልገውን ፋይናንስ የሚያገኘው ከአገራት መዋጮና ከልማት አጋሮች ከሚገኝ ድጋፍ ነበር። በተለይ የልማት አጋሮች ለፕሮግራም ማስፈጸሚያ በዓለም ባንክ አስተባባሪንት በከፈቱት ትረስት ፈንድ ከፍተኛ ድጋፍ ሲያደርጉ ቆይተዋል። የግብጽና ሱዳን ትብብሩን ለቆ መውጣት የሁለቱን አገራት አገራዊ መዋጮ ሙሉ በሙሉ ያስቀረ ሲሆን የልማት አጋሮችም የሚሰጡት ድጋፍ እንደሚቀንስ ግልጽ እየሆነ መጣ። በዚህ ረገድ ግብጽ የልማት አጋሮች ፕሮግራም ፋይናንስ ከማድረግ እንዲቆጠቡ ተከታታይ ጥሪ ማድረግ ጀመረች።
የምስራቅ ናይል የቴክኒክ አህጉራዊ ጽ/ቤት ውስጥ የሚሠሩ የሁለቱ አገራት ሠራተኞችም ቀስ በቀስ ሥራቸውን እየለቀቁ ወደ አገራቸው ተመለሱ። መሥሪያ ቤቱ የሚሠራቸው ሥራዎች በሙሉ በጋራ የሚሠሩ በመሆናቸው የሁለቱ አገራት ተሳትፎ እየቀነሰ በመምጣቱ ሥራው የጋራ ሳይሆን የአንድ አገር ወይንም የተቋሙ እየመሰለ መጣ። ጽ/ቤቱ ለሥራው የሚያስፈልገውን መረጃ የሚያገኘው ከአገራቱ በመሆኑ ከግብጽና ከሱዳን መረጃ ማግኘት አልቻለም። ይህ ደግሞ የጥናት ሥራዎች ውጤት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደር ጀመረ። የጥናት ውጤቶችም በጋራ መጽደቅ ሲገባቸው የሁለቱ አገራት ያለመሳተፍ የማጽደቁን ሥራ አስተጓጎለው።
እ.አ.አ ጁላይ 2012 ተሰብስቦ የነበረው የናይል
ተፋሰስ የሚኒስትሮች ም/ቤት የምስራቅ ናይል የሚኒስትሮች ም/ቤት የተፈጠረው ችግር እንዲፈታ ውሳኔ አስተላለፈ። በተጨማሪም የልማት አጋሮች የምስራቅ ናይል አገራት የተፈጠረውን ችግር እስከ ታህሳስ 2012 ድረስ ተሰብስበው ካልፈቱ የፕሮግራም ፋይናንስ እንደሚያቋርጡ አሳወቁ።
ኢትዮጵያ በወቅቱ የምስራቅ ናይል የሚኒስትሮች ም/ቤት ሰብሳቢ እንደመሆኗ እ.አ.አ ኖቬምበር 2012 የሁለቱን አገራት የቴክኒክ አማካሪዎችና የሚስትሮች ም/ቤት ስብሰባ በማካሄድ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ሀሳብ አቀረበች። ከብዙ ውጣ ወረድ በኋላ ሁለቱ አገራት የኢትዮጵያን ሀሳብ ተቀብለው ወደ አዲስ አበባ መጡ። ኢትዮጵያ በዚህ ስብሰባ ላይ በወሰደችው የሰከነና ስልታዊ እርምጃ ሱዳን ወደ ትብብር መድረኩ እንድትመለስ ስታደርግ፣ ደቡብ ሱዳን የምስራቅ ናይል የድርጊት መርሃ ግብርን እንድትቀላቀል ከውሳኔ እንዲደረስ አድርጋለች። በሌላ በኩል ግብጽ ወደ ትብብር የመመለሱን ስምምነት ብትቀበልም ሚኒስትሩ ካይሮ ከደረሱ በኋላ ውድቅ አደረጉት። ይህ ኢትዮጵያ የወሰደችው እርምጃ የምስራቅ ናይል የድርጊት መርሃ ግብርም ሆነ እሱን ለመተግበር የተቋቋመውን ጽ/ቤት ከመፍረስ አድኖታል። የሱዳን ወደ ትብብሩ መመለስና የደቡብ ሱዳን የምስራቅ ናይል ተፋሰስ ትብብርን መቀላቀል የትብብር ሂደቱን ማጠናከር ብቻ ሳይሆን የግብጽን ትብብሮቹን የማዳከም እርምጃም አለዝቦታል።
ምዕራፍ አራት ከ2013 - እስከ አሁን
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት
ኢትዮጵያ የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን የማጽደቅ ሂደቱን በግብጽ ጥያቄ መሰረት ለሁለት ዓመት ካዘገየች በኋላ እ.አ.አ ጁን 2013 ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አቅርባ አስጸደቀች። ይህ የኢትዮጵያ ስምምነቱን የማጽደቅ ተግባር ሌሎች አገራትም ስምምነቱን እንዲያጸድቁ ረድቷል። በዚሁ መሰረት በዚያው ዓመት ኦገስት ላይ ሩዋንዳ፣ ማርች 2015 ታንዛኒያ፣ ኦገስት 2019 ኡጋንዳ፣ ኦክቶበር 2013 ቡሩንዲ አጽድቀውታል። ስምምነቱ ተፈጻሚነት እንዲኖረው ስድስት አገራት አጽድቀው፤ ያጸደቁበትን ሰነድ አፍሪካ ኅብረት ማስቀመጥ ይጠበቅባቸዋል። ስድስተኛው የማጽደቂያ ሰነድ አፍሪካ ኅብረት በገባ በ60ኛው ቀን ስምምነቱን ባጸደቁት አገራት ዘንድ አስገዳጅ ይሆናል። ሁሉም አገራት ያጸደቁም፣ ያላጸደቁም እንዲሁም ያልተቀበሉ አካላት ዓይናቸውን ወደ ኬንያ አዙረው መጠበቅ ጀመሩ። ከስድስቱ ፈራሚዎች ያላጸደቀችው አገር ኬንያ ብቻ በመሆኗ። ይሁን እንጂ ያልተጠበቀው ተከሰተና ጁላይ
2024 ደቡብ ሱዳን ስምምነቱን በማጽደቅ ስድስተኛ አገር ሆነች። እንደሚታወቀው ደቡብ ሱዳን ስምምነቱን አልተደራደረችምም አልፈረመችምም። ደቡብ ሱዳን ያልተደራደረችው በወቅቱ ሉዓላዊ አገር ስላልነበረች ነው። የተደራደረችው እንደ አንድ ሱዳን ሆና ነው። ስምምነቱን ስላልፈረመችም በቀጥታ ማጽደቅ አትችልም። የምትችለው አክሴሽን የሚባል ሂደት በማለፍ ያጸደቁ አገራት ላይ መጨመር ስለነበረ ይንኑ ገቢራዊ አድርጋለች። የደቡብ ሱዳንን አጽዳቂ አገሮች ላይ መጨመር ተከትሎ የአፍሪካ ኅብረት በ60ኛው ቀን ማለትም ኦክቶበር 13 ቀን 2024 የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ተፈጻሚ መሆኑን አሳወቀ። ስምምነቱም ተፈጻሚ መሆን ከጀመረበት ዕለት ጀምሮ የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን ተቋቁሟል። ኮሚሽኑ ሥራውን በሙሉ አቅሙ ለመጀመር የተወሰኑ ቅድመ ሁኔታዎች መሟላት አለባቸው።
ኮሚሽኑ ስምምነቱን ባጸደቁ ስድስት አገራት ዘንድ ህጋዊ ሰውነት ማግኘት አለበት። እንዲሁም የኮሚሽኑ መቀመጫ ከሆነችው ከኡጋንዳ ጋር የዋና መሥሪያ ቤት መቀመጫ ስምምነት መፈጸም ይኖርበታል። የኮሚሽኑ ዝርዝር የአደረጃጀት ጥናት መካሄድ አለበት። አገራቱም ለኮሚሽኑ የሚሰጡትን ተግባርና ኃላፊነት በዝርዝር ማዘጋጀትና መስማማት ይኖርባቸዋል። ለኮሚሽኑ የሚያስፈልገው የሰው ኃይል፣ የፋይናንስ እና የቁሳቁስ ፍላጎት ተሰልቶ መሟላት እንዲሁም የረዥም ጊዜ ዕቅድ እና የአጭር ጊዜ መርሃ ግብር ላይም ከስምምነት መድረስ ያስፈልጋል። የስምምነቱ አንቀጽ 31 እንደደነገገው የናይል ትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ተግባራዊ ሲደረግ የተፋሰስ ኮሚሽኑ የናይል የትብብር መድረክን መብት፣ ግዴታና ሀብት ይወርሳል ይላል። የትብብር መድረኩን መብት፣ ግዴታና ሀብት ኮሚሽኑ እንዲወርስ ደግሞ መታለፍ ያለባቸው ህጋዊ ጉዳዮች አሉ። የናይል የትብብር መድረክን ያቋቋሙት አስር አገራት ሲሆኑ ስድስት አገራት ያቋቋሙት ኮሚሽን የተቋሙን መብት፣ ግዴታና ሀብት ለመውረሱ ቢቻል ቢቻል ሁለንተናዊ ስምምነት፤ ካልሆነም የተወሰኑ ህጋዊ ዘዴዎችን ተጠቅሞ ሊቃጡ የሚችሉ ተግዳሮቶችን ማለፍ ያስፈልጋል። ስድስቱ የስምምነቱ አጽዳቂ አገራት የናይል የትብብር መድረክን መብት፣ ግዴታና ሀብት ለናይል ተፋሰስ ኮሚሽን ለማውረስና ሽግግሩንም የተረጋጋ ለማድረግ የሽግግር ጊዜ እንደሚያስፈልግ ተስማምተዋል። ይህም የሽግግር ጊዜ ከአንድ ዓመት እስከ አንድ ዓመት ተኩል ሊፈጅ ይችላል። ለዚህም የሚረዳ ፍኖተ ካርታ አዘጋጅተው በማጽደቅ ወደ ሥራ ገብተዋል።
በትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱ እንደተደነገገው የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን ዋና ውሳኔ ሰጪ የርዕሰ ብሔርና ርዕሰ መንግሥት ኮንፈረንስ ነው። የኮሚሽኑ የፖሊሲና ሌሎች ስልታዊ ጉዳዮች ውሳኔ የሚሰጡት በናይል ተፋሰስ የሚኒስትሮች ም/ቤት ነው። እነኚህ ከላይ የተጠቀሱት አካላት በግልጽ የሚታወቁ በመሆናቸው ይህ የኮሚሽኑ ውሳኔ ሰጪ አካል ተቋቁሟል ብሎ መውሰድ ይቻላል። ለሚኒስትሮች ም/ቤት የማማከር አገልግሎት የሚሰጡና የሴክሬታሪያቱን ሥራ በቅርብ የሚከታተሉ የቴክኒክ አማካሪ ኮሚቴ እና የሴክተር አማካሪ ኮሚቴ ይኖረዋል። የኮሚሽኑንም የየዕለት ሥራ የሚተገብር፣ ብቃት ባላቸው ባለሙያዎች የሚመራ የናይል ተፋሰስ ሴክሬታሪያት ይኖራል። ኮሚሽኑ በዋናነት የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ለአገራቱ የሰጠውን መብት በአግባቡ እንዲጠቀሙና የጣለባቸውን ግዴታ በወቅቱ እንዲወጡ የመርዳት ኃላፊነት ይኖርበታል። በተጨማሪም ኮሚሽኑ በአገራቱ መካከል ያለውን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ የማሸጋገር፣ የተፋሰሱ የውኃ ሀብት ዘላቂና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ እንዲተዳደር፣ የውኃ ጥበቃ፣ ቁጥጥር እና እንክብካቤ በብቃት እንዲከናወን ያደርጋል። የተፋሰሱ አገራት የኢኮኖሚና የቴክኒክ አቅም ዝቅተኛ በመሆኑ ኮሚሽኑ አገራቱ ያላቸውን የፋይናንስ፣ የአደረጃጀትና የሰው ኃይል አቅም አቀናጅተው ፕሮጀክቶችን በጋራ እንዲያለሙና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያግዛል። የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ሲፈረም ያልተቋጨው የንዑስ አንቀጽ 14b ጉዳይም ኮሚሽኑ በሙሉ አቅሙ መንቀሳቀስ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በስድስት ወር ውስጥ እልባት እንዲያገኝ ያደርጋል። እንደ ፍትሃዊና
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
ምክንያታዊ የውኃ አጠቃቀም ያሉ ተጨማሪ ጥናት፣ ምርምርና ድርድር የሚያስፈልጉት አንቀጾች ላይ አገራቱን ያስተባብራል ያግዛል። በስምምነቱ ውስጥ የተካተቱና በአገራቱ መከበር ያለባቸውን ዓለም አቀፍ ህጎችና መልካም ተሞክሮዎች ያለመጣሳቸውንና መከበራቸውንም ያረጋግጣል። ጎን ለጎንም ስምምነቱን ፈርማ ያላጸደቀችው ኬንያ፤ ስምምነቱን ተቀብላ ያልፈረመችው ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ እንዲሁም ስምምነቱን ውድቅ ያደረጉት ግብጽና ሱዳን ሀሳባቸውን ቀይረው የስምምነቱ አካል እንዲሆኑ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ እና ደቡብ ሱዳን ያሉበት ኮሚቴ ተቋቁሞ እንቅስቃሴ ተጀምሯል። ኬንያ የስምምነቱ ፈራሚ እንደመሆኗ መጠንና መሰረታዊ ፍላጎቷም ከላይኛው ተፋሰስ አገራት ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ ስምምነቱን በቅርቡ ታጸድቃለች ተብሎ ይጠበቃል። ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፤ ግብጽና ሱዳን ካልፈረሙ በስተቀር የሚል ሽፋን የምታቀርብ ቢሆንም ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጥረት ከተደረገ የምትቀላቀልበት ዕድል በጣም ሰፊ ነው። ግብጽና ሱዳን በቅድሚያ ያጸደቁ አገራትን አጋርነት ለማዳከም፣ የናይል ተፋሰስ የትብብር
መድረክ ወደ ኮሚሽን እንዳይሸጋገርና ኮሚሽኑም እንዳይጠናከር በመሞከር ላይ ይገኛሉ። ይህ ካልተሳካ የሚቋቋመው ኮሚሽን ደካማና ውጤት የማያመጣ እንዲሆን ይተበትቡታል፤ በተለያየ የተሳትፎ ሥርዓት ውስጥ በመግባት ከውስጥ ለመቦርቦር ይሞክራሉ። ይሁን እንጂ የሚደራጀው ኮሚሽን ጠንካራና ወሳኝ፣ ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን ከተቸረው ግብጽና ሱዳን በናይል ውኃ ላይ ቁልፍ፣ ቁልፍ ውሳኔዎች ከሚሰጥበት መድረክ መጥፋት ስለማይችሉ ወደ ትብብር መመለሳቸው አይቀርም። ዋናው ጥያቄ መቼ እና በምን አይነት ሁኔታ የሚል ይሆናል። በአንድ ተፋሰስ ውስጥ ተፈጻሚ የተደረገ ህጋዊ ስምምነትን ሁሉም የተፋሰሱ አገራት ላይቀበሉት ይችላሉ። የስምምነቱ አካል ያልሆኑ አገራትን በተለያየ ሁኔታ እንዲሳተፉና አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ማድረጉ የተለመደ አሰራር ነው። እነዚህን አገራት ማሳተፉ ወደ ትብብሩ እንዲገቡ የማበረታታት፣ ትብብሩ ላይ ሊያደርሱ የሚችሉትን ተጽዕኖ የመቀነስና ኮሚሽኑ የሚሠራቸው ሥራዎች ግልጽና አካታች እንዲሆኑ ያግዛል። በናይል ተፋሰስም የስምምነቱ አካል ያልሆኑ
አገራት የተሳትፎ ጥያቄ ማንሳታቸው አይቀርም። ይህንን ጥያቄ አገራቱ በጥንቃቄ ሊያጤኑት ይገባል። ጥያቄው ለትብብርና መልካም አስተዋጽኦ ለማበርከት ከሆነ ሊስተናገድ ይችላል። ከውስጥ ለማዳከም ከሆነ ግን የተለየ እይታ ያስፈልጋል።
ኬንያ ስምምነቱን ካላጸደቀች የትብብሩ አጋር (Dialogue Partner) ተደርጋ ሁሉንም መረጃ እንድታገኝ፣ ፕሮጀክትና ጥናት በጋራ እንድትተገብር፣ ስብሰባዎች ላይ የመሳተፍና የፋይናንስ አስተዋፅኦ የማድረግ ዕድል ሊሰጣት ይችላል። ኮንጎ ዴሞክራትክ ሪፖብሊክ ስምምነቱን የተቀበለች በመሆኑና ወደ ትብብር ለመመለስ ትንሽ ድጋፍ ስለሚያስፈልጋት የሙሉ ታዛቢነት (Observer Status) ደረጃ ሊሰጣትና በሁሉም ስብሰባዎች ላይ የመሳተፍና አግባብነት ያላቸው መረጃዎችን የማግኘት ዕድል ሊሰጣት ይችላል። በሌላ በኩል ሱዳንና ግብጽ ስምምነቱን ባለመቀበላቸው እንዲሁም ለማዳከም እየጣሩ በመሆናቸው ወደ ትብብር እንዲመጡ ሲባል የውስን ታዛቢነት (Limited Observer Status) ደረጃ ተሰጥቷቸው በተመረጡና ቁልፍ ውሳኔ በማይሰጥባቸው ስብሰባዎች ላይ የመሳተፍና ምስጢራዊ ያልሆኑ መረጃዎችን የማግኘት ዕድል ሊያገኙ ይችላሉ።
የናይል የትብብር መድረክ
እ.አ.አ በ2013 ሱዳን ወደ ናይል ትብብር መድረክ መመለሷ የምስራቅ ናይል ንዑስ ተፋሰስ ትብብር ላይ መነቃቃትን አስከትሏል። በ2014 ደቡብ ሱዳን የምስራቅ ናይል የድርጊት መርሃ ግብር አባል ለመሆን ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ መድረኩን ተቀላቀለች። በዚህም ከ2010 ጀምሮ በኢትዮጵያ ተሳትፎ ብቻ ሥራውን ሲያከናውን የነበረው የምስራቅ ናይል ትብብር በሦስት አገራት የተሟላና ጠንካራ ተሳትፎ ማንሰራራት ጀመረ።
የግብጽ ከትብብሩ መውጣት ያልተመቻቸው የልማት አጋሮች ለመድረኩ የሚሰጡትን የፋይናንስ ድጋፍ በከፍተኛ መጠን ቀነሱ። ለዚህም ቅነሳ ዋና ዋና ምክንያቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተከስቶ የነበረው የኢኮኖሚ ዕድገት መቀዛቀዝ፣ በርካታ አገራት የሚሰጡትን ድጋፍ ስደተኝነትን ለመቀነስ ማዋላቸውና ግብጾች የልማት አጋሮች ለናይል ትብብር ድጋፍ እንዳይሰጡ የሚያደርጉት ጥረት ውጤት ነው። የልማት አጋሮች የፕሮግራም ማስፈጸሚያ ድጋፍ መቀነስ ብቻ ሳይሆን ፋይናንሱ ጥቅም ላይ የሚውልባቸውንም የትብብር አይነቶች ለውጠዋል። ለምስራቅ ናይል የቴክኒክ አህጉራዊ ጽ/ቤት ለልማት ፕሮጀክቶች ማዘጋጃ ይመደብለት የነበረው ፋይናንስ ሙሉ በሙሉ ተቀይሮ የፕሮጀክት ዝግጅትን የሚያግዙና የፕሮጀክት አፈጻጸምን የሚያሻሽሉ ዘርፎች ላይ እገዛ መስጠት ጀመሩ።
ይህንንም ተከትሎ የምስራቅ ናይል የቴክኒክ አህጉራዊ ጽ/ቤት ከአገራቱ ጋር በመነጋገር ትኩረቱን ለአገራቱ የጋራ ፕሮጀክት ከማዘጋጀት አገራቱ ፕሮጀክት ሲያዘጋጁ ወይንም ሲተገብሩ ወደሚረዳቸው ጉዳዮች ማተኮር ጀመረ። የመረጃ አሰባሰብና አተናተንን ዘመናዊ ማድረግ፣ የዕውቀት ማዕከላትን ማጠናከር፣ የጎርፍ ትንበያ ቅድመ ማስጠንቀቂያን ማሻሻል፣ የግድብ ደህንነትን የሚያረጋግጡ ሥራዎች መሥራት፣ የውኃ ዲፕሎማሲ፣ የአቅም ግንባታ፣ የኢንተርንሺፕ ፕሮግራም፣ የከርሰ ምደር ውኃን ከገጸ ምድር ውኃ ጋር አቀናጅቶ መጠቀም፣ የመስኖ ውኃ ብቃት ማሳደግ፣ የግድብ አስተዳደር ማቀናጀትና በመሳሰሉ ዘርፎች ላይ በማተኮር ለአገራት
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ በማበርከት ላይ ይገኛል።
ግብጽን ወደ ትብብር መድረክ መመለሱ የሚኖረውን አዎንታዊ ጥቅም ትኩረት ውስጥ በማስገባት በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል። እ.አ.አ ኖቬምበር 2012 ላይ ኢትዮጵያ ያካሄደችው ሙከራ ሱዳንን ወደ ትብብሩ የመለሰ፣ ደቡብ ሱዳን የትብብሩ አካል እንድትሆን ያደረገ ቢሆንም ግብጽን ግን ሊያሳምን አልቻለም። ሱዳንና ኡጋንዳ በተናጥል ግብጽን ወደ ትብብር ለመመለስ ተደጋጋሚ ጥረት አድርገው እንደነበር ይታወቃል። በ2016 ኡጋንዳ፣ ሱዳን እና ሩዋንዳ ያሉበት የናይል ተፋሰስ የሚኒስትሮች ም/ቤት ያቋቋመው ኮሚቴ ግብጽ ወደ ትብብሩ ላለመመለስ የወሰነችባቸውን ምክንያቶች እንዲያጠናና ለምክር ቤቱ እንዲያቀርብ በተወሰነው መሰረት ከግብጽ የውኃና መስኖ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በመነጋገር ርፖርቱን አቅርቧል። በመቀጠልም የናይል ሚኒስትሮች ም/ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ኢንተቤ ላይ በማድረግ የግብጽን ምክንያቶችና ፍላጎት ለመረዳት ቢሞክርም የግብጽ ጥያቄ የተፈረመው የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት እንደገና ለድርድር እንዲቀርብ ስለሆነ ማስተናገድ አልተቻለም።
በ2017 የናይል ተፋሰስ የርዕሳነ ብሔር ወይንም መንግሥት ሰብሳቢ ነኝ በሚል የኡጋንዳው ፕሬዚደንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ የመሪዎች ስብሰባ ጠርተው ነበር። የዚህ የናይል ተፋሰስ የመጀመሪያው የመሪዎች ጉባዔ ዓላማ ግብጽን ወደ ትብብር መመለስ የነበረ ቢሆንም በመጨረሻው ደቂቃ ላይ የግብጽን ጥያቄ በዚህ ደረጃ ማስተናገዱ ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ስለሚችል አጀንዳው በተፋሰሱ
ልማት ላይ እንዲያተኩር ተደርጎ ጉባዔው በሰላም ተጠናቋል።
በሌላ በኩል የናይል ተፋሰስ የትብብር መድረክ የሽግግር ጊዜ ተቋም ሆኖ ለረዥም ጊዜ መቆየት ለብዙ የልማት አጋር አካላት መሰላቸትን ፈጥሯል። የትብብር መድረኩ እስከመቼ ነው የሽግግር ጊዜ ተቋም ሆኖ የሚቀጥለው? መቼ ነው ወደ ቋሚ ተቋምነት የሚሸጋገረው የሚለው ጥያቄ በተደጋጋሚ ይቀርብ ነበር። በሌላ በኩል ደግም ግብጽ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱን ያለመፈረሟና ከትብብር መድረኩ መውጣቷ ያሳስባቸዋል። እነዚህ ሁለት ጉዳዮች እርስ በእርስ የሚጋጩ ሆነው ነው የተገኙት። የልማት አጋሮች የናይል ተፋሰስ አገራት ቋሚ የተፋሰስ ኮሚሽን እንዲያቋቁሙ ይፈልጋሉ። ኮሚሽኑ ደግሞ የሚቋቋመው የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ሲጸድቅ መሆኑና ግብጽ ስምምነቱን አንዳልተቀበለች ሲያስቡ ግራ ይገባቸዏል።
ይህ በእንዲህ እያለ ደቡብ ሱዳን የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን ስድስተኛ አገር በመሆን ስትቀላቀልና ስድስቱ አጽዳቂ አገራት በማዕቀፉ መሰረት ቋሚ የተፋሰስ ኮሚሽን በማቋቋም የናይል የትብብር መድረክን የሽግግር ጊዜ ተቋምነት ለማብቃት ሲንቀሳቀሱ የልማት አጋሮች መቃወማቸው አስገራሚ ጉዳይ ሆኖ ተገኝቷል። ለናይል ተፋሰስ የሚሰጡትን የፋይናንስ ድጋፍ ሙሉ በሙሉ እንደሚያቋርጡም አስታውቀዋል። ስድስቱ አገራት የናይል ተፋሰስ ኮሚሽንን ሲያቋቁሙ የሽግግር ጊዜ የትብብር ተቋም የነበረው የናይል የትብብር መድረክ በተረጋጋ
ሁኔታ የገባቸውን ግዴታዎች፣ የተሰጠውን መብት እና ያካበተውን ሀብት ለኮሚሽኑ በማውረስ እንደሚከስም ይጠበቃል። ይህንንም ሽግግር የተሳካ ለማድረግ ስድስቱ አገራት የተለያዩ ስልቶችን ለመጠቀም አቅደዋል። ላለፉት 15 ዓመታት የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትንም ሆነ የትብብር መድረኩን ለማዳከምና ለማፍረስ በዓመት እስከ 10 ሚሊዮን ዶላር ስትመድብ የቆየችው፤ ትብብሩን ከውስጥ ለመሸርሸር፣ የትብብር ሂደቱ የፋይናንስ ድጋፍ እንዳያገኝ፤ በአገራት መካከል ይታይ የነበረው ጥብቅ ትብብር እንዲሻክርና መጠራጠር ስር እንዲሰድ ስታደርግ የቆየችዋ ግብጽ የናይል የትብብር መድረክ ባለቤት መሆኗን በማወጅ ወደ ትብብር መድረኩ ተመልሳለች። ግብጽ ይህንን ስታደርግ በትብብሩ አምና ሳይሆን ከ25 ዓመታት ከፍተኛ ጥረት በኋላ በናይል ተፋሰስ ውስጥ ፍትሃዊ የውኃ አጠቃቀም ሊያሰፍን ይችላል ተብሎ የታመነበትን ኮሚሽን የማቋቋም ጥረት ከውስጥ ሆና በማኮላሸት አሁን ያለውን እኔ ብቻ ልጠቀም እናንተ ካላይ ውኃውን እያያችሁ ላኩልኝ ፖሊሲዋን ለማስቀጠል ነው። ይህ ደግሞ ጊዜ ያለፈበት ኋላቀር አስተሳሰብ ስለሆነ ውድቅ መሆኑ አይቀሬ ነው።
ማጠቃለያ
ከፍተኛ የውኃ እጥረት ባለበት የናይል ውስጥ የሚታየው በከፍተኛ ደረጃ የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የከተማነት ዕድገት፣ የኢንዱስትሪ መስፋፋት፣ ከከባቢ አየር ለውጥ እና ከተፈጥሮ ውድመት ጋር ተጣምሮ የወሃ ሀብት አስተዳደሩን አስቸጋሪ አድርጎታል።
የናይል ተፋሰስ ሁሉን አቀፍ ህጋዊ እና ተቋማዊ
ማዕቀፍ ከሌላቸው ጥቂት ተፋሰሶች ውስጥ አንደኛው ነው። የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በዘላቂነት ለመጠቀም ከተፈለገ አገራቱ በጋራ በመነጋገር ህጋዊ እና ተቋማዊ ማዕቀፍ ሊያበጁለት ይገባል።
ላለፉት በርካታ ዓመታት በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በዚህ አኳያ የተሞከሩ ሙከራዎች በርካታ አመርቂ ውጤቶችን ያስገኙ ቢሆንም ሁሉንም አገራት ሊያሳትፉ አልቻሉም። በናይል ተፋሰስ ውስጥ ትብብር አማራጭ አይደለም። በተፋሰሱ ውስጥ መተባበር ግዴታ መሆኑ ይታወቃል።
የናይል ተፋሰስ አገራት ላለፉት 25 ዓመታት የሽግግር ጊዜ ተቋም በነበረው የናይል የትብብር መድረክ ዙሪያ እንዲሁም ቋሚ ህጋዊና ተቋማዊ ማዕቀፍ በመፍጠር የሽግግር ጊዜ የትብብር ተቋሙን ወደ ቋሚነት ለማሸጋገር የሚችል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ሲያዘጋጁ ቆይተዋል። አሁን የትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱ አስገዳጅ ለመሆን የሚያስፈልገውን ስድስት የማጽደቂያ ሰነድ ቁጥር ያገኘ በመሆኑ ቋሚ ኮሚሽን የማቋቋሙ ሥራ በይፋ ተጀምሯል።
ስምምነቱን ያጸደቁት ስድስቱ የናይል ተፋሰስ አገራት የሚያቋቁሙት የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን የሚጠበቅበትን ግዴታ በአግባቡ ይወጣ ዘንድ አገራቱ ጠንካራ ሥልጣንና ኃላፊነት መስጠት፣ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ድጋፍ ማድረግ፣ አስፈላጊውን የሰው ኃይል የፋይናንስ እና የቁሳቁስ ፍላጎት ማሟላት፣ እንደ አስፈላጊነቱም ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋር ራሱን የሚቀያይር፣ ተዓማኒነት የተቸረው፣ ጠንካራ ተቋም ማደራጀት ይጠበቅባቸዋል።
ፖለቲካ
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
ትናንት ዛሬ እና ነገን
ለማስታረቅ. . .
በፍቅርተ ባልቻ
“ታሪክ የማኅበረሰባዊ ግንኙነት ቅሪት ነው። ግንኙነቱ ፖለቲካዊ ብቻ አይደለም። ኢኮኖሚያዊና ሰብዓዊ ትሩፋትንም ያካትታል። በዚህ ውስጥ
በሰዎችና በአገራት መካከል የሚፈጠረውን ዕድገት፣ ግጭት ውጣ ውረድና ፈተና ይመዘግባል ሀብት መፍጠር፣ የግዛት መስፋፋትና መጥበብ፣ ጠላትና ወዳጅ መሆን፣ ወዘተ. የጋራ ዝክረ ጠባዮች ናቸው። እንግዲህ ትርክት ከዚህ ሥር የሚቀዳና የሚመዘዝ ውርስ ነው።
ትርክት ሆን ተብሎም ይሁን በተለምዶ በዓላማ የሚዘጋጅ ንግርት ነው። ብዙ ጊዜ ታሪክን፣ እምነትን፣ ባህልን አና አመለካከትን ይይዛል፤ የሚነገርበት ምክንያት አለው። የሚዘጋጀውም ለዚያ ምክንያት ሲባል ነው። የሚካተቱት
ከተዘጋጀበት ዓላማ ጋር የሚሄዱ ሃሳቦችና ታሪኮች ናቸው። ብዙ ጊዜ የትርክቶች በጎነትና እኩይነት በትርክት ቀራፂዎቹ እጅና ፈቃድ ወይም
ቁጥጥር ስር ሲወድቅ ይታያል። እነዚህ ጉዳዮች በበጎ ዓላማ ከተዘጋጁ በአንድ አገር ሕዝቦች መካከል መግባባትና አንድነትን እንድሚፈጥሩት ሁሉ፤ ለእኩይ ዓላማ ከተዘጋጁ ደግሞ መቃቃር በመፍጠር የግጭት አዙሪት ውስጥ ይከታሉ
. . .“ እያለ ይቀጥላል - “የትርክት ዕዳና በረከት“ የተሰኘውና በ2016 ዓ.ም ለንባብ የበቃው የሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት መፅሃፍ መግቢያ።
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
የቀደመ ሥልጣኔ ያላት ኢትዮጵያ፤ ያን ሥልጣኔ እና ታሪኳን አጽንታ መዝለቅ አልቻለችም። ብዙ ውጣ ውረዶችን ማለፏን ታሪኳ ያስረዳል። በተለያዩ ጊዜያት የነበሩ መንግሥታት ወደ ቀደመ ሥልጣኔዋ ለመመለስ እና ከከፍታ ማማ ላይ እንድትወጣ ለማደረግ የየበኩላቸውን ጥረት ቢያደርጉም በውስጣዊ እና ውጫዊ ተግዳሮቶች ምክንያት ትልሟ እውን አልሆነም። በታሪኳ ላይ የጋራ መረዳትም አልተፈጠረም።
በ2010 ዓ.ም የተደረገውን ለውጥ ተከትሎ ወደ ሥልጣን የመጣው የለውጡ መንግሥት ኢትዮጵያ ከችግሮቿ የምትወጣባቸውን መንገዶች በመለየት መፍትሄ ለመሻት ተግባራዊ ለማድረግ በሰፊው እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። አገሪቷን እና ሕዝቦቿን ከችግሮቹ ማውጫ መንገዶች ሆነው ከተለዩት መካከል በአገራዊ ምክክር የጋራ ችግሮችንና ልዩነቶችን የማስታረቅ ጥረትን ጨምሮ የወል ትርክትን መገንባት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመደመር መንግሥት መፅሃፋቸው ይህንን ሃሳብ እንዲህ ገልፀውታል፤ “በተለያዩ ክሥተቶች ውስጥ አልፎ የመጣ ማኅበረሰብ ስለ ትናንት የተለያየ ዕይታ ይኖረዋል። በትናንት ዕይታ የሚፈጠር ትርክት የማኅበረሰብን የሕይወት ዘይቤ ይቀርጸዋል። ትርክት በመሠረቱ የማስተባበርም
የመበተንም እኩል ይል አለው። በዋናነት የያይል ምንጩ ምስል ከሳችና አስተሣሣሪ መሆኑ ነው። ያልነበርንበትን ትናንት እንዳለን አድርጎ ያሳያል። ከዚህ ባለፈ ምናባዊ ማኅበረሰብ (imagined communities) ለመፍጠር ያስችላል። ይህ ኃይል ለብልጽግና ወይም ለጥፋት ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል። የማኅበረሰብ ልዩነቶች እንደተከበሩ አካታች ትርክቶች ላይ በመሥራት ዛሬንና ነገን ውብ ማድረግ ይቻላል”
ትርክት. . .
ትርክቶች (Narratives) ከዚህ በፊት በታሪክ ተፈጽመው ይሆናል ተብለው በሚታሰቡ ክስተቶች መነሻነት በዛሬ ሕይወታችን ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር በቃል፣ በጽሑፍ፣ በትወና ወይም በሌላ አመቺ የመገናኛ መንገዶች ከአንዱ ወደ ሌላው፤ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፉ መልዕክቶች ናቸው። እነዚህ መልዕክቶች እንደ ታሪክ ይነገራሉ፤ በግለሰቦች እና በቡድኖች ክርክር ወቅት በማስረጃነት ይቀርባሉ።
በፅሁፋችን መግቢያ የጠቀስነው የትርክት ዕዳና በረከት መጽሐፍ ትርክቶች የትናንት ታሪኮችን እንደ
እርሾ በመጠቀም ዛሬ ላይ ለምንፈልገው አሉታዊም ይሁን አዎንታዊ ፍላጎቶቻችን ማስፈጸሚያነት እንደሚውሉ ይነገራል። የትርክት ዕዳና በረከት መፅሃፍ ትርክቶች ተቀባይነት የሚኖራቸው ስለማኅበረሰቡ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ግልጽ በሆነ የጊዜና የድርጊት ፍሰት ሲቀርቡ ድርጊቶቹም ትርጉም ባለው ሁኔታ መቀመጥ ሲችሉ እንደሆነ ያስነብባል።
ግለሰባዊና አገራዊ ክስተቶች ተነጣጥለው ከነበሩበት፣ የታሪክ ቅኝቶችን በማድረግ አገናኝ መስመሮችን በአግባቡ በማጥናትና ከሌሎች ክስተቶች ጋር በተያያዘ ያሉትን የክንዋኔ ውጤቶች ለማግኘት የሚደረግ ሂደትንም ያጠቃልላል - ትርክት። በመሆኑም የአገራት የታሪክ ክፍሎች በዚህ ሂደት ባለፈው የነበረውን፤ በአሁኑ እና በወደፊቱ መካከል የሚኖረውን ትስስሮሽ የሚያስተካክሉ ገለጻዎች በባለሙያዎች “ትርክት“ ተብለው ይበየናሉ።
ትርክቶችን በአግባቡ መረዳት በዘመኑ ውስጥ የተስተናገዱትንና የነበሩትን በርካታ የተበታተኑ ክስተቶች በወቅትና በቦታ በማደራጀት፣ በማቀናጀት፣ በማኅበረሰቡ ዙሪያ ስለነበረው ሁኔታ መረዳትና ማስተዋል እንዲሁም ማኅበራዊ ማንነቶቻቸውንና እሳቤያቸውን መገንዘብ ዛሬ ላይ የሚበጀውን የአኗኗር ሥርዓት ለመመስረት እንደሚያስችልም ይጠቅሳል።
የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ትርክትን “ለሰው ልጆች የሚነገሩ መረጃዎች፣ እውነታዎች፣ እውነቶች፣ ታሪኮች፣ አፈ ታሪኮች፣ ክስተቶች ወዘተ … ድምር ውጤት ነው። የሰው ልጆች እውነታን
ለመሳል የሚያገለግላቸው የመረጃዎች አቅም ውጤት ነው። የሰው ልጆችን የዕውቀትና የስሜት አቅም የሚገነባ የመረጃዎች ፍሰት ኃይል ነው“ ሲሉ ይገልፁታል።
ትርክትን ንዑስ እና ዓብይ በማለት በሁለት ከፍለው የገለፁት ዶ/ር ቢቂላ፣ ንዑስ ትርክት (Micro Narrative) የእኔ ክልል፣ የእኔ ዞን፣ የእኔ ወረዳ፣ የእኔ ብሄር፣ የእኔ ጎሳ፣ የእኔ ሃይማኖት፣ የእኔ ማንነት፣ ወዘተ … ጉዳዮች መገለጫዎቹ ሲሆኑ፤ ዓብይ ትርክት (Grand Narrative) የነገሮች ትስስር፣ የጋራ ማንነት፣ የሁላችንም ጉዳይ፣ አገራዊ፣ ቀጣናዊ፣ ዓለም አቀፋዊ፣ የጋራ ችግር፣ የጋራ መፍትሄ፣ የጋራ ፍላጎት፣ በመሳሰሉት ላይ ትኩረት የሚያደርግ መሆኑን ያብራራሉ።
በሌላ መልኩ ትርክቶች ነጠላ እና ገዢ በሚል ይገለፃሉ፤ ነጠላ ትርክት ነጠላ ግብ፣ ህልም እንደማለት ሲሆን ገዢ ትርክቶች አገር በመገንባት ሂደት የላቀ አስተዋጽኦ ያላቸው እንደሆኑ ይታመናል። የጋራ አገር፣ የጋራ ብልጽግና፣ የጋራ ትውልድ፣ ብሩህ ያማረ መጪ ዘመን እንዲኖር ካስፈለገ እዚህ ላይ በደንብ መሥራት ይጠይቃል። የበለጸገች ኢትዮጵያን መገንባት የምንችለው በዚህ መልኩ ነው።
“ያለ ትርክት መኖር አይቻልም“ የሚሉት የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዚዳንት አቶ ዛዲግ አብርሃ “በራሳችን ወይስ በሌሎች ትርክት ነው እየተመራን ያለነው?“ ሲሉ ይጠይቃሉ። አያይዘውም ትርክት ዓለም አቀፍ ገጽታ እንዳለው፤ አቅጣጫን ከማሳየት ባለፈ ማንነትን ለመቅረጽ ብሎም ሕዝብን ለማንቀሳቀስ እንደሚያገለግል ይጠቅሳሉ።
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
አቶ ዛዲግ ትርክት ባህልን ለማሻገር እንዲሁም ውሳኔ ለማሳለፍ እንደሚጠቅም አንስተዋል። “ትርክት ዓለምን የምናይበት መነፅር ነው፤ ትርክቷን የዘነጋች አገር እንዴት መነሳት እንዳለባት አታውቅም፤ ትርክት ማንነትን የሚቀርፅ በመሆኑ አገር የሚወለደው በጋራ ትርክት ነው። ስለሆነም የጋራ ትርክትን መገንባት የጋራ መፃኢ ዕጣ ፈንታን ለመወሰን የሚያስችል ነው” ይላሉ።
ትርክት ለምን፣ እንዴት?
በፖለቲካ ውስጥ ያሉ ተዋንያን ትርክቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ እያስገኙ ያሉትን ተጽዕኖ ይገነዘባሉ። በዚህም የተነሣ ራሳቸውን ከማኅበረሰቡ ጋር ለማስተሳሰርና ለተነሱበት ዓላማ ስኬት ሲሉ ጉዳዩን እንደ ተግባቦት መሣሪያ ይጠቀሙበታል።
የትርክት ጽንሰ ሀሳብ ከሥነ ጽሑፋዊ ህልዮት ባሻገር በሌሎች የጥናት መስኮች መቃኘት መጀመሩ የቅርብ ጊዜ ክስተት ስለመሆኑ በትርክት ዕዳና በረከት መጽሐፍ ተመላክቷል። መጽሐፉ ትርክት በማኅበራዊ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ የምርምር አጀንዳ ሆኖ እስኪዋሀድ ድረስ ጊዜ እንደወሰደ ያስነብባል።
ይህም ፖለቲከኞች (የፈጠራ ወሬዎችን በመደጋገም እውነት አድርጎ በማቅረብ ማሳመን ይቻላል ብለው የሚያምኑ) በርዕዮተ ዓለም የተዋጁ ቡድኖች፣ የወጡበትን ማኅበረሰብ የተበዳይነት ስሜት በማስረጽ በርካታ ጥፋቶች እንዲፈጠሩ አድርጓል።
ትርክቶችን በአራት ዓበይት ክፍሎች ያስቀመጠው የትርክት ዕዳና በረከት መጽሐፍ፤ የመጀመሪያው ክስተቱን ማጎን (Domination of Incrementum) ይህ ተፈጥሯል የሚሉትን
ታሪካዊ ጥፋት ለማኅበረሰቡ ደጋግሞ በማቅረብ፣ ከፍ ባለ የቁጣ ድምጸት በመናገር የተበዳይነት ስሜት እና ቁጭት የተሰማቸው ለማስመሰል መጣር ነው። የእያንዳንዱን የታሪክ ክስተት ቃላትን ረገጥ አድርጎ በመናገር ትኩረት መሳብና እውነት ማስመሰል ዋነኛ ገጽታቸው ነው። በእርግጥ ይህን ለመልካምና ለአገር ግንባታ ቢጠቀሙት በዚያው ልክ ማኅበረሰቡን ማንቃትና ማስተማር ያስችላቸው ነበር። ነገር ግን በበርካታ አገራት ይህ አልሆነም።
ሁለተኛው ንጽጽር ማድረግ (comparison) ነው። አንድን ታሪክ ወይም የአንድን ወገን በተለይ በዳይ ነው የሚሉትን ማኅበረሰብ ነጠላ ታሪክ በመምዘዝና በመጠምዘዝ ለንጽጽር መጠቀም ነው። የትርክቱ ይዘት ከነበረው ሃቅ ጋር የማዛመድ፣ በዘመን፣ በቦታና በሥልጣኔ የተለያየ፣ ጉዳዩ የማይገናኝና ከማኅበረሰቡም ጋር አብሮ የማይሄድ መሆኑን ልቦናቸው የሚያውቅ ቢሆንም ይህ ትርጉም አይሰጣቸውም ወይም አያስጨንቃቸውም።
በግምት ማሳመን (Presumption) ሦስተኛው ዓበይት ክፍል ሲሆን ይህም የሀሰት ትርክትን በመፈብረክ ማኅበረሰቡን ለአመጽ ለማነሳሳት የሚጠቀሙበት ነው። በዚህም ማኅበረሰቡን እነርሱ በሰፉት የታሪክ ልክ ብቻ እንዲለካ የሚያደርጉበት ሂደት ነው።
አራተኛው አፍራሽ ቃላትንና ሀሳቦችን ማደርጀት (Cumulation-congries) ነው። ይህ ለአንድ ማኅበረሰብ በሌላው የተሰጡ ናቸው የሚሏቸውን ቃላት፣ ቅጽል ስሞች፣ ሀሳቦች፤ ተረቶች፣ ንግግሮች፣ አባባሎች ወዘተ. . . በመሰብሰብ ትርክቶቻቸውን ለማሳመን እንደ ቅመም የሚጠቀሙበት
አካሄድ ነው። ዓላማቸውም በማኅበረሰቡ ውስጥ ሥር የሰደደ ጥላቻ እንዲፈጠርና አለመተማመን እንዲነግሥ ማድረግ ነው። እንዲህ ያሉትን የተወሳሰቡ ቃላት ለፖለቲካዊ ፕሮፖጋንዳ መጠቀም በተማሩት ልሂቃን ዘንድ የተለመደ መሆኑን የሚጠቅሰው መጽሐፉ ትርክትን እንዴት ተገቢ ባልሆነ መንገድ እየተጠቀሙበት እንዳሉ አስነብቧል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ መነሳት ያለበት ሌላው ነጥብ ስለ አንድ ሕዝብ የሚነገሩ ታሪካዊ ትርክቶች በሁሉም ረገድ የተሟሉ ናቸው ብሎ ማሰብ ስህተት መሆኑ ነው። በራሱ በትርክት ጠባይ ወይም በተራኪው ፍላጎት፣ አልያም ደግሞ ዘመኑ በሚፈጥረው ተጽዕኖ የተነሳ በአንድ ወይም በጥቂት ነገሮች ላይ ሊያተኩር ይችላል። በዘመኑ የደረሰ ሰው ማድረግ ያለበት እያሰፋ፣ እያካተተና እያሟላ መሄድ ነው።
የአገራትን ታሪክ የሚያሳዩ ታሪካዊ ትርክቶች ብዙ ጊዜ የዚያን አገር ሕይወት በሚያሳዩ በአንድ ወይም በጥቂት የታሪክ ገጽታዎች ላይ ሊያተኩሩ ይችላሉ። የአንድን ታሪክ
የትርክት ዋና ሀሳብ የመምረጥ ጉዳይ የታሪክ ባለሙያውን ወይም ደግሞ የታሪክ ባለሙያዎቹን ፍላጎት የሚያንጸባርቅ ነው።
ትርክቶች ምንም እንኳን በታሪክ እውነታና ክስተት ላይ የተመረኮዙ ቢሆኑም ዓላማቸው ግን ሊፈጥሩት የሚያስቡት ነገር ነው። ትርክት ዓላማ ተኮር ነው። የትርክት ተረኩንም የሚያሰናስለው በዚህ ዓላማ መሠረት ነው።
ሌላው በትርክት ሂደት ሊታይ የሚገባው የታሪክ ክስተትን የማግነን ጠባይ ነው። ይህ የማግነን ጠባይ በተለይ ለአሉታዊ ጉዳዮች ሲጠቀሙበት ይበልጥ የመጉላትና ከፍ ብሎ የመሰማት ዕድል እንዲኖር ያደርጋል። ይህን የሚያደርገው ሀሳቡ ችግሮችን ብቻ እየቀነሰ የማስጮህ ሥሪት ስላለው ነው በማለት ሄንሪ ቶልቻርድ ሥልጣን በፖለቲካዊ ትርክት ውስጥ በሚለው የአሜሪካን ምርጫ በታዘበበት ጽሑፉ ውስጥ ገልጦ ነበር።
ይህም ፖለቲከኞች የታሪኩ ባለቤት የሆነውን ማኅበረሰብ ለማሳመጽ፣ ለማሳመንና ተቀባይነት ለማግኘት የተለያዩ የትርክት አቀራረብ
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
አማራጭ ስልቶችን በመንደፍ የተበየነ መሆኑም ይወሳል። ዓላማውም ታሪክን ማሳወቅ ሳይሆን ለፖለቲካ አመጽ መሣሪያነት መጠቀም ነው።
“እ.አ.አ በ1990ዎቹ አጋማሽ ትርክት ወለድ ግጭቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ በመበራከታቸው የማኀበራዊ ሳይንስ ተመራማሪዎችን ቀልብ የሳበ ክስተት ነበር። በመሆኑም በትርክት ዙሪያ በርካታ ጥናቶች በተለያየ እይታ እንዲጠኑ ዕድል ከፈተ” ሲል ያስነበበው የትርክት ዕዳና በረከት መጽሐፍ፤ ትርክት ሲገነባና ሲያፈርስ በየአገራቱ በክስተትነት ተዘግቦ በታሪክ ድርሳን ተቋጥሯል ይላል።
የፖለቲካ አሰላለፎችና የሰዎች መዋቅራዊ የስትራቴጂ ቀረጻዎች በጊዜና በሂደት ለውጥ “ፖለቲካው“ የተወሰነ ማኀበረሰብ ላይ ብቻ ያተኮረ ሥርዓት እንዲሆን አድርጎታል። ይህ ሁኔታ በሂደት የሥልጣን ሽኩቻ እንዲፈጠር ሰበብ ሆኗል። እነዚህ የፖለቲካ አመጾች የነበረውን ወይም የተጀመረውን የአገረ መንግሥትና የብሔረ መንግሥት ግንባታ በብዙ አገራት ወደኋላ መልሰዋል።
በሌላ በኩል የተሳኩ የኅብረብሔራዊ ተረኮች በኅብረተሰቡ ውስጥ ሥር እንዲሰዱ ከተደረጉ በአገር ላይ ያላቸው በጎ ተጽዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም። ለዚህም በትልቁ በምሣሌነት የምትጠቀሰው ቻይና ናት። ቻይና የአንድ ፓርቲ ሥርዓትና የብዝኃ ሕዝብ ተሳትፎ በሚለው ዘመናዊው ትርክቷ “የቻይና ህልም“ በሕዝቡ ውስጥ ማስረጽ ያልከበዳት የመገናኛ ብዙኃኗን በአግባቡ በመጠቀሟ ስለመሆኑ ይነገራል። የቻይና መንግሥት “የቻይናዊያንን ታሪክ በአግባቡ መተረክ“ ለሚለው ሀሳብ ከፍ ያለ ትኩረት መስጠቱ፣ ቻይና ላስመዘገበችው ሁለንተናዊ ዕድገት ምክንያት ስለመሆኑ በጉዳዩ ላይ የተካሄዱ ጥናቶች አመላክተዋል።
ትርክት በአመዛኙ በታሪክ ሂደት ውስጥ የነበሩ ችግሮች ላይ የሚያተኩር ነው። ታሪክን በሳይንሳዊ አጠናን ገለልተኛ ሆኖ በማጥናት እውነታዎችን የሚያቀርብ ሳይሆን በቀደመው ዘመን የነበሩትን ታሪካዊ ዘገባዎች የሚከስት ብቻ ነው። በመሆኑም በታሪክ አቅራቢው ወይም በተናጋሪው ፍላጎትና ዓላማ ክንዋኔው ሊጋነን፣ ሊዛባ፣ ሊዘለል ወይም ሊጠፋ ይችላል።
ታሪክ እና ትርክት
“ታሪክ የማኅበረሰባዊ ግንኙነት ቅሪት ነው። ግንኙነቱ ፖለቲካዊ ብቻ አይደለም። ኢኮኖሚያዊና ሰብዓዊ ትሩፋትንም ያካትታል። በዚህ ውስጥ በሰዎችና በአገራት መካከል የሚፈጠረውን ዕድገት፣ ግጭት ውጣ ውረድና ፈተና ይመዘግባል። ኃብት መፍጠር፣ የግዛት መስፋፋትና መጥበብ፣ ጠላትና ወዳጅ መሆን፣ ወዘተ… የጋራ ዝክረ ጠባዮች ናቸው። ትርክት ከዚህ ሥር የሚቀዳና የሚመዘዝ ውርስ ነው” ሲሉ በታሪክ እና በትርክት መካከል ያለውን ቁርኝት ያብራራሉ - ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት።
አያይዘውም ትርክት የአብሮነት ታሪካዊ መሰረት ስለመሆኑ በማንሳት ሰዎችን ከየት እንደተነሱ እና ወዴት እንደሚደርሱ ያመላክታቸዋል ብለዋል። ለአብሮነታቸው ትርጓሜ የሚያገኙት ከትርክት ነው። በጥቅሉ በሕዝብ ውስጥ መነሳሳትን፣ አብሮነትን እና መለያየትን የሚፈጥር የአገርን ታሪክ፣ የወደፊት ተስፋዋን እና ዛሬ ላይ የሚኖረውን ሚና እና ክስተቶችን የምንመለከትበት መነጽር ነው።
ታሪክ የሚጻፈው በትርክት መሰረትነት ነው። ታሪክ ዝም ብሎ አይሰራምም፣ አይመዘገብምም። የታሪክ ምዝገባ ዓላማን ተከትሎ የሚሄድ ነው። ዓላማው የታሪክ አጻጻፉን ይወስነዋል። ዓላማው የሚመጣው ከትርክቱ ነው። የትርክት ዕዳና በረከት መጽሀፍ ይህን ለማስረዳት አሜሪካን እንደማሳያ ይጠቅሳል፤ እንዲህ በማለት “አሜሪካ ከጥንት ጀምሮ ሰዎች ሲኖሩባት የኖረች አገር ናት፤ ብሎ የሚያምን ሰው ‘ኮሎምበስ አሜሪካን አገኛት‘ የሚለውን ተረክ አይቀበልም። አሜሪካ ተገኘች/ አልተገኘችም የሚለው የታሪክ አገላለጽ በዓላማ የሚነገር የትርክት ውጤት ነው”።
ታሪክ የቀደምት ክስተቶች፣ ሁነቶች፣ ድርጊቶች፣ አስተሳሰቦችና እምነቶች ቅደም ተከተላዊ አቀማመጥ ነው። ይህን ቅደም ተከተል ሕይወት
የሚዘራበት ትርክት ነው። በትርክቱ ውስጥ ትርጉም፣ ተጽዕኖ እና ብያኔ አለ። ያ ትርጉም፣ ተጽዕኖና ብያኔ የሚሰጠው ደግሞ በዛሬው ዕውቀት፣ ፍላትና የዕድገት ደረጃ ላይ ሆኖ ነው። የታሪክ ሂደትን ለግጭትና ለብጥብጥ የሚዳርገው ከክስተቱ በላይ ለክስተቱ የሚሰጠው ትርጉምና ብያኔ፣ ከክስተቱም ዛሬ ያመጣል ተብሎ የሚታሰበው ተጽዕኖ ነው። ትሁት አተራረክ ነገሮችን በቅደም ተከተል ከማስቀመጥ በላይ ነው የሚባለው ለዚህ ነው።
ከልብ ወለድ እና ከአፈታሪኮች ገለጻ በበለጠ ትርክቶች በታሪክ ትምህርት ይገለጻሉ፤ ምክንያቱም ታሪካዊ ትርክቶች ተበታትነውና ቅርጽ አልባ ሆነው ከሚነገሩበት ሂደት ተላቀው ክዋኔዎቹ በአግባቡ ተገጣጥመው ትርጉም ያለው ክዋኔ መሆናቸውን
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
ማመላከት ይችላሉ።
ታሪክ በዛሬው አመለካከት ላይ ተመሥርቶ ስለ ትናንት የሚነግር ትርክት ነው። የዛሬ አመለካከት በተቀየረ ቁጥር የታሪክ ትርክትም አብሮ ይቀየራል። ምክንያቱም ምንም እንኳን ትናንትን ለመቀየር ባንችል፣ ዛሬ የሚቀያየረው አመለካከታችን ስለ ትናንት የተለያዩ ጥያቄዎችን እንድናነሳ ያደርገናል።
ምንም እንኳን ታሪካዊ ትርክቶች ልብ ወለዳዊ ሀሳብ እንዲኖራቸው ተደርገው ቢነገሩም፣ የቀደመውን ታሪካዊ እውነታ ሊቀይሩት አይችሉም። አንዳንድ ጊዜ ታሪካዊ ትርክቶች አማልክታዊ አፈታሪኮችን አካተው ስለሚነገሩ የታሪኩን እውነትነት ሊያዛንፉና በጊዜው በትክክል ምን እንደተከናወነ ለማወቅ አዳጋች ሊያደርጉት ይችላሉ። እነዚህ አፈታሪኮች በአንድ ማኅበረሰብ ወይም አካባቢ ብቻ የተፈጠሩ ሳይሆኑ በሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች ውስጥ የተለመዱ ናቸው። በመሆኑም በእነዚህ አፈ ታሪካዊ ትርክቶች ውስጥ በአመዛኙ የተዛቡ ትርክቶች እየተመረጡ
ለፖለቲካዊ ፕሮፖጋንዳ እንዲውሉ ተደርገዋል።
ትርክት እና ታሪክ በእጅጉ የተያያዙ ጉዳዮች ናቸው። ታሪክ እውነት አይደለም፣ ውሸትም አይደለም። ታሪክ ወደ እውነት የቀረበ ክስተት ነው። አንድን ኩነት ወይም ክስተት ሰዎች በተለያየ መንገድ ይገልጹታል። የነበረውን ክስተት የታሪክ ምሁራን ለእውነት የቀረበው ታሪክ ይህ ነው ይላሉ። ይህ ሂደት አለአግባብ ማጉላት ካለበት፤ ለምሣሌ የነበረውን ኩነት ተገቢ ባልሆነ መንገድ ለግለሰቦች እና ለቡድኖች የሚሰጥ ከሆነ፣ አላስፈላጊ ንጽጽርም ካለበት፣ ታሪኩን በማዛባትም የቀረበ ከሆነ ወደ እውነት አይቀርብም።
በታሪካዊ ትርክት ውስጥ የተለመደው አቀራረብ ትርክትን ማስጮህ ነው። ይህ ሂደት ከነበረው ታሪካዊ ጣዕምና ሀሳብ በተቃራኒው ለራስ ሀሳብ እንዲመች አድርጎ ማቅረብ ነው። በዚህ ጊዜ አገራዊና ማኅበረሰባዊ ታሪክ ተቀባይነት እንዲያጣ ለማድረግ ስለሚሰራ ታሪኮቹ አሻሚና አጠራጣሪ እንዲሁም ወገንተኛ እንዲሆኑ ይደረጋል። እነዚህ
ታሪክ አዛናፊዎች የማይታመኑ፣ ውሸታሞች፣ ቃል አቀባዮች እና የራሳቸው የፖለቲካ ወይም የሥልጣን አጀንዳ ያላቸው ናቸው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ጊዜ የታሪክ ሙግቶች ከትናንት ይልቅ በዛሬ ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ክርክሩ ትናንት ያ ድርጊት በመደረጉ የሚመጣ ሳይሆን፣ ዛሬ ያንን ድርጊት በምንመለከትበት መነጽር የተነሳ የሚመጣ ነው። ስለሆነም የሰው ልጅ አመለካከት እስከተለዋወጠ ድረስ በታሪክ ላይ የሚኖረን ክርክር መቼም ቢሆን ይኖራል።
ሥልጣኔ እና ትርክት
በብዙ ሊቃውንት ዘንድ የተለመደው የሥልጣኔ ትርጓሜ የተወሳሰበ ማኅበረሰብ መፍጠር የሚል ነው። የማኅበረሰቡን ጠባይ መግራት የሚችል፤ የሞራልና የሕግ ሥርዓት፤ ተግባቦትን የሚያቀላጥፉ የተግባቦት ዘዴዎች፤ ሸቀጦችን ለማምረት የሚችል የዳበረ የምርት መሣሪያዎች፤ ሥነ መንግሥት፤ የተትረፈረፈ የምግብ ምርት ያለው እንዲሁም የላቀ ባሕል መፍጠር የቻለ ማኅበረሰብ ሠልጥኗል እንደማለት ነው።
የትኛውም ሥልጣኔ የአንድ ወገን ብቻ ውጤት አይደለም። የሥልጣኔዎች መጀመር አንዱ ምክንያት የሰዎች ኅብረ ብሔራዊ ግንኙነት ነው። ለዚህም ነው ብዙዎች ሥልጣኔዎች የከተማ ሥልጣኔዎች የሆኑት። ምንም እንኳን በአካባቢው በኖረው ሕዝብ ቢጀመሩም ሥልጣኔዎች በዚያው አይቀጥሉም። በተጨማሪ ክሂሎት፣ ተሰጥኦ፣ ሀብትና የሰው ጉልበት ይፈልጋሉ። በዚህ የተነሣ ሥልጣኔዎች ወይ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ይስፋፋሉ፣ ወይም ሰዎች ወደ ሥልጣኔዎች ይመጣሉ።
ሰዎች በባሕሪያቸው የተሻለ ቦታ ሄዶ የመኖር ፍላጎት አላቸው። በዚህም የተነሳ በአስተዳደር፣ በንግድ፣ በአኗኗርና በምቾት የተሻለ ወደሆነ ቦታ ይሄዳሉ። ልክ ዛሬ የብዙ አገር ዜጎች ወደ አሜሪካ እንደሚጓዙት። በዚህም የተነሣ ሥልጣኔዎች ባሉበት ብዙ ዓይነት ማኅበረሰቦች፣ ባህሎችና እምነቶች ይሰባሰባሉ።
ኅብረ ብሔራዊነት የኢትዮጵያ ጥንታዊ ታሪኳና መልኳ መሆኑን ሥልጣኔዎቿ ይነግሩናል። ሁሉም በሚባል መልኩ የኢትዮጵያ ሥልጣኔዎች እርስ በእርስ የተገናኙ ናቸው። ለዚህም ሃይማኖት፣ ንግድ፣ ጦርነትና የሕዝቦች እንቅስቃሴ ከፍተኛውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
የሥልጣኔ ታሪኮቻችን እንደሚያስረዱት ለሥልጣኔዎቻችን መክሰምም ሆነ መዳከም ሁለት ሁነኛ ምክንያቶች አሉ። የመጀመሪያው በውስጥ የሚደረግ የሥልጣን ትግል ነው። በመሪዎች መካከል የሰከነ የሥልጣን ሽግግር አለመኖር የሚያመጣው የሥልጣን ትግል፣ ሥልጣኔዎቻችን እንዲዳከሙ ወይም እንዲከስሙ አድርጓቸዋል። ሁለተኛው የእርስ በእርስ ጦርነት ነው። በአንድ ሥልጣኔ ውስጥ ወይም በሁለት ሥልጣኔዎች መካከል በተፈጠሩ ጦርነቶች የተነሣ፤ ሥልጣኔዎች የፈጠሩትን ኃብት ጦርነት ይበላዋል። ከተማ ይፈርሳል፤ ሕዝብ ይበተናል፤ ኃብት ይወድማል።
የኢትዮጵያ ሥልጣኔዎች ሲስፋፉ የፈጠሯቸው ስህተቶችና ጥፋቶች የኢትዮጵያ ብቻ መልኮች አይደሉም። በዓለም ላይ የተነሡ እና የተስፋፉ ሥልጣኔዎች ሁሉ ጠባይ ነው። ሥልጣኔዎች የባሮችን ጉልበት በዝብዘዋል፤ ግዛታቸውን ለማስፋፋት ጦርነትን እንደመሣሪያ ተጠቅመዋል።
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
ከሌሎች ዓለማት መማር ካለብን ትምህርት አንዱ ልዩ ልዩ ሥልጣኔዎች ያደረሱት በደልና ግፍ እንዴት ተፈታ? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ነው። የትርክት ዕዳና በረከት “በአንድ አገር በሚኖሩ የተለያዩ ተገዳዳሪ ሥልጣኔዎች መካከል የተፈጠሩ ችግሮችን የመፍቻ መንገድ ያስፈልጋል። ለዚህ ሦስት መፍትሔዎች በዋናነት ቢነሱ መልካም ነው” ሲል ቀጣዮቹን ምክረ ሀሳቦች ያቀርባል።
የመጀመሪያው ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ነው። የሥልጣኔዎችን ኅብረ ብሔራዊነት መቀበል ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ ታሪክ ባለብዙ መልክ ነው። የተለያዩ ሥልጣኔዎች ውጤት ነው። በትርክታችን ልንከተለው የሚገባንም ይሄንን እውነታ ነው።
ሁለተኛው እውቅና መስጠት ነው። በተለያዩ ዘመናት የተፈጠሩ የኢትዮጵያ ሥልጣኔዎች ላስከተሉት ጣጣ በጋራ እውቅና መስጠት ይገባል። የጠፉ ሥልጣኔዎች አሉ። ማንነታቸውን ያጡ ሕዝቦች አሉ። ከቦታቸው የተገፉ ማኅበረሰቦች አሉ። በዘመናት ታሪካችን
ውስጥ ባልተገባ ሁኔታ የተቀረጹ ማኅበረሰቦች አሉ። ጥፋቱ የአንድ እና የሁለት ወገን አይደለም። ከዚህ ትምህርት በመውሰድ ወደፊት እንዳይደገም መሥራት ከዚህ ዘመን ትውልድ እና አመራር ይጠበቃል።
ሦስተኛው ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር ነው። ሥልጣኔዎቻችን በሰጡን ዕሴት እንዴት መኩራት እንዳለብን፤ ያመጡብንን ጣጣ ደግሞ እንዴት መፍታት እንዳለብን ብሔራዊ ምክክር ይፈልጋል። ምክክሩ ትናንት የተደረገውን ምን እናድርገው? አይደለም። ትናንት የተደረገውን ነጋችንን እያሰብን ምን እናድርግ? ነው። በጋራ እንደበደልን ሁሉ በጋራ ይቅርታ መጠየቅ አንዱ መንገድ ነው። ትምህርት ሰጪ የየሥልጣኔዎቹን ትምህርቶች በአገር አቀፍ ደረጃ መጠቀም ወሳኝ ነው። የትምህርት ሥርዓታችን የልዩ ልዩ ሥልጣኔዎችንን ታሪክ፣ አስተዋጽኦና ድክመቶች የምንማርበት ዕድል እንዲኖረው መሥራት ያስፈልጋል።
አገረ መንግሥት እና ትርክት
ኢትዮጵያ በጥንታዊና በዘመናዊ ታሪኳ የውጭና የውስጥ ጦርነት በብሔረ መንግሥት እና በአገረ
መንግሥት ግንባታዋ ላይ ያሳረፈው ጠባሳ በኢኮኖሚያዊ፣ በማኅበራዊ፣ በፖለቲካዊ ሥሪቶች እና በተቋማት ግንባታ ላይ ይታያል።
“እረፍት አልባው ጦርነት የመንግሥታትን ትኩረት ወንበር ማጽናት ላይ ስላደረገው ስብራቱን ከማከም በስብራት ላይ ስብራት እየደራረበ እንዲሄድ አድርጎታል። ቁስሎቹ ዘመናትን እየተሻገሩ ዛሬም የብሔረ መንግሥት እና የአገረ መንግሥቱ ፈተናዎች ሆነው ቀጥለዋል። ያልተጠናቀቀው የብሔረ መንግሥት ግንባታና ያልደረጀው የአገረ መንግሥት ግንባታ፣ በትርክቶች ውል አልባነት የአገረ መንግሥቱን ተቀባይነት ፈተና ውስጥ ከቶታል” በማለት ጦርነቶቹ ያስከተሉትን ችግሮች የሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት መጽሐፍ ያብራራል።
በርካታ ተመራማሪዎች (የአገረ መንግሥት ግንባታ) እና (የብሔረ መንግሥት ግንባታ) የተለያዩ ሂደቶች መሆናቸውን ያስረግጣሉ። የአገረ መንግሥት ግንባታ ማለት አንድ መንግሥት የመንግሥትነት ግዴታውን እንዲወጣ የሚያስችሉ መዋቅሮችን በብቃት መገንባት መቻል ነው። በአንጻሩ የብሔረ መንግሥት ግንባታ በአንድ አገር ውስጥ ያሉ የተለያዩ ቡድኖች በመካከላቸው የሚፈጥሩትና የሚጋሩት የጋራ ረቂቃዊ ማንነት ግንባታ ማለት ነው። የአገረ መንግሥት ግንባታ የመንግሥት ተቋማትን በመገንባትና በማጠናከር ላይ የሚያተኩር ሲሆን የብሔረ መንግሥት ግንባታ ግን በይበልጥ በዜጎች እና በግዛታቸው መካከል ስላለው ግንኙነት ያተኩራል።
ብሔረ መንግሥት ማለት በሀሳብ ያለ ማኅበረሰብ ነው፤ ያም ስለ ማኅበረሰቡ የጋራ ማንነትና ዕሴቶች
ያላቸው የጋራ ትርክት ነው። ይህም ትርክት ስለተሳታፊ ማኅበረሰቦችና ስለ መሪዎቻቸው፣ የእነርሱን ማኅበረሰብ ምን ልዩ እንዳደረገው፣ በተለይም ደግሞ ከሌሎች ጋር በተነጻጸረ መልኩ የሚሰጥ ገለጻ ነው።
የብሔረ መንግሥት ግንባታ በአንድ አገረ መንግሥት ውስጥ የሚኖሩ ማኅበረሰቦች በቡድንና በግለሰብ ደረጃ የአገረ መንግሥቱ አባልነት ስሜት እንዲያድርባቸው የማድረግ ተልዕኮ ነው። የአንድ አገር አብዛኛው ሕዝብ የጋራ ማንነት የሚፈጥርበትና የሚያዳብርበት የተራዘመ ተግባር ነው።
በአንድ በኩል ሕዝቡ ለብሔራዊ አንድነት ሲል የከፈለው መስዋዕትነት አለ። በሌላ በኩል አብዛኛው ሕዝብ ከአንድነቱ አገኛለሁ ብሎ የሚጠብቀው ተጨባጭ ጥቅም አለ። የብሔረ መንግሥት ግንባታ ውጤታማ ሆነ የሚባለው በሁለቱ ፍላጎቶች መካከል በቂ የሚባል መመጣጠን ሲኖር ነው። ይህ ሚዛን ካልተጠበቀ በአንድ አገር ውስጥ በአንድነት መኖር የሚያጓጓ አይሆንም።
በምዕራቡ ዓለም ታሪክ የአገረ መንግሥት ግንባታ ከብሔረ መንግሥት ግንባታ እንደቀደመ ይተረካል። ለዚህም መነሻ የሚያደርጉት የመንግሥት ምሥረታውና ግንባታው በአገሬው መጀመሩና መጎልበቱ ነው። በአንጻሩ በቅኝ ግዛት ሥር የነበሩ አገራት ማንነታቸውን በተቻለ መጠን የመጠበቅ ነገር ቢኖርም በአገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ የነበራቸው ድርሻ ይህ ነው የሚባል አልነበረም። በመሆኑም በቅኝ ግዛት ሥር የነበሩ አገራት በአመዛኙ ከአገረ መንግሥት ግንባታው ይልቅ የብሔረ መንግሥት ግንባታ (ማንነት ፈጠራው)
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
በታሪክ ይቀድማል።
ወደ አገራችን መለስ ብለን ስናይ የኢትዮጵያ ሥነ መንግሥት ታሪክ በአገሬው ሰው አንዴ በጋራ አንዴም በተናጠል የየራሱ የአገረ መንግሥት ግንባታዎችን አሳልፏል። በመሆኑም ከሞላ ጎደል የኢትዮጵያ የአገረ መንግሥት ግንባታ ታሪክ ከብሔረ መንግሥት ግንባታ ይቀድማል ማለት ይቻላል።
ይሁንና የአገረ መንግሥት ግንባታው በግዛት መስፋፋት የተነሳ የእርስ በእርስ ግጭት የበረከተበት በመሆኑ የብሔረ መንግሥት ግንባታ ሂደቱ በግጭቶች ተሸብቦ በአፍራሽ ትርክት እየተጠላለፈ እንዲመጣ አድርጎታል። ከዚህም በተጨማሪ በአንድ የመነሻ ሀሳብ ለረዥም ጊዜ የዘለቀ የብሔረ መንግሥት ግንባታ ስላልነበረን የተጠናቀቀ የብሔረ መንግሥት ግንባታ ልንፈጥር አልቻልንም።
ለአንድ ወገን ዓላማ የተቀረጸ፣ ልዩነትና ብዝሃነትን ያልተቀበለ፤ ማቀራረብና ማግባባት ዓላማው ያልሆነ፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን የማይፈጥር ትርክት ባለፉት ዘመናት ኢትዮጵያን ብዙ ፈትኗታል። ብዙ ዋጋም አስከፍሏታል። በተከታታይ የተነሱ የፖለቲካ ኃይሎች የተከተሉት ወይም ሊከተሉት የሚፈልጉት የትርክት መንገድ አገራችንን ወደ ውስብስብ ችግር እንዴት እንደከተታት እናያለን። የትርክቶቻችን መወላገድ አገራችን የሚያግባባ ትምህርት እንዳይኖራት አድርጓል።
አገር የትርክት ውጤት ናትና፤ ትርክታቸው ከመጻዒ ዕጣ ፋንታቸው ጋር የገጠመላቸው አገራት የአገረ መንግሥት እና የብሔረ መንግሥት ግንባታቸውን አጠናቀው ኢኮሚያዊ ፉክክር እና
እሳቤያቸው በሉላዊ የዓለም ማኅበረ ፖለቲካ ገዥ እንዲሆን እየተፋለሙ ይገኛሉ። አገራችን ለዚህ የሥነ መንግሥት ዑደት ገና ናት። የዚህ ምክንያቱ የተቃርኖ ትርክት ዋጋ እያስከፈለን ነው።
መውጫ መንገዶች …
“መነጠል ያጎድላል፣ ወንድማማቾች ነን፤ ትስስር ያዋጣል፤ የተበታተነ አቅማችንን ማሰባሰብ ብንችል ተዓምር እንሰራለን። ያለፈው ትውልድ የሠራልን ለዛሬ ስንቅ የሚሆን ብዙ ነገር አለን፤ ካለፈው ተምረን፣ ዛሬ ጥሩ ሠርተን ነገን የተሻለ እናደርጋለን። ከትናንት በተቀበልነው ላይ አሻሽለን ለልጆቻችን እናስረክባለን፤ ሁል ጊዜ መማር፣ መሻሻል፣ ማደግ“ የመደመር ትርክት እሳቤዎች ናቸው ሲሉ ዶ/ር ቢቂላ ያብራራሉ።
ትርክት ያድናል፣ ትርክት ይገድላል በማለት የትርክትን ሁለት ተቃራኒ ገጽታዎች የጠቀሱት ዶ/ር ቢቂላ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የትርክት መዛነፎች በርካታ ጉዳቶች እያስከተሉ ስለመሆኑ በማንሳት፤ በአገራችን ብቻውን ተፍጨርጭሮ የፈለገበት ሊደርስ የሚችል የኅብረተሰብ ክፍልም ሆነ ቡድን የለም፤ የተጀመረው ለውጥ የኢትዮጵያን ስብራቶች በሚጠግን መንገድ እንዲጓዝ ሁላችንም ኃላፊነት አለብን፤ ለኢትዮጵያ መድሃኒት የሆነው ትርክት ወንድማማችነት፣ እህትማማችነትና አብሮነት እንደሆነ በአጽንኦት ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት ‘ከዕዳ ወደ ምንዳ’ በሚል ርዕስ በተካሄደ የውይይት መድረክ ላይ “ሁሉም ነገር የትርክት ውጤት ነው። ትርክት አገር ለመገንባትም፣ ለማጥፋትም ከፍተኛ አቅም አለው። አዎንታዊ መስተጋብርን መምረጥ የተሻለች ኢትዮጵያን
ለማየት ያግዛል። ልክ እንደ ሕግ የምንቀበላቸው ሕግ ያልሆኑ በሰው አዕምሮ ውስጥ እንደ ትርክት የተወሰዱ መፈተሽ ያለባቸው በጣም በርካታ ጉዳዮች አሉ። አንዱ ስለ አገራችን ያለን እይታ ነው” ብለዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ጸጋ በትክክልና በአግባቡ ለመጠቀም ተግተን ከሠራን ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሰች አገር መገንባት እንችላለን። ይህን እውን ለማድረግ በሁሉት መንገድ ትርክትን መገንባት እንችላለን። አንደኛው በመገናኛ ብዙሃን፣ ሁለተኛው በትምህርት ቤቶች አማካኝነት።
በየዘመኑ የነበረው ውጤት በዘመኑ የነበረው ትውልድ ድል ነው። አሁን የሚሠራው ታሪክም ለልጆቻችን መስፈንጠሪያ መነሻ ኃይላቸው ነው። ታሪክን ማዛባት ልማድ የሆነበትን ፖለቲካ ማጽዳት ያስፈልጋል፤ ሁሉንም ነገር በእውነት እና በልኩ ማስቀመጥ ያስፈልጋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያየ ብሔር እና ማንነት ስላለ ያለው ብቸኛው አማራጭ አብሮ መኖር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንንም አምኖ በመቀበል
በአገሪቷ ሰላም ማስፈን ያስፈልጋል ብለዋል። የማያግባቡንን ነገሮች መተው፣ በሚያግባቡን ጉዳዮች ላይ በመሥራት የራሳችንን ትርክት መገንባትና መፍጠር እንደሚገባም እንዲሁ።
በአገራችን “ሁለንተናዊ ለውጥ የምናመጣው የራስን በማጉላትና የሌላውን በማኮሰስ ሳይሆን የራስን ማክበርና የሌላውንም አምኖ መቀበል ሲቻል ነው። የወል የሆነ ተረክ፣ የወል የሆነ ሀሳብ፣ የወል የሆነ ትርክት መፍጠር ስንችል አገራችንን እናሻግራለን”።
እያንዳንዱ የኢትዮጵያን ለውጥ የሚፈልግ መሪ ብዝሃነትን፣ አብሮነትን፣ እኩልነትን፣ ማንነቶችን መቀበል ይኖርበታል። መቆም ያለብን በጋራ፣ በሰላም፣ በፍቅር አብሮ ለመኖር ነው። በዚህ መልክ ከሠራን የልጆቻችን ኢትዮጵያ መልክ አሁን ካለው በእጅጉ የተለየ እና ያማረ እንደሚሆን በልበ ሙሉነት መግለጽ ይቻላል።
የመደመር መንግሥት መጽሐፍ ስለ ትርክት. . .
የመደመር መንግሥት የተሰኘው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) 4ኛ መፅሀፍ በርካታ አገራዊ ጉዳዮችን በማንሳት ሰፊ ትንታኔዎችን አቅርቧል። መጽሐፉ “አማራጭ ዕይታ፤ የጋራ ትርክት“ በሚለው ንዑስ ርዕሱ ትርክትን የተመለከቱ ሀሳቦችን እንዲህ አንስቷል።
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
የፖለቲካችን አንዱና ዋንኛው ክፍተት ከመታገያ አጀንዳችን ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ በማብራራት ጀምሮ የጋራ አጀንዳን በመፍጠር አጠቃላይ ሕዝቡን አስተባብሮ በመምራት ረገድ ክፍተት አለበት። ማንነት ላይ የሚያተኩር፣ ከትልቅ አሰባሳቢ ጉዳይ ይልቅ ለልዩነት ቦታን የሚሰጥና አለመግባባት የሰፈነበት ነው።
በመጠፋፋት ላይ የተመሰረተው የሁለቱ ጫፍ ፖለቲካ፣ በሀሳብ ገበያው እኩል ቀርቦ የመወዳደር ፍላጎት አይታይበትም። ከዚህም በላይ ይህ በማንነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ፣ ሌላ ተጨማሪ አማራጭን ይዞ በመምጣት ረገድ ክፍተት አለበት። ፖለቲካችን ከአለመረጋጋት ወጥቶ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚያስችል እንዲሆን፣ አግላይ ከሆነ የማንነት ፖለቲካ መውጣት አለበት። ፖለቲካችን የአማራጭ ሀሳቦች እጥረት ብቻ ሳይሆን፣ ዋልታ ረገጥ ማንነት ላይ የተመሰረተም ነው።
ፖለቲካችን ሁሉን ሊያቀራርብ በሚችል አማራጭ ትርክት እጥረት በሁለቱ ዋልታ ረገጥ ትርክቶች ሽኩቻ ይናጥ ነበር። ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማረጋገጥና የጋራ ግብን አንግበን በጋራ ጥረት ወደ ብልጽግና ለማምራት፣ በፅንፍና ፅንፍ ያሉ ትርክቶችን ሊያስታርቅ የሚችል ሦስተኛ አማራጭ ትርክት ያስፈልጋል።
ሐሳብ በፖለቲካ ውስጥ የፍላጎት መገለጫና እነዚህን ፍላጎቶች ማሳካት የሚቻልበትን መንገድ የሚተነትን ነው። መደመር ከአክራሪ ማንነቶች በመውጣት በሐሳብ ላይ የቆመ ፖለቲካን ይከተላል። መደመር የሰው ልጆችን ፍላጎቶች ማለትም የኃብት፣ የክብርና የነጻነት ፍላጎቶችን መሰረት ያደረገ ነው። እነዚህን ለማሟላት ደግሞ
የራሱን አማራጭ ይዞ ቀርቧል። ብልጽግና የእነዚህ ሰብዓዊ ፍላጎቶች መሟላት ውጤት ነው።
ብሔራዊ ትርክት በነጻነት፣ በእኩልነትና በወንድማማችነት፣ በእህትማማችነት ላይ የተመሰረተ ነው። አቀራራቢ በሆነ ታሪክ ላይ ይገነባል። የትናንትን ብቻ ሳይሆን የዛሬን አብሮነትና የነገ የጋራ ዕጣ ፈንታችንን የሚያመለክት ነው።
ወደ ሐሳብ ገበያ በምናደርገው ጉዞ፣ ለፖለቲካ ገበያ በር የሚከፍቱ ያለፉ ስብራቶቻችንን መጠገንና መሻገር ያስፈልገናል። ለሀሳብ ገበያ መሰረትን ለመጣልና ስብራቶችን ለመጠገን የሚያስችል ብሔራዊ መግባባት የሚያመጣ ምክክር አስፈላጊ ነው።
ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና የተረጋጋ ፖለቲካ ብልጽግናን ለማረጋገጥ መደላድል ነው። ልዩነት በአግባቡ አለማቻቻልና መከፋፈል ብልጽግናን ለማምጣት እንቅፋት ነው። ምክንያቱም በትብብርና በውድድር መካከል ሚዛን ከመጠበቅ ይልቅ ያልተገባ ሽኩቻን ይፈጥራል። ሕዝብን በአንድ ላይ አስተባብሮ ወደ ብልጽግና ዓላማ ለመምራት አዳጋች ይሆንበታል። የፖለቲካ ኃይሎች፣ የተለያዩ ማንነቶች እንዲሁም በአጠቃላይ ማኅበረሰቡ ለአንድ ከፍ ላለ ዓላማ ከመቆም ይልቅ ለአነስተኛና ለአንጻራዊ ጥቅም ፉክክር ውስጥ እንዲገባ በማድረግ ኃይል ይበትናል።
በተጨማሪም፤ ልዩነትን የሚፈጥረው ሽኩቻ ትብብርን ከማጥፋት ባሻገር ያልተረጋጋ ፖለቲካዊ ሁኔታና የሰላም መደፍረስ ይፈጥራል። በመሆኑም የመንግሥት ትኩረት፣ አቅምና ሀብት እንዲበታተን በማድረግና ፍጥነትን በመቀነስ፣ ብልጽግና ሊረጋገጥ የሚችልበት ጊዜ እንዲራዘም ያደርጋል።
ብሔራዊ መግባባት የአገራችን ለውጥ ማነቆዎች የሆኑ ጉዳዮችን የምንፈታበት መንገድ ነው። የረጅም ጊዜ ችግሮቻችንንና ስብራቶቻችንን በመጠገን በአንድ ላይ ወደ ፊት የምንሻገርበት መንገድ ነው። በፖለቲካ ወደ ፊት ሳይሻገሩ በኢኮኖሚ ሙሉ ለሙሉ ወደፊት መሻገር የማይታሰብ ነው።
አገራዊ ምክክር፤ በአንድ በኩል አንድነትና ኅብረትን በማጠናከር ልሂቃንና ሕዝብ ለአንድ ከፍ ላለ ዓላማ በአንድ ላይ እንዲቆሙ ያደርጋል። በዚህም ጥረቶች ሁሉ በአንድ አቅጣጫ እንዲፈሱ ያደርጋል። በሌላ በኩል ፖለቲካዊ መረጋጋትና ሰላምን በመፍጠር የመንግሥት ትኩረት፣ ሀብትና ጊዜ ሳይበታተን ብልጽግናን ለማረጋገጥ ብቻ እንዲውል ያደርጋል።
መደመር አገርን ከገባችበት ችግር በማላቀቅ ወደ ትክክለኛው የለውጥ ምሕዋር የሚመራ ዕሳቤ ስለመሆኑም በመጽሐፉ ተብራርቷል። የመደመር መንግሥት፣ አገራዊ ጸጋዎቻችንን በማቀናጀትና በማስተባበር ረገድ ካለው ሚና ባልተናነሰ በፍጥነት የምንጓዝበትንም መንገድ
የቀመረ አስተሳሰብ ነው።
ነገን የተሻለ ለማድረግ የትናንት፣ የዛሬና የነገ ተደራራቢ ኃላፊነቶቻችንን በአስቸኳይ እንድንወጣ ያደርጋል። እንዲሁም ተለዋዋጭ በሆነው የዓለም ሁኔታ ውስጥ ጥንካሬያችንን ለማረጋገጥና ከግባችን ለመድረስ እንድንፈጥን ያስችላል። የመደመር መንግሥት ፍጥነትና ፈጠራን መሰረት ያደረገ እሳቤም ነው።
የመደመር መንግሥት የመፍትሔውን መንገድ ውሱንነት ለማረምና ዘገምተኛውን ጉዞ ለማፍጠን የሚችል ቀመር ሆኖ መምጣቱም በመጽሐፉ ተብራርቷል። ከመደመር እሳቤ የሚቀዳው የመደመር መንግሥት ኢትዮጵያዊ የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ እሳቤ ነው። ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ የሚቻለው ትብብርን ያስቀደመ ሥርዓት በመዘርጋትና ፖሊሲዎችን ገቢር ነበብ በሆነ መንገድ አውጥቶ በቅንጅት በመተግበር ነው።
የትርክት ምንጮች
ክፍተቶችና አጋጣሚዎች
ያለፍንበት መንገድ ውጣ ውረዶች
ታሪኮችና አፈ ታሪኮች
መረጃዎች ስኬቶችና ፈተናዎች
ውድድሩን የማሸነፍ ምርጫ …
ማኅበራዊ
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
በመንገሻ ገ/ሚካኤል
ጥራት (Quality) ትልቅ ሳይንስ ነው። በርካታ ትምህርቶች በተለያዩ የትምህርት ተቋሟት ይሰጣሉ፤ በጣም ትልልቅ መጽሐፍትም የተጻፉበት ጽንሰ ሀሳብ ነው - ጥራት። የጥራትን ምንነት ለመግለጽ ብሎም ለመመዘን የሚያገለግሉ የተለያዩ ዘዴዎች አሉ። እነዚህ ጥራትን ለመግለጽ እንዲሁም ለመለካት የሚጠቅሙ መመዘኛዎች እንደሚሰጠው አገልግሎት ወይም እንደሚመረተው ምርት ዓይነት ይወሰናሉ። ተገልጋዩም ጥራት ያለው አገልግሎት አገኘሁ ለማለት፣ ተቋምም ጥራት ያለው አገልግሎት ሰጠሁ ማለት የሚችለው የተለያዩ መለኪያዎችን ሲያሟላ ስለመሆኑ ብዙኃኑን የሚያስማማ ነጥብ ነው።
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሁለት የጥራት ምሰሶዎች እንዳሉ ይገለጻል፤ አንደኛው ሥራን ሁልጊዜ በትክክል መሥራት ሲሆን ሁለተኛው ሁልጊዜ የተሻለ የአሠራር መንገድን መከተል ነው። ሁለቱ የጥራት ምሰሶዎች በትይዩ እና አቻ በአቻ መተግበራቸው ውጤታማ አፈጻጸም ላይ ለመድረስ ወሳኝ ነው።
ጥራትን ለማስጠበቅ ከሚገፉን ምክንያቶች የመጀመሪያው፣ ደንበኛው የመጠየቁ ጉዳይ ነው። ደንበኛ ሁልጊዜ የሚፈልገውን ይጠይቃል። ይህም ደንበኛው ገበያውን እንዲመራው ወይም ደንበኛ ተኮር የሆነ ሥርዓት እንዲኖር ወይም እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል። አገልጋዩን ወይም አምራቹን ወደ ፉክክር በማስገባት ለለውጥ እንዲሠራ እንደሚያነሳሳ ይታመናል።
ዓለም በሉላዊነት አንድ በሆነችበት በዚህ ዘመን በአንዱ የዓለማችን ክፍል የሚከናወን ተግባር፣ የሚሰጥ አገልግሎት፣ ምርት እና አገልግሎት ወደ ሌላው ተደራሽ ለማድረግ በርካታ ምቹ ሁኔታዎች አሉ። ይህ የሉላዊነት በጎ አስተዋጽኦ እንዳለ ሆኖ በተቃራኒው የሚያጋጥሙና
እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችም አሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳው አንደኛው ነጥብ በዓለም ምርት እና አቅርቦት ሰንሰለት እንዲሁም አገልግሎት አሰጣጥ በጥራት እና ቅልጥፍና እኩል ተወዳዳሪ ሆነው ባልተገኙት ላይ የሚፈጥረው አሉታዊ ተጽዕኖ ነው።
ይህን ሁኔታ በቅጡ የተገነዘቡ አካላት ለዚህ ሁነኛ መፍትሔ አበጅተዋል፤ መፍትሔውም ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን በማዘጋጀት ብቁ ሆነው ለሚገኙ እውቅና በመስጠት በዚህ የዓለም መድረክ ላይ ንቁ ተሳታፊ ሆነው እንዲዘልቁ ማስቻል።
እነዚህ መመዘኛዎች በዓይነታቸው የተለያዩ ሲሆኑ ተቋማት ወይም ባለሙያዎች እንደሚሰጡት አገልግሎት፣ እንደ ሙያ መስካቸው እንዲሁም እንደሚያመርቱት ምርት የሚስማማቸውን መርጠው የሚተገብሩበት በሂደቱም የሚያስፈልገውን ቅድመ ሁኔታ አሟልተው እውቅና የሚያገኙበትን አሠራር ይተገብራሉ።
በዓለማችን ተግባራዊ ከተደረጉ ዓለም አቀፍ መመዘኛዎች መካከል ISO 9001፣ ISO 14001 ፣ ISO 22000፣ ISO፣ ISO 27001፣ ISO 50001፣ ISO 13485፣ ISO 22301፣ ISO 21001 እንዲሁም፣ ISO 41001 እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ። ተቋማት እና ግለሰቦች እነዚህን በተናጠል ወይም በቅንጅት እያንዳንዳቸው የሚጠይቋቸውን መመዘኛዎች በሟሟላት እውቅና ይሰጣቸዋል። እነዚህ ዓለም አቀፍ መመዘኛዎች የየራሳቸው ዓላማዎች እና የትኩረት መስኮች
አሏቸው።
የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት (ISO 9001) ምንድን ነው?
የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት (Quality Management System - ISO 9001) አንዱ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ የተደረገ የጥራት ማስጠበቂያ ስልት ነው። የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት የሥልጠናና ድጋፍ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መንግሥቱ ተፈራ ጥራት የሚለካባቸው የተለያዩ ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊ እና የኩባንያ ደረጃዎች እንዳሉ ይገልፃሉ። ከእነዚህ ዓለም አቀፍ ደረጃዎች የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት (ISO 9001) አንዱ ነው። የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት (ISO 9001) በዓለም ላይ በስፋት ተግባራዊ የተደረገ የጥራት ሥራ አመራር ደረጃ ነው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ድርጅቶች የISO 9001 የምስክር ወረቀት (Certificate) ተጠቃሚዎች ናቸው። የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት (ISO 9001) ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው መስፈርት ሲሆን የምርቶች ወይም የአገልግሎቶች ጥራት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዲኖረው ያስችላል። አገልግሎቱ ወይም ምርቱ ደንበኛን በሚያረካ መልኩ የአሠራር ሥርዓትን ተከትሎ እንዲከናወን የሚያስችል ሂደትም ነው።
አንድ ተቋም ወይም አምራች ጥራትን ለማረጋገጥ በተለይ ደግሞ ምርቱን ወጥ በሆነ መንገድ ለማምረት የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት ተግባራዊ የሚያደርግ መሆኑን አቶ መንግሥቱ ይናገራሉ። አንድ ምርት ወይም አገልግሎት
በአያያዝ፣ በአቅርቦት ወይም በባለሙያ ምክንያት ሊበላሽ ይችላል፤ ይህንን ለማስቀረት የጥራት ሥራ አመራር ደረጃዎችን ተግባራዊ ማድረግ አንዱ አማራጭ ነው ይላሉ።
የጥራት ሥራ አመራርን መተግበር አንድ ምርት ወይም አገልግሎት ወጥነት እንዲኖረው ያስችላል። አንድ አምራች ወይም አገልግሎት ሰጪ ተቆጣጣሪም ቢሆን የሚሰጠው አገልግሎት ወይም የሚያደርገው ቁጥጥር ወጥነት አለው ማለት የሚቻለው እንደዚህ ዓይነት ደረጃዎችን በመተግበር ነው። እነዚህ ደረጃዎች በሦስተኛ ወገን ተፈትሸው ሲረጋገጡ አንድ ተቋም እውቅና ያገኛል።
የጥራት ሥራ አመራር መርሆች
ደንበኛ ተኮር (Customer Focus)
የISO 9001 የመጀመሪያው መርህ ደንበኛ ተኮር መሆን የሚለውን ነው። ደንበኞች የውስጥና የውጭ ደንበኞ ተብለው ሊከፈሉ ይችላሉ፤ ደንበኛ ተኮር ማለት ደንበኞን ለማርካት፣ የደንበኞችን ፍላጎት በመለየትና በማወቅ ፍላጎታቸውን ለማሟላት የሚሠራ መሆን አለበት። ይህን ማድረግ ሲችል የጥራት ሥራ አመራር ተተገበረ ይባላል።
አመራር (leadership)
ደንበኛ ተኮር ለመሆን ቁርጠኝነት ያለው መሪነት ያስፈልጋል። በተለይም ከፍተኛው አመራር ጥራትን ለማረጋገጥ ቁርጠኛ መሆን አለበት። ጥራትን ማስጠበቅ ከፍተኛ ወጪ ያስወጣል ከሚል የተሳሳተ አመለካከት የፀዳና ጥራቱን የጠበቀ ምርትና አገልግሎት ማቅረብ ወጪ ሳይሆን ከፍተኛ ገቢም እንደሚያስገኝ የሚገነዘብ አመራር የጥራት ሥራ
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
አመራርን ለመተግበር ወሳኝነት አለው። ጥራቱን ያልጠበቀ ምርትና አገልግሎት ኪሳራን ያመጣል። የጥራት ሥራ አመራርን ለመተግበር ዋናውን ሚና የሚጫወተው የበላይ አመራር ሲሆን ይህም ጥራትን ለማስጠበቅ ወሳኝነት አለው። ሥራዎችን በጥራት ሥራ አመራር መርሆችና መስፈርቶች መሰረት መምራት ከተቻለ አንድ ተቋም ውጤታማ ይሆናል።
ተሳትፎ (engagement of
የጥራት ሥራ አመራርን ለማረጋገጥ ከበር እስከ ወንበር ማለትም ከታችኛው የጥበቃ ሠራተኛ እስከ ላይኛው ከፍተኛው አመራር መሳተፍ አለበት። የጥራት ሥራ አመራር በአንድ ሰው ወይም በአንድ ክፍል ብቻ የሚተገበር አይደለም። የተቋሙን ሠራተኞች አጠቃላይ ተሳትፎ ይጠይቃል። የጥራት ሥራ አመራር ሲባል ደንበኛ ተኮር ሥርዓት ከመዘርጋት ጋር የተያያዘ ሲሆን ይህ ሥርዓት መጀመር ያለበት በር ላይ ካለው የጥበቃ ሠራተኛ ይሆናል። ደንበኛ ተኮር ሲባል በር ላይ ያለው ጥበቃ ደንበኞችን ያከብራል ወይ? የሚለው እንደ አንድ መመዘኛ ይወሰዳል። የጥራት ሥራ አመራርን ለማረጋገጥ የምልዓተ ሠራተኛ ተሳትፎ ግድ ይላል።
ሂደት ተኮር (process approach)
በአንድ ተቋም ውስጥ የሚገኙ የሥራ ክፍሎች የተቋሙን ደንበኞች ፍላጎት ማሰብ መቻል አለባቸው። በሥራ ክፍል መታጠርን ማስወገድ ይገባል። የሥራ ክፍሎች እርስ በእርሳቸው አንዱ አቅራቢ አንዱ ተቀባይ ሆነው የሚያገለግሉ ሲሆን በሰጪና ተቀባይ መካከል የሚኖረው ግንኙነት ደንበኛን ማዕከል ያደረገ ይሆናል።
ሂደት ተኮር ሲባል የምርት እና አገልግሎቱን የመጨረሻውን ተጠቃሚ እያሰቡ መሥራት ነው። አንድ ምርት ለማምረት የምንጠቀምበት ግብዓት ጥራቱን የጠበቀ ካልሆነ የሚሰጠን ውጤትም በዚያው ልክ ጥራቱ የተጠበቀ አይሆንም። በሂደት ተኮር አስተሳሰብ ደንበኛን የሚያረካ ሥራ ለመሥራት ከመጀመሪያው ጥሬ ዕቃ ቅበላ ጀምሮ አልቆለት ደንበኛው ጋር እስከሚደርስ ያለውን ሂደት መከታተልን ያካትታል። “የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው” የሚል አገርኛ አባባል በጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት ተቀባይነት የለውም። በጥራት ሥራ አመራር እሳቤ አንድ ምርት የሚመረትበት ሂደት በጥራቱ ላይ ወሳኝነት አለው።
መሻሻል (improvement)
ዓለማችን አሁን ያለችበት የቴክኖሎጂ ልህቀት ላይ የደረሰችው በየጊዜው በተመዘገቡ ትንንሽ ለውጦች አማካኝነት ነው። በISO 9001 የጥራት ሥራ አመራር እሳቤም ጥራት በአንድ ጊዜ የሚረጋገጥ ጉዳይ አይደለም። በአንድ ተቋም ጥራትን ለማረጋገጥ በየጊዜው መሻሻልን ይጠይቃል። አንደኛውና ዋነኛው የመሻሻል መገለጫው ስህተትን አለመድገም ነው። አንድ ጊዜ የሠራውን ስህተት መልሶ የሚደግም ተቋም የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት ተግብሯል ማለት አይቻልም። ስህተት ሲያጋጥም የሚያርምበትና የተሻለ ደረጃ ላይ የሚደርስበትን አሠራር ማበጀት ይኖርበታል። በጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት አንድ ተቋም ስህተቱን የሚያርምበት መመሪያዎች እንዲያዘጋጅ ይገደዳል። ISO 9001 የጥራት ሥራ አመራር ሁልጊዜ መሻሻልን ይጠይቃል።
መረጃ ላይ ያተኮረ ውሳኔ አሰጣጥ
በጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት ከማይፈቀዱ ነገሮች አንዱ በመረጃ ያልተደገፈ ውሳኔ መስጠት ነው። የሥራ ኃላፊዎች የትኛውም ዓይነት ውሳኔ በሚያሳልፉበት ጊዜ መረጃዎች ተጠንተውና ተተንትነው ሊቀርቡላቸው ይገባል። በተለይም እንደ ተቋም የሚወሰኑ ውሳኔዎች በጥናት ላይ የተመሰረቱ መሆን አለባቸው።
የውጭ ግንኙነት ማኔጅመንት (relationship management)
ተቋማት ብቻቸውን የሚቆሙ ባለመሆናቸው ከሌሎች አካላት ጋር በመሆን ለደንበኛ አገልግሎት የሚሰጡበት ሁኔታ ይኖራል። ቢያንስ በትንሹ አቅራቢዎች ይኖሯቸዋል። ለምሣሌ ጥሬ ዕቃ
አቅራቢው ጥሬ ዕቃውን ጥሩ አድርጎ ማቅረብ ካልቻለ የመጨረሻው ውጤት የተሻለ ይሆናል ተብሎ አይታሰብም። በመሆኑም ጥሬ ዕቃ አቅራቢውም ይሁን መሃል ላይ ዕቃውን ወስዶ እሴት ጨምሮ ለደንበኛ የሚያስረክበው አካል ጋር ጥሩ ግንኙነት መመስረት አንዱ የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት መርህ ነው። እውቅና ከተሰጠው ተቋም ጋር የሚሠሩ ድርጅቶች የጥራት ሥራ አመራርን ተግባራዊ ያደረጉ እንዲሆኑም ይመከራል።
የISO 9001 የጥራት ሥራ አመራር ፋይዳዎች
ISO 9001 የጥራት ሥራ አመራር በተቋም ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የጋራ መግባቢያ
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
ቋንቋ መፍጠር ችለዋል። በአሁኑ ጊዜ በተለይም በዓለም አቀፍ ገበያ ለሚሳተፉ ድርጅቶች የISO 9001 የምስክር ወረቀት መያዝ ማለት ለደንበኞች፣ ለአጋሮች እና ለባለድርሻ አካላት ለጥራት ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል ማለት ነው። በአንድ ተቋም የጥራት ሥራ አመራር ተግባራዊ ማድረግ መልካም አሠራርን ለማስቀጠል ያስችላል። በእያንዳንዱ የምርት ሂደት ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ቀጣይነት ያለው የለውጥና የምርት ማሻሻያ ሥርዓት እንዲኖር በማድረግ ጥራት ያለው ምርት ለማምረት ያስችላል።
የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት የሥልጠናና ድጋፍ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መንግሥቱ ተፈራ የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓትን ተግባራዊ ማድረግ ጠቀሜታው ዘርፈ ብዙ ነው ይላሉ። ምርት ወይም አገልግሎት አቅራቢዎች የጥራት ሥራ አመራርን ሲተገብሩ
በደንበኞቻቸው ዘንድ የላቀ ታማኝነት ይኖራቸዋል። በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ በርካታ ተቋማት በISO 9001 እውቅና ያገኙ ሲሆን እስከ 2017 ዓ.ም (እ.አ.አ) በነበረው ጥናት በቻይና ብቻ 393 ሺህ ተቋማት በዚህ ደረጃ ዕውቅና አግኝተዋል። በዚህም ቻይና በISO 9001 የጥራት አመራር ተግባራዊ ማድረጓ ለኢኮኖሚያዊ ዕድገቷ የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል።
የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት መተግበር የምርትና የአገልግሎት አሠጣጥ ጥራትን በማሳደግ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን ያስችላል የሚሉት አቶ መንግሥቱ ዓለም አቀፉን ገበያ ሰብሮ ለመግባት የጥራት ሥራ አመራር ደረጃዎችን መተግበር የግድ ነው ይላሉ። በአሁኑ ጊዜ የምርት ሰንሰለቱ በደንበኞት ፍላጎት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ አምራቾችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በደንበኞች ምርጫ ብቻ ከገበያ ውጪ የሚሆኑባቸው አጋጣሚዎች ይስተዋላሉ። ከፍተኛ የንግድ ውድድር በተፈጠረበት የዘመነ ግሎባላይዜሽን ጥራት ብቸኛ የማሸነፊያ መንገድ ሆኖ ተከስቷል።
የጥራት ሥራ አመራር ተቋማት ቀጣይነት ያለው መሻሻል እንዲኖራቸው ያደርጋል። በፍጥነት ተለዋዋጭ በሆነው ዓለም ውስጥ ወሳኝ የሆነውን የመማር፣ የመላመድና የመሻሻል አስተሳሰብ እንዲላበሱ ያደርጋል። ቅልጥፍና ያለው አገልግሎት ለመስጠት እንዲሁም በሥራ ሂደት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታትም የISO 9001 የጥራት ሥራ አመራርን መተግበር ሁነኛ መፍትሔ ነው። የጥራት ሥራ አመራር አምራቾችና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ንቁ የአደጋ ግምገማ እንዲኖራቸው የሚያበረታታ ሥርዓት በመሆኑ ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት አስቀድመው እንዲያውቁ ያግዛቸዋል።
ISO 9001ን የጥራት ሥራ አመራር ተመራጭ የሚያደርገው ሌላው ምክንያት ግልጽ የአሠራር ሥርዓት መትከል ማስቻሉ ነው። የአሠራር ሥርዓቱ ሥራዎች በዘመናዊ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች እንዲከወኑ ስለሚፈቅድ ግልጽና ጥራት ያለውና ሁሉም የሚተማመንበትን ሥርዓት እንዲዘረጉ ጠቅሟቸዋል። ደንበኞቻቸውም በየዕለቱ ስለሚቆጣጠሯቸው አሠራራቸውን በየወቅቱ ለመፈተሽ ይረዳቸዋል።
ሥራን በውዴታና በተነሳሽነት እንዲተገበር ማድረጉም ሌላው የISO 9001 ትልቁ ፋይዳ ነው። በጥሬ ዕቃ ግዥና አቅርቦት እንዲሁም በማምረት ሂደት የሚኖርን ሥጋት በሥርዓት ለመፍታት ከማገዙ ባሻገር በምርቶች ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ ለሚችሉ የውስጥና የውጭ ተግዳሮቶች በቀላሉ ምላሽ መስጠት ያስችላል።
የISO 9001 የጥራት ሥራ አመራር ወጥነት ያለው ምርት ለማምረት ይረዳል። በአንድ ፋብሪካ ወይም አገልግሎት ሰጪ ተቋም ውስጥ የሚሰጡ አገልግሎቶች ወይም የሚቀርቡ ምርቶች ወጥነት እንዲኖራቸው ማድረግ የሚቻለው እንዲህ ዓይነት የአመራር ሥርዓቶችን መተግበር የምንችል ከሆነ ብቻ ነው የሚሉት አቶ መንግሥቱ፤ አሁን ያለው የገበያ ውድድር ዋጋ ላይ ብቻ ያተኮረ አይደለም። ደንበኞች ጥሩ ጥራት ያለው፣ በጊዜው የሚቀርብና ዝቅተኛ ዋጋ ያለው ምርትና አገልግሎት ይፈልጋሉ በመሆኑም የእነዚህን ደንበኞች ፍላጎት ለማሟላት የጥራት ለውጥ አመራር መተግበር ግድ ይላል። የጥራት ሥራ አመራር በሂደት የተመሰረተ ስለሆነ ምርትና አገልግሎቶችን በጊዜው ለማቅረብ፣ ዋጋ ለመቀነስና ጥራትን ለማስጠበቅ ያስችላል። ከፍተኛ ፉክክር ባለበት ገበያ አሸንፎ ለመውጣትና ቀጣይነት ያለው ተቋም ለመመስረት የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት መተግበር የግድ ይላል።
የጥራት ሥራ አመራር ትግበራ በኢትዮጵያ
ኢትዮጵያ በተለያዩ ዓለም አቀፋዊ የጥራት ሥራ አመራር ደረጃዎች ተሳታፊ ናት። ከእነዚህ ደረጃዎች መካከል የISO 9001 የጥራት ሥራ አመራር ደረጃ አንዱ ሲሆን የISO 9001 አባልም ናት። ዓለም አቀፍ ደረጃዎች በሚዘጋጁበት ጊዜ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት አንዱ ተሳታፊ ሲሆን እ.አ.አ በ2015 ዓ.ም በተሻሻለው የISO 9001 የጥራት ሥራ አመራር ዝግጅትን ተሳትፋለች።
በኢትዮጵያ የጥራት ሥራ አመራር ትግበራን አስፈላጊነት በሚመለከት የተሻለ ግንዛቤ መፈጠሩን ያወሱት አቶ መንግሥቱ፤ በኢትዮጵያ ደረጃ እስከአሁን የጥራት ሥራ አመራር አስገዳጅ ባይደረግም አንዳንድ ተቋማት በፍላጎታቸው የጥራት ሥራ አመራርን ተግባራዊ ማድረግ
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
ጀምረዋል።
የውጭ ግንኙነት ያላቸው ተቋማት በሰፊው እየመጡ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ሥልጠናና ድጋፍ እየሰጠ ለሰርተፊኬሽን እንዲበቁ እያደረግን ነው የሚሉት አቶ መንግሥቱ፤ በተለይ የግብርና ምርቶችን ወደ ውጭ የሚልኩ አካላት የጥራት ሥራ አመራር ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን አንስተዋል።
በተለይ የውጭ ደንበኞች ላሏቸው አምራቾችና አገልግሎት ሰጪዎች የጥራት ሥራ አመራር መተግበር አስገዳጅ ቅድመ ሁኔታ ነው። ለምሣሌ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን የኢትዮጵያ መርከቦች በየትኛውም ዓለም መንቀሳቀስ እንዲችሉ የISO 9001 መመዘኛን አሟልቶ እውቅና ማግኘት ግድ የሚለው በመሆኑና ሥራውን የሚያከናውነውም በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ካላቸው አካላት ጋር በመሆኑ በእነሱ ደረጃና ልክ ሆኖ ለመገኘት የሚጠበቅበትን የቤት ሥራ አከናውኖ እውቅናው ተሰጥቶታል።
በአገራችን ISO 9001 ተግባራዊ ካደረጉ ተቋማት መካከል የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር አንዱ ነው። ነሐሴ 30 ቀን 2017 ዓ.ም የእውቅና ምስክር ወረቀት በተቀበለበት ወቅት ሚኒስትሯ ሙፈሪሃት ካሚል እንዳሉት ተቋሙ የዘርፉን ተልዕኮ ማሳካት የሚያስችሉ የለውጥ ሥራዎች ሲተገብር ቆይቷል። የለውጥ መሣሪያዎችን አሰናስኖ በመጠቀም ተጨባጭ ውጤት ማግኘቱን፤ በጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት የተቀመጡ መስፈርቶችን ለማሟላት በትጋት ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰው ዓለም አቀፍ ዕውቅናውም ተቋሙን ለበለጠ ትጋት የሚያነሳሳ መሆኑን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ተቋማት ጥራትን የመለያ መንገዳቸው በማድረግ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪና ተቀባይነት እንዲኖራቸው ሁላችንም መትጋት አለብን ያሉት ሚኒስትሯ፤ ሥራን በብቃትና በጥራት መከወን ጊዜው የሚጠይቀው አርበኝነት መሆኑን፤ የተገኘው ዕውቅና የቴክኒክና ሙያ ሥራን ጨምሮ ተቋማቸው የሚያከናውናቸውን ተግባራት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ እንደሚያስችል ተናግረዋል። በቀጣይም በጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት የተቀመጡ መስፈርቶችን በማሟላትና ወጥነት ያለው አገልግሎት በመስጠት የደንበኞችን እርካታ ለመጨመር ሁሉም እንዲተጋ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ሌላው በአገራችን እውቅና ያገኘ ተቋም የአዲስ አበባ ተግባረ ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ሲሆን እውቅናውም የተሰጠው በ2016 ዓ.ም ነው። ኮሌጁ በዘርፉ የላቀ አበርክቶ ያለውና በመዲናዋ በአንጋፋነቱ የሚጠቀስ ተቋም እንደመሆኑ በቴክኖሎጂና በኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ሙያተኞችን በማሠልጠን ከከተማዋ ባለፈ ለአገር ልማትና ዕድገት ባለውለታ ስለመሆኑ ይገለጻል።
የጥራት ሥራ አመራር እውቅና የምስክር ወረቀት ማግኘቱ አገልግሎቱንና ተወዳዳሪነቱን ይበልጥ እንዲያሳድግ እንደሚያግዘውና የሚያሠለጥናቸውን ባለሙያዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ይበልጥ ተፈላጊ እንደሚያደርጋቸው ይታመናል። ኮሌጁ የISO 9001 መመዘኛዎችን መሰረት አድርጎ መሥራቱ የቴክኖሎጂ ኤክስቴንሽን ክንውኖች ጥራታቸውን ጠብቀው የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጡ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። የአሠራር ሥርዓቱ ብክነትን በመቀነስ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመርና ወጥ የሆነ አሠራር
ለመከተል ብሎም ለላቀ ሥራ የሚያነሳሳ ነው።
በሌላ በኩል የቱሪዝም ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚሰጡ እውቅናዎች መካከል አንዱ የሆነውን ISO-21001 መተግበር ጀምሯል። ኢንስቲትዩቱ በወርሃ መስከረም 2018 ዓ.ም በትምህርት ሥራ አመራር ሥርዓት ISO 21001 ዓለም አቀፍ ዕውቅና ማግኘቱን ተከትሎ የምስክር ወረቀት ተሰጥቶታል። ይህም ኢንስቲትዩቱ የቱሪዝም ዘርፉን በማነቃቃት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለውን የመማር ማስተማር ሥራ ለማከናወን የሚያስችለው እንደሆነ ይታመናል።
የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መሠረት በቀለ (ዶ/ር) እውቅናው በተሰጠበት መድረክ ቱሪዝም የኢትዮጵያ የማንሰራራት
ዘመን ዋነኛ መሰረት የሚሆን ዘርፍ እንደሆነ አንስተው፤ የሰው ኃብትና የመሰረት ልማት እንዲሁም የአሠራር ሥርዓት መዘመንና መሰናሰን ለአገር ልማትና ዕድገት ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ጠቁመዋል።
እነዚህን አራት ተቋማት እንደ ማሳያ አነሳን እንጂ ሌሎችም የዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን በማሟላት ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ገብተዋል። እነዚህ የዓለም አቀፍ የጥራት አመራር ሥርዓት እውቅናዎች በትክክልም የኢትዮጵያ የማንሰራራት ከፍታ ማሳያዎች ናቸው።
የጥራት ፖሊሲ - ለምን?
በዓለም አቀፉ ገበያ በተለይም በወጪ ምርቶች
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
መዳረሻ አገራት የሚገኘው ሸማች በመረጃ የዳበረና ንቃተ ህሊናዉ ከፍ ያለ ከመሆኑ ባሻገር በምርትና አገልግሎቶች ጥራትና ደህንነት ቁጥጥር የሚያደርጉ ተቋማት ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥጥራቸውን እያጠበቁ ይገኛሉ።
በአንድ ወገን የወጪ ምርት መዳረሻ ገበያዎች በአቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ ብዛት ያላቸውን አገራት በማሳተፍ፣ አገልግሎቶችና ግብዓቶች ጥራታቸውና ደህንነታቸው ተጠብቆ በአነስተኛ ዋጋ፣ በተፈላጊ መጠን፣ በአስተማማኝ ሁኔታና በዘላቂነት እንዲቀርቡላቸው ይፈልጋሉ። በሌላ በኩል ላኪ አገራት ለተመሳሳይ የምርት መዳረሻ ገበያ ተመሳሳይ፣ ጥራቱና ደህንነቱ የተረጋገጠ ብሎም የተቆጣጣሪ አካላትን መስፈርት ያሟላ ምርት፣ አገልግሎት ወይም ግብዓት በማቅረብ በሂደቱ ብቸኛ ተጠቃሚ ለመሆን ውድድሩን አጠናክረውታል።
ስለሆነም አምራቹ፣ አገልግሎት ሰጪውም ሆነ አቅራቢው ቀጣይነቱ የተረጋገጠ፣ ፍላጎት መራሽ፣
ደንበኛ ተኮር፣ ምሉዕ፣ ወጪ ቆጣቢ፣ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን በመቋቋም አገልግሎቱን ማስቀጠል የሚችል፤ የመደገፍ፣ የማብቃትና የቁጥጥር ተልዕኮን ያነገበና የተሰናሰለ የጥራት መሰረተ ልማት ምህዳር ተግባራዊና ተደራሽ ማድረግ ይጠይቃል።
የተናበበ እና የተቀናጀ ርብርብ በማድረግ ወደ ውጤታማነት በመቀየርና አገራዊ ልማቱንና ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ አገራዊ ጥረቶችን የሚያስተሳስር የጥራት ፖሊሲ መኖሩ ታምኖበታል። መንግሥት የጥራት መሰረተ ልማት ሥርዓት በጥብቅ መሰረት ላይ እንዲቆም ካለው ቁርጠኝነት በመነሳት የጥራት ፖሊሲ አዘጋጅቷል።
ፖሊሲው አገራዊ የልማት ግቦችና አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሞች ከግባቸው እንዲደርሱ ውጤታማ፣ ቀልጣፋና የተሳለጠ የጥራት መሰረተ ልማት ሥርዓት በማስፈን በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በአቅም ግንባታና በቁጥጥር ላይ የተግባር ድግግሞሽን እንደሚያስቀር ይጠበቃል።
“ከተናበበ መዋቅራዊ አሠራርና የቴክኒክ ደንብ አፈፃፀም ጀምሮ፣ የደረጃ ዝግጅትና ትግበራ፣ ሥነ ልክ፣ አክሪዲቴሽን፣ የተስማሚነት ምዘና፣ የገበያ ክትትል፣ የአቅም ግንባታ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ፣ የተግባቦት፣ የሥልጠና እና የትምህርት ሥራዎችን በማቀናጀት የጥራት ባህል ግንባታ እንዲያካትት ማድረግ ተገቢ ነው“ በሚል መፍትሔዎችን እና መከናወን ያለባቸውን ተግባራት የዘረዘረው በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ በ2015 ዓ.ም ይፋ የሆነው የኢትዮጵያ የጥራት ፖሊሲ (ረቂቅ) ሰነድ ነው።
ሰነዱ አያይዞም አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታን በቅጡ በመረዳት የኢትዮጵያ መንግሥት የጥራት መሰረተ ልማት ስትራቴጂ ቀርጾ ወደ ተግባር መገባቱን ጠቅሶ አገልግሎቱን የሚሰጡ አካላት የደረጃ፣ ሥነ ልክ፣ አክሪዲቴሽን እና ተስማሚነት ምዘና ተቋማትን ቀዳሚ ትኩረት ሰጥቶ እንዲጠናከሩ እየተሠራ መሆኑን አመላክቷል።
ፖሊሲው ተጠያቂና ተገማች አሠራርን በቀጣይነት በማሻሻል ፍትሃዊ የንግድ ውድድር እንዲሰፍን በማድረግ፤ አገራዊ ምርትና ምርታማነትን በዓይነት፣ በጥራት፣ በመጠን በማሳደግና እሴት በመጨመር የገቢ ምርቶችን መተካት እንዲሁም የወጪ ምርትና አገልግሎትን ተወዳዳሪ በማድረግ አገራዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ይታመናል።
በፖሊሲው ጥራትን ለማስቀመጥ እንደመፍትሔ ከተመላከቱ ነጥቦች መካከል አንደኛው የጥራት መሰረተ ልማት ሥርዓትን ማስፈን ነው። ይህን ተከትሎ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ንግድ ተወዳዳሪ መሆን የሚያስችላትን የጥራት መንደር
መስርታለች። የጥራት መንደሩ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት እና የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለሥልጣንን የያዘ ነው። የጥራት መንደሩ የተገነባው ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶች ጥራትና ደህንነትን ለመቆጣጠርና ለማስጠበቅ ሲሆን፤ የኢትዮጵያን ንግድ፣ የዘርፉን ዕድገትና ተወዳዳሪነት ለማሻሻል የሚያስችል በአፍሪካ ግዙፉ የጥራት መንደር ነው።
የጥራት መንደሩ ዓለም ከደረሰበት ደረጃ ጋር የሚሄዱ ዘመናዊ የፍተሻ ቤተሙከራዎች የተገጠሙለት ሲሆን ከዓለም አቀፍ ደረጃዎች ጋር ተስማሚ ጥራት እንድታረጋግጥ፣ የቴክኒክ መሰናክሎችን እንድትቀንስና በዓለም አቀፍ ንግድ ያላትን ተሳትፎ እንድታሻሽል ጉልህ አስተዋፅኦ አለው። የጥራት መንደሩ ኢትዮጵያን በወጪ ንግድ በአፍሪካ ቀዳሚ ለማድረግ የተያያዘውን ራዕይ ለማሳካትም ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ይጠበቃል።
ሕዳር 2017 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ወደ ሥራ የገባው ይህ “የጥራት መንደር” የአገሪቷን ደረጃዎች ልማት፣ የሥነ-ልክ፣ የዕውቅና አሰጣጥ፣ የተስማሚነት ግምገማ፣ የገበያ ክትትል እና የጥራት ማስተዋወቅን በማጠናከር ለንግድ ድርጅቶች የሚሰጠውን የጥራት ማረጋገጫ አገልግሎት ለማሳደግ ያለመ ነው።
ተግዳሮቶችን በጨረፍታ …
Insight assurance የተሰኘው ድረገጽ (Top Challenges to Achieving ISO Standard
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
Certification and How to overcome them) በሚል ርዕሰ ለንባብ ያበቃው ጽሑፍ የጥራት ሥራ አመራርን ተግባራዊ ለማድረግ ወደ እንቅስቃሴ በሚገባበት ወቅት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ከመፍትሔዎቻቸው ጋር ተንትኖ አቅርቧል።
በጽሑፉ እንደ ችግር ከተመላከቱት ውስጥ አንደኛው የጊዜ፣ የበጀት እና የሰው ኃይል እጥረት ሲሆን፤ ሁለተኛው ለውጥን የመፍራትና የመሸሽ አዝማሚያ በሠራተኞችና በአመራሮች ዘንድ መኖሩ ነው። ተያይዞ የሚነሳው ሌላው ነጥብ በአመራር ሥርዓቱ እና በተመረጠው የሥራ አመራራ መካከል አለመጣጣም የሚያጋጥም መሆኑ ነው። የሥራ ክፍሎች እኩል እና ተከታታይነት ባለው መልኩ የማይተገብሩ ከሆነ በውጤታማነቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳረፉ አይቀርም። በተለይም የለውጥ ሥራ አመራር ትግበራውን ተከታታይነት ያለው ሳይሆን የአንድ ጊዜ ተግባር አድርጎ የመረዳት ሁኔታም ያጋጥማል።
ጽሑፉ እነዚህን ችግሮች ሙሉ ለሙሉ እንዳይኖሩ ወይም እንዳያጋጥሙ መጠበቅ ሳይሆን ችግሮቹን አስመልክቶ የዳሰሳ ጥናት በማከናወን ማስተካከል
የሚቻልባቸውን ስልቶች ተግባራዊ እያደረጉ መጓዝ የአመራሮች የቤት ሥራ ሊሆን እንደሚገባ ምክረ ሀሳብ አቅርቧል።
በአገራችንም ጥራትን ማረጋገጥን እንደ ተጨማሪ ሥራ የሚቆጥሩ የሥራ ኃላፊዎች መኖራቸውን የሚናገሩት አቶ መንግሥቱ የጥራት ሥራ አመራር የሚተገብር ተቋም የሁሉንም ሥራዎች ኃላፊነት በየሰው ኃይሉ ከፋፍሎ ስለሚያስቀምጥ ስትራቴጂክ አመራሩ በቂ ጊዜ እንዲያገኝ የሚያስችል መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል ይላሉ።
የጥራት ሥራ አመራር ተግባራዊ ባላደረጉ ተቋማት የሚሠሩ የበላይ አመራሮች ስትራቴጂክ በሆኑ ጉዳዮች ከማተኮር ይልቅ በቀን ተቀን ሥራዎች ይጠመዳሉ። አቶ መንግሥቱ ከዚህ ችግር ለመውጣት ተቋማት የጥራት ሥራ አመራር ተግባራዊ ማድረግ እንደ አንድ አማራጭ መውሰድ ይኖርባቸዋል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።
ሲጠቃለል
ኢትዮጵያ የአፍሪካ የብልፅግና ተምሣሌት የመሆን ራዕይዋን ማሳካት የሚያስችላትን የ10 ዓመት
የልማት ዕቅድ አስቀምጣለች። በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በአይሲቲ፣ በቱሪዝም እና በግብርና ምርታማነትን በማሳደግና እሴት በመጨመር የምርት መዳረሻ ገበያን ማበራከትን ታሳቢ ያደርጋል። ይህን ዕቅድ ለማሳካት የምርትና የአገልግሎት አሠጣጥ ጥራትን በማሳደግ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ የመገኘት ምርጫው የእኛ ነው።
አገሪቷ በዓለም አቀፍ ገበያ ያላትን የገበያ ድርሻ ለማሳደግና ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት ከሚያስችሉ አማራጮች መካከል ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃዎችን ተግባራዊ ማድረግ አንዱ እና ዋናው እንደሆነ እርግጥ ነው። ከእነዚህ ደረጃዎች አንዱ የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት (ISO 9001) ሲሆን ትግበራው በአገራችን የሚገኝበትን ሁኔታም በዚህ ጽሑፍ ለማሳየት ተሞክሯል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚሰጡ አገልግሎቶችና የንግድ ልውውጦች ዓለም አቀፍ ተቀባይነት በማስገኘት ብሎም የአገርን ገጽታ በመገንባት እኩል ተፎካካሪ እና ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት ጉልህ አስተዋጽኦ አላቸው። እነዚህን የጥራት ማረጋገጫዎች ለኢኮኖሚው መሰረት በሆኑ ዘርፎች የሚኖራቸው አዎንታዊ አስተዋጽኦ ደማቅ ነው።
በግብርና፣ በንግድ፣ በአምራች ኢንደስትሪው፣ በሕክምና፣ በቱሪዝም አገልግሎት፣ በማሪታይም ትራንስፖርት እና በሌሎችም መስኮች እንደየሥራ ባህሪያቸው የሚስሟሟቸውን የጥራት መመዘኛዎች በመፈተሽ ወደ ትግበራ እንዲገቡ ለማስቻል የአመራሩን በተለይ ሥራውን በባለቤትነት የሚከታተሉ ተቋማትንና ባለድርሻ
አካላትን ቁርጠኝነት ይጠይቃል።
እነዚህን እውቅናዎች ለማግኘት መሥራቱ ከኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ባሻገር የአገርን ገጽታ ለመገንባት ይረዳል። ስለሆነም እውቅናውን ለማግኘት አግኝቶም ጥራትን አስጠብቆ ለመቀጠል ተከታታይነት ያለው ሥራ ማከናወን የሚመለከታቸው አካላት የቤት ሥራቸው ሊያደርጉት ይገባል።
በጥቅሉ የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት ISO 9001 እና ሌሎች የጥራት ማስጠበቂያ ስልቶች ካላቸው ጥቅም አንጻር በአገራችን ያለው አፈጻጸም ብዙ የሚቀረው ስለመሆኑ መረጃዎቹ እማኞች ናቸው። በመሆኑም በቀጣይ በአብዛኞቹ ተቋማት ተግባራዊ በማድረግ አገራችን በዓለም መድረክ የምታደርገውን ፉክክር ለማሸነፍ የሚያስችላትን የቤት ሥራ ከወዲሁ ማከናወን ያስፈልጋል።
ኢኮኖሚ
የገንዘብ ወንጀሎችና
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
የዓለም ሥጋት
በጌታቸው ያለው
እ.አ.አ በ2024 የዓለማችን የገንዘብ ሀብት የዕድገት ማማ ከመቼውም ጊዜ በላይ የላቀ መሆኑን የ2025 የዓለም የሀብት ሪፖርት ያሳያል። እስካለፈው ሰኔ ድረስ የዓለም የሀብት መጠን 305 ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር ደርሷል። ይህም የምንጊዜም ከፍተኛው የዓለም የገንዘብ ሀብት መጠን ሆኖ ተመዝግቧል። እንዲያም ሆኖ ዕድገቱ ወደ ሰሜን አሜሪካ ያዘነበለ መሆኑን የስዊዘርላንድ ኅብረት ባንክ (Union Bank of Switzerland- UBS) ዓመታዊ ሪፖርት ያሳያል።
ዓለም አቀፍ የፋይናንስ አገልግሎት ኩባንያ እና የዓለም ሀብት ደረጃን በመግለጽ የሚታወቀው ይኸው ባንክ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ከጠቅላላው የዓለም ሀብት ከግማሽ በላይ የሚሆነውን አሜሪካ እና ቻይና በጋራ ይዘውታል።
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
እ.አ.አ የ2025 የመጀመሪያ ወራት ፈጣን ሰው ሰራሽ አስተውሎት- መር የቴክኖሎጂ ዕድገት፣ የጂኦ-ፖለቲካ ተለዋዋጭነት እና ኢ-ተገማች በሆነ ከፍተኛ የዋጋ ንረት ምክንያት የፋይናንስ ተጋላጭነት ቀጣይነት ባለው መልኩ የገበያ አለመረጋጋትን ሲፈጥር ታይቷል። ይሁን እንጂ በዚህ ሁሉ ፈተናዎች መሃል ዓለም አቀፉ ሀብት ያለማቋረጥ እንደሚያድግ የመስኩ ትንበያዎች ያመላክታሉ። እነዚህ ትንበያዎች እንደሚያሳዩት ካለፉት ሁለት ዓመታት ይበልጥ ጠንካራ የሀብት ዕድገት አፈፃጸም እንደሚታይ ይጠበቃል።
ፈተናዎቹ ግን እነዚህ ብቻ አይደሉም። የዓለም ሀብት በገንዘብ ወንጀሎች ምክንያት ከፍተኛ ተጽዕኖም አድሮበታል። እናም የገንዘብ ወንጀሎች እንዴት ያሉ ናቸው፤ ተጽዕኗቸውስ የቱን ያህል ፈታኝ ነው የሚለውን በጥቂቱ ማየት ያስፈልጋል።
የገንዘብ ወንጀል (Financial Crime)
ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ጨምሮ ሰፋ ያሉ ሕገ-ወጥ የገንዘብ እንቅስቃሴዎችን የሚያጠቃልል ሲሆን በገንዘብ
ወንጀል ምክንያት ግለሰቦችን፣ ንግዶችን ወይም የመንግሥታትን ጥቅም የሚጎዳ ተግባር ነው። ዓላማውም ሌሎችን ለኪሳራ በመዳረግ ሕገ-ወጥ የገንዘብ ጥቅም ማግኘት ነው።
ዓለም አቀፍ የገንዘብ ወንጀሎች ሥጋት ሲባል የፋይናንስ ሥርዓቶችን ለሕገ-ወጥ ጥቅም የሚያውሉ ሕገ-ወጥ ተግባራትን የሚያካትት ነው። እንደ ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ ማጭበርበር እና ሙስና ያሉ ሕገ-ወጥ ድርጊቶች ዓለማችን በየዓመቱ በትሪሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ገንዘብ እንድትዘረፍ የሚያደርጉ ናቸው። ይህም በፋይናንሺያል ሥርዓቱ ላይ እምነትን የሚሸረሽር ተግባር ሆኖ ሕዝብና አገራትን ለጉዳት ሲዳርግ ይስተዋላል።
የገንዘብ ወንጀል ዓይነቶች
ማጭበርበር (Fraud) ከገንዘብ የማጭበርበር ዓይነቶች አንዱና ተጠቃሽ የወንጀል ድርጊት ነው። የኦንላይን ማጭበርበሮችን ጨምሮ የገንዘብ ማጭበርበር፣ ጉቦ እና ሙስና፣ ግብር ማጭበርበርና ማሸሸ እና ያልተገባ የገንዘብ አሊያም የንብረት ጥቅምን ለማግኘት ሲባል የሚፈጸም ማታለል ወይም ሕገ-ወጥ ድርጊትን ያካትታል። ይህ ወንጀል ከሚያካትታቸው የወንጀል ተግባራት መካከል ሸቀጦችን፣ አገልግሎቶችን ወይም ብድር ለማግኘት ሲባል የሌላን ሰው ማንነት
መጠቀም፤ የማንነት ማጭበርበር (Identity Fraud) አንዱ ነው።
ሰዎችን በማታለል ዋጋ በሌላቸው ወይም አዋጭ ባልሆኑ መስኮች ሙዓለነዋይ እንዲያፈሱ ማበረታታት የኢንቨስትመንት ማጭበርበር (Investment Fraud)፤ ባንኮችን ወይም ደንበኞቻቸውን ዒላማ ያደረገ የባንክ ማጭበርበር ተግባር፤ የድርጅት እና የዋስትና ማጭበርበር በአክሲዮን ወይም በሸቀጦች ገበያ ውስጥ ባለሀብቶችን ለነዋይ ጥቅም ሲባል ለማሳሳት ብዙውን ጊዜ በኩባንያዎች አሊያም በወኪሎቻቸው የሚደረጉ የማጭበርበር እና ሕገ- ወጥ ድርጊቶችን የሚያመለክተው የድርጅት እና የዋስትና ማጭበርበር (Corporate & Secu- rities Fraud)፤ የሀሰት ገንዘብ ወይም የፍጆታ ዕቃዎችን ማምረትን የሚያጠቃልለው ሀሰተኛ ማጭበርበር (Forgery and Counterfeiting) እንዲሁም ቴክኖሎጂ ላይ ተመርኩዞ በበይነመረብ (Internet) በመጠቀም የሚፈፀም ማጭበርበር እና ውስብስብ የገንዘብ ጥቃት የማድረስ ተግባርን የሚመለከተው ሳይበርን መሰረት ያደረጉ የገንዘብ ወንጀሎች (Cyber Financial Crimes) ተጠቃሾች ናቸው።
የገንዘብ ወንጀሎች በዓይነታቸው የበዙ እና ውስብስብ እንደመሆናቸው መጠን አፍሪካ እና ቀሪውን ዓለም ሰቅዘው የያዙት እንደ ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍ እና ገንዘብ ነክ የሳይበር የወንጀል ድርጊቶች የዚህ ጽሁፍ ዋና ትኩረቶች ይሆናሉ።
ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር (Money Laun- dering)
ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ዋናውን ምንጭ በመሰወር ሕጋዊ አስመስሎ እንዲታይ የማድረግ የወንጀል ተግባር ነው። ዓላማውም ውስብስብ በሆኑ የባንክ ዝውውሮች ወይም የንግድ ልውውጦች ውስጥ በማሳለፍ በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ጥቅም ላይ ማዋል ነው።
ይህ ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር የተለያዩ ደረጃዎች ያሉት ሲሆን እነሱም፡-
• ምደባ (Placement)፡- ሕገ-ወጥ ገንዘቦችን በፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ ማስተዋወቅ
• መደራረብ (Layering):- የገንዘቡን ምንጭ ለማድበስበስ ተከታታይ ግብይቶችን ማካሄድ
• ውህደት (Integration)፡- በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኘውን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ወደ ኢኮኖሚው ማስገባት ናቸው።
ታሪካዊ አመጣጡ
ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር የሚለው ጽንሰ-ሃሳብ በዚህ ጊዜ ተጀመረ የሚል የሰነድ ማስረጃ እስካሁን በውል አልተገኘም። የቃሉ ስያሜም ከዚህ ጊዜ አንስቶ ጥቅም ላይ መዋል ጀመረ የሚል አስረጂ ሰነድ የለም። ለዚህም ይመስላል ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር የሚለው ስያሜ እና ወንጀሉ መቼ እንደተጀመረ ለማወቅ በተለያዩ ዘመናት በርካታ ጥናትና ምርምሮች የተካሄዱት፤ በመካሄድም ላይ ያሉት።
በጉዳዩ ላይ ከተደረጉ ጥናቶች መካከል በብዙዎች ዘንድ ለእውነት የቀረበ በሚል በማጠቃሻነት በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኘው በአሜሪካዊው የታሪክ ምሁር ስተርሊንግ ሲግሬቭ
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
የተደረገው ጥናትና በኋላም ለህትመት በበቃው Lords of the Rim የተሰኘው መጽሃፍ ነው። ስተርሊንግ ሲግሬቭ በመጽሐፉ ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት ቻይናዊያን ነጋዴዎች በንግድ ሥራ ላይ ስለሚያደርጉት የሀብትና የገንዘብ ማሸሽና መደበቅ ተግባር በስፋት ዳሷል።
ቻይናዊያኑ ነጋዴዎች በዚያን ዘመን በሚያገኙት ትርፍ ላይ ከመንግሥት ይደርስባቸው በነበረ ጫና በእጅጉ ተማረው ሀብታቸውን ከአገር ውጭ ያሸሹና ይደብቁ እንደነበረ መጽሃፉ ያስረዳል። በዘመኑ የነበረው መንግሥትም በርካታ ነጋዴዎች ገቢያቸው የተገኘው ከጥቁር ግብይት፣ ከዝርፊያ እና ከማጭበርበር ነው ብሎ ያምን ስለነበር ‘ስግብግቦች’ ሲል ይፈርጃቸው እንደነበር መጽሃፉ ያወሳል።
ያኔ ሀብትን ከቻይና ውጭ በመደበቅ፣ በማንቀሳቀስና በመዋዕለ ንዋይ መልክ ያዘዋውሩ እንደነበር ሲግሬቭ ማሳያዎችን ጠቅሶ ጽፏል። ምንም እንኳን ‘ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር’ የሚል በዘመኑ የተበየነ ቃል አሊያም ጽንሰ- ሃሳብ ባይኖርም የሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር መርሆዎች በቻይናዊያን ነጋዴዎች ዘንድ እንደነበሩ ሲግሬቭ ያብራራል።
ሆኖም ነጋዴዎቹ በሕገ-ወጥ መንገድ ገንዘብን ወደ ተንቀሳቃሽ ንብረቶች በመለወጥ የኢኮኖሚ ሕጉ ከሚፈቅደው ውጭ ኢንቨስት ያደርጉ እንደነበር በመጽሃፉ ተገልጿል። እነዚህ ደግሞ የሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ድርጊት ዓይነተኛ መገለጫዎች በመሆናቸው ታሪካዊ መነሻው ከዚህ ይጀምራል ሲል ይሞግታል። አሁን ድረስ በርካታ ሕገ-ወጥ የገንዘብ አዘዋዋሪዎች ይህን ዘዴ እንደሚጠቀሙ ሲግሬቭ በማሳያነት ይጠቅሳል።
በጥቅሉ ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ታሪካዊ አመጣጥ እና ዝግመተ ለውጥ ሲዳሰስ ከሺህ ዓመታት አንስቶ በዓለም የኢኮኖሚ ውጣ ውረድ ውስጥ ሥር የሰደደ ሰንኮፍ መሆኑን ያሳያል። ድርጊቱ ከቀደመው ዘመን አንስቶ እስከ ዘመነኛው ትውልድ ድረስ የግለሰቦችን፣ የማኅበረሰብን፣ የአገራትን ብሎም የዓለምን ኢኮኖሚ ከመጉዳቱ ባለፈ ለሕዝቦች ሠላም ፈተና መደቀኑን ቀጥሏል።
አገራትና ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር
ገንዘብ ዓለምን ከሚያንቀሳቅሱ ወሳኝ መዘውሮች በቀዳሚነት ይጠቀሳል። ይሁንና የሁሉም ገንዘብና ገንዘብ-ነክ ጉዳዮች እንቅስቃሴ በሕጋዊ መንገድ ብቻ ሲከናወን አይስተዋልም። በየዓመቱ በትሪሊዮን የሚቆጠር ዶላር በፋይናንሺያል ሥርዓት ውስጥ የሚዘዋወር ቢሆንም ሕጋዊነቱን ሳይጠብቅ የሚደረገው ዝውውርም ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። እንደ ማጭበርበር፣ ሙስና፣ ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር እና ሕገ- ወጥ ንግድ ባሉ ድርጊቶች የአገራት ኢኮኖሚ ከመጎዳት አልፎ ለሠላምና መረጋጋት ጠንቅ ሲሆን ይስተዋላል። በአንፃሩ እንደ ሆሊውድ ያሉ የዓለማችን ግዙፍ የፊልም ኢንዱስትሪዎች በገንዘብ ወንጀሎች ዙሪያ ለሚሰሯቸው መሳጭ ፊልሞችና የቴሌቪዥን ትዕይንቶች ጠቃሚ የመነሻ ሃሳብ በመሆን ዳጎስ ያለ ዶላር ያስገኝላቸዋል።
በገንዘብ ወንጀሎች ዙሪያ ከተሰሩና ዓለም አቀፍ ዝናን ከተጎናጸፉ ፊልሞች መካከል The Laun- dromat, Dirty Money፣ Ozark፣ The Tin- der Swindler፣ Inventing Anna፣ The Wire እና The Mechanism የተሰኙትን በማሳያነት
መጥቀስ ይቻላል። ፊልሞቹ የገንዘብ ወንጀሎች የሰውን ልጅ እንዴት ያለ ቀውስ ውስጥ እንደሚዘፍቁትና ከግለሰብ አልፈው ማኅበረሰባዊና አገራዊ ብሎም ዓለም አቀፋዊ ፈተናዎችን እየፈጠሩ እንደሆነ ፍንትው አድረገው ያሳያሉ። በእርግጥም ፊልሞቹ የገሃዱን ዓለም ነበራዊ ሁኔታ የሚያንፀባርቁ ናቸው።
እንደ ባዜል ኢንስቲትዩት ኦን ገቨርናንስ የ2025 የፀረ-ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር አመላካች ሪፖርት ከሆነ ሃይቲ፣ ቻድ፣ ማይናማር፣ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ (DRC)፣ ኮንጎ ሪፐብሊክ፣ ሞዛምቢክ፣ ጋቦን፣ ጊኒ-ቢሳዎ እና ቬኔዝዌላ ከፍተኛ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ሥጋት የታየባቸው አገራት ናቸው።
ማይናማር በዓለም አቀፍ ደረጃ 8 ነጥብ 17 በመቶ በማስመዝገብ ቀዳሚ ስትሆን የካሪቢያን ደሴት አገር የሆነችው ሃይቲ 7 ነጥብ 92 በመቶ ሁለተኛ እንዲሁም ዴሞክራቲክ ኮንጎ 7 ነጥብ 73 በመቶ በማስመዝገብ ሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል። ከአሥሩ ከፍተኛ ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ከሚታይባቸው አገራት መካከል ስድስቱ የአፍሪካ አገራት መሆናቸው ደግሞ አህጉሪቱ በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ምን ያህል ጉዳት እንደሚደርስባት ያሳያል።
ባለፈው ሐምሌ የወጡ የአፍሪካ የፋይናንስ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት አፍሪካ በፋይናንስ ወንጀሎች ምክንያት በየዓመቱ እስከ 100 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ ታጣለች።
አሁን ላይ የውጭ አገራት የበጀት ድጎማና የገንዘብ ድጋፍ እየቀነሰ ሲሄድ የአፍሪካ መንግሥታት አዳዲስ የገንዘብ አማራጮችን ማየት ጀምረዋል። በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርና በመሰል ወንጀሎች ሳቢያ አህጉሪቱ ምን ያህል ገንዘብ እያጣች ስለመሆኗ ማጤን ግድ ብሏቸዋል።
አፍሪካዊያን ይህንን የገንዘብ ወንጀል መግታት ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ እንደሆነ ከመቼውም ጊዜ በላይ የተገነዘቡት ይመስላል። እናም በቅርቡ ኢትዮጵያ ያስተናገደቸው የምሥራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ፀረ- ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድን (ESAAMLG) 50ኛ ጉባዔ ይህን መሰሉን አህጉራዊ ጉዳት ለመታደግ ቀጣናዊ ጥረት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
አይረሴ ግዙፍ የገንዘብ ዝውውር ቅሌቶች
በየዓመቱ ከሦስት እስከ አምሥት በመቶ የሚሆነው የዓለማችን የአገር ውስጥ ምርት (GDP) ለሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ሰላባ እንደሚሆን መረጃዎች ያሳያሉ። ይህ በገንዘብ ሲሰላ ከትሪሊዮን ዶላር በላይ ይደርሳል። ከተራ ሌብነት እስከ ሥልጣንን መከታ አድርገው የሚዘርፉ (Kleptocrats) እና ከአገራቸው ገንዘብና ሀብት እስከሚያሸሹ አምባገነኖች ድረስ በዚህ ሕገወጥ ድርጊት እንደሚሳተፉ የዓለም አቀፉ ፋይናንሺያል የድርጊት ግብረ ኃይል (FATF) መረጃ ያስረዳል።
በተለይ ዕጽ አዘዋዋሪዎች፣ ሽብርተኝነትን በገንዘብ በሚደግፉና በሙሰኞች የሚደረጉ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውሮች በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ላይ ተጽዕኖ እያሳደሩ የሚገኙ ከባድ የገንዘብ ወንጀሎች ሆነው ቀጥለዋል።
የፋይናንሺያል ሥርዓት የማንነት ማረጋገጫና ማጭበርበርን በመከላከል የተሰማራው አይደንፋይ (iDenfy) የተሰኘ ኩባንያ እንደሚለው በየዘመኑ የአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪዎች፣ አሸባሪዎች፣ እንደ ባንኮች ያሉ የገንዘብ ተቋማት በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ውስጥ ተሳትፏቸው የጎላ ነው። በተጨማሪም ከነጋዴዎች እስከ ጉምቱ ፖለቲከኞች በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ቅሌት ሲዘፈቁ ማየት የተለመደ መሆኑን ያስረዳል።
እዚህ ላይ የ37ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሪቻርድ ኒክሰን የዎተር ጌት አይረሴ ቅሌት (The Wa- tergate Scandal) ተጠቃሽ ነው። ፕሬዚዳንቱ ከልገሳ እና ከሌሎች ሕገወጥ ምንጮች የተገኘን ገንዘብ ለዳግም ምርጫ ዘመቻ ለማዋጣት “Pass-through” የተሰኘ ቴክኒክ ተጠቅመው በመገኘታቸው ከሥልጣን እንዲለቁ ሆኗል።
ወደተነሳንበት ርዕስ እንመለስና የዓለማችን አይረሴ ግዙፍ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ቅሌቶች ተብለው በሕግ አስከባሪዎች ይፋ የተደረጉ ከዳንስኬ እስከ ዋቾቪያ ባንኮች የተፈጸሙ የገንዘብ ማጭበርበር ቅሌቶችን እንቃኝ።
የዳንስኬ ባንክ ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቅሌት
ዳንስኬ ባንክ ዋና መቀመጫውን ኮፐንሀገን ከተማ ያደረገ የዴንማርክ ዓለም አቀፍ የባንክ እና የፋይናንስ አገልግሎቶች ኮርፖሬሽን ኩባንያ ሲሆን ከአገሪቷ ታላላቅ ባንኮች አንዱ ነው። በታሪክ የዳንስኬ ባንክ ቅሌት (Danske Bank Mon- ey Laundering Scandal) በመባል የሚታወቅ ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር የወንጀል ድርጊት ሆኖ ተመዝግቧል።
ይህ ባንክ አሜሪካ እና ሕንድን ጨምሮ በተለያዩ አገራት ቅርንጫፎችን መስርቶ ይሠራል። እንዲያም ሆኖ በምሥራቅ አውሮፓዊቷ ኢስቶኒያ ያለው የባንኩ ቅርንጫፍ በተደጋጋሚ በገንዘብ ማጭበርበር ቅሌት ተነክሮ እንደነበር ሕግ አስከባሪዎች ደርሰውበታል።
እ.አ.አ ከ2007 እስከ 2015 ባለው ጊዜ ከሩሲያ፣ ላቲቪያ እና ኢስቶኒያ ከመሳሰሉት የቀድሞ ሶቭዬት ኅብረት አገራት 800 ቢሊዮን ዩሮ አጠራጣሪ ግብይት በዚሁ ባንክ የኢስቶኒያ ቅርንጫፍ የገንዘብ ማጭበርበር ቅሌት ተፈጽሟል። ድርጊቱ በዓለማችን ከተከሰቱ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ቅሌቶች መካከል በአስደንጋጭነቱ ቀዳሚና ትልቁ ሆኖ ተመዝግቧል።
ቅሌቱ በዳንስኬ ባንክ የፀረ-ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ቁጥጥር ረገድ ጉልህ ድክመቶች እንዳሉበት አሳይቷል። በዚህም ምክንያት ባንኩ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ለአሜሪካ ተቆጣጣሪዎች እና ከ400 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለኢስቶኒያ መንግሥት እንዲከፍል ተገዷል።
የማሌዢያ የኢንቨስትመንት ፈንድ ቅሌት (1MBD Scandal)
አንድ የማሌዥያ የልማት ቤርሀድ (1MDB) የማሌዢያ መንግሥት የኢንቨስትመንት ፈንድ ሲሆን በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ያለ አግባብ የተመዘበረበት ታሪክ በዓለም የምንጊዜም ግዙፍ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ቅሌቶች አንዱ ሆኖ የተመዘገበ ነው።
መሀመድ ናጂብ ቢን አብዱል ራዛክ እ.አ.አ ከ2009 እስከ 2018 የማሌዢያ 6ኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉ ፖለቲከኛ ናቸው። ታዲያ የማሌዢያ የኢንቨስትመንት ቅሌት ከእኚህ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትርና የካቢኔ ሰዎቻቸው ጋር የተያያዘ ነው።
የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ናጂብ ራዛክን ጨምሮ ከፍተኛ የአገሪቷ ባለሥልጣናት ገንዘቡን ለግል ጥቅማቸው እና የተንቆጠቆጡ የአኗኗር ዘይቤዎችን ለመደገፍ ያዋሉት ነበር ተብሏል። ቅሌቱ በበርካታ አገራት ውስብስብ የገንዘብ ልውውጦችና የገንዘብ ማጭበርበር ዘዴዎችን ያካተተ ነበር።
የማሌዢያ የኢንቨስትመንት ፈንድ (1MDB) ከምሥረታው ጀምሮ የማጭበርበር ተግባር ማዕከል እንደነበር ሾልከው የወጡ የፋይናንሺያል ሰነዶች ያስረዳሉ። ከመንግሥት የቦንድ ሽያጭ የተገኘ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ስዊዘርላንድ፣ ሲንጋፖር እና አሜሪካ በሚገኙ የባንክ ሒሳቦች እንዲዘዋወሩ ተደርጓል።
እ.አ.አ ከ2013 ከማሌዢያ አጠቃላይ ምርጫ በፊት ወደ 731 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ በጠቅላይ ሚኒስትር ናጂብ የግል የባንክ ሒሳብ ውስጥ ገብቷል። ይህም ዕዳዎችን ለመክፈል፣ የእርሳቸውን የክሬዲት ካርድ እና የትዳር አጋራቸውን ከፍተኛ ወጪ ለመሸፈን ይውል
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
እንደነበር ይፋ ሆኗል። ያም ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትር ናጂብ የቀረበባቸውን ውንጀላ በማጣጣል ገንዘቡ ከሳዑዲ ልዑል የተበረከተላቸው እንደሆነ በመግለፅ ለመከላከል ጥረዋል።
በዚህ ቅሌት በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ወደተለያዩ የባንክ ሒሳብ ቁጥሮች እና ንብረቶች ተዘዋውሯል፤ ይህም በአሜሪካ፣ በስዊዘርላንድ እና በሌሎች አገራት ባለሥልጣናት ምርመራ ተደርጎበት ተረጋግጧል። በመጨረሻም ቅሌቱ በወቅቱ ለነበረው የማሌዢያ መንግሥት ውድቀት አስተዋጽኦ አድርጓል።
እንደ ጎልድማን ሳክስ እና ዶቼ ባንክ ያሉ ዋና ዋና የፋይናንስ ተቋማት በግብይቱ ላይ ተሳትፈዋል በሚል ማጭበርበርን በማቀላጠፍ ሚናቸው ላይ ምርመራና ክስ ቀርቦባቸዋል። በዚህም ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እንዲቀጡ ሆኗል።
ይኸው ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ያመጣው ቅሌት እ.አ.አ በ1957 ማሌዢያ ነፃ አገር ከሆነች ጀምሮ ሥልጣን በያዘው የናጂብ ራዛክ የፖለቲካ ፓርቲ ማለትም የተባበሩት ማሌይ ብሔራዊ ድርጅት (UMNO) እንዲከስም በማድረግ መንግሥታቸውንም ለውድቀት ዳርጓል።
የHSBC የገንዘብ ማጭበርበር ቅሌት
የሆንግኮንግ እና ሻንጋይ የባንክ ኮርፖሬሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር (The Hong- kong and Shanghai Banking Corpora- tion-HSBC) በመባል የሚታወቀው ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት በሎንዶን ከተማ የሚገኝ የእንግሊዝ ግዙፍ ባንክ ነው።
ከዓለማችን ታላላቅ ባንኮች አንዱ የሆነውን ይህን ባንክ የአሜሪካ ባለሥልጣናት እ.አ.አ በ2012 በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ቅሌት እና በሌሎች ተያያዥ የገንዘብ ወንጀሎች ተሳትፎ አድርጓል በሚል ክስ አቅርበውበት ነበር። ባንኩ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከል ተገቢውን ቁጥጥር ባለማድረጉ ጭምር ነው ለክስ የተዳረገው። ክሱን ተከትሎ በተደረገ ማጣራትና ምርመራ HSBC ባንክ በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ውስጥ ተዘፍቆ ተገኝቷል። ባንኩ በግልጽ ከታወቀው ከ881 ሚሊዮን ዶላር በላይ ከሜክሲኮ ሲናሎአ እና ከኮሎምቢያው ኖርቴ ዴል ቫሌ የአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪዎች ጋር ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር በማከናወን በቅሌት ተመዝግቧል።
ተጨማሪ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ባንኩ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ በሕገወጥ መንገድ በሒሳቡ ሲያንቀሳቅስ በምርመራ የተገኘ ሲሆን ገንዘቡም ከአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪዎችና ከአሸባሪ ድርጅቶች የተገኘ ስለመሆኑ ተረጋግጧል። እንደ ኢራን፣ ሶሪያ እና ሱዳን ባሉ አገራት በአሜሪካ የተጣሉ ማዕቀቦችን የጣሰ አሠራር ተከትሏል በሚልም ክስ ቀርቦበት 1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር እንዲቀጣ ሆኗል። የቅጣቱ ምክንያት ለሜክሲኮ የአደንዛዥ እፅ አዘዋዋሪዎች ዋነኛ የገንዘብ ማስተላለፊያ ሆኖ በማገልገሉ ነው። ባንኩ በተጨማሪ 665 ሚሊዮን ዶላር የፍትሐ ብሔር ተገዢነት ቅጣት የተጣለበት ሲሆን የፀረ-ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ቁጥጥር ላይም ችግሮች እንዳሉበት ያጋለጠ ሆኗል።
ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ቅሌቱ ለባንኩ እና ለባለድርሻ አካላት ከፍተኛ መዘዝ ከማስከተሉ ባሻገር ለከፍተኛ የገንዘብ ችግር የዳረገው ነበር። ድርጊቱ የባንኩን መልካም ስም እና ዝና በማጉደፍ
ለፋይናንስ አለመረጋጋት ዳርጎታል።
የዋቾቪያ ባንክ የገንዘብ ማጭበርበር ቅሌት
መቀመጫውን በቻርሎት ሰሜን ካሮላይና ያደረገው ዋቾቪያ ባንክ እ.አ.አ በ1879 የተመሰረተ በአሜሪካ አራተኛው ግዙፍ ባንክ ነው። እ.አ.አ በ2008 ለዌልስ ፋርጎ በሽያጭ ተላልፏል። ባንኩ በዌልስ ፋርጎ መገዛቱን ተከትሎ እ.አ.አ 2010 ከአሜሪካ ፌዴራል ዐቃቤ ሕግ ጋር አንድ ስምምነት ላይ ይደርሳል። ስምምነቱ ዋቾቪያ ባንክ በአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪዎች የሚጠረጠሩ የገንዘብ ዝውውሮች ክትትልና ሪፖርት ማድረግን የሚመለከት ነበር። ስምምነት ባይደረስም የፋይናንስ ሥርዓት ሕጋዊነትን ተከተሎ መሥራት ይጠበቅበታል።
ይሁን እንጂ ባንኩ ለአደንዛዥ ዕጽ ማዘዋወሪያ ዓላማ የሚውሉ አውሮፕላኖችን ለመግዛት የሚያገለግል ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ (390 ቢሊዮን ዶላር) ዝውውሮችን በመፈጸም ሪፖርት ያለማድረግ ክስ ቀርቦበታል። ዕጽ አዘዋዋሪዎች በዋቾቪያ ባንክ ሒሳቦች ሕገወጥ
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
የገንዘብ ዝውውር ሲያደርጉ ባንኩ የእነዚህን ገንዘቦች ምንጭ ማረጋገጥ አልቻለም ነበር።
ዋቾቪያ ባንክ በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ቅሌት የተመሰረተበትን ክስ እልባት ለመስጠት 160 ሚሊዮን ዶላር ለአሜሪካ መንግሥት በቅጣት ከፍሏል።
ለማሳያነት እነዚህን አነሳን እንጂ በየዓመቱ በተለያዩ አገራት በርካታ ውስብስብ የገንዘብ ማጭበርበር ቅሌቶች እንደሚፈጸሙ ከዓለም አቀፍ የምርመራ ጋዜጠኞች ጥምረት (ICIJ) እና ከአሜሪካ ግምጃ ቤት የፋይናንስ ወንጀሎች ማስፈጸሚያ መረብ (FinCEN) ሰነዶች የተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ።
የሚገርመው ግን አሜሪካ እና እንግሊዝ በሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ውስጥ ቀዳሚ ሚና ያላቸው አገራት መሆናቸው ነው። እ.አ.አ በ2020 በተደረገ ጠንካራ ምርመራ እንግሊዝ ውስጥ በአሜሪካ በተመዘገቡ የሼል ኩባንያዎች የሚያልፍ “ዓለም አቀፍ ሕገወጥ የገንዘብ ማዘዋወሪያ ቀለበት” መኖሩ ይፋ ሆኗል።
የሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ተጽዕኖ
የገንዘብ ወንጀሎችን ለአገር እና ለዓለም አቀፍ ደህንነት አስጊ አድርጎ የመመልከቱ ጉዳይ እ.አ.አ መስከረም 2024 በስቶክሆልም ስዊድን በተካሄደው የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ወንጀሎችን ለመዋጋት (GCFFC) የመሪዎች ጉባዔ ዋና አጀንዳ ነበር።
በጉባዔው የገንዘብ ወንጀሎች የደኅንነት ሥጋት እንደሆኑ መተማመን ላይ የተደረሰ ሲሆን ወንጀለኞች በሕገወጥ መንገድ ያገኙትን ገንዘብ ከኢኮኖሚ አልፎ ፖለቲካዊ ተጽዕኖ ለማሳደርና
ማኅበራዊ ሥርዓትን ለማናጋት፣ መንግሥታዊና ኢኮኖሚያዊ መዋቅሮችን ለማሽመድመድ ሊጠቀሙበት የሚችሉበትን መንገድ መዝጋት እንደሚገባ አቋም ተይዟል።
የገንዘብ ወንጀሎችን ገጽታዎች ብቻ ሳይሆን በወንጀሎቹ ውስጥ የሚሳተፉ ተዋንያን ሰንሰለት በሠላም፣ በመረጋጋት እና በማኅበራዊ ትስስር ላይ የሚያስከትሉትን ተጽዕኖ ግምት ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ ነው።
አሁን ላይ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር የዓለም አገራትን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ መረጋጋትን አደጋ ላይ የሚጥል ወንጀል ሆኗል። የወንጀል ድርጊቱ ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋትን ጨምሮ፣ መንግሥታትን ገቢ ማሳጣት፣ የገንዘብ ግብይት መቋረጥና የግሉ ዘርፍ መዳከምን በመፍጠር አስከፊና ዘርፈ ብዙ ተጽዕኖዎችን ሲያስከትል ታይቷል።
ወንጀልና ሙስና እንዲባባስ በማድረግ ብሎም ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለውን አመኔታና ቅቡልነት በመሸርሸር የአገራት ሥልጣን በሕዝብ ከተመረጡ ሕጋዊ መንግሥታት ወጥቶ በሕገወጥ መንገድ በወንጀለኞች እጅ እንዲገባ እስከማድረግ የሚደርስ ተጽዕኖ ያሳድራል።
በዚህ ረገድ ማሳያ ተደርጋ የምትወሰደው አገር ሄይቲ ነት። እ.አ.አ በ2004 የአገሪቷ ፕሬዚዳንት የነበሩት ዣን በርትራንድ አሪስቲድ በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ ሄይቲ ለዓመታት በዘለቀ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እየታመሰች ትገኛለች። በአገሪቷ የተንሰራፉት የወንጀል ቡድኖች ሄይቲ ከሕገወጥ የሰዎች ዝውውር እስከ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ ከሕገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር
እስከ አደንዛዥ ዕጽ ዝውውር በማከናወን መንግሥት እስከ መጣል የደረሰ ትዕይንት አስተናግዳለች።
አፍሪካዊቷ ደዴሞክራቲክ ኮንጎ ሪፐብሊክም በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር በተለይ ከተፈጥሮ ማዕድን ዝርፊያ ጋር በተያያዘ መረጋጋት ከራቃቸው አገራት አንዷ ሆናለች። በእነዚህ የወንጀል ድርጊቶች ሀብቷ ከመዘረፉ ባሻገር የሠላም እጦት ያጠላባት ሆናለች።
የገንዘብ የወንጀል ድርጊቶች በፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች ውስጥ ከፍ ያለ ሚና የሚጫወቱ ሲሆን የመንግሥት ተቋማትን እስከማዳከም የሚደርስ ጫና ይፈጥራሉ። በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕዝብ በፋይናንሺያል ተቋማትና መንግሥታት ላይ ያለው አመኔታ እንዲሸረሸር የሚያደርግ ሲሆን ገቢን ያሳጣል፣ የውጭ ኢንቨስትመንትን ይቀንሳል፣ በመጨረሻም አጠቃላይ የፋይናንስ ሥርዓቱን ታማኝነት ይጎዳል።
እነዚህ በግለሰቦች ወይም በተደራጁ ቡድኖች ሊፈፀሙ የሚችሉ ወንጀሎች ከግለሰብ እስከ መንግሥት እና አጠቃላይ ኢኮኖሚ ድረስ ያሉ የተለያዩ አካላትን የሚጎዱ ናቸው።
ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍ
ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍ (Financing Terrorism) የሽብር ተግባራትን፣ አሸባሪዎችን ወይም አሸባሪ ድርጅቶችን ለመደገፍ በማሰብ ገንዘብ የመሰብሰብ ወይም የመስጠት ተግባር ነው። በጥቅሉ የሽብር ተግባርን ውስብስብ በሆኑ የፋይናንስ አውታሮች ተጠቃሚ የሚያደርግ የገንዘብ ድጋፍ ነው።
ሽብርተኝነት በአገራት ብሎም በዓለም ሠላምና ደህንነት ላይ ጉዳት የሚያስከትል፣ በሰው ልጆች መብቶችና ነፃነቶች ላይ የሚቃጣና በሠላምና ያለ ሥጋት የመኖር ሁኔታን የሚያሳጣ ከባድ ወንጀል ነው። ይህ ወንጀል አፈፃፀሙ ውስብስብ፣ ከማቀድ ጀምሮ በርካታ ወንጀል ፈፃሚዎችን የሚያሳትፍ፣ በአብዛኛው ዓለምአቀፋዊ ትስስር የሚኖረው፣ በገንዘብ የሚደገፍ የተደራጀ የወንጀል ዓይነት ነው።
የሽብር ወንጀል ያለ ገንዘብ የሚታሰብ አይደለም። የገንዘብ ድጋፉም
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
ከአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪዎች፣ ከእገታ እና ከሕገወጥ ንግድ ከመሳሰሉ የወንጀል ድርጊቶች ወይም ከልገሳ፣ ከሕጋዊ ገቢዎችና በሕጋዊ የንግድ ድርጅቶች ካሉ ምንጮች ሊመነጭ ይችላል።
ከገንዘብ ማጭበርበር ጋር በሚመሳሰል መልኩ የሽብርተኝነት ፋይናንስ ሦስት ደረጃዎች ያሉት ሲሆን እነዚህም ገንዘብ መሰብሰብ፣ ማንቀሳቀስ እና መጠቀም ናቸው። አሸባሪዎች ገንዘብ ለማግኘትና ለማስተላለፍ የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ። በዚህ ረገድ ሕጋዊ ንግዶችን እና ለትርፍ ያልተቋቋሙ ድርጅቶችን በመጠቀም ሕገወጥ ተግባራትን ለመሸፈን ወይም ልገሳዎችን ለመሰብሰብ ያውሏቸዋል። በወንጀል ተግባራት ውስጥ በመሳተፍ በእገታ፣ በዘረፋ፣ በሕገወጥ ንግድ ሀብት ይሰበስባሉ። አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የፋይናንሺያል ጥበቃዎችን
አልፎ ዘረፋና ገንዘብን በሕገወጥ መንገድ ማዘዋወርንም ይጠቀማሉ።
አፍሪካ የሽብርተኝነት አስከፊ ተጽዕኖ ገፈት ቀማሽ ከሆኑ አህጉራት መካከል ትጠቀሳለች። ሽብርተኝነትን በገንዘብ በሚደግፉ አካላት ሠላምና መረጋጋቷ አደጋ ላይ ሲወድቅ ዓመታት ተቆጥረዋል። ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ አፍሪካ፣ ከሰሜንና ማዕከላዊ አፍሪካ እስከ ደቡባዊ አፍሪካ ሽብርተኝነትን በገንዘብ በመደገፍ የአገራት ሠላም እየደፈረሰ ይገኛል።
በምዕራብ አፍሪካ ቦኮ ሃራም፣ በምሥራቅ አፍሪካ አል ሸባብ፣ አል ቃይዳ እና እሥላማዊ መንግሥት (IS) እንዲሁም በሳህል አፍሪካ የተሰማራው ጀመዓት ኑስርት አል ኢስላም ወል ሙስሊሚን (JNIM) ባሉ አሸባሪዎች ሰላሟ ሲታመስ ይታያል። ይህ ሁሉ ሲሆን አሳዛኙ ነገር ለአሸባሪዎቹ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ሕዝቦችን ለሽብር ጥቃት ሰለባ ማድረጉ ነው።
አሸባሪነትን በገንዘብ መደገፍ የዜጎችን ሕይወት አደጋ ላይ በመጣል ብቻ አያበቃም፤ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እንዲፈጠር በማድረግ፤ ኢኮኖሚያዊ ጥቅምን በማሳጣትና ዕድገትን በማጓተት መፃኢ ዕድልን የሚያጨልም እኩይ ተግባር ነው።
አፍሪካ ከዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ጋር በመተባበር የአሸባሪዎችን የገንዘብ
ምንጭ በማድረቅ የአሸባሪዎችን የገንዘብ አቅም መግታት ይጠበቅባታል። የአፍሪካ ኅብረት እና ሌሎች አህጉራዊ ድርጅቶች በመተባበር ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመደገፍ ድርጊትን ለመግታት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
በቅርቡ ኢትዮጵያ ያስተናገደችው የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ፀረ-ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድን 50ኛው የመንግሥታት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ 25ኛው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ እና ስምንተኛው የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የውይይት ጉባዔ አፍሪካ-መር ጥረቱ ትኩረት ስለማግኘቱ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመደገፍ ወንጀልን መከላከል ብሔራዊ ኮሚቴ ሊቀ መንበር እና የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለምፀሐይ ጳውሎስ ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመደገፍ ወንጀልን መከላከል በኢትዮጵያ ብሔራዊ አጀንዳ ሆኖ እየተሠራበት መሆኑን ግልጽ አድርገዋል።
በኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍ በሽብር ወንጀል ሕግ ውስጥ በዋናነት ተደንግጎ የሚገኝ የወንጀል ድርጊት ዓይነት ነው። በኢትዮጵያ የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ቁጥር 1176/2012 ቀደም ሲል በ2001 ዓ.ም የወጣውን የፀረ- ሽብር አዋጅ ተክቶ ተደንግጓል።
በአዋጁ አንቀፅ 3 ላይ የሽብር ድርጊቶች፣ የወንጀል ፍሬ ነገሮችን የሚዘረዝር እና በወንጀል ተጠያቂ የሚያደርግ መሆኑ የተመለከተ ሲሆን በአንቀፅ 9/2/ ደግሞ ለሽብርተኝነት ድጋፍ ማድረግ በተመሳሳይ የሚያስቀጣ የወንጀል ድርጊት መሆኑ በግልጽ ተቀምጧል።
በዚህ መሰረት ለሽብርተኝነት ሊደረግ ከሚችለው ድጋፍ አንዱ የሆነው የገንዘብ ወይም የንብረት ድጋፍ በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 780/2005 መሰረት ቅጣት የሚፈጸም ይሆናል።
የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ሚና
ዓለም ከአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪዎች እስከ ሳይበር ወንጀለኞች፤ ከታክስ አጭበርባሪዎች እስከ ሕገወጥ የገንዘብ አዘዋዋሪዎች፤ ሽብርተኝነትን በገንዘብ ከመደገፍ እስከ ሕገወጥ የሰዎችና የመሣሪያ ዝውውር ፈተና ተጋርጦባታል።
መንግሥታት፣ የፋይናንስ ተቋማትና ዓለምአቀፍ ተቆጣጣሪዎች ሕገወጥ ፍሰቶችን ለመከታተልና ለማስቆም ብሎም የገንዘብ ወንጀልን ለመከላከል በየጊዜው ጥረት ቢያደርጉም ፈተናው ግን አሁንም ድረስ ቀጥሏል። የቅርብ ጊዜ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በተያዘው የፈረንጆቹ 2025 ዓመት በጂኦ-ፖለቲካዊ ተለዋዋጭነት፣ በቁጥጥር ማሻሻያዎችና በቴክኖሎጂ ዕድገት ምክንያት ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ምኅዳሩ እየሰፋ መጥቷል።
በዚህ እያደገ በመጣው የፋይናንሺያል አገልግሎቶች ዲጂታይዜሽን፣ ሕገወጥ የዲጂታል ገንዘብ ዝውውር (በተለይም በክሪፕቶከረንሲ) ምክንያት የፋይናንስ ወንጀል የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ ሆኗል። ይህን ተከትሎ የሚስተዋለውን የወንጀል ድርጊት በቅጡ
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
ለመረዳት ጽንሰ ሃሳቡን ዘርዘር አድርጎ መመልከቱ ይጠቅማል።
የገንዘብ የሳይበር ወንጀል (Cybercrime in Finance)
ኢንተርኔትን አልያም ዲጂታል ቴክኖሎጂን በሕገወጥ መንገድ ተጠቅሞ ገንዘብ ወይም ሌላ የገንዘብ ጥቅምን ለማግኘት ሲባል የሚፈጸም ወንጀል ነው። ማንነትን በማጭበርበር፣ ሶፍትዌሮችን ተጠቅሞ የሳይበር ጥቃቶችን በመፈጸም፣ ኢ-ሜይል እና የፋይናንሺያል ሂሳብን በማጭበርበር፣ የክሬዲት ካርድ ወይም ሌላ የክፍያ ካርድ መረጃ ለመስረቅ የሚደረግ ሙከራንም ያጠቃልላል። እነዚህ ወንጀሎች የፋይናንሺያል ተቋማትና ግለሰቦች ላይ ያነጣጠሩ የክፍያ መረጃዎችን በመዝረፍ፣ ያልተፈቀደላቸውን የሒሳብ ቁጥሮች በማግኘትና የግል መረጃዎችን በመስረቅ ለተጨማሪ ማጭበርበር ጥቅም ላይ ይውላሉ።
ወንጀለኞቹ የተለመዱ ቴክኒኮችን እንደ ማልዌር ያሉ ሶፍትዌሮችን፣ ማኅበራዊ ገፆችን እና እንደ ሰውሰራሽ አስተውሎት (AI) ያሉ የተራቀቁ የማጭበርበሪያ ስልቶችንም ይጠቀማሉ። ውስብስብና ረቂቅ እየሆነ የመጣውን የገንዘብ ወንጀል ለመከላከል አገራት እንደ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ያሉ አዳዲስና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመፍትሄነት መጠቀም ጀምረዋል።
ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የገንዘብ ወንጀሎችን ለመከላከል ለፋይናንስ ተቋማት ወሳኝ መሣሪያ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። ምክንያቱም ሰው ሰራሽ አስተውሎት ግዙፍ ዳታን በአጭር ጊዜ በመተንተን የማጭበርበር ባህሪያትን ነጥሎ ማወቅ
የሚያስችል አቅም ያለው በመሆኑ ነው። ይህ ደግሞ ማጭበርበርና ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን በመከላከል ረገድ ወሳኝ ድርሻ እንዳለው የሚያሳይ ነው። ያም ሆኖ ወንጀለኞች በተራቀቀ መንገድ ሀሰተኛ የፋይናንስ ሰነዶችን ለመፍጠር ጄኔሬቲቭ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን (GAI) ተጠቅመው የወንጀል ተግባር ለመፈጸም ጥረት ማድረጋቸው አልቀረም። ይህን መሰሉን ወንጀል ቀድሞ ለመከላከል የፋይናንስ ተቋማት ንቁ የሆነ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ገቢራዊ በማድረግ ከረቀቁና ከአዳዲስ የወንጀል ሥጋቶች ራሳቸውን መጠበቅ ግድ ይላቸዋል።
እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ ሰው ሰራሽ አስተውሎት የገንዘብ ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመዋጋት ወሳኝ ድርሻ እንዳለው ሁሉ የገንዘብ የሳይበር ወንጀል እንዲበራከት የሚጫወተው ሚናም ቀላል እንዳልሆነ ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ ሕገወጥ የገንዘብ ፍሰቶችን ለመግታት በሚደረገው ሰፊ እንቅስቃሴ አጠራጣሪ ግብይቶችን ለማጣራት ፊቱን ወደ ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ማዞሩን አሳውቋል። ባንኩ አጠራጣሪ ግብይቶችንና የተጭበረበሩ ድርጊቶችን ለመለየት የሰው ሰራሽ አስተውሎት መሣሪያዎችን መጠቀም መጀመሩን እወቁት ብሏል።
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዳታዎችን በመቃኘትና ትክክለኛነታቸውን በማረጋገጥ ረገድ ሰው ሰራሽ አስተውሎት በቅፅበት በመለየት የገንዘብ ዝውውሩ ወዲያው እንዲቋረጥ ያደርጋል። በዚህም በአገርና በሕዝብ ላይ ሊደርሱ የሚችሉ የገንዘብ ጥቃቶችን ያስቀራል።
የዓለም ባንክ ሪፖርት እንደሚያሳየው ከዓለማችን
ሕዝብ 67 ነጥብ 4 በመቶ ያህሉ እ.አ.አ በ2023 የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን ችሏል። በዚህም ከሰዎች ጋር ለመገናኘት፣ የኦንላይን ግብይት ለመፈጸም ብሎም ለምርምርና ፈጠራ ኢንተርኔትን ሲጠቀም በአንፃሩ የኢንተርኔት ተጠቃሚነት ያመጣቸው ጉልህ አደጋዎችም ነበሩ። ይህም ከዓለም ሕዝብ ከሁለት ሦስተኛ በላይ የሚሆነውን ለሳይበር ወንጀል ተጋላጭ እንዳደረገው ባንኩ ያስረዳል። እናም ሥጋቱ እያደገ፣ ኢኮኖሚን እያናጋ፣ ወሳኝ መሠረተ ልማቶችን እያስተጓጎለና በዲጂታል ዓለም ላይ ያለውን እምነት እየሸረሸረ ነው ሲል አስጠንቅቋል።
በአዲሱ የሳይበር ወንጀል ሥምምነት መሰረት ለሳይበር ወንጀል የሚሰጡ ምላሾች ፈጣን፣ የተሻለ ቅንጅትና የበለጠ ውጤታማ እንዲሁኑ እየተሠራበት ይገኛል። ይህ ደግሞ የዲጂታል ዓለሙን ከገሃዱ ዓለም እኩል ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን የሚያስችል ነው።
የገንዘብ ወንጀሎችን መከላከል
በዓለም ዙሪያ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ በሽብርተኝነት፣ በሙስና፣ በአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር፣ በታክስ ስወራ እና በሌሎች ሕገወጥ ተግባራት ምክንያት አገራት ኢኮኖሚያዊ፣ ማኀበራዊ እና ፖለቲካዊ ተግዳሮቶች እየገጠሟቸው ይገኛሉ። ከእነዚህ
ሕገወጥ ተግባራት የሚመነጨውን የገንዘብ ፍሰት መከታተልና መግታት እንዲሁም የተሳተፉትን ወንጀለኞች ተጠያቂ ማድረግ ከመንግሥት ባለፈ የፋይናንስ ተቋማት በልዩ ሁኔታ የመፍትሄው አካል እንዲሆኑ ይፈለጋል።
የገንዘብ ወንጀሎችን መከላከል የሚያስችሉ ውጤታማ ፖሊሲዎችና እርምጃዎች የፋይናንስ ሥርዓቱ የተረጋጋና እምነት የሚጣልበት እንዲሆን ቁልፍ ሚና አላቸው። ነገር ግን የገንዘብ ወንጀል ካለው ረቂቅነትና ውስብስብ ባህሪያት አኳያ መንግሥት ብቻውን በመከላከል ስኬት ሊያመጣ አይቻለውም። ይልቁንም ከአገራዊ፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ብሎም ከአገራት ጋር በትብብር መሥራትን ይጠይቃል።
እዚህ ላይ ትብብር ሁሉንም ዓይነት የገንዘብ ወንጀሎች ለመከላከል ወሳኝ ድርሻ እንዳለው ሊታወቅ ይገባል። የተባበሩት መንግሥታት 193 አባል አገራት የሳይበር ወንጀልን ለመከላከል ለአምሥት ዓመታት ያህል ድርድር ሲያካሂዱ ቆይተው እ.አ.አ ታህሳስ 24 ቀን 2024 ኒውዮርክ
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
ላይ አዲስ ታሪካዊና ሕጋዊ አስገዳጅ ሥምምነት አፅድቀዋል። ሥምምነቱ በሳይበር ወንጀል ላይ የመጀመሪያውና ሁሉን አቀፍ ሥምምነት ሲሆን ይህም መንግሥታት ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመዋጋት የተለያዩ እርምጃዎችን እንዲወስዱ የሚፈቅድ ነው። በተጨማሪም ከባድ ወንጀሎችን ለመቆጣጠር የኤሌክትሮኒክስ ማስረጃዎችን ለመጋራትና ዓለም አቀፍ ትብብርን ለማጠናከር ያለመ ነው።
በዚህ በኩል ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ አገራት እንደ የፋይናንስ ድርጊት ግብረ ኃይል (FATF) እና ዓለም አቀፍ ቅንጅት (Global Coalition) ከመሳሰሉ የፀረ-ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርና ሽብርን በገንዘብ መደገፍን የሚቆጣጠሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር ለመሥራት እያደረጉት ያለውን ጥረት አጠናክረው መጠቀል እንዳለባቸው ያሳያል።
አዲሱ የሳይበር ወንጀል ሥምምነት መንግሥታት የሳይበር ወንጀል አደጋዎችና ሥጋቶችን ለመቀነስና ለመቆጣጠር የመከላከያ እርምጃዎችን
እንዲያዘጋጁ የሚጠይቅ ጭምር ነው። የሕግ ማዕቀፎችን ማጠናከር፣ ሕጎችና መመሪያዎችን ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ቁጥጥር ደረጃዎች ጋር ማጣጣም ያስፈልጋል። ወንጀለኞች ሕግ ፊት ቀርበው ተጠያቂ የሚሆኑበትን የሕግ ማስከበር ሥርዓት ማረጋገጥም ይገባል።
የፋይናንስ ወንጀል መከላከልን ማረጋገጥ በድርጅቶችና በግለሰቦች ላይ የሚኖረውን ምልከታና አያያዝ ጭምር ያካትታል። ይህም ጠንካራ የፋይናንስ ወንጀል ሥጋት አስተዳደር ስልቶችን መተግበር (Financial Crime Risk Management Strategies) ለመረጃ ትንተና እና ሥጋት መጠቆሚያ የሚረዳ የላቀ ቴክኖሎጂ መጠቀም፣ ደንበኞችን ማወቅና ተገቢ ጥንቃቄ ማድረግ፣ የሠራተኞች ሥልጠናና ግንዛቤ ማሳደግ በተጨማሪም ከሕግ አስከባሪና ተቆጣጣሪ አካላት ጋር በቅንጀት መሥራትን ይጠይቃል።
ወንጀለኞች ከሳይበር ወንጀል ጋር የተያያዙ የኤሌክትሮኒክስ ማስረጃዎችን ለማጥፋት ዕድል ከማግኘታቸው አስቀድሞ ወይም በተለመዱ
የአሠራር ሂደቶች ከመሰረዛቸው በፊት ሊፈተሹ ይገባል። ይህን ለማድረግ ደግሞ የ24/7 ኔትዎርክ ማግኘትና በዚያ ልክ የክትትልና ቁጥጥር ሥራን መሥራት ይገባል።
የገንዘብ ወንጀሎችን ለመከላከል ከሚያስፈልጉ ትብብሮች መካከል የመንግሥትና የግል ዘርፍ ሽርክናዎች (PPPs) ይጠቀሳሉ። እነዚህ በመንግሥታት፣ በተቆጣጣሪዎችና በንግዱ ማኅበረሰብ መካከል የሚደረጉ ትብብሮች ቅድመ ስጋትን ለመለየት የመረጃ መጋራትን የሚፈጥሩ በመሆናቸው ወንጀሉን በመከላከል ረገድ ወሳኝ ድርሻ አላቸው።
ሌላው የቴክኖሎጂ ኢንቨስትመንት ማስፋፋትና ማጠናከር ጉዳይ ነው። የፋይናንስ ተቋማትና መንግሥታት አደጋን ለይቶ ለማወቅና ተገዢነትን (Compliance) ለማሳደግ በላቁ ትንታኔዎች፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎት እና የመረጃ አያያዝ ላይ ሀብት በማፍሰስ መስራት ይገባቸዋል።
የኢትዮጵያ የፋይናንሺያል ኢንተለጀንስ አገልግሎት (FIS) ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍን የመሳሰሉ የገንዘብ ወንጀሎችን ለመዋጋት እየሠራ የሚገኝ አገራዊ ተቋም ነው። የፋይናንሺያል ግብይቶችን በመመርመር፣ መረጃዎችን በመተንተን እና ከአገር ውስጥም ሆነ ከዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የፋይናንስ ሥርዓቱን ጤናማነት ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። በዚህ ረገድ ተቋሙ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን በመከላከል በኢትዮጵያ የገንዘብ ወንጀሎችን ለመከላከል ከዓለም አቀፍና አህጉራዊ ተቋማት ጋር እየሠራ ይገኛል።
ተቋሙ በቅርቡ ከ130 በላይ በሚሆኑ በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ተግባር የተሰማሩ ግለሰቦችና ድርጅቶችን የባንክ ሒሳብ በመዝጋት የወሰደው እርምጃ የአገሪቷ የፋይናንስ ሥርዓት ጤናማነቱን ጠብቆ እንዲቀጥል የሚያደርግ ነው። በዚህ ረገድ የሚታዩ ጅማሮዎችን አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል። ከዚህ በተጓዳኝ የገንዘብ ወንጀልን ለመከላከል ከኅብረተሰቡ ምን ይጠበቃል የሚለውን ማየቱ አስፈላጊ ነው። ወንጀሉ በሰው ልጆች መብትና ነፃነት እንዲሁም በአገር ሠላምና ደህንነት ላይ ጉዳት የሚያደርስ በመሆኑ ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍና ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን በመከላከል ረገድ ኅብረተሰቡ የራሱን ድርሻ ሊወጣ ይገባል።
ኅብረተሰቡ ከአሸባሪዎችና በአሸባሪነት ከተሰየሙ ድርጅቶች ራሱን በማራቅና ማንኛውም የቀጥታም ሆነ የተዘዋዋሪ የገንዘብም ይሁን የንብረት ድጋፍ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ እንዳያደርግ ግንዛቤ መያዝ አለበት። የሚያስተውላቸውን አጠራጣሪ ነገሮች በአቅራቢያው ለሚገኙ የሕግ አስከባሪ አካላት መረጃ በመስጠት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ማስቻልም ተገቢ ይሆናል።
መቀመጫውን በስዊዘርላንድ ያደረገው የባዝል የፀረ-ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ተቋም የቅርብ ግዜ አመላካች ሪፖርት ይፋ እንዳደረገው በዓለም አቀፍ ደረጃ የተያዙና የተመለሱ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር መጠን ከአንድ በመቶ የበለጠ አይደለም። እናም አገራት የገንዘብ ወንጀሎች የዓለም ሥጋት ሆነው እንዳይቀጥሉ እስካሁን ካደረጉት ጥረትና ትብብር በላይ የላቀ ሥራ መሥራት ይጠብቃቸዋል።
ማኅበራዊ
የሰቆጣ ቃልኪዳን
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
የትውልድ ተስፋ
በሙሴ መለሰ
በፀጥታ ውስጥ የትውልድን ብርሃን የሚያጨልመው መቀንጨር
በዓለም ላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕጻናት ሙሉ አካላዊ እና አዕምሯዊ አቅማቸው ላይ ሳይደርሱ ዕድሜያቸውን ይቆጥራሉ። የዚህ ልብ ሰባሪ ክስተት መነሻ መቀንጨር (stunting) ይባላል። የሥነ ምግብ ባለሙያዎች መቀንጨርን በዓለም አቀፍ ደረጃ ስር የሰደደ ቀውስ ያስከተለና የጉዳቱ መጠን የገዘፈ ነገር ግን የአስከፊነቱን ያህል በቂ ትኩረት ያላገኘ ጉዳይ ነው ይሉታል። እንደ ግጭቶች እና ሌሎች የዓለም ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ቀውሶች አርዕስተ ዜና ሲሆን አይታይም። በቀላሉም የሕዝብን ትኩረት አይስብም። ይሁንና
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
የመቀንጨር ጉዳቶች ትውልድ ተሻጋሪ የሆኑ መዘዞችና የአንድ አገር ልማትና ጉዞ ላይ ሊቀበለበስ የማይችል ጣጣን ያስከትላል።
የሕጻናትን ሰውነት ቀስ በቀስ እየጎዳ አዕምሯቸው እና የመፍጠር አቅማቸውን እያደከመ በመሄድ፣ በድምጽ አልባነቱ ውስጥ ውስጡን ዘላቂ መዘዝ እያመጣ ይገኛል። መቀንጨር ሕጻናትን በለጋ ዕድሜያቸው ጊዜ ብቻ ጎድቶ የሚያበቃ ብቻ አይደለም፤ ዳፋው እስከ ሕይወታቸው መጨረሻ የሚከተላቸው እንጂ። ሕጻናት እጅግ በጣም ቁልፍ በሚባለው የዕድሜ ክልል ማለትም ከተወለዱ እስከ ሁለት ዓመት ባለው ጊዜ የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት ሲገባቸው በምግብ እጦት ምክንያት ዕድገታቸው አሉታዊ ተጽእኖ ይደርስበታል።
የመቀንጨርን ጉዳት አካላዊ ብቻ አድርጎ ማየት የችግሩን ሙሉ ምስል እንደማያሳይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ይገልጻል። የመቀንጨር ችግር ያለባቸው ሕጻናት ትምህርታቸውን
በአግባቡ መከታተል እንደማይችሉና ለበሽታ ተጋላጭነታቸው የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ከሚያገኙ ሕጻናት ጋር ሲነጻጻር እጅጉን ሰፊ እንደሆነ አመላክቷል። የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት በማምጣት አቅማቸውን በሚገባ አውጥተው እንዳይጠቀሙ ያደርጋል። ሕጻናት በምግብ እጦት መቀንጨራቸውን ዩኒሴፍ ‘የሕጻናት መብቶች ጥሰት’ ሲል ይገልጸዋል። ይህም ትውልድ ለአንድ አገር የሚኖረው ድርሻ እንዲኮስስ ያደርጋል። መቀንጨር ድምጽ የለውም፤ ኢኮኖሚን በአንድ ጊዜ አያቃውስም ወይንም ሕዝብ ላይ በቶሎ ስጋትን አይጭርም ነገር ግን ጉዳቱ አያሌ እና ስር የሰደደ ነው። የሕጻናትን አቅም ከመንጠቅ እስከ የአገርን ዕድገት ወደኋላ እስከ መጎተት የሚደርስ የረጅም ጊዜ ተጽእኖ አለው።
እንደ ዩኒሴፍ መረጃ በዓለም ላይ ዕድሜያቸው ከአምስት በታች የሆኑ ከ140 ሚሊዮን በላይ ሕጻናት የመቀንጨር ችግር አለባቸው። በአንዳንድ አገራት ከሶስት ሕጻናት አንዱ የመቀንጨር ችግር
አለበት። የዓለም ጤና ድርጅት በቅርቡ ባወጣው መረጃ እ.አ.አ በ2024 በዓለም ላይ ከሚኖሩ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት 23 ነጥብ 2 በመቶው መቀንጨራቸውን ገልጿል። 42 ነጥብ 8 ሚሊዮኑ የአካል መቀጨጭ ሰለባ ሆነዋል። የመቀንጨር ፍጹም ተቃራኒ የሆነው የሕጻናት ከልክ በላይ ውፍረት አሃዝም 35 ነጥብ 5 ሚሊዮን መድረሱን ድርጅቱ አመልክቷል። እነዚህን አስደጋንጋጭ የአሃዝ መረጃዎች ሰጥቶ ከማለፍ አሻግሮ ማየት ያስፈልጋል።
መቀንጨር ገና መኖርን በቅጡ ያላጣጣሙ ሕጻናትን ዕድገታቸውን፣ ኃይላቸውን እና አቅማቸውን የሚሰርቅ አደገኛ የማኅበረሰብ ጤና ቀውስ ነው። የመቀንጨር ምልክቶች እንደ ሌሎች በሽታዎች ወዲያው የሚለዩ አይደሉም። ጉዳዩ የሆስፒታሎችና የጤና ተቋማትን የድንገተኛ ህሙማን ክፍሎችን ሲያጨናንቅ አይታይም። ሕጻናቱም ምግብ አጣን ብለው አቅማቸው ተዳክሞ ሲወድቁ እምብዛም አንመለከትም። ይህ የመቀንጨር ዝምታዊ ባህሪይ ችግሩ እንዳይታይና መላ እንዳይበጅለት አድርጓል ማለት ይቻላል። አንድ ሕጻን ከእናቱ ማህፀን ወጥቶ ይህቺን ዓለም የመቀላቀል ዕድል ቢገጥመው እንኳን መቀንጨር የሚባል መጥፎ ደዌ እንደ ልቡ እንዳያድግ ሳንካ ይሆንበታል። ሕጻን መቀንጨር ገጠመው ማለት ማኅበረሰብ፣ አገር ከዚያም አልፎ ዓለም ያ ልጅ ሊያበረክተው የሚችለውን አስተዋጽኦ እንዲያጣ ያደርጋል። የመቀንጨር ዋነኛ መንስኤ ምግብ አለማግኘት ብቻ አይደለም ሕጻናት ለዕድገታቸውና ለጤናቸው የሚያስፈልጋቸውን ተመጣጣኝ ምግብ ማጣታቸውም ጭምር ነው።
ዩኒሴፍ በዓለም ላይ 149 ሚሊዮን ሕጻናት የተመጣጠነ የምግብ እቅርቦት እጥረት እንዳለባቸው ይገልጻል። የምግብ እጦቱ የሚጀምረው ሕጻናት ሲወለዱ ብቻ እንዳልሆነ ልብ ይሏል። የሥነ ምግብ ባለሙያዎች እናቶች በቂ እና ተመጣጣኝ ምግብ አለማግኘታቸው፣ ደካማ የእናቶች ጤና እንክብካቤ በማህፀን ውስጥ ያሉ ሕጻናት ዕድገት ላይ ጉዳት ያስተከትላል ይላሉ። በተለይም የምግብ ዋስትና ችግር ባለበት፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት በሌለበት እና የጤና አገልግሎት በተገደበባቸው ስፍራዎች መወለድ ችግሩን የበለጠ የከፋ ያደርገዋል። እነዚህ ተግዳሮቶች ቀውሱን አባባሽ ማዕበሎች ይሆናሉ።
የሕጻናት ሰውነት ከፅንሰት እስከ ሁለት ዓመት ባለው ዕድሜ ማግኘት የሚገባቸውን በንጥረ ነገር የበለፀገ ምግብ ሳያገኝ ሲቀር ጉዳቱ ዘላቂ ይሆናል። የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት በቂ ምላሽ ሳያገኝ ሲቀር ስር ሰዶ መቀንጨርን ያስከትላል። የችግሩን ግዝፈት ከተለያዩ ዘርፎች አንጻር እንመልከት።
የዓለም ባንክ መቀንጨር በዓለም ላይ ምርታማነትን በመቀነስ፣ ከፍተኛ የጤና እንክብካቤ ወጪ በማስወጣትና በትምህርት ውጤቶች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ በማሳደር ዓለም 10 በመቶ ጥቅል ዓመታዊ ምርቷን በችግሩ ምክንያት እንድታጣ እንደሚያደርግ ያመለክታል። ይህ አሃዝ እጅጉን ግዙፍ የሚባል ነው። ከምርታማነት መቀነስ አንጻር የቀነጨረ ህጻን ሲያድግ በጉልምስና ዕድሜው የሚኖረው አካላዊ አቅምና ብቃት የተገደበ መሆኑንና አዕምሯዊ ዕድገቱ መዳከሙ ሙሉ አቅሙን እንዲያጣ በማድረግ ለአገር መስጠት የሚችለውን የምርታማነት ምጣኔ እንዲቀንስ
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
ያደርጋል። አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በመቀንጨር ችግር አልፈው ያደጉ ወጣቶች ይሄ ቀውስ ካልነካቸው ተመሳሳይ የዕድሜ ክልል ከሚገኙ ዜጎች አንጻር 20 በመቶ ያነሰ ገቢ ያገኛሉ። መቀንጨር በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን በስፋት ከማጥቃቱ አኳያ የአገር የሰው ኃይል ምርማታነትንና ተወዳዳሪነትን በመቀነስ፣ ፈጠራን በማዳከም እና ንቁ የኢኮኖሚ ተሳትፎን በመገደብ በገንዘብ ሊተመን የማይችል ሁሉን አቀፍ ጉዳት ያስከትላል።
መቀንጨር ያለባቸው ሕጻናት ለበሽታና ሕመም የመጋለጥ ዕድላቸው ሰፊ ሲሆን ይህም በወጣትነትና በጉልምስና ዕድሜያቸው የስኳር እና የልብ ህመሞችን ጨምሮ በበርካታ አስከፊ በሽታዎች እንዲያዙ ያደርጋል። ይህም የጤና ሥርዓቱን የረጅም ጊዜ ጫንቃ ተሻካሚ በማድረግ የጤና ዘርፉ ላይ ጫና ያሳድራል። የሚታመም ሰው በበዛ ቁርጥ አንድ አገር ለማኅብረሰብ ጤና የምታወጣውን ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲመነደግ ያደርጋል። ይህም ታማሚ ባለበት ቤተሰብ ውስጥ የኢኮኖሚ ቀውስ ያስከትላል። በተለይ እጅ አጠር የሆኑ ቤተሰቦች ያላቸውን ጥሪት ለሕክምና ብቻ ወጪ በማድረግ ለችግር ይጋለጣሉ። መቀንጨር በልጅነት ዕድሜ የአንጎል ዕድገት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። መቀንጨር የትኩረት እጥረትን ይፈጥራል የሚሉት ባለሙያዎቹ ይህም ሕጻናት በትምህርት ገበታቸው ዝቅተኛ አፈጻጸም እንዲኖራቸው ያደርጋል። መቀንጨር ያለባቸው ሕጻናት የትምህርት መጀመሪያ ዕድሜያቸው በጣም የዘገየ፣ ትምህርት በጊዜ የሚያቋርጡና ዝቅተኛ ውጤት የሚያስመዘግቡ ይሆናሉ።
መቀንጨር የሰውን ልጅ በሽታ የመከላከል አቅም የሚያዳክም ከመሆኑ አኳያ የሞት ምጣኔን መጨመሩም ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው። የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት የመቀንጨር ችግር ያለበት ሕጻን መቀንጨር ከሌለባቸው ሕጻናት አራት እጥፍ የመሞት ዕድል አለው። መቀንጨር በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕጻናትን በዋናነት ለሚገድሉት የሳንባ ምች (ኒሞኒያ) እና የተቅማጥ በሽታዎች መከሰት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተቀምጧል። መቀንጨር ማኅበራዊ ክህሎትና ሕጻናት ከእኩዮቻቸው ጋር ተግባብተው እንዳያድጉና እንዳይኖሩ ሳንካ የሆነ የማኅበረሰብ ጤና ቀውስ ነው።
መቀንጨር ያለባቸው ሕጻናት ማኅበራዊ ክህሎቶችን ለመማር ረጅም ጊዜ የሚወስድባቸው ሲሆን ይህም ስሜታችውን በመጉዳት የአቻ ግንኙነታቸውን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ባለሙያዎች ይናገራሉ። ይህ መሆኑ ሕጻናት በራስ መተማመናቸው ዝቅ እንዲል፣ ማኅበራዊ መስተጋብራቸው እንዲላላ፣ ባህሪያቸው እና ስሜታቸውን ለመግራት እንዲቸገሩ ያደርጋል። መቀንጨር አገራት ከሚቀርጿቸው የልማት ግቦች ተፈጻሚነትና ስኬታማነት ላይ ያላቸው ተጽዕኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በተለይም እንደ ዘላቂ ልማት ግቦች ያሉ ዓለም አቀፍ ማዕቀፎች በችግሩ ምክንያት መንገዳቸው ጋሬጣ ይገጥመዋል። በተለይም በጤና፣ በትምህርት፣ በምግብ እና በኢኮኖሚ እድገት የተያዙ ግቦች በመቀንጨር እጅጉን እየተፈተኑ ይገኛሉ።
የዘላቂ ልማት ግብ ሁለት ማጠንጠኛ የሆነው ረሃብን የማጥፋት ግብ በዚህ ዝምተኛ አጥፊ
በ2016 ዓ.ም ባወጣው መረጃ ዕድሜያቸው ከአምሥት ዓመት በታች የሆኑ 39 በመቶ ሕፃናት የመቀንጨር፣ 11 በመቶዎቹ ደግሞ የመቀጨጭ ሰለባ ናቸው። ከነዚህም ሕጻናት አብዛኞቹ በገጠሪቷ የኢትዮጵያ ክፍል እና ልማት በበቂ ሁኔታ ባልተስፋፋባቸው ስፍራዎች የሚገኙ ናቸው። ይህ ቁጥር እ.አ.አ በ1990ዎቹ ከነበረበት 60 በመቶ መቀነሱ ይበል የሚያሰኝ ነው። ይሁንና እነዚህ ሕጻናት የመቀንጨር ሰለባ መሆናቸው ትምህርታቸውን በሚገባ እንዳይከታተሉ፣ ሲያድጉ መተማማኛ የሚሆናቸውን የሥራ ዕድል እንዳያገኙ እንዲሁም ዕድሜ ልካቸውን በአስከፊ የበሽታ ቁራኛ ውስጥ እንዲያሳልፉ ያደርጋል። ይህ መቀንጨርን በተጎጂው ሕጻን እና ቤተሰቡ ላይ እንዲቀር የሚያደርግ ጉዳይ አይደለም። በኢትዮጵያ ልማት ውስጥ ትልቅ መዋቅራዊ ሳንካ የሚሆን ነው።
ትውልዶች በድህነት ወጥመድ እንዲኖሩ የሚያደርገው መቀንጨር
ምክንያት እየተስተጓጎለ ይገኛል። ይህም በድምር ውጤት የድህነት ቅነሳ፣ የሥርዓተ ጾታ እኩልነት እና ዓለም አቀፍ የትምህርት ተደራሽነት ግቦች አዝጋሚ ለውጥ እንዲኖራቸው ያደርጋል። መልከ ብዙ እና ዘላቂ ጉዳት የሚያስከትለውን መቀንጨር አንዳንዶች የአካል፣ የአዕምሮ እና የሥነ ልቦና የዕድሜ ልክ እስራት ሲሉ ይገልጹታል። አንድ ሕጻን የመቀንጨር ችግር አለበት ማለት የመኖር ዕድሉን አጣ ማለት ነው። ይሄ ስር ሰዶ በመሄድ በትውልዶች መካከል የማይሽር ጉዳትን በማስከተል ህልሞችን አጨናግፎ ያስቃራል። የዓለም ባንክ “መቀንጨር በዓለም ላይ እኩልነት የሰፈነበት ዕድገት እንዳይኖር ካደረጉ ዋና ሳንካዎች መካከል አንዱ ነው። መቀንጨር የተመጣጠነ ምግብ ጉዳይ ብቻ አይደለም። ከእይታ የተወሰረ የአገራት ከፍተኛ የልማት ቀውስ ነው” ሲል ይገልጸዋል።
በኢትዮጵያ መቀንጨርን የማጥፋት እርምጃዎች
መቀንጨርን ማጥፋት ለኢትዮጵያ የምግብ እና የጤና ግቦችን ከማሳካት የዘለለ ትልቅ አንድምታ አለው። ይህን የዝምታ ደዌ ታሪክ ማድረግ አገር እንድትበለጽግ፣ እንድትለማ እና እንድታድግ ከማድረግ ብሔራዊ ውጥን ጋር የተቆራኘ ነው። ጤና ሚኒስቴር
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ በድህነት ቅነሳ፣ የጤና አገልግሎትን ተደራሽነት በማስፋትና ኢኮኖሚዋን በማሳደግ ከፍተኛ ለውጦችን አስመዝግባለች። ይሁንና መቀንጨር ግለሰቦችን በሕይወታቸው የኡደት ጊዜ ውስጥ በሙሉ ኋላ የመቅረትና ሌሎችን ያለመጥቀም ቅርቃር ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋል። የቀነጨረ ሕጻን የቀነጨረ ወጣት እና ጎልማሳ የመሆን ዕድሉ ሰፊ ከመሆኑ አኳያ በዚህ አስከፊ ቀውስ ውስጥ ያለፈ የሰው ኃይል የሚያገኘው ገቢ ዝቅተኛና ምርታማነቱም ዝቅትኛ ይሆናል። የሚወልዳቸው ልጆችም እሱ ባደገበት መንገድ ለማደግ ይገደዳሉ። ይህን አስከፊ አዙሪት መስበር ለኢትዮጵያ የምርጫ እና የአስፈላጊነት ጉዳይ ሳይሆን የህልውና እና የቀጣይ መጻዒ ጊዜዋ በብርሃን የተሞላ እንዲሆን ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል። ይህም ለዘላቂ ልማት መረጋገጥ ሚናው አይተኬ ነው ቢባል የተጋነነ አይሆንም።
ዕድገትን የሚጎትተው መቀንጨር
መቀንጨር ኢትዮጵያን ከሰው ኃይሏ በሚፈለገው ደረጃ ማግኘት የሚገባትን ምርታማነት የሚቀንስ፣ የጤና ወጪዎችን ከፍ ያደረገና በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ተጽዕኖ ያሳደረ ነው። ይህም ዜጓቿን ወደ መካከለኛ ገቢ እርከን የማሸጋገር ህልም ላላት ኢትዮጵያ ህልሟን እንዳታሳካ ትልቅ ጋሬጣ ይሆናል። ምርታማ ዜጋ እና አዕምሮውን በላቀ አቅም የሚጠቀም ሰው ቀነሰ ማለት አገሪቷን በዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ ተወዳዳሪ እንዳትትሆን ያደርጋታል። የዕድገት እክል የሆነውን መቀንጨር ማጥፋት ለዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ጉልህ ሚና ይኖረዋል።
መቀንጨር - እኩልነት እንዳይሰፍን የሚያደርገው ሳንካ
መቀንጨር ዘር፣ ጾታ እና ማንነት ሳይለይ ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍል የሚጎዳ መጥፎ ህመም ነው። የተመጣጠነ ምግብ ከማያገኙ እናቶች እንዲሁም የጤና ክብካቤ፣ ንጹህ የመጠጥ ውኃ እና ብዝሃ የንጥረ ምግብ አቅርቦት በተገደበበት አካባቢ የሚወለድ ሕጻን ችግሩ ካልነካው ሕጻን ጋር እኩል ዕድገትና አቅም ሊኖረው አይችልም። መቀንጨርን ማስወገድ የእኩልነትን አለመረጋገጥ ከስር መሰረቱ ነቅሎ የሚጥል ነው። የምግብ ምርታማነት ባደገበት፣ የማኅበራዊና የጤና አገልግሎቶች ተደራሽነት ባደገባቸው አካባቢዎች
የሚወለድ ሕጻን የመቀንጨር ዕድሉ ዝቅተኛ መሆኑ ችግሩን መፍታት በተዘዋዋሪ ፍትሃዊ የአገልግሎት ተደራሽነትን ያሰፍናል። ስለዚህም መቀንጨር የሌበት ሕጻን እንደማንኛውም ሕጻን እኩል የመማር፣ እኩል የማደግ እና የስኬት ማማ ላይ መድረስ ይችላል።
የሰው ኃይል ልማት ስጋት
የኢትዮጵያን ጨምሮ የየትኛውም አገር ልማትና ስኬት ማዕከል ሕዝብ ነው። ሕዝብ ሀብት ነው። ሕዝብ የዕድገት ሞተርና የአገር የልማትና የዕድገት መንገድ ቀያሽ ነው ቢባል ሁሉንም ያስማማል። ታዲያ መቀንጨር የዜጎችን አካላዊና አዕምሯዊ ልማት በማዳከም ሙሉ አቅማቸውን ለአገራቸው እንዳይሰጡ ያደርጋል። ጥራት ያለውና የሠለጠነ የሰው ኃይልን ይቀንሳል። በትምህርት፣ በኢኖቬሽን እና በኢንዱስትሪ ላይ መዋዕለ ንዋይ አብዝታ እያፈፈሰች የምትገኘው ኢትዮጵያ መቀንጨር ተወዳዳሪነቷ ላይ የተደቀነ ትልቅ ስጋት ነው። አብዛኛው ሕዝቧ ወጣት ለሆነው ኢትዮጵያ የዜጎቿ ጥንካሬና ጤናማነት እጅጉን ወሳኝ እንደሆነ የሚያጠራጥር ጉዳይ አይደለም። መቀንጨርን ማጥፋት ትውልድ መጠበቅና ዜጎችን ምርታማና ጤናማ ዜጋ የማድረግ ውጥን ያለው መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ መቀንጨርን ማጥፋት የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የአገርን መጻኢ ጊዜ የሚወስኑ ዜጎችን በዘላቂ መሰረት ላይ በማስቀመጥ እኩልነትና ፍትሃዊነትን የማረጋገጥም ጉዳይ ጭምር ነው።
መቀንጨርን ታሪክ ለማድረግ ቆርጦ የተነሳው የሰቆጣ ቃል ኪዳን
በኢትዮጵያ የሕጻናትን መቀንጨር ለማጥፋት ትልቅ ህልም የያዘው የሰቆጣ ቃል ኪዳን ያለፈው የፋይዳ ግዝፈት ምንድነው? የሚል ጥያቄ ቢነሳ ከላይ መቀንጨር ያለውን ዓለም አቀፋዊ ሁሉን አቀፍ ችግር እና ዘርፈ ብዙ ፈተና መመልከት በቂ ነው የሚል ምላሽ መስጠት ይቻላል። የሰቆጣ ቃል ኪዳን ይህን በጸጥታ ወጀብ ውስጥ ሕጻናትን እያሰቃየ ያለውን መቀንጨር ሁሉን አቀፍና በተቀናጀ ሁኔታ የመፍታት ግብን የያዘ ሰነድ ከመሆኑ ባለፈ የተሻገረ ጠንካራ የፖለቲካ ፍላጎትና ቁርጠኝነት እንዲሁም ዘርፈ ብዙ ባለድርሻ አካላትን በአንድ ጥላ ስር ያሰበሰበ ነው።
ሕጻናት በቂ እና የተመጣጠነ ምግብ አለማግኘታቸው በሰው ኃይል ልማት፣ የኢኮኖሚ ዕድገት እና የማኅበረሰብ ደህነት ላይ ቀጥተኛ የሆነ ተጽዕኖ አለው። መንግሥት ይህን አንገብጋቢና ጊዜ የማይሰጥ ጉዳይ ለመፍታት የሰቆጣ ቃል ኪዳንን ይፋ አድርጓል። በኢትዮጵያ ዕድሜያቸው ከሁለት ዓመት በታች በሆኑ ሕጻናት ላይ የሚከሰተውን የመቀንጨር ችግር በ2022 ዓ.ም ዜሮ ለማድረግ የሰቆጣ ቃል ኪዳን ፕሮግራምን በ2007 ዓ.ም ይፋ በማድረግ ትግበራውን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
የሰቆጣ ቃል ኪዳን የሁሉም ክልል ርዕሰ መስተዳድሮች እና ከንቲባዎች በተገኙበት በነሐሴ 2007 ዓ.ም በሰቆጣ ከተማ የተፈረመ ሲሆን በ15 አመት ፍኖተ ካርታው መሰረት ከ7 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሕጻናትን ከመቀነጨር ለመታደግ የተገባ አገራዊ ቃል ኪዳን ነው፡፡ ይህም መቀንጨር በጤና፣ በትምህርት፣ በሰው ኃብት ልማት እና በአገር ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ በመግታትና በመቀንጨር
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
ምክንያት በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ዕድገት ላይ የሚደርሰውን ተጽዕኖ በመቀነስ፤ የትምህርት አቅምን በማሳደግ እና ምርታማነትን በመጨመር ለአገር ኢኮኖሚ የሚያደርገውን አስተዋጽኦ ከፍ ለማድረግ የሚረዳ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
የሰቆጣ ቃል ኪዳን 10 ስትራቴጂካዊ መስኮች
የሰቆጣ ቃል ኪዳን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ የክልል ቢሮዎች፣ የልማት አጋሮች እና የቴክኒክ አጋሮች የሚተገብሯቸው 10 ስትራቴጂካዊ ዓላማዎች አሉት። እነዚህ ባለድርሻ አካላት ለዓላማዎቹ መሳካት የጋራ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ይሰራሉ። ግቦቹም የሴቶችን፣ ከሁለት ዓመት በታች ሕጻናት እና ልጃገረድ ሴቶችን የጤናና የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ማሻሻል፤ ዓመቱን ሙሉ ምግብን መቶ ፐርሰንት ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ፤ አነስተኛ ይዞታ ያላቸውን አርሶ አደሮች ምርታማነት እና ገቢ ማሻሻል፤ የድህረ ምርት ብክነትን ዜሮ ማድረስ፤ ዘላቂ የምግብ ሥርዓትን የሚያረጋግጡ የኢኖቬሽን ሥራዎች በተሻለ ሁኔታ መጠቀም (በዋናነት የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ዘላቂ የግብርና አሠራርን መከተል)፤ ዓለም አቀፍ የውኃ እና የንጽህና አጠባበቅ ተደራሽነትን ማረጋገጥ እንዲሁም መልካም የሚባሉ የግል ንጽህና ልምዶችን መተግበር፤ በትምህርት ላይ ያሉ ሕጻናትን የጤና እና የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ማሻሻል፤ የሚያጠቡ እናቶችና የሚጠቡ ልጆች የተመጣጠነ ምግብ ተደራሽነት ማሳደግ፤ የሥርዓተ ጾታ እኩልነትን ማረጋገጥ፣ ሴቶችን ማብቃት እና የሕጻናት ጥበቃን ማጠናከር እንዲሁም የባለ ብዙ ወገን ባለድርሻ አካላት ትብብር ማጠናከር እና አቅምን ማጎልበት ናቸው።
አሥሩ የሰቆጣ ቃልኪዳን ስትራቴጂካዊ ትልሞች ሁሉን አቀፍና በተቀናጀ ሁኔታ ከኢትዮጵያ መቀንጨር እና የተመጣጠነ ምግብ እጦትን ማጥፋት ላይ ያጠነጠኑ ናቸው። ጤና፣ የምግብ ዋስትና፣ የግብርና ምርታማነት፣ ውሃ፣ የንጽህና አጠባበቅ፣ ትምህርት፣ የሥርዓተ ጾታ እኩልነት እና ውጤታማ ቅንጅት የመሳሰሉ ቁልፍ ጉዳዮች ዘላቂ በሆነ ሁኔታ መፍትሄ እንዲያገኙ የሚሠራ ነው። የእነዚህ ሥራዎች መዳረሻ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በአንድ የጋራ ማዕቀፍ ውስጥ በማሰባሰብ ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ ነው።
ለ15 ዓመታት እንዲተገበር ታቅዶ ወደ ሥራ የገባው የሰቆጣ ቃል ኪዳን ሶስት የትግበራ ምዕራፎች አሉት።
የኢኖቬሽን ምዕራፍ (ከ2010 እስከ 2013 ዓ.ም)
ይህ የትግበራ ወቅት የቃል ኪዳኑን ገቢራዊነት የመፈተሻ ወይም የፕሮጀክቱ ጽንሰ ሀሳብ የማረጋገጫ ጊዜ (proof of concept) የሚል ስያሜ ሊሰጠው ይችላል። የሰቆጣ ቃል ኪዳን በሙከራ ደረጃ በትግራይ እና በአማራ ክልል በሚገኙ 40 ወረዳዎች የተተገበረበት ወቅት ነው። ወረዳዎቹ የተመረጡት ያለባለባቸውን የመቀንጨር ከፍተኛ ችግርና ተጋላጭነት መሰረት በማድረግ ሲሆን ወረዳዎቹ የሰቆጣ ቃል ኪዳን መተግበሪያ ትምህርት ቤቶች ናቸው ማለት ይቻላል።
ከዚህ ምዕራፍ ቁልፍ ምሰሶዎች አንዱ የባለድርሻ አካላት የቅንጅት አሠራር ማዕቀፎችን መዘርጋት
ነው። የጤና፣ የግብርና፣ የውሃ፣ የመስኖ እና ኢነርጂ፣ የሴቶች እና ሕጻናት እንዲሁም የፋይናንስ ዘርፉ ለተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት አጀንዳ በአንድ ጣሪያ ስር ተሰባስበዋል። የተቋማዊ ቅንጅታዊ አሠራር ማዕቀፎች (MSNCPs) በአገር አቀፍ፣ በክልል እና በአካባቢ ደረጃ የተቋቋሙ ሲሆን ይህ በጋራ ዕቅድ ማውጣት፣ በጀት መጠቀምንና በጋራ ተልዕኮ እንዲፈጸም ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትን መሰረታዊ መንስኤዎች በመለየት ዘላቂ መፍትሄ ማበጀት የሚያስችሉ ማኅበረሰብ ተኮር ሥራዎች ተከናውነዋል። የጓሮ አትክልቶችን የመትከል፣ በአነስተኛ ይዞታ እንስሳት የማርባት፣ የሥርዓተ ትምህርት ግንባቤ መፍጠሪያ ንቅናቄዎች የማድረግ፣ የተማሪዎች የምግባ መርሃ ግብሮችን የመተግበር፣ በንጹህ መጠጥ ውኃ እና በሕዝብ ጤና አጠባበቅ ላይ የሚያተኩሩት ፕሮጀክቶች (ዋሽ) በወረዳዎቹ ተከናውነዋል። የሥርዓተ ምግብ ማስተባበሪያ ቢሮዎች በማቋቋምና ባለሙያዎችን በመመደብ መርሃ ግብሩ በሚተገበርባቸው አካባቢዎች የቴክኒክ ድጋፎች ተደርገዋል። በማኅበረሰብ ደረጃ ፍቱን እና ፈጠራ የታከለባቸው መፍትሄዎች የኢኖቬሽን ፈንድ በማቋቋምና በየአካባቢው ከሚገኙ ተቋማት ጋር በማስተሳሰር በወረዳ ደረጃ
ለሚከናወኑ ሥራዎች ድጋፍ ተደርጓል። የቁጥጥር፣ የክትትል እና የግምገማ አሠራሮችን በመዘርጋት ሥራዎች ያመጡትን አዎንታዊ ለውጥ በተከታታይ በመገምገም ጥንካሬዎችን የበለጠ ለማላቅ ያሉ ክፍተቶችን እየሞሉ ለመሄድ ተችሏል።
በዚህ የኢኖቬሽን ምዕራፍ የባለድርሻ አካላት ትብብር ምን ያህል አዋጪና ውጤታማ እንደሆነ በወረዳ ደረጃ ለመመልከት ተችሏል። በሁሉም ዘርፎች ግልጽ አመላካቾች ያላቸው ውጤት ተኮር የአስተዳደር ማዕቀፎች የተቀረጹ ሲሆን በማኅበረሰብ ደረጃ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትን የሚያሻሻሉ ሥራዎች ተከናውነዋል።
መቀንጨርን ማስወገድና የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትን ተደራሽ ማድረግ ብሔራዊ የልማት ፖሊሲ እና የትኩረት ማዕከል ሆኖ እንዲቀጥል ትልቅ ሚና ተጫውቷል። በመጀመሪያው የሙከራ ምዕራፍ ትግበራ ነፍሰጡር እና ጡት
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
የሚያጠቡ እናቶች እንዲሁም ከአምሥት ዓመት በታች ያሉ ሕጻናትን የጤና እና ሥርዓት ምግብ ማረጋገጥ፤ በንጥረ ነገር የበለጸጉ ምግቦችና የንጹህ መጠጥ ውኃ ተደራሽነትን ማረጋገጥ መቻሉን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል። በታችኛው የአስተዳደር እርከን ደረጃ የቴክኒክ ብቃት ላይ የታዩ ክፍተቶች፣ የተቀናጀ የመረጃ ሥርዓት በሚፈለገው ደረጃ አለመጠናከር እንዲሁም ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎች በዚህ የኢኖሼሽን ምዕራፍ ውስጥ ከታዩ ፈተናዎች መካከል በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።
የማስፋፋት ምዕራፍ (ከ2014 - 2018 ዓ.ም)
ይህ ምዕራፍ (Expansion Phase) ከመጀመሪያው የኢኖቬሽን ምዕራፍ ሥራዎች ትምህርቶችን በመውሰድ የተቀረጸ ነው። በመጀመሪያው ምዕራፍ ውጤት ያስገኙ የድርጊት መርሃ ግብሮችን የማስፋት ዓላማ የያዘ መሆኑን የሰቆጣ ቃል ኪዳን ሰነድ ያመለክታል። በዚህም በአማራ እና በትግራይ ክልሎች በሚገኙ ወረዳዎች ብቻ
ተወስኖ የነበረውን የቃልኪዳኑን የተፈጻሚነት ወሰን ወደ ሌሎች ክልሎችና ወረዳዎች እንዲሰፋ ምክንያት ሆኗል። በሁሉም ዘርፎች የአቅም ግንባታና ተቋማዊ መዋቅር ማጠናከር እና መረጃን መሰረት ያደረገ ውሳኔ ሰጪነት አጽንኦት የተሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው። ሁለተኛው ምዕራፍ በነሐሴ 2013 ዓ.ም ይፋ ሆኗል። ከሁሉም ክልሎች የተመረጡ 240 ወረዳዎች ላይ የመቀንጨር ችግርን ለማቃለል ዕቅድ እንደተያዘም በወቅቱ ተገልጾ ነበር። በአሁኑ ወቅት በዚህ ምዕራፍ የተካተቱ ወረዳዎች ብዛት ወደ 314 ከፍ ማለቱን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
በፌዴራል፣ በክልል እና በአካባቢ ደረጃ የባለድርሻ አካላትን የተጠያቂነት ሥርዓት ማስፈን፣ ሥርዓተ ምግብን ከመንግሥት ሥርዓትና የበጀት ዝግጅት ጋር ማስተሳሰር፣ በተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት የድርጊት መርሃ ግብሮች ውስጥ የማኅበረሰብ ተሳትፎን ማስፋት እንዲሁም ሴቶች እና ወጣቶችን ማብቃት፣ ውጤታማ የሆኑ የድርጊት መርሃ
ግብሮችን ተቋማዊ ማድረግና ከአገራዊ እና በክልል ደረጃ ከሚገኙ ፖሊሲዎች ጋር ማሰናሰል አበይት የትኩረት መስኮች ናቸው። ለዚህኛው ምዕራፍ እንደ ስኬት መለኪያ የሆኑ ሶስት ጉዳዮች ተቀምጠዋል። የሕጻናትን ዕድገትን ማሻሻል እና በቤተሰብ ደረጃ የንጥረ ምግብ ብዝሃነት ማስፋት የመጀመሪያው ነው። የክልል መንግሥታት ለተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትና ለሥርዓተ ምግብ የሚመድቡትን በጀት መጨመርና ከሲቪክ ማኅበረሰብ ተቋማት፣ ከልማት አጋሮችና ከግሉ ዘርፍ ተዋንያን ጋር ያለውን የትብብር አድማስ ማስፋት ሌሎች ቁልፍ የስኬት መለኪያዎች ሆነው ተቀምጠዋል።
በማስፋፊያው ምዕራፍ የሰቆጣ ቃል ኪዳን ከአማራ እና ከትግራይ ክልሎች ውጪ ወደ ሌሎች ክልሎች የማስፋት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል። አፋር፣ ሶማሌ፣ ኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና የደቡባዊ ኢትዮጵያ ክፍሎች ላይ ቃል ኪዳኑ እየተተገበረ ነው። የባለብዙ ባለድርሻ አካላት ማዕቀፎች በክልል፣ በዞን እና በወረዳ ደረጃ ስር የሰደደ ሲሆን የሥርዓተ ምግብ ማስተባበሪያ ቢሮዎች በተለያዩ ወረዳዎች እንዲሰፉ ተደርጓል። የጤና፣ የግብርና፣ የትምህርት እና የውኃ ዘርፎች የተመጣጠነ ምግብ ተደራሽነት መለኪያዎችን በተግባራዊ ዕቅዶቻቸው ውስጥ አካተዋል። ይህ ምዕራፍ ቴክኖሎጂን በስፋት መጠቀም የተቻለበት ነው። ዲጂታል ምስላዊ መግለጫዎችና የሁኔታዎች መከታታያና መቆጣጣሪያ ሥርዓቶች በሁሉም ደረጃ ውሳኔ አሰጣጥ ላይ ለውጦች እንዲመጡ አስችሏል። የሰቆጣ ቃል ኪዳንን የሚተገብሩ በርካታ የመስክ ሠራተኞች እና ባለሙያዎች ወደ ሥራ የተሰማሩት በሥርዓተ ምግብ ዕቅድ ቀረጻ፣ በበጀት ዝግጅትና ትግበራ ላይ ተከታታይ ሥልጠናዎችን በመውሰድ
ነው። የሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም የሴቶች እና ወጣት ጥምረቶች ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ በስፋት በማከናወን ለውጥ እንዲመጣና ተጠያቂነት እንዲሰፍን አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ።
አየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ ሌሎች ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ ክስተቶች፣ የፋይናንስና የሀብት አሰባሰብ እንዲሁም የአቅም ግንባታ ውስንነቶች በዚህ ምዕራፍ በተግዳሮትነት ይጠቀሳሉ። በሌላ መልኩ በምዕራፉ ማጠናቀቂያ (በ2018 ዓ.ም) ትግበራ የሚከናወንባችውን ወረዳዎች ወደ 520 ለማድረስ ዕቅድ መያዙን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።
የማስፋት ምዕራፍ (ከ2019 - 2022 ዓ.ም)
ሶስተኛው ምዕራፍ የሰቆጣ ቃል ኪዳንን አገራዊ መልክ እንዲያዝ የማድረግ ምዕራፍ (Scale-up phase) ይሰኛል። ይህ ምዕራፍ ቃል ኪዳኑ ሙከራ እና ማስፋፊያን ተሻግሮ የሕጻናትን መቀንጨር ታሪክ የማድረግ ውጥን ወደሚያሳከበት ደረጃ የሚያሸጋገርበት ነው። በዚህ ምዕራፍ የሰቆጣ ቃል ኪዳንን በኢትዮጵያ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች ለመተግበር ዕቅድ የተያዘ ሲሆን በተለይም የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትን በወረዳዎቹ ተደራሽ የማድረግ ጉዳይ የተለየ ትኩረት ተሰጥቶታል። የተመጣጠነ ምግብ ተኮር አገልግሎቶች በሁሉም ወረዳዎች ላይ ተቋማዊ መዋቅር እንዲኖረው የማድረግ ግብ ተይዟል። የአካል መቀጨጭ እና ከልኩ ያነሰ የክብደት መቀነስ ምጣኔዎችን መቀነስ፣ ነፍሰጡር እናቶችና ታዳጊ ሕጻናት በሚመገቡት ምግብ ውስጥ ያሉትን ንጥረ ምግቦች አቅርቦት መጨመር፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና በቤተሰብ ደረጃ የንጥረ ምግቦች ብዝሃነትን
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
ማስፋት ትኩረት ተሰጥቷቸዋል። በተለይም ለበለጠ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ዓመቱን ሙሉ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ በንጥረ ነገር የበለጸገና በተመጣጣኝ ዋጋ የሚገኝ ምግብ እንዲያገኙ ለማድረግ እንደሚሰራ በቃል ኪዳን ሰነዱ ላይ ሰፍሯል።
ለተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የማይበገርና ጠንካራ ምላሽ የሚሰጥ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ሥርዓት መገንባትንም አካቶ ይዟል። የሰቆጣ ቃል ኪዳንን ከለጋሾች ድጋፍ በማላቀቅ በአገር በቀል ፋይናንስ የመተካት ውጥን ከመጨረሻው ምዕራፍ አንኳር የትኩረት ማዕከሎች መካከል በዋናነት የሚጠቀስ ነው። በሁሉም የመንግሥት የአስተዳደር እርከን ውስጥ የባለድርሻ አካላት የዕቅድ ቀረጻ፣ ትግበራ እና የክትትል ሥርዓትን ተቋማዊ መልክ ማስያዝ፣ በማኅበራዊ እና የባህሪይ ለውጥ የተግባቦት ሥራዎች ላይ የሚፈሰውን መዋዕለ ንዋይ በማሳደግ በተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ዘላቂ ለውጥ መፍጠር ትኩረት የተሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው። የሃይማኖት መሪዎች፣ የሴቶች አደረጃጀቶች እና የወጣቶች ጥምረቶች በየአካባቢያቸው ያሉ ችግሮችን በመፍታት ለወከሉት ማኅበረሰብ ተምሣሌት እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚገባ ተቀምጧል። በሁለተኛው ምዕራፍ ውጤቶች የተገኘበትን የኢኖሼሽን፣ ቴክኖሎጂ እና የምርምር ሥራዎችን በላቀ ደረጃ ለመጠቀም እንደሚሠራ የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
በማጠቃለያ ምዕራፉ በመቀንጨር እና በተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ላይ የሚለካና አገር አቀፋዊ ተጽዕኖ ያለው ውጤት የማግኘት ትልቅ ራዕይ ተሰንቋል።
ሁሉንም ሕጻናት በተቀናጀ የሥርዓተ ምግብ ሥራ ውስጥ ተጠቃሚ የማድረግ ዓላማን የያዘ ሲሆን የሰቆጣ ቃል ኪዳን ለኢኖቬሽንና ለአካባቢያዊ ባለቤትነት አጽንኦት ይሰጣል። በዚህ ምዕራፍ የሚታዩ ለውጦች በባለድርሻ አካላት የሥርዓተ ምግብ መረጃ ሥርዓት (MNIS)፣ በብሔራዊ የዳሰሳ ጥናቶችና በማኅረሰብ ደረጃ በበለጸጉ የውጤት መለኪያዎች ክትትል ይደረግበታል።
መቋጫ - ከቃል ኪዳን ወደ ታሪካዊ አሻራ
እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ባለፉት አሥርት ዓመታት መቀንጨርን መከላከል ላይ የነበሩ ስኬቶችን ወደኋላ ሊመልሱ የሚችሉ ጉዳዮች አሉ ሲል ስጋቱን ያስቀምጣል። መቀንጨር አሁንም ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት መሆኑ ቀጥሏል። ዩኒሴፍ አገራት መቀንጨርን ለመከላከል የሚመድቡትትን ገንዘብ ካልጨመሩና የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ላይ በላቀ ትጋት ካልሰሩ ያሉ ለውጦች ወደኋላ ይመለሳሉ ሲል አስጠንቅቋል። የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትን እና የምገባ መርሃ ግብሮችን ማስፋት፣ ከመቀንጨር ውጪ የአካል መቀጨጭ ችግርን ለመፍታት የክትትልና ቁጥጥር ሥርዓትን ማጠናከር እንዲሁም የምግብ ዋስትና፣ የግል ንጽህና አጠባበቅ፣ የእናቶች ጤና ክብካቤና ትምህርትን ጨምሮ መቀንጨርን አስቀድመው መከላከል የሚያስችሉ ንጥረ ምግብ ተኮር ሥራዎችን ማከናወን እንደሚገባ አሳስቧል።
ዩኒሴፍ መቀንጨር አስፈላጊው እርምጃ በጊዜ ከተወሰደበት የሕጻናትን ዕድገትና ጤና መጠበቅ እንደሚቻል ያስቀምጣል። ቅድመ መከላከል ቁልፉ መሣሪያ እንደሆነም ይገልጻል። በ2017 በጀት
ዓመት የሰቆጣ ቃል ኪዳን ትግበራ ሽፋንን ወደ 334 ወረዳዎች ማድረስ መቻሉን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። በበጀት ዓመቱ የሰቆጣ ቃል ኪዳን ትግበራን በማስፋት ከ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ዕድሜያቸው ከሁለት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትን እንዲሁም ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ነፍሰ ጡር እና የሚያጠቡ እናቶችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የአፈጻጸም ሪፖርቱ ያሳያል። በአገር አቀፍ የጤና መድህን የጤና አገልግሎትን ለማጠናከርና ሽፋኑን ለማስፋት በሚደረገው ጥረት በ2017 በጀት ዓመት ከአባላት መዋጮና ከመንግሥት ድጋፍ ከ19 ቢሊዮን ብር በላይ ማሰባሰብ ተችሏል። በ2018 በጀት ዓመት የሰቆጣ ቃል ኪዳን ፍኖተ ካርታ አፈጻጸምን ወደ 520 ወረዳዎች (70 በመቶ) ለማድረስ መታቀዱ እና ለዚህም 3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በጀት እንደሚያስፈልግ ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
በቃልኪዳኑ መሠረት በ2022 ዓ.ም መቀንጨርን ዜሮ ለማድረግ የምግብና ሥርዓተ ምግብ ተግባራትን ሽፋን ማሳደግ እንዲሁም በቂ ሀብት መመደብ ላይ በሁሉም ክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች ተመሳሳይ ሥራዎችን ማከናወን እንደሚገባ በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል። የሰቆጣ ቃል ኪዳንን እስከ ታችኛው የቀበሌ መዋቅር ማስተግበር ከተቻለ፤ መቀንጨርን እንደ አገር ማስቀረት እንደሚቻልም ተወስቷል። ሥርዓተ ምግብን ለማሻሻልና ሀገራዊ የጤና ግቦችን ለማሳካት የሌማት ትሩፋት፣ የአረንጓዴ አሻራ እና ሌሎች ኢኒሼቲቮች ወሳኝ ሚና እያበረከቱ መሆኑንም ገልጿል።
ኢትዮጵያም የሕጻናትን መቀንጨር ታሪክ
ለማድረግ በሰቆጣ ቃል ኪዳን አማካኝነት የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት እና የንጥረ ነገሮችና ኃይል ሰጪ ምግቦችን ተደራሽነት ማረጋገጥ ላይ አበክራ እየሠራች ነው።
ከእነዚህ ሥራዎች መካከል ጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአርባምንጭ ከተማ ይፋ የሆነው የሌማት ትሩፋት አንዱ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ “ሌማት አርሶ አደሩን፣ አርብቶ አደሩን እና ሸማቹን የሚያገናኝ ድልድይ ነው፤ በቂ እና አመርቂ ምግብ ማግኘት ነው፤ በቂ የመጠን፣ አመርቂ የይዘት ጉዳይም ነው” ብለዋል። የሌማት ትሩፋት ከሰቆጣ ቃል ኪዳን አንጻር የህጻናትን በንጥረ ነገር የበለጸገ ምግብ የማግኘት ምጣኔ የሚሳድግ ሲሆን ለቤተሰብ እና ለእናቶች የተመጣጠነ ምግብ በአቅራቢያቸው እንዲያገኙ አድርጓል። የወተት ተዋጽኦዎችና የዶሮ እርባታ ብዝሃ የምግብ አማራጮችን በማስፋትና የአመጋገብ ዘይቤን በማሻሻል ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
ሌማት በኢትዮጵያ የገጠር አካባቢዎች የሚገኙ ህጻናት የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ በማድረግ መቀንጨር፣ መቀጨጭ እና የተዛባ ዕድገትን የመከላከል አስተዋጽኦ ይኖረዋል። ይህም የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትን በጠንካራ መሰረት ላይ በማስቀመጥ ህጻናት ጤናማ ዕድገት እንዲኖራቸው በማድረግ በአገር አቀፍ ደረጃ መቀንጨርን ለማጥፋትና ጤናማ ትውልድ ለመገንባት የተያዘውን ዕቅድ የሚደግፍ ኢኒሼቲቭ ነው።
ሌላው መንግሥት በአገር አቀፍ ደረጃ እየተገበረው ያለው የተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብር ከዕለት
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
ምገባ ባለፈ በተመጣጠነ ምግብ አማካኝነት የህጻናትን አካላዊና አዕምሯዊ ዕድገት ይደግፋል። በትምህርት ቤቶች ባልተቋረጠ ሁኔታ የሚቀርበው በንጥረ ነገር የበለጸገ ምግብ የሚፈልጉትን ኃይል እንዲያገኙ በማድረግ ጤናማ ዕድገት እንዲኖራቸው፣ በትምህርታቸው ላይ የበለጠ ትኩረትና የተሻለ ውጤት እንዲኖራቸው የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል።
የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር የተማሪዎችን መጠነ ማቋረጥ በመቀነስ ተማሪዎችን ውጤታማ የማድረጉ ጉዳይ በተለያዩ ጥናቶች የተረጋገጠ ነው። የሚቀርበው ምግብ ህጻናትን ከረሃብ ከመታደግ ባሻገር ቁልፍ የሚባሉ የንጥረ ምግብ ግብዓት ክፍተቶችን በሙሙላት መቀንጨር እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ይከላከላል። መርሃ ግብሩ ያልተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት አዙሪትን በመስበር ጤናማ፣ አይበገሬ እና የተማረ የሰው ኃይል መገንባትም ያስችላል።
በአጠቃላይ የሌማት ትሩፋት እና የተማሪ ምገባ መርሃ ግብሮች ብዝሃና በንጥረ ነገር የበለጸጉ የምግብ አይነቶችን በማስፋት የሰቆጣ ቃል ኪዳን የያዘውን የህጻናት መቀንጨርን ዜሮ የማድረስ ግብን እውን የሚያደርጉ ተጨማሪ አቅሞች ናቸው። የእነዚህ ተግባራት ውጤቶች በኢትዮጵያ መጪው ጊዜ ብሩህ እንደሆነ የሚያመላክቱ ናቸው።
የሰቆጣ ቃል ኪዳን በኢትዮጵያ መቀንጨርን ለማጥፋት ለተያዘው ዕቅድ የተስፋ ብርሃን ነው። የቃል ኪዳኑ ቀጣይነት ያለው ስኬታማነት በዘላቂ ኢንቨስትመንት፣ በጠንካራ የባለድርሻ አካላት ትብብር እና አይበገሬነት ላይ የተመሰረተ
መሆን ይኖርበታል። ለዚህም በአገር አቀፍ ደረጃ ያለው የባለድርሻ አካላት የትብብር ማዕቀፍ በክልል እና በወረዳ ደረጃ መስፋት ይኖርበታል። ክልላዊ የቴክኒክ ቡድኖችን ማቋቋምና ሥራዎችን በፌደራል ደረጃ ካሉ ስትራቴጂዎች ጋር ማጣጣም ያስፈልጋል።
እንደ ሥነ ምግብ ባለሙያዎች ገለጻ፤ የሰቆጣ ቃል ኪዳንን የሚያስፈጽሙ ባለድርሻ አካላት የተመጣጠነ ምግብ ፕሮግራም፣ በጀት፣ ትግበራ እና ቁጥጥር ላይ ያላቸውን የጋራ ትብብር ሊጠናከርና አቅማቸው ሊገነባ ገባል። የማኅበረሰብ መሪዎች፣ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች፣ የሴት አደረጃጀቶችና በታችኛው የአስተዳደር እርከን ያሉ አመራሮችን ያሳተፈ የተቋማዊ ባለቤትነት ሥራ በየደረጃው የማውረድ እንዲሁም አፈጻጸምን መሰረት ያደረገ የተጠያቂነት ሥርዓት መዘርጋትም ያስፈልጋል።
ለሰቆጣ ቃል ኪዳን ማስፈጸሚያ የሚያስፈልገውን የገንዘብ ፍላጎት ከመካከለኛ እና የረጅም ዘመን የወጪ ማዕቀፎች ጋር ማስተሳሰርና ማዕቀፉን የሚያስተገብሩ ቁልፍ የሴክተር ተቋማት የተቀናጀ የሀብት ማሰባሰብ ማዕቀፍ እንዲኖራቸውም ይመከራል። ከፋይናንስ ጋር በተገናኘ የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ እና የተቋማት ማኅበራዊ ኃላፊነት ፈንዶችን ጨምሮ የተለያዩ የፋይናንስ አማራጮችን በመጠቀም ዘላቂ የፋይናንስ ፍሰትን ማረጋገጥ ይገባል። የሰቆጣ ቃል ኪዳን ትግበራን አስመልክቶ ያሉ መረጃዎችን እስከ ታችኛው የአስተዳደር እርከን ድረስ የተናበበ ማድረግ የሚገባ ሲሆን የዲጂታል መሰረተ ልማትን ማስፋት የተሳለጠ የመረጃ ሥርዓት እንዲኖር የሚኖረው ሚና ወሳኝ ነው።
የተግባቦትና የግንዛቤ መፍጠር ለሰቆጣ ቃል ኪዳን ቀሪ የትግበራ ጊዜ ውጤታማነት ያለው ድርሻ ቀላል የሚባል አይደለም።
የሰቆጣ ቃል ኪዳን ውስጥ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አቅም መገንባትና ከሥርዓተ ምግብ ማዕቀፍ የበለጠ ማስተሳሰር ያስፈልጋል። በተለይም የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል ጋር የተሰናሰነ የግብርና ምርታማነትን የማሳደግ አካሄድን የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትን ከማሻሻል ሥራዎች ጋር ማቀናጀት ይገባል። ጠንካራ የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና የአደጋ ምላሽ ሥርዓትን መገንባት በአደጋዎች ወቅት ሕጻናት ሊያጋጥማቸው ከሚችል የምግብ እጥረት ወይም አቅርቦት መጓደል ሊጠብቃቸው ይችላል። ሕጻናት ብዝሃነቱ የተረጋገጠ፣ ወላጆቻቸው በተመጣጣኝ ዋጋ ገዝተው ሊመግቧቸው የሚችሉ እና ንጥረ ነገራቸው ከፍሉ ያሉ ምግቦችን ማግኘታቸውን መከታተልና የሚያስፈልገውን ምላሽ መስጠት ተገቢ ነው። ሁሉን ባሳተፈ የጋራ ሥራ የመቀንጨርን መሰረታዊ መንስኤ እንዲፈታ ማድረግ ይቻላል። በሥርዓተ ምግብ ሥራዋ በምሣሌነት የምትጠቀሰው ኢትዮጵያ
የሕጻናት መቀንጨርና የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ውስብስብ ችግሮችን ለመፍታት እያከናወነች ላለው ሥራ የሰቆጣ ቃል ኪዳን እንደ ትልቅ ማሳያ ይጠቀሳል።
ኢትዮጵያ በሰቆጣ ቃል ኪዳን የምትሻው የሕጻናት መቀንጨርን ማጥፋት ብቻ አይደለም። ጤናማ፣ ጠንካራ እና የስኬት አቅምን የታጠቀ ትውልድ መገንባት ጭምር እንጂ። ይህም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ጤናማ እና አምራች እንዲሆን ያለው ድርሻ ጉልህ ነው። የሰቆጣ ቃልኪዳን ስኬት ኢትዮጵያ በዓለም ሥርዓተ ምግብ ውስጥ ታሪካዊ አሻራ እንድትጥልና የመሪነት ሚና እንድትወጣ ያስችላታል። መንግሥት ሲመራ፣ ሕዝብ ሲሳተፍ እና የባለድርሻ አካላት ትብብር ሲጠናከር ወይም ራዕይ፣ ትብብር እና ዘላቂ ሥራ ሲጣመሩ ድምር ውጤቱ ዜሮ የሕጻናት መቀንጨር ግብ ማሳካት እንደሚቻል ሌላው ዓለም ከኢትዮጵያ ትምህርት ይወስዳል።
ማኅበራዊ
ከምቹ እስከ ልህቀት ማዕከልነት
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ እና በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ትብብር የተዘጋጀ
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
በፍቅርተ ባልቻ
ሥነ-ተዋልዶ ስለ ሴት እና ወንድ ልዩ ልዩ የመራቢያ አካላት ሥርዓትና ሥራዎቻቸው የሚያጠና ሳይንስ ነው። የታወቀ በሽታ ወይም የአካል ጉድለት አለመኖር ብቻ ሳይሆን አካላዊ፣ ማኅበራዊ እና አዕምሯዊ ሙሉ ጤነኛነትን የሚያካትት ሰፊ ፅንሰ ሀሳብ ነው። የሥነ-ተዋልዶ ጤና (Reproductive health) በአብዛኛው ከመዋለጃ አካላቶቻችን ጋር የተያያዘ ጤናችንን ይመለከታል። የሴት እና የወንድ የመራቢያ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ጤነኛ እንዲሆኑ ይሠራል - የሥነተዋልዶ ጤና።
ተግዳሮት የሌለበት ወሲባዊ ሕይወት እንዲኖረን፤ ሕመሞች ወይም ችግሮች ሲከሰቱ ደግሞ በዚያው ልክ ድጋፍ የሚሰጥበት፤ በአጠቃላይ ከሕመም፣ ከአደጋና ከጭንቀት ነጻ የሆነ የመራቢያ አካል እንዲኖር የሚሠራ የጤና ዘርፍ ነው። የሥነ-ተዋልዶ ጤና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የእናቶች እና የህጻናትን ሞት ለመቀነስ፣ ሁለንተናዊ ጤናው የተጠበቀ ብቁ ዜጋ ለመፍጠር፣ የሴቶችን እኩልነት
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
ለማረጋገጥ፣ ወዘተ ... ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል።
የሥነ-ተዋልዶ ጤና በውስጡ በርካታ አገልግሎቶችን አካቶ ይዟል። ከእነዚህ መካከል የመጀመሪያው የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ነው። የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ባልና ሚስት ዘመናዊ የእርግዝና መከላከያዎችን በመጠቀም መቼ፣ በምን ያህል ጊዜ ልዩነት እና ምን ያህል ልጆችን መውለድ እንዳለባቸው የሚወስኑበት ዘዴ ነው።
ሌላው በሥነ-ተዋልዶ ጤና የሚሰጠው አገልግሎት የእናቶችን ጤና መጠበቅ ነው። ይህም የተሟላና ደረጃውን የጠበቀ የቅድመ ወሊድ ክትትልን፣ በጤና ተቋም በሠለጠነ ባለሙያ የወሊድ አገልግሎት ማግኘትን፣ የድህረ ወሊድ ክትትል እና የተለያዩ የሕክምና አገልግሎቶችን ያካትታል። የሴት ልጅ ግርዛት እና ያለ አቻ ጋብቻ ከመሳሰሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የመጠበቅ እና ማንኛውንም አገልግሎት ያለምንም መድሎ እና መገለል የማግኘት መብትንም ያጠቃልላል።
የአባላዘር በሽታዎችን የመከላከል እንዲሁም ማከም የሥነ-ተዋልዶ ጤና የትኩረት መስኮች ናቸው። የማህፀን በር ካንሰር ልየታ እና ሕክምና፤ ከዘጠኝ እስከ 14 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ታዳጊዎች የማህፀን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት መስጠት ከሥነ-ተዋልዶ ጤና ዘርፍ የትኩረት መስኮች መካከል ናቸው። በተጨማሪም ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለመከላከል እና ለመዋጋት ይሠራል።
ለታዳጊዎች ስለ ሥነ-ተዋልዶ ሥርዓት ማስተማር፤ የመካንነት ችግር ላለባቸው የምርመራ እና ሕክምና አገልግሎቶችን መስጠት፤ የማህፀን በር እና የጡት ካንሰር እንዲሁም የማህፀን የውስጠኛው ግድግዳ ካንሰሮች ልየታ እና ሕክምና በሥነ-ተዋልዶ ጤና አማካኝነት የሚሰጡ አገልግሎቶች ናቸው።
በኢትዮጵያ የሥነ-ተዋልዶ ጤናን ለመጠበቅና ለማሻሻል መንግሥት በርካታ እርምጃዎችን እየወሰደ
ይገኛል። የጤና ፖሊሲውን ከመከለስ ጀምሮ የሥነ-ተዋልዶ ጤና የሚመራበትን ስትራቴጂ በማዘጋጀት ወደ ተግባራዊ አፈጸጸም እንዲለወጡ እየተሠራ ነው። መሠረታዊ የጤና አገልግሎቶችን ተደራሽነትና ጥራታቸውን ለማሳደግ በመንግሥትና በማኅበረሰቡ ትብብር የተከናወኑት ተግባራት ውጤታማ ስለመሆናቸው የተለያዩ አስረጂዎችን ማንሳት ይቻላል።
ሥነ-ተዋልዶ በሜዲካል ኮሌጁ
አንጋፋው የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ፤ የተደራሽነት አድማሱን እያሰፋ፣ ጥራቱን እያረጋገጠ የመጣ የእውቀትና የምርምር ተቋም ነው። በብዙ መልኩ በአገራችን በሕክምና ዘርፍ በሚሰጡ አገልግሎቶች ብሎም በመማርና ማስተማር ሥራው በምሣሌነት ይጠቀሳል።
ፕሮፌሰር ድልአየሁ በቀለ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የማህፀንና ጽንስ ሐኪም ናቸው። በሜዲካል ኮሌጁ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ያገለገሉ ሲሆን አሁን የማስተማርና የሕክምና አገልግሎቶችን ጎን ለጎን ይሰጣሉ። ፕሮፌሰር ድልአየሁ ተቋሙ ከምስረታው ጀምሮ የሥነ-ተዋልዶ አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር ያነሳሉ። ሆኖም የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑ አገልግሎቶቹን በነባሩ ህንጻ በአንዲት ጠባብ ክፍል ውስጥ እንዲሰጥ ምክንያት መሆኑን፤ ለብዙ ጊዜም የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎቶች በነርሶች እና ሚድዋይፎች (ሐኪሞች ብዙም ሳይሳተፉ) ይሰጡ እንደነበር ያስታውሳሉ።
ሲስተር ፍቅርተ እሸቴ በተቋሙ ለረጅም ዓመታት በነርስነት አገልግለዋል፤ አሁንም በማገልገል ላይ ይገኛሉ። እርሳቸው እንደሚገልጹት፤ በሜዲካል
ኮሌጁ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ ሲሰጥ ቆይቷል። በወቅቱ እናቶች ለቅድመ እና ለድህረ ወሊድ ክትትል ወደ ተቋሙ ሲመጡ የቤተሰብ ዕቅድ እና ከሥነ-ተዋልዶ ጤና ጋር የተያያዙ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ይደረግ ነበር።
እንደ አብዛኞቹ ሜዲካል ኮሌጆች ለሥነ-ተዋልዶ ጤና ትኩረት ባለመሰጠቱ በጣም አነስተኛ በሆነ በማይታይ፣ የሰዎችን ስሜትና ፍላጎት በማያከብር ሁኔታ በአንድ ትንሽ ክፍል ውስጥ የተጀመረው ይህ አገልግሎት እየተስፋፋና ከጊዜ ወደ ጊዜ የተጠቃሚው ኅብረተሰብ ቁጥርና ፍላጎት እያደገ መምጣቱን አንስተዋል።
የለውጥ እርሾ
የሥነ-ተዋልዶ ጤና ሕክምና በባህሪይው ነጻነትን፣ ምስጢራዊነትን የሚፈልግ መሆኑን ከተሞክሯቸው በመነሳት የሚገልጹት ፕሮፌሰር ድልአየሁ በተገልጋዮች ፍላጎትና በተቋሙ ባለው የሥነ-ተዋልዶ አገልግሎት አሰጣጥ መካከል ያለውን ክፍተት በተመለከቱ በጎ አድራጊዎች አማካኝነት አዲስ ሀሳብ መምጣቱን ጠቅሰዋል።
ይህን ተከትሎ በአዲስ አሰራርና አደረጃጀት እንዲሁም አገልግሎት መስጫ ቦታ በማመቻቸት “ምቹ ክሊኒክ” የሚል ስያሜ የተሰጠው የሥነ- ተዋልዶ ጤና ላይ የሚሠራ ክሊኒክ ተቋቁሟል። ክሊኒኩ ተገልጋዮች እንደመጡ ወዲህና ወዲያ ማለት ሳይጠበቅባቸው በቀጥታ ገብተው የፈለጉትን የሕክምና እና የምክር አገለግሎቶች እንዲያገኙ አስችሏቸዋል።
ምቹ ክሊኒክ በሥነ-¬ተዋልዶ ጤና የሚሰጠውን አገልግሎት ለማስፋት ብሎም ለተጠቃሚዎች
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
ተስማሚ በማድረግ ረገድ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዳለው አያጠያይቅም። ክሊኒኩ ወደ ሥራ መግባቱን ተከትሎ የአገልግሎት አድማሱን በማስፋት የማህፀን ጫፍ ካንሰር ልየታ እንዲሁም ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች ማማከር እና የሕክምና አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ሲስተር ፍቅርተ ገልፀዋል።
ክሊኒኩ ከአሥር ዓመት በፊት ሲቋቋም ይዞ የመጣው ሀሳብ፣ አደረጃጀት እንዲሁም አሠራር በአገር አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያ ስለነበር እንደ ምሣሌ ተወስዶ አሥር በሚጠጉ የጤና ተቋማት ምቹ ክሊኒክ ተከፍቷል። የዓለም አገራትን ልምድ በመውሰድ የተከፈተው ይህ ክሊኒክ በተቋሙ ከሚሰጡ ሌሎች አገልግሎቶች በተለየ መልኩ በማስተናገድ ተቀባይትን ማግኘቱን በወቅቱ የነበሩ ባለሙያዎች ምስክሮች ናቸው።
ተቋሙ የማስተማሪያ ኮሌጅ እንደመሆኑ በመማር ማስተማር ላይ የተቀናጀ አሠራር እንዳልነበር የሚያነሱት ባለሙያዎቹ ምቹ ክሊኒክ ወደ ሥራ ከገባ በኋላ የቅድመ እና የድህረ ምረቃ ተማሪዎች የተግባር ልምምድ በማድረግ ክህሎት ይዘው እንዲወጡ ማድረግ መቻሉን በመጥቀስ የክሊኒኩን አስተዋጽኦ አመላክተዋል። በምቹ ክሊኒክ ሐኪሞች፣ ነርሶች እና ሚድዋይፎች የተቀናጀ አገልግሎት የሚሰጡበትን አሠራር ለማበጀት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል።
የሥነ-ተዋልዶ ጤና ተገልጋዮችን ከሌሎች ታካሚዎቸ ጋር በአንድ ቦታ ለማስተናገድ አስቻይ ያልሆኑ የተለያዩ ምክንያቶች እንዳሉ ፕሮፌሰር ድልአየሁ ሲያብራሩ “ግላዊነትን መጠበቅ ሊያስቸግር ይችላል፣ ውጣ ውረድም
ስለሚኖረው ለሌላ እንግልት ይዳረጋሉ። ጾታዊ ጥቃት የደረሰባት ሴት ብዙ ሥነ-ልቦናዊ ችግር ውስጥ ነው የምትሆነው። ጽንስ ለማቋረጥ ሕጉ የሚፈቅድላቸው እናቶች በተለያዩ ውጣ ውረድ ውስጥ ቢያልፉ ብዙ ይቸገራሉ“ ብለዋል። ምቹ ክሊኒክ ለዚህ መፍትሔዎችን አስቀምጧል፤ የመጀመሪያው ቦታው ፊት ለፊት እንዲሆን፣ ሌላው ከሌሎች አገልግሎቶች በተለየ መልኩ በክሊኒክ ውስጥ ካርድ እንዲያወጡና ያለ ምንም ውጣ ውረድ በቀላሉ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ናቸው።
በክሊኒኩ አገልግሎት አሰጣጥ ወቅት የሚያጋጥሙ ችግሮች አሁንም ማደግ እንዳለበት በማመላከታቸው ወደ ሌላ ምዕራፍ እንዲሸጋገር መነሻ መሆናቸውን ያወሱት ፕሮፌሰር ድልአየሁ፤ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ፣ ቦታው እየጠበበ እና አገልግሎት ለመስጠት በማስቸገሩና አገልግሎቱን በስፋት መስጠት የሚያስችል የራሱ ማዕከል የማዘጋጀት ሃሳብ በመምጣቱ የአዲስ ህንጻ ግንባታ ተወጠነ ይላሉ።
አዲስ ምዕራፍ …
የምቹ ክሊኒክ አቅም እና የተገልጋዮች ፍላጎት የተመጣጠነ ባለመሆኑ ክሊኒኩን ወደ ልህቀት ማዕከልነት ለማሳደግ የተወጠነ ሲሆን ተቋሙ ይህንን ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በመቀየርና የተለያዩ ተባባሪ አካላትን በማሳተፍ ያስገነባው ባለ አራት ፎቅ ዘመናዊ ህንጻ ጳጉሜን 2 ቀን 2017 ዓ.ም ለምረቃ በቅቷል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ
ኃላፊዎች ተገኝተዋል። በዕለቱም የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ መሰል ማዕከላት ለሁለንተናዊ አገራዊ ዕድገት ሁነኛ ሚና ስለሚኖራቸው በመላ አገሪቷ እንዲስፋፉ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
የሥነ-ተዋልዶ ጤና የልህቀት ማዕከል (Center of Excellence in Re- productive Health) የሚል ስያሜ የተሰጠው የቀድሞው ማዕከል በተዘጋጀለት አዲስ ህንጻ ሙሉ በሙሉ የሥነ-ተዋልዶ ጤና ሕክምና እንዲሰጥ ተመቻችቷል። አሁን ሴቶች እና ሕጻናት በምቹ ክሊኒክ ይሰጡ የነበሩ ሁሉንም ዓይነት የሥነ-ተዋልዶ ጤና አገልግሎቶችን ጥራትና ደረጃቸውን ጠብቀው የሚያገኙበት 11 ክፍሎች አሉት። አገልግሎት ለማግኘት የሚመጡ እናቶች ልጆቻቸውን የሚያቆዩበት ማረፊያ ክፍል እና የሚጫወቱበት ሥፍራም ተዘጋጅቶላቸዋል።
በማዕከሉ ራሱን የቻለ ዘመናዊ የቀዶ ሕክምና ክፍል መኖሩን በሥነ-ተዋልዶ ልህቀት ማዕከል ጠቅላላ ሐኪም እና አስተባባሪ ዶክተር አማኒ ኑረዲን ነግረውናል። ጥናት እና ምርምሮች የሚካሄዱባቸው ምቹ ስፍራዎችም ተዘጋጅተዋል። በልህቀት ማዕከሉ የሕክምና አገልግሎት አሰጣጡን ተኝተው እና በተመላላሽ የሚታከሙ በሚል የገለጹት ዶክተር አማኒ በማዕከሉ ተኝተው ለሚታከሙ 20 አልጋዎች
እንዲሁም አራት የማገገሚያ ክፍሎች መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።
በህንጻው ላይ ተማሪዎች ከመመረቃቸው በፊት ልምዳቸውን ለማዳበር ልምምድ የሚያደርጉበት ቦታ የተመቻቸ ሲሆን ቤተ-መጻህፍትም ይገኛል። ለምረቃ የበቁ ሐኪሞች እና ባለሙያዎች ዕውቀትን እና ልምዳቸውን የሚያዳብሩበትና ሥልጠና የሚያገኙበት ቦታም ተዘጋጅቷል።
የማዕከሉ መስፋፋት ደንበኞች ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኙ አስችሏል የሚሉት ሲስተር ፍቅርተ ከዚህ ቀደም በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚቻለው አንድ ሰው ብቻ እንደነበረና አሁን አስፈላጊ ግብዓቶች ስለተሟሉና በቂ ክፍሎች ስላሉ በርካታ ተገልጋዮቸን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ እንዳስቻላቸው ገልፀዋል።
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
ማዕከሉን ምን ልዩ ያደርገዋል?
በሜዲካል ኮሌጁ በሥነ-ተዋልዶ ሕክምናዎች ላይ አሉ የሚባሉ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ብቁ ሐኪሞች፤ በእነዚህ ባለሙያዎች በተለያየ ደረጃ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ያሉ ሐኪሞች ይገኛሉ። እነዚህ ሁሉ በአንድ ላይ ሆነው ሚድዋይፍ እና ነርሶችም ተጨምረው የየዕለቱን አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋል።
የልህቀት ማዕከሉ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት አማራጮች በሙሉ (ሁሉንም ዓይነት ዘዴዎች) ማካተት ይኖርበታል፤ እየተሠራ ያለውም ሁሉንም ዓይነት አማራጮች ለተገልጋዮች ለማቅረብ ነው። ለረጅም ጊዜ የሚያገለግሉ የቤተሰብ ዕቅድ አማራጮች በማዕከሉ በልዩነት እና በሰፊው የሚሰጡ አገልግሎቶች ናቸው። ከአንዳንድ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ጋር በተያያዘ ከበድ ያሉ ጉዳዮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ። ለእነዚህ ጉዳዮች የመጨረሻ የተባለውን መፍትሔ ለመስጠት እንደሚሠሩ የልህቀት ማዕከል የተሰኘበትም አንደኛው ምክንያት ይኸው መሆኑን ነው ፕሮፌሰር ድልአየሁ የሚገልፁት።
በአገራችን ፅንስ ማስወረድ ሕጋዊ የሚሆንባቸውና የሚፈቀድባቸው ሁኔታዎች አሉ። በአስገድዶ መደፈር (በተለይም በቅርብ ቤተሰብ) ምክንያት የተረገዘ ከሆነ፣ በእርግዝናው ምክንያት የእናትየው የጤና ሁኔታ አስጊ ሲሆን፣ ልጁ ከተወለደ በኋላ በሕይወት መቆየት እንደማይችል በተለያዩ ምርመራዎች ከተረጋገጠ እንዲሁም ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች እርግዝና ሲያጋጥማቸው ፅንሱ እንዲቋረጥ ሕጉ ይፈቅዳል።
“ከዚህ ቀደም እነዚህ አገልግሎቶች ተደራሽ ስላልሆኑ ሴቶች ወይም አፍላ ወጣቶች ወደ ሕገወጥ ውርጃ ይሄዳሉ፤ በዚህ ምክንያት በጣም ብዙ ሞቶችን እናይ ነበር፤ የማህፀን መውጣት፣ መድማት የመሳሰሉት አደጋዎችም ያጋጥሙ ነበር። አሁን አገልግሎቱን ወደ ማዕከሉ በመምጣት ማግኘት ይችላሉ። ይህ ደግሞ በእነዚህ ምክንያቶች የሚሞቱ እናቶችን ቁጥር ለመቀነስ ብሎም ጤንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ለማድረግ የሚኖረው አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም” ብለዋል ፕሮፌሰር ድልአየሁ።
ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች እና ሕጻናት ወደ ማዕከሉ በመምጣት ከሕክምና ጀምሮ እስከ ፖሊስ ምርመራ ድረስ ያሉ ሁሉንም ዓይነት አገልግሎቶች
በአንድ ላይ ይሰጣሉ። ጾታዊ ጥቃት ላጋጠማቸው ሴቶች የሚሰጡ አገልግሎቶችን የእርግዝና እና የአባላዘር በሽታዎች (ኤች.አይ.ቪን) ጨምሮ ምርመራ፣ ቁስለቶች ካሉ እነሱን ማከም እንዲሁም የሥነ-ልቦና ድጋፍና የማማከር አገልግሎቶች ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን የማዕከሉ ጠቅላላ ሐኪም እና አስተባባሪ ዶክተር አማኒ ጠቅሰዋል።
ጾታዊ ጥቃት እንደደረሰ ወዲያው ወደ ጤና ተቋማት የመምጣት ሁኔታ እምብዛም አልተለመደም። በዚህ ምክንያት የአባለዘር በሽታዎችና እርግዝናን ለመከላከል፣ እንዲሁም ለፖሊስ የሚሆኑ ማስረጃዎችን ለመሰብሰብ ችግር ያጋጥማል፤ በመሆኑም ችግሩ ሲያጋጥም ተገቢውን የሕክምናና የሕግ አገልግሎት ለማግኘት በአፋጣኝ ወደ ሕክምና ተቋማት መሄድ ተገቢ ነው።
በማዕከሉ ከካንሰር ምርመራና ሕክምና ጋር የተያያዙ አገልግሎቶች የሚሰጡ ሲሆን የማህፀን ጫፍ ካንሰር ተጠቃሽ ነው። የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማግኘት ወደ ማዕከሉ ለሚመጡ እናቶች ስለ ማህፀን ጫፍ ካንሰር ግንዛቤ ማስጨበጥ፣ አስቀድመው በመመርመር ራሳቸውን እንዲጠብቁ ማድረግ፣ በሽታው ካለም ቀጠሮ ሳያስፈልጋቸው ሕክምናውን ወዲያው ማግኘት የሚችሉበት አሠራር ተበጅቶ ተግባራዊ ሆኗል።
መዳረሻው …
የልህቀት ማዕከሉን በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና አግኝቶ ከሌሎች አገራት ተማሪዎችና ሐኪሞችን እየጋበዘ ከፍ ወዳለ ደረጃ የሚሸጋገርበት ሁኔታ እንደሚኖር የገለፁት ዶክተር አማኒ፤ ወደ
መዳረሻው የሚወስደውን ጉዞ መጀመሩን አክለዋል። አገልግሎት አሰጣጡን የተሟላና ጥራቱን የጠበቀ ለማድረግ፤ ባለሙያዎችን በመጋበዝ ሥልጠና እና ምርምር በማካሄድ ለማዳበርም ታቅዷል። የልህቀት ማዕከሉን አዳራሾችና ሰርቶ ማሳያዎች በመጠቀም፤ ከአጋር ድርጅቶች እና ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሥራት በአፍሪካ ታዋቂና ስመጥር የማሠልጠኛ ማዕከል ለማድረግም እንዲሁ።
ከአገር ውስጥ ባሻገር ከተለያዩ አገራት ባለሙያዎችን በመጋበዝና ማዕከሉን በማስተዋወቅ በአፍሪካ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ አገልግሎቶቹን ለማስፋት ውጥን ተይዟል። በተለይ የሴቶች እና የአፍላ ወጣቶችን ጤና በመጠበቅና በማዘመን የላቀ አገልግሎት በመስጠት አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍት ተስፋ ሰንቋል።
ፖለቲካ
አስተማማኙ መንገድ
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
በመንገሻ ገ/ሚካኤል
የሰው ልጆች የተሻለ የኑሮ ሁኔታ ፍለጋ፣ ግጭትን ለመሸሽ፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በኢኮኖሚያዊ ችግሮችና በመሳሰሉት ምክንያቶች ቀያቸውን ለቀው ይፈልሳሉ ወይም ይሰደዳሉ። ፍልሰቱ በአገር ውስጥ ወይም ከአገር ውጪ ሊሆን ይችላል። የአገር ውስጥ የምንለው ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ የሚደረገውን ነው፤ ሌላው ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር ወይም ክፍለ ዓለም የሚደረግ ጉዞ ነው። ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (IOM) ሪፖርት እንደሚያሳየው በፈረንጆቹ አቆጣጠር 2024 ዓ.ም ብቻ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ281 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በስደተኝነት ተመዝግበዋል። ቁጥሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደሆነም ሪፖርቱ አመላክቷል።
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
በተለይም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በዓለማችን እየተካሄዱ ያሉ ጦርነቶችና አለመረጋጋቶች መፈናቀልን በማስከተል የስደተኞች ቁጥር ከፍ እንዲል አድርጓል። ሰዎች አገራቸውን ጥለው ከሚሰደዱባቸው መንገዶች ሕጋዊውና ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ በሕግ የተደገፈው ፍልሰት ወይም ስምሪት አንደኛው ነው። ሁለተኛው በሕገወጥ መንገድ ድንበር በማቋረጥ የሚደረገው ፍልሰት ነው። አሁን አሁን ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ወይም ስደት በተለየ ሁኔታ ስር የሰደደ ችግር ሆኖ ዓለምን እያነጋገረ ነው። በተለይም አፍሪካ ከፍተኛ የወጣቶች ፍልሰት እና ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር በቀዳሚነት የሚስተዋልበት አህጉር ነው። የዓለም መንግሥታትና ተቋማት ሕገወጥ ስደትን ለመቀነስ ቢቻል ደግሞ ለማስቆም የተለያዩ እርምጃዎችን ሲወስዱ ቆይተዋል። የስደተኞች መነሻ የሆኑትም ሆኑ ስደተኞች የሚመጡባቸው አገራት ስደትና ስደተኞችን ይከላከሉልናል ያሏቸውን እርምጃዎች ሲወስዱ ቆይተዋል። ሰዎች ከሚኖሩበት ስፍራ በሕገ-ወጥ መንገድ
እንዲወጡ የተለያዩ ገፊ ምክንያቶች ቢኖሩም በተለይም በታዳጊ አገራት ላይ በስፋት የሚስተዋለው የተሻለ ኑሮ ፍለጋ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። በኢትዮጵያም በርካታ ዜጎች በሕገወጥ መንገድ የሚሰደዱ ሲሆን እንደ ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ የሚወሰደው ሥራ አጥነት ነው። የሕገወጥ ደላሎች መበራከትና ስደትን እንደ መልካም አጋጣሚ መመልከት በሕገወጥ መልኩ ለሚከናወነው ስደት ሌላው መንስኤ ስለመሆኑ ይገለጻል። ሕገወጥ ስደትን ለመከላከል በአገር ውስጥ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር ዜጎች በሕጋዊ መንገድ ብቻ ወደ ተለያዩ አገራት ተንቀሳቅሰው መሥራት የሚያስችላቸውን አሠራር መዘርጋት ያስፈልጋል። መንግሥት የፍልሰተኞችን ተጋላጭነት በመቀነስና የዜጎችን ደህንነት በመጠበቅ መደበኛ የሆኑ የፍልሰት አማራጮችን ለማስፋት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል። ዜጎች ሕጋዊውን መንገድ ተከትለው ወደ ሥራ እንዲሰማሩ ለማስቻል የውጭ አገር የሥራ ስምሪት አሠራርን ለመዘርጋት እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ከጥረቶቹ መካከል ነው። መንግሥት
በውጭ አገር ለሥራ የሚሰማሩ ኢትዮጵያዊያን መብታቸው፣ ደህንነታቸውና ክብራቸው በዘላቂነት መጠበቁን ለማረጋገጥ የተለያዩ የለውጥ ተግባራትን እያከናወነ ነው። ከዚህ አንጻር በቴክኖሎጂ የተደገፈ ቀላልና ቀልጣፋ የውጭ አገር ሥራ ስምሪት አገልግሎት መስጠት በቀዳሚነት ይጠቀሳል።
የውጭ አገር ሥራ ስምሪት ለምን?
ወጣቶችን በአደገኛ ጉዞ ከኢትዮጵያ ለመሰደድ ከሚያበቋቸው ምክንያቶች አንዱ በአገር ውስጥ ያለው የሥራ አጥነት ችግር መሆኑ አያጠራጥርም። ዜጎች በሕገወጥ እንቅስቃሴ ከአገር ሲወጡ ለበርካታ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና አካላዊ ጉዳቶች የሚጋለጡበት አለፍ ሲልም ባሕር ላይ ሕይወታቸውን የሚያጡበትና የደላሎች ሲሳይ የሚሆኑባቸውን አጋጣሚዎች ማየት የተለመደ ሆኗል። የውጭ አገር ሥራ ስምሪት ሕጋዊ ማዕቀፍ እንዲኖረው የሚደረግበት አንደኛው ምክንያት ሕገወጥ የሰዎችን ፍልሰት ለመከላከል ነው። የሥራ ስምሪትን ሕጋዊ ማድረግ ዜጎች የመንግሥት ከለላ አግኝተው
ደህንነታቸውና ክብራቸው ተጠብቆ ወደ ሥራ እንዲሰማሩ ከማድረግ አንጻር ትልቅ ጠቀሜታ አለው። የውጭ አገር ሥራ ስምሪት ለዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ የላቀ ፋይዳ አለው። ሕጋዊ የውጭ አገር ሥራ ስምሪት እንደ ሥራ ዕድል አማራጭ ተደርጎ ይወሰዳል። የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ዳንኤል ተሬሳ በዓመት ለግማሽ ሚሊዮን ያህል ዜጎች በውጭ አገር ሥራ ስምሪት የሥራ ዕድል መፍጠር እንደተቻለ ይናገራሉ። ሌላው የውጭ አገር ሥራ ስምሪት አስፈላጊ የሚሆንበት ምክንያት ዜጎች በውጭ አገር በሥራ ላይ በሚሰማሩበት ጊዜ ከአገራቱ እውቀትና ልምድ ቀስመው ሲመለሱ በአገራቸው ሁለንተናዊ ዕድገት ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ ተብሎ መታሰቡ ነው። የውጭ አገር ሥራ ስምሪት ኢትዮጵያ ከሬሚታንስ የምታገኘውን ገቢ ከማሳደግ አኳያ ያለው አስተዋጽኦም የላቀ ነው። በሁለት አገራት መካከል የሠራተኞች ልውውጥ በሚኖርበት ጊዜ ለሠራተኛው አቅራቢ ብቻ ሳይሆን ለተቀባዩም ከፍተኛ ጠቀሜታን ያስገኛል። ስለሆነም የውጭ አገር ሥራ ስምሪት የአገራት የሁለትዮሽ መልካም ግንኙነት መፍጠሪያ መሣሪያ ተደርጎ ይወሰዳል። በአጠቃላይ
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
በሕጋዊ መንገድ የሚደረግ የውጭ አገር ሥራ ስምሪት ለአገርም ለዜጎችም የሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ፋይዳ ቀላል የሚባል አይደለም።
አሰራሩን ለማዘመን
በአገራችን የውጭ አገር ሥራ ስምሪት መደበኛ ወይም ሕጋዊ አሠራርን ተከትሎ አገልግሎት መስጠት የተጀመረው በ1990ዎቹ መጀመሪያ እንደሆነ ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል። የውጭ አገር ሥራ ስምሪት ከዚያ ቀደም ሲልም የነበረ ቢሆንም በሕግ ተደግፎ ኤጀንሲዎች ፍቃድ አውጥተው አገልግሎት መስጠት የጀመሩበትና ዘርፉ በሕግ እንዲመራ የተደረገው በ1990ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ነው። ታዲያ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የዘርፉን ዕድገት ግምት ውስጥ በማስገባት፣ በየጊዜው የሚለዋወጡ ነባራዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ በማድረግ የውጭ አገር ሥራ ስምሪት የሚመራባቸው የሕግ ማዕቀፎች በየጊዜው እየተሻሻሉ መጥተዋል። የውጭ አገር ሥራ ስምሪት ትልቁ እና ዋነኛው ጉዳይ በሕግና በፖሊሲ የተደገፈ የውጭ ሥራ ስምሪት ወይም የሠራተኛ ስምሪትን ማካሄድ ነው የሚሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ሚኒስቴሩ በአዲስ መልክ ከተደራጀበት ባለፉት አራት ዓመታት ዜጎች ወደ ውጭ አገር በመሄድ የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ከማድረግ አንጻር በርካታ የሪፎርም ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰዋል። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባለፉት ሦስት ዓመታት የውጭ አገር ሥራ ስምሪትን ለማዘመን ተግባራዊ ካደረጋቸው የለውጥ ሥራዎች መካከል አገልግሎት አሰጣጡን ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ወረቀት አልባ በማድረግ በዲጂታል ሥርዓት መተካቱ ነው። በዚህም የሥራ ገበያን በዲጂታል ሥርዓት
መምራት የሚያስችል የዳታቤዝ ማዕከል ተገንብቶ ወደ ሥራ ተገብቷል። ሚኒስቴሩ ያበለጸገው የኢትዮጵያ ሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት E-LMIS- ብቁ (Ethiopian Labor Market Information System) በኢትዮጵያ ያለውን የሥራ ሥርዓት ግዙፍ በሆነ ሲስተም ቀጣሪን ከሠራተኛ፣ ሠራተኛን ከሥራ ጋር እንዲሁም አጠቃላይ በሥራ ዙሪያ ያሉ ተግባራትን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ ሲሰራ ቆይቷል። ዜጎች ለውጭ አገር የሥራ ስምሪት የሚመዘገቡበትና ተያያዥ አገልግሎቶችን የሚያገኙበት በወረዳ ደረጃ አንድ ማዕከል በማቋቋምና በሲስተም በመታገዝ በሁሉም ክልሎች ሥራ ፈላጊዎች አቅራቢያቸው በሚገኙ ማሠልጠኛ ተቋማት እንዲሠለጥኑ በማድረግ ላይ ይገኛል። ይህ አሰራር የዜጎችን እንግልት ከመቀነስ ባሻገር ከተቀባይ አገር አሠሪዎቻቸው ኮንትራታቸው በአጭር ጊዜ እንዲመጣላቸው አስችሏል። ከሦስት ዓመት በፊት አንድ ውል ለማጽደቅ እስከ ሦስት ወር ይፈጅ የነበረ ሲሆን አሁን አገልግሎቱ በቴክኖሎጂ የተደገፈ በመሆኑ ከአምስት ደቂቃ በላይ እንደማይወስድና ሚኒስቴሩ በቀን ከሁለት ሺህ በላይ የሠራተኞችን ውል እያጸደቀ መሆኑን አቶ ዳንኤል ገልፀዋል። እየተተገበረ ያለው የሌበር ማርኬት ሲስተም ከሁሉም ኤምባሲዎች ጋር የተሳሳረ በመሆኑ በውጭ አገር የሚሰማራውን ሠራተኛ እንቅስቃሴ ለመከታተል የሚያስችልና የትኛውም በውጭ አገር ያለ ዜጋ ችግር ቢያጋጥመው በአንድ ጥሪ ወደ ኤምባሲ መልዕክት ማስተላለፍ ያስቻለ ነው። በሌላ የሚኒስቴሩ የሪፎርም ሥራ ወደ ውጭ አገራት ለሥራ የሚሰማሩ ዜጎች የ21 ቀን የክህሎት ሥልጠና መስጠት ይጠቀሳል። ሥልጠናው ዜጎች
በሥራ ገበያ ውስጥ ብቁ እና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ዕውቀቶችን ለማስጠበቅ እንዲሁም ከዚህ ቀደም በመደበኛ ወይም በኢ-መደበኛ መንገድ የቀሰሟቸውን የቀደሙ ዕውቀቶች እና ክህሎቶችን የሚያዳብሩበት ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ አንደኛው የመወዳደሪያ አቅማችን ሥልጠና ነው የሚሉት ሚኒስትር ዴኤታው ዜጎቻችን ከተለያዩ አካባቢዎች ስለሚመጡ የሚሄዱበት አገር ምን እንደሚጠብቃቸው የሚያስገነዝብ ሥልጠና በየዘርፉ እየተሰጣቸው ነው ይላሉ። ሥልጠናቸውን አጠናቀው ወደ ውጭ አገራት የሚሄዱ ዜጎች ብቃታቸው በምዘና ተረጋግጦ የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ይሰጣቸዋል። ማንኛውም በውጭ አገር ለሥራ የሚሰማራ ሠራተኛ በሚቀጠርበት የሥራ መስክ ትምህርት ወይም ሥልጠና ወስዶ ወይም በማንኛውም ሁኔታ ዕውቀትና ክህሎት አግኝቶ አግባብነት
ካለው የትምህርት ተቋም ወይም የምዘና ማዕከል የተሰጠ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ማስረጃ መያዝ እንደሚኖርበት ተገልጿል። ሥልጠናው ወደ ውጭ አገር የሚሰማሩት ሠራተኞች ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያስችል ነው። የሥራ ገበያ ፍላጎትን መሰረት ባደረገ መልኩ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከተቀባይ አገሮች እና ሕጋዊ ድርጅቶች ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት በመፈራረም ሕጋዊ የውጭ አገር ሥራ ስምሪትን ለማጠናከር እየሰራ እንደሆነም ተጠቅሷል። ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከስድስት የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት የተፈራረመች ሲሆን እነሱም ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ኳታር፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬት፣ ጆርዳን፣ ሊባኖስ እና ኩዌት ናቸው። ይህን ሂደት መከተል ያስፈለገው ዜጎች በሚሰማሩባቸው አገራት የሚደርስባቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በማስቀረት ክብራቸው፣ ደህንነታቸውና ጥቅማቸውን ለማስከበር ነው።
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
ሕጋዊ የሥራ ስምሪቱን በቴክኖሎጂ በመታገዝ ለመምራት በተከናወኑ ሥራዎች በርካታ ውጤቶች ተገኝተዋል። አገሪቷ ከውጭ አገር ስምሪት ዘርፍ ማግኘት ያለባትን ጥቅም ለማስጠበቅ ብልሹ አሠራርን የሚቀርፍ ሥርዓት ለመዘርጋት አስችሏል። በዚህም ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን በመከላከል ረገድ መሻሻል ታይቷል። ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር በርካታ ለውጦች የመጡበት ነው የሚሉት አቶ ዳንኤል ከአራት ዓመት በፊት በዓመት ይላኩ የነበሩትን ከ40 ሺህ የማይበልጡ ሠራተኞች ቁጥር ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ማድረስ ተችሏል ይላሉ። ይህ ውጤት የተገኘው መንግሥት ዘርፉን የማስተዳደርና የመቆጣጠር አቅሙን በማሳደግ፣ የዘርፍ ተዋናዮች ለሆኑት ኤጀንሲዎችም ሁኔታዎች እንዲመቻችላቸው በመደረጉ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
የተሻሻለው አዋጅ
እንደ አገር በተለያዩ ዘርፎች የደረስንበትን ደረጀ ባማከለ መልኩ ሕጎች በየጊዜው እየተሻሻሉ ነው። በውጭ አገር ለሥራ የሚሰማሩ ኢትዮጵያዊያንን የሚመለከተው የውጭ አገር ሥራ ስምሪት አዋጅም
ከአራት ዓመት በኋላ ማሻሻያ ተደርጎበታል። የአዋጁ ማሻሻያ በውጭ አገር ለሥራ የሚሰማሩ ኢትዮጵያዊያን መብታቸው፣ ደህንነታቸውና ክብራቸው በዘላቂነት መጠበቁን ለማረጋገጥ የሚያስችል ሆኖ ተዘጋጅቷል። አዋጁ የውጭ አገር ሥራ ስምሪት አገልግሎት ለዜጎች ቀልጣፋና ተደራሽ መሆን እንዲችልና ሕገወጥ የሥራ ስምሪትን መቀነስ የሚያስችል በቴክኖሎጂ የተደገፈ ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ነው። በዘርፉ የሚደረገው የሥራ ስምሪት፣ የሥልጠና ምደባ፣ የብቃት ምዘናን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶች ግልጽና ከሰው ንክኪ ነጻ የሆነ የአሠራር ሥርዓት እንዲኖራቸውም አድርጓል።
የሕግ ማሻሻያው ትልቁ መነሻ በሥራ ላይ ያጋጠሙ የሕግ ክፍተቶችን ለመቅረፍ እንደሆነ አቶ ዳንኤል ይናገራሉ። የዘርፉን ተዋንያን ለመቆጣጠርና ለማስተዳደር የማይመቹ ሁኔታዎች ስለተፈጠሩ ጥናት በማካሄድ ዋና ዋና የዘርፉ ማነቆዎችን ለመፍታት የሕግ ማዕቀፉን ማሻሻልን አስፈላጊ አድርጎታል።
ቀደም ሲል የነበሩት አዋጆች በዋናነት ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ብቻ ትኩረት ያደረጉ ሲሆኑ በአዲሱ አዋጅ ያደጉ አገራትን ለማካተት ጥረት ተደርጓል። አዲሱ አዋጅ ሥራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ራሳቸውን ሪፎርም እንዲያደርጉ የሚያስገድድም ጭምር ነው። የውጭ አገር ሥራ ስምሪት በቀጥታ ከሰዎች ሕይወት ጋር የተያያዘ ስለሆነ ማንም የሚገባበት ዘርፍ አይደለም የሚሉት አቶ ዳንኤል ዜጎች በተቀባይ አገሮች ላይ ችግር ከገጠማቸው በቶሎ ደርሰው መፍታት የሚችሉ በፋይናንስ የተደራጁ እና በዘርፉ ዕውቀትና አቅም ያላቸው ኤጀንሲዎች እንዲገቡበት ይደረጋል ብለዋል። አሁን በአገሪቷ የሚገኙ በርካታ ቁጥር
ያላቸው ኤጀንሲዎች ሰብሰብ ብለው በኩባንያ ደረጃ እንዲመጡና በኤጀንሲዎች መካከል ጤናማ የሆነ ፉክክር እንዲኖር ዕድል የሚሰጥ የሕግ ማዕቀፍ መሆኑንም አክለዋል።
ሕገ-ወጥ ስደትን ለማስቀረት የአዋጁ ፋይዳ
አዋጁ የሥራ ገበያ ፍላጎትን መሰረት ባደረገ መልኩ ከተቀባይ አገራትና ሕጋዊ ድርጀቶች ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት߹ የመግባቢያ ሰነድ ወይም አግባብነት ያለው ስምምነት በመፈራረም ሕጋዊ የውጭ አገር ሥራ ስምሪትን ያጠናክራል። በዚህም በሰው የመነገድና ሰውን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያስችላል። የተሻሻለው የውጭ አገር ሥራ ስምሪት አዋጅ ዋና ዓላማ የደላላን ሚና መቀነስ መሆኑን አቶ ዳንኤል ይናገራሉ። የውጭ አገር ሥራ ስምሪት በርካታ ዓለም አቀፍ ደላሎች የሚሳተፉበት በመሆኑ በየጊዜው ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል የሚፈልግ ዘርፍ ነው። ዜጎች በሕገ ወጥ ደላሎች እንዳይጎዱና ላልተፈለገ ወጪና እንግልት እንዳይዳረጉ ከማድረግ አንፃር ከዘርፉ የደላላን እጅ ማንሳት ያስፈልጋል። ታዲያ በአዲሱ አሰራር ሥራ ፈላጊ ዜጎች በሲስተም ላይ ከተመዘገቡ በኋላ ያለ ደላላ ጣልቃ ገብነት ኤጀንሲዎች የቀረቡትን መስፈርቶች አይተው እንዲመድቡ የሚያስችል ነው። በመሆኑም የተሻሻለው አዋጅ ሕገወጥ የሰዎችን ዝውውርን ለመግታት የመንግሥትን የመቆጣጠርና የመከታተል አቅም የሚያሳድግ ነው። የዜጋን ጥቅም፣ ደህንነትና ክብር ከማስጠበቅ ባሻገር በኤጀንሲዎች በኩል ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎችንም የሚፈታ ነው። በዚህ መልኩ የኢትዮጵያ መንግሥት ከመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ጋር የተፈራረማቸውን የሁለትዮሽ
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
ስምምነት መሰረት በማድረግ በዜጎች ፍላጐት ላይ የተመሰረተ የሠራተኛ ስምሪት እየተካሄደ ነው። የተሻሻለው ሕግ ቀደም ሲል ሠራተኞች የጤና ምርመራ፣ የትራንስፖርት በሚሉ ምክንያቶች ያወጡ የነበረውን አላስፈላጊ ወጪም አስቀርቷል። በአዲሱ ሕግ ሥራ ፈላጊዎቹ የሥልጠና እና የፓስፖርት ብቻ እንዲከፍሉ፣ የጤና ምርመራ ወጪ በኤጀንሲዎች እንዲሸፈን የሚደረግ ሲሆን የቪዛ፣ የአየር ትኬት የመሳሰሉት ወጪዎች በአሠሰሪው እንዲሸፍን ያዛል። ሠራተኛው የሚጠበቅበት ፓስፖርቱን መያዝ እና ሥልጠና መውሰድ ብቻ ነው።
ክትትልና ድጋፍ
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ባለው ግንኙነት አማካኝነት በኤምባሲዎቻችን በኩል በውጭ አገር ለሥራ ያሰማራቸውን ዜጎች ክትትል ያደርጋል። ችግሮች ሲያጋጥሙ ለኤምባሲዎች የማሳወቅ ተግባር እያከናወነም ይገኛል። ሥራና አሰሪ አገናኝ ኤጀንሲዎችም የላኳቸው ሠራተኞች ያሉበትን ሁኔታ የመከታተል ኃላፊነት አለባቸው።
ሠራተኞች ማንኛውም ዓይነት ችግር ሲያጋጥማቸው ባሉበት ሆነው መረጃ መስጠት የሚችሉበት አሠራር የተዘረጋ ሲሆን በየአገራቱ የሚገኙ ኤምባሲዎችም ፈጣን ምላሽ የሚሰጡበት ሁኔታ ተመቻችቷል። የተሻሻለው የውጭ አገር ሥራ ስምሪት አዋጅ በኤምባሲዎች የሠራተኞችን ጉዳይ የሚከታተል ሌበር አታሼ እንዲመደብ በግልፅ ያስቀምጣል።
ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር በኤምባሲዎች ውስጥ ያለ ማንኛውም ባለሙያ አጠቃላይ የሠራተኛውን ጉዳይ እንዲያግዙ ሲደረግ የቆየ ሲሆን በአዲሱ ሕግ የራሱ ሌበር አታሼ (ዲፕሎማት) እንዲመደብለት ያስገድዳል። እነዚህ እርምጃዎች በውጭ አገራት ለሥራ የሚሰማሩ ኢትዮጵያዊያን መብታቸውና ክብራቸው እንዲጠበቅ ከማድረግ አኳያ የተደረጉ ጥረቶች መሆናቸውን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ገልጿል።
ቅንጅታዊ አሠራር
የውጭ አገር ሥራ ስምሪት በርካታ ተዋናዮች የሚሳተፉበት ዘርፍ ነው። እንደ አገር ከዘርፉ መገኘት ያለባትን ጥቅም ለማግኘት ቅንጅታዊ አሠራሮች አስፈላጊ ናቸው። በዚህም ዘርፉ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የሚመራ በርካታ ተቋማትን ባቀፈ ኮሚቴ እየተመራ ይገኛል። የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ተወካዮች፣ የፀጥታ ተወካዮች የኮሚቴው አባላት ሲሆኑ በየወሩ እየተገናኙ ሥራዎችን ይገመግማሉ። በሌላ በኩል ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የተቋቋመውና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው ግብረ ኃይልም ሕጋዊ የሥራ ስምሪትን ፈጣን እና ቀልጣፋ በማድረግ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ከመቀነስ አኳያ ትልቅ አበርክቶ አለው። ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች እየተቀያየሩ በመሆናቸው ከሁሉም ባለድርሻ አካላትና መዳረሻ አገራት ጋር ያለውን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል።
ማጠቃለያ
ዜጎች በሕገወጥ መንገድ ወደ ውጭ አገር እንዲወጡ ገፊ ከሆኑ ምክንያቶች ሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎችና ደላሎች የሚሰጧቸው የተሳሳተ መረጃ አንዱ
ቅንጅታዊ አሠራር
ሲሆን በተለይም በአብዛኛው ከገጠራማው የኢትዮጵያ ክፍል በሕገወጥ መልኩ የሚሰደዱ ዜጎች ትክክለኛ መረጃ ባለማግኘታቸው እንደሆነ ይገለጻል። በመሆኑም ዜጎች ሕገወጥ መንገድ መርጠው ላልተፈለገ እንግልትና ወጪ ብሎም የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይጋለጡ ሕጋዊውን መንገድ እንዲከተሉ የማስገንዘቡ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር መገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም የውጭ አገር ሥራ ስምሪት አሠራሩ ቀላልና ቀልጣፋ መሆኑን ለማስገንዘብ እየሠራ ይገኛል። ሆኖም የውጭ አገር የሥራ ስምሪት ሰዎች በቀላሉ የሚታለሉበት ዘርፍ በመሆኑ አሁንም ችግሩን ለመቅረፍ ቀጣይነት ያላቸው የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረኮች ማዘጋጀት ያስፈልጋል። በትምህርት ቤቶች፣ በሃይማኖት ተቋማት፣ በአገር ሽማግሌዎች፣ በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በየደረጃው የግንዛቤ ፈጠራ መሥራትና የሕገ- ወጥ ፍልሰትን አስከፊነት ማስተማር የሁሉም ዜጋ ተግባርና ኃላፊነት ሊሆን ይገባል።
በአገር ውስጥ ምቹ የሥራ ዕድሎች የሚስፋፉበትን ሁኔታ ለመፍጠር መንግሥት እያደረገ ያለው ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ ወደ ውጭ አገር በመሄድ ለመሥራት ፍላጎት ያላቸውና ብቁ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን መብታቸው፣ ደህንነታቸው እና ክብራቸው ተጠብቆ ባላቸው ችሎታና አቅም ሠርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል ከመንግሥት ይጠበቃል። ዜጎች ላልተፈለገ እንግልትና ወጪ እንዲሁም ለሰብዓዊ ጥሰቶች ሳይዳረጉ መደበኛውን አሠራር ተከትለውና አስፈላጊውን ሥልጠና ወስደው ወደ ሥራ መሰማራት እንደሚችሉ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል። ወደ ውጭ አገራት ሄደው መሥራት የሚፈልጉ ዜጎችም ቀላልና ቀልጣፋ ሕጋዊ መንገድ እንዳለ መገንዘብ አለባቸው። የዜጎች የውጭ ሥራ ስምሪት ከወረዳ ይጀምራል፤ አቅራቢያቸው በሚገኝ ወረዳ ተመዝግበውና ሥልጠና ወስደው ወደሚፈልጉት አገር መሄድ እንደሚችሉ የተዘረጋወ አሠራር ይፈቅዳል። ዜጎች በዚህ ሥርዓት በተፈጠረው ዕድል ተጠቅመው ራሳቸውን ከአላስፈላጊ ወጪ እና እንግልት ማዳን ይችላሉ።
ማኅበራዊ
የቆዳ ሕክምናው
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
(በአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እና በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ትብብር የተዘጋጀ)
የስኬት ጉዞ …
በመንገሻ ገ/ሚካኤል
ለስጋ ደዌ በሽታ ህሙማን ሕክምና መስጫና መንከባከቢያ ይሆን ዘንድ በንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለሥላሴ ተመርቆ በ1924 ዓ.ም አገልግሎት መስጠት ጀምሯል። በቀድሞ ስሙ የመላው አፍሪካ የስጋ ደዌ የቲቢ መከላከያ እና ትምህርት መስጫ ማዕከል፤ የአሁኑ የአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከስጋ ደዌ ባሻገር በቆዳ ሕክምናዎች ላይ የዳበረ ልምድ ያለው ተቋም ነው። ሆስፒታሉ በስጋ ደዌ ብቻ ሳይወሰን በየጊዜው ሥራውን በማስፋት ሁሉን አቀፍ የሕክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።
ሆስፒታሉ ከሕክምና ባሻገር በሥልጠና ዘርፍም በርካታ ባለሙያዎች በማፍራት የአገር ባለውለታ ነው። የአንጋፋ ሥልጠና ማዕከል ባለቤት የሆነው ሆስፒታሉ በሕክምና ዘርፍ በርካታ ባለሙያዎችን
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
በማሠልጠንም ቀዳሚ ነው። በተለይም ከቆዳ በሽታዎች ጋር በተያያዘ ትልቅ ልምድ ያለው በመሆኑ ከአገር ውስጥ አልፎ ከተለያዩ አገራት የሚመጡ የሕክምና ባለሙያዎች ሥልጠና የሚወስዱበትና ጥናትና ምርምር የሚያካሂዱበት ትልቅ ተቋም ነው።
አበይት አገልግሎቶች
የአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሥራውን የጀመረው በቆዳ ሕክምና እንደሆነ በሆስፒታሉ የቆዳና አባላዘር ሕክምና ስፔሻሊስትና የሕክምና ክፍሉ ኃላፊ ዶክተር አለምፀሀይ ጌታቸው ይናገራሉ። ሆስፒታሉ በዋናነት የስጋ ደዌን በሽታን ለማከም የተቋቋመ ሲሆን የስጋ ደዌ ታካሚዎች ሕክምና የሚደረግላቸው በቆዳ ሐኪሞች መሆኑን ያነሳሉ። ከምስረታው ጀምሮ የቆዳ
ሕክምና አገልግሎትን ለስጋ ደዌ ታካሚዎች ብቻ ሲሰጥ የቆየ ሲሆን ከ1950ዎቹ በኋላ ባሉት ጊዜያት የቆዳ ሕክምና ክፍል በማቋቋም ከስጋ ደዌ ሕክምና ባሻገር የተለያዩ የቆዳ ሕክምና አገልግሎቶችን ጀምሯል።
ተደራሽነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራቱም እየጨመረ የመጣው ይህ ተቋም ለቆዳ ሕክምና በአገር አቀፍ ደረጃ የሪፈራል ማዕከል ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል። የሆስፒታሉ የቆዳ ሕክምና ክፍል በዓመት እስከ 166 ሺህ ታካሚዎችን ያስተናግዳል። ከእነዚህም መካከል 160 ሺህ ታካሚዎች በተመላላሽ፣ ስድስት ሺህ የሚሆኑት ደግሞ አልጋ ይዘው የሕክምና አገልግሎት የሚያገኙ ናቸው።
በሆስፒታሉ ከፍተኛ የታካሚዎች ቁጥር የሚያስተናግደው ይኸው ክፍል አገልግሎቱን በስጋ ደዌ ሕክምና ጀምሮ አሁን ሁሉንም ዓይነት የቆዳ ህመሞች በማከም ላይ ይገኛል። ከሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ለሚመጡ ታካሚዎች በቆዳ ላይ ከሚከሰት የካንሰር በሽታ በስተቀር ሁሉንም ዓይነት የቆዳ ሕክምና ይሰጣል።
በቆዳና በአባላዘር በሽታዎች ሕክምና ክፍሉ የቀዶ ሕክምናን ጨምሮ የተለያዩ የቆዳ ምርመራዎች ይሰጣሉ የሚሉት ዶክተር አለምፀሀይ በቆዳ፣ በጥፍርና በፀጉር ላይ ለሚከሰቱ ሕመሞች ሕክምና እየተሰጠ እንደሆነም ይናገራሉ። ሆስፒታሉ መነሻው አድርጎ የተነሳው የስጋ ደዌ ሕክምና በመሆኑ አሁንም ሆስፒታሉ በርከት ያሉ የስጋ ደዌ ታካሚዎችን ያስተናግዳል። ቆንጭር (Leishmaniasis) የተባለው በሽታ ሌላኛው በቆዳና
በአባላዘር ሕክምና ክፍሉ ከፍተኛ የታካሚ ቁጥር ያለው የጤና ችግር ነው። የሕክምና ክፍሉ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ የቆዳ በሽታዎች እንዲሁም በአለርጂ፣ ከዘር ለተወረሱ የቆዳ በሽታዎች እንዲሁም በግብረ ስጋ ግንኙነት ለሚተላለፉ የአባላዘር በሽታዎች የሕክምና አገልግሎት ይሰጣል።
የሆስፒታሉ የቆዳና አባላዘር ክፍል በዘርፉ ዘመናዊ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት በሚያስችሉ የተለያዩ ዘመናዊ መሣሪያዎች የተደራጀ ነው። በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚገኙ ሌሎች የሕክምና ተቋማት በተለየ ሁኔታ በዚህ ሆስፒታል ብቻ የሚሰጡ የተለያዩ የቆዳ ሕክምናዎችና ምርመራዎች መኖራቸውን ዶክተር አለምፀሀይ ያነሳሉ። የቆዳ ቀዶ ሕክምና አንደኛው ሲሆን በፈሳሽ ናይትሮጅን የሚሰጥ የቆዳ ሕክምና (Cryo- therapy) ስጋ ደዌና ቆንጭርን ለማወቅ የሚረዱ ምርመራዎች በሆስፒታሉ የሚገኙ አገልግሎቶች ናቸው።
ከቆዳ ላይ ተቆርጦ የሚወሰድ የናሙና ምርመራ (Histopa- thology) ሌላው በሕክምና ክፍሉ የሚሰጥ ምርመራ ነው።
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
በአገራችን በዚህ ሙያ ሥልጠና የወሰዱት ሁለት ባለሙያዎች ብቻ ናቸው፤ አንደኛው በአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቆዳና አባላዘር ሕክምና ክፍል ውስጥ በማገልገል ላይ ይገኛሉ።
ሆስፒታሉ ከሕክምና ባሻገር የሥልጠና አገልግሎት እንዲሰጥ ታሳቢ ተደርጎ የተቋቋመ በመሆኑ በልዩ ሁኔታ ከቆዳ ሕክምናዎች ጋር በተያያዘ የሥልጠና ማዕከል ሆኖ ያገለግላል። በአገር ውስጥ ከሚገኙ የቆዳ ሕክምና ስፔሻሊስቶች አብዛኞቹ በማዕከሉ የሠለጠኑ ናቸው። በአገሪቷ የሚገኙና የቆዳ ሕክምና የሚሰጡ ማዕከላትም የአለርት
ውጤቶች ናቸው። ሆስፒታሉ ከሕክምና አገልግሎት በተጨማሪ እንደ ሌሎች መሰል ተቋማት በስፔሻላይዜሽን ሕክምና ዘርፎች ሐኪሞችን በማሠልጠን የአገሪቷን የጤና አገልግሎት እንቅስቃሴ በመደገፍ ጉልህ አበርክቶ አለው።
አለርት የቆዳ ሕክምና ተማሪዎች የቆዳ ሐኪሞች ሆነው የሚወጡበት ተቋም ነው የሚሉት ዶክተር አለምፀሀይ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት አብዛኞቹ የቆዳ ሐኪሞች አለርት ሆስፒታል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበበር ያስተማራቸው እንደሆኑ ያነሳሉ። ሆስፒታሉ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር አጫጭርና የስፔሻሊቲ ሥልጠናዎችን እየሰጠ ሲሆን በዓመት እስከ 15 ተማሪዎችን ያስመርቃል።
በአገራችን የቆዳ ሕክምና ፈላጊዎች ቁጥር ከፍተኛ ቢሆንም በዘርፉ ያሉት ባለሙያዎች በጣም ጥቂቶች ናቸው። ሆስፒታሉ ይህንን ችግር ለማቃለል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ከሚያሠለጥናቸው ተማሪዎች በተጨማሪ በየዓመቱ ከመላ አገሪቷ ለሚመጡ ከመቶ እስከ 150 ለሚሆኑ የጤና ባለሙያዎች በጤና ሚኒስቴር ድጋፍ በስጋ ደዌና በሌሎች የቆዳ ህመሞች ላይ ሥልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል።
ሆስፒታሉ ከቆዳ ሕክምና ጋር በተያያዘ ከአገር ውስጥ አልፎ ከአፍሪካ፣ ከአውሮፓ እና ከእስያ ለሚመጡ ባለሙያዎችም ሥልጠና ይሰጣል። ከውጭ ለሚመጡ ባለሙያዎች የሚሰጠው ሥልጠና ከስጋ ደዌ እና ቆንጭር ጋር የተያያዘ እንደሆነ ዶክተር አለምፀሀይ ይናገራሉ።
የአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከሕክምና ሥልጠና ባሻገር ከአርማወር ሀንሰን የምርምር ማዕከል ጋር በመሆን የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን ያከናውናል። የምርምር ሥራዎቹ በስጋ ደዌና ቆንጭር ላይ ያተኮሩ ሲሆኑ ለበሽታዎቹ የሚሰጡ መድሃኒቶችን መሞከርን ጨምሮ ለህትመት የበቁ የምርምር ውጤቶች መኖራቸውንና እነዚህ የምርምር ውጤቶች የስጋ ደዌ በሽታን ስርጭት በመቀነስ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ዶክተር አለምፀሀይ ገልፀዋል።
ሆስፒታሉ በአገልግሎት ዘመኑ በቆዳ ሕክምና ዘርፍ እንደ አገር ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል። በተለይም በአገራችን ለረጅም ዓመታት የማኅበረሰቡ የጤና ጠንቅ የሆነውን የስጋ ደዌ በሽታ ስርጭት በመቀነስ ያበረከተው አስተዋጽኦ የላቀ ነው። ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር ውጤታማ ሥራ አከናውኗል። ዶክተር አለምፀሀይ እንደሚሉት የስጋ ደዌ ታካሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ እየቀነሰ የመጣ ሲሆን ሆስፒታሉ በዓመት ሦስት ሺህ የሚጠጉ ታካሚዎችን ያስተናግዳል። የዓለም ጤና ድርጅትም ኢትዮጵያ የስጋ ደዌ በሽታን ለማጥፋት በተደረገው ጥረት ውጤታማ ሥራ መስራቷን ገልጿል።
ሆስፒታሉ በራሱ ከሚያከናውናቸው ተግባራት በተጨማሪ በኢትዮጵያ የስጋ ደዌ ላይ የሚሠሩ የተለያዩ ተቋማትን በመደገፍና በማሠልጠን የስጋ ደዌ ሕክምናን አስመልክቶ ያለው ግንዛቤ እና እውቀት እንዲጎለብት ብዙ ተንቀሳቅሷል።
የዘርፉ ተግዳሮቶች
እንደ አገር በቆዳ ሕክምና ከፍተኛ የሆነ የሠለጠነ የሰው ኃይል እጥረት መኖሩ የዘርፉ ትልቁ ተግዳሮት ሆኖ ቀጥሏል። በአገር ደረጃ እስከ ሁለት
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም
መቶ የቆዳ ሐኪሞች ቢኖሩም ካለው የሕክምና ፍላጎት ጋር ሲነጻጸር ቁጥሩ በጣም አነስተኛ ነው። ስለሆነም የቆዳ ሕክምና አገልግሎትን ለኅብረተሰቡ ለማዳረስ አሁንም የሠለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት ላይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ዶክተር አለምፀሀይ ጠቁመዋል። የቆዳ ሕክምና በከተሞች ብቻ የታጠረ መሆንና አሁንም ድረስ ከከተማ ራቅ ባሉ አካባቢዎች ላይ ተደራሽ አለመሆኑን ሌላው የዘርፉ ተግዳሮት ነው።
የአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቆዳ ሕክምና አገልግሎትን ለማስፋት ከተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች ለሚመጡ ባለሙያዎች መለስተኛ የቆዳ ህመሞችን ማከም የሚያስችሉ ሥልጠናዎችን እየሰጠ ቢሆንም በስፔሻሊቲ ደረጃ የሠለጠኑ ባለሙያዎች ባለመኖራቸው አሁንም ተደራሽነቱን በሚፈለገው ደረጃ ማሳደግ አልተቻለም።
የሆስፒታሉ የቆዳና የአባላዘር ሕክምና ክፍል ከሚያስተናግደው የሰው ብዛት አኳያ የክፍሎች መጣበብ መኖራቸውን እና ዘመኑ የደረሰባቸው አዳዲስ መሣሪያዎች አለመኖራቸው የሕክምና ክፍሉ አሉኝ የሚላቸው እጥረቶች ናቸው።
ስለሆነም በቆዳ እና በአባላዘር ሕክምናዎች ላይ የሚሠሩትን ሥራዎች በቀጣይ በይበልጥ ለማስፋት ቀደም ሲል የተመላከቱትን ችግሮች መቅረፍ የሚያስችሉ መፍትሔዎችን ማስቀመጥ፣ መፍትሔዎቹንም ወደ ተግባር መለወጥ የሚመለከታቸው ባለድርሻ እና አስፈጻሚ አካላት ትኩረት ይጠይቃል።
የልህቀት ማዕከል የመሆን ራዕይ
የአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እንደ አህጉር የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና፣ የዓይንና የቆዳ ሕክምና የልህቀት ማዕከል የመሆን ራዕይ አለው። ሆስፒታሉን የልህቀት ማዕከል ለማድረግ ከመረጣቸው ዘርፎች አንዱ የቆዳ ሕክምና ነው። በዚህም አሁን እየሰጠ ከሚገኘው ሕክምና የላቀ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉትን ሥራዎች እያከናወነ ይገኛል። ከእነዚህ ሥራዎች አንዱ አገልግሎቱን ከአገር ውስጥ አልፎ ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ለማስፋት የቆዳ እና የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት የሚሰጥበት ህንፃ እያስገነባ ይገኛል። ህንጻው ሲጠናቀቅ የሆስፒታሉ የቆዳ ሕክምና ጥራትና ተደራሽነት እንደሚያግዝ ይጠበቃል። እንዲሁም ተቋሙ ከሕክምና ምርምር ተቋምነት በተጨማሪ ወደ ትምህርት ተቋም በመቀየር ሰፊ አገልግሎት ለመስጠት ያስችለዋል።
ሆስፒታሉ ተጨማሪ ዘመናዊ መሣሪያዎችን በማስገባት ዓለም በቆዳ ሕክምና ዘርፍ የደረሰበትን የሕክምና አገልግሎት የመስጠት ራዕይ አለን የሚሉት ዶክተር አለምፀሀይ ለአገሪቷ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ አህጉር ደረጃ የተሻለ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ዝግጀት እየተደረገ ነው።
በተጨማሪም በተፈጥሮ የሚመጣ ጥቁረትን ጨምሮ በቆዳ ላይ በብጉርና ሌሎች ምክንያቶች የሚወጡ ጠበሳዎችን ለማከም የሚረዳውንና በጨረር የሚሰጠውን የሌዘር እና የፎቶቴራፒ (Phototherapy) ሕክምና ለማስጀመር መታቀዱን በሆስፒታሉ የቆዳና አባላዘር ሕክምና ስፔሻሊስትና የሕክምና ክፍሉ ኃላፊ ዶክተር አለምፀሀይ ዶክተር አለምፀሀይ ጠቁመዋል።
ነጋሪ 8ኛ ዓመት ቁጥር 31 ህዳር 2018 ዓ.ም