ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም - ኢዜአ ነጋሪ








ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም

ዲፕሎማሲያችን . . .


ማውጫ

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በየሁለት ወሩ የምትታተም መጽሔት መስከረም 2009 ዓ.ም ተመሰረተች
አድራሻ፦
አራዳ ክፍለ ከተማ
ስልክ ቁጥር
+251-11-55-00-11
+251-11-56-39-31
+251-11-56-52-21
ፋክስ ቁጥር
+251-11-55-16-09
enanegari@gmail.com
ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጽናት
06
ብሪክስ የአዲሱ ሥርዓተ ሉል ማዕቀፍ
22
ዲፕሎማሲያችን
38
ለመድኃኒት አቅርቦት ችግር ...
48
ኢትዮጵያ በእንግዶቿ አንደበት
54
ወባን ከኢትዮጵያ . . .
66
የአፍሪካና አፍሪካዊነት ፋና . . .
74
የዓይን ሕክምና ክፍሉ ጉዞ
88
ምስለ ሕክምና ለጤና ባለሙያው
94
ጥንታዊው ሀገር በቀል ዕውቀት
102
መልዕክት
ውድ የነጋሪ አንባቢያን ሰላምታችን በያላችሁበት ይድረሳችሁ። ነጋሪ ዛሬም ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ይዛ መጥታለች። በዚህ ዕትሟ በውጭ ግንኙነት መስክ ብዙ የካበተ ወረት ያላት፣ በጸረ ቅኝ ግዛት ትግል የራሷን ነፃነት ከማስከበር አልፋ ሌሎች አፍሪካዊያን ያደረጉትን የጸረ ቅኝ ግዛት ተጋድሎ የደገፈች፣ በዓለም አቀፍ መድረኮች የመንግሥታቱ ማኅበር ብቸኛዋ አፍሪካዊት አባል አገር ከመሆን ጀምሮ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መስራች እንዲሁም በበርካታ ድርጅቶች መስራች አልያም ቀዳሚ አባል አገራት መካከል የምትገኘውና በርካታ ስኬቶችን የተጎናጸፈችው ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ዋነኛ መገለጫዋ ከነበረው ተሽኮርማሚነት ወደ ተፅዕኖ ፈጣሪነት ከፍ ማለቷን የሚተነትን፤ የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲ አሁናዊ ቁመና የሚቃኝ ፅሁፍ ዐቢይ ጉዳይዋ አድርጋለች።
የፓን አፍሪካዊነት እንቅሰቃሴ ተፀንሶ እንዲወለድ ከፍተኛ መነሳሳት እንዲፈጠር ያደረጉ ክስተቶችን ስላስተናገደችው፣ እንቅስቃሴው ፍሬ አፍርቶ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን እንዲወልድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስላበረተችው፤ የአፍሪካ አገራትን ከቅኝ አገዛዝ የማላቀቅ ግብ እውን እንዲሆን የአንበሣውን ድርሻ ስለተጫወተችው ኢትዮጵያ ፋና ወጊነት የሚያትተው ሌለው ርዕሰ ጉዳይዋም የቅኝ ግዛትን መጥፎ ጠባሳ የሚያሳየውን የሣራ ቤርትማንን አሳዛኝ ታሪክ ያወሳል።
በኢትዮጵያ ለሚገኙ ልዩ ልዩ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነት፣ ባሕል፣ ቋንቋ፣ ታሪክ፣ ቅርሶችና ሌሎች መገለጫዎች እውቅናና ክብር የሰጠው፤ በልዩነት ውስጥ አንድነትን በማጉላት የኢትዮጵያ ጥንካሬ የሆነውን የብዝኀነቷን ውበት፣ አንድነትና የጋራ ታሪክ ማሳያ የሆነው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ካስገኛቸው በርካታ ጠቀሜታዎች መካከል የቱሪዝም ዕድገት፣ ኢንቨስትመንት መሳብ፣ ማኅበራዊ ልማት ማስፋፋትና ሌሎችም ጉዳዮች የተካተቱበት ፅሁፍ ሌላው የነጋሪ ጉዳይ ነው።
“. . . በፈረንጆቹ የዘመን ቀመር 2001 ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ እና ቻይና አንድ ማኅበር ወጠኑ። ስብስባቸውንም የአገራቱን የእንግሊዝኛ የመጀመሪያ ሆሄያት በመውሰድ “BRIC” (ብሪክ) የሚል ስያሜ አወጡለት። . . . “ ነጋሪ የአዲሱ ‘ሥርዓተ-ሉል’ ማዕቀፍ ስለሆነው ብሪክስ፣ ኢትዮጵያ በብሪክስ ማዕቀፍ የመግባቷ አንድምታና የብሪክስ ዓለም አቀፉዊ ዝርዝር ጉዳዮችን ዳስሳለች።
በቅርቡ የብልፅግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔን እንዲታደሙ ተጋብዘው አዲስ አበባን ተዘዋውረው የተመለከቱ፤ በአዲሷ አዲስ አበባ ውበት የተደነቁ የተለያዩ አገራት እንግዶች ኢትዮጵያን እንዴት ተረዷት፤ አዲስ አበባን እንዴት አገኟት? እንግዶቹ ግላዊ ምልከታቸውን አጋርተዋል። አገሮቻቸው ከኢትዮጵያ ጋር ስለነበራቸውና አሁን ስላላቸው ግንኙነት ብዙ ብለዋል፤ ኢትዮጵያን በእንግዶቿ አንደበት በነጋሪ የውስጥ ገፅ ይመልከቱ።
“. . .ኢትዮጵያ ያላት ቱባ ባሕል ከጥንት ጀምሮ በጥንታዊያን የዓለም ሕዝቦች የተደነቀ ቢሆንም ስለ አገራችን የቀደመ ሥልጣኔና ጥበብ፣ የተፈጥሮ ፀጋ፣ አሁን እየሰራን ያለነውን ሥራ፣ አሁናዊውን ከድህነት የመውጣት ትግልና ወደ ብልፅግና ማማ የመውጣት ግስጋሴ እንዲሁም እያስመዘገብን ያለውን ውጤት ለተቀረው ዓለም ለማሳወቅ የምናደርገው ጥረት በእጅጉ ደካማ ነው. . . የሚለው ፀሐፊ፤ ቀደምት ጥበባችንን፣ የተፈጥሮ ፀጋዎቻችንን፣ ባሕልና ወጋችንን፤ የአገራችንን መልካም ገፅታዎች ለዓለም የምናሳይበት ጊዜው አሁን ሊሆን ይገባል ይላል- አገር በቀል ዕውቀቶች ላይ አተኩሯል።
ምስለ ሕክምና ለጤና ባለሙያው የላቀ ክህሎት፣ ወባን ከኢትዮጵያ ምድር ለማጥፋት፣ የዓይን ሕክምና ክፍሉ ጉዞ ወደ ቴሪሸሪ እንዲሁም ለመድኃኒት አቅርቦት ችግር መፍትሄ ያበጀው አዋጅ የሚሉ ርዕሰ ጉዳዮችም በነጋሪ ተካተዋል።
መልካም ንባብ!
ዋና አዘጋጅ
ፈለቀ ሽኩር
ም/ ዋና አዘጋጅ
የሺመቤት ደመቀ
አዘጋጅ
መንገሻ ገ/ሚካኤል
አርት ዳይሬክተር
ነብዩ መስፍን
nebiyou1st@gmail.com
ድረ-ገፅ
www.ena.et/web/negari
ፖለቲካ

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጽናት . . .

በፈትሂ ማህዲ ወዚር (ዶ/ር)
በኢፌዲሪ ሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ
በኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በመላው አገሪቷ በተለያዩ ደረጃዎችና ሁነቶች ላለፉት 18 ዓመታት በተከታታይ ብሔራዊ በዓል ሆኖ በድምቀት እየተከበረ ዘልቋል። በዓሉ እንዲከበር የአገሪቷ ሕገ-መንግሥት ሕጋዊ መሠረት የሚሰጠው ሲሆን ለበዓሉ መነሻ ተደርገው ሊወሰዱ ከሚችሉትና በሕገ-መንግሥቱ ከተደነገጉት በርካታ አንቀጾች መካከል አንቀጽ 39 የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እና አንቀጽ 40 የባሕል መብቶች ጥበቃ በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው። በዓሉ እነዚህን የሕገ-መንግሥቱን ድንጋጌዎች በተጨባጭ ለመተግበር ከሚጠቅሙ ቁልፍ መሣሪያዎች

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
መካከል አንዱ ሲሆን በኢትዮጵያ ለሚገኙ ልዩ ልዩ ብሔር ብሔረሰቦች ለማንነታቸው፣ ለባሕላቸው፣ ለቋንቋቸው፣ ለታሪካቸው፣ ለቅርሶቻቸውና ለሌሎች መገለጫዎቻቸው እውቅናና ክብር ለመስጠት፤ በልዩነት ውስጥ አንድነትን ለማጉላት፣ የአገሪቷ ጥንካሬ በብዝኀነቷ ላይ ነው የሚለውን እሳቤ ለማጠናከር እንዲሁም የፌዴራል ሥርዓቱ ለብሔር ብሔረሰቦች እውቅናና ክብር መስጠቱን ለማሳየት ያለመ ነው። የኢትዮጵያን የብዝኀነት ውበት፣ አንድነትና የጋራ ታሪክ የሚያሳይ ታላቅ በዓል ሲሆን ብሔር ብሔረሰቦች እርስ በእርሳቸው የባሕል ልውውጥ እንዲያደርጉ፣ ዕውቀታቸውንና ልምዶቻቸውን እንዲጋሩ እንዲሁም አንድነታቸውን የበለጠ እንዲገነቡ ምቹ መድረክ ከመፍጠር ባሻገር ለአዎንታዊ የአገር ገጽታ ግንባታ የበኩሉን ጉልህ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛል።
የበዓሉን ዓላማዎች፣ ጠቀሜታዎች እንዲሁም የፈጠራቸውን አዎንታዊ ተጽዕኖዎች ጠቅለል ባለ መልኩ ስንመለከት ለብዝኀነት እውቅና መስጠትና ማክበር፣ አንድነትን ማጠናከር፣ የባሕል ልውውጥ ማድረግ፣ ቱሪዝምን ማሳደግ፣ የአገር ገጽታን መገንባት እንዲሁም የኢኮኖሚ ዕድገት ማምጣት በዋናነት ይጠቀሳሉ። በዓሉ የኢትዮጵያን ብዝኀነት በመገንዘብና በማክበር ረገድ ወሳኝ ሚና የሚጫወት ሲሆን ብሔር ብሔረሰቦች የማንነታቸው መገለጫ የሆኑትን ባሕላዊ አልባሳት፣ ምግቦችና መጠጦች፣ ሙዚቃዎችና ጭፈራዎች/ዳንሶች እንዲሁም ሌሎች በርካታ የማንነታቸው መገለጫዎችን በማሳየት ውበታቸውን እንዲያጋሩ አስችሏቸዋል።
ይህም የአንድነትን ስሜት በማጠናከር ሁሉም ብሔር ብሔረሰብ የራሱ ልዩነት እንዳለውና እነዚህም ልዩነቶች የአገር ሐብቶች መሆናችው ጎልቶ መታየቱ በብሔር ብሔረሰቦች መካከል የተሻለ ግንኙነት እንዲፈጠር አድርጓል። በዓሉ ብሔር ብሔረሰቦችን በአንድ ላይ በማሰባሰብ የአንድነት ስሜት እንዲጨምርና እንዲጠናከር ይረዳል። በበዓሉ አከባበር ላይ የሚቀርቡ የጋራ መዝሙሮች፣ ባሕላዊ ጭፈራዎች፣ ጨዋታዎችና መሰል ትዕይንቶች የአንድነትን መንፈስ ለማጎልበት ይጠቅማሉ። እሴቶችን፣ አፈ ታሪኮችን እና የአኗኗር ዘይቤዎችን እንዲለዋወጡ ዕድል ስለሚፈጥር ባሕላዊ ሐብቶችን ለመጠበቅና ለማዳበር ያስችላል።
ይህ ብቻም አይደለም የበዓሉ ተሳታፊዎችና ታዳሚዎች፣ የአገር ውስጥና የውጭ አገራት ጎብኚዎች የኢትዮጵያን የባሕል ብዝኀነት እንዲመለከቱና አገሪቷን በተሻለ ሁኔታ እንዲያውቁ ስለሚያደርግ ለቱሪዝም ዘርፍ ዕድገትና ገጽታ ግንባታ የበኩሉን ፋይዳ ያበረክታል። በበዓሉ አከባበር ላይ ለሽያጭ የሚቀርቡ ባሕላዊ የዕደ- ጥበብ ቁሳቁስ፣ ምግቦችና መጠጦች እንዲሁም ተዛማጅ አገልግሎቶች በዓሉ ለሚከበርበት አካባቢ ማኅበረሰብ ገቢ ከመፍጠር ባለፈ ኢኮኖሚውን የማነቃቃት ሚና ስለሚኖረው የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት ጠቀሜታ አለው።
የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ከባሕላዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች አንፃር ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ከመሆኑ ባሻገር በክልሎች መካከል የባሕል ልውውጥ በመፍጠርና አንድነትን በማጠናከር ረገድ ጉልህ ሚና ይጫወታል። በዓሉ በሚከበርበት ክልል የማንነት መገለጫዎችና እሴቶች፣ የባሕላዊ ምግብ አሰራሮች፣ አልባሳትና ጌጣጌጦች፣ ሙዚቃና ጭፈራዎች ወዘተ . . . ለዕይታ የሚቀርቡ በመሆናቸው የሌሎች ክልሎች ማኅበረሰቦች እነዚህን ባሕሎችና እሴቶች እንዲያውቁ፣ እንዲያደንቁ በማድረግ በአዲሱ ትውልድ ዘንድ የባሕል ዕውቀትን ለማስፋፋት ይረዳል። የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ከሁሉም የአገሪቷ ክልሎች እንዲሁም ከተለያዩ አገራት የሚመጡ ታዳሚዎችና ጎብኚዎች እንዲገናኙና ወዳጅነት እንዲመሰርቱ በማድረግ በሕዝቦች መካከል ያለውን ማኅበራዊ ትስስር የበለጠ ያጠናክራል። በሌላ በኩል በዓሉ በሚከበርበት ክልል የተገኙ የልማት ስኬቶች ለሌሎች ክልሎች እንደ አብነት ስለሚቀርቡ ተሞክሮ እንዲወስዱና ተመሳሳይ ስኬቶችን እንዲያስመዘግቡ ያበረታታል።
ኢትዮጵያዊያን አንድ እንደሆኑ የሚያሳየው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ብሔራዊ የአንድነት ስሜት እንዲፈጠር፣ የጋራ መግባባት፣ መከባበርና መቻቻል እንዲኖር የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረክታል። በዓሉ የኢትዮጵያን ታሪክና የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች የሚጋሩትን ታሪክ (ለምሣሌ የአድዋ ድል) በማስታወስ የጋራ ማንነትን በላቀ ደረጃ ያጠናክራል።
የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ኅብረብሔራዊ አንድነትና ወንድማማችነትን በማጽናት በአገሪቷ ውስጥ የሚኖረውን የብዝኀ ባሕላዊ ሐብት በማክበርና የጋራ መግባባት በመፍጠር አገራዊ አንድነት ላይ በርካታ አዎንታዊ ተጽዕኖዎችን አሳርፏል።
ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
በርካታ ብሔር ብሔረሰቦችን በአንድ መድረክ በጋራ በማሰባሰብና በማዝናናት የአንድነት ስሜት ይበልጥ እንዲጎላ እያደረገ ያለው እንዲሁም ዜጎች ብዝኀነት ላይ ያላቸውን የተለያየ አመለካከትና ግንዛቤ ወደተሻለ ደረጃ ከማምጣትና ልዩነቶችን ከማጥበብ አንፃር የጎላ ፋይዳ ያለው ይህ በዓል በተለይ ወጣቶች በበዓሉ ተሳትፏቸው የአንድነት መንፈስ በውስጣቸው እንዲጠናከር በማድረግ በአንድነት በመሰባሰብ እና በመደሰት አንድነታቸው የበለጠ እንዲጎለብት እያደረገ ነው። ይህም በዜጎች ውስጥ የብሔርና የኢትዮጵያዊነት ስሜት ሚዛኑን እንዲጠብቅ በማድረግ በኢትዮጵያዊነት ላይ የተመሰረተ የብሔርተኝነት ስሜት ለመፍጠርና ለማሳደግ የበኩሉን ፋይዳ በማበርከት ላይ ይገኛል። በዚህም የአገር ፍቅር እና ለአገር ተቆርቋሪነትን ያጠናክራል፤ ምክንያቱም በዓሉ በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባሕል እና ስኬቶች ላይ ስለሚያተኩር አገራዊ ፍቅርን ይበልጥ ማነሳሳቱ አይቀርም።
የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን የሚሆን የጋራ መለያን ለመፍጠር ምቹ በመሆኑ የተለያዩ ባሕሎችን በአንድ በማጣመር የወንድማማችነት ስሜትና አገራዊ አንድነት እንዲጠናከር የበኩሉን ፋይዳ ያበረክታል። በዓሉን የተመለከቱ የተለያዩ ሲምፖዚየሞችና የፓናል ውይይቶች መካሄዳቸውም አንዱ ብሔር የሌላውን ብሔር ታሪክ፣ እሴት፣ ባሕል ወዘተ . . . በሚገባ እንዲረዳና የብዝኀነትን ውበትና ፋይዳዎች የበለጠ እንዲገነዘብ በማድረግ የብሔር ጽንፈኝነትን ለማስወገድ የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ የሚያግዝ ይሆናል። በዓሉ ኢትዮጵያዊያን ልዩነቶቻቸውን ለማክበር፣ አንዱ ለሌላው እውቅና እንዲሰጥና በአንድነት በጋራ ለመቆም የሚሰባሰቡበት በመሆኑ በመካከላቸው ሊኖር የሚችለውን ግንብ እንዲያፈርሱና የመግባቢያ ድልድዮች እንዲገነቡ ያለው አበርክቶ ጉልህ ነው። በአጭሩ ክብረ በዓሉ የመደመር ስሜትን ስለሚያጎለብት አንድነትን የበለጠ ከማጠናከር ባለፈ ሕዝቡ ልዩነትን አምኖ እንዲቀበል፣ ፈተናዎችን በጋራ እንዲታገል እንዲሁም በላቀ ትብብርና ስምምነት አገሪቷን ወደ ብልፅግና ማሸጋገር እንዲያስችል ጥሩ መድረክ በመሆን እያገለገለ ይገኛል።
መላው ኢትዮጵያዊያን በሚጋሯቸው ባሕላዊ እሴቶች ላይ የሚያተኩረው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ለሁሉም እኩል ዕድል የሚሰጥና ተሳትፎን የሚያበረታት በመሆኑ የጋራ መንፈስን በማጠናከር የእርስ በእርስ መቀራረብን፣ መተዋዋቅን፣ መከባበርን፣ መዋደድንና መቻቻልን እንደሚያሳድግ ይታመናል። ምክንያቱም በዓሉ የተለያዩ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባሕሎቻቸውን እንዲለዋወጡ እኩል ዕድል መስጠቱና ልዩነቶቻቸውን በማክበር ላይ ስለሚያተኩር ጠቀሜታውን የጎላ ያደርገዋል።
ክብረ በዓሉ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች የማንነታቸው መገለጫ የሆኑትን ባሕላዊ እሴቶቻቸውን ለማሳየትና የሌሎችን ባሕል መማር እንዲችሉ ጥሩ ዕድል እንደሚፈጥር ይታወቃል። ይህ ደግሞ የባሕል ልዩነቶችን በመቀበል እና በመከባበር ላይ የተመሰረተ የጋራ መግባባትን ያጠናክራል፤ ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን የሚሆን የጋራ መለያ ይፈጥራል፣ አገራዊ የአንድነት ስሜትን በማጠናከር ሰላም እንዲሰፍን ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። ዜጎችን በጋራ በማሰባሰብና በማዝናናት የአንድነት ስሜትን ያጎለብታል፣

በቀላሉ ተግባብተው በጋራ እንዲኖሩ ያበረታታል፣ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ለመግባባት ጥሩ መደላድል ይፈጥራል፣ የሰላም መንፈስን ያስፋፋል፤ እንዲሁም በብሔሮች፣ በጎሳዎችና በክልሎች መካከል ሊከሰቱ የሚችሉ ግጭቶችን ለመቀነስ ብሎም ለማስቀረት በእጅጉ ያግዛል።
የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ከኢኮኖሚ ዕድገት አንጻር ያለውን ጠቀሜታ በከፊሉ ስንመለከት በየዓመቱ በተለያዩ ክልሎች መከበሩ የክልሎችን የመሠረተ ልማት ግንባታና ኢንቨስትመንት ከማነቃቃት አንፃር የበኩሉን አዎንታዊ ተጽዕኖ ያሳርፋል። በዓሉ በሚከበርበት ክልል መንግሥት የመንገድ፣ የኤሌክትሪክ፣ የውሃ አቅርቦት እና ሌሎች መሠረተ ልማቶች ግንባታ ላይ እንዲያተኩር ያደርጋል። ምክንያቱም የበዓሉን ታዳሚዎች ለማስተናገድና ለጎብኚዎች አገልግሎት ለመስጠት በተቻለ መጠን እነዚህን መሠረተ ልማቶች ማሟላት አስፈላጊ በመሆኑ ነው። ስለዚህ በዋና አዘጋጅነት
ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
ተመርጦ በዓሉ በሚከበርበት ክልል በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ አገራት ባለሐብቶች ስለሚሳተፉ የክልሉን እምቅ የኢንቨስትመንት አቅሞችና ዕድሎች ለማስተዋወቅ ይረዳል። ይህም በክልሉ ውስጥ በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ኢንቨስትመንት እንዲጨምርና የልማት ዘርፎች እንዲነቃቁ ያስችላል። ላለፉት 18 ዓመታት በዓሉ በተከበረባቸው ክልሎች የተለያዩ መሰረተ ልማቶች ተገንብተዋል፤ ከተሞች ጽዱና ውብ እንዲሆኑ ዕድል በመፈጠሩ አበረታች ውጤቶች ታይተዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በዓሉን ለማክበር የሚገነቡ መሰረተ ልማቶችና የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ክብረ በዓሉ ከተጠናቀቀ በኋላም ክትትልና ድጋፍ እንዲሁም ልዩ ትኩረት በመስጠት ልማቱ ዘለቄታዊ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል።
ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በአገሪቷ ብዝኀነት ውስጥ አንድነትን ለማጉላት ያለመና በየዓመቱ አንድ ዋና አዘጋጅ ክልል በመምረጥ በተለያዩ ክልሎች በማዘዋወር ይከበራል። ይህ በዓል በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ የአገሪቷን የልማት ጉዳዮች ከማጉላት አንጻር የበኩሉን አዎንታዊ ተጽዕኖ ሲያበረክት ቆይቷል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በዋናነት የሚጠቀሰው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሲሆን በዓሉ ለግባታው መፋጠን የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
በዓሉ በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ያለው አዎንታዊ ተጽዕኖ በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ መልኩ ሊታይ ይችላል። ቀጥተኛ ተጽዕኖ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው በዓሉ በሚከበርበት ወቅት በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን በኩል የግድቡ አስፈላጊነት እና ግንባታውን በሕዝብ ተሳትፎ ማጠናቀቅ እንደሚቻል በተደጋጋሚ መጠቀሱ በሕዝቡ ዘንድ ግንዛቤ ከመፍጠሩ ባሻገር በግንባታው ላይ የነቃ ተሳትፎ እንዲደረግ አስችሏል። በተዘዋዋሪ ደግሞ በዓሉ በሚከበርበት ጊዜ በተለያዩ ክልሎች የሚካሄዱ የልማት ስራዎችና የተገኙ ስኬቶች አመርቂ ውጤት ማምጣታቸው በሕዝቡ ዘንድ የአገር ፍቅርና የአንድነት ስሜት እንዲጠናከር አድርጓል። ይህ ደግሞ በሌላ መልኩ የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ ለሌሎች አገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች የሚኖረው ድጋፍ እንዲጨምር ማድረጉ አይቀርም።
ስለዚህ ከግድቡ ጋር በተያያዘ የግንባታውን ዓላማና ታሪካዊ አስፈላጊነት፣ የአገሪቷን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያፋጥን መሆኑና ለቀጣናው አገራት የሚያስገኛቸውን ጠቀሜታዎች፣ በታቀደው ጊዜ እንዲጠናቀቅ ሊሰጠው ስለሚገባው ትኩረት፣ በአገር ሀብትና በራስ አቅም ብቻ መገንባቱ በዓይነቱ ልዩና ለታዳጊ አገሮች ተምሣሌት መሆኑን፣ ኢትዮጵያዊያን በትብብር የጀመሩትን በብቃትና በጽናት ማጠናቀቅ እንደሚችሉ፣ የአንድነትና የአይበገሬነት ተምሣሌት እንደሆነ፣ ወዘተ. . . በተደጋጋሚ በማጉላት በዓሉ እነዚህን ዓላማዎች ለማሳካት እንደ አንድ ወሳኝ መድረክ መጠቀሙ ፋይዳ እያስገኘ መሆኑ ይታመናል።
ከሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ የጎረቤት አገራት በግድቡ ዙሪያ ያላቸውን የተሳሳተ ግንዛቤ፣ አመለካከትና አቋም ሰላማዊ በሆነ መንገድ በማረምና በመታገል የውጭ ጣልቃ ገብነት እንዳይኖር ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን በመቆም የበኩሉን ታሪካዊ እገዛ እንዲያደርግ ይህ በዓል ጥሩ የግንዛቤ ማስጨበጫና የአንድነት ስሜት

መፍጠሪያ መድረክ ሆኖ ያገለግላል። የማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ የሃይማኖት እና የጎሳ መሪዎች ወዘተ የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን በተመለከተ ክብረ በዓሉን እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም የሚያስተላልፉት መልዕክት የሕዝቡን ተሳትፎና ድጋፍ ይበልጥ ለማጎልበት ትልቅ ጠቀሜታ እያስገኘ ይገኛል። የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጉዳይ በብሔራዊ ደረጃ ልዩ ትኩረት በተሰጠበት ጊዜ በዓሉ መከበሩ ሕዝባዊ ንቅናቄ ለመፍጠርና ዜጎች በአንድ ድምጽ ለአገራዊ ራዕይ በአንድነት እንዲቆሙና ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ ከማድረግ ባለፈ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለው ግንኙነት እንዲጎለብትና ሕዝቡ መንግሥት የሚያካሂዳቸውን ብሔራዊ ፕሮጀክቶች እንዲደግፍ በማድረግ ለግንባታው የተለየ ትርጉም እንዲያገኝ አስችሎታል። የሕዳሴ ግድብ ግንባታ የኢትዮጵያን ኩራት ከፍ የሚያደርግና ለአፍሪካዊያን አንድነት የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል የሚል ስሜትና እምነት በሕዝቡ ዘንድ በመፍጠር የላቀ ድጋፍ ለማሰባሰብ አስችሏል።
የብሔር ብሔረሰቦች ቀን የአገሪቷን የፌዴራል
ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
ሥርዓት በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባትና ብልጽግናን ከማረጋገጥ አንጻር ያለውን ጠቀሜታ ጠቅለል ባለ መልኩ መመልከት ተገቢ ይሆናል። እንደሚታወቀው አሁን ያለው የአገሪቷ የፌዴራል ሥርዓት ለተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች እውቅናና ክብር በመስጠቱ በብሔሮች እንዲሁም በክልሎች መካከል መተባበርን፣ በጋራ መስራትንና በሰላም አብሮ መኖርን አጎልብቷል። ከዚህ አንጻር በዓሉ በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦችን ተሳትፎ በማሳደግ፣ ለብዝኀነት ተገቢውን እውቅናና ክብር በመስጠት፣ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ግንኙነት በማጠናከር እንዲሁም የሲቪክና የፖለቲካ ተቋማትን ተሳትፎ በማጎልበት የፌዴራል ሥርዓቱ እንዲጠናከር የበኩሉን ፋይዳ አበርክቷል ማለት ይቻላል።
በዓሉ የፌዴራሊዝም ሥርዓት መሠረታዊ መርህ የሆነውን የብሔር ብሔረሰቦችን እኩልነትና ራስን በራስ ማስተዳደርን የሚያንፀባርቅ ሲሆን ይህም የፌዴራል ሥርዓቱን ሕጋዊነትና ተቀባይነት ለማጠናከር ይረዳል። የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች በፌዴራል ሥርዓቱ ግንባታና አስተዳደር ላይ በቀጥታ እንዲሳተፉ እኩል ዕድል ስለሚሰጥ የዜጎችን፣ የብሔር ብሔረሰቦችን፣ የክልሎችንና የዳያስፖራዎችን አገራዊ የባለቤትነት ስሜት በማጠናከር ለሥርዓቱ ቀጣይነትና ዘላቂነት የበኩሉን አዎንታዊ ተጽዕኖ ያሳርፋል። በዓሉ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች የአንድ አገር ዜጎች መሆናቸውን ከማስታወስ ባሻገር ባሕላዊ ልዩነቶቻቸውን በማክበር የፌዴራል ሥርዓቱ ያለውን የብዝኀ አቀባበል መርህ ስለሚያጠናክር በብሔር ብሔረሰቦች መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ያሻሽላል።
በየዓመቱ በወርኃ ሕዳር የሚከበረው ይህ በዓል ብዝኀነትና እኩልነትን የሚያጎላ መሆኑ በብሔሮች እና ብሔረሰቦች መካከል መግባባትን ለማስቀጠል ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ይህ ደግሞ የአገሪቷን ብዝኀ ሐብት ለአገራዊ አንድነት ማጠናከሪያ ስለሚጠቅም የፌደራል ሥርዓቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩሉን አስተዋፅኦ ያበረክታል። ብሔር ብሔረሰቦች ለኢትዮጵያ ታሪክ፣ ማንነትና ዕድገት ላበረከቱት አስተዋጽኦ እውቅና ስለሚሰጥ የፌዴራል ሥርዓቱን ቅቡልነት የበለጠ እንዲጨምር ያደርጋል። በተጨማሪም የፌዴራል መንግሥት እና የክልል መንግሥታት በጋራ እንዲሰሩ የሚያስችል መድረክ ከመፍጠር ባሻገር የፖለቲካ ተቋማትንና የሲቪክ ማኅበራትን አቅም በማጠናከር ለፌዴራል ሥርዓቱ መረጋጋት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ይታመናል። ምክንያቱም ክብረ በዓሉ በጎሳዎች፣ በብሔር ብሔረሰቦች እንዲሁም በክልሎች መካከል ሊፈጠሩ የሚችሉ ክፍተቶችን ከማጥበብና ሊስተዋሉ የሚችሉ አለመተማመኖችን ከማስወገድ ባሻገር በጋራ እንዲሰባሰቡና ባሕሎቻቸውን በማካፈል እርስ በእርስ በተሻለ መንገድ እንዲረዳዱና እንዲተዋወቁ የላቀ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ ነው።
የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የኢትዮጵያን ብልጽግና ከማረጋገጥ አንጻር ካስገኛቸው በርካታ ጠቀሜታዎች መካከል የቱሪዝም ዕድገት፣ ኢንቨስትመንትን መሳብ፣ ማኅበራዊ ልማት ማስፋፋትና የመሳሰሉት በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው። ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው በዓሉ የውጭ እና የአገር ውስጥ ጎብኚዎችን መሳብ መቻሉ የአገሪቷን የገቢ ምንጭ በማሳደግ፣ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር እና የመሰረተ ልማትን በማፋጠን ለኢኮኖሚ ዕድገት
አስተዋጽኦ ያበረክታል። በዓሉ ኢትዮጵያ የብዝኀነት አገር መሆኗን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ ስለሚያስችል የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ እና የኢንዱስትሪ ልማትን ለማፋጠን የበኩሉን ፋይዳ ያበረክታል። በብሔር ብሔረሰቦች መካከል የመተሳሰብ እና የመቻቻል ስሜትን በማጠናከር የማኅበራዊ ልማትን ማፋጠን ስለሚያስችል የሰላም እና የደህንነት ሁኔታ እንዲሻሻል በማድረግ ለኢኮኖሚ ዕድገት ጠቃሚ መሠረት በመጣል እገዛ እንደሚያደርግ ይታመናል።
በዓሉ በሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች እኩል ተሳትፎ ሲደረግበት እያንዳንዱ ብሔር በአገሩ ልማት ውስጥ እኩል ድርሻ እንዳለው ማሳየት የሚያስችል በመሆኑ በፍትሐዊነት የተመሰረተ አንድነትን ለመገንባት ጠቃሚ መሠረት ይጥላል። ይሁንና ለግል ወይም ለቡድናዊ የፖለቲካ ጥቅም በማዋል አገራዊ አንድነትን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉና ጥላቻና መከፋፈልን የሚያበረታቱ ጽንፈኛ አስተሳሰቦችን የሚያራምዱ አካላት ለፖለቲካ መሣሪያነት እንዳይጠቀሙበት ከፍተኛ ጥንቃቄና ትኩረት ይሻል። ምክንያቱም ይህ በዓል የጥቂት ቡድኖች ብቻ ሳይሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በባለቤትነትና ያለምንም አይነት ተጽዕኖ በነፃነት የሚያከብሩት በመሆኑ ነው።
በዓሉ የኢትዮጵያን ብልጽግና በተሳካ መልኩ እንዲያረጋግጥ አሁን እየተከበረ ያለበትን ዘዴ በየጊዜው በመፈተሽና በመገምገም ጠንካራና ውጤታማ የሆኑትን አሰራሮች የበለጠ ማጠናከርና ማስፋት እንዲሁም መታረምና መስተካከል የሚገባቸውን ጉዳዮች በመለየት በቀጣይ የተሻለ ውጤትና ስኬት እንዲያስገኝ ማድረግ ተገቢ ነው።
የበዓሉን አከባበር በዋና ባለቤትነት የሚመሩት የፌዴራልና የክልል መንግሥታት እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የሚያደርጉትን አስተዋጻኦ አጠናክረው ለቀጣዩ ትውልድ በተሻለ ሁኔታ ማስተላለፍ ይጠበቅባቸዋል። በዓሉም ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በእኩል ደረጃ የሚሳተፉበት መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ይህንን ለማድረግ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን በመወከል የተቋቋሙ ኮሚቴዎች በዓሉን ለማክበር በሚዘጋጀው ዕቅድ ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ማጠቃለያው በንቃት መሳተፍ ይኖርባቸዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በቀጣይ የበለጠ ትኩረት ከሚሹ ጉዳዮች መካከል የሚጠቀሱት በዓሉን በተሻለ መንገድ ለማስተዳደርና ሊከሰቱ የሚችሉ ማናቸውም ዓይነት አሉታዊ ተጽዕኖዎችን በተቻለ መጠን ለመቀነስና ለማስወገድ የሚያስችሉ ግልጽ የሆኑ መመሪያዎችን ማዘጋጀት፣ ያሉትን መመሪያዎች መገምገም፣ መከለስና በየጊዜው ማሻሻል ተገቢ ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪ የመንግሥት ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና የኅብረተሰብ አባላት በጋራ በመስራት በዓሉ በሰላምና በአንድነት እንዲከበር ለማድረግ የሚረዱ ስትራቴጂዎችና የአሰራር ማዕቀፎችን ማዘጋጀት ያስፈልጋል። በተመሳሳይ በዓሉን ለፖለቲካ ዓላማ መጠቀምን ለመከላከል እንዲያስችል ጠንካራ ሕጋዊና ተቋማዊ ማዕቀፍ መዘርጋት ይገባል።
ከዚህ ጎን ለጎን በዓሉ የፌዴራል ሥርዓቱን መሠረታዊ መርሆዎች ለኅብረተሰቡ በቀላል መንገድ ለማስተማሪያነት መጠቀም እንዲያስችል መደበኛ የአሰራር ሥርዓት በመዘርጋት ከትምህርት

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
ተቋማት (ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች) ፣ ከታዋቂ ግለሰቦች፣ ከምሁራን፣ ከጎሳ መሪዎች፣ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከሃይማኖት መሪዎች፣ ከኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችና ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር መደበኛ የአሰራር ሥርዓት በመዘርጋት በጋራ መስራትን አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋል።
ሴቶች በባሕላዊ እሴቶችና በአገራቸው ልማት ውስጥ ጉልህ ሚና እንደሚጫወቱ ስለሚታወቅ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ በልዩ ሁኔታ ትኩረት መስጠት አስፈላጊ ነው። ሌላው ትኩረት የሚሻው የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ ሲሆን ክብረ በዓሉ ለሁሉም ዜጎች እኩል ተደራሽ እንዲሆን አካል ጉዳተኞች በበዓሉ ላይ እንዲሳተፉ አመቺ ሁኔታን መፍጠርና ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል።
በሌላ በኩል የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ጽንፍ የረገጠና አክራሪ የብሔርተኝነት ስሜት ተስፋፍቶ በብሔር ብሔረሰቦች መካከል አለመግባባትና ግጭት እንዲፈጠር ሊያደርግ ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግና ሚዛንን መጠበቅ ተገቢ ይሆናል።
ክብረ በዓሉ በአንድነትና በጋራ መኖር ላይ ያተኮረ እንዲሁም ከላይ በዝርዝር ለተገለጹት ዓላማዎች ብቻ እንዲውል ልዩ ትኩረት ማድረግ አስፈላጊ ነው።
ፍትሐዊ አገራዊ አንድነት ለአንድ አገር ዘላቂ ልማት ጠንካራ መሠረት መሆኑ ይታወቃል። ሁሉም ዜጎች እኩል ዕድል ሲያገኙና በጋራ ሲሠሩ አገሪቷ በፍጥነት እንድትበለጽግ እገዛ ማድረጉ አይቀርም። የአገራችን የብሔር ብሔረሰቦች በዓል በፍትሐዊነትና እኩል ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ አገራዊ አንድነት እንዲመጣና ይህም ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ቅርስ ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው።
በዓሉ ወንድማማችነት፣ እህትማማችነት፣ አንድነት፣ ፍቅርና መቻቻል የሚሉ መልዕክቶችን ለኀብረተሰቡ በቀጥታ ስለሚያስተላልፍ አገራዊ አንድነትና ሰላምን ለማጠናከር እጅጉን ይረዳል። የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች በጋራ የሚያከብሩትና የጋራ መለያ የሚፈጥር በመሆኑ የአንድነትን ስሜት
ያጠናክራል። ዜጎች እርስ በእርስ ሲተማመኑና ሲከባበሩ ግጭትና አለመረጋጋት ይቀንሳል ይህም ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ትልቅ ሚና ይኖረዋል። እነዚህ ተዳምረው ደግሞ የአገሪቷን መልካም ገጽታ ከመገንባት ባሻገር የውጭ ግንኙነት ዲፕሎማሲው የበለጠ ተደማጭነት እንዲኖረው፣ በላቀ ደረጃና በሚፈለገው መንገድ ተጽዕኖ እንዲፈጥር የበኩሉን ድርሻ ያበረክታል። ሰላም፣ የውስጥ ጥንካሬና አንድነት ያለው አገር ሌሎች አገራትን ለመሳብና ከእነሱ ጋር በአጋርነት ለመስራት አዳጋች እንደማይሆንበት መገንዘብ ያስፈልጋል።
ሌላው መነሳት ያለበት የትምህርት ቤቶችና የቤተሰብ ሚና ሲሆን የብሔር ብሔረሰቦች በዓል እሴቶች ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ ቤተሰብና ትምህርት ቤቶች የጎላ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ። ከትምህርት ተቋማት ጋር በተያያዘ (በተለይ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች) የክብረ በዓሉን ታሪክ፣ ዓላማ እንዲሁም አስፈላጊነትን በተመለከተ ማስተማር ታዳጊው ትውልድ በዚህ ባሕላዊ በዓል ላይ የበለጠ እንዲሳተፍና ጠቀሜታውን እንዲገነዘብ ያደርጋል። ስለዚህ የትምህርት ሥርዓቱ በዓሉን እንደ አንድ አስፈላጊ የአገር ባሕል ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በማስተማር በታዳጊዎች ውስጥ የአንድነት ስሜት እንዲዳብር ማድረግ ያስፈልጋል። በሌላ በኩል ቤተሰቦች በዓሉን በቤታቸው በማክበርና ለልጆቻቸው ትርጉሙን በማስረዳት በትውልድ አንድነት ላይ ትልቅ ሚና መጫወት ይችላሉ። ወላጆች ልጆቻቸው በባሕላቸውና በታሪካቸው የሚኮሩ እንዲሆኑ በማስተማር በትውልዶች መካከል የሚፈጠረውን ግንኙነት ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲጠናከር ማድረግ ይጠባቅባቸዋል። ማኅበረሰቡ እንደ ማኅበረሰብ በዓሉን በጋራ በማክበርና በመደገፍ አንድነትን ሲያጠናክር መንግሥት ደግሞ የበዓሉን አከባበር በመምራት፣ በማስተባበር፣ አስፈለጊ ግብዓቶችን በመመደብ፣ በማደራጀትና በማስተዋወቅ ረገድ ንቁ ሚና መጫወቱ ስኬታማ ውጤቶች እንዲገኙ ያስችላል። የመገናኛ ብዙኃንም በዓሉን በስፋት በማስተዋወቅና አዎንታዊ መልዕክቶችን በማስተላለፍ በኅብረተሰቡ ውስጥ አንድነትን ለማጠናከር በእጅጉ ስለሚረዱ ሚናቸው የላቀ ይሆናል።
በዓሉ ወጣቶች በባሕላዊ እሴቶች ላይ እንዲያተኩሩና በአገራቸው ልማት ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሚያበረታታ መሆን ይኖርበታል። ስለዚህ በዓሉን ወጣቶች የላቀ ተሳትፎ በሚያደርጉበት መልኩ ማዘጋጀት ላይ የበለጠ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል። አብነት ለመጥቀስ ያህል የወጣቶች የባሕል ቡድኖችን በመጋበዝና የወጣቶችን ሀሳቦች በማካተት በዓሉን የበለጠ ሳቢና ውጤታማ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል። የወጣቶች ተሳትፎ የአገር አንድነትን በሚያጎሉና በጋራ በሚከወኑ ዝግጅቶች ላይ እንዲሳተፉ ለማድረግ እንዲያመች አገራዊ መዝሙር በጋራ እንዲዘምሩ፣ የጋራ ውዝዋዜዎች (ጭፈራዎች) እንዲኖራቸው፣ የክህሎትና ፈጠራ ውድድሮች ላይ እንዲሳተፉ፣ በጋራ እንዲመገቡና ሌሎች መሰል በርካታ ክዋኔዎችን እንዲጋሩ በማድረግ የአንድነትን ስሜት በትውልዱ ውስጥ የበለጠ ማስርፅ ይቻላል።
ከላይ በዝርዝር ለመግለጽ እንደተሞከረው በየዓመቱ የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦችና
ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
ሕዝቦች ቀን አገራዊ አንድነትን የበለጠ ማጠናከርን እንደ አንድ ዋና ግብ በማስቀመጥና ይሄንንም ግብ ለማሳካት ላለፉት 18 ዓመታት አገራዊ በዓል ሆኖ ሲከበር እስከአሁን ዘልቋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በልዩ ትኩረት ሊታይ የሚገባው ከክብረ በዓሉ ዓላማ በተቃራኒ አገራዊ አንድነትን የሚሸረሽሩና በዜጎች፣ በጎሳዎች፣ በብሔሮች ከዚያም ሲያልፍ በክልሎች መካከል አለመግባባት፣ መከፋፈልና ግጭቶችን ሊያስከትሉ የሚችሉ ጉዳዮችን በጥቂቱ መመልከት ተገቢ ይሆናል።
አገራዊ አንድነትን ከሚሸረሽሩ ጉዳዮች መካከል ያልተፈቱ ታሪካዊ ቅሬታዎች መኖር አንዱ ተጠቃሽ ምክንያት ነው። ለምሣሌ በድንበርና ወሰን ላይ የሚነሱ አለመግባባቶች ወይም ቀደም ሲል የተፈጸሙ ኢፍትሃዊ ጥፋቶች ስር የሰደደ ጥላቻ እንዲፈጠር የሚያደርጉ ከሆነ፣ የብሔር ወይም የጎሳ ልዩነትን መሰረት የሚያደርጉ ግጭቶች ሊፈጠሩና የማያቋርጥ የውጥረት ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ። በሌላ በኩል የብሔር እና የባሕል አድሎአዊነት ሲኖር በተወሰኑ ብሔር ወይም ባሕላዊ ቡድኖች ላይ በዘዴ የሚያደሉ ፖሊሲዎች ወይም ተግባራት ቂምን እና ጥላቻን ሊያባብሱና የተወሰኑ ቡድኖችን ከፖለቲካዊ፣ ከኢኮኖሚያዊ ወይም ከማኅበራዊ ዕድሎች ማግለል ወደ ቅሬታ ሊያመራ ይችላል። በተጨማሪም የኢኮኖሚ አለመመጣጠን የሚስተዋል ከሆነ በሐብት ክፍፍል ውስጥ ያሉ ልዩነቶች፣ የሐብት እና የኢኮኖሚ ዕድል እኩል አለመዳረስ ወደ ያልተፈለገ ፉክክርና ግጭት ሊመራ ይችላል። ድህነት እና ሥራ አጥነት በተለይም የተወሰኑ ብሔረሰቦችን ፍትሀዊ ባልሆነ ሁኔታ ሲጎዳ የኅብረተሰብ አለመረጋጋት መንስኤ ሊሆን ይችላል። የፖለቲካ አለመረጋጋት ሲኖር፤ ለምሣሌ ከሙስና እና አምባገነንነት ጋር በተያያዘ በተጋነነ ሙስና ወይም በአምባገነን አገዛዝ የሚታወቁ የፖለቲካ ሥርዓቶች ቅሬታና ብስጭት ሊፈጥሩ ይችላሉ። ፖለቲከኞች የብሔር ወይም የብሔር ስሜትን ለግል ጥቅማቸው ከተጠቀሙ ውጥረትን ያባብሳል። በተፈጥሮና ሌሎች ሐብቶች አግባብ ያልሆነና ሚዛኑን ያልጠበቀ ውድድር ሲኖር እንደ መሬት፣ ውሃ ወይም ማዕድን ባሉ ውስን ሐብቶች ላይ ሚዛኑን ያልጠበቀ ፉክክርና ውድድር ወደ ከፍተኛ ግጭት ሊሸጋገር ይችላል።
ከዚህ በተጨማሪም አካባቢያዊ ውጥረት ሲከሰት የአካባቢ መራቆት ወይም እጥረት በሐብት ላይ የተመሰረቱ ግጭቶችን ሊያባብስ ይችላል። የማንነት ፖለቲካ በስፋት የሚታይ ከሆነ እጅግ የከፋ ብሔርተኝነት ወይም ጎሰኝነት ወደ አግላይ አስተሳሰቦችና ጠላትነት ሊመራ ይችላል፤ የሃይማኖት ብዝሃነትን አለመቀበልና በእኩልነት አለመመልከት ወይም አለማስተናገድ የሃይማኖት አለመቻቻልን መሰረት በማድረግ የሚነሱ ውጥረቶችና ሃይማኖትን ለፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ማዋል ወደ ብጥብጥና ግጭት ሊያሸጋገሩ ይችላሉ። ደካማ የሕግ የበላይነት ሲያይል ለወንጀሎች እና ለሰብዓዊ መብት ረገጣ ተጠያቂነት አለመስጠት የሕግ የበላይነትን አዳክሞ ያለመከሰስ ባሕልን ያዳብራል። እንዲሁም ደካማ ወይም አድሏዊ የሆነ የዳኝነት ሥርዓት ለፍትሕ መጓደል አስተዋፅኦ ያደርጋል፤ የውጭ ጣልቃገብነት፣ የውክልና ጦርነቶች ደግሞ የተለያዩ ብሔር ወይም ብሔረሰቦችን በጂኦ ፖለቲካዊ ምክንያቶች በመደገፍ የውጭ ተዋናዮች ተሳትፎ ግጭቶችን ያባብሳል። ሕገወጥ የጦር መሳሪያ ንግድና ኮንትሮባንድ፤ የጥላቻ ንግግሮችን የሚያሰራጩ ሚዲያዎች ወይም የተወሰኑ

ብሔረሰቦችን የሚያራግቡ ፕሮፓጋንዳዎች ውጥረቶችን ያባብሳሉ።
በአንጻሩ በቴክኖሎጂ እና በድህረ እውነት ተጽዕኖ የሚሰራጭ የሀሰት መረጃ ወይም አሉባልታ ለከፋ ጭንቀትና ግጭት አስተዋፅኦ ያደርጋል። በግጭት ወይም በስደት ምክንያት ማኅበረሰቦችን ከሚኖሩበት ቀዬ ማፈናቀልም ወደበለጠ አለመረጋጋት ያመራል። የባሕል ልዩነቶችን ችላ የሚሉ ፖሊሲዎች ወይም ድርጊቶች ቂም ሊያስከትሉ ይችላሉ። የባሕላዊ ግንዛቤ እጥረት አላዋቂነት እና የተዛባ አመለካከት ሲኖር ስለተለያዩ ብሔሮች ወይም ብሔረሰቦች የተዛባ አመለካከትና አለመረዳት ቀጣይነት ያለው አለመተማመንና ጥላቻ እንዲፈጠር አስተዋጽኦ ያደርጋል።
በሌላ በኩል ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን የበለጠ የሚያጠናክሩና የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በሚፈለገው ደረጃ ግቡን እንዲመታና ስኬታማ እንዲሆን እገዛ የሚያደርጉና ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥሩ የሚታመንባቸውን አገራዊ ጉዳዮችን በጥቂቱ መመልከት ተገቢ ይሆናል። በዋናነት ከሚጠቀሱት መካከል አካታች ዴሞክራሲያዊ አስተዳደርና ፖሊሲዎች
ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
መኖር የመጀመሪያው ነው። የተለያዩ ብሔሮች ውክልናና ተሳትፎን የሚያረጋግጡ ሁሉን አቀፍና ዴሞከራሲያዊ የአስተዳደር መዋቅሮች እንዲሁም ብዝኀነትን፣ አኩልነትንና ፍትሃዊነትን መሠረት ያደረጉና ከአድሎአዊ አሰራር የጸዱ ፖሊሲዎች ለማኅበራዊ ትስስርና ስምምነት አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። ለባሕል ልዩነት አክብሮት እና ለባሕልና ቅርስ ጥበቃ ማድረግ ሌላው ተጠቃሽ ጉዳይ ነው። በአንድ ብሔር ውስጥ ላሉ የተለያዩ ቡድኖች የባህል ስብጥር እውቅና መስጠትና ማክበር ኩራትንና ማንነትን ያጎለብታል። እንዲሁም የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን ባሕላዊ ቅርሶች ለመጠበቅ የሚደረግ ጥረት እርስ በእርስ መከባበርና መግባባት አንዲኖር ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። ሌላው ዋና ጉዳይ ፍትሃዊ የሐብት ከፍፍል፣ ዕድሎችና የልማት ጥቅማ-ጥቅሞች መኖር ነው። በተጨማሪም ሁሉን አቀፍ ሥርዓተ ትምህርትን የሚያራምዱ አካታች የትምህርት ሥርዓቶች መኖር የሁሉንም ብሔረሰቦች ታሪክና አስተዋፅኦ በመገንዘብ የጋራ ብሔራዊ ማንነትን ለመገንባት ያግዛል። በሌላ በኩል ማኅበራዊ ውህደት እና መስተጋብር ሌላው ተጠቃሽ ጉዳይ ሲሆን በተለያዩ ብሔረሰቦች መካከል ውይይትና መስተጋብርን የሚያበረታታ ድልድይ መገንባት የተዛባ አመለካከትን ለማስወገድና ግንዛቤን ለማስፋት ይረዳል። ከዚህ በተጨማሪም በብሔሮች መካከል ችግሮች ሲፈጠሩ ውጤታማ ባሕላዊና ዘመናዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች በአካባቢ እና በአገር አቀፍ ደረጃ መኖራቸው አለመግባባቶች ከመባባሳቸው በፊት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ይረዳሉ።
የሕግ የበላይነትን የሚያስከብር ገለልተኛ የሕግ ሥርዓት መኖሩ ዜጎች የፍትሃዊነት ስሜት እንዲሰማቸው ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል። እንዲሁም ኃላፊነት የሚሰማው መገናኛ ብዙኃን እንዲኖር ማድረግ ስሜት ቀስቃሽነትን የሚያስወግድና ያልተዛባ ዘገባን የሚያበረታታ ሚዲያ እንዲፈጠር ያስችላል። ይህ ደግሞ የጎሳ ግጭቶችን ከማባባስ የሚቆጠብ አዎንታዊ ትረካ እንዲኖር አስተዋጽኦ ከማድረግ ባለፈ የሕዝቡን ብዝኀነት የሚያንፀባርቅ የመገናኛ ብዙኃን እንዲዳብር ይረዳል። ይህ ብቻ አይደለም ዓለም አቀፍ ትብብር እና ድጋፍን በማጠናከርና ዲፕሎማሲያዊ ተሳትፎን በማጎልበት ከጎረቤት አገራትና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ያለን መልካም ግንኙነት ለሰላም ግንባታ ጥረት ድጋፍ እንዲሆን ያደርጋል። የሰብዓዊ ዕርዳታና ድጋፎች ላይ ትኩረት ማድረግ በችግር ጊዜ የሚደረጉ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ዕርዳታዎች አገራዊ መረጋጋትን እንዲያመጡና ግጭቶች እንዳይባባሱ ያደርጋሉ። በተጨማሪም አካታች የአመራር ሥርዓትን በመተግበር ለአገራዊ አንድነትና ውህደት የሚሟገቱና በንቃት የሚሰሩ የፖለቲካና የማኅበረሰብ መሪዎችን በየደረጃው ማፍራትና በየጊዜው ማብቃት ጠቀሜታው የጎላ ይሆናል። እንዲሁም የማኅበረሰብ አንቂ ሞዴሎችን በመለየት በማኅበረሰቦች ውስጥ መቻቻል እና መግባባትን የሚያበረታቱ ግለሰቦችን በአዎንታዊ ጎን በመጠቀም በሌሎች ላይ ብዝኀነትን እና አገራዊ አንደነትን በተመለከተ በጎ ተጽዕኖ እንዲያሳድሩ ማድረግ ጥቅሙ የላቀ ይሆናል።
የማኅበረሰብ ልማት መርኃ ግብሮችን በመቅረጽ ብሔርና ዘር ሳይለዩ ለጋራ ዕድገት አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ማድረግ ጠቀሜታው የጎላ ነው። የዴሞክራሲ ተቋማትን የበለጠ ማጠናከርና ችግሮች ሲኖሩ በንግግርና በውይይት መፍታት
እንዲሁም በጠመንጃ ኃይል ፍላጎትን ለማሳካት የሚደረጉ ጥረቶችን ማስወገድ፤ ቅሬታዎችና በደሎች በሽግግር ፍትህ ማዕቀፍ እንዲታዩ ማስቻል ሰላምና አንድነትን ለማምጣት ትልቅ ፋይዳ ይኖራቸዋል። አነዚህ ከላይ በጥቂቱ የተዘረዘሩት ጉዳዮች እርስ በእርስ የተሳሰሩ መሆናቸውንና ዘላቂ ሰላም እና አንድነትን የበለጠ ለማጠናከር የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ጥረት የሚጠይቅ መሆኑን መገንዘብ ጠቃሚ ነው።
ስለሆነም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል መከበር ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ያስገኛቸውን ስኬቶች የበለጠ አጠናክሮ ለማስቀጠል፤ አገራዊ አንድነትን ለማረጋገጥ ለብዝኀነት የተሰጡ ሕጋዊ እውቅናዎችን ማስፋትና እንደ አስፈላጊነቱ ማሻሻል፣ በዓሉን በተመለከተ የሕግ ማዕቀፎችን እንደ አስፈላጊነቱ በየጊዜው ማሻሻል፣ የአሠራር ሥርዓቶችን መከለስ እንዲሁም በብዝኀነት አጠባበቅና አያያዝ ዙሪያ የሚሰሩ ተቋማትን የበለጠ ማጠናከር ያስፈልጋል።
ዴሞክራሲና ፍትህን የበለጠ በማጎልበት ብዝኀነትን በእኩልነትና በፍትሃዊነት ማስተዳደርና ማስተናገድ ያስፈልጋል። ሕዝባዊ አንድነት፣ አብሮነትንና እኩልነትን ሊሸረሽሩ የሚፈልጉ ኃይሎችን መታገልና ያሏቸውን ማንኛውንም ጥያቄዎች በዴሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ እንዲያቀርቡ ምቹ ሁኔታ መፍጠርና የፍትህ ተቋማትን ማጠናከር ያስፈልጋል። የፌዴራሊዝም አስተምህሮን የማስፋት ተግባር ልዩ ትኩረት የሚያስፈልገው ሲሆን ፅንፈኛ ብሔርተኛነት አሰተሳሰብን ለመቀነስና ለመቀየር የአስተምሮት ስርፀት ሥራው ተቋማዊ በሆነ ሥርዓት እንዲሆን የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናከሮ ማስቀጠል የበለጠ ውጤት ለማምጣት ይረዳል።
በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ የፌዴራሊዝምና ሕገ- መንግሥት አስተምህሮ ማዕከል ተገንብቶ ተቋማዊ በሆነ መልኩ አገልግሎት መስጠቱ የሚታወቅ ቢሆንም ቀጣይነት ባለው መልኩ በጥናት ሳይ የተመሰረቱ ሥራዎችን በስፋት አጠናክሮ መስራት ያስፈልጋል። ከላይ የተዘረዘሩትን አሉታዊ ምክንያቶች ለማስወገድና ችግሮችን በአግባቡ ለመፍታት እያንዳድንዱ ዜጋ መንግሥት በየደረጃው በመላ አገሪቷ የሚተገብራቸውንና የሚጠቀማቸውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ዕቅዶችና ስትራቴጂዎች በሚገባ መረዳትና ስኬታማ ውጤት እንዲያመጡ የላቀ ተሳትፎና የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅበታል። የኢትዮጵያ ብሔሮችና ብሔረሰቦች በሰላም አብረው እንዲኖሩና እጅ ለእጅ ተያይዘው እንዲበለጽጉ ሁላችንም ብሔራችንን፣ ዘር እና ሃይማኖታችንን እንዲሁም ሌሎች ልዩነቶቻችንን እርስ በእርስ ለመተዋወቅ፣ ለመቀራረብ፣ ለመደማመጥ፣ ለመከባበር፣ ለመረዳዳት፣ ለመተጋገዝ እንዲሁም በጋራ ለመበልፀግ መጠቀም ያስፈልጋል።
በአጠቃላይ ጠንካራና ተቀባይነት ያለው ብሔረ መንግሥትና አገረ መንግሥት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ብዝኀነትንና ኅብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ሥርዓትን ይበልጥ ማጠናከር እንዲሁም ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ አድርጐ መስራት ያስፈልጋል።
ፖለቲካ

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
ብሪክስ

የአዲሱ ‘ሥርዓተ- ሉል’ ማዕቀፍ
በአየለ ያረጋል
ቅምሻ…
ዳግማዊውን የዓለም ጦርነት ተከትሎ የዓለም ምጣኔ ሐብት ተቃወሰ። የብዙኀኑ አገራት ዕድገት ተሰናከለ። ይህ ሁነት ታዲያ በተለይ ኃያላን መንግሥታት የወሰን ዘለል ቀጣናዊ እና የበይነ- አገራዊ ትብብሮችን እንዲናፍቁ አስገደደ። በሂደትም ለዛሬዋ የአንድ ወገን የበላይነት የሰፈነባት መልክዓ-ዓለም እንድትፈጠር እርሾ ጣለ። ከብዝኀ-ወገን ይልቅ የአንድ ወገን ‘ሥርዓተ ሉል’ ወይም አግላይ ‘መልክዓ-ዓለም’ ሥርዓት ተፈጠረ።
ድሕረ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ቀዝቃዛው ጦርነት ቀጠለ። ዓለም በአሜሪካ የሚሾረው የካፒታሊስቱ ዓለም እና ሶቪዬት

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
ሕብረት ባሰለፈችው የኮሚኒስት ጎራ ተከፈለች። ከአሥርት ዓመታት በኋላ ሶቪዬት ሕብረት ተበታተነች፤ የሶሻሊስቱ ጎራም ከሰመ። ቀዝቃዛው ጦርነትም ቀዘቀዘ።
በቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን ግን አያሌ የአገራት ጥምረቶች መዋቀራቸው አልቀረም። በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1962 የኢንዱስትሪ ብልፁግ አገራት ‘ቡድን-10’፣ በ1964 ታዳጊ አገራት የ’ቡድን-77’፣ በ1970 ‘ቡድን-5’ (በኋላ ቡድን ሰባት)፣ በ1999 ደግሞ ‘ቡድን 20’ ጥምረቶች ተመሰረቱ። ይህ የበይነ-አገራት ትብብር አንድም ጸጋን ተጋርቶ ዕድገትን ማስቀጠል፣ አንድም በሌሎች ላይ የራስን ተጽዕኖ ለመዘርጋት፣ በሌላ በኩል ደግሞ የምዕራብ መራሽ ንጥል መልክዓ-ዓለምን ለመለወጥ ያለመ እንደሆነ አጥኚዎች አትተዋል። በዓለም ንግድ ምህዳር ውስጥ ብቅ ያሉ አዳጊ አገራትም የየራሳቸውን ጎራ መመስረትና መተባበራቸውን ቀጠሉ።
በዚህ መሀል ግን የደቡብ ንፍቅ ክበብ ክፍለ ዓለም ተገለለ። ደሃ አገራት ዳር ቀሩ - በተለይ በአፍሪካ። በሂደትም ሁለተኛው የዓለም ጦርነት የወለደው የአንድ ወገን መልክዓ-ዓለም የገደዳቸው አገራት መፍትሔ ሻቱ። በጥቂት ምዕራባዊያን የበላይነት ተፅዕኖ ስር የወደቀውን መልክዓ ዓለም እና የመንግሥታቱን ድርጅት ሥርዓት መልክ መለወጥ በሚል መምከር ያዙ።
ከሁሉም በፊት በቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን አንድ ሁነት ነበር። በ1955 (እ.አ.አ) በዛሬዋ ኢንዶኔዥያ የተካሄደው የባንዱንግ የአፍሮ-ኤዥያ ጉባዔ ለዚህ ፈር ቀዳጅ ነበር። ኢትዮጵያን ጨምሮ 29 የዓለም አገራት በባንዱንግ ጉባዔ ተሳትፈዋል። ጉባዔው የኤዥያና የአፍሪካ አገራትን ወዳጅነትና አጋርነት መመስረት፣ ቅኝ ግዛትና የእጅ አዙር ቅኝ ግዛትን ከአገራት መንቀል፣ የደቡብ ደቡብ ትብብርን
ማጠናከር፣ ሰላማዊ፣ ሚዛናዊና አካታች ‘ሥርዓተ- ሉል’ (Joint Global Governance) መፍጠር የሚል ዓላማ ያነገበ ነበር። የብሪክስ ጥምረትም የባንዱንግ ጉባዔ እርሾ እንደነበረው መናገር ይቻላል።
የባንዱግ ጉባዔ በዩጎዝላቪያው አብዮተኛ ማርሻል ጆሴፍ ቲቶ መሪነት አብዛኛው የዓለማችን አገራት ያሰባሰበው የገለልተኛ አገራት ንቅናቄ እንዲወለድ መሰረት ጥሏል። ዛሬም የብዝኀ ዓለም ለመፍጠር ለሚደረጉ ጥረቶች የዘርፉ ምሁራን የባንዱንግ ጉባዔ እሴቶችን እንደ መሰረት ይወስዷቸዋል። በዚህ ፅሁፍ የብሪክስ አመሰራርት፣ አመክንዮ፣ ግብና የአዲሱ ‘የብዝኀ ሥርዓተ ሉል’ መፃዒ ዓለም ግንባታ የሚኖረው ፋይዳ ይዳሰሳል።
ከባንዱንግ እስከ ብሪክስ፤ የብዝኀ-ዓለም ድምጾች
የአፍሪካ-ኤዥያ ጉባዔ ይሉታል የሚያዝያ 1955ቱን የባንዱንግ ጉባዔ። ከኢትዮጵያ በስተቀር በአብዛኛው ታዳሚያን አገራት ከቅኝ አገዛዝ ነጻ የወጡ የአፍሪካና የኤዥያ አገራት ነበሩ። በዚህ ጉባዔ ኢትዮጵያና ሌሎች አምስት የአፍሪካ አገራት ማለትም ግብጽ፣ ሱዳን፣ ላይቤሪያ፣ ጋና (የዚያኔዋ ጎልድ ኮስት) እና ሊቢያ ተሳትፈዋል። ሌሎቹ አገራት በቅኝ ግዛት ስር ነበሩና። (በነገራችን ላይ በባንዱንግ ኮንፈረንስ የተሳተፉ የወቅቱ የብሪክስ አባላት ቻይና፣ ሕንድ፣ ኢትዮጵያ፣ ግብጽ፣ ኢራንና ሳዑዲ ዓረቢያ ናቸው)።
በዚያ ዘመን የሕንድ፣ የፓኪስታን፣ የኢንዶኔዥያ፣ የሲሪላንካ፣ የበርማ እና መሰል አገራት መሪዎች ከቀዝቃዛው ጦርነት ጎራ ይልቅ ብዙ ሆነን፣ በትብብርና በጋራ ሰላማዊ ዓለም መገንባት አለብን የሚል ንቅናቄ አንግበው ነበር። ሰላም፣ ፍትህና ዓለም አቀፍ ኃላፊነት እሴቶች እንዲሰፉ፣ ዓለም አቀፉ የመንግሥታት ድርጅት አሳታፊነት እንዲኖረው የሚጎተጉቱ ሃሳቦች ተስተናግደውበታል። ከየአገራቱ ጥሬ ዕቃዎችን ወደ ምዕራባዊያን ከማጋዝ ይልቅ የደቡብ ደቡብ ትብብርን በማጠናከር በይነ- ደቡብ የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር መገንባት አለብን የሚሉ ሀሳቦች ነበሩ። ይህ ውጥን ታዲያ ከዛሬው የብሪክስ ፍልጎትና መሻት ይለያል ማለት አይቻልም፤ ይልቁኑም የበይነ-ደቡብ ንፍቀ ክበብ ትብብር የተጸነሰበትና ለዛሬው የብሪክስ እሳቤ እርሾ የተጣለበት ነበር ለማለት ያስደፍራል።
የባንዱንግ ጉባዔ መሳካት የዛሬዋን ኢንዶኔዥያ መሰረት የጣሉትና የአገሪቷ የድህረ ነፃነት ቀዳሚው ርዕሰ መንግሥት ሱከርኖ ዱኤሌ ነበሩ። ፕሬዚዳንት ሱካርኖ በጉባዔው ላይ ያደረጉት የአስደናቂ ንግግራቸው ዐውድ የጉባዔው ታዳሚያን በኢኮኖሚ ርዕዮተ ዓለም፣ በሃይማኖት አስተምሮም ሆነ በሥርዓተ መንግሥት ባሕሪ፣ በብዝሃኀነታቸው እና በማንነታቸው ሳይወሰኑ በብዝኀነት ውስጥ አንድነትን፣ ወንድማማችነትን በዓለም ምህዳር ላይ ማንበር ያለመ ስለመሆኑ ነበር ያወሱት። ከንግግራቸው ሃሳብ ስንመዝም እንዲህ የሚል ይገኝበታል።
“ይህ ዕለት በሰው ልጆች ታሪክ ሁሉንም መልክና ቀለም ያሰባሰበ ሁነት ነው። አገሬ ይህን በማስተናገዷ ኩራት ይሰማኛል። ይህ ሁነት ወደነገዋ ዓለም አዲስ መሳፈሪያ ምዕራፍ መክፈቻ ነው። በተሳታፊዎቹ መካከል መልከ ብዙ ልዩነቶች ቢኖሩም ለመሰባሰብ አላገደንም። ብዝኀነታችንን ማንስ ይክደዋል? ትልቆቹም ትንሾችም አገራት እዚህ አሉ። ሁሉም ሃይማኖቶች እዚህ መሃል
ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
ይገኛሉ። ሁሉንም አይነት የፖለቲካ መልኮች እዚህ አሳትፈናል። ማንኛውም ኢኮኖሚያዊ አስተምህሮ በዚህ አዳራሽ ተወክሏል። እዚህ ያሰባሰበን ብዝኀነት ነው። አንድነት ነው። ይህ ጉባዔ አንዱ ሌላውን የሚጋፋበት ሳይሆን የወንድማማቾች ኮንፈረንስ ነው”።
የባንዱንግ ጉባዔ ባለ አሥር ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል። ይህ ድንጋጌ “አስሩ በሰላም አብሮ የመኖር እሴቶች” (THE TEN PRINCIPLES OF PEACEFUL CO-EXISTENCE) በሚል ይታወቃል። አስሩ ነጥቦች ሲጠቃለሉ ሰብዓዊ መብት፣ የአገራት ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት፣ ያለ ዘር ልዩነት በእኩል መታየት፣ ጸረ-ጣልቃገብነት እና ገለልተኝነት፣ የግጭቶች ሰላማዊ አፈታት፣ የጋራ ጥቅምና ትብብርን ማሳደግ እንዲሁም ፍትህና ዓለም አቀፋዊ ግዴታዎችን መወጣትን የተመለከቱ ናቸው።
በፈረንጆቹ የዘመን ቀመር 2001 አራቱ አገራት ማለትም ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ እና ቻይና አንድ ማኅበር ወጠኑ። ስብስባቸውንም የአገራቱን የእንግሊዝኛ የመጀመሪያ ሆሄያት በመውሰድ “BRIC” (ብሪክ) የሚል ስያሜ አወጡለት። ስያሜውን አሃዱ ብለው ያስተዋወቁት ጎልድማን ሳክስ የተሰኘው የአሜሪካው የፋይናንስ ተቋም የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ጂም ኦ’ኔል ናቸው።
የብሪክስ አመሰራረት ምጣኔ ሐብታዊ ትብብር እንደነበር ይወሳል። ሁሉን አቀፍ ሥርዓተ ሉል ማስፈን እና ከጣልቃገብነት የጸዳ ሉላዊ ትብብር መገንባት መሆኑን አባላቱ አሳወቁ። በተለይም አሜሪካ መላውን ዓለም ‘እግር ከወርች’ ያሰረችበትን የዶላር መገበያያን በአማራጭ መገበያያ ገንዘብ መተካት እንደሚያስፈልግ ይፋ አደረጉ። አዲስ የዓለም ሥርዓት (NEW WORLD ORDER) አይቀሬነት ቀስ በቀስ ተቀነቀነ።
ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ (በ2010) አፍሪቃዊቷ አገር ደቡብ አፍሪካ ስብስቡን ተቀላቀለች። ጥምረቱም ብሪክስ (BRICS) ተሰኘ። የደቡብ አፍሪካ መቀላቀል ደግሞ የገለልተኛ አገራት ንቅናቄ (Non Aligned Movement) ፅንሰ ሃሳብ መሰረት ትብብሩ እንዲያድግ አስችሎታል። ደቡብ አፍሪካ በአፍሪካ የተሻለ ዕድገት ባለቤት መሆኗ ብቻ አይደለም። አንድም ከብራዚል ጋር የሚኖራት ስትራቴጂካዊ ስፍራነት፣ አንዲሁም ብሪክስና አገራቱ ከአፍሪካ ጋር ለሚኖራቸው ቀጣይነት ያለው ትብብር እንደ ሁነኛ በር ለመጠቀም ሁነኛ ስፍራ ተሰጣት።
በእርግጥ የብሪክስ ጥምረት አገራቱ አምሥት መሆናቸው ብቻ ሳይሆን የአባላቱ ምንነት የተለየ መልክ ነበረው። ይኸውም አገራቱ በዓለም ላይ በሥነ ሕዝብ፣ በኢኮኖሚ አቅምና በግዛታቸው ግዝፈት ሲለኩ ወደ ‘ብዝኀ ሥርዓተ ሉል’ ለመግባት እንደሚቻል ተስፋ ተጥሏል።
ብሪክስ ከአምሥቱ አገራት ባሻገር ባሳለፍነው ዓመት ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች አምስት አገራትን ወደ ጥምረቱ በመቀላቀል አባላቱን ወደ አስር አሳደገ። በ2023 (እ.አ.አ) ደቡብ አፍሪካ ላይ በተካሄደው የብሪክስ ጉባዔ ኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች እና ኢራን ብሪክስ ላይ ሲደመሩ ጥምረቱ ‘ብሪክስ እና ሌሎች’ (BRICS+) የሚል ስም ያዘ። ለውጡ ግን የስም ብቻ አልነበረም። የብሪክስ ዕድገትና የዓለም አገራትን ቀልብ መሳብ ከስም በላይ ትልቅ አንድምታ ተሰጠው። ይህ ደግሞ የምዕራብ
መራሹን ሸውራራ ዓለምን አግላይና የዕጅ አዙር ቅኝ ግዛት ሥርዓት ለመገዳደር ተጨማሪ መሰረት ጣለ። ለዚህ ደግሞ አሃዞቹ እና ግቦቹ አመላካች ናቸው።
ብሪክስ እና አሃዞች
የብሪክስ መቋቋምና እመርታ በአንድ ወገን የሚሾር ዓለም ባለቤቶችን ብርክ አስይዟል። ብሪክስ የዓለም አገራት የስበት አስኳል ሆኗል። አብሮ ማደግን፣ በትብብር መልማትን፣ ፍትህና ሚዛናዊ ሥርዓተ ሉልን የሚሹ አገራት ፊታቸውን ወደ ብሪክስ ማዕቀፍ እያዞሩ መጥተዋል። የብሪክስ ማዕቀፍ ዛሬ ሳይሆን ነገ ምን አይነት ተጽዕኖ እና ተገዳዳሪ ጎራ እንደሚሆን አሃዞች ይናገራሉ።
ብሪክስ የ3 ነጥብ 5 ቢሊዮን የዓለም ሕዝብን ይወክላል። ከ45 በመቶ በላይ የሚገመተው የዓለም ሕዝብ በብሪክስ ታቅፏል ማለት ነው። የጥምረቱ አባል አገራት ዓመታዊ ዕድገት ወደ 29 ትሪሊዮን ዶላር ይጠጋል። ይህም ከዓለም ኢኮኖሚ 28 በመቶውን ይሸፍናል። የባለ ፈጣን ዕድገት አገራት የብሪክስ ቤተሰብ ናቸው። የብሪክስ ሕብረት 44 በመቶውን የዓለም ነዳጅ ድፍድፍ ዘይት ምርት የያዘም ነው።
የብሪክስ አባላት 30 በመቶውን የዓለም መልክዓ ምድር ይሸፍናሉ። አባል አገራቱ ደግሞ የዓለምን 35 በመቶ ዓመታዊ ጥቅል ምርት ያመነጫሉ። በአማካይ አንድ አራተኛው ኤክስፖርት ከነዚህ አገራት ይወጣል። ከ30 በላይ አገራት የብሪክስን ቤተሰብነት ለመቀላቀል ጥያቄ አቅርበዋል።
በእርግጥ የብሪክስ (BRICS+) አባል አገራት ማንነትም ስምና ቁጥር ብቻ አይደለም። በመልከ ብዙ መለኪያዎች የየራሳቸው ልዩና ስትራቴጂካዊ አገራት መሆናቸው የጥምረቱን ስብስብ ይበልጥ ያገዝፈዋል።
ቻይናም ቻይና፣ ሩስያም ሩስያ ናቸው፤ ብራዚልና ሕንድም እንዲሁ፤ ደቡብ አፍሪካም ብትሆን። እነዚህን ነባር የብሪክስ ምሰሶዎች ዘለን አዳዲሶቹን አባላት በወፍ በረር እንቃኝ።
ምድረ ቀደምቷ አገራችን ኢትዮጵያ በአፍሪካም ሆነ በዓለም የዲፕሎማሲ ታሪክ የደመቀ ገድሏ፣ ጂኦ- ፖለቲካዊ አቀማመጧ፣ የአፍሪቃዊያን ቀንዲልነቷ፣ የአፍሪካ ፖለቲካ ማዕከልነቷ ተደማምሮ ብሪክስ አፍሪካን ስትራቴጂካዊ አጋር ለማድረግ አይነተኛ አገር ትሆናለች። ተንታኞች የኢትዮጵያን አባልነት እንደ አገርም፣ እንደ አፍሪካም ልዩ ትርጉም ይሰጡታል።
ግብጽ በሰሜን አፍሪካ እና የዓረቡ ዓለም ተፅዕኖ ፈጣሪ እንዲሁም የዓረብ ሊግ መሥሪያ ቤት መገኛ ናት። አውሮፓዊያኑ እንደ ስትራቴጂ አገር የሚወስዷት መሆኗም እሙን ነው።
ኢራን በጠንካራ ኢኮኖሚዋ እና ለምዕራባዊያን የማትመች ተገዳዳሪ አገር መሆኗ ይታወቃል። የዓለማችን ሶስተኛዋ የነዳጅ ክምችት ያላት አገር ነች። የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በዓለም ኢኮኖሚ ወሳኝ ድርሻ አላት። በሎጂስቲክስ፣ በንግድ እና በወጪ ምርቶች ክፍፍል ላይ የወቅቱ የዓለማችን የስበት ማዕከል ሆናለች። ሳዑዲ ዓረቢያ የእስልምናው ዓለም መሪ ተደርጋ ትቆጠራለች። በእስልምና አማኒያን ዘንድ ቀዳሚዋ ተመራጭ አገር ነች።
ስለዚህ ሁሉም አገራት የየራሳቸው ልዩ መልክና

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
ክብር አላቸው። በዓለም ላይ የሚታፈሩበት እና የሚከበሩበት መለያ ይዘዋል። ይህን ተናጠላዊ ክብር ወደ ብሪክስ ማዕቀፍ መሰባሰቡ ብሪክስ የሚኖረውን ተዓማኒነት ይጨምራል። እንደ ቡድን ብቻም ሳይሆን በአፍሪካ፣ በላቲን አሜሪካ፣ በእስያና በመካከለኛው ምስራቅ የሚኖረው ተዕጽኖ ፈጣሪነት ከፍተኛ ይሆናል። በተለይም የምሥራቁ ንፍቀ ክበብ አገራት ዕኩልና የጋራ ተጠቃሚነትን ሂደት በማየት ለብሪክስ አዎንታዊ አተያይና የመቀላቀል መሻት እንዳሳደረባቸው ጥናቶች ያሳያሉ።
የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለብሪክስ ቴሌቪዥን በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት ከ30 በላይ አገራት ብሪክስን ለመቀላቀል ጥያቄ አቅርበዋል። ሩሲያ የ2024 የብሪክስ ሊቀመንበር እንደነበረች ይታወሳል። ሚኒስትሩ እንደሚሉት የብሪክስ አባል አገራት ብቻ ሳይሆን የብሪክስ ወዳጅ አገራት የሚል ትብብር ለመመስረትም ጥረት እየተደረገ ነው። በሩሲያ ካዛን ከተማ በተካሄደው የብሪክስ ጉባዔ አባል ያልሆኑ አሥር ወዳጅ አገራትም ጉባዔውን መታደም ችለዋል። ይህም የብሪክስ ሙሉ አባል ባይሆኑም እንኳ ከአባል አገራቱ ጋር የሚኖራቸው መግባባትና ትብብር ለመጻዒው ተስፋ ብሩህ ተስፋ ሰንቋል።
የዓለም አቀፍ ተቋማት ሪፎርም
የዓለም መንግሥታት አወቃቅር ኢ-ፍትሃዊነትና ሚዛን መሳት እንዲታረም ትግል ከተጀመረ ግማሽ ምዕተ ዓመት አልፏል። ዳሩ ዛሬም ችግሩ አልተፈታም። እናም የመንግሥታቱን ድርጅት ጨምሮ የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት መዋቅራዊ ሪፎርም እንደሚያሻው ዕሙን ነው።
ለማሳያነት 37 በመቶ ካፒታል ገበያ በአምሥት አገራት ቁጥጥር ስር ነው። የዓለማችን 162 አገራት
በካፒታል ስቶክ ያላቸው ድምፅ 30 በመቶ ብቻ ነው (በአማካይ ከአንድ በመቶ በታች ማለት ነው)። ቀሪው 70 በመቶው በ20 አገራት የተያዘ ነው።
ዝቅተኛና ከፍተኛ ገቢ ባላቸው አገራት መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ መጥቷል። ይህን ክፍተት ለማረም ቢወተወትም አልተሳካም። የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ሥርዓት አልተሻሻለም።
የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF) እና ዓለም ባንክ ለዚህ ማሳያ ናቸው። በዓለም ኢኮኖሚ ድርሻ እና የምርት መጠን ግማሹን የሚሸፍኑት ታዳጊ አገራት በተቋማቱ ላይ ግን የባለቤትነት መብት ተነፍጓቸዋል። ብሪክስም ይህን ይሞግታል። በእስካሁን ጥረትም በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የታዳጊ አገራት ተሳትፎ እንዲሻሻል ሙከራ ቢያደርግም ዛሬም ይህ ነው የሚባል ለውጥ አልመጣም።
የፋይናንሥ ጥናት ምሁሩ ፕሮፈሰር ዋንግ ዎን ሉላዊነት በዓለም አስተዳደር ሥርዓት ላይ ጉልህ ተፅዕኖ እንዳለው ያትታሉ። የዓለም አስተዳደር ሲባል የበላይነት ፍላጎትን ሚዛን መጠበቅ እና በዓለም ላይ የጋራ ግቦችን ዕውን ማድረግን ይመለከታል። ለምሣሌ ሐብትን አቀናጅቶና የጋራ ተቋም መስርቶ መጠቀም (እንደ ዓለም ባንክና አይ ኤም ኤፍ)፣ ዓለም ወደ አንድ መንደር የሚለው ጽንሰ ሃሳብ የአንድ ወገን ብቻ ሳይሆን ሁሉን ያማከለ እና ለጋራ ጥቅም የቆመ ሥርዓት የመገንባት ገዳይ ነው።
እ.አ.አ በ2020 በወጣው ጥናት ብሪክስ አዳዲስ አባላትን ሳይጨምር ቀዳሚዎቹ አምሥቱ አገራት ብቻ ከዓለም ኢኮኖሚ 19 በመቶ ኤክስፖርት፣ 16 በመቶ ኢምፖርት እንዲሁም 19 በመቶ የወጪና ገቢ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ድርሻ ነበረው።
የፀጥታው ምክር ቤትን ጨምሮ የመንግሥታቱ ድርጅት ሁሉን አቀፍ ተቋማዊ ማሻሻያ ሌላው ጉዳይ ነው። የድርጅቱ አወቃቅር በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግሥት የነበረውን ድባብ እንጂ የብዝኀ ዓለምን መልክ አልያዘም የሚል አሳማኝ መከራከሪያ አለው። ምክንያቱም የሁለተኛው ዓለም ጦርነት አሸናፊ አገራት ብቻ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ተሰጥቷቸዋልና። በፀጥታው ምክር ቤት አፍሪካ እና ላቲን አሜሪካ አልተወከሉም። ሌሎች የኤዥያ አገራትም በሚገባ ተወክለዋል ማለት አይደለም። አባላቱን ከ113 ወደ 193 ያሳደገው የመንግሥታቱ ድርጅት ለምዕራባዊያን መሣሪያ ሳይሆን ሁሉንም ያቀፈና ለሁሉም የቆመ የጋራ ማኅበር መሆን አለበት ነው ጥያቄው። በፀጥታው ምክር ቤት የሚታዩ አብዛኞቹ ጉዳዮች አፍሪካ ነክ ቢሆኑም አፍሪካዊያን ግን ድምጽ መስጠት የሚያስችል ቋሚ መቀመጫ የላቸውም። ስለዚህ ከሪፎርም አቀንቃኝ አደረጃጀቶች መካከል ደግሞ የብሪክስ ጥምረት ግንባር ቀደሙ ነው። ድምጽን በድምፅ የመሻር መብት ያላቸው ሩሲያ እና ቻይና ሳይቀሩ የድርጅቱን ሪፎርም ሲያስተጋቡ ቆይተዋል።
የቻይናው ፕሬዚዳን ሺ ጂንፒንግ ከአንድ ወር በፊት በካዛን በተካሄደው የብሪክስ+ መሪዎች ጉባዔ ላይ የበይነ-ደቡብ ንፍቀ ክበብ መለወጥ ለጋራ ብልጽግና ለተሻለ፣ ሰላማዊና ፍትሃዊ ዓለም ግንባታ እንደሚበጅ እንዲህ ገልጸው ነበር።
“የዓለም አቀፉ ምህዳር ምንም መልክ ይኑረው እኛ እንደ ቻይና ምንግዜም የደቡብ ንፍቀ ክበብ በልባችን ቦታ አለው፤ የዘረጋነውን መሰረታችንንም
ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
እንቀጥላለን። የደቡብ ንፍቀ ክበብ አገራት በብሪክስ ሙሉ አባልነት፣ በብሪክስ+ ወዳጅነት በመቀላቀል ለሰው ልጅ ሁሉ የተሻለ ነገ ለመገንባት የደቡቡን ንፍቀ ክበብ ጥንካሬ ማቀናጀት ግድ ይለናል። ለጋራ ብልጽግና መጣር አለብን። የደቡብ ክፍለ ዓለም ለልማት ተነስቷል፤ በልማትም ይበለፅጋል። ለጋራ ዕድገት መንቀሳቀስ እና በዓለም አቀፉ የኢኮኖሚ አስተዳደር ተሃድሶ ውስጥ ንቁ እና መሪ ሚና መጫወት ይገባናል። የደቡብ ክፍለ ዓለም ልማት መርሐ ግብር ከሦስት ዓመት በፊት ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ወደ 20 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚጠጋ የዕድገት ገንዘብ ማቅረብ እና ከአንድ ሺህ አንድ መቶ በላይ ፕሮጀክቶች እንዲጀመሩ አስችሏል። ሁሉንም ስልጣኔዎቻችንን ማስተዋወቅ፣ ማስማማትና በጋራ ማልማት አለብን። ብዝኀ ሥልጣኔ የዓለማችም ጥራት መሰረት ነው። ሥልጣኔን እንጋራ። እንደየ አገራዊ ዐውዳችን ወደ ዘመናዊነት ለመራመድ የሚያስችል ተግባቦትና ውይይት ይኑረን። ቻይና የደቡብ ንፍቀ ክበብ አሳቢያን ጥምረትን በማስተባበር የሕዝብ ለሕዝብና ልምድ ቅመራ እንዲጎለብት ትሰራለች”።
ከ15ቱ የፀጥታው ምክር ቤት አባላት መካከል ሥድስቱ ምዕራባዊያን ናቸው። ይህ ደግሞ ከሕዝብ ቁጥራቸው፣ ከኢንዱስትሪ አቅምና የቆዳ ስፋታቸው አኳያ ሚዛናዊ አይደለም። ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድና ደቡብ አፍሪካ ብቻቸውን 40 በመቶውን የዓለም ሕዝብ ይሸፍናሉ። ስለዚህ ብራዚል፣ ሕንድ እና ሌሎች የአፍሪካ አገራት ውክልና በፀጥታው ምክር ቤት መኖር እንዳለበት ብሪክስ ያምናል።
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዘንድሮው የካዛን ጉባዔ ላይ የብሪክስ መስፋፋት የብዝኀ መልክዓ ዓለም እየተፈጠረና የአሜሪካ መራሹን ሥርዓተ ሉል እየሞገተ ነው ብለው ነበር። አብዛኛው ክፍለ ዓለም ብሪክስን እየተቀላቀለ በመሆኑ ብዙኀኑ የዓለም ማኅብረሰብ የሚሻውን ለሁሉም የተመቸ ሥርዓተ ሉል በመገንባት ላይ መሆኑን እንደሚያመለክት አንስተዋል። ፕሬዚዳንት ፑቲን የብሪክስ መንገድ ከባንዱንግ ጉባዔ የአካታችነት እሴቶች ጋር የሚጣጣም እንደሆነም እንዲህ ነበር የገለጹት።
“የማኅበራችን የትብብር ጉዞ በእኩልነት፣ በወዳጅነት፣ በእርስ በእርስ ጥቅሞች በመከባበርና ነገን ታሳቢ ባደረገ ስትራቴጂካዊ መርሆዎች ላይ የተመሰረተ ነው። ይህ አካሄድ ደግሞ የብዙኀኑን የዓለም ማኅብረሰብ መርህ መሻት የሚያሟላ ነው”።
ዕውቁ ዲፕሎማት የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ደግሞ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ገንዘብ አሰጣጥ ውሳኔዎች በአንድ ወገን ፍላጎት ላይ የተንጠለጠሉ በመሆናቸው የታዳጊ አገራትን የልማት ፍላጎት እንደማይደግፉ ጠቅሰዋል። በዓለም የንግድ ድርጅት ረገድም በድርጅቱ ውስጥ ማንኛውንም ችግር ለመፍታት የተቋቋመው የግጭት አቤቱታ ሰሚ ክፍል ከዓመታት በፊት ታግዷል። ስለዚህ ነባር ተቋማትን ሪፎርም ከማድረግ ባሻገር አማራጭ የክፍያ ሥርዓት መዘርጋት፣ ባንኮች በየአገራቱ ገንዘቦች የሚጠቀሙበት አሰራር መዘርጋት እና ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጀምሮ ዶላርን በብቸኛ መሣሪያነት የሚጠቀመውን የመድህን ሥርዓት መለወጥ አጀንዳዎች ላይ እየሰራ ነው። ዶላር

የአገራት መጨቆኛ መሣሪያ በመሆኑ አማራጭ መላ መምታት ይሻላል ባይ ናቸው ሴርጌይ ላቭሮቭ። እናም ተዓማኒ፣ ቀጣይነት ያለውና ዘላቂ ሥርዓት እውን ለማድረግ ዕድሎች ተመቻችተዋል።
የብሪክስ ማዕቀፍ ፍልስፍና ዴሞክራሲያዊ የዓለም ግንኙነት፣ የታዳጊ አገራት በሚዛናዊ ሥርዓተ ሉል ተሳትፎን ማረጋገጥ በተለይም ደቡቡና ምስራቁ ክፍለ ዓለም በመንግሥታቱ ድርጅት ሚዛናዊ ውክልና እንዲኖረው ማስቻል እንዲሁም የራሱ የሆነ የፋይናንሥ ተቋም በማቋቋም ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሥርዓት ማበጀት ነው።
ከዚህም ባሻገር የብሪክስ አባላት አፍሪካዊያን የሚወተውቱትን የመንግሥታቱን ድርጅት መዋቅራዊ ማሻሻያ እና የአፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ውክልና የማግኘት ጉዳይ ዳር እንዲደርስ መደገፍ እንደሚገባም አንስተዋል።
የብራዚሉ ፕሬዚዳንት ሉዊዝ ሉላ ዳሲልቫ ባሳለፍነው
ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
ዓመት በተካሄደው 37ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ተገኝተው ያስተላለፉት መልዕክት ለአፍሪካ-ብራዚልም ሆነ ለደቡብ- ደቡብ ትብብር ያነሳሳ ነበር። አፍሪካ እና ብራዚል ትግል የሚያጋራቸው ብቻ ሳይሆን ከ200 ሚሊዮን በላይ ብራዚላዊያንም መሰረታቸው አፍሪካ እንደሆነ እንደሚያምኑ ገልጸዋል። አዲሱን የብዝኀ ዓለም ጎዳና አብረን መራመድ አለብን ሲሉም ነበር ንግግራቸውን የጀመሩት። ብራዚል ከአፍሪካ ጋር በትብብር ማደግ እንደምትሻ ለዚህ ደግሞ ለሰብዓዊ ልማት የሚሆን አካታች ትምህርት ላይ የራሷን ሚና እንደምትወጣ ነው የገለጹት።
“የጋራ ፈተናዎቻችንን ለማሸነፍ አዲስ ሥርዓተ ሉል መገንባት ይገባናል። በርዕዮተ ዓለም ጎራ ላይ የተመሰረተ ሥርዓተ ዓለም ለመመለስ መሞከር በዛሬው ገሃድ ዓለም አይሰራም። የብዝኀ-ዓለም መልክ መፈጠሩ አይቀሬ ነው። አዳጊ አገራትን በማቀፍ በዓለም መድረክ ላይ ወሳኝ ድርሻ የያዘው የብሪክስ ትብብር እየገሰገሰ መሆኑ አይካድም። የታዳጊ አገራትን ተሳትፎ ሳያካትቱ በዓለም ላይ ዕድገትን፣ የአካባቢ ጥበቃን፣ ፍትሃዊነትን እና ነጻነትን ማረጋገጥ አይቻልም” ነበር ያሉት።
ቀጥለውም አሁናዊ ሉላዊ ፈተናዎችን ለመቋቋም የደቡቡ ንፍቀ ክበብ አይተኬ ሚና እንዳለው አንስተዋል። የኒዮ-ሊብራል ሥርዓት በሽታዎች የሚታከሙት በዘረኞችና የሌላ-ጠል ቀኝ ዘመሞች አለመሆኑን እና ልማትም ለጥቂቶች ብቻ የተተወ እንዳልሆነ ይልቁኑም የደቡቡን ንፍቀ ክበብ ያሳተፈ አዲስ ማኅበራዊ ውል መመስረት እንደሚያሻ ገልጸዋል። አፍሪካ ከምግብና ከኃይል ጥገኝነት ተላቃ በጤናው፣ በኢኮኖሚው መስክ ራስ-በቅ እንድትሆን ትብብር ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል። ለዚህ ደግሞ የቡድን 20 እና የብሪክስ አይነት አደረጃጀቶች ወሳኝ እንደሆኑ አንስተዋል።
“በአብዛኛው አፍሪካዊያን የሆኑ 60 አገራት ከትምህርትና ጤና ይልቅ ሐብታቸው የሚውለው ለብድር ክፍያ ነው። ይህ ደግሞ የዓለም ባንክ እና የዓለም ገንዘብ ድርጅትን የመሳሰሉ ቆሞ ቀር ተቋማት የተዛባ አሰራር እና ቀውስ አባባሽ ተፈጥሮ እንደሆነ ያመላክታል። ሚዛናዊ እና የማይከፈሉ ብድሮችን መፍትሄ ለማበጀት በባቡር፣ በመንገድ፣ በታዳሽ ኃይል መሰረተ ልማቶችን ወደ ተጨባጭ ሐብት ለመለወጥ አሻግሮ ማየት ያስፈልጋል። አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እግር በእግር መፍጠር አለብን። ሰው ሰራሽ አስተውሎት በጥቂቶች ቁጥጥር ስር ሆኖ ለሀሰተኛ መረጃ ስርጭት፣ ለሥራ አጥነት፣ ለጥላቻና መገለል ምቹ ምህዳር መፍጠር የለበትም። ያለ አፍሪካ ደቡብ ክፍለ ዓለም የለም። አፍሪካና ብራዚልን ማስተሳሰር ሲባል ታሪካዊ ቁርኝቶችን መመለስ፣ አዲስና የጋራ የሆኑ ብዝኀ- ዓለም መገንባት ማለት ነው”።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በሩሲያው የካዛን የብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ ላይ ብሪክስ ወደ ፍትሃ-ዓለም እየተጓዘ እንደሆነ እንዲህ ገልጸው ነበር።
“ወደ ግማሽ የሚጠጋውን የዓለም ሕዝብ ያቀፈው እና አንድ ሶስተኛውን የዓለም ዓመታዊ ጥቅል ምርት (GDP) በሚይዘው ብሪክስ አስገራሚ ዕድል አይቻለሁ። ብሪክስ ይበልጥ ወደ ብዝኀ መልክዓ ዓለም ለሚደረገው ጉዞ አሸጋጋሪ ኃይል ለመሆን የሚያስችል አቅም አለው። ትብብራችን የዛሬን ፈተናዎች ከመፍታት ባሻገር አካታችና ፍትሃዊ ብዝኀ ዓለም ለመገንባት መሰረት መጣል አለበት።
የአዲሱ ልማት ባንክ መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ዕውን ለማድረግ አማራጭ የፋይናንሥ ሥርዓት ይፈጥራል። ስለዚህ ብሪክስ ሚዛናዊ ብዝኀ- ዓለምን በመተግበር ልዩ አቋም እንደሚከተል እምነቴ ነው”።
የብሪክስ የብዝኀ-ዓለም አማራጭ ቅያሴዎች
ብሪክስ በምዕራባዊያን ቀጥተኛና ዕጅ አዙር ስር የሆኑ ዓለም አቀፍ ተቋማት ነፃነትን ማረጋገጥ በውትወታ ብቻ እንደማይሳካ ያመነ ይመስላል። በዚህም በዓለም ላይ አዳዲስ አተያይ ያለው የብዝኀ ምጣኔ ሐብታዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እየቀየሰ ነው።
በዚህም አዳዲስ አማራጮችን ቀይሷል። ከብሪክስ አማራጮች መካከል አንዱ የልማት ባንክ ማቋቋም ነው። የአዲስ ልማት ባንክ ምስረታ ይፋ የሆነው በ2014 (እ.አ.አ) በብራዚሏ ፎርታሌዛ በተካሄደው ጉባዔ ነው። ይህን ተቋም የዓለም ባንክ ተፎካካሪ ሁሉን አቀፍ ዓለም አቀፋዊ ተቋም ማድረግ ነው። አዲሱ ልማት ባንክ ሁሉንም አገራት ታሳቢ ያደረገ በተለይ ታዳጊ አገራትን በማቀፍ ውጤታማ ማድረግ ነው።
ሌላው የቡድን-20 አገራት በዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም እና ንግድ ሥርዓት ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያሳድጉ መደገፍ ነጻነት ያለውና ምቹ ዓለም አቀፍ የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢ መፍጠር አንዱ የብሪክስ ትኩረት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የዓለም አቀፍ የፋይናንሥ ሥርዓት የተዛባ መሆኑ አገራት ኢኮኖሚያዊ ፈተናዎችን እያስተናገዱ ስለመሆኑ ሲያብራሩ “የዓለም የኢኮኖሚ ማዕቀፍ መዛባት ለኢ-ዕኩልነት፣ ለዋጋ ንረትና ሥራ አጥነት እየዳረገ በመሆኑ ከምንጊዜውም በላይ የጋራ ጥረት ይጠይቃል። ብሪክስ ሚዛናዊ እና ብዝኀ ዓለም ሥርዓት እንዲፈጠር ይደግፋል የሚል እምነት አለኝ። በተለይ ኢትዮጵያ የመንግሥታቱ ድርጅትና እና የፀጥታው ምክር ቤት ሥርዓት የማሻሻልን ጉዳይ ልዩ ትኩረት ትሰጠዋለች። ጉዳዩ ተራ ውክልና ብቻ ሳይሆን የፍትህ፣ የእኩልነትና ሁሉም አገራት በዓለም ሥርዓት ውስጥ የሚኖራቸውን ተሳትፎ የማረጋገጥ ጉዳይ እንጂ” ሲሉ በካዛኑ የብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ ላይ ለአፍሪካ የተረፈ ድምጽ አሰምተዋል።
የዓለም ንግድ ድርጅትን ሪፎርም በተመለከተ ድርጅቱን ማሻሻል ወይም አዳዲስ አማራጭ ሥርዓትን መዘርጋት የሚል ነው። የባለብዙ ወገን ጥምረት ደግሞ የዓለም ንግድ ድርጅትን ዕውን ለማድረግ ያግዛል።
ብሪክስ ዓለም አቀፍ የብዝኀ ዓለም ቅያሴዎችን ዕውን ለማድረግ የአገራት ጥናት ኮሚቴዎች መመስረት ነው። ሁሉም አባል አገራት ትብብርን ለማጠናከር የሚሰሩ ብሔራዊ የጥናት ኮሚቴዎች እያቋቋሙ ነው። እነዚህ ተቋማት በደቡብ ንፍቀ ክበብ ሃሳብ መለዋወጥ፣ መማማር፣ ሁሉን ተጠቃሚ ያደረገ ሥርዓተ ዓለም መገንባት በመጨረሻም ብዝኀ-ዋልታ ዓለም ዕውን ማድረግ ነው።
ኢትዮጵያ በብሪክስ ማዕቀፍ
ኢትዮጵያ በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ በተካሄደው 15ኛው የብሪክስ ጉባዔ ነበር ብሪክስን የተቀላቀለችው። ይህ በዲፕሎማሲው ታሪክ ደማቅ አሻራ ያሳረፈ አጋጣሚ ነበር። አንድም ሁለንተናዊ

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
ድል ያገኘችበት፤ በአፍሪካ የሚኖራት ተዕጽኖ እና ተደማጭነቷ የሚጎላበት ዕድል የሰፋበት።
እናም ኢትዮጵያ በብሪክስ ማዕቀፍ ውስጥ ለመግባቷ አንድምታው መልከ ብዙ እንደሆነ ባለሙያዎች ሲናገሩ ይደመጣል። ለአብነትም አንድም በብሪክስ ኅብረት ውስጥ ያላት ተፈላጊነት መኖሩን፣ በሌላ በኩል በመፃዒው ዓለም ውስጥ ብሩህ ተዋናይ ለመሆን ያላትን ቁርጠኝነት የሚያጎላ መሆኑ ነው።
ኢትዮጵያ ምድረ ቀደምት፣ በጥንተ ሥልጣኔ የዳበረች፣ ቅኝ ያልተገዛች እና በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ደማቅ አሻራ ያላት አገር ናት። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዚህ ጉባዔ ተገኘተው ባደረጉት ንግግር ይህን ሃቅ አንስተዋል።
“ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት፣ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት መስራችነት ጨምሮ በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ የነበራት ተሳትፎ ወሳኝ ትርጉም ነበረው። ኢትዮጵያ በዓለም በመንግሥታቱ ድርጅት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ የነበራትን ሚና ጨምሮ በቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ዲፕሎማሲ መድረክ የነቃ ተሳትፎ ያላት አገር ናት። ስለሆነም የበለጸገ ታሪካችን፣ የዳበረ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ግንኙነታችን ብሎም ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ባለብዙ ወገን ተቋማት ተሳትፏችን ለብሪክስ ጎራ አስፈላጊነቷ ብቻ ሳይሆን በዓለም መድረክ ላይ አካታችነትና ሚዛናዊ ድምጽ ለማስተጋባት እንደሚያስችል እሙን ነው። ኢትዮጵያ በብሪክስ ማዕቀፍ ውስጥ በተባበረ ክንድ በመስራት ሁሉንም ተጠቃሚ በሚያደርግ ሥርዓት እንዲገነባ የበኩሏን ሚና ትወጣለች። ኢትዮጵያ ለባለብዙ ወገን አካታች ሥርዓት ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጣለሁ።”
በኢትዮጵያ ወጣት በሚበዛው የሰው ኃይሏ ለትብብር፣ ለፈጠራና ለሰው ኃይል አቅርቦት ወሳኝ ሚና እንዳለም እንዲሁ። ኢትዮጵያ እንደ አፍሪካ ቀንድ መገኛነቷ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጧ
አፍሪካን፣ መካከለኛው ምስራቅ እና የተቀረውን ዓለም ለማስተሳሰር ከሚኖራት ምቹ ሁኔታ አኳያ ለብሪክስ አባላት ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ሁሉን አቀፍ ትስስር የማይናቅ ሚና እንደሚኖረው አብራርተዋል። በዚህም ብሪክስ ያልተሰሙ ድምጾች እንዲሰሙ፣ የደቡብ ደቡብ ትብብር እንዲጎለበት እና የነገ የጋራ ሕልሞችን ዕውን ለማድረግ መሰረት እንደተጣለ ነው ያነሱት።
“ኢትዮጵያ ሁልጊዜም የባለብዙ ወገን ትብብር አቀንቃኝ አገር ናት። ብሪክስም ደግሞ ሚዛናዊና ዕኩልነት የሰፈነበት ብዝኀ ሥርዓተ ዓለም እንዲፈጠር ከየዓለም ማዕዘናት ሁሉ የሚስተጋቡ ድምጾችን ምላሽ ለመስጠት አንዱ ኢኒሼቲቭ ነው” ብለዋል።
በበይነ-ብሪክስ ጠንካራ ምጣኔ ሐብታዊ ትብብርን በተመለከተም በካዛኑ ጉባዔ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።
“ከሰሃራ በታች ሶስተኛዋ ግዙፍ የኢኮኖሚ ባለቤቷ ኢትዮጵያ ወጣትና ንቁ ሠራተኛ ያላት፣ የሚታረስ ሰፊ መሬት የታደለች እና በታዳሽ ኃይል ፀጋ የተሞላች ናት። እነዚህ ፀጋዎች ለኢንቨስትመንትና ንግድ አይተኬ ሚና አላቸው። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውም ለኢኮኖሚ ዕድገት አዲስ መንገድ ከፍቷል። በብሪክስ አገራት መካከል በተለይም በግብርና፣ በታዳሽ ኃይል፣ በቱሪዝም እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት ጭምር ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ ትብብር መገንባት አለብን። የብሪክስ አዲሱ ልማት ባንክም በመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች አማራጭ የፋይናንሥ ምንጭ ይሆናል ብዬ አምናለሁ”።
የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉትም የብሪክስ አባልነት በአይቀሬው የአዲስ ሥርዓተ ሉል ውሳኝ የጋራ ጥቅምን ለማረጋገጥ ፋይዳው ጉልህ ነው። እንደ ቡድን ብቻም ሳይሆን ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባላት ጋር ያላት ትብብር፣ ታሪካዊ ወዳጅነትና የነገ ተስፋ ይበል የሚያሰኝ ነው።
ኢትዮጵያ እና የብሪክስ አባላት
የኢትዮጵያ የባለ ብዙ ወገንና የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲ እመርታ እያሳየ መምጣቱ እሙን ነው። ኢትዮጵያ በብሪክስ ማዕቀፍ ውስጥ መቀላቀሏም ከአባል አገራቱ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ሁሉን አቀፍ ትብብርና አጋርነት ለማጎልበት ያግዛታል። በተለይም ከአባል አገራቱ ጋር ያላት ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ጠንካራ ቁርጠኝት በዓለም አቀፍ ትብብር ዘርፍም ይበልጥ ለማጎልበት እንደሚያስችል ይታመናል።
ኢትዮ ሩሲያ፡-
የኢትዮ-ሩሲያ ወዳጅነት ታሪካዊ ተብሎ የሚገለጽ ብቻ አይደለም። የክፉ ቀን ወዳጅ “A friend in need is a friend indeed” ይሉት የነጮች አባባል የሚገልጸው እንጂ። በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኤቭጌኒ ተርክሂን ብዙ ጊዜ የሁለቱን አገራት ወዳጅነት “የመንፈስ መተሳሰር” ሲሉ ይገልጹታል። በታላቁ አሌክሳንደር ፑሽኪን ደም የተሳሰሩ ብቻ ሳይሆን በየዘመኑ የነበራቸው ወዳጅነትና መተሳሰብ በተግባር የተገለጠ ነው።
ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው 126 ዓመታትን አስቆጥሯል። የሚያመሳስላቸው ታሪካዊ ዑደትም ያላቸው ሁለቱ አገራት ኢትዮጵያ ፋሺዝምን ስታሸንፍ፣ ሩሲያ ናዚዝምን ድል ነስታለች። ሩስያ በአፍሪካ ውስጥ ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመረችው ከኢትዮጵያ ጋር ነው። በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ለመጀመሪያ ጊዜ ኤምባሲ የከፈተችው አዲስ አበባ
ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
ውስጥ ነው። ለሩሲያና አፍሪካ ቀጣይነት ያለው ያለው ትብብርና ግንኙነትም የኢትዮጵያ ሚና ከፍተኛ ነው።
ሩሲያ እና ሩሲያዊያን ለኢትዮጵያ በበጎም፣ በክፉም ዘመናት ውለታ ውለዋል። ከአንድ ምዕተ ዓመታት በፊት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ለሩሲያው ንጉስ (ጻር) ዳግማዊ ኒኮላስ በፃፉት ደብዳቤ “ኢትዮጵያ ከእግዚአብሔር እና ከሞስኮ መንግሥት በቀር ሁነኛ ወዳጅ የላትም” ያሉትም የሁለቱን አገራት ዕውነተኛ ወዳጅነት በቅጡ ይገልጣል። በአድዋ ጦርነት አይተኬ ሚና የተጫወተውን የሩሲያን ቀይ መስቀል ድጋፍ ጨምሮ ሩሲያ በየዘመናቱ ኢትዮጵያ የሉዓላዊነት ስጋትና ዓለም አቀፍ ጫና ሲጋረጥባት ከጎኗ ነበረች። በሶቪየት ዩኒየን ዘመንም ከ20 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ነጻ የትምህርት ዕድል አግኝተው ተምረው ተመልሰዋል። በኢትዮጵያ የጤናና የትምህርት ተቋማት እንዲስፋፉ ውሳኝ ሚና ተጫውታለች። በመንግሥታቱ ድርጅት የነበሩ ፀረ-ኢትዮጵያ ውሳኔዎችን በመቃወምም ሩስያ ወሳኝ ውለታ ነበራት።
የኢትዮ-ሩሲያ የባሕል፣ የፖለቲካ፣ የታሪክና የዲፕሎማሲ ወዳጅነት ጥልቅና ታሪካዊ ቢሆንም በኢኮኖሚው መስክ ያላቸውን አቅም ግን በቅጡ እንዳልተጠቀሙ ይወሳል። ባለፉት ቅርብ ዓመታት ግን ይህን ዕድል በቅጡ ለመጠቀም በቁጭት የተነሱ ይመስላል። አሁናዊ የኢትዮ-ሩሲያ ወዳጅነትና ትብብር ከፖለቲካ ወደ ኢኮኖሚም ተሸጋግሯል። የብሪክስ ማዕቀፍ ደግሞ ሌላ መሰረት ጥሏል። ይህ በሁለቱ አገራት መሪዎችም ተረጋግጧል። ሁለቱ አገራት በኢነርጂ፣ በኢንፎርሜሽን ደህንነት፣ በአየር ትራፊክ፣ በኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂዎችና በአቶሚክ ኢነርጂ አጠቃቀም ረገድ ስምምነቶችን አድርገዋል።
ኢትዮ-ቻይና፡-
የኢትዮ-ቻይና ኢ-መደበኛ ግንኙነት ሺህ ዘመናትን ቢያስቆጥርም ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነታቸው በ196ዎቹ የጀመረ ነው። ይኸውም ቀዳሚ አፄ ኃይለሥላሴ እና ማኦ ዚዶንግ ዘመን ሁለቱ አገራት ወዳጅነታቸውን በተለያዩ ማዕቀፎች አጠናክረዋል። የቻይና ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ግንኙነትና ኢኮኖሚያዊ ትብብር ባለፈው ግማሽ ምዕተ ዓመት ውስጥ እየጎለበተ የመጣ ነው። በሂደትም የአገራቱ ግንኙነት ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት አድጓል። በንግድ፣ በኢንቨስመንት፣ በብድርና ድጋፍ፣ በትምህርትና በሌሎችም ዘርፎች ያላቸው ትብብር ከየትኛውም አገር በበለጠ መሰረት ያለው ነው። ዲፕሎማቲክ ትብብራቸው ለሕዝብ ለሕዝብ ትስስር፣ ለኢኮኖሚ ትብብርና ዓለም አቀፍ አጋርነት በጅቷል።
ኢትዮጵያ እንደ አፍሪካ ማዕከልነቷ በቻይና በኩል ልዩ ስፍራ የሚሰጣት ናት። በቅርቡ ደግሞ የኢትዮ- ቻይና ግንኙነት በሁሉም ሁኔታዎች ወደማይቀያየር ስትራቴጂካዊ አጋርነት (All-Weather Strategic Cooperation Partnership) ተለውጣል። የብሪክስ ማዕቀፍ ደግሞ ለዚህ ተጨማሪ ዕድልና አጋጣሚ ነው።
ኢትዮ-ብራዚል፡-
የሁለቱ አገራት ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በፈረንጆቹ አቆጣጠር 1951 የተመሰረተ ሲሆን በ1960 ሁለቱም አገራት ኤምባሲዎቻቸውን ከፍተዋል። አጼ ኃይለሥላሴ ለይፋዊ ጉብኝት ወደ ብራዚል ባቀኑበት በ1953 ዓ.ም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ መደረጉን ተከትሎ ለዓመታት ኤምባሲያቸውን ዘግተው ቢቆዩም የሁለቱ አገራት ትብብር ግን እያደገ
መጥቷል። ብራዚል በአፍሪካ ሕብረት ቋሚ ታዛቢም ናት። በግብርና፣ በታዳሽ ኃይል፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በትምህርትና በማኅበራዊ ልማት መስኮች ትብብር ማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራት ተከናውነዋል። ከስድስት ዓመታት በፊትም ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማዳበር የሚያስችል ፖለቲካዊ ምክከር ያደረጉ ሲሆን በግብርና ዘርፍ የጋራ ፕሮጀክቶች ገቢራዊ ተደርገዋል። የብራዚሉ ፕሬዚዳንት በሚያዝያ 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት መድረጋቸውን ተከትሎም ትብብሩ ይበልጥ እያደገ መጥቷል። ሁለቱ አገራት በብሪክስ ማዕቀፍ ስር መሆናቸው ለሁለትዮሽም ሆነ ለደቡብ ደቡብ ትብብር መጎልበት ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል።
ኢትዮ-ደቡብ አፍሪካ፡-
ሁለቱ አገራት በተለይም በፓን አፍሪካ መንፈስ የሚተሳሰሩ የረጅም ጊዜ ወዳጆች ናቸው። የአድዋ ባለድሏ ኢትዮጵያ የዘር ተኮሩ አፓርታይድ ሥርዓት ትግል ንቅናቄ ምሣሌ ነበረች። ኔልሰን ማንዴላን ጨምሮ ለታጋዮች ሥልጠና ሰጥታለች። አገሪቷ ነጻ እንደወጣችም ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን አጠናክራለች። ይህም በሂደት የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርና ወዳጅነት አጎልብቷል። በፈረንጆቹ ሰኔ 1996 ኢትዮጵያ ኤምባሲዋን ፕሪቶሪያ ላይ ከፍታለች። የሁለትዮሽ ግንኙነቱ በመጎልበቱ በመጋቢት 2004 (እ.አ.አ) የኢትዮ-ደቡብ አፍሪካ ሁሉን አቀፍ ትብብር ማዕቀፍን ተፈራርመዋል። በፓን አፍሪቃዊነት እና ወንድማማችነት መንፈስ የተጀመረው ትብብር ወደ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት አደገ። በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በኢንዱስትሪ ከፍተኛ የሚኒስትሮች ስምምነትን ጨምሮ በርካታ የመግባቢያ ሰነድ ስምምነቶች ተፈራረመዋል።
ደቡፍ አፍሪካ በአፍሪካ በኢንዱስትሪ የበለጸገች አገር ስትሆን ኢትዮጵያም በተፈጥሮ ጸጋዎች የታደለችና የአፍሪካ ፖለቲካዊ ማዕከል ናት። በአፍሪካ ጉልህ ተጽዕኖ ያላቸው አገራቱ በሁለትዮሽም ሆነ በብሪክስ የነበራቸውን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትብብር ይበልጥ እንደሚያልቁት ያታመናል።
ኢትዮጵያ ከነባር የብሪክስ አባላት ብቻ ሳይሆን ከአብዛኞቹ አዳዲስ የብሪክስ አቻዎቿ ጋር ያላት ግንኙነት እየዳረበ መጥቷል። ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ጋር ያላት ወዳጅነት ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት እያደገ መጥቷል። መልከ ብዙ የትብብር ማዕቀፎች ወደ ገቢር ተለውጠው ከፍተኛ ምጣኔ ሐብታዊ እመርታ እንዲያመጡ አስችሏል። የኢትዮጵያና የሳዑዲ ዓረቢያ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት እየዳበረ የመጣ ሲሆን ኢትዮ- ኢራን ግንኙነትም ትልቅ ተስፋ ያለውና እየተሻሻለ የመጣ ነው። ስለዚህ ብሪክስ ተጨማሪ አቅም ነው።
በሌላ በኩል ብሪክስ ታሪካዊ ባላንጣ አገራት እንዲቀራረቡ ዕድል አመቻችቷል። ለምሣሌ በታሪክ የሚጠቀሰው የሕንድ እና የቻይና ባላንጣነት ወደ መቀራረብ እንዲመጣ አስችሏል። ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው ኢትዮጵያና ግብፅም በውሃ ፖለቲካ መነታረኮች ቢቀጥሉም ብሪክስ ሁለቱ አገራት ከፉክክር ወደ ትብብር እንዲመጡ የሚያስችል እንጂ የሚያቃቅር አይሆንም።
ነገረ-ብሪክስን ስናጠቃልለው ኢትዮጵያ በብሪክስ ማዕቀፍ መግባቷ ከምዕራቡ ወይም ከምስራቅ የመወገን ሳይሆን የሁሉንም ወገን ወዳጅነትና የጋራ ጥቅምን መሰረት ያደረገ ነው።
ያቆየን!
ፖለቲካ

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
ዲፕሎማሲያችን . . .

በዓለም መኩሪያ
መግቢያ
በዓለም አቀፍ ግንኙነት መስክ የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ብዙ ክስተቶችን ላስተናገደው ለሃያኛው ክፍለ ዘመን አንዳንድ ጉዳዮችን ፍጻሜ ያሰጠ ሲሆን ሌሎች አዳዲስ ክስተቶችም እንዲፈጠሩ አድርጓል። የሁለት ዋልታ ዓለም ለአጭር ጊዜም ቢሆን ቀርቶ የአንድ ዋልታ የበላይነት የክፍለ ዘመኑ መልክ መስሎ የተከሰተ ቢሆንም በአጭር ጊዜ ሁኔታው መሰረታዊ ለውጥ አሳይቷል። ቻይና በ1978 በጀመረችው የሪፎርም አብዮት በአጭር ጊዜ በኢኮኖሚም ሆነ በዲፕሎማሲ አቅሟ ፈርጥማ መውጣት ስትጀምር ከሶቪየት ኅብረት ፍርስራሽ የወጣችው ሩሲያ በአጭር ጊዜ ወደ ማንሰራራት
ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
መጥታለች። ሕንድ፣ ብራዚል፣ ቱርክ እና ሌሎችም አገራት የተጽዕኖ አድማሳቸውን ማሳደግ የጀመሩት በክፍለ ዘመኑ መባቻ ውስን ዓመታት ውስጥ ነበር። ይህም ሌላ አይነት መልክ ያለው ዓለማዊ ሁኔታን ፈጥሯል።
በዓለም አቀፍ ትስስር ምክንያት ዕድገቱና ተጽዕኖው በአጭር ጊዜ የጎመራው የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ በዓለም አቀፍ መድረክ ፈርጣማ ጡንቻ ያላቸው የቴክኖሎጂ ተቋማት መንግሥታዊ ያልሆኑ ተዋንያን (non-state ac- tors) ሆነው እንዲወጡ አድርጓቸዋል። እነዚህ ተቋማት የመረጃ ፍሰትን በማሳለጥ፣ ግንኙነትን በማቃለልና ሕይወትን የተሻለ በማድረግ ረገድ ያላቸው አዎንታዊ ሚና እንደተጠበቀ ሆኖ መንግሥታት ላይ የሚነሱ አመጾች መናኸሪያ፣ የሐሰት መረጃ መሰራጫ በመሆን የነበራቸው ሚናም ከፍተኛ ነው። አብዛኞቹ ተቋማት በአንድ አገር ባለቤትነት የሚተዳደሩ በመሆናቸው በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የዚያች አገር ፖሊሲ ማስፈጸሚያ መሣሪያዎች መሆናቸው አልቀረም።
በአገራችን ለውጥ የመጣበት ወቅት በዓለም መድረክ የነበረው የዓለም አቀፍ ግንኙነት መልኩ አዳዲስ ክስተቶች የሚስተዋልበት ጊዜ ነበር። ቁልፍ ወደቦችን፣ ጠባብ መተላለፊያ ሰርጦችንና ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን አካባቢዎች ለመቆጣጠር የሚደረገው ዓለም አቀፋዊና ቀጣናዊ ፉክክር የጋለበት ነበር። ፉክክሩ በሁሉም አካባቢዎች ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበትና አካባቢያዊ የበላይነትን ለመቆጣጠር የሚደረጉ ፉክክሮች ጫፍ የደረሱበት ጊዜም ነበር። ይህም በተለምዶ በሚታወቁት ዓለም አቀፋዊ ልዕለ ኃያላን ብቻ ሳይሆን ቀጣናዊ ‘አለቃዎችንም’ ጭምር ያሳተፈ ነው።
ዓለምን በማስተሳሰር የጊዜና የቦታ ልዩነትን ያጠፉት ማኅበራዊ ሚዲያዎች በአገራት አመጽ ማቀጣጠያ መሣሪያ አልያም በምርጫ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ መሆን ችለው ነበር። በማኅበራዊ ሚዲያ የሐሰት መረጃዎች እና ድኅረ እውነት እንዲሁም የምርጫ ዘመቻን በተለየ መልኩ ተጽዕኖ በሚያሳድሩ የአልጎሪዝም ስሪቶች ትርጉም ያለው ልዩነት እየፈጠሩ ነበር። “የዓረብ ፀደይ አብዮቶች” በሚል ጥቅል መጠሪያ በሚታወቁት በሰሜን አፍሪካ እና መካከለኛው ምስራቅ አገራት በሥልጣን ላይ ያሉ መንግሥታትን አቅም የሚገዳደር አቅም ለተቃዋሚዎች በማበርከት የሥርዓት ለውጥ ያስከተሉት እነዚህ ማኅበራዊ ሚዲያዎች በአሜሪካ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እና በእንግሊዝ ከአውሮፓ ኅብረት የመውጣቱ ሕዝበ ውሳኔ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድረው ነበር።
ከዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችም በተጨማሪ አህጉራዊና ቀጣናዊ ሁኔታዎችን ብንመለከት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም አንጻር በርካታ ፋይዳ ያላቸው ዕድገቶች የሚስተዋሉበት ጊዜ ነበር። ከስዊዝ ቦይ እስከ ሞምባሳ ወደብ ባለው ረጅም የቀይ ባሕር፣ የኤደን ባሕረ ሰላጤ እና የሕንድ ውቅያኖስ ጠረፍ ላይ በርከታ አገራት የተለያየ መጠን ያላቸው የጦር ሠፈሮችን መስርተዋል። በተፈጥሮ ሀብት (በተለይ ውሃ) ላይ ያተኮረው ዲፕሎማሲያዊ ግብግብ ከዚህ አኳያ አንዱ መሰረታዊ ጉዳይ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ አገራት በሚነሱ የጽንፈኝነትና የመጤ ጠልነት አስተሳሰቦች

ምክንያት ኢትዮጵያዊያን በመካከለኛው ምስራቅ በአፍሪካ እንዲሁም በሌሎች አገራት ቀጥተኛ የሰብዓዊ መብት ገፈፋ ሲደረግባቸው እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። ትውልደ ኢትዮጵያዊው ደግሞ በአኩራፊነትና በመገለል ስሜት ከአገራዊ ጉዳዮች ወይ ተነጥሎ ወይንም ደግሞ ጽንፍ በመያዝ ልማታዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎችን ከመደገፍ ይልቅ ሁሉንም ነገር በፖለቲካ ብቻ በማየት ዋልታ ረገጥ አቋም የያዘበት ጊዜ ነበር። በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልድ ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው ጉዳይ ንቁ ተሳታፊ የሚሆኑበት አልያም ደግሞ አቋም ይዘው የሚቆሙባቸው መንገዶች በጊዜው አልተስተዋሉም።
በዚህ ዓለማዊ አውድ ውስጥ ሆኖ ሉዓላዊነት እና ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስጠብቅ እንዲሁም አገራዊ ክብርን የሚያስከብር የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ
ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
ለመንደፍ በጣም አስፈላጊ ከሆኑ ነገሮች መካከል ጥንቁቅ፣ ንቁና ዝግጁ የሆነ፣ ሁኔታዎችን በቅርበት እየተከታተለ ምላሽ መስጠት የሚያስችል የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መፍጠር እጅግ በጣም አስፈላጊ ሆኗል። በመሆኑም በለውጡ ማግስት ከተደረጉ ሪፎርሞች አንዱ የውጭ ግንኙነት እሳቤን ከመደመር እሳቤ አንጻር በመቃኘት አዲስ እይታና ስትራቴጂ መንደፍ ነበር።
የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ክለሳ
የመደመር የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ይህንን ነባራዊ ሁኔታና እውነታ በመገንዘብ ወቅቱን የሚመጥን፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና አገራዊ ክብር የሚያስጠብቅ የፖሊሲ አማራጭ መከተል በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ወደ ስራ ገብቷል። ከለውጡ በፊት የነበረው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ከ18 ዓመት በላይ ያገለገለ በመሆኑ በርካታ ጠንካራ ጎኖች ቢኖሩትም ለወቅቱ ነባራዊ ሁኔታ የማይመጥን በመሆኑ መታደሱ በጣም አስፈላጊ ነበር። የውጭ ግንኙነት ፖሊሲው ከይዘትና ከቅርጽ አንፃር በርካታ ውስንነቶች የነበሩት መሆኑን በመገምገም የፖሊሲውን ጥንካሬዎች የበለጠ የሚያጠናክርና አዳዲስ እይታዎችን የሚጨምር የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂ መንደፍ አስፈላጊ ሆኗል።
ከይዘት አንጻር ፖሊሲው በዕድሜ መርዘም ምክንያት ከወቅቱ ጋር ሊሻሻሉ የሚገባቸው በርካታ ጉዳዮች ነበሩት። ለአብነት ያህል በፖለሲው ውስጥ ሰፊ ክፍል የያዘው ሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን) ይጠቅመናል ወይስ ይጎዳናል የሚል ሙግትና እንዴት እንቅረበው የሚሉ ስልቶች ዝርዝር ነው። ይህ ፖለሲው በረቀቀበት ወቅት ትክክል የነበረ ቢሆንም በለውጡ ወቅት ግን ጊዜው ያለፈበት ሙግት ነበር። ግሎባላይዜሽን “እንግባ/አንግባ” የሚል ክርክር የሚነሳበት ጉዳይ ከመሆን አልፎ ዓለማዊ ነባራዊ ሁኔታ ወደመሆን ተሸጋግሯል። ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ የሳይበር ደህንነት እና የሳይበር ምህዳር አስተዳደርን የመሳሰሉ አዳዲስ ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ፋይዳቸው ከፍ ብሎ መጥቷል። ሌሎች ከይዘት አንጻር ሊነሱ ከሚችሉ ጉዳዮች መካከል የደቡብ ሱዳን እንደ አገር ራሷን መቻል፣ የቻይና ፖሊሲው ሲወጣ ከነበረችበት በሰፊ ርቀት ላይ ባለ ሁኔታ መገኘት፣ እንደ ተርኪዬ የመሳሰሉ አገራት ሚና ማደግ ሊጠቀሱ ይችላሉ።
ከቅርጽ አንጻርም ፖለሲው ክፍተቶች ነበሩበት። ከዚህም ውስጥ ዋነኛው አገራትን የሚፈርጅ መሆኑና ለሕዝብ በሚወጣ ሰነድ ጥቅም ላይ ሊውሉ የማይገባቸው ኢ-ዲፕሎማሲያዊ አገላለጾችን ጭምር የያዘ መሆኑ ነው። በመሆኑም ፈጣን ማሻሻያዎችን በመውሰድ የፍልስፍናና ተግባር ቅኝት መውሰድ አንገብጋቢ በመሆኑ በፍጥነት ወደ ስራ ተገብቷል። በዚህም ባለፉት ስድስት ዓመታት በርካታ ውጤቶች ተመዝግበዋል። ከእነዚህም ውስጥ ዋና ዋናዎቹ እንደሚከተለው ቀርበዋል።
ከተሽኮርማሚነት ወደ ተጽዕኖ ፈጣሪነት መሻገር
ኢትዮጵያ በውጭ ግንኙነት መስክ ብዙ የካበተ ወረት ያላት አገር ናት። በጸረ ቅኝ ግዛት ትግል የራሷን ነፃነት ከማስከበር በላይ ሌሎች አፍሪካዊያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ያደረጉትን የጸረ ቅኝ ግዛት ተጋድሎ አቅሟ በቻለው ሁሉ ደግፋለች። በዓለም አቀፍ መድረኮች የመንግሥታቱ ማኅበር ብቸኛዋ አፍሪካዊት አባል አገር ከመሆን ጀምሮ
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መስራች በመሆን በበርካታ ድርጅቶች መስራች አልያም ቀዳሚ አባል አገራት መካከል ትገኛለች። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረት ከፍተኛውን ድርሻ በመወጣት የድርጅቱ መቀመጫ መሆን የቻለች አገር ናት። የበርካታ ዓለም አቀፍ ሰነዶች፣ ስምምነቶችና ኮንቬንሽኖች ከመጀመሪያ ፈራሚዎች መካከል ነች። በሰላም ማስከበር ግንባር ቀደም ተጠቃሽ የሆነው መከላከያ ሠራዊቷ በብዙ አገራት ተሰማርቶ ሕዝባዊ ወገንተኝነቱን በተግባር መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር አሳይቷል። ከዚህ በተጨማሪ በሁሉም አቅጣጫዎች ወደ ሁሉም አገራት ሊባል በሚችል ደረጃ የሚበር ሰንደቅ ዓላማዋን ከፍ አድረጎ የሚጓዝ ስኬታማ አየር መንገድ አላት።
ይህን ሁሉ ስኬት የተጎናጸፈችው አገራችን የውጭ ግንኙነት ዋነኛ መገለጫዋ የነበረው ግን “ተሽኮርማሚነት” ነው። ይህም ፍላጎትን አንጥሮ፣ አጀንዳ አስመዝግቦ በየአደባባዩና በየኮሪደሩ ሃሳብን ከማስረዳትና ተጽዕኖ ከመፍጠር ይልቅ የሚቃጡ አጀንዳዎች ላይ ምላሽ በመስጠትና “በምን ይሉኝ” የሚገለጽ ነበር። ይህንን በመቀልበስ ፍላጎትን ደፈር ብሎ በመግለጽ ረገድ የሕዳሴው ግድብ ድርድር ጥሩ መነሻ ሲሆን ይበልጥ የተገለጸው ግን በባሕር በር ጥያቄ ነው። “መቶ ሃያ ሚሊዮን ሕዝብ ይዘን ታሽጎብን ልንኖር ሊፈረድብን አይገባም፤ የባሕር በር ያስፈልገናል” የሚለው ሃሳብ ሲነሳ ለሁሉም ሰው ያልተጠበቀ የሆነውም ለዚያ ነው። ጥያቄውን ማንሳት ብቻ ሳይሆን በተከታታይነትና በግለት በመስራት አሁን ጥያቄው በዓለም አቀፍ መድረክ ተቀባይነት እንዲኖረው ማድረግ ተችሏል። “እንዴት የባሕር በር ያስፈልገናል የሚል ጥያቄ ታነሳላችሁ?” ከሚለው “እንዴት ይሳካ የሚለው ላይ እንነጋገር እንጂ እንደሚያስፈልጋችሁ እሙን ነው” ወደሚለው ተቀይሯል። የባሕር በር ጥያቄን ማንሳት እንኳን በተቀረው የዓለም ክፍል በአገር ውስጥም የሚያስወግር ጥያቄ የነበረ ቢሆንም ጉዳዩን ፈርጠም ብሎ በማንሳት ብዙ አማራጮችን መፍጠር ተችሏል። በተለይ የአንካራው ስምምነት ኢትዮጵያ “ዘላቂ፣ አስተማማኝ እና የተረጋገጠ” የባሕር በር እንደሚያስፈልጋትና ይህንንም እውን ለማድረግ ሶማሊያ መስማማቷን ያጸና ሰነድ ነው።
ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ
ለውጡ በውጭ ግንኙነት ረገድ ካመጣቸው ዐበይት ልዩነቶች መካከል አንዱ ዜጋ ተኮር ዲፕሎሲን ማስተዋወቁ ነው። ይህም በሁለት መልኩ ይገለጻል። የመጀመሪያው ዜጎች ባሉበት አገር ሁሉ ሠብዓዊ መብታቸው ተከብሮ እንዲኖሩ ማድረግ ነው። ይህም ዜጎች ለስራ ወደ ውጭ አገር ከመሄዳቸው በፊት አስፈላጊውን ሥልጠና ወስደውና በሥራ ስምምነት ማዕቀፍ እንዲሄዱ ማድረግ፣ ከሄዱም በኋላ በተለያየ ምክንያት የሚደርስባቸውን ጫና እና እንግልት መፍታት የኤምባሲዎች ዋነኛ ተልዕኮ እንዲሆን ማድረግ ነው። ይህም ሆኖ መብታቸው የሚጣስ ከሆነ ወደ አገራቸው የሚመለሱበትን መንገድ ማገዝ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በዚህ ጉዳይ ላይ የቃልና የፖሊሲ መመሪያ ብቻ ሳይሆን የተግባር ዓርአያነትም በማሳየት ለጉዳዩ ያላቸውን ትኩረትና ክብደት አሳይተዋል። በለውጡ ማግስት በግብጽ በነበራቸው ቆይታ በእስር ላይ የነበሩ ኢትዮጵያዊያንን በተሳፈሩበት አውሮፕላን ይዘው በመምጣት ተደርጎ የማያውቅ የተግባር ዓርአያነት

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
አሳይተዋል። በመቀጠልም በኳታር በነበራቸው የስራ ጉብኝት በሕክምና ስህተት ልጇ ኮማ ውስጥ ገብቶ ለበርካታ ዓመታት ልጇን በሆስፒታል ስታስታምም የነበረች እናት ፍትህ እንድታገኝና የልጇን ሕክምና በአገሯ ማስቀጠል እንድትችል አድርገዋል። በ2010 ዓ.ም መጨረሻ ከአምባሳደሮች ጋር በነበራቸው ቆይታም “ኤምባሲዎቻችን ዜጎቻችን ሲደሰቱም ሆነ ሲያዝኑ የሚሰባሰቡበት ካልሆነ ትልቅ ጉድለት ነው” በማለት ለጉዳዩ አጽንዖት ሰጥተዋል።
በዚህም ምክንያት ጉዳዩ የውጭ ግንኙነት አንድ የትኩረት አቅጣጫ በመሆኑ የዜጎችን ደህንነትና መብት ለማስከበር ሚሲዮኖቻችን ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው ተሰማርተዋል። በሳዑዲ ዓረቢያ እና በሌሎችም የመካከለኛው ምስራቅ አገራት በእስር ላይ የነበሩ ዜጎች ጉዳያቸው ተጣርቶ በአገራቱ መቀጠል የማይችሉት ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ ተደርገዋል። በታንዛኒያ፣ ዛምቢያ እና ሌሎችም የደቡባዊ አፍሪካ አገራት በእንግልት ላይ የነበሩ ዜጎች ተለቀው ወደ አገራቸው እንዲገቡ ማድረግ ተችሏል።
በአጠቃላይ ባለፉት ስድስት ዓመታት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ዜጎች ከእስርና እንግልት ተፈትተው ወደ አገራቸው በሰላም እንዲገቡ ማድረግ ተችሏል። ይህም በአመቺ ጊዜ ብቻ ሳይሆን የኮቪድ ወረርሽኝ በነበረባቸው አስጨናቂ ወራት ጭምር የተደረገ ነው። በወቅቱ ወደ መቶ ሺህ የሚገመቱ በሳዑዲ ማጎሪያ ጣቢያ የነበሩ ዜጎቻችንን በአጭር ጊዜ ወደ አገራቸው ማምጣት ተችሏል።
ሚዛናዊ የውጭ ግንኙነት እይታ
ሌላው የውጭ ግንኙነት ስኬት ሚዛናዊ የውጭ ግንኙነት እይታ መፍጠር ነው። በአጠቃላይ
ከመደመር መርሆዎች ውስጥ አንደኛው ሚዛናዊነት እንደሆነ ይታወቃል። ይህም ፍጹም ተቃራኒ ከሚመስሉ ጉዳዮችና እይታዎች ጠቃሚውን ብቻ ነቅሶ በመውሰድ ከሁለቱም ነጠላ እይታዎች የተሻለ እይታ መፍጠር ነው። መደመር በውጭ ጉዳይ መስክ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ሚዛናዊ እይታን ያራምዳል። ይህን በሚያደርግበትም ጊዜ የሚዛናዊ እይታው ማስጠበቂያ ካስማዎች ሉዓላዊነት እና ብሔራዊ ጥቅም ናቸው። እነዚህን ሁለት ጉዳዮች እንደ መልህቅ በመጠቀም ማንኛውም ጉዳይ ላይ ጽንፍ የረገጠ አቋም ሳይያዝ ከሁሉም የተሻለውን ለመጠቀም ይሞክራል። ይህንን የመደመር የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ሚዛናዊነት ለማሳየት ሦስት አብነቶችን መጥቀስ ይቻላል።
የመጀመሪያው የዓለም አቀፍ መድረክን የሚመለከትበት መነጽር ነው። እንደሚታወቀው የዓለም አቀፍ መድረክን በሚመለከት እውናዊ (ሪያሊስት) እና ሃሳባዊ (አይዲያሊስት) የሚባሉ ሁለት ዐበይት እይታዎች አሉ። በእውናዊ እይታ መሰረት ዓለም የፉክክር መድረክ በመሆኗ አገራት ራሳቸውን በወታደራዊና በኢኮኖሚያዊ መስኮች አፈርጥመው ካልወጡ በስተቀር መጨረሻቸው ህልውናቸውን ማጣት ነው ብሎ ያምናል። የአገራት ግንኙነት በመሰረቱ የሀብትና የተጽዕኖ ቅርምት ስለሆነ ጠንካራ ጡንቻ ያልያዘ ወይም ጠንካራ ጡንቻ ካለው ያልተጠጋ በዓለም አቀፍ ሕግጋትና መርሆዎች ተማምኖ ሊኖር አይችልም ይላል። ሃሳባዊ እይታ በበኩሉ አገራት ከእሽቅድምድም ይልቅ በትብብር ቢሰሩ የሚያተርፉት ብዙ እንደሆነ በማስገንዘብ ጡንቻ ከማፈርጠም ይልቅ የትብብር መስኮችን ማስፋት፣ ዓለም አቀፍ የግጭት አስወጋጅ ተቋማትና መርሆዎችን ማጠናከር ላይ ሊያተኩሩ እንደሚገባ ያሳስባል።
መደመር የሁለቱን እይታዎች፣ ፉክክር እና ትብብርን ሚዛን ማስጠበቅ ከሚለው አጠቃላይ መርሁ ጋር በማስተሳሰር ይመለከተዋል። በዚህም ለዘላቂ የሰው ልጆች ዕድገት ትብብርም ሆነ ፉክክር አስፈላጊ መሆናቸውንና በሚዛናቸው ከተያዙ ጠቃሚ መሆናቸውን ያስቀምጣል። በመሆኑም ለትብብርና ለጋራ ማደግ ያለስስት መስራትና ተቋማትን የማጠናከር ሂደት ላይ የድርሻችንን መወጣት እንዳለ ሆኖ ከዚህ ያፈነገጡ ክስተቶች በብሔራዊ ደህንነትና ሉዓላዊነት ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ደግሞ ራስን የመከላከል አቅም ላይ በርትቶ መስራት እንደሚገባ ያምናል። በዚህ ረገድ ባለፉት ስድስት ዓመታት በሁለቱም መስኮች በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል ውጤቶችም ተመዝግበዋል’።
ሁለተኛው መደመር ሚዛን መጠበቅ እንደሚያስፈልግ የሚያራምደው አቋም ማሳያ ብሔራዊ ኃይል ግንባታ ላይ ያለው እይታ ነው። የብሔራዊ ኃይል (አቅም) ማሳያዎች ሁለት ሲሆኑ እነሱም ገር ኃይል (ሶፍት ፓወር) እና ጠጣር ኃይል (ሃርድ ፓወር) ናቸው። ገር ኃይል ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን በመጠቀም ያለ ከባድ ኢንቨስትመንት ተጽዕኖ የማሳደር ሂደት ነው። ለዚህም የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶች፣ ኪነ-ጥበብ፣ ዳያስፖራና ሌሎችም ተሰሚነት ያላቸው አካላት ተሳትፎ ከፍተኛ ድርሻ አለው። ጠጣር ኃይል የሚባለው ደግሞ በወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ አቅም የሚገለጽ አቅም ነው።
ባለፉት ስድስት ዓመታት በሁለቱም መስኮች
ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
በርካታ ሥራዎችን በመሥራት ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል። የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን ማጠናከር፣ ጎረቤቶችን የማሸማገልና እርቅ እንዲወርድ ውጤታማ ሥራ መስራት፣ ዳያስፖራ (ትውልደ ኢትዮጵያ እና ሁለተኛ ትውልድ ዳያስፖራዎችን) በአገራቸው ጉዳይ ንቁ ተሳታፊ ማድረግ እንዲሁም የቱሪዝም መዳረሻዎችን ማስፋትና ማስተዋወቅ በዚህ መልኩ ሊታዩ የሚችሉ ስኬቶች ናቸው። በጠጣር ኃይል ረገድም መከላከያ ላይ የተሰሩ በርካታ ኢንቨስትመንቶች እና የተገኙ ውጤቶች ማሳያዎች ናቸው። የነበሩትን የምድር እና የአየር ኃይሎች በከፍተኛ ሁኔታ ከማጠናከር በተጨማሪ የባሕር ኃይል እና የሳይበር ኃይል የተጨመረለት የመከላከያ ሠራዊታችን በሁሉም መስክ የተጠናከረና ውጤታማ መሆን ችሏል።
ብሪክስን መቀላቀል
ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ ካለፉት ስድስት ዓመታት ስኬቶች አንደኛው ነው። ብሪክስ በመጀመሪያ በቻይና፣ ሕንድ፣ ሩሲያ እና ብራዚል የተመሰረተና ኋላ ላይ ደቡብ አፍሪካን የጨመረ ጥምረት ነው። ጥምረቱ “ደቡባዊ ንፍቀ ክበብ” በመባል የሚታወቀው የዓለም ክፍል በኢኮኖሚና በዲፕሎማሲ ተሰሚ እንዲሆን የተቋቋመ መድረክ ነው። ጥምረቱ ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማትን ለመተካት አልያም ለማፍረስ ሳይሆን በእነዚህ ተቋማት ውስጥ የምዕራባዊያን አገራት ያላቸውን ያልተገራና ያልተመጣጠነ ተጽዕኖ ለመገዳደር የተመሰረተ ነው።
ኢትዮጵያ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ መካተቷ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ይኖሩታል። የመጀመሪያው ከአባል አገራቱ ጋር ያለን የሁለትዮሽ ግንኙነት መጠናከር ነው። ቻይና እና ኢትዮጵያ ስትራቴጂያዊ ወዳጅነት የመሰረቱ አገራት ሲሆኑ በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በፋይናንስና በዲፕሎማሲ ሰፊ ግንኙነት መስርተዋል። ከሩሲያ ጋር በወታደራዊ፣ በባሕልና በሃይማኖት ሰፊ ግንኙነት አለን፤ በዲፕሎማሲ መስክም ያለመቆራረጥ የቀጠለ ወዳጅነት መስርተናል። ከሕንድ እና ከደቡብ አፍሪካ ጋርም ሰፊ ግንኙነት አለን። በአጠቃላይ ብሪክስ ከእነዚህ እና አዲስ ከተቀላቀሉ አገራት ጋር ያለንን ጠንካራ ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር ያስችላል።
ሁለተኛው ፋይዳው ደግሞ መድረኩን በመጠቀም ስለ አገራችን እምቅ አቅምም ሆነ ብሔራዊ ጥቅማችንን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ሃሳባችንን የማቅረብ ዕድል መስጠቱ ነው። በቅርቡ የብሪክስ አባል አገራትን የተቀላቀለችውን ኢንዶኔዥያን ጨምሮ የዓለምን ከግማሽ በላይ ሕዝብ፣ ሰፊ መሬት፣ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ድርሻ እና ታዳጊ ኢኮኖሚ ባለቤት ናቸው። በዚህ መድረክ አገራችን በአባልነት መሳተፏ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል። እንደ ዓረብ ሊግ በመሳሰሉ ማኅበራት ኢትዮጵያ በሌለችበትና አቋሟን ባላስረዳችበት ምን አይነት መግለጫዎች እንደሚወጡና ምን አይነት አቋም እንደሚያዝ ላስተዋለ ብሪክስን መቀላቀላችን ምን ያህል ፋይዳ እንደሚኖረው መረዳት አያዳግተውም። ከዚህ በተጨማሪ የብሪክስ አገራት በልማት ባንክ በኩል የልማት ድጋፍ ማግኘት የሚያስችል ዕድል አላቸው። ለአብነት ያህል በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት የብሪክስ አባል አገራት ከዚህ የልማት ባንክ ለእያንዳንዳቸው የአንድ ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ተደርጎ እንደነበር ያስታውሷል።
የቀጣናዊ ጥምረት ጅምሮች
ኢትዮጵያ በፓን አፍሪካኒዝም የጸና እምነት ያላትና ለዚህም የሚቻላትን ሁሉ ስታደርግ የቆየች መሆኑ እሙን ነው። ይህም በኢኮኖሚው መስክ ሲታይ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣናን ቀድመው ከፈረሙና ካጸደቁ አገራት መካከል አንዷ ናት። በተጨማሪም ለቀጣናዊ ጥምረት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ቀስ በቀስ እያደገ ለሚሄድ ቀጣናዊ ጥምረት የሚያግዙ እንደ መሰረት ልማት ትስስር የመሳሰሉ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛል። ለዚህም ኢትዮጵያን ከኬንያ እና ደቡብ ሱዳን ጋር የሚያስተሳስረው የመንገድ መሰረተ ልማት አንዱ ማሳያ ነው። ጅቡቲ፣ ኬንያ እና ሱዳንን ተጠቃሚ ያደረገውና እስከ ታንዛኒያ ድረስ ለመዘርጋት በሂደት ላይ የሚገኘው የኤሌክትሪክ መስመርም ሌላው የቀጣናዊ ጥምረት ማሳያ ነው።
“ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ”
በለውጡ ዓመታት “ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄዎች” በሚል መርህ በርካታ ጥረቶች ተደርገው ውጤቶች ተመዝግበዋል። ይህንን በሚገባ ለመግለጽ ሁለት ክስተቶችን ማንሳት ይቻላል። የመጀመሪያው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድርድር ነው። የሕዳሴ ግድብ ድርድር ከግድቡ ግንባታ መጠንሰስ ጀምሮ የቀጠለና ብዙ ውጣ ውረዶችን ያሳለፈ ነው። በዚህ ሂደት የአሜሪካ መንግሥት ለማደራደር በሚል በሂደቱ ላይ አሉታዊ ጫና ሲያሳድር “ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ” በሚል ጉዳዩ ወደ አፍሪካ ኅብረት እንዲመጣ በማድረግ መፍትሄ መስጠት ተችሏል። ሁለተኛው ማሳያ ደግሞ የፕሪቶሪያ ስምምነት ነው። ከህወሓት ጋር የነበረውን ግጭት ለመፍታት የአውሮፓ ኅብረት፣ አሜሪካ እና ሌሎችም ምዕራባዊያን ኃይሎች ከፍተኛ ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም ድርድሩን የአፍሪካ ኅብረት እንዲመራው በማድረግ በአፍሪካዊ መፍትሄ ሰላማዊ ድርድሩን የተሳካ ማድረግ ተችሏል።
የዓለም አቀፍ መድረኮች ተሳትፎና አስተናጋጅነት
የኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ መድረኮች ተሳትፎና አዘጋጅነት ባለፉት ስድስት ዓመታት የበለጠ ተጠናክሯል። ከታላቁ የሰላም ኖቤል እስከ የዓለም ምግብ ድርጅት (ፋኦ) እንዲሁም ሌሎች የበርካታ ተቋማት ሽልማቶችን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) አሸንፈዋል። ከዚህም በተጨማሪ በርካታ የሁለትዮሽ ውይይቶች በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች አገራት ተካሂደዋል። ኢትዮጵያ በቻይና- አፍሪካ፣ በሩሲያ-አፍሪካ፣ በጃፓን- አፍሪካ፣ በሳዑዲ ዓረቢያ፣ በፈረንሳይ፣ በአሜሪካ እና በቱርክ-አፍሪካ መድረኮች ንቁ ተሳታፊ ነበረች። በኢትዮጵያም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ስፖርታዊ እና ሌሎችም መልክ ያላቸው በርካታ መድረኮችን አስተናግዳለች። ይህም በዓለም ሦስተኛዋ የዲፕሎማሲ መገኛነታችንን ያስቀጠለ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ድል ነው።
በአጠቃላይ የውጭ ግንኙነት ስኬት የአገራዊ ስኬት ተቀፅላና ማሳያ ነው። ባለፉት ስድስት ዓመታት የተገኙት የውጭ ግንኙነት ስኬቶችም ይህንን የሚያሳዩ ናቸው። በቀጣይም የተቋማት ግንባታ እና የሪፎርም ሥራዎች ይበልጥ ተጠናክረው የበለጠ ውጤታማነት በዓለም መድረክ ላይ እንደሚገኝ ተስፋ አደርጋለሁ።
ማኅበራዊ

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
ለመድኃኒት አቅርቦት ችግር
በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት እና በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ትብብር የተዘጋጀ

መፍትሔ ያበጀው አዋጅ
በቤተልሔም ባሕሩ
የጤና እክል አጋጥሟቸው ከሕመማቸው ለመፈወስ ወደ ጤና ተቋማት የሚሄዱ ታካሚዎች ለሌላ ድካምና እንግልት ከሚዳረጉባቸው ጉዳዮች አንዱ በሐኪም የታዘዘላቸውን መድኃኒት በቀላሉ ማግኘት አለመቻላቸው ነው። መዳንን ተስፋ አድርጎ ወደ ሕክምና ተቋም ያቀና ታካሚ ከሕመሙ ለመፈወስ ጤንነቱን ለመመለስ የሚያግዘውን መድኃኒት ‘የለም’ ተብሎ መመለስ ቅሬታን የሚፈጥርበት በጤና ተቋማት ላይ ያለውን አመኔታም የሚያጎድልበት ጉዳይ ሲሆን ይስተዋላል። እውቀትና ልምድ ያካበቱ ባለሙያዎችም ሆኑ በዘመን አመጣሽ መሣሪያ የተደራጀ የጤና ተቋም መኖር ከመድኃኒት አቅርቦት ውጭ ለሕሙማን በሽታን መርምሮ

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
ከመለየት የዘለለ ፋይዳ አይኖራቸውም። ስለሆነም ታካሚ ከሕመሙ ድኖ ወደ ቀድሞ ጤንነቱ እንዲመለስ የሚያግዘው መድኃኒት ለተጠቃሚው ኅብረተሰብ በአግባቡ ተደራሽ መሆን ይገባዋል። ለዚህ ደግሞ የመድኃኒት አቅርቦትና ፍላጎትን በአግባቡ መምራት የሚያስችል ሕግ የግድ ይላል።
በኢትዮጵያ ለኅብረተሰቡ ፍትሃዊ፣ ተደራሽና ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለመስጠት በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ሲሆን የተለያዩ የሕግ ማሻሻያዎችም እየተደረጉ ይገኛሉ። የአገሪቷ የጤና ፖሊሲ መከላከልና አክሞ ማዳን ላይ ያተኮረ ነው፤ ይህም የሕክምና ግብዓትና የጤና ተቋማት ተደራሽነትን ማስፋት የሚጠይቅ ነው። በቅርብ ዓመታት የጤና ተቋማትን አቅም የማሳደግና የማስፋት ሥራ እየተሰራ ሲሆን ተቋማቱ ሥራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ የመድኃኒት አቅርቦት አሰራርን እንዲሁም የሰው ኃይሉን ዘመኑን የዋጁ እንዲሆኑ ማድረግ ይጠይቃል።
በጤናው ዘርፍ ጤናማና አምራች ዜጋ የማየትን የአገር ራዕይ ማሳካትና መምራት የሚያስችሉ የልማት ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችን እና ዕቅዶችን ነድፎ በመተግበር ሰፊ መሰረት ያለው፤ ፈጣን፣ ቀልጣፋና ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ ልማትን የማፋጠንና ድህነትን የማስወገድ ዓላማን ያነገበው የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የመድኃኒት አቅርቦቱን በማዘመን ኅብረተሰቡ በመድኃኒት እጥረት ሳቢያ የሚያሰማውን ቅሬታና እሮሮ መፍታት የሚያስችል አዋጅ አዘጋጅቷል። አዋጁ ምን ነገሮችን ይዟል በምን መልኩስ ለመድኃኒት አቅርቦት ችግሩ መፍትሄ ይሰጣል የሚለውን በዚህ ፅሁፍ በአጭሩ እንቃኛለን።
አዋጁ ለምን አስፈለገ?
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕዳር 17 ቀን 2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎትና
የመድኃኒት ፈንድ አዋጅ ቁጥር 1354/2017ን ማፅደቁ ይታወቃል። ተቋሙ የሚመደብለት በጀት ባይኖርም በአስፈፃሚ አካላት ማቋቋሚያ አዋጅ 1263/2014 ባለ በጀት መሥሪያ ቤት በሚል ነበር የፀደቀው። በመሆኑም ይህን የሕግ ክፍተት ለማስተካከል ከዚህ ቀደም ሲሰራበት የቆየውን የተቋሙን ማቋቋሚያ አዋጅ 553/1999 መለወጥ ማስፈለጉን የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱልቃድር ገልገሎ ያስረዳሉ። አዋጁ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎትና ፈንድን ማቋቋም የሚልና ተቋሙ የፈንድ ተጠቃሚ በመሆኑ ፈንዱን ለመጠቀምና ለማስተዳደር አስፈላጊ እንደሆነም አክለዋል።
ይህ ተቋም በተለያዩ አካባቢዎች የሚጠቀምባቸው 63 መጋዘኖች እንዳሉት፤ በእነዚህ መጋዘኖች የሚሰሩ አብዛኞቹ ሠራተኞችም መልካም ሥነ- ምግባር የተላበሱና የተሰጣቸውን የሕዝብ አደራ ተቀብለው መድኃኒቶችን በአግባቡ የሚያሰራጩ ቢሆኑም አንዳንድ ሥነምግባር የጎደለው፣ መመሪያን ተከትሎ የማይሰራ ሠራተኛ መኖሩን ዋና ዳይሬክተሩ አልሸሸጉም። ታዲያ ይህን መሰል ችግር ሲገጥም አስተዳደራዊ እርምጃዎችና ወደ ሕግ አካላት የማቅረብ ሥራ እየተሰራ ቢሆንም የሕግ ክፍተት የሚያጋጥምበት ጊዜ ስላለ መድኃኒት የሰው ሕይወት መሆኑን በአግባቡ ተረድቶ የሚሠራ ሠራተኛ እንዲኖር ለማስቻል ጠንካራ የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት ጠቃሚ መሆኑን አንስተዋል። ከዚህ አኳያ አዋጁ ከዚህ ቀደም በሰው ኃይል አስተዳደር ላይ ይስተዋል የነበረውን ችግር በመፍታት የተቋሙን የሰው ኃይል በአግባቡ ለመምራት የሚያግዝም ነው።
ቀደም ሲል የነበረው አዋጅ የሰው ኃብቱን በራስ ማስተዳደር የማያሰችል በመሆኑ በአንዳንድ ሠራተኞች ላይ ከሥነ ምግባር ጋር ተያያዞ የሚያጋጥሙ ችግሮች መኖራቸውን የጠቀሱት ዶ/ር አብዱልቃድር አዲሱ አዋጅ ይህን ችግር በመፍታት የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለቱ የሚፈልገውን ብቃት ያለው የሰው ኃይል ለማፍራት የሚያግዝ እንደሆነ ነው የተናገሩት። አዲሱ አዋጅ ዘርፉ የሚፈልገውን ብቃት ያለውና ጠንካራ የሰው ኃይል ለማስተዳደርና ጠንካራ ሥርዓት ለመፍጠር የሚያስችልም ነው።
በቀድሞው አዋጅ ያልነበረና በአዲሱ አዋጅ መካተት እንዳለበት የታመነበት ሌላው ጉዳይ የኅብረተሰቡን የመድኃኒት ፍላጎትና አቅርቦት ለማመጣጠን ያለመው ውል የተገባለት የአቅርቦት ሥርዓት ነው። የጤና መድህን ተጠቃሚዎች ቁጥር ብቻ ከ50 ሚሊየን በተሻገረበት በአሁኑ ጊዜ የመድኃኒት ፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን ችግሩን ለመፍታት ፈጣን ምላሽ ሰጪ መሆንን የሚጠይቅ በመሆኑ ውል የተገባለት የአቅርቦት ሥርዓት በአዋጁ እንዲካተት ተደርጓል።
ውል የተገባለት የአቅርቦት ሥርዓት የጤና ተቋማት የሚፈልጉትን ያህል መድኃኒት መጥነው ከበጀቱ ጋር ወደ ተቋሙ ልከው ውል የሚገቡበትና ተጠያቂነትን ያካተተ ሥርዓት ነው። ይህም ከዚህ ቀደም በስፋት የስተዋል የነበረውን የመድኃኒት አቅርቦትና ፍላጎት አለመመጣጠን ችግር ለመፍታትና ውሉን ያፈረሰው አካል ተጠያቂ የሚሆንበትን አሰራር ያካተተ ነው። ኅብረተሰቡ በመድኃኒት አቅርቦት ችግር እንዳይጎዳ ይህ አሰራር ሚናው የጎላ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ የተጠያቂነት ሥርዓትን ለማስፈን ለሚጠቅመው ለዚህ አሰራር አስፈላጊው
ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
የመመሪያ ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ ነው።
ሌላው የአዋጁ ጠቀሜታ መድኃኒት በብድር ወስደው በማይመልሱ ተቋማት ሳቢያ የኦዲት ግኝት የሚሆነውን የብድር ገንዘብ ለማስመለስ የሚያስችል አሰራር ማካተቱ ነው። ተቋማት በፈፀሙት ውል መሰረት በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ብድራቸውን ካልመለሱ በባንክ ሂሳባቸው ውስጥ ከሚገኘው ገንዘብ እንዲወሰድ የሚስማሙበት አሰራር በአዋጁ ተደንግጓል። ይህ ድንጋጌ ተቋማት በውሉ ላይ ያስቀመጡትን የማያቀርቡ ሆነው ሲገኙ በቀጥታ ከባንክ ሂሳባቸው ላይ የመቁረጥና ገቢውን የመሰብሰብ ሥልጣን ለተቋሙ የሰጠ የአዋጁ ክፍል ነው።
በተጨማሪም የሕይወት አድን መድኃኒቶችና በጤና ፕሮግራም የሚቀርቡ ግብዓቶችን ወደ ጤና ተቋማት ከማድረስና ከማጓጓዝ ጋር የሚያጋጥመውን እንግልትና ወጪ ለመቀነስና መድኃኒቶችን በፍጥነት ተደራሽ ማድረግና ማቅረብ የሚቻልበት አሰራርም ለተቋሙ ተመቻችቷል።
የኅብረተሰቡን የመድኃኒት ፍላጎት ለማሻሻል እንዲቻል ከመንግሥትና ከግሉ ዘርፍ ጋር በአጋርነት መስራት የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት ለመዘርጋት የግል አጋርነት ጥናት የተጠናቀቀ ሲሆን፤ ይህም በተቋሙ በተለያየ ምክንያት የመድኃኒት እጥረት ቢያጋጥም በግሉ ዘርፍ በተመሳሳይ ዋጋና አቅርቦት እንዲኖር የሚያስችል ሥርዓት እንደሆነ ዶ/ር አብዱልቃድር ጠቁመዋል። ሥርዓቱ ኅብረተሰቡ የአቅርቦት ችግር እንዳይገጥመው በማድረግ ለጠቅላላው የአገሪቷ የመድኃኒት ችግር መፍትሄ ይሰጣል የሚል ሃሳብ የያዘ ነው።
ሌላው የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ከአገር ውስጥና ከውጭ ጥራታቸውና ፈዋሽነታቸው የተጠበቁ መድኃኒቶችን ገዝቶ በወቅቱ ለጤና ተቋማት ከማድረስ ባሻገር ከሚያቀርባቸው ግብዓቶች በተለያዩ ምክንያቶች ለብልሽት ቢዳረጉ ለምሣሌ በጥራት ጉድለት፣ በሽረት ጊዜ ማለፍ ወዘተ. . .መድኃኒቶች ከገበያ ቢወጡ ወይም አገልግሎት ባይሰጡ አግባብ ባለው መልኩ በመሰብሰብ የሚወገድበት ሥርዓት ባለመኖሩ የጤና ተቋማት ጥቅም ላይ የማይውሉ መድኃኒቶችን ለበርካታ ዓመታት በመጋዘናቸው ውስጥ በማከማቸት ለቦታ ጥበትና ለአላስፈላጊ ወጪ ሲዳረጉ ቆይተዋል። ይህን እንደ አገር ለማስወገድ አገልግሎቱ አዋጁ ላይ ባካተተው መሰረት የአወጋገድ መመሪያ በማዘጋጀት ጥቅም ላይ የማይውሉ መድኃኒቶችን ማስወገድ የሚያስችል ሥርዓት በመዘርጋት ለመንግሥትና ለግል የጤና ተቋማት በሙሉ አቅም የማስወገጃ ወጪ ሸፍነው መገልገል የሚችሉ መሆኑን ዶ/ር አብዱልቃድር ጠቁመዋል።
ጥቅም ላይ የማይውሉ መድኃኒቶች አወጋገድ ሥርዓት አስተዳደርን በተመለከተ እንደ አገር ከፍተኛ ክፍተት ያለበት በመሆኑ በአዲሱ አዋጅ እንዲካተት ተደርጓል። በዚህም አገልግሎቱ በ19 ቅርንጫፍቹ አማካኝነት ተሸከርካሪዎቹ መድኃኒቶችን ወደተለያዩ ቦታዎች ካደረሱ በኋላ ሲመለሱ ጥቅም የማይሰጡ መድኃኒቶችን ጭነው በማምጣት በአገልግሎቱ ስር በሚተዳደሩትና በተለያዩ ቦታዎች በተገነቡት ስምንት በከፍተኛ የሙቀት መጠን በሚሰሩ (13000ዲ.ሴ) ዘመናዊ ማስወገጃ ማዕከላት (ኢንሲኔተሮች) ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣንና ከአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን
ጋር በመሆን ከአካባቢ ብክለት ነፃ በሆነ መንገድ የማኀበረሰቡን ጤና ሳይጎዱ እንዲመክኑ ያደርጋል።
የአዋጁ ፋይዳ
አዋጁ ተጠያቂነትን ለማስፈን እንዲሁም የአቅርቦት ሰንሰለቱ ሥነ-ምግባር ባለውና የማኀበረሰብ አገልጋይ ነኝ ብሎ በሚያምን የሰው ኃይል እንዲደራጅ የሚያግዝ ዘመን ተሻጋሪና የተቋሙን ችግር ይፈታል ተብሎ የታመነበት ነው።
በፌዴራል የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጅ 1333/2016 አንቀፅ 87 መሰረት በማዕከል የሚፈፀሙ የመድኃኒት አቅርቦቶችና የሕክምና መሣሪያ ግዥዎች እንዲሁም የተወሰኑ ዕቃዎችን ልዩ ባህሪያቸውን ከግምት በማስገባት ልዩ የግዥ አፈጻጸም ወይም ንብረት አስተዳደር መመሪያ ማውጣት እንደሚችሉ ከቀረቡ ዝርዝር ነገሮች መካከል ይገኛል። ከዚህ ቀደም መድኃኒት እንደማንኛውም ዕቃ ይገዛ እንደነበር በዚህም መድኃኒት ለመግዛት ረጅም ጊዜ እንደሚወስድ ዶክተር አብድልቃድር ገልፀዋል። ይህ ሥርዓት ተጠያቂነትን ማስፈን የሚችል ፈጣን የግዥ ሥርዓት ሲሆን ከአፍሪካ አገራት ጋር በትብብር ግዥ መፈፀም የሚያስችል እንደሆነም ተናግረዋል። በቅርቡ ፀድቆ ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው አዲሱ የግዥ ሥርዓት ወደ ፍትህ ሚኒስቴር መላኩንም አስረድተዋል።
ይህ አሰራር እንደ ካንሰር፣ የኩላሊት እጥበትና ንቅለ ተከላ ያሉ የአቅርቦት እጥረት የሚያገጥማቸው ሕክምናዎችን መድኃኒቶችን ከአፍሪካ አገራት ጋር በጥምረት መግዛት የሚያስችል አሰራር ነው። መሰል የግዥ ሥርዓትን እየተገበሩ ባሉ የአፍሪካ አገራት በጥምረት ግዥ መፈጸም መድኃኒትን በዘላቂነት በማቅረብ የኅብረተሰቡን ጥያቄ መመለስና ቅሬታዎችን መፍታት አስችሏል። መመሪያው ከአዲሱ አዋጅ ጋር በጥምረት ሲተገበር የተቋሙን የዘመናት ችግሮች የሚፈታ በመሆኑ ለትግበራው የሚተጋ ቁርጠኛ አመራርና ሠራተኛ እንደሚሻ ዶክተር አብዱልቃድር አፅንኦት ሰጥተዋል።
አዋጁ መቼ ይተገበራል?
አዋጁ ተቋሙ በ2030 ሊደርስበት የወጠነውን ፈጣንና ምላሽ ሰጪ ተቋም የመሆን ራዕይ እውን ለማድረግ አስተዋፅኦ ያለው ነው። የግዥ ሥርዓቱ ከተስተካከለና ሥነ¬¬-ምግባር የተላበሰ የሰው ኃይል ካለ በአንዳንድ ክፍሎች እስከ 10 በመቶ የደረሰውን የሠራተኛ ከተቋሙ የመልቀቅ ምጣኔ በመቀነስ ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች ማደራጀት ያስችላል። ኃላፊነቱን በአግባቡ የማይወጣና የማይሰራ ሠራተኛን በመለየትም በሥልጠና የመደገፍና ውጤታማ የሆነ የአፈፃፀም ሥርዓት መከተልን ተቋሙ በአዋጅ ያመላከተውና የሚሰራበት አካሄድ ነው።
አዲሱ አዋጅ በቀደሙ የተቋሙ አመራሮች ተጀምሮ፤ አሁን ባለው አመራር ዘመኑን የዋጀ እንዲሆን ለማድረግ በጥልቀት ተመርምሮ የተዘጋጀ ነው። አዋጁን ለመተግበር የሚያስችሉ ደንቦችና መመሪያዎች ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ በመሆናቸው አዋጁ በነጋሪት ጋዜጣ መታተሙን ተከትሎ ሙሉ በሙሉ ወደ ትግበራ ይገባል።
ፖለቲካ

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
ኢትዮጵያ

በእንግዶቿ አንደበት
በአየለ ያረጋል
ምድረ ቀደምቷ ኢትዮጵያ የአፍሪካዊያን መናገሻ ናት። የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከልም እንዲሁ። አዲስ አበባም የኢትዮጵያ መታያ ናት። የኢትዮጵያ አየር መንገድም የአፍሪካዊያን መጓጓዣ ፓን አፍሪካ አየር መንገድ ነው። አዲስ አበባ የአየር መንገዱን ተሸጋጋሪዎች፤ ገቢና ወጪዎችን ሰርክ ትቀበል፣ ትሸኛለች። በሌላ አነጋገር አዲስ አበባ የአፍሪካዊያን ፌርማታ ናት-ማረፊያም፣ መሰፋፈሪያም። በእነዚህ ዕድሎች አዲስ አበባ በየወቅቱ ትጎበኛለች። ጉብኚዎቿም ትዝብታቸውን ይተርኩላታል። በአዲስ አበባ መስኮትም ኢትዮጵያን
ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
ይቃኛሉ።
በቅርቡ የብልፅግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔን እንዲታደሙ የተጋበዙ የተለያዩ አገራት እንግዶች አዲስ አበባን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል። እንግዶቹ ኢትዮጵያን እንዴት ተረዷት፤ አዲስ አበባን እንዴት አገኟት የሚለውን ግላዊ ምልከታቸውን አጋርተዋል። አገሮቻቸው ከኢትዮጵያ ጋር ስለነበራቸው ግንኙነት፣ አሁናዊ የመንግሥታት ቁርጠኝነት እና የወደፊት ተስፋም እንዲሁ።
ኤልያስ ሙሳ ዳዋሌህ
(የፒፕልስ ራሊ ፎር ፕሮግረስ ፓርቲ ዋና ፀሐፊ እና የጅቡቲ ፋይናንስ ሚኒስትር)
“እንኳን አደረሳችሁ” ሲሉ በአማርኛ ቋንቋ ንግግራቸውን የጀመሩት የጎረቤት አገር ጅቡቲ ተወካይ አቶ ኤልያስ ሙሳ “የአይበገሬነት፣ የአንድነትና የአሸናፊነት መንፈስ ተምሣሌት በሆነው በአድዋ ድል መታሰቢያ በመገኘቴ ትልቅ ኩራት፣ ደስታ፣ ክብር ይሰማኛል” በማለት ንግግራቸውን ቀጠሉ. . .
“በመላ ኢትዮጵያ ያለው ስር ነቀል ለውጥ የሚደነቅ ነው። የኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ አስደናቂ ለውጥ ላይ መሆኗን መስክረናል። አዲስ አበባ በመሰረተ ልማት ግንባታና በክትመት ሂደት አብዮት ላይ መሆኗን አይቻለሁ፤ አዲስ አበባ ዛሬ እንደ ስሟ የበለጠ አዲስ ናት”።
“የገጠሩም ክፍል እያደገ ነው” ያሉት አቶ ኤልያስ፤ በእርስዎ ቆራጥ አመራር (ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ) አሁን ላይ ኢትዮጵያ ራሷን በመቻል በተለይ በግብርና ምሣሌ እየሆነች ነው። ኢትዮጵያ በጥቂት ዓመታት ውስጥ በምግብ ራስን በመቻልና ጠንካራ ኢኮኖሚ በመገንባት ትልቅ ውጤት አስመዝግባለች ሲሉ አውስተዋል።
ፖለቲካ ውስጥ ርዕይ ማስቀመጥ በጣም አስፈላጊ ነው። ከዚህ በላይ ግን ርዕይን ተግባራዊ ማድረግ በጣም ወሳኝ ነው። ርዕይን ለማሳካት የሚውል ሀብትን በተመለከተ ተጠያቂነት ማስፈን በጣም አስፈላጊ ነው። አፍሪካ ውስጥ ርዕይ በማስቀመጥ ብዙ ፓርቲዎች ተሳክቶላቸዋል። ነገር ግን ተጠያቂነት ማስፈን ላይ ክፍተቶች አሉባቸው። ኢትዮጵያ በመደመር ፍልስፍና እነዚህን ሦስቱን አግኝታለች።
“ኢትዮጵያ ምንጊዜም የቀጣናው ምሰሶ ናት። የቀጣናው የሰላም ዘብ እና የቀጣናዊ ምጣኔ ሀብታዊ ትስስር አምሳል ናት። ጅቡቲ ለኢትዮጵያ ቀጣናዊና ሉላዊ አዎንታዊ ሚና ከበሬታ ትሰጣለች። እናም ኢትዮጵያ ዛሬም ቀጣናዊ የሰላም ዘብነቷን፣ የኢኮኖሚያዊ ትብብር ቀንዲልነት ሚናዋን በማጠናከር የመሪነት ሚናዋን መቀጠል አለባት። ኢትዮጵያ ለምክክርና መግባባት የሚበጁ አይነተ ብዙ ባሕላዊ እሴቶች አሏት። የኢትዮጵያዊያን ሰላም፣ አንድነትና ጥንካሬ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው ዋስትና ነው። የጋራ መዳረሻችንን ለመቀየር ‘ድር ቢያብር አንበሳ ያስር’ የሚለው የኢትዮጵያዊያን አባባል ማሳያ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
ፒተር ላም ቦዝ
(የደቡብ ሱዳን ሕዝቦች ነጻነት ንቅናቄ SPLM ዋና ፀሐፊ)
የዛሬው ፖለቲከኛ ፒተር ላም ቦዝ ከረጅም ዓመታት በፊት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ


ነበሩ። ኢትዮጵያን በቅጡ ያውቋታል። “ከዓመታት ቆይታ በኋላ አዲስ አበባ ስመጣ የማውቃትን አዲስ አበባን አጣኋት” ሲሉ ለውጧን አድንቀዋል።
“አሁን ካለንበት ስፍራ ከዚህ በፊት የማውቃት ፒያሳ ዛሬ ጠፋችኝ። ፒያሳ በውበት አሸብርቃለች። ከዚህ የምንማረው ቁምነገር ቢኖር አገርን እንዴት በግልጽ ርዕይ መለወጥ እንደሚቻል ነው። የማውቃት አዲስ አበባ አትመስልም፤ ተለውጣለች። በመሰረተ ልማት ተቀይራለች” ብለዋል።
“ … አሁን የምንገኘው በቤተ መንግሥት ውስጥ ነው፣ እዚህ ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ በዚህ ቤተ መንግሥት በኩል ማለፍ በራሱ ከባድ ነበር” ሲሉ ቆይታቸውን በምልሰት አጋርተዋል።
ፒተር ላም ቦዝ የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳንን ታሪካዊ ወዳጅነትም እንዲህ ተርከውታል።
የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን ግንኙነት ሲወሳ


ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
የጠላት ወረራ ዘመንን ማስታውስ ግድ ይላል። በአውሮፓዊያን አቆጣጠር 1941 አጼ ኃይለሥላሴ በእንግሊዝ አጋዥነት ከስደት በሱዳን በኩል ሲመለሱ ንጉሠ ነገሥቱን ያጀቧቸው እግረኛ ወታደሮች ነጮች ሳይሆኑ ደቡብ ሱዳናዊያን ነበሩ። እነዚህ ደቡብ ሱዳናያዊያንና ሱዳናዊያን ኢጣሊያን ከኢትዮጵያ ለማስወጣት ከአርበኞች ጋር ሆነው ተዋግተዋል።
ለደቡብ ሱዳን ነጻነትም ኢትዮጵያዊያን በየዘመኑ ከደቡበ ሱዳን ጎን ነበሩ። ከአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ሁሉም የኢትዮጵያ መሪዎች ለደቡብ ሱዳን አለኝታ ነበሩ። ደቡብ ሱዳን እ.አ.አ በ2024 በሕግ አውጪ ምክር ቤቷ ያፀደቀችው የናይል ትብብር ማዕቀፍ ስምምነት የሁለቱ አገራት ትስስር ዋነኛ ማሳያ ነው። በትምህርት ዘርፍ በአውሮፓዊያኑ ዘመን አቆጣጠር በ2025 ብቻ 632 ደቡብ ሱዳናዊያን በኢትዮጵያ ነጻ የትምህርት ዕድል አግኝተዋል። አስደናቂ ስኬት ነው። በመሰረተ ልማት እየተሳሰርን ነው። የአፍሪካ ችግር በአፍሪካዊ
መፍትሄ መፈታት አለበት የሚለው መርህ ወሳኝ ነው ብለዋል።
ኑዶሎ ኪቤት
(የደቡብ አፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ አባል)
ኑዶሎ ኪቤት የኢትዮጵያን ከፍታ አድዋን ከመሰሉ ጥንተ ታሪኳ ቃኝተው፤ ከፓን አፍሪካዊነት ንቅናቄ አስተሳስረው፣ ከዛሬው ምጣኔ ሀብታዊ ጉዞ ተስፋዋን ፈትተው እንዲህ ገልጸዋታል።
“ኢትዮጵያ ሁልጊዜም የአፍሪካ የነፃነትና የአይበገሬንት ቀንዲል ናት። ይህቺ ትልቅ አገር በቅኝ ግዛት ያልተንበረከከችና የሰው ልጅ መንፈሰ ጠንካራነት ትዕምርት ናት። ይህ የሕዝቦቿን ብርቱ ጥንካሬ እና የመሪዎቿን ብቃት ማሳያ ነው።
ከአድዋ ድል ጀምሮ እስከ አፄ ኃይለሥላሴ በነበሩ ሉዓላዊነትን የማስከበር አኩሪ ገድሎቿ ኢትዮጵያ የራሷን ክብርና ሉዓላዊነት ብቻ አይደለም ያስከበረችው። ይልቁንም ለወንድም አፍሪካዊያን የነጻነት ትግል መንፈስን ያወረሰች አገር ናት። ለዚህ ነው በ1963 የአፍሪካዊያን አንድነት እንዲጠናከርና ፓን አፍሪካዊነት እንዲያብብ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አዲስ አበባ ውስጥ የተመሰረተው።
በብዝሃነት ውስጥ ጸንተን መኖር ያለውን ፋይዳ አይተናል። አፄ ኃይለሥላሴ፣ ኩዋሜ ንኩሩማህ፣ ጁሊየስ ኔሬሬ፣ ኔልሰን ማንዴላ፣ ኦሊቨር ታምቦ እና መሰሎቻቸው አፍሪካዊያን ለአንድነት የከፈሉት የትግል ዋጋ ለዛሬም መነሳሳት የሚፈጥር ነው።
ኢትዮጵያ ያደረገቸው ድንቅ ሪፎርም በኢኮኖሚ፣ በሰላም፣ በአገር አንድነት ጅማሮው ለአፍሪካም የሚበጅ ነው። የኢትዮጵያዊያን ስኬት የአፍሪካ ስኬት ነው፤ ፈተናዎቻችሁም የአፍሪካ ነው። እንደ ፓን አፍሪካዊነት፣ እንደ አብዮተኝነት፣ እንደ ትግል ጓድነት ለአፍሪካ እና ለሕዝባችን በትብብርና በአጋርነት እንሰራለን። በየትኛውም ክፍላተ አፍሪካ የአፍሪካ ትንሣኤና መሪነት መበሰር አለበት። ዕድሜ ለብልፅግና፣ ዕድሜ ለፓን አፍሪካዊነት” ብለዋል።
ኑዶሎ ኪቤት የአፍሪካዊያን ርዕሰ መዲና የሆነችውን የአዲስ አበባን የከተሜነት እመርታም እንዲህ ገልጸዋል።
“በእውነቱ እጅግ ተደንቄያለሁ። አዲስ አበባ በሁሉም አቅጣጫ ልማት ላይ ናት። መንገዶች፣ ሰማይ ጠቀስ ፎቆች ዕጽዋት እየተተከሉ አይቻለሁ። ለእኔ እንደዚህ ያለ መልሶ ማልማት አላየሁም። ለእኛም መነሳሳት ፈጥሮልናል። እኛም ወደ አገራችን ስንሄድ ቃልን በተግባር ለማሳየት እንሰራለን። በእውነት የብልጽግና ፓርቲን ቃልን በተግባር በቀጥታ በዓይናችን አይተናል”ብለዋል ሥራ አስፈፃሚዋ።
ዛፈር ሲራካያ
(የተርኪዬ ኤኬ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር)
ከዛፈር ሲራካያ ንግግሮች የሚከተለውን ሃሳብ መዘናል።
“ኢትዮጵያ በአፍሪካ የታሪክ ገጾች ውስጥ በጉልህ የምትነበብ አገር ናት። ከጥንተ ዓለም ሥልጣኔ ማዕከላት አንዷ ናት። በባሕል፣ በታሪክ፣ በብዝሃነት፣ በእምነት፣ በቋንቋና በቅርስ የበለጸገችና በፈተናዎች ሳትበገር ዘመናትን የተሻገረች አገር ናት። ኢትዮጵያ በዓለም ላይ አስደናቂ ታሪክ ካለቸው አገራት አንዷ
ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
ናት። ይኸውም ኢትዮጵያ ለዘመናት ለወራሪዎቿ ሳትበገር ሉዓላዊነቷን አስከብሯ መኖሯ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ክፍለ ዓለማት የነፃነት ታጋዮች ፋና ወጊ መሆኗ ነው።
እኛ ተርኪዬዎች የነፃነትን መንፈስ በቅጡ እንገነዘባለን። ተርኪዬና ኢትዮጵያ በነጻነት፣ በሉዓላዊነትና በአይበገሬነት መንፈስ እሴቶችን ይጋራሉ። የኢትዮጵያና የተርኪዬ ጥብቅ ቁርኝት በታሪክ የተቃኘ ነው። በሱልጣን አብዱል ሃሚድ ዳግማዊ የተጀመረው የሁለቱ አገራት ትስስር በ1926 ተርኪዬ ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ ስትመሰርት ተቋማዊ ሆኖ ቀጥሏል። ይህም ከሰሃራ በታች የመጀመሪያው የተርኪዬ ኤምባሲ ነበር። ይህ በታሪክ ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ ላለን ትልቅ ስፍራ ሁነኛ ምስክር ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሁለቱ አገራት ወዳጅነት በትምህርት፣ በንግድና በባሕል ዘርፎች ላለፉት አስርት ዓመታት ይበልጥ እያበበ የመጣ ነው። የአፍሪካ ሕብረት ማዕከል በሆነችው ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያዊያን ትልቅ ቦታ አለን”።
ዛፈር ሲራካያ ተርኪዬ ለአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል። አገራቸው በኢትዮጵያና ተርኪዬ መካከል ለዘመናት የዘለቀውን የዲፕሎማሲ ግንኙነትና የሁለትዮሽ ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥልም እንዲሁ።
ዌላርስ ጋሳማጌራ
(የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር ፓርቲ ዋና ፀሐፊ)
ጋሳማጌራ የሩዋንዳና የኢትዮጵያ የባለብዙ ወገን ትብብር በጽኑ መሰረት ላይ የቆመ እንደሆነ ጠቅሰዋል። የሁለቱ አገራት ግንኙነት እንዲጠናከር መሪዎቹ ላበረከቱት አስተዋፅኦ አመስግነዋል። “እኛ አፍሪካዊያን ሁልጊዜም ከኢትዮጵያ ብርታትና አይበገሬነት እንማራለን”ም ብለዋል። አንድነት ፓርክን ጨምሮ የአዲስ አበባን መልኮች የታዘቡት እኒህ አንጋፋ ፖለቲከኛ “አዲስ አበባን ለመጀመሪያ ጊዜ ተዘዋውሬ ጎብኝቻለሁ። ባየሁት ነገር ተገርሜያለሁ። መጎብኘት ያለባት ከተማ ናት። እስከአሁን ባየሁት ተደስቻለሁ” ብለዋል።
የኢትዮጵያን የታሪክና ቅርስ ሀብት እና አያያዟን በተመለከተም “ኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ አላት። አንድነት ፓርክ የትናንት ትውስታንና ታሪካዊ ዐውድን ለመማር የሚያስችል ቦታ ነው። በፓርኩ በርካታ ታሪካዊና ባሕላዊ የዕደ ጥበብ ሥራዎችን ተመልክቻለሁ። የሁሉንም የአገሪቷን አካባቢዎች የሚወክሉና የሚያሳዩ የዕደ ጥበብ ሥራዎች ናቸው። የሚያስደንቅ ታሪካችሁን ያሳያል። የትናንት ታሪክ ወረታችሁን ጠብቃችሁ በማቆየትና ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ ትልቅ ሥራ ሰርታችኋል። እኛም ብዙ እንማርበታለን”።
አልሀጅ አሊቡካር ዳሎሪ
(የናይጄሪያ ኤፒሲ ፓርቲ ምክትል ሊቀ- መንበር)
“ዛሬ ፓርቲዬን ኤፒሲንና የፓርቲያችንን ሊቀ መንበር ዶክተር ዑመር አብዱላሂን ወክዬ በብልጽግና ጉባዔ ላይ መልዕክት ላስተላለፍ እዚህ በመገኘቴ ትልቅ ክብርና ኩራት ይሰማኛል። ይህ ስብሰባ የፖለቲካ ስብሰባ ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም አንድነትና ልማት ለማጠናከር ያለንን ቁርጠኝነት የምናከብርበትም ኹነት ነው። በሁለቱ የአፍሪካ ትላልቅ አገራት መካከል (በኢትዮጵያና በናይጄሪያ) ያለውን የጠበቀ ወዳጅነትም


ያመላክታል። ናይጄሪያና ኢትዮጵያ በመከባበርና የጋራ እሴትን በመሻት ላይ የተመሰረተ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ ታሪካዊ ግንኙት አላቸው። ይህም ግንኙነት በተለያዩ የትብብር መስኮች ተጠናክሯል። ለአብነት በዲፕሎማሲ፣ በንግድና በባህል ግንኙነቱ ተጠናክሯል” ያሉት የኤፒሲ ምክትል ሊቀ መንበር አዲስ አበባ እንደደረሱ ከተማዋን ተዘዋውረው የማየት ዕድል እንደገጠማቸውና በተመለከቱት የኮሪደር ልማት ሥራ መደነቃቸውን ተናግረዋል።
“ኤፒሲ እና ብልጽግና የጋራ ግብና ራዕይ አላቸው። ሁለቱም ፓርቲዎች ለሕዝባቸው ምጣኔ ኃብታዊ ዕድገትና መልካም አስተዳደር ለማስፈን እንዲሁም የበለጸገ አገር ለመፍጠር ቁርጠኛ ናቸው። እንደ አገር የሚገጥሙን ፈተናዎች ሊለያዩ ይችላሉ ነገር ግን መፍትሄው ያለው በትብብር ውስጥ ነው። ወደፊት ለመራመድ ፈጠራ የታከለበትና የጋራ ቀርጠኝነት ያስፈልጋል። በሁሉም የትብብር መስኮች ያለንን ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር እንሰራለን”።
“ኢትዮጵያ የአፍሪካ አገራት መሪ ናት። መንግሥት አሁን ላይ አስደናቂ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። እዚህ በመምጣቴ ተደስቻለሁ። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫነቷን የሚመጥን ተግባር አከናውናለች”።


ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
አንድሬ ክሊሞቭ
(የዩናይትድ ሩሲያ ፓርቲ ሱፕሪም ካውንስል ቢሮ አባልና የሩሲያ ፌዴሬሽን ሴናተር)
እኒህ የሩሲያ አንጋፋ ፖለቲከኛ አንድሬ ክሊሞቭ የኢትዮ-ሩሲያን ታሪካዊ ወዳጅነትና ትስስር ከአሌክሳንደር ፑሽኪን የዘር ግንድ ጋር በማስተሳሰር እንዲህ ገልጸውታል።
“የሩሲያ ሥነ-ጽሑፍ አባት አሌክሳንደር ፑሽኪን ዘመዶቹ የተወለዱት ከዚሁ ከኢትዮጵያ ነው። አሌክሳንደር ፑሽኪን የፅሁፍ ሥራዎች ብቻ ሳይሆን አደባባይና ሀውልት አለው። እኔ እንደምኮራ እናንተም ልትኮሩበት ይገባል። ከቀድሞ አጋራችን የቀድሞ አጋሮች ጋር ከአዳዲስ ስትራቴጂካዊ አጋሮች ጋር የበለጠ ከፍተኛ ጉዳዮች እንዲኖሩን እንፈልጋለን። በሁለቱ አገራት፤ በዓለም አቀፋዊ ግንኙነታችን ውስጥ
ሥሩ በጣም ጥልቅ እንደሆነ እናውቃለን”
“ኢትዮጵያና ሩሲያ አያሌ ዓመታትን ያስቆጠረ ታሪካዊ ወዳጅነት አላቸው። በንግድ፣ በሰብዓዊ ድጋፍ፣ በተለያዩ መስኮች ላይ የተመሰረተ ግንኙነታቸውም እያደገ መጥቷል። የኢትዮ- ሩሲያ ትብብር በሁለትዮሽና በባለ ብዙ ወገን በተለይም የብሪክስና የአፍሪካ-ሩሲያ የትብብር ማዕቀፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል። የዩናይትድ ሩሲያ ፓርቲ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ያለው ግንኙነት የበለጠ እንዲጠናከር ይሰራል። የእስካሁን የዕድገት ጉዟችሁ አስደናቂ ነው። በትክክለኛው ሃዲድ ላይ ናችሁ-በርቱ። ኢትዮጵያና አፍሪካ ለዘላለም ይኑሩ”
ከአራት ዓመት በፊት አዲስ አበባ እንደነበሩ ያወሱት ሴናተር አንድሬ ክሊሞቭ አዲስ አበባ በአራት ዓመታት ያሳየችውን ለውጥ “የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት መልሶ ማልማት ሥራ ይበል የሚያሰኝ ነው። በአፍሪካ አህጉር የተወሰኑ ቦታዎችን ተዟዙሬ ጉበኝቻለሁ። ከሰሜናዊ የሜዲትራንያን እስከ ደቡብ አፍሪካ ጫፍ ድረስ። እንደዚህ ግን ብዙ ዘመናዊ ቦታዎችን አላየሁም። አዲስ አበባ ግን በእውነቱ ዘመናዊ ከተማ እና እውነተኛ ከፍ እያለች የምትገኘው አፍሪካ ትክክለኛ መዲና ናት”።
ኒኮዲሞስ ቦሬ
(የኬንያ ዩናይትድ ዴሞክራቲክ አሊያንስ ፓርቲ ኤክዚኪዩቲቭ ዳይሬክተር)
ኒኮዲሞስ ቦሬ “በአንድነት ፓርክ፣ ተፈጥሮን ከሰው ሰራሽ ሥልጣኔ እንዲሁም ቤተ-መንግሥትን ከሕዝብ ጋር ማስተሳሰር መቻሉ አግራሞትን ፈጥሮብኛል” ብለዋል።
“ጥበበኛው እና ባለ ራዕዩ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አስደናቂ ስኬቶችን አስመዝግበዋል። እኔ ከስድስት ሰባት ዓመታት በፊት እዚህ መጥቼ ነበር፤ አውሮፕላን ማረፊያው እንኳ እንደ አሁኑ አልተሻሻለም ነበር። ከአምስት ስድስት ዓመታት በኋላ ተመልሼ ብመጣ አዲስ አበባን ማመን በማልችለው ለውጥ ውስጥ እንደማያት እርግጠኛ ነኝ። ምክንያቱም ፈጣን ዕድገት ላይ ናት፤ መንገዶች፣ በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ ዜጎች የሚገነቡ ዘመናዊ ቤቶች በፍጥነት እየተገነቡ ነው። መንገድ እየተስፋፋ ተመልክቻለሁ፤ አሮጌ ቤቶች አሁን ደረጃቸውን የጠበቁ ሆነው ተገንብተዋል። ይህ የኢትዮጵያን ጥቅል የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያመላክት ነው” ሲሉ ነው የተናገሩት።
ሲምበርሼ ሙቤንጌግዊ
(የዚምባብዌ ዛኑ ፒኤፍ ፓርቲ የውጭ ግንኙነት ዋና ጸሃፊ)
የ79 ዓመቱ የዕድሜ ባለጸጋ ሲምበርሼ ሙቤንጌግዊ በትውልድ አገራቸው ዚምባብዌ ጉምቱ ፖለቲከኛና የዲፕሎማሲ ሰው ናቸው።
ከአዲስ አበባ እንግዶች አንዱ የነበሩት የዚምባብዌው ዛኑ ፒኤፍ ፓርቲ የውጭ ግንኙነት ዋና ጸሃፊ ሲምበርሼ ሙቤንጌግዊ የአገሪቷን ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ እና የፓርቲያቸውን መልዕክት ባስተላለፉበት ንግግራቸው እንዲህ ብለዋል፡- “ዛኑ ፒኤፍ ፓርቲ ኢትዮጵያ አፍሪካ ውስጥ ብቸኛዋ ለቅኝ ገዢዎች ያልተንበረከከች አገር በመሆኗ ትልቅ አድናቆትና ዕውቅና ይቸራታል”።
“የኢትዮጵያዊያን የአርበኝነት መንፈስ ለፀረ ቅኝ ግዛትና የአፓርታይድ ሥርዓት ትግል እንዲቀጣጠል
ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
ቁልፍ አበርክቶ ነበረው። አብዛኞቹ የአፍሪካ የነጻነት ትግሎች በኢትዮጵያዊያንና በቆራጥ ኢትዮጵያዊያን ቁሳዊ፣ ሞራላዊና ዲፕሎማሲያዊ ድጋፎች የታጀቡ ነበሩ”።
የዚምባብዌ የነጻነት ኃይሎች ታሪክም ከዚህ የተለየ አይደለም ያሉት ዋና ፀሐፊው፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ታጋዮች ከኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ሥልጠናዎች እንዲሁም የጦር መሣሪያ ድጋፍ እንዳገኙ አውስተዋል። ዚምባብዌ ቅኝ ገዥዎችን ታግላ ድል ስትቀዳጅ የኢትዮጵያና የሕዝቧን ውለታ እንዳልረሳች ጠቁመዋል።
ብልፅግና ፓርቲ በታሪካዊቷ አገር ኢትዮጵያ ሰላም፣ ልማትና ብልፅግና ለማምጣት በመታተር በአጭር ጊዜ ያሳካቸውን ድሎች አድንቀዋል። የኢትዮጵያን የለውጥ ጉዞ “በእርግጥም አስደናቂና የማይታመን” ሲሉ አሞካሽተውታል። እንዴትስ ይህ ሁሉ ስኬት መጣ ሲሉም ተጠየቅ ሰንዝረዋል።
“በአዲስ አባባ ከተማ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች እኔን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የውጭ አገር ዜጋ ያማለሉ ተጨባጭ የለውጥ ምስክሮች ናቸው። በእርግጥም አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና የሆነችው በአጋጣሚ አይደለም፤ አዲስ አበባ ሁላችን የምንመካባት ውብ ከተማችን ናት” ሲሉ በኩራት ተናግረዋል።
አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት ዋና መሥሪያ ቤት መሆኗን የሚመሰክሩ አስደናቂ ለውጦችን እያሳየች መሆኗን ገልጸዋል።
“አዲስ አበባን ተዟዙሬ ስቃኛት ያየሁት ልማት አስደንቆኛል። ጽዳቷ ያስደምማል፤ የልማት ሥራዎቿ ሰማይ ጠቀስ ህንፃዎቿ ያስደንቃሉ፣ በሁሉም ቦታ የግንባታ ሥራዎች ይታያሉ። ኢትዮጵያ በእርግጥም በብልጽግና ዘመን ላይ ትገኛለች። አዲስ አበባ የአፍሪካ ዋና መቀመጫ ናት፣ በዚህም በጣም እንኮራለን”።
ፕሮፌሰር መሀመድ ሳዲኪ
(የሞሮኮ ናሽናል ራሊ ኦፍ ኢንዲፔንደንትስ / አር ኤን አይ/ ፓርቲ ተወካይ)
ፕሮፌሰር መሀመድ ሳዲኪ ኢትዮጵያ አስደናቂ የልማት ጉዞ እንዲሁም በአገራዊም ሆነ በአፍሪካ አቀፍ አንድነትና ሰላም ላይ ያላትን ቁርጠኝነት በማድነቅ ነው ንግግራቸውን የጀመሩት።
“ኢትዮጵያና ሞሮኮ የጥንታዊ ታሪክ ባለቤቶች ናቸው። የኢትዮጵያ እና የሞሮኮ ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት፣ የመበልጸግ ርዕይ እና ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ታሪካዊ አጋርነት ላይ የተመሰረተ ትብብር ነው። ሁለቱ አገራት ከ1960ዎቹ ጀምሮ የፓን አፍሪካዊነት እሳቤ እንዲያብብ ወሳኝና ንቁ ተሳትፎ ነበራቸው። የኢትዮ-ሞሮኮ ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት፣ የመበልጸግ ርዕይ እና ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ታሪካዊ አጋርነት ላይ የተመሰረተ ትብብር ነው”።
ፕሮፌሰር መሀመድ ሳዲኪ ሁለቱ አገራት በአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የጋራ ፍላጎት እንዳላቸው አንስተዋል። የሁለቱ አገራት የግሉ ዘርፍ ተዋንያን በኢኮኖሚው መስክ እመርታ የሚጫወቱትን ወሳኝ ሚናም እንዲሁ። ከፈረንጆቹ 2016 ወዲህ ደግሞ የሞሮኮው ንጉሥ በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት የኢትዮ-ሞሮኮ ፖለቲካዊ ወዳጅነት ወደላቀ ደረጃ እንዲሸጋገርና ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸው እንዲጎለብት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ


አጋጣሚ እንደነበር ጠቅሰዋል። “የአገራቱ የምጣኔ ሀብት አጋርነትና ትብብር በደቡብ-ደቡብ ማዕቀፍ የጋራ ፈተናዎችን ለመከላከል የሁለቱ አገራት የግል ዘርፍ የልማቱ ዋነኛ ተሳታፊ እንዲሆኑ ዕድል የሚሰጥ ነው”።
ሳማት ኑር ታተዛ
(የካዛኪስታን አማናት ፓርቲ አባልና እና የአገሪቷ ፓርላማ የታችኛው ምክር ቤት አባል)
ሳማት ኑር ታተዛ አዲስ አበባ ለኑሮ የምትመች፤ ነዋሪዎቿም እንግዳ ተቀባይ ስለመሆናቸው መስክረዋል። የኢትዮጵያ የልማት ትሩፋቶች አፍሪካ በልማት ጎዳና ላይ መሆኗን የሚያሳዩ መሆናቸውን ገልጸው፤ ይህም “ኢትዮጵያ በአፍሪካ የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች መሆኗን ያሳያል” ብለዋል። በተለይም ብሔራዊ ቤተ መንግሥትና ሙዚየምን ከተመለከቱ በኋላ እንዲህ ብለዋል፡-
“አዲስ አበባ በጣም ውብ ከተማ ናት አትሞቅም አትበርድም ለኑሮ ተስማሚ ነች። ነዋሪዎቿም በጣም ሳቂታና እንግዳ ተቀባይ ናቸው። ሙዚየሙ የኢትዮጵያን ታሪክ በአግባቡ ሰንዶ የያዘ ነው። በሙዚየሙ በጣም ውድ የሆኑ ሀብቶችን ተመልክተናል። አፍሪካ ቀደም ብላ ወደኋላ የቀረች ነበረች አሁን ግን ብዙ ለውጦችን ተመልክተናል አፍሪካን ማየት ከፈለግህ በቅድሚያ ኢትዮጵያን ማየት አለብህ። ከዚያ ሌሎቹን ትመለከታለህ። በኢትዮጵያ የተመለከትነው ነገር በጠቅላላ በጣም የሚደነቅ ነው”።
የኢትዮጵያ ዕድገት የሚታይና የሚጨበጥ መሆኑን የገለጹት ሳማት ኑር ታተዛ፤ “ለውጡ ለአፍሪካ ብሎም ለማዕከላዊ እስያ ዓርአያ የሚሆን ነው” ብለዋል።
ኢትዮጵያና ካዛኪስታን ጠንካራ ወዳጅነት፤ በሰላምና በዘላቂ ልማትም የጋራ መርህ ያላቸው አገራት መሆናቸውን በመጥቀስ ይህንን አጋርነት ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ ለማስፋትና ለማጠናከር መሠራት እንዳለበት ተናግረዋል።
ማኅበራዊ

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
ወባን ከኢትዮጵያ
በጤና ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ትብብር የተዘጋጀ

ምድር ለማጥፋት
በመንገሻ ገ/ሚካኤል
የወባ በሽታ በተለይም ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ አገራት ዋነኛ የጤናና የማኅበራዊ ዕድገት ችግር ስለመሆኑ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃዎች ያመላክታሉ። እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2023 ብቻ በ83 የዓለም አገራት 263 ሚሊዮን የወባ ታማሚዎች መመዝገባቸውንና 597 ሺህ ሰዎች በዚሁ ምክንያት ሕይወታቸውን ማጣታቸውን የሚገልፀው የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ 94 ከመቶ ከሚሆነው የወባ በሽታ ታማሚዎች ቁጥር እና 95 ከመቶውን የሞት ድርሻ የሚይዘው አህጉራችን አፍሪካ መሆኑን ያሳያል። ናይጄሪያ፣ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ ኒጀር እና የተባበሩት ታንዛኒያ ሪፐብሊክ ደግሞ ከፍተኛ የወባ በሽታ ጫና ያለባቸው የአፍሪካ አገራት ናቸው።

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
ኢትዮጵያ ባለፉት አሥር ዓመታት በወባ በሽታ ሳቢያ በየዓመቱ የሚከሰተውን የሕመምና የሞት መጠን በመቀነስ በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግባለች። ሆኖም ግን ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለያዩ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ምክንያቶች የበሽታው ሥርጭት መጠን መጨመሩን ከጤና ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያሳያል። ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የዝናብ መቆራረጥ መኖሩ፣ የወንዞች መቆራረጥና በአንዳንድ አካባቢዎች የድርቅ መከሰት፣ ከመስኖ ልማት መስፋፋት ጋር ተያይዞ በየአካባቢው ያቆረ ውሃ መኖር እንዲሁም የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ተከትሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ በግብዓት አቀርቦት ላይ ባስከተለው ጫና ምክንያት የአጎበር፣ የኬሚካሎችና የመድኃኒቶች ዋጋ መጨመርና የአቅርቦት መቀነስ ለበሽታው ስርጭት መጨመር አስተዋፅኦ አበርክተዋል። እንዲሁም በአንዳንድ የአገሪቷ አካባቢዎች የፀጥታ ችግር መከሰትና በማኅበረሰቡ ዘንድ “ወባ ጠፍቷል”

የሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ መፈጠሩም ለወባ በሽታ መጨመር በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።
በመሆኑም ይህን የወባ በሽታ ስርጭት ለመቀልበስና ብሎም ከአገሪቷ ለማጥፋት የጤና ሚኒስቴር የተለያዩ ስልቶች ነድፎ በመተግበር ላይ ይገኛል። በጤና ሚኒስቴር የወባና ሌሎች ቬክተር ወለድ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዴስክ ኃላፊ አቶ ጉዲሳ አሰፋ በዓለም እና በአገር አቀፍ ደረጃ የወባ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ሥራዎችን የሚጎዱ ተግዳሮቶች መፈጠራቸውን በማንሳት ጤና ሚኒስቴር ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ ቀደም ብሎ በሥራ ላይ የነበረውን ብሔራዊ የወባ በሽታን የማስወገድ ስትራቴጂክ ዕቅድ (NATION- AL MALARIA ELIMINATION STRATEGIC PLAN) በማሻሻል ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል። ስትራቴጂክ ዕቅዱ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር እስከ 2027 ድረስ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን በወባ ምክንያት የሚከሰተውን የሞት ምጣኔ በ50 በመቶ፣ በበሽታው የሚያዙ ሕሙማንን ቁጥር በ60 በመቶ መቀነስ እንዲሁም ዝቅተኛ የወባ ስርጭት ባለባቸው አካባቢዎች ሙሉ ለሙሉ በሽታውን ለማጥፋት ታስቦ የተዘጋጀ ነው።
እንደ አገር ሦሶት ስልቶችን ነድፈን እየሰራን እንገኛለን የሚሉት አቶ ጉዲሳ አንደኛው ከፍተኛ
ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
ጫና ባለባቸው አከባቢዎች ጫናውን መቀነስ መሆኑንና በተጨማሪም ዋነኛው የትኩረት መስክ መሆኑን ይናገራሉ። በዚህ ስልት ከፍተኛ የወባ በሽታ ጫና ያለባቸውን 222 ወረዳዎች በመለየት የበሽታ መከላከልና ቁጥጥር ሥራ ተጠናክሮ እየተሠራ ስለመሆኑ ገልፀዋል። በተለይም በሰሜን ምዕራብ እና በደቡብ ምዕራብ የአገሪቷ አካባቢዎች የሚገኙ ወረዳዎች ከፍተኛ የወባ ጫና ያለባቸው በመሆናቸው ጫናውን ለመቀነስ እየተሰራ ይገኛል። ሁለተኛው የትኩረት መስክ ዝቅተኛ የወባ ስርጭት ባለባቸው አካባቢዎች ሙሉ ለሙሉ ወባን ማጥፋት የሚል ነው። ይህ ሥራ የሚሰራው በአብዛኛው የምስራቁ የአገሪቷ ክፍል ነው። ሶስተኛው ስልት ከዚህ ቀደም በተሠሩ ሥራዎችና በተፈጥሮም ከወባ ነፃ የሆኑ አካባቢዎች ላይ የወባ በሽታ ዳግም እንዳይከሰት የመከላከል ሥራ መሥራት ነው።
የወባ ትንኝ ቁጥጥርን ለማጠናከር ኅብረተሰቡ የመኝታ አጎበር እንዲጠቀም ማቅረብ፣ የቤት ውስጥ የፀረ ወባ ትንኝ ኬሚካል ርጭት ማካሄድና የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ መሥራት፣ የወባ በሽታ ምርመራና ሕክምና አገልግሎት መስጠት፣ የወባ በሽታ ቅኝትና ምላሽ ማጠናከርና ማኅበረሰቡ በወባ መከላከል መቆጣጠርና ማስወገድ ላይ ያለውን ግንዛቤ ማጎልበት የሚያስችሉ የተለያዩ ግንዛቤ መፍጠሪያዎችን ማካሄድ በጤና ሚኒስቴር በኩል የወባ በሽታን ለማጥፋት እየተከናወኑ የሚገኙ ዋና ዋና ተግባራት ናቸው።
በአገራችን 76 ከመቶውን የአገሪቷን የወባ በሽታ ጫና የሚሸከሙት 222 ወረዳዎች ናቸው። በእነዚህ ወረዳዎች የወባ ትንኝ ቁጥጥር፣ ቅኝት፣ ክትትልና ግምገማ በማድረግ በሽታው መጨመር በሚያሳይባቸው አካባቢዎች በወረርሽኝ መልክ ተከስቶ ጉዳት እንዳያደርስ አፋጠኝ ምላሽ እየተሰጠ ይገኛል።
ጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን ብሔራዊ የድንገተኛ አደጋዎች ማስተባበሪያ ማዕከል (National Emer- gency Operation Center) በማቋቋም ወደ ሥራ መግባቱን የገለፁት አቶ ጉዲሳ በዚህም ወቅታዊ የወባ ስርጭትን ለመግታት እየተሠሩ ያሉትን ሥራዎች በየዕለቱና በየሣምንቱ በመገምገም ለክልሎች ግበረ መልስ የሚሰጥ ሲሆን ይህ አገራዊ የትብብር ሥርዓት (Platform) በክልሎችም እስከ ወረዳ ድረስ መዋቅሩን በመዘርጋት ወደ ሥራ የተገባበት መሆኑን አክለዋል። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በአጠቃላይ ከወባ በሽታ ስርጭት ጋር ተያይዞ የሁኔታዎች ግምገማ በማድረግ የሁሉም ክልሎች ጤና ቢሮ ኃላፊዎች፣ የወባ ፕሮግራምን የሚደግፉ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት፣ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በተገኙበት አገር አቀፍ የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል። በዚህም የወባ በሽታ የመከላከልና መቆጣጠር ሥራዎች ትኩረት በማግኘቱ የበሽታው ስርጭት የመቀነስ አዝማሚያ ያሳየ ሲሆን፤ እስከ ታህሳስ 2017 ዓ.ም ድረስ 76 በመቶ የወባ አስተዋፅኦ የነበራቸውን ወረዳዎች ወደ 52 ነጥብ 8 በመቶ ማውረድ ተችሏል።
ከወባ በሽታ መከላከያ መንገዶች አንዱ የመኝታ አጎበር መጠቀም ነው። በዚህም የጤና ሚኒስቴር ለወባ ተጋላጭ ለሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች የመኝታ አጎበሮች ስርጭት እያደረገ ይገኛል። አንድ የመኝታ አጎበር በጥንቃቄ ከተያዘ ከአንድ እስከ

አምሥት ዓመት አገልግሎት መስጠት የሚችል ሲሆን ጤና ሚኒስቴር እንደ ስትራቴጂ የሚከተለው በየሦስት ዓመቱ ምትክ አጎበሮችን ማሰራጨት ነው። ሚኒስቴሩ በ2015 እና 2016 ዓ.ም በጀት ዓመት 19 ነጥብ 7 ሚሊዮን የመኝታ አጎበሮችን ያሰራጨ ሲሆን በ2017 በጀት ዓመትም 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን አጎበሮችን ማሰራጨቱን አቶ ጉዲሳ ገልፀዋል። እነዚህ አጎበሮች የወባ ትንኝ በመከላከል ውጤታማነታቸው የተረጋገጠና የዓለም ጤና ድርጅት ያስቀመጠውን መስፈርት የሚያሟሉ መሆናቸውንም አክለዋል። በተለይም በዚህ ዓመት የተሰራጨው አጎበር ከዚህ ቀደም በነበረው ኬሚካል ሳይሆን በሁለት አዳዲስ ኬሚካሎች የተነከረ፣ በዓይነቱም የተለየና በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ የተደረገ ነው።
በተጨማሪም ጤና ሚኒስቴር ለወባ የተጋለጡና ለወባ ወረርሽኝ ቅርብ የሆኑ ከፍተኛ የወባ ስርጭት የሚከሰትባቸውን ወረዳዎች በመለየት የቤት ውስጥ የፀረ ወባ ትንኝ ኬሚካል ርጭት በማድረግ ላይ ይገኛል። እስከ አሁን በተመረጡ 167 ወረዳዎች የቤት ውስጥ የፀረ ወባ ትንኝ ኬሚካል ርጭት የተደረገ ሲሆን በዚህም ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ቤቶች የኬሚካል ርጭት ተደርጎላቸዋል። የበሽታውን ስርጭት በኅብረተሰቡ ተሳትፎ ለመከላከል በተደረገው ጥረትም የወባ ትንኝ መራቢያ ስፍራዎችን የማዳፈንና የማፋሰስ ሥራዎች ተሠርተዋል። በኅብረተሰቡ ጉልበት ማዳፈን በማይቻልባቸው አካባቢዎች ፀረ-ዕጭ ኬሚካል እንዲጠቀሙ እየተደረገ ነው።
በተያዘው በጀት ዓመት መጀመሪያ ላይ ትንበያ

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
በማድረግ ለወባ በሽታ ምርመራና ሕክምና አገልግሎት የሚውሉ ግብዓቶች ግዥዎች መካሄዳቸውን የገለፁት አቶ ጉዲሳ በዚህም ፈጣን የመመርመሪያ ኪት እና የተለያዩ የፀረ-ወባ መድኃኒቶች ለሁሉም የጤና ተቋማት ተሰራጭቷል ብለዋል። ብሔራዊ የድንገተኛ አደጋዎች ማስተባበሪያ ማዕከል ከተቋቋመ በኋላ ከመድኃኒት እጥረት ጋር ተያይዞ በአንዳንድ አካባቢዎች ሲቀርቡ የነበሩ ቅሬታዎችን በመቀበል በአፋጣኝ መፍታት እንደተቻለ የሚናገሩት አቶ ጉዲሳ ከፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎችም የግብረ ሰናይ ድርጅቶችን በመጠቀም ተደራሽ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የወባ መድኃኒቶች ውጤታማ ስለመሆናቸው በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ በአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩትና በተመረጡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የፈዋሽነት ደረጃቸው በየጊዜው ፍተሻ ይደረግለታል። ይሁንና በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለው የመድኃኒት አጠቃቀም ጉድለት የሚስተዋልበት ነው። መድኃኒቶችን ለቤተሰብ ማጋራት፣ አልፎ አልፎ ወደ ግል ጤና
ተቋማት በመሄድ ደረጃቸውን ያልጠበቁና በኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ያልተመዘገቡ መድኃኒቶችን የመጠቀም ሁኔታም ይስተዋላል። ኅብረተሰቡ እንደዚህ ዓይነት መድኃኒቶችን ከመውሰድ መቆጠብ እንዳለበት የሚመክሩት አቶ ጉዲሳ በጤና ሚኒስቴር የሚቀርቡ መድኃኒቶች ፈዋሽነታቸው የተረጋገጠና ያለ ክፍያ በነፃ የሚቀርቡ መሆናችውን ጠቁመዋል። እነዚህ መድኃኒቶች የጤና ባለሙያዎች በሚሰጡት ትዕዛዝና ምክር መሰረት መወሰድ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
የወባ መተላለፊያ ወቅትን አስመልክቶ በየደረጃው በፌዴራል፣ በክልሎች፣ በወረዳዎችና በቀበሌዎች የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት ባካተተ መንገድ የአድቮኬሲና የማኅበረሰብ ንቅናቄዎች ተካሂደዋል። በእነዚህ የማኅበረሰብ ንቅናቄዎች ከክልሎች ከፍተኛ ኃላፊዎች ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ ለወባ በሽታ ትኩረት እንዲሰጠው በማድረግ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል ይላሉ አቶ ጉዲሳ። በንቅናቄ ሥራው ከፍተኛ ጫና ያለባቸውን አካባቢዎች በመምረጥ ‘የወባ ሣምንት ንቅናቄ’ በሚል በ300 ወረዳዎች ላይ እንዲካሄድ ለክልሎች የቴክኒክና የገንዘብ ድጋፍ ተደርጓል።
በጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች የሚመራ ቡድን ወደ ሁሉም ክልሎች በመንቀሳቀስ ድጋፍና ክትትል አድርጓል። የድጋፍና ክትትሉ ዋና ዓላማ በአጠቃላይ በወባ እና በመጀመሪያ ደረጃ ጤና እንክብካቤ በተጨባጭ መሬት ላይ የተሠሩ ሥራዎችን ማየት፣ ችግሮችን መለየት፣ በቀጣይ የሚያስፈልጉ ድጋፎችን መለየት ነው። በዋናነነት ንቅናቄው እስከ ታችኛው ደረጃ ላይ የሚገኙ የአመራር ኣካላት ለወባ ፕሮግራም ትኩረት እንዲሰጡ፣ ችግሮች ካሉም እንዲፈቱ በተለይም በማኅበረሰብ ደረጃ የሚሰሩ የንቅናቄ ሥራዎችን እንዲመሩ ለማድረግ መሆኑን አክለዋል።
ጤና ሚኒስቴር አገራዊ ስትራቴጂክ ዕቅድ ማዘጋጀቱን ተከትሎ የወባ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተሰራው ሥራ ተጨባጭ ውጤት አስገኝቷል። እንዲያም ሆኖ የወባ በሽታ አሁንም ዋነኛ የኅብረተሰብ ጤና ችግር በመሆኑ በወባ መከላከል፣ መቆጣጠርና ማስወገድ ላይ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ድጋፍ የሚጠይቅ ነው።
የወባ በሽታን ለመከላከል ብሎም ለማጥፋት እንደ አገር እየተደረገ ካለው ጥረት ባሻገር ኅብረተሰቡ የወባ መተላለፊያ ወቅትን በመገንዘብ ራሱንና ቤተሰቡን ከበሽታው መጠበቅ ይኖርበታል። ውሃ የሚያቁሩና በተለይ በመኖሪያ ቤቶች አካባቢ ለትንኝ መራቢያ የሚሆኑ የተከማቹ ውሃዎችን ማፋሰስ፣ እንደ እንሰት ተክልና ሌሎቸ በመኖሪያ አካባቢ የሚገኙ ቁሳቁስ ውሃ በመያዝ ለትንኝ መራቢያ ምቹ እንዳይሆኑ መከታተልና ሁልጊዜ የአልጋ አጎበር መጠቀም የገቢ ነው። አጎበርን ቢያንስ እስከ ሦስት ዓመት ድረስ በአግባቡ መያዝና በትክክል መጠቀም እንዲሁም የወባ ምልክት ሲታይ በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ምርመራ ማድረግና መድኃኒት ሳያቋርጡ መውሰድም መዘንጋት የለበትም።
ፖለቲካ

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
የአፍሪካና አፍሪካዊነት ፋና -

ኢትዮጵያ
በሔኖክ ታደለ
ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካዊነት እንቅሰቃሴ ተፀንሶ እንዲወለድ፤ ከፍተኛ መነሳሳት እንዲፈጠር ያደረጉ ክስተቶችን ያስተገደች አገር ናት። እንቅስቃሴው ለበርካታ አሥርት ዓመታት ፍሬ አፍርቶ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን እንዲወልድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክታለች። ድርጅቱ በዋናነት ያስቀመጠውን የአፍሪካ አገራትን ከቅኝ አገዛዝ የማላቀቅ ግብ እውን አድርጎ በአዳዲስ ግቦች ወደ አፍሪካ ሕብረት ባደገበት ጊዜም ሆነ ከዚያ በኋላ የኢትዮጵያ ድጋፍ በመጠንም ሆነ በዓይነት እየጨመረ ሄዷል።
አገሪቷ ለዘመናት የፓን አፍሪካኒዝም ፅኑ ተሟጋች ከመሆን አልፋ ለፓን አፍሪካ ሕልሞች መሳካትም ሆነ ለአህጉሪቱ ያበረከተችው

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
አስተዋጽኦ አዲስ አበባ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ እንድትሆን አስችሏታል። ይህ ጽሑፍ ኢትዮጵያ ከቅድመ ፓን አፍሪካ እንቅስቃሴ አንስቶ እስከ አሁን ለሕብረቱ ያበረከተችውን እና እያበረከተች ያለውን አስተዋጽኦ ይዳስሳል።
ሣራ ቤርትማን እና ትዕይንተ አፍሪካዊያን
ወቅቱ እ.አ.አ 1810፤ ቦታው ብሪታንያ። የለንደኑ ኤግዚቢሽን ማሳያ አዳራሽ ዓይኖቻቸው እስኪጎለጎሉ ወደ መድረኩ አፍጥጠው በሚጠባበቁ ነጭ እንግሊዛዊያን ጢም ብሎ ሞልቷል። ሰዎቹ ፒካዲሊ ሰርከስ ተብሎ በሚጠራው አዳራሽ የታደሙት እንደ ክፉ አውሬ በብረት ርብራብ ሳጥን ውስጥ እርቃኗን ሆና እንድትታይ የተገደደችውን ጥቁር አፍሪካዊት ሴት ተክለ ሰውነት ለማየት ነው።
ሣራ ቤርትማን ለእነዚህ ተመልካቾች አፍሪካ ውስጥ ከሚገኝ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት የመጣች አፍሪካዊት እንጂ ሌላ አልነበረችም፤ ስለ እርሷ የሰውነት ክብር የሚገደው አንድም አልነበረም። የኤግዚቢሽኑ ዓላማ ሣራ ክብሯ ተደፍጥጦ፣ የሰውነት ክብር አጥታ፣ እርቃኗን በሕዝብ ፊት እንድትቆም በማድረግ አፍሪካዊያን ከዝንጀሮነት ወደ ሰውነት በማደግ ላይ እንዳሉ ማሳየት ነበር።
ወጣቷ ሣራ ከ21 ዓመቷ ጀምሮ በለንደንና በፓሪስ ኤግዚቢሽኖች ከአደገኛና ተናካሽ የአፍሪካ እንስሳት ጋር ለሕዝብ እንድትታይ ተደርጋለች። ክረምት ከበጋ ሳይባል እንደ ተናካሽ አውሬ በሰፊ የብረት ርብራብ ሳጥን ውስጥ እርቃኗን ቆማ ለሕዝብ በመታየት ከፍተኛ ገቢ አስገኝታለች። የተመልካቹ
ቁጥር ሲበዛና የምታስገኘው ገቢ ሲጨምር የተሻለ ክፍያ ሊገኝ ይችላል በሚል ወደ ፓሪስ ተወስዳለች። ምስኪኗ ሣራ በፓሪስ የገጠማት መከራ እጅግ መሪር ነበር፤ በዚህም የተነሳ ወደ ትውልድ አገሯ ደቡብ አፍሪካ መመለስ እንደናፈቃት ሕይወቷ ያለፈው ገና በ26 ዓመቷ ነው።
የሣራ አሳዛኝ ታሪክ በሞቷ ብቻ አላበቃም፤ ከህልፈቷ በኋላ ሰውነቷ ተቆራርጦ በፓሪስ ሙዚየሞች ውስጥ እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ድረስ ለ200 ዓመታት ያህል ለሕዝብ ሲታይ ቆይቷል። ልክ እንደ ሣራ ሁሉ በርካታ ጥቁር አፍሪካዊያን ወጣቶች በመላው አውሮፓ በሚገኙ “የሰው መካነ አራዊቶች” ውስጥ እንደ ክፉ አውሬ በብረት ርብራብ ሳጥኖች ውስጥ ከአፍሪካ ብርቅዬ እንስሳት ጋር ሲጎበኙ ቆይተዋል።
በእጅጉ አሳፋሪ ከሆኑት ምሣሌዎች መካከል እ.አ.አ 1889 በፓሪስ ኤግዚቢሽን መንደር በመቶዎች የሚቆጠሩ አፍሪካዊያን “የጥቁሮች መንደር” ተብሎ በተሰራ ግልጽ መኖሪያ በተመልካቾች መሀከል እንዲኖሩ የተደረገበት ይጠቀሳል። በተመሳሳይ በጀርመን አገር የብርቅዬ እንስሳት ነጋዴው ካርል ሃገንቤክ ከዱር እንስሳት ጎን ለጎን በባርነት የተገዙ ጥቁር አፍሪካዊያንን በማሳየት እጅግ ትርፋማ የነበረበትም እንዲሁ።
እነዚህ ኤግዚቢሽኖች ላይ እንዲታዩ ከተደረጉት አፍሪካዊያን የሚበዙት ከትውልድ መንደራቸውና አገራቸው ርቀው በደረሰባቸው ስቃይ ለሕልፈት ተዳርገዋል፤ ልክ እንደ ሣራ ሞታቸው እንኳን ከውርደትና ከስቃይ ኑሮ አልታደጋቸውም፤ ሰውነታቸው ተቆራርጦ የነጮችን የዘር የበላይነት በሳይንሳዊ ዘዴ ለማረጋገጥ ለሚሰሩ የተለያዩ የምርምር ጣቢያዎች ተከፋፍለዋል።
“የሰው ዘር ተኮር ኤግዚቢሽኖች” ወይም በእነርሱ ቋንቋ “የሰው መካነ አራዊቶች” የአውሮፓዊያን ቅኝ ገዢዎችን የዘር የበላይነት እሳቤ ከፍ ለማድረግና የአፍሪካዊያንን የበታችነት ትርክት ለመገንባት የተደረገ ፕሮፓጋንዳ ነበር። ይህም ነጮቹ ራሳቸውን እንደ ምርጥ ዘር እንዲያዩ በማድረግ የተስፋፊነት ስሜታቸውን በማናር አፍሪካን ለመቀራመት፣ መሬቷን በቅኝ ግዛት ለመያዝ እርስ በእርሳቸው እንዲፎካከሩ አድርጓል።
ለጀግኖች አባቶቻችን ምስጋና ይግባቸውና፤ ኢትዮጵያዊያን ቅኝ ባለመገዛታችን ከዚያ ፍፁም ውርደት ውጭ ሆነን ቆይተናል። ይሁንና ያንን ሁኔታ የመቀየር ዕድል የፈጠረው የበርሊን ጉባዔ ለሌሎች አፍሪካዊያን ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያዊያንም አደጋ ደቀነ።
የበርሊን ጉባዔና የአውሮፓዊያን ሽኩቻ በአፍሪካ
በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ የአውሮፓ ኃያላን የግዛት ይዞታና የኢኮኖሚ የበላይነትን ለማረጋገጥ ርህራሄ የለሽ ፍትጊያ ጀመሩ። ይህ የእርስ በእርስ ፍትጊያ በአውሮፓዊያን መካከል አላስፈላጊ ግጭት መፍጠር ጀመረ። በመሆኑም ስጋቱን ለመቅረፍ የአውሮፓ አገራት አፍሪካን በሰላማዊ መንገድ ለመቀራመት የሚያስችል ድርድር የማድረግ አስፈላጊነት ላይ ግልጽ አቋም ያዙ።
ይህንን ተከትሎ እ.አ.አ. የ1884/85 የበርሊን ኮንፈረንስ ላይ አፍሪካን በሰላማዊ መንገድ የመቀራመት “Scramble for Africa” ዕቅድ ላይ
ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
ስምምነት ደረሱ። ስምምነቱ የአውሮፓ አገራት ያለ እርስ በእርስ ግጭት የአፍሪካን ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት እንዲበዘብዙ፣ ለሚያመርቷቸው ሸቀጦች አዲስ ገበያ እንዲያገኙና የተፅዕኖ ክልላቸውን ያለ እርስ በእርስ ፀብ እንዲያሰፉ ሁኔታዎችን ያመቻቸ ነበር። ስምምነቱ አውሮፓዊያን ቅኝ ገዥዎችን ሲያስማማ አፍሪካዊያን ግን በቅኝ ገዥዎች ይደርስባቸው የነበረውን መከራ ሲበዛ አባሰው።
በዚያ የክፍፍል ስምምነት መዘዝ በርካታ አፍሪካዊያን ብሔረሰቦች ራሳቸውን በተለያዩ ሰው ሠራሽ አገራት ውስጥ አግኝተዋል፤ አስቀድመው የነበሩ ባሕላዊ የንግድ መስመሮች ተዘግተው በአዳዲስ ተተክተዋል፤ የጎሳ ግጭቶችም ተባብሰዋል፤ በርካታ የአፍሪካ ብሔሮች መሬታቸውና የተፈጥሮ ሀብታቸው ተዘርፏል፤ እንደ አልማዝ እና ወርቅ ያሉ ሀብቶቻቸው በገፍ ወደ አውሮፓ ተግዘዋል። ነባር የአፍሪካ መንግሥታት ፈራርሰው በአውሮፓዊያን ቅኝ ገዥዎች ተተክተዋል። እንደ ናሚቢያ በመሳሰሉ አገራት አዲስ የጀርመኖች አገር ለመፍጠር ሲባል መጠነ ሰፊ የዘር ማጥፋት ተፈጽሟል። በዚያ ሳቢያ እስከ አሁን ድረስ በቆዳ ስፋቷ ከጀርመን በእጥፍ በምትበልጠው ናሚቢያ የሚኖረው ሕዝብ ከሦስት ሚሊዮን አይበልጥም - ይህም ከጀርመን ሕዝብ በ27 እጥፍ ያነሰ ነው።
ከዚያም አልፎ በአፍሪካ የተደረገው ሽኩቻ የአፍሪካን ባሕልና ማንነት ሲበዛ እንዲሸረሸር አድርጓል። ብዙውን ጊዜ አገር በቀል ልማዶችን በማፈን ወይም በማግለል የአውሮፓ ኃያላን የየራሳቸውን ቋንቋዎች፣ ኃይማኖቶች እና ማኅበራዊ ደንቦችን በአፍሪካዊያን ላይ እንዲጭኑ አድርጓል። ይህ የባሕል ጥቃት በአፍሪካ ማኅበረሰቦች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል፤ ይህም ለባሕላዊ ቅርሶች መጥፋትና በአንዳንድ ማኅበረሰቦች መካከል የመገለል ስሜት እንዲኖር አድርጓል። በበርካታ የአፍሪካ አገራት የባሕላዊ ሥርዓቶች መስተጓጎል ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ተጽዕኖ አስከትሏል። ችግሩ ተባብሶ ከነፃነት በኋላ እንኳን ለብዙ የአፍሪካ አገራት ፖለቲካዊ አለመረጋጋትና ግጭት መንስኤ በመሆን - እስከዛሬ ዘልቋል።
በአውሮፓዊያን ቅኝ ገዥዎች በዘፈቀደ የተሰመሩ ድንበሮች የግጭትና የውጥረት መንስኤ ሆነው ሲቀጥሉ፤ የኢኮኖሚ ብዝበዛና የፖለቲካ መቆራረጥ ለብዙ የአፍሪካ አገራት ልማት ማነስ እና ለድህነት አስተዋጽኦ አድርገዋል። የዘር መድልዎና የቅኝ ግዛት ሥነ-ልቦናዊ ተፅዕኖ አሁንም በአፍሪካዊያን ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን እንደቀጠለ ነው። የውርደት ታሪኮቹ የአፍሪካዊያንን ቅስም እና ሞራል እንክት አድርገው በመስበር በመላ አህጉሪቱ የተሸናፊነት ስሜት አንግሰው ቆይተዋል።
ታሪክ ቀያሪው የአድዋ ድል
እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና የመሳሰሉት አገራት ግዛታቸውን ሲያስፋፉ ተዳክማ የነበረችው ኢጣሊያ ራሷን አጠናክራ ነፃነቷን ጠብቃ ሳትወረር የቆየችውን ኢትዮጵያን ወረረች። በወረራው ሳቢያ የአፍሪካ ታሪክ በፍጹም ሽንፈት ሊደመደም ጫፍ የደረሰ መሰለ።
ኢትዮጵያዊያን ግን የኃይማኖት፣ የዘርም ሆነ የቋንቋ ልዩነት ሳይገድባቸው ወራሪውን የኢጣሊያን ጦር በታላቅ ሕብረት ተፋለሙ። ያኔ የተፋለሙት ግን ወራሪ ኃይልን ብቻ ሳይሆን የቅኝ ገዥነትን፣ የአውሮፓዊያንን የዘር የበላይነት እንዲሁም የጥቁር ዘር የበታችነት አስተሳሰብን ነበር። ወራሪው

የኢጣሊያ ጦር የቱንም ያህል የተሻለ የጦር መሣሪያ ቢታጠቅም፤ ምንም ያህል ጭካኔ ቢያሳይም በአድዋ ጦርነት ለአገራቸው እና ለሰንደቅ ዓላማቸው ከፍ ያለ ፍቅር ባሳዩት ኢትዮጵያዊያን አሳማኝ በሆነ መልኩ ሽንፈትን ተከናነበ። ድሉ ከድል በላይ ወሳኝ ነበር። በሺህዎች የሚቆጠሩ ወራሪ የኢጣሊያ ወታደሮች ሞቱ፣ ገሚሶቹ ወደኋላ አፈገፈጉ። ኢትዮጵያ በፀረ ቅኝ አገዛዙ ጦርነት አሸናፊ ሆና በመውጣቷ ወራሪዋ ኢጣሊያን በዚያው ዓመት መጨረሻ በተፈረመው የአዲስ አበባ ስምምነት ለኢትዮጵያ ነፃነት በይፋ እውቅና ሰጠች።
አንድ ጥቁር አፍሪካዊ መንግሥት የአውሮፓ ቅኝ ገዢን ጦር ስኬታማ በሆነ መንገድ ሲያሸንፍ የአድዋ ድል የመጀመሪያው ነበር። በመሆኑም የድሉ ብስራት በሠዓታት ውስጥ ዓለምን እንደ ሰደድ እሳት አዳረሰ። የድሉ ዜና ለአውሮፓዊያን ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ለሚገኙ በቅኝ ገዢዎች በደረሰባቸው ጭቆና የላሸቁ ጭቁን ሕዝቦች ጆሮ ደረሰ። የዓድዋ ድል

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
ከኢትዮጵያ ድንበር ተሻግሮ በዓለም አስተጋባ፣ የፓን አፍሪካኒዝም ጥሪ ደወል ሆነ። ቅኝ አገዛዝ ሊገታ የማይችል በሚመስልበት በዚያ ጊዜ አንድነትና ቁርጠኝነት ጭቆናን ማሸነፍ እንደሚያስችል ጽኑ ምስክር ሆነ።
በቅኝ ግዛት ውስጥ የሚገኙ ጥቁሮች ልክ እንደ ኢትዮጵያዊያን ወንድሞቻቸው ሁሉ በዓላማ ጽናት፣ ኃይማኖትና ዘር ሳይገድባቸው፣ የበታችነት ስሜት ሳይሰማቸው ቅኝ ገዢዎችን በጽናት መፋለም ከቻሉ ድል አይቀሬ መሆኑን አስረዳ። በመሆኑም የአድዋው ድል ቅኝ ግዛትን በምን ዓይነት መንገድ እና እንዴት መቋቋም እንደሚቻል ያሳየ ትልቅ ተምሣሌት ሆነ። በርካታ ጥቁር ሕዝቦች ከአድዋ ድል ባገኙት ከፍተኛ መነቃቃት የጥቁሮች የውርደትና የበታችነት ዘመን እንዲያበቃ መሥራት ጀመሩ። ከድሉ በተገኘ መነቃቃት በመላው ዓለም የፓን አፍሪካ እንቅስቃሴ ጎመራ፤ የኢትዮጵያኒዝም እንቅስቃሴ ማንሰራራት ጀመረ።
ይህ ድል የኢትዮጵያን ነፃነት ከማስጠበቅ አልፎ የአውሮፓዊያንን የአይበገሬነት አፈ ታሪክ ሰበረ። አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለማትን የያዘ ሰንደቅ ዓላማ የፓን አፍሪካኒዝም ቀለም፤ የአንድነት እና የነፃነት ምልክት ሆነ። የአድዋ ትሩፋት አህጉር አቀፍ የነጻነት እንቅስቃሴ መሰረት ጣለ።
የአድዋ ድል እና በፓን አፍሪካኒዝም ላይ ያለው ተጽዕኖ
የአድዋ ድል የነጮችን የበላይነት አስተሳሰብ የሰበረ፣ የጥቁሮችን የበታችነት አስተሳሰብ ፉርሽ ያደረገ ብቻ ሳይሆን በካሪቢያን የሚገኙ ጥቁሮች ወደ አፍሪካ መመለስ አለባቸው - አፍሪካም አንድ ልትሆን ይገባል የሚለው አስተሳሰብ እየገነነ እንዲመጣ አደረገ። በዚያ አስተሳሰብ ተመስርቶ በአፍሪካም ሆነ በካሪቢያን በርካታ የነፃነት ታጋዬች ተነሱ።
በቀጣዮቹ አሥርት ዓመታት አድዋ የተቃውሞና የነፃነት ምልክት ሆነ። የአፍሪካ መሪዎችና ምሁራን ከጋናው ክዋሜ ንኩሩማህ እስከ ደቡብ አፍሪካው ኔልሰን ማንዴላ ድረስ ከቅኝ አገዛዝ እስከ ፀረ አፓርታይድ ለጀመሩት ትግል ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው የአድዋ ድል ከፍተኛ መነሳሳት ከፈጠረባቸው ታዋቂ ፓን አፍሪካኒስቶች መካከል የጋናው ክዋሜ ንኩርማን፣ የጃማይካው ማርኩስ ጋርቬይ እንዲሁም የአሜሪካው ደብሊው .ኢ.ቢ ዲቡዋ ይገኙበታል።
ክዋሜ ንኩርማን ‘የአድዋ ድል በአፍሪካ ታሪክ ውስጥ አንድ ትልቅ የታሪክ እጥፋት ነው - አፍሪካዊያን በተባበረ ክንድ ከተነሱ ቅኝ ገዢዎችን ማሸነፍ እንደሚችሉ ያሳየ ታሪካዊ ክስተት ነው’ ሲሉ፤ የጃማይካን ጥቁር ሕዝቦች ወደ አፍሪካ ለመመለስ እንቅስቃሴ ያስጀመሩት ታዋቂው ፓን አፍሪካኒስት ማርኩስ ጋርቬይ እንቅስቃሴ የጀመሩት በአድዋ ድል ተነስተው እንደሆነ አውስተዋል። የአድዋ ድል ያለፍላጎታቸው ወደ ካሪቢያን የተወሰዱ ጥቁሮች አፍሪካዊ ማንነታቸውን ዳግም እንዲጠይቁ ያስቻለና ለአፍሪካ አንድነትና መልሶ ግንባታ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ያነሳሳ ክስተት ነው።
ታዋቂው ጥቁር አሜሪካዊ ፓን አፍሪካኒስት ዲቡዋ ‘አድዋ የዘር የበላይነት አስተሳሰብን የሰበረና የፓን አፍሪካ አንድነትን ያጋጋለ ክስተት ነው’ ብለዋል።
ኢትዮጵያ በለኮሰችው የአድዋ ድል እሣት በተሟሟቁ ፓን አፍሪካኒስቶች እንቅስቃሴ የተነሳ የአፍሪካ አንድነት እንቅስቃሴዎች ተፋፋሙ። ቅኝ ገዢዎች ከአፍሪካ ተባረው አፍሪካ አንድ ትልቅና ጠንካራ አገር እንድትሆን ከየአቅጣጫው ጥረቱ ተጀመረ። እነዚያ የፓን አፍሪካ እንቅስቃሴዎች የኋላኋላ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመስረት የአስተሳሰብ መሠረት ጣሉ። የአድዋ ድል ለተከታታይ አሥርት ዓመታት የጥቁሮች ትግል ቀንዲል ሆኖ ዘለቀ።
በመሆኑም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመሥረት እጅግ አስፈላጊውን የሞራል ስንቅ በማቀበል ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክታለች ማለት ይቻላል።
ለብቻ ከመቆም የተወሰደ ትምህርት
እ.አ.አ በ1935 ኢትዮጵያ ሉዓላዊት አገር እና የሊግ ኦፍ ኔሽን አባል ሆና ሳለ በፋሺስት ኢጣሊያ ሌላ አረመኔያዊ የቅኝ ግዛት ወረራ ተደረገባት። በአውሮፓ ኃያላን የበላይነት የተያዘው ሊግ
ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
ኦፍ ኔሽን ኢትዮጵያ ምንም እንኳን የሊጉ አባል ብትሆንም፤ ሊጉ አንድ አባል አገር ሌላ አባል አገርን መውረርን ቢከለክልም፤ የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ኢትዮጵያን ለማንበርከክ የኬሚካል ጦር መሣሪያና የተከለከሉ መርዞችን ሲጠቀም እንዳላየ ሆኖ አልፏል።
እ.አ.አ. በ1936 በጄኔቫ በተካሄደው የሊግ ኦፍ ኔሽን ጉባዔ ፊት ፍትህን የተማፀኑት የወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ፍትህን ሳያገኙ የቀሩት በሊጉ ውስጥ አብረዋቸው ሊቆሙ የሚችሉ ነፃ የአፍሪካ አገራት ባለመኖራቸው ነበር። ኢትዮጵያ ከጄኔቩ ጉባዔ ያገኘችው ትምህርት የአፍሪካ አገራት ነፃ እስካልወጡ ድረስ፣ ቅኝ ገዢዎች በአፍሪካ ሥልጣን ላይ እስከቆዩ ድረስ፣ የኢትዮጵያም ሉዓላዊነት አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል ነበር። በመሆኑም ኢትዮጵያ ራሷን ከቅኝ ገዢዎች ከመጠበቅ ባሻገር ሌሎች አፍሪካዊያን ለነፃነታቸውና ቅኝ ግዛትን ለመደምሰስ የሚያደርጉትን ትግል መደገፍ እንደሚገባት በግልጽ ያሳየ ክስተት ሆኗል።
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ፀረ-ቅኝ ግዛት ትግሎች የሰጠችው ድጋፍ
ከአምሥት ዓመታት በኋላ ፋሺስቱ የኢጣሊያ ጦር እንደለመደው ሽንፈቱን ተቀብሎ ከኢትዮጵያ ወጣ። ከዚያ በኋላ ለቀጠሉት አሥርት ዓመታት ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ሥር ለሚማቅቁ የአፍሪካ አገራት ዳግማዊ የሞራል ተምሣሌት ብቻ ሆና አልቀረችም ቀጥተኛ ድጋፍ ሰጪ በመሆን፣ በሥልጠና፣ በዲፕሎማሲ፣ ለታጋዮች ጥገኝነት በመስጠትና በመሳሰሉት ረገድ ብርቱ አስተዋጽኦ አድርጋለች። ከዚህ አኳያ በአልጄሪያ፣ በአንጎላ፣ በሞዛምቢክ እና በመሳሰሉት አገራት ለተካሄዱ የነፃነት እንቅስቃሴዎች የዲፕሎማሲ እና የገንዘብ ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር፤ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባልነቷ ያገኘችውን መድረክ በመጠቀም አፍሪካ ከቅኝ አገዛዝ ነፃ እንድትወጣ ለማድረግ ለበርካታ ዓመታት ብቻዋን የአህጉሪቱ ድምጽ ሆናለች።
ጉምቱ-ጉምቱ የፀረ ቅኝ አገዛዝና የፀረ አፓርታይድ መሪዎችንና የነፃነት ታጋዮችንም አሠልጥናለች። የኋላ ኋላ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ለመሆን የበቁት እውቁ የነፃነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ በኢትዮጵያ ወታደራዊ ሥልጠና እንዲወስዱ አግዛለች። ማንዴላ የሕይወት ታሪካቸውን በጻፉበት መጽሐፋቸው ላይ በኢትዮጵያ ያገኙት ሥልጠናና ልምድ ግንዛቤያቸውን እንዴት እንዳሰፋውና እንዳጠናከረው እንዲሁም አፓርታይድን ለመዋጋት ያላቸውን ቁርጠኝነት እንደጨመረው አትተዋል። በተመሳሳይ ከነፃነት ትግል በኋላ የዚምባብዌ ፕሬዚዳንት ለመሆን የበቁት ሮበርት ሙጋቤም አገራቸውን ከቅኝ ግዛት ነፃ ለማውጣት በኢትዮጵያ ሰፊ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል።
ኢትዮጵያ በፋሺስት ኢጣሊያ ላይ ዳግም ድል የተጎናፀፈችበት ኹነት እና በኋላም ለአፍሪካ የነፃነት እንቅስቃሴዎች ያደረገቻቸው ድጋፎች የአህጉሪቱ የተስፋ ብርሃን እንድትሆን አስችሏታል። የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ መሠረታዊ ቀለማት የአፍሪካ አንድነትና የፀረ ቅኝ አገዛዝ ተቃውሞ ምልክት ሊሆን የቻለውም ለዚያ ነው። በርካታ የአፍሪካ አገራት ከቅኝ አገዛዝ ነፃ ሲወጡ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ቀለማት ለራሳቸው ሰንደቅ ዓላማ ተጠቅመውባቸዋል።
የካዛብላንካ እና ሞንሮቪያ ቡድኖች
የአፍሪካ አገራት ከቅኝ ግዛት ነፃ መውጣት መጀመራቸውን ተከትሎ የካዛብላንካ እና ሞንሮቪያ ቡድኖች ተፈጠሩ። ቡድኖቹ ለአህጉሪቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ያላቸው ራዕይ በእጅጉ የተለያየ ነበር። በመካከላቸው የተፈጠረው ያለመግባባት የአፍሪካዊያንን አንድነት አደጋ ላይ ጣለው።
የካዛብላንካ ቡድን አፍሪካ በፍጥነት ልትዋሃድና አንድ ትልቅ፣ ጠንካራ አገር ልትሆን ይገባል በሚሉ አገራት የሚመሩ ናቸው። የካዛብላንካ ቡድን እንደ ጋናው ኩዋሜ ንኩርማህ ባሉ ጠንካራ መሪዎች የሚመራ፣ አፍሪካ ፈጣንና ሙሉ የፖለቲካ አንድነት ሊኖራት ይገባል፣ አንድ ወጥ የሆነ አህጉር፣ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት፣ አንድ የጋራ መገበያያ ገንዘብና የጋራ የመከላከያ ኃይል ያስፈልጋታል የሚል ነበር። ይህ ቡድን እንደ ጋና፣ ጊኒ፣ ማሊ፣ ሞሮኮ፣ አልጄሪያ እና ግብጽ ያሉ አገራትን ያቀፈ ነበር።
የሞንሮቪያ ቡድን ደግሞ ናይጄሪያ፣ ላይቤሪያ እና አብዛኞቹ ፈረንሣይኛ ተናጋሪ የአፍሪካ አገራትን ያካተተ ሲሆን፤ በድንገት ወደ አንድነት ከመምጣት ይልቅ ቀስ በቀስ መዋሃድን የመረጡ አገራት ቡድን ነው። አባላቱ ከማንኛውም የፖለቲካ ውህደት አስቀድሞ በኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ቀስ በቀስ ውህደትና ትብብርን በማምጣት ላይ ያተኮረ ነው። አገራቱ ብሔራዊ ሉዓላዊነት ሊኖራቸው ይገባል የሚሉ አገራት ቡድንም ነበር።
ሁለቱም ቡድኖች ፓን-አፍሪካኒስቶች ቢሆኑም መሠረታዊ ልዩነቶች ነበሯቸው። ይሁንና ሁለቱም ቡድኖች በአፍሪካ አንድነት እና የበለጸገች አፍሪካን እውን በማድረግ ረገድ ሕልማቸው ተመሳሳይ ሲሆን፤ በአካሄዱ ላይ ግን መስማማት አልቻሉም።
ኢትዮጵያ አጀንዳው ሰፍቶ የአፍሪካን መጻኢ ዕድል አደጋ ላይ እንዳይጥል ብርቱ ጥረት አድርጋለች። በመሆኑም ሁለቱን ወገኖች ለማቀራረብና በመካከላቸው ያለውን ልዩነት ለማጥበብ ወሳኝ ሚና ተጫውታለች። ባደረገችው ሰፊ ጥረትም ሁለቱ ወገኞች ልዩነታቸውን እንዲያጠቡ በማገዝ እ.አ.አ በ1963 ኢትዮጵያ ውስጥ፣ ሁለቱንም ሃሳቦች የሚደግፉ የአፍሪካ መሪዎች የተሰባሰቡበትን ጉባዔ በአዲስ አበባ አስተናገደች። ቡድኖቹ ልዩነቶቻቸውን በማጥበብ በዚሁ ጉባዔ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (OAU) ተመሠረተ። በምሥረታው ላይ ኢትዮጵያ ወሳኝ ሚና የነበራት ሲሆን ለአፍሪካ በራስ የመወሰን ጉዞም ትልቅ እርምጃ የሚባል ነው።
ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተመሰረተው ኢትዮጵያ ሁለቱ ቡድኖች ልዩነታቸውን እንደሚፈቱ አስቀድማ እርግጠኛ በመሆኗ አስቀድማ በገነባችው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሕንጻ ውስጥ ነበር፤ ይህም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ያበረከተችው አስተዋጽኦ አካል ነው።
ድርጅቱ ከቋቋመ ጀምሮ በዋናነት በቅኝ ግዛት ሥር ይማቅቁ የነበሩ የአፍሪካ አገራት ነጻ እንዲወጡ ድጋፍ ሰጥቷል። በዚያ ረገድም ኢትዮጵያ እንደ ድርጅቱ አባልነቷ ከቅኝ ግዛት ነፃ ያልወጡ አገራት ነፃ እንዲወጡ ካደረገችው የዲፕሎማሲ፣ የሥልጠና እና የሞራል ድጋፍ በተጨማሪ ነጻ የወጡ የአፍሪካ አገራት ወጣቶች የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ በማድረግ፣ የአየር ክልሎቻቸውን በመጠበቅ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲጠናከር ብርቱ ድጋፍ ስትሰጥ ቆይታለች። የሰላም አስከባሪ በሚያስፈልግባቸው የአፍሪካ አገራት በመሠማራት የአህጉሪቱን ሰላም ለመጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክታለች። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በሥራ ላይ በነበረባቸው 39 ዓመታት የአፍሪካን ውህደት በማቀንቀን፣ የፀረ ቅኝ አገዛዝ ትግሎችን በመደገፍ፣ የድርጅቱን መተዳደሪያ በማጽደቅ ሂደትና የነፃነት ተምሣሌት በመሆን የኢትዮጵያ አስተዋጽኦ የአንበሣውን ድርሻ ይወስዳል።
የኢትዮጵያ አስተዋጽኦ ለአፍሪካ ኅብረት
እ.አ.አ በ2002 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪካ ኅብረት (AU) ሲሸጋገር ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ አንድነት ጉልህ ሚና መጫወቷን በመቀጠል በአፍሪካ ዲፕሎማሲ ግንባር ቀደም ሆና ወጥታለች ማለት ይቻላል። አስተዋጽኦ ካደረገችባቸው ቁልፍ ዘርፎች መካከል የአፍሪካ ኅብረት ዋና መሥሪያ ቤት አስተናጋጅነቷ ተጠቃሽ ነው። አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ ሆና እንድትቀጥል መደረጉ በራሱ ኢትዮጵያ በአህጉራዊ ጉዳዮች ውስጥ ያላትን ማዕከላዊ ሚና ያጎላል። ይህም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት አጀንዳ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደርና የአፍሪካን አንድነት ለማስፈን ራዕይዋን ለማራመድ የተሻለ መድረክ ሰጥቷታል።
በአህጉሪቱ በሚገኙ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎችና ግጭቶችን በመፍታት በተደረጉ በርካታ ጥረቶች ውስጥ በንቃት የተሳተፈችውና አሁን ይህ ተሳትፎዋ የቀጠለው ኢትዮጵያ እንደ ሶማሊያ ሩዋንዳ እና ሱዳን ባሉ አገራት ለተደረጉ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ወታደሮች በማዋጣት ለክልላዊ መረጋጋት ያላትን ቁርጠኝነት አሳይታለች። ኢትዮጵያ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ውስጥ የሚከሰቱ ግጭቶችን በማሸማገልና በተፋላሚ ወገኖች መካከል ውይይት እንዲጀመር በማድረግ ጥረቶች ውስጥም ንቁ ተሳታፊ ነች።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ የኢኮኖሚ ውህደትን በጽኑ የምትደግፍ ሲሆን፤ እንደ አፍሪካ አህጉራዊ የነፃ ንግድ ቀጠና (AfCFTA) ባሉ ውጥኖች ውስጥ በንቃት ተሳትፋለች። በአህጉሪቱ ውስጥ ንግድ እና ኢንቨስትመንትን ለማሳለጥ ክፍለ አህጉራዊ ጠቀሜታ ያላቸውን መሠረተ ልማቶች በመሥራት ላይ መሆኗም ሌላው አስተዋፅኦዋ ነው።
ለአህጉሪቱ ችግሮች የአፍሪካ መሪነት መፍትሄዎችን አስፈላጊነት ዘወትር አፅንኦት በመስጠት፤ የአፍሪካ አገራት በልማት አጀንዳዎቻቸው ላይ የበለጠ ራሳቸውን እንዲችሉና ባለቤትነት እንዲኖራቸው በማሳሰብ “ለአፍሪካ ችግሮች የአፍሪካ መፍትሄዎች” የሚለውን ሀሳብ የምታራምደው
አገራችን፤ በአፍሪካ ዘላቂ ልማት ለማስፈን እየሰራች ሲሆን ትኩረቷን በግብርና፣ በትምህርት እና በጤና አጠባበቅ ዘርፎች ላይ አድርጋለች፤ የራሷን ልምዶችና ምርጥ ተሞክሮዎችም ማካፈል ችላለች። ዘላቂ የልማት ግቦችን (SDGs) ለማሳካት በአፍሪካ ኅብረት ተነሳሽነቶች እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን በማጠናከር፤ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በመፍጠር፤ በተለያዩ ግንባሮች ትብብር እንዲኖር በማበረታታት የጋራ ተግዳሮቶችን ለመፍታትና የጋራ ጥቅሞችን ለማስከበር በሁለትዮሽና ባለ ብዙ ወገን ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ውስጥ የነቃ ተሳትፎ አላት።
እ.አ.አ በ2019 የተጀመረው የአረንጓዴ ልማት ተነሳሽነት በአህጉሪቱ በአካባቢ ጥበቃ ረገድ ኢትዮጵያን ቀዳሚ አድርጓታል። ከ40 ቢሊዮን የሚበልጡ ዛፎችን በዘመቻ በመትከል የደን ሽፋኗን ማሳደግ ችላለች። ውጥኑ በዓለም ትልቅ ከሚባሉ የደን መልሶ ማልማት ዘመቻዎች አንዱ በመሆኑ ይህንን ሰፊ ልምዷን ለጎረቤት የአፍሪካ አገራት በማካፈልና የዛፍ ችግኞችን በመስጠት የደን ሽፋናቸውን እንዲጨምሩ እያገዘች ነው። በተጨማሪም አፍሪካን በታዳሽ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማውጣት ንጽህና ታዳሽ ኃይል በማምረት የአፍሪካ አገራት አስተማማኝና ርካሽ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንዲያገኙ በዚህም የኢኮኖሚ ልማታቸውን እንዲያሳድጉ በመሥራት ላይ ትገኛለች።
በዓለም አቀፍ መድረኮች የአፍሪካን ጥቅም በማቀንቀን በዓለም አቀፍ የባለብዙ ወገን መድረኮች ላይ በቋሚነት የምትሰራው ኢትዮጵያ፤ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አፍሪካ ቋሚ መቀመጫና የላቀ ተሰሚነት እንዲኖራት ከመጣር ጀምሮ የአፍሪካ ኅብረት ወደ G20 እንዲገባ እስከማድረጉ ሂደት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአፍሪካን ድምጽ አጉልታለች።
በጥቅሉ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ለአፍሪካ አንድነት ያበረከተችው አስተዋጽኦ ዘርፈ ብዙ ነው። የአፍሪካ ኅብረት ዋና መሥሪያ ቤትን ከማስተናገድ ጀምሮ ሰላምና ደህንነት በማስፈን፣ የኢኮኖሚ ውህደት በማራመድና በአፍሪካ የሚመሩ መፍትሄዎችን በመደገፍ የአህጉሪቱን አቅጣጫ በመቅረጽ ወሳኝ ሚና መጫወቷን ቀጥላለች።
ኢትዮጵያ ለ2063 አጀንዳ ስኬት
በአፍሪካዊያን የሚመራ አህጉር መፍጠር፤ ሁሉን አቀፍ ዕድገትና ዘላቂ ልማት ላይ የተመሰረተ፣ የበለጸገ፣ የተረጋጋና ሰላማዊ አፍሪካን መገንባት የአፍሪካ ኅብረት የአጀንዳ 2063 ዋነኛ ግቦች ናቸው። ውጥኑ በውስጡ በርካታ ግቦችን ያቀፈ ሲሆን ከአፍሪካ ድህነትና ረሃብን ማስወገድ፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ ጤናና ደህንነትን ማስፋፋት፣ ጥራት ያለው ትምህርት ማዳረስ፣ የጾታ እኩልነትን ማሳካት፣ በቂ ሥራዎች መፍጠር፣ ዘላቂ ኢንዱስትሪያላይዜሽን ማስፋፋት፣ ጠንካራ መሰረተ ልማት መገንባት፣ የአካባቢ ጥበቃን ማረጋገጥ፣ ሰላምንና ደህንነትን ማስፋፋት፣ መልካም አስተዳደር ማስፈን፣ ዴሞክራሲን ማጠናከር፣ ክልላዊ ውህደትን ማሳደግ እንዲሁም አፍሪካን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደማጭነት ያላት ተዋናይ ማድረግ የመሳሰሉት ለአብነት ይጠቀሳሉ።
ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
ኢትዮጵያ ይኸው ውጥን ገና በሃሳብ ደረጃ ከነበረበት ጊዜ አንስቶ ድጋፍ ስትሰጥ ቆይታለች። ለበርካታ አሥርት ዓመታት ለአፍሪካ ስታደርግ እንደቆየችው ሁሉ በቀጣዮቹ የዕቅዱ ዓመታትም በዘላቂ መሠረተ ልማት ላይ ኢንቨስት በማድረግ አህጉሪቱ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካትና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ለምታደርገው ጥረት አስተዋጽኦ ማድረግ ትችላለች። በውጥኑ ላይ ከተቀመጡት ግቦች በሚበዙቱ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ውጤት ስታስመዘግብ የቆየችባቸው ዘርፎች ሲሆኑ በተለይ በመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት፣ በዘላቂ ልማት ግቦችና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በሚደረጉ ጥረቶች ሰፊ ልምድ አላት። ኢኮኖሚዋ በከፍተኛ ደረጃ በማደግ ላይ በመሆኑ በቀጣዮቹ ዓመታትም በርካታ ተጨማሪ ውጤቶች እንደሚገኙ ይጠበቃል። በመሆኑም በዘርፉ ያካበተቻቸውን ሰፊ ልምዶች ለሌሎች የአፍሪካ አገራት በማካፈል ረገድ ሰፊ አስተዋጽኦ እንደምታደርግ እሙን ነው።
የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ድርጅት (IGAD) እና የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (COMESA)፤ አሁን ደግሞ ነፃ የአፍሪካ የንግድ ቀጠና አባል የሆነችው ኢትዮጵያ ሰፊ ገበያ ያላት እንደመሆኗ ማዕቀፉ ሰፊ ተጨማሪ ገበያ የሚፈጥርላት በመሆኑ ውጥኑን ስኬታማ በማድረግ አጀንዳ 2063 ስኬታማ እንዲሆን ታግዛለች፤ ይህም ለአጀንዳው ስኬት እጅግ አስፈላጊ ነው።
ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር ለመገናኘት የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መሠረተ ልማቷን ማጠናከርና ኢንቨስት ማድረግ መቻሏ የክልል ውህደትን የሚያበረታታ ሲሆን የኃይል ውጤታማ ስርጭት ድንበር ተሻግሮ እንዲስፋፋ በማድረግ ኢኮኖሚያዊ ልማትና ትብብርን ያሳድጋል።
በከፍተኛ የታዳሽ ኃይል ሀብት ከኮንጎ በመቀጠል በአፍሪካ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ በመጠናቀቅ ላይ ካለው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ብቻ ወደ ስድስት ሺህ ሜጋዋት የሚጠጋ ኃይል የማምረት ትልም አላት። ይህ ኃይል የአገሪቷን ፍላጎት ሸፍኖ የሚተርፍ በመሆኑ ከምስራቅ አፍሪካ አገራት የኃይል ቋት ጋር በማገናኘት አገራቱ ርካሽ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኙ በማስቻል ክልላዊ የኃይል አቅርቦት ደህንነትና አስተማማኝነትን በማላቅ በአካባቢው የኢንዱስትሪ ልማት እንዲኖር ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ይህ የኤሌክትሪክ ኃይል ኤክስፖርት የማድረግ የኢትዮጵያ ውጥን ከአጀንዳ 2063 ዓላማዎች ጋር የሚጣጣምና ተመጣጣኝና ንጹህ ኃይል ለማግኘት የክልልና አህጉራዊ የኃይል ቋቶች እንዲገናኙ የሚያስችል ነው።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ በውሃ ኃይል ልማትና አስተዳደር ያላትን እውቀትና ልምድ ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች በማካፈል ላይ መሆኑ ይህ የአቅም ግንባታ በአህጉሪቱ ዘላቂ የኃይል መፍትሄዎች ማልማትን ያፋጥናል።
ኢትዮጵያ እየገነባቻቸው የሚገኙት ከጎረቤቶቿ ጋር የሚያገናኙና ድንበር ተሻጋሪ ንግድና የሰዎች እንቅስቃሴን የሚያመቻቹ የመንገድ አውታረ መረቦች ክፍለ አህጉራዊ ንግድንና ውህደትን ያበረታታል፣ ቱሪዝምን ያሳድጋል። በዚህ ረገድ ባለፉት ዓመታት ያስመዘገበችው የመንገድ ልማትና በቀጣዮቹ ዓመታት የሚገነቡ መጠነ ሰፊ የመንገድ ልማቶች አህጉሪቱን በመሠረተ ልማት ረገድ የበለጠ በማስተሳሰር ለ2063ቱ የአፍሪካ
ግብ ትልቅ ስንቅ ይሆናል። ይህ ለሌሎች የአፍሪካ አገራት ሞዴል ሆኖ የአህጉሪቱን የመሠረተ ልማት በማሻሻል የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣናን ውጥን ስኬታማ እንዲሆን ያደርገዋል።
በአፍሪካ የሰላም ማስከበር ዘመቻዎች ውስጥ ሰላምንና ደህንነት በማስጠበቅ ትልቅ አበርክቶ ያላት ኢትዮጵያ በመጪዎቹ ዓመታትም በአህጉሪቱ ሰላምና ደህንነትን በማስፋት ግንባር ቀደም ሚናዋን እንደምትቀጥል እሙን ነው። በተመሳሳይ መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲን በማጠናከር ረገድ ትልቅ እመርታ አሳይታለች። በዘርፉ ከወንድም የአፍሪካ አገራት ልምድ ከመቅሰም ባሻገር የራሷን ልምድ ታካፍላለች።
ባለፉት ዓመታት በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የአፍሪካ አጀንዳዎች ትኩረት እንዲያገኙ ስትጥር የቆየችው ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አቅሟ እያደገ በመምጣቱ ዓለም አቀፍ ተሰሚነቷ እየጨመረ ሄዶ የብሪክስ አባል አገር አድርጓታል። በመሆኑም ብሪክስን ጨምሮ በተለያዩ የባለብዙ ወገን መድረኮች ላይ የአፍሪካን ጥቅም ማስጠበቋን ትቀጥላለች።
የሣራ ቤርትማን መካነ-መቃብር
እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር 1994 በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ሥርዓት ተገርስሶ በፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ የሚመራው የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ (ANC) ሥልጣኑን እንደተረከበ ካከናወናቸው ተግባራት መካከል የፈረንሣይ መንግሥት 200 ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በፈረንሣይ የስቃይ ውርጅብኝ የደረሰበትን የሣራ ቤርትማን አፅም ወደ ደቡብ አፍሪካ እንዲመልስ ዘመቻ ማካሄድ ነበር። ኤ.ኤን.ሲ ለስምንት ዓመታት ባደረገው ያላሰለሰ ጥረት የሣራ ቤርትማን አስከሬን ወደ ደቡብ አፍሪካ ተመልሶ በክብር እንዲያርፍ አድርጓል። ዛሬ የሣራ ቤርትማን መካነ መቃብር በደቡብ አፍሪካ ምስራቅ ኬፕ ክፍለ ሀገር-ሃንክሊ በሚሰኝ ሥፍራ ይገኛል። በ10 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የተገነባው መካነ መቃብሯ በየዓመቱ በብዙ ሺህ በሚቆጠሩ ቱሪስቶች ይጎበኛል።
ኤ.ኤን.ሲ በደቡብ አፍሪካ የፀረ አፓርታይድ ትግል ባደረገባቸው ዓመታት እጅግ ወሳኝ ድጋፍ ካደረጉ አገራት መካከል ኢትዮጵያ በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች። የአፍሪካ አባት እስከመባል የደረሱት የነፃነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ ኢትዮጵያ ውስጥ በኮልፌ ፈጥኖ ደራሽ ቅጥር ግቢ ወታደራዊ ትምህርትና ሥልጠና ወስደዋል። ማንዴላ የትግል ታሪካቸውን አስመልክቶ በጻፉት መጽሐፍ በኢትዮጵያ የወሰዱት ሥልጠና ፓርቲያቸውን ውጤታማ እንዲያደርጉ እንዳገዛቸው ገልጸዋል። ለዚህም ነው ከዓመታት እስር እንደተፈቱ ኢትዮጵያን የጎበኙት።
በኢትዮጵያ ድጋፍ ስኬታማ የሆኑት ማንዴላ የሣራ ቤርትማን አጽም ለበርካታ ዓመታት በግዞት ከቆየበት ፈረንሣይ ወደ ትውልድ አገሯ እንዲመለስ ማድረጋቸውና የደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች ከነጭ አገዛዝ ነፃ እንዲወጡ በማስቻላቸው - ኢትዮጵያ የሣራ ቤርትማን አጽም ወደ ሀገሩ ተመልሶ በክብር እንዲያርፍ ብቻ ሳይሆን አዲሱ የደቡብ አፍሪካ ትውልድ ከነጮች የበላይነት ጭቆና ተላቆ በአፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ እንዲገነባ ማገዟ አገራችን ለአፍሪካ የነፃነት ታሪክ ያበረከተችው ትልቅ አስተዋጽኦ ውጤት ነው ማለት ይቻላል።
ማኅበራዊ

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
የዓይን ሕክምና ክፍሉ ጉዞ
(በአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እና በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ትብብር የተዘጋጀ)

የዓይን ሕክምና ክፍሉ ጉዞ
ወደ ቴሪሸሪ. . .
የአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የዓይን ሕክምና ክፍል አመሰራርት ከሆስፒታሉ ታሪክ ጋር የተቆራኘ ነው። ሆስፒታሉ ሲመሰረት በተለይ ከስጋ ደዌ ሕክምና አገልግሎት ጋር በተያያዘ ሲሆን የአገልግሎት አድማሱን በማስፋት አሁን ከ29 አይነት በላይ የሕክምና አገልግሎቶችን በመስጠት ይታወቃል።
የዚህ ስመጥር ሆስፒታል አመሰራረት እንዲህ ነው፤ . . . አፄ ኃይለሥላሴ የስጋ ደዌ ሕመምን በዘላቂነት ለመከላከል፣ ሕሙማኑም የሕክምና ዕርዳታ የሚያገኙበትን መንገድ ለማመቻቸት በማሰብ ሆስፒታሉ አሁን በሚገኝበት (ዘነበወርቅ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ) ለስጋ ደዌ ሕሙማን አገልግሎት የሚሰጥ የሕክምና ማዕከል መቋቋም

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
እንዳለበት ወሰኑ። ይህን ሃሳባቸውንም ዶ/ር ቶማስ ላምቤ ለሚሰኝ ሚሲዮናዊ አጋሩት።
ዶክተር ቶማስ ላምቤ የንጉሡን ፍላጎት በመረዳት እንቅስቃሴ አደረገ። በ1924 ዓ.ም በዶክተሩ አስተባባሪነትና በኢትዮጵያ መንግሥት ጥረት የስጋ ደዌ ሕክምና ማዕከሉ ግንባታ እውን ሆነ። ከሁለት ዓመት በኋላም ይኸው የስጋ ደዌ ሕክምና ማዕከል በንጉሡ ሴት ልጅ ስም “ልዕልት ዘነበወርቅ መታሰቢያ ሆስፒታል” ተብሎ ተሰየመ። ሆስፒታሉ የስጋ ደዌ ሕክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ እያለ እ.አ.አ በ1965 ዓ.ም ስለ ሆስፒታሉ የሰሙ የአፍሪካ መሪዎች ለንጉሡ አንድ ሀሳብ አቀረቡላቸው፤ ሀሳቡ የስጋ ደዌ ሕክምና ሆስፒታሉ የአፍሪካ ማሠልጠኛ ማዕከል ይሁን የሚል ነበር። አፄ ኃይለሥላሴ በሀሳቡ መስማማታቸውን ተከትሎ ዓለም አቀፉ የስጋ ደዌ
ሕክምና ኮሚቴም ድጋፍ በመስጠቱ ሆስፒታሉ የመላው አፍሪካ የስጋ ደዌ መከላከያና የሥልጠና ማዕከል ሆነ። ስያሜውም አለርት ተሰኘ።
የአሁኑ “አለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል” አለርት (ALERT) የሚለውን ስያሜ ያገኘው (All Africa Leprosy, Tuberculo- sis and Rehabilitation Training) ከሚለው የእንግሊዝኛ ስያሜው አህፅሮተ ቃል ነው።
አለርት ከመነሻው ከስጋ ደዌ ሕመም ጋር ለተያያዙ የጤና እክሎች ሕክምና ለመስጠት የተቋቋመ ቢሆንም በሒደት ግን አጠቃላይ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጥ ሆስፒታል ሆኗል። ከዚያም ባሻገር በጤናው ዘርፍ የምርምር ሥራዎችን ያከናውናል፤ የሥልጠና አገልግሎትም ይሰጣል።
ከዚህ አኳያ ለጤናው ዘርፍ ብቁ ባለሙያዎችን በማፍራት ለአገር ዕድገት ባበረከተውና እያበረከተ ባለው አስተዋፅኦ ወደር አይገኝለትም። የሕክምና፣ የምርምርና የሥልጠና አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም ለመሆንና አሁን የሚገኝበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ዓመታትን ተጉዞ በርካታ የስኬት ምዕራፎችን ተሻግሯል።
በበርካታ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ዘወትር የሚታወስና የማይዘነጋ ብቻ ሳይሆን፤ በአፍሪካ አህጉርም በጤናው ዘርፍ ስሙ የገነነ ተቋም ነው። በኢትዮጵያ ቀደም ካሉት ጊዜያት ጀምሮ ከስጋ ደዌ ሕመም ጋር ለተያያዙ የጤና ችግሮች መፍትሔ ከመስጠት ባሻገር በዘርፉም ብቸኛው የሕክምና የጥናትና ምርምር ማዕከል ሆኖ ከዘጠና ዓመታት በላይ ዘልቋል።
በበርካታ አይነት የሕክምና አገልግሎቶቹ ራሱን እያበቃና እያሳደገ የሚገኘው ይህ ሆስፒታል በአዲስ አበባ በተለምዶ ዘነበ ወርቅ በሚባለው አካባቢ ከፍታ ላይ በሚገኝ ስፍራ ላይ ይገኛል። መልክዓ ምድራዊ አቀማመጡ ባማረ፣ በነፋሻማ አየር በታጀበ ሰፊ ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኝ፣ በአንጋፋ ዕድሜው ለበርካቶች ጤናማ ሕይወት ያጎናፀፈ፣ የመኖር ተስፋን ዳግም ያለመለመና እያለመለመ የሚገኝ የፈውስ መንደር ነው።
አለርት በ1981 ዓ.ም የዓለም ጤና ድርጅት የስጋ ደዌ ማሠልጠኛ ተባባሪ ማዕከል ሆነ። ይህን መሰል ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘቱ ለዕድገቱ አዎንታዊ ሚና መጫወቱ አልቀረም። ሆስፒታሉ ከሕክምናና ከሥልጠና አገልግሎት ባሻገር የምርምር ሥራዎችንም እንዲያከናውን እ.አ.አ በ1970 ዓ.ም የአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩትን በመክፈት መንቀሳቀስ ጀመረ። ከሀገራዊ የስጋ ደዌ ማዕከልነት ወደ አህጉራዊ ተቋምነትም የተሸጋገረው የአለርት ማዕከል፣ በሥልጠናና በምርምር ሥራዎች በአፍሪካ እየተስፋፋ የመጣውን የስጋ ደዌ የጤና ችግር ተፅዕኖ ለመቀነስ ጉልህ ሚና አበርክቷል።
በሆስፒታሉ ከስጋ ደዌ ሕክምና አገልግሎት ጎንለጎን ከሚሰጡ የሕክምና አገልግሎቶች መካከል የዓይን ሕክምና ክፍል አንዱ ነው። የስጋ ደዌ ሕመም ቆዳን፣ ዓይን እና ሌሎች የሰውነት ክፍሎችን የሚጎዳ በሽታ ነው። በዓይኖቻችን ብሌን ውስጥ የሚገኙት ስሜትን የሚፈጥሩ ነርቮች በስጋ ደዌ ከተጎዱ ጉድፍ ቢገባባቸውም የሕመም ስሜት አይኖራቸውም። ዓይናችን መኖሩ ደግሞ ከዓይን ዕንባ ተግባራት ጀምሮ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው የሰውነታችን ክፍሎች ናቸው። ዓይንን ማለስለስ፣ በውስጡ ያለው ኬሚካልና የሚገቡ ጀርሞችን
ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
መግደል፣ አቧራን አጥቦ ማስወጣት፣ ኦክስጅንን በፈሳሽነት ወስዶ ወደ ምግብነት ማድረስ ከዓይን ዕንባ ተግባራት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
የሆስፒታሉ የዓይን ሕክምና ክፍል ከ45 ዓመታት በፊት ዓይነ ስውርነትን ለመከላከል የሚያደርገው ጥረት ተከትሎ Christian Blind Mission (CBM) በተሰኘው የበጎ አድራጎት ድርጅት አማካኝነት የተቋቋመ ነው።
ክፍሉ ከዚህ ቀደም ባለው ጊዜ 30 ቁጥር እየተባለ በሚጠራው ቦታ ላይ በጥቂት የሕክምና ባለሙያዎች አገልግሎቱን የተጀመረ ሲሆን ወደተለያዩ ክልሎች በመሄድ የቀዶ ሕክምና ይሰራ ነበር። በወቅቱ የነበረው የሕክምና ክፍል ለስጋ ደዌ ታካሚዎች ብቻ ከሚውል ተገልጋዩ ማኅበረሰብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበዛ በመሄዱ በChristian Blind Mission /CBM/ የበጎ አድራጎት ድርጅት ሕክምናውን ተደራሽ ለማድረግ አሁን በሚገኝበት ስፍራ ላይ ህንፃ ተሰራ።
በዚያን ጊዜ አምስት አልጋዎች ብቻ የነበሩት የሕክምና ክፍሉ አሁን 17 የሴቶች እና 17 የወንዶች በድምሩ 34 አልጋዎች፣ እያንዳንዳቸው ሁለት ሐኪሞችና አምስት ነርሶች የሚገኙባቸው አምስት የመመርመሪያ ክፍሎች አሉት። በክፍሉ ስምንት ስፔሻሊስቶች፣ ሰባት ኦርቶሜትሪስት፣ በዓይን ሕክምና ሙያ ለአንድ ዓመት የሰለጠኑ ሰባት ኦፍታልሚክ ነርሶች፣ አንድ ካታራክት ሰርጂን በአጠቃላይ ከ50 በላይ የተለያዩ ባለሙያዎችን ይዞ በቀን ከ260 በላይ ተገልጋዮችን በማስተናገድ ላይ ይገኛል።
በተመላላሽ ሕክምናም የሞራ ግርዶሽ፣ ግላኮማ፣ የመነፅር ምርመራ፣ የሞራ ቀዶ ሕክምና፣ የዓይን ግፊት ምርመራና ሌሎችም አገልግሎቶች ይሰጣሉ። ማንኛውም የቀዶ ሕክምና (Sur- gery) የሚሰራለት ታካሚ ባዮሜትሪ ይታያል፤ ዕድሜው ከ45 ዓመት በላይ የሆነ ታካሚ የዓይን ግፊት ምርመራ ይደረግለታል፤ የደም ግፊት ካለው ደግሞ የነርቭ ምርመራም ይደረጋል፤ የመነፅር አገልግሎት የሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች ምርመራ ተደርጎላቸው ይታዘዝላቸዋል . . . እነዚህ የሕክምና አገልግሎቶች በዓይን ክፍል የሚሰጡ ናቸው።
የዓይን ሕክምና ክፍሉ የሚሰጠው Optical coherence tomography (OCT) ምርመራ አገልግሎት ከሌሎች ሆስፒታሎች ልዩ ያደርገዋል። ይህ የሕክምና መሣሪያ የዓይናችንን ውፍረት፣ የነርቩን ሁኔታ ሬቲናው ምን ላይ እንዳለ የሚያሳይ ነው። ከቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅና ከተለያዩ ሆስፒታሎች ወደ አለርት የዓይን ሕክምና ክፍል የሚላኩ ተገልጋዮች ተመርምረው ውጤታቸውን ይዘው ይወስዳሉ።
በዋናው የዓይን ቀዶ ሕክምና ክፍል አራት የቀዶ ሕክምና አልጋዎች የሚገኙ ሲሆን አራት ሐኪሞች በአንድ ጊዜ አገልግሎቱን ይሰጣሉ። በሌላኛው ክፍል ደግሞ የዓይን ቀዶ ሕክምና ላይ መጠነኛ ጉዳቶች ሲደርሱ የሚሰሩ ሲሆን ሁለት ባለሙያዎችም ይገኛሉ።
አለርት ከአዲስ አበባ በተጨማሪ የዓይን ሕክምና አገልግሎት በስፋት ባልተዳረሰባቸው ክልሎች በሚገኙ ለምሣሌ በቦረና፣ ወረኢሉ፣ ግንደበረት፣ ኢጀጅ፣ ዶዶላ እና ሌሎችም አካባቢዎች ባለሙያዎችን በመላክ የዓይን ሞራ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት በነፃ ይሰጣል።
ሌላው በመንግሥት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት
ቤቶች የዓይን እይታ ምርመራ በማድረግ መነፅር የሚያስፈልጋቸው ከሆስፒታሉ የሚያገኙበት ነው። በዚህ በዚህ አገልግሎት በ2016 ዓ.ም በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ከ52 ሺህ በላይ ተማሪዎች ምርመራ ተደርጎላቸዋል። ይህም ዓይነ ስውርነትን መከላከል ብቻ ሳይሆን ከቅርብና ከሩቅ የማየት ችግር ባጋጠማቸው ተማሪዎች ላይ ሊደርስ የሚችለውን የዕይታ ችግር ከወዲሁ ለማስወገድ የተደረገ ነው። በዚህም ከጥቁር ሰሌዳ ላይ ማየት እየተቸገሩ ከጎደኞቻቸው የሚፅፉ ተማሪዎችን ችግር መቅረፍ ተችሏል። ከዚህ እሳቤ በመነሳት የሚሰጠው አስቀድሞ የመከላከል የልየታ ሕክምና አለርትን ከሌሎች ሆስፒታሎች ለየት የሚያደርገው አንዱ ተግባር ነው።
የተማሪዎች የዓይን ምርመራና የመነፅር ግዥን በተመለከተ የመነፅር ዋጋ ገበያው ላይ ውድ በመሆኑ በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ ጥራቱን የጠበቀ ማምረቻ ሥራ እንዲጀምር ተደርጓል። በመነፅር ማምረቻው መነፅር የሚሰሩ ሁለት ባለሙያዎች እንዲሁም አንድ አስተርጓሚ (የምልክት ቋንቋ ባለሙያ) አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።
የዓይን ሕክምና ክፍሉ ደረጃውን የጠበቀ የሕፃናት የዓይን ሕክምና ማዕከል በማስገንባት ላይ ሲሆን በቅርቡ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል።
የዓይን ሕክምና አገልግሎት በጥምረት ለመስጠት በጤና ሚኒስቴርና በሲቢኤም ድርጅት የተመሰረተውን ክላስተር የሚመራው አለርት ሆስፒታል ነው። በውስጡም ቦሩሜዳ፣ ወልድያ፣ ወሊሶ፣ አዳማ፣ ደብረማርቆስና ሌሎችም 12 ሆስፒታሎች ይገኙበታል። ለዚህም በሲቢኤም ድጋፍ የሚያገኙ ሆስፒታሎችን የማስተባበር፣ በጀቱን በአግባቡ እንዲጠቀሙ የማድረግ፣ የተለያዩ መድኃኒቶችና ግብዓቶች እጥረት እጥረት ሲፈጠር እንዲሟሉ በማስተባበር የሚያከናውናቸው ተግባራት ልዩ የሚያደርጉት ናቸው።
በተጨማሪም የዓይን ሕክምና ክፍሉ በሰው ሃብት ግንባታ ረገድ ለጠቅላላ ሐኪሞችና ነርሶች፣ ከሌሎች ክልሎች ለሚመጡ ባለሙያዎች መሰረታዊ የዓይን ሕክምና አሰጣጥ ሥልጠና ይሰጣል። ይህም የዓይን ሐኪሞች በሌሉበት አካባቢ ቀለል ያሉ የዓይን ሕመም ችግሮችን ማከም እንዲችሉና ከበድ ያለ የቀዶ ሕክምና የሚያስፈልገውን ወደ ሆስፒታል እንዲልኩ ለማስቻል ነው።
በሆስፒታሉ በየዕለቱ ለሕክምና የሚመጡ ተገልጋዮች ወደ ሕክምና ክፍሎች ከመሄዳቸው በፊት በመቆያ ቦታዎች ላይ ዓይነ ስውርነትን ሊያስከትሉ በሚችሉ እንደ ሞራ፣ ግላኮማና ሌሎች በሽታዎችን አስመልክቶ ማኅበረሰቡ ምን ማድረግ አለበት? እንዴት መከላከል ይቻላል? በሚሉት ላይ ተከታታይ የጤና ትምህርቶች ይሰጣሉ።
የአለርት ሆስፒታል እነዚህ ሁሉ ጥረቶች ጥረት የዓይን ስፔሻላይዜሽን ተቋም ለመመስረትና የሕክምና ክፍሉን ወደ ቴሪሼሪ አይ ኬር ዩኒት (እንደ የዓይን ሞራ ግርዶሽ እና ግላኮማ አጣዳፊ ሕክምና እንዲሁም በስፔሻሊስት ሐኪሞች የሚሰጥ ከፍተኛ ሕክምናና ልዩ ክትትል የሚሰጥበት) ከፍ በማድረግ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር የስፔሻላይዜሽን የትምህርት ፕሮግራም የመጀመር ግብ ተግባራት ናቸው።
ማኅበራዊ

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
ምስለ ሕክምና ለጤና ባለሙያው
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ እና በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ትብብር የተዘጋጀ

የላቀ ክህሎት
በመንገሻ ገ/ሚካኤል
በምስለ ሕክምና (Simulation) የተመሰረተ የሕክምና ሥልጠና በጤና ሳይንስ ሥርዓተ-ትምህርት ዝግጅት አንዱ የማስተማሪያ ዘዴ ነው። ምስለ ሕክምና ወይም በእንግሊዝኛ አጠራሩ Simulation የምንለው በሰው አካላት ተመሳስለው በተሰሩና የሰው አካል ክፍል የሚያከናውናቸውን ተግባራት ከእውነታው ጋር በሚመሳሰል መልኩ በማየት፣ በመሞከር፣ በመስራት እና ግብረ መልስ በማግኘት ጭምር ትምህርት የሚሰጥበት መንገድ ሲሆን፤ የጤና ባለሙያዎች ወደ ውስብስቡ የሕክምና ዘርፍ ከመሰማራታቸው በፊት አስፈላጊውን ክህሎት የሚያገኙበት የማስተማሪያ ዘዴ ነው።

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
በምስለ ሕክምና (Simulation) ላይ የተመሰረተ ሥልጠና በሕክምና ትምህርት ልምምድ ወቅት በታካሚዎችና በተማሪዎች ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ጉዳቶችን ለመቀነስ ታስቦ የሚሰጥ የሥልጠና አይነት ነው። ይህም በየመስኩ የሚገኙ የጤና ሳይንስ ባለሙያዎች ወደ ሥራ ዓለም ከመሰማራታቸው በፊት በመደጋገም እና በመሞከር እውቀት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። ለጀማሪዎች ብቻ ሳይሆን በሥራው ላይ ለሚገኙ የሕክምና ባለሙያዎችም ዓይነቱ ይለያይ እንጂ በምስለ ሕክምና (Simula- tion) ትምህርት (ሥልጠና) ይሰጣቸዋል።
በፋብሪካ የተመረቱና በኮምፒዮተር የሚታገዙ የሰው ምስለ አካል እንዲሁም ከተለያዩ ቁሳቁስ ምስለ ሕክምና ሞዴሎችን በመስራትና በማሳየት ማስተማር ይቻላል። በተጨማሪም በእንስሳት አካል ላይ የተመሰረተ የምስለ ሕክምና ትምህርት ይሰጣል። በግ እና አሳማን በእንስሳት አካል ላይ ለሚሰጠው የምስለ ሕክምና ትምህርት አብነት መጥቀስ ይቻላል። በእንስሳት አካል የቀዶ ሕክምናን ማስተማር በሕክምና ትምህርት ቤቶች ተመራጭ መንገድም ነው።
የጤና ተቋማት በየጊዜው የሠራተኞቻቸውን አቅም ለማጎልበትና አዳዲስ የሕክምና ትምህርት ምሩቃን ወደ መደበኛ ሥራ ከመሰማራታቸው በፊት የተግባር ልምድ የሚቀስሙበት የምስለ ሕክምና (Simulation) የሕክምና ክህሎት ማሠልጠኛ አላቸው። በዚህ ፅሑፍ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም የሕክምና ኮሌጅ የምስለ ሕክምና (Simulation) እና የሕክምና ክህሎት ማሠልጠኛ ማዕከልን በወፍ በረር እንቃኛለን።
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም የሕክምና ኮሌጅ የምስለ ሕክምና እና የሕክምና ክህሎት ማሠልጠኛ በተቋሙ ውስጥ በትምህርትና ምርምር (Academic and Research) ዘርፍ በዳይሬክቶሬት ደረጃ የሚገኝና የተቋሙ ተማሪዎች፣ ሠራተኞች እንዲሁም የጤና ባለሙያዎች የሕክምና
ክህሎታቸውን የሚያሳድጉበት ማዕከል ነው። በተጨማሪም የክህሎት ግምገማና የመመዘኛ ፈተናዎች ይሰጡበታል፤ ከጥናትና ምርምር ጋር የተገናኙ ሥራዎችንም ይሰራል።
በታካሚዎች ላይ የሚደርሱ ማናቸውንም አይነት አካላዊና ሥነ-ልቦናዊ ጉዳቶች መከላከል፣ ተማሪዎች አስፈላጊውን ክህሎት የሚያገኙበትን ዕድል መፍጠር እንዲሁም ሁሉም ተማሪዎች ከትምህርታቸው ጋር የተገናኘውን የሕክምና ክህሎት እንዲያዳብሩ ማስቻል የሥልጠና ማዕከሉ የተቋቋመበት ዋና ዓላማ ነው።
በምስለ ሕክምና (Simulation) እና የሕክምና ክህሎት ማሠልጠኛ ማዕከሉ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የሕክምና ክህሎቶችን ለማስተማር እንዲያግዙ በፋብሪካ የተመረቱ፡ በቀላሉ በአካባቢ ከሚገኙ ቁሳቁሶች የተሰሩና በኮምፒዩተር በመታገዝ ድምጽ የሚያውጡ መሣሪያዎች ተደራጅተዋል። አሻንጉሊት መሰል ማስተማሪያዎቹ ደም መቅዳት፣ ለሕሙማን ግሎኮስ መቀጠል፣ የሰው የአካል ክፍልን በግልጽ በማሳየት የተለያዩ የሕክምና መሰረታዊያንን ለማስተማር ያግዛሉ። ሌሎቹ ደግሞ በኮምፒዩተር በመታገዝ በሕመም ወቅት የሚከሰት የአተነፋፈስ፣ የልብ ምት ሥርዓትና የደም ግፈት መጠንን የሚያሳዩ ሲሆኑ ድምፅ በማውጣት የሚናገሩም ይገኙበታል።
የሥልጠና ማዕከሉ የአንድ የጤና ተቋምን መሰል ሕክምና መስጫ ክፍሎች የሚገኙበት ነው። የክፍሎቹ አደረጃጀት የሕክምና አካባቢ ገጽታን የተላበሰ ነው። እነዚህ ክፍሎች ሁሉንም በጤና ጣቢያ ወይም በሆስፒታል የሚገኙ እንደ የጽኑ ሕሙማን፣ የቀዶ ሕክምና፣ የእናቶችና ሕፃናት፣ የሕፃናት እና የተመላላሽ ሕክምና ክፍሎችን ይዘዋል። እያንዳንዱ ክፍል የራሱ በልዩ ልዩ መንገዶች የሚሰሩ ምስለ ሕክምና መሳሪያዎችን ያካተተ ነው።
የሕክምና ኮሌጁ የምስለ ሕክምና (Simulation) ክህሎት ማሠልጠኛ ለሕክምና ክህሎት ሥልጠና ከሚጠቀምባቸው የተለያዩ ሞዴሎቹ በተጨማሪ እንስሳትን እንደ ግብዓት በመጠቀም ትምህርት ይሰጣል የሚሉት የማዕከሉ ዳይሬክተር ወ/ሮ ልዩጌጥ አበበ በተለይ የቀዶ ሕክምናን ለማስተማር በእንስሳት አካል ማሳየት ውጤታማ እንደሆነ ይገልፃሉ።
የቀዶ ሕክምና ክህሎትን ለማዳበር በግ በማረድ ተማሪዎች በአንገት ላይ የሚሰራ የአየር ቱቦ፣ የደረት እንዲሁም በአንጀት ላይ የሚደረጉ የቀዶ ሕክምና አይነቶችን እንዲለማመዱበት ይደረጋል። በሰው ላይ እንደሚሰራ ዓይነት ተመሳሳይ የሕክምና መሣሪያ ተጠቅሞ በበግ ዓይን፣ በአሳማ አንጀት ላይ የቀዶ ሕክምና ይሰራል። እግር የመቁረጥ አይነት የሕክምና ቅደም ተከተሎችን (Procedures) ለማስተማር ደግሞ በሸንኮራ አገዳ ላይ ልምምድ እንደሚደረግ የገለጹት ዳይሬክተሯ ከእነዚህ በተጨማሪ በሥራ ክፍሉ የተፈበረኩ የተለያዩ ማስተማሪያ ሞዴሎች እንዳሏቸው ይናገራሉ።
የጤና ተማሪዎች ወደ መደበኛው የሕክምና ሥራ ከመግባታቸው በፊት በሲሙሌሽን ላይ የተመሰረተ የሕክምና ትምህርት እንዲለማመዱ የሚደረገው ጥራት ያለው ባለሙያ ለማፍራትና ወደ እውነተኛው ሥራ ሲቀላቀሉ ቶሎ ለመልመድ ያስችላቸዋል፤ ሥራቸውንም ወደፊት በተግባር
ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
ዳር ያደርሳሉ በሚል የሳይንሳዊ የማስተማር ዘዴ ትምህርት እሳቤ አንዱ በመሆኑ ነው። በዚህ ዓይነት መንገድ ሕክምናን በማስተማር በየትኛውም የሕክምና ትምሀርት ቤቶች ማስተማር የሰርክ ተግባር ነው።
ተማሪዎች የንድፈ ሀሳብ ትምህርት ተከታትለው በቀጥታ በጤና ተቋም ውስጥ ሥራውን ቢጀምሩ በቂ ክህሎት ስለማይኖራቸው የሕክምና ስህተት ሊፈጥሩ ያችላሉ። የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ጭንቀት ስለሚታይባቸው እነሱም በቶሎ ወደ ሕክምና ሥራ ለመግባት ፈቃደኛ አይሆኑም። በዚህ ረገድ የሕክምና ኮሌጁ የምስለ ሕክምና (Simulation) ይህንን ችግር ለመቅረፍ ዓይነተኛ መፍትሄ እንደሆነ የትምህርት ባለሙያዎች ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ።
በጥሩ የምስለ ሕክምና (Simulation) የተማሩ ሠልጣኞች ወደ ሥራ ሲሰማሩ አይቸገሩም። በምስለ ሕክምና የተለማመዱ የሕክምና ባለሙያዎች ውጤታማ መሆናቸውን በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ያመለክታሉ።
የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም የሕክምና ኮሌጅ የምስለ ሕክምና እና የሕክምና ክህሎት ማሠልጠኛ ማዕከል የሚሰጠው አገልግሎት ከዓመት ወደ ዓመት እየጨመረ መጥቷል። ባለፈው ዓመት ብቻ የውጭ ሠልጣኞችን ሳይጨምር ስድስት ሺህ የሚጠጉ ባለሙያዎች ሠልጥነዋል።
እነዚህ ሠልጣኞች በተለያዩ ፕሮግራሞችና ጊዜ አገልግሎት ያገኙ ናቸው። በማዕከሉ የሠልጣኞች ብዛት በዚህ ዓመት ከ20 በመቶ በላይ ጭማሪ እንዳለ የሚያመላክተው የማዕከሉ ሪፖርት ቀደም ሲል ሥልጠናውን ሲጠቀሙ ያልነበሩ የትምህርት ክፍሎችም አገልግሎቱን እያገኙ መሆኑ ተገልጿል።
በሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የሚታዩ የሕክምና ስህተቶችን ለመቀነስ ማዕከሉ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው። ወ/ሮ ልዩጌጥ የባለሙያዎችን የተግባቦትና የሙያ ክህሎት በማጎልበት ውጤታማ ሥራ እየተሰራ እንደሆነ ይናገራሉ። አሁን አሁን በሆስፒታሎች በሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ዘንድ የሚስተዋለውን የብቃት ችግር ለመቅረፍና በኮሌጁ ያለውን የሙያ ክፍተት በመለየት አስፈላጊውን እገዛና ድጋፍ ለመስጠት የምስለ ሕክምና ማዕከሉ አበርክቶ ትልቅ ነው ይላሉ።
ማሠልጠኛ ማዕከሉ ተማሪዎች የጽንሰ ሃሳብ ትምህርታቸውን አጠናቀው የተግባር ልምምድ ያደርጉበታል። ይህም ቀጥተኛ የሆነውን ሕክምና ለመስጠትና ክህሎታቸውን ለማዳበር የምስለ ሕክምና (Simulation) በዘርፉ አቅም ይፈጥርላቸዋል። የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች ከትምህርት መርሃ ግብራቸው እኩሌታው በምስለ ሕክምና ላይ የተመሰረተ ነው።
እንደ ኮቪድ-19 አይነት ያሉ አዳዲስ ወረርሽኞች/ በሽታዎች ቢከሰቱ በአገራችን የድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት ምላሽ አሰጣጥን ውጤታማ ለማድረግ የምስለ ሕክምና (Simulation) እና የሕክምና ክህሎት ማሠልጠኛ ማዕከላት ጉልህ ሚና አላቸው። ይህ የሕክምና ትምህርት አንድ ጊዜ ተሰጥቶ የሚያበቃ ሳይሆን በዓለማችን በየጊዜው እያደገና እየተቀያየረ የሚሄደውን ከሕክምና ጋር ተያያዥ የሆነ ዘመናዊና በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር የሚያስተዋውቅ ነው የሚሉት የማዕከሉ ዳይሬክተር፤ በአገር አቀፍ ደረጃ የጤና ባለሙያዎችን ብቃት ማረጋገጥ፣ የሕክምና

አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ በተቀመጠው መስፈርት መሰረት ማድረግ ካስፈለገ እነዚህን ማዕከላት ማጠናከር የግድ ይላል ባይ ናቸው።
የምስለ ሕክምና (Simulation) እና የሕክምና ክህሎት ማሠልጠኛ ማዕከላት የብቃት ምዘና አገልግሎት የሚሰጡ በመሆኑ ማዕከሉም እንደማንኛውም የሕክምና ትምህርት የነርሶች፣ የሐኪሞች እና ሌሎች የጤና ባለሙያዎችን ክህሎት እንደሚመዝን የገለጹት ወ/ሮ ልዩጌጥ ለዚህም ፎርማቲቭ (Formative) እና ሰማቲቭ (Sumative) የምዘና ዘዴን እንደሚጠቀም አክለዋል። ፎርማቲቭ (Formative) የሚሰኘው ተማሪዎች በትምህርት ሂደት ውስጥ ማወቅ የሚጠበቅባቸውን ክህሎቶች መረዳታቸውን ለማረጋገጥና መሥራት የሚችሉ መሆናቸውን ለማወቅ የሚሰጥ የምዘና ፈተና ሲሆን፤ ሰማቲቭ (Summative) ደግሞ የጤና ባለሙያዎች ከአንድ ደረጃ ወደ ሌላ ደረጃ ሲሸጋገሩ ወይም ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ የብቃት ደረጃቸውን ለመለካት የሚሰጥ ፈተና ነው።
በእነዚህ መስፈርቶች አንድ በማንኛውም የጤና ሳይንስ ዘርፍ የሚሠለጥን ባለሙያ ብቁ መሆኑን ለማረጋገጥ ቢያንስ ከ10 እስከ 12 የሚሆኑ የተለያዩ ብቃትን የሚለኩ የክህሎት ፈተናዎችን ይፈተናል። ሌላው በማዕከሉ በተዘጋጁ የሕክምና

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
የምርመራ ጣቢያ በሚመስሉ ክፍሎች (sta- tions) እየተዘዋወሩ ከአንድ በላይ ፈታኝ ባለበት እንዲፈተኑ የሚደረግበት ነው። ይህ ፈተና ከፅንሰ ሀሳብ ፈተና የሚለየው እየሰሩ የሚፈተኑት ወይም የተግባር መሆኑ ነው። Objective Structured Clinical Examination (OSCE) ይሰኛል።
ሌላው የማስተማሪያ ዘዴ
የምስለ ሕክምና እና የሕክምና ክህሎት ማሠልጠኛ ማዕከሉ አንድ ሰው ሐኪም ዘንድ የሚቀርብ ታማሚ ሆኖ የሚቀርብበት የ’Standardized patients’ መርሃ ግብር ለመጀመር በዝግጅት ላይ ይገኛል። ይህ ማለት አንድ ሰው ሐኪም ዘንድ የሚቀርብ ታማሚ ሆኖ ይቀርባል፤ ሐኪሙ ጋር ቀርቦ የሚናገረው ነገር የተጠና ነው። ለምሣሌ የስኳር ሕመምተኛ ሊሆን ይችላል፤ ሕመሙ እንዳለበት ይናገራል ወይም ይተውናል ማለት ይቻላል። ይህ ዓይነቱ የማስተማሪያ ዘዴ ጥቅሙ የጤና ሳይንስ ተማሪዎች የሕክምና ምርመራና የተግባቦት ክህሎቶችን እንዲለማመዱ ለማድረግ ነው። ሰውዬው ሕመምተኛ መስሎ ጤና ባለሙያው ዘንድ የሚቀርብበት መንገድ የአካል ምርመራና የተግባቦት ሥልጠና ለማድረግ ተመራጭ ከመሆኑ ባሻገር አዋጭም ነው፤ ምክንያቱም ቴክኖሎጂ በመጠቀም ያንን ማድረግ ከወጪው አንፃር በጣም ውድ በመሆኑ ነው። ይህ የሥልጠና ዘዴ በአብዛኛው በአውሮፓ እና በአሜሪካ ጥቅም ላይ ውሏል።
ባደጉ አገራት የጤና ትምህርትን በምስለ ሕክምና ለማስተማር በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ምስለ ሕክምና ማስደገፍ በኢትዮጵያ ውድ በመሆኑ መጠቀም ባይቻልም መተግበሪያዎችን የሚያበለጽጉ ባለሙያዎች በዚህ ዘርፍ ብዙ
መስራት እንደሚችሉ ያነሱት ወ/ሮ ልዩጌጥ እርሳቸውና የሥራ ባልደረቦቻቸው የሥልጠና ሞዴሎችና ሌሎች ለሥልጠና አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን መስራታቸውን በመግለፅ በምስለ ሕክምና ለማስተማር በቴክኖሎጂ የሚደግፉ የፈጠራ ባለሙያዎች በእጅጉ እንደሚያስፈልጉ ጠቁመዋል።
ሕክምናን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ በምስለ ሕክምና ማስተማር በሠለጠኑ አገራት በእጅጉ እያደገ ያለ ዘርፍ ስለመሆኑ ጥናቶች ያሳያሉ። ሆኖም በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም የሕክምና ኮሌጅ የሲሙሌሽንና ሕክምና ክህሎት ማሠልጠኛ ማዕከል የሚጠቀምባቸው አንዳንድ ምስለ ሕክምና (ሲሙሌተሮች) ከ17 ዓመት በፊት የተገዙ በመሆናቸው የመለዋወጫ እቃዎች አለመኖር፣ የአንዳንድ ሶፍት ዌሮች መሻሻል አለመቻል፣ የኮምፒዩተር መተግበሪያ ፈቃድ እድሳት አለመኖር ዋነኛ ተግዳሮቶች ናቸው።
አብዛኞቹ ምስለ ሕክምና በዕርዳታ የተገኙ በመሆናቸው የመለዋወጫ ዕቃዎች እጥረት ያጋጥማል። ግብዓቶቹ በአገር ውስጥ ሲሙሌተር የሚያቀርቡ ትላልቅ ኩባንያዎች ባለመኖራቸው በገበያ ላይ በተፈለገው ደረጃ የማይገኙ ናቸው። ከባህር ማዶ ለማስመጣትም የውጭ ምንዛሬ ችግር አለ። የግዥ ሥርዓቱ ለዚህ አለመመቸትና በቂ የጥገና ባለሙያዎችና የሠለጠነ የሰው ኃይል አለመኖር ለማዕከሉ ትልቅ ተግዳሮት እንደሆኑበት ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።
ግዙፍ ሀብት በሚጠይቀው በዚህ ማዕከል አንድ ተማሪ በቀዶ ሕክምና መስፋት እስከሚለማመድ ድረስ ብቻ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች በርካቶች ናቸው። ለሁሉም ሠልጣኝ ግብዓት ተሟልቶለት መሠልጠን ተገቢ ቢሆንም እንዲህ አይነት ወጪዎች የማዕከሉን አገልግሎት እየገደቡት ይገኛሉ።
በምስለ ሕክምና እና የሕክምና ክህሎት ሥልጠና ከሌሎች አገራት ጋር ሲነፃፀር ወደኋላ ቀርተናል የሚሉት ወ/ሮ ልዩ ጌጥ ማዕከሉ ተግዳሮቶች ቢኖሩበትም የሕክምና ባለሙያዎችን ብቃት ከፍ ለማድረግ ጥረቱን መቀጠሉን፤ በምስለ ሕክምናና የሕክምና ክህሎት ዙሪያ የሁሉም ትምህርት ክፍሎች መምህራንና ባለድርሻ አካላት ሥልጠና የሚወስዱበት የሥልጠና መመሪያ (Manual) መዘጋጀቱንና ይህም ማዕከሉ ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያጠናክር፣ ሌሎች ኮሌጆችም ልምድ የሚቀስሙበትና የማዕከሉን እውቅና ከፍ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።
“ወደፊት ባለን የቴክኖሎጂ አቅምና ውስን ሀብት በመጠቀም ሁሉንም በምስለ ሕክምና የማስተማር ዘዴ ተግባራዊ የማድረግ ሃሳብ አለን” ብለዋል።
የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም የሕክምና ኮሌጅ የምስለ ሕክምናና ሕክምና ክህሎት ማሠልጠኛ ማዕከል ያሉበትን የውስጥ ችግሮች ለማቃለል ሥልጠናዎች በመስጠት የማዕከሉን ገቢ የማሳደግ ዕቅድ ይዟል። በዚህም ማዕከሉን በግብዓትና በሰው ኃይል በማጠናከር የአገልግሎት ጥራቱን ማረጋገጥ አብይ ዕቅዱ ነው። ኮሌጁ ዘመናዊ የምስለ ሕክምና የሕክምና ክህሎት ሥልጠና በላቀ ደረጃ ለመስጠት ተዘጋጅቷል። ወ/ሮ ልዩጌጥ ኮሌጁ የላቀ የሚያደርገውን የምስለ ሕክምና ዘመኑ ባፈራው ቴክኖሎጂ ታግዞ ተማሪዎቹን የሚያሠለጥን ተቋም እንደሚሆን እምነታቸውን ገልፀዋል።
ማኅበራዊ

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
አገር-በቀል ዕውቀት

በጸሀፌ-ተውኔት አያልነህ ሙላቱ
እንደ መነሻ
ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪክ ያላት፣ በጥንታዊ ቅርሷ የዳበረች፣ የአገር-በቀል ሥልጣኔ፣ ዕውቀትና ጥበብ ምንጭ የተባለች...፣ የሰው ልጅ መገኛ-አናስር የሆነች፣ በረጅም ዘመን ነፃነቷ ለዓመታት ሲዘመርላት የኖረች አገር ናት፤ እውነትም ናት። ዛሬ ብዙ የአፍሪካ አገሮች ኢትዮጵያን የሚጠሯት የነፃነት ፋና አብሪ! ብለው ብቻ ሳይሆን የዘር ግንዳቸው ማያያዣ ሥር አድርገው ጭምር ነው።
አገራችን ያላት ቱባ ባሕል ከጥንት ጀምሮ በጥንታዊያን የዓለም
ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
ሕዝቦች የተደነቀ ቢሆንም፤ የእኛ ትውልድ ግን አንድም በንቀት የሚያየው አንድም በዝምታ የሚያልፈው ጉዳይ እየሆነ መጥቷል። የአገር በቀል ዕውቀታችንን በጎ ገጽታ የሌሎች አገራት ሕዝቦች በአድናቆት የሚያዩትን ያህል በእኛ ዘንድ በእጅጉ የደበዘዘ ነው። ኢትዮጵያዊያን አብዛኛውን ጊዜ ይሉኝታ ስለሚያጠቃን ስለራሳችን፣ ስለ አገራችን የቀደመ ሥልጣኔና ጥበብ፣ የተፈጥሮ ፀጋ፣ አሁን እየሰራን ያለነውን ሥራ፣ እያደረግን ያለውን ከድህነት የመውጣት ትግልና ወደ ብልፅግና ማማ የመውጣት ግስጋሴ እና እያስመዘገብን ያለውን ውጤት እንኳን ለተቀረው ዓለም ለማሳወቅ የምናደርገው ጥረት በእጅጉ ደካማ ነው። በውስጣችን ያለውን እውነት ለዓለም ሕብረተሰብ መግለጽ ያስጨንቀናል።
እውነት በራሷ እንደ ተፈጥሮ አበባ ጊዜ ጠብቃ የምትፈነዳ ብትሆንም አጠገቧ ያለ ገላጭ ሰው ግን የግድ ያስፈልጋታል። እኛ የምንኖረው ሐቃችንን በልባችን ውስጥ አምቀን ነው። በዚህም ሳቢያ ብዙ የምንደነቅባቸውንና ዕውቅና ልናገኝባቸው የምንችልባቸውን ክህሎቶች ሸሽገን ሳንጠቀምባቸው በከንቱ አሳልፈናቸዋል። በአንፃሩ ለኢትዮጵያ በጎ አመለካከት የሌላቸው ደካማ ጎኖቻችችንን ብቻ ቆፍረው በማውጣት፣ መሳለቂያ ሲያደርጉን ኖረዋል። ይሄ ሊበቃ ይገባል ቀደምት ጥበባችንን፣ የተፈጥሮ ፀጋዎቻችንን፣ ባሕልና ወጋችንን፤ በአጠቃላይ የአገራችንን መልካም ገፅታዎች ለዓለም የምናሳይበት ጊዜ አሁን ሊሆን ይገባል።
ይህ አበሻን ብቻ ሳይሆን ዓለምን ጭምር ያስደመመ ታላቅ አገር በቀል ዕውቀት አስደማሚ የጥበብ መድረክ ተዘጋጅቶለት ሊሞገስ የሚገባው ነው። በአገር በቀል ባሕል ላይ ተመሥርቶ የሚዘጋጅ ቱባ ጥበባዊ ዝግጅት ሁለት ገጽታ ይኖረዋል። አንድም የአገሪቷን ሕዝብ በልዩነት-አንድነት ክር ያስተሳስራል፤ ሁለትም የዓለም ሕዝብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በእኛ ላይ የገነባውን አሉታዊ ገጽታ ሊያስቀይር ይችላል። በዚህም የዓለም ሕዝብ ከአስገራሚው ጥንታዊ ቱባ ባሕላችን ጋር በቅርብ ሊተዋወቅ ይችላል። በአጭሩ የአገር በቀል ዕውቀትን ላለፉት ረጅም ዘመናት በጥቅም ላይ አላዋልናቸውም። ሳይሰራባቸው ስለዘለልናቸው በብዙዎች የፈጠራ ሰዎችና ምሁራን ዘንድ ከፍተኛ ቁጭት አሳድረው አልፈዋል። ከእነዚህ ቁጭቶች አንድ ሁለቱን እንጥቀስ።
ቁጭት-አንድ፡- የታላላቅ ታሪኮችና ቅርሶች መገኛ የሆነችው አገራችን የራሷን ሚሊኒየም አክብራለች። በዚያ ታላቅ ክብረ በዓል ላይ ከዚህች ጥንታዊት አገር በዓለም ላይ ጎልቶ የሚታይ አገር በቀል የጥበብ ውጤት ይጠበቅ ነበር። ቀደምት ታሪክ፤ ጥንታዊ ትውፊት፤ ልዩ የዘመን አቆጣጠር ካላት ኢትዮጵያ ልዩ አገር በቀል ዝግጅት የጠበቁ አገራት ጥቂት አልነበሩም። ምክንያቱም ሚሊኒየሙ ለዘመናት በተደረጉ እንቅስቃሴዎች በሁሉም ዘርፎች የተገኙ ውጤቶች መቋጫ ስለሆነ፤ ዓለም ከዚህች ልዩ አገር ልዩ የጥበብ ሥራ መጠበቁ ክፋት የለውም። ነገር ግን የበዓሉ አከባበር በጎረቤት አገር ሙዚቃና እስክስታ ሆነ። በወቅቱ ባሕላችን እንዲያም ሲል ኪነ- ጥበባችን የደረሰበትን የዕድገት ደረጃ የሚጠቁም ምንም አይነት አገር በቀል በሳል ዝግጅት አልቀረበም። ይህን ሚሊኒየም አስታከን የአገራችንን ገፅታ የሚለውጥና ታሪክና ባሕሏን የሚያስከብር፤ ዓለም-አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የጥበብ ሥራ ማዘጋጀት ሳይቻል ቀርቶ ዕድሉ
አመለጠን። ይህን ትርዒት ማዘጋጀት የሚችሉ ባለሙያዎች ግን ነበሩን። ዛሬም አሉን።
ቁጭት-ሁለት፡- የአፍሪካ አንድነት ሃምሳኛ ዓመት በመዲናችን ተከበረ። ኢትዮጵያ ከነፃነት ፋና አብሪነት ጀምሮ የአፍሪካ ባለውለታ ናት። የአፍሪካ አንድነት መሥራች ብቻ ሳትሆን መዲና ጭምር ናት። በዚህ ታላቅ ክብረ-በዓል ላይ የሚቀርብ፣ የአፍሪካን ዘመናዊ ውስብስብ ሕይወት የሚያሳይ፣ ከቅኝ ግዛት በፊትና በኋላ ያለውን የአፍሪካን ቱባ ባሕልና ታሪክ የሚያንፀባርቅ፣ ደረጃውን የጠበቀ በሳል የጥበብ ሥራ ከአገራችን ይጠበቅ የነበረ ቢሆንም አልሆነም። ሁነቱ በደቦ በተውጣጣ ጭፈራ ብቻ ታሰቦ ታለፈ።
ኢትዮጵያ አሁን ታላቅ ተጋድሎ ላይ ትገኛለች፤ ድህነትን አሸንፋ የድህነት ታሪኳን ለመቀየር ብሎም ወደ ብልፅግና ማማ ለመውጣት እያከናወነቻቸው ከሚገኙ ተግባራት መካከል አንደኛው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ነው፤ በአሁኑ ወቅት የግድቡ ግንባታ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ይገኛል። ይህ ፕሮጀክት ጊዜውን ጠብቆ ሲጠናቀቅ የዚህች አገር ታላቅ የታሪክ ክንውን መሆኑ አይቀሬ ነው። አገራችን ለዘመናት ለጎረቤቶቿ ቆማ ጧፍ እያበራች ማብላት፣ ወንዞቿን እያፈሰሰች ጎረቤቶቿን መመገብ፤ በራሷ አንጡራ ሀብት እንዳትጠቀም በተለያዩ አሻጥሮች ተተብትባ እንድትራብ መደረጉ፣ ሌላውም ሌላውም . . . ከዓባይ ግድብ ፍፃሜ ጋር እንደሚያበቃለት መላው ሕዝብ ተስፋ ሰንቋል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ተብትቦ ካሠራቸው የድህነት ናጫ ገመድ ከሚያላቅቋቸው ታላላቅ ፕሮጀክቶች አንዱ መሆኑን የተረዱት ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ በሕዳሴው ዘመን የዓባይን ወንዝ ለመገደብ ደፋ ቀና እያሉ ናቸው። በርካታ አገራት ታሪካዊ የሆኑ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ገንብተው ለምረቃ ሲያበቁ አይረሴና ዘመናትን የዘለቁ የጥበብ ሥራዎችን በማዘጋጀት ነው፤ በመሆኑም ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊያን ትልቅ የታሪክ አሻራ የሆነው ይህ ታሪካዊ ግድብ ሲጠናቀቅ፣ ይህንኑ የሚያጎላ አገር በቀል የጥበብ ሥራ ይጠበቃል። ኢትዮጵያንና ሕዝቧን በዓለም የሚያስጠራ እንዲሆን ጥረቱ አሁን መጀመር አለበት። የእኛ ልምድ በአብዛኛው “ሠርገኛ መጣ. . .” ሲሆን ይስተዋላል፤ ኪነ-ጥበብ ደግሞ በረጋ መንፈስ እንጂ በዘመቻ አይከናወንም። በግድቡ የፍፃሜ በዓል ላይ የሚቀርብ ደረጃውን የጠበቀ የኪነ-ጥበብ ዝግጅት ከአሁኑ መታሰብ አለበት። ይህ የጥበብ ዝግጅት ለግድቡ ፍፃሜ ታሪካዊ ቅርስነቱን ጠብቆ አብሮት ይዘልቃል። ማስታወሻ ሆኖ በቅርስነትና በቱሪስት መስህብነትም ለዘመናት አብሮን ይናራል። ስለሆነም ግድቡ ፍፃሜውን ሲያገኝና ለምርቃት ሲበቃ ኪነ-ጥበብ የምታቀርበው “እጅ መንሻ ምን ሊሆን ይገባል..?” የሚለው ጥያቄ ከተቻለ አሁን ይታሰብበት ባይ ነኝ-ሌላ ቁጭት እንዳንጨምር፡
አገር በቀል ኪነ-ጥበብ
የዕድገት መሣሪያ የሆኑት የአገር በቀል ኪነ- ጥበባት ውጤቶች ባህሪይ ወገናዊነት፣ ገላጭነት፣ ውሁዳዊነት፣ አብሮነት፣ ሀቃዊነት ወዘተ.. ናቸው። አገር በቀል ኪነ-ጥበባት በሕዝብ የተፈጠሩ የሕዝብ ሀብቶች ናቸው። መሠረታቸውን በአገር በቀል ወይም በነባር ዕውቀት ላይ አድርገው ከዘመኑ በተጨባጭ የሕዝብ አገልጋይ ይሆናሉ። ከዚያም ወደ ሕዝብ ዘልቀው በመግባት የሕብረተሰቡ አካል
ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
ሆነው በቀጥታ ለሕዝብ ይደርሳሉ።
ባሕል የሰው ልጅ በረጅም ዘመን ታሪኩ ተፈጥሮን ለማወቅ፣ ለመቋቋም፣ ለመቆጣጠርና የራሱን ሕልውና ለማረጋገጥ፣ ባደረገውና በሚያደርገው ትግል የፈጠረውና የሚፈጥረው፤ በየጊዜው እያደገ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የኖረና የሚኖር፤ አጠቃላይ የቁሳዊና መንፈሳዊ ቅርሶች ክምችት መገለጫ ነው። ባሕል ሰውን ከሌሎች እንስሳት የለዩት የማሰብ የመፍጠርና የማምረት ችሎታ ውጤቶቹ ናቸው። እንደማናቸውም ነባራዊና ሕሊናዊ ክስተቶች ባሕልም ለዲያሌክቲካዊ ሕግ ተገዥ ስለሆነ አንድ ባሕል ይፈጠራል፣ ያድጋል፣ በየትውልዱ ተሀድሶ እያገኘ ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋል።
አገር በቀል ሕዝባዊ ኪነ-ጥበብ ማኅበራዊ ዕውነታን በትክክል የሚያንጸባርቅ፣ ለሕዝባዊ ሥርዓት ግንባታ ህሊናዊ ሁኔታዎችን የሚያመቻች፣ ማኅበረሰብን ከጎታችና ኋላቀር አመለካከትም ሆነ እምነት የሚያላቅቅና ከፀረ-ዴሞክራሲ ኃይላትና ከተፈጥሮ አደጋዎች ጋር በቁርጠኝነት እንዲታገል የሚያነሳሳ ነው። በሌላ በኩል በጋራ ጥረት ለጋራ ብልጽግና መሥራትን ያበረታታል። ዴሞክራሲያዊ ስነ ምግባርን ያሰርጻል። የአገር ፍቅርንና አርበኝነትን ይገነባል። ዓለም አቀፋዊነትን ያጠነክራል። የውጭ የባሕል ወረራንና ለዘመናት በሕዝቡ መንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ ሰርጾ በመግባት ጠንቅ የሆነውን ጎታች ልማድን ይዋጋል። በምትኩም አገር በቀል ሕዝባዊ ባሕል ይገነባል። በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በቱባ ባሕል ላይ የተገነባ አዲስ ባሕላዊ ሰው ይፈጥራል።
ለኢትዮጵያ ሕዝብ የባሕል ዕድገት መፋጠን ጥርጊያ ጎዳናን መቀየስ እንዲችሉ፣ ሰርጸው ገብተው እንዲያብቡና እንዲዳብሩ፣ አገር በቀል ሕዝባዊ ኪነ-ጥበባት በኅብረተሰባችን ውስጥ የሚጫወቱትን ወሳኝ ሚና ጠጋ ብሎ መገምገምና ቀጥተኛ ፈር የሚያስይዝ መዋቅር መዘርጋት አስፈላጊ ነው። “..የዘመናዊ ዕድገታችን መሠረት እንዲሆን የምንፈልገው አገር በቀል ኪነ-ጥበብ ምን አይነት ነው?” የሚለው ጥያቄም መልስ ማግኘት አለበት። የጎበጠ ዛፍ በለጋነቱ ቢታረቅ ቀጥ ብሎ ሊያድግ ይችላል። ኪነ-ጥበብም በአገር በቀል ዕውቀት ላይ ተመሥርቶ ተገቢውን መስመር ይዞ ካደገ ጤናማና ሕዝባዊ ይሆናል።
በየአካባቢው የሚቀርቡ ዘመናዊ የፈጠራ ሥራዎች ከጥራትም ሆነ ከኪነ ጥበባዊ ደረጃ አኳያ ሲቃኙ ብዙዎቹ ችግር እንዳለባቸው ይስተዋላሉ። በተለይም ዘመናዊ የኪነ-ጥበብ ውጤቶችን በጊዜያዊ ጠቀሜታ ብቻ የመወሰኑና የወደፊቱን ብሩህ ዘመን አቅርቦ በማሳየት ወጣቱን ለሚጠብቀው ኃላፊነት ለማዘጋጀት ያለመቻል ሁኔታ በአፋጣኝ መሻሻል ያለበት ጉልህ ጉድለት ነው።
ኪነ-ጥበባት ይህን “ጉልህ ጉድለት” በአፋጣኝ ማሻሻል የሚችሉት፤ የሕዝባዊ ባሕል ግንባታ ከሚጠይቀው የኪነ-ጥበባት አደረጃጀት አንጻር፣ በአገር በቀል ዕውቀት ጽኑ መሰረት ላይ ሲቋቋሙ ነው። በየአካባቢው የተቋቋሙትና የሚቋቋሙት አማተር የኪነ-ጥበባት ቡድኖች ብዙዎቹ ብልጭ ብለው ሲጠፉ፣ ለምልመው ሲጠወልጉ፣ ጠንክረው ሲዳከሙ የምናያቸው በጽኑ የአገር በቀል ጥበብ መሰረት ላይ የተደራጁ ባለመሆናቸው ጭምር ነው።

ኪነ-ጥበባት በአፍላነታቸው በጥሩ አገር በቀል ዕውቀት መሠረት ላይ ካልተገነቡና ሙያዊ አመራር ካልተሰጣቸው በውጪው ዓለም ባሕል ተፅዕኖ ሥር ወድቀው በአገራችን ጎልቶ በሚታየው የኩረጃ ሕይወት ቀውስ ውስጥ ገብተው ጨርሰው መውጫ ሊያጡ ይችላሉ። ይህ ዘመናዊው የውጭ የኪነ- ጥበብ ወረራ በሕዝባዊው ኪነ-ጥበብ ውስጥ ሰርጎ ከገባ በኋላ ማስወጣቱ እጅግ ከባድና የመረረ ስለሚሆን ከአሁኑ ሽንጥን ገትሮ የመዋጋቱ ጉዳይ በባሕል መስክ የተሰለፉ ሁሉ ተቀዳሚ ተግባር ነው።
የኪነ-ጥበብ ሥራዎች የትግልና የለውጥ መሣሪያነታቸው፣ የሥነ ምግባርና የውበት መገለጫነታቸው የሚረጋገጠው በይዘትና በቅርጻቸው ማራኪ፤ መሠረታቸው የአገር በቀል
ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
ዕውቀት ሆነው ሲዘልቁ ነው። በአገራችን ውስጥ የሚደመጠው አብዛኛው የዘፈን-ግጥምና ዜማ፣ ውዝዋዜና ጭፈራ ጨርሶም ፈረንጃዊ አይደለም፣ ፈጽሞም ባሕላዊ አልሆነም። የግጥሙ ይዘት ጥራት የለውም። አልፎ አልፎ የድሮው ዘፈንና ግጥም እንዳለ ተገልብጦ እየቀረበ ነው። አልፎ- አልፎ ደግሞ ግጥሙ ውበት-አልባ የጋዜጣ ጽሑፍ ግልባጭ ይመስላል። የሥነ ግጥም ምጣኔ የጎደለው፣ ዝርው፣ ስሜት የማይነካና የማያመራምር ነው። የሙዚቃ ዜማችንም ፈር እየለቀቀና ለዛ እያጣ እየመጣ ነው። ከምክንያቶቹ አንዱ የሙዚቃ ደራሲያን ቱባ ባሕላዊውን ሙዚቃችንን መሰረት አድርገው ለማዘመን ከመመራመር ይልቅ በቀጥታ ከውጭ መገልበጡን ተቀዳሚ ተግባር አድርገው በመያዛቸው ይመስለኛል። ከዚህም ሁሉ በላይ በየሙያ መስኩ የሃያሲያን አለመኖር ችግሩን የበለጠ እንዲባባስ አድርጎታል። ጥንታዊው የቅኔ ዘረፋና ነጠቃ ለዘመናዊው ሃያሲያን መሠረት ሊሆናቸው ከቶ አልቻለም። ጥንታዊው የቅኔ ዘረፋ የዕርምት መነሻ ሆኖ የሂስ ጥበባችንን ማሳደግ እንደሚችል የገባን ስንቶቻችን ነን?
የአገር በቀል ኪነ-ጥበብ መሰረቷና ምንጯ ሰፊው ሕዝብ ነው። ጥበብ ሕዝባዊ እንድትሆን ደግሞ ከያኒው የኪነ-ጥበብ ምንጭና መሰረት የሆነውን የሕዝቡን ታሪክና ሕይወት ጠንቅቆ ማወቅ ይኖርበታል። የሕዝቡን ታሪክና ባሕል ጠንቅቆ ለማወቅ ደግሞ ወደ ሕዝቡ መጠጋት ያስፈልጋል። ወደ ሕዝቡ ለመጠጋትም ሕዝብ መውደድንና የሕዝብ ወገን መሆንን ይጠይቃል። ከቱባ ባሕሉ ርቆ ለባዕድ ባሕል የተገዛ የኪነ-ጥበብ ባለሙያ፣ በሕብረተሰቡና በእሱ መካከል ከፍተኛ ክፍተት እንደሚኖር አስቀድሞ ሊረዳው ይገባል። የጥበቡ
ሰው የአገር በቀል እውቀት መሠረት የሌለውን ዘመናዊውን ወራሪ ኪነ-ጥበብ፤ ከሕዝቡ ቱባ ባሕል ጋር አስታርቆ ወይም አዋህዶ በፈጠራ ሥራው ለማቅረብ ቢፍጨረጨርም ውጤቱ ከሁለት ያጣ ጎመን ይሆንበታል። ከባሕሉም- ከፈረንጁም ሳይሆን በመሀል ተንጠልጥሎ ይቀራል። ይህ ዓይነቱም ተጋቦት ወደ ሕዝባዊ ኪነ-ጥበባት እንዳይሸጋገር ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል።
እነዚህ ዓይነቶቹ የጥበብ ሰዎች፤ ዘመናዊውን ኪነ- ጥበብ የአገር በቀል ዕውቀት መሠረት ሳይኖረው በባዶ ሜዳ ላይ አብቅለን ኢትዮጵያዊ ኪነ-ጥበብ አድርገን እናበልጽገው የሚሉ ናቸው። ይህ ግን ፈጽሞ የማይታሰብ ነው። በነጭ ቱባ ባሕል ላይ የተገነባ ጥበብ የሚሸተው ፈረንጅ-ፈረንጅ እንጂ ከቶም ኢትዮጵያዊ አይሆንም። አበው “ዘሬን ብተው ይዘርዝረኝ!” እንዲሉ። እነዚህ የዋህ ምሁራን፤ ነጮች “የዘመነ ባሕል አላቸው” በሚል እሳቤ፤ በዝቅተኛነት ስሜት ከፈረንጅ ለቀሰሙት ጥበብ ማካካሻ ይሆን ዘንድ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የራሳቸውን አገር በቀል የሕዝብ ባሕል ዝቅ አድርገው ለማሳየት ይጥራሉ። ከዚያም አልፎ ሕዝቡ እንደነሱ የነጮቹን ባሕል እንዲያከብርላቸው፣ እንዲያመልክላቸውና እንዲያሞግስላቸው ይሻሉ። የኋላ-ኋላ ግን የሚተዉት በራሳቸው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን በፈረንጆቹም ጭምር ነው።
በተቃራኒው ደግሞ ከሕዝብ ጉያ የወጡ፣ ነባሩን- ቱባ-ሕዝባዊ ባሕላቸውን መሠረት አድርገው ዘመናዊውን ካባ ከላይ ለመደረብ የሚጥሩ፣ ነባሩን የኪነ-ጥበብ ፈለግ ለመከተል ደፋ ቀና የሚሉ፤ በጣም ጥቂት ይሁኑ እንጅ አሉ። የዚህ ኪነ-ጥበብ ፈለግ ተከታዮች መሠረታቸው የፀና ቢሆንም አቅማቸው ገና አልጎለበተም። የማጠናከሪያ መድረክም ሆነ የድጋፍ-እጅ ከመንግሥትም ሆነ ከሕብረተሰቡ አልተዘረጋላቸውም። ዘመን- አመጣሹ የውጭው ብልጭልጭ ባሕል በእጅጉ ተጭኗቸዋል። መጤውን ባሕል የሚደግፈውን ያህል፣ ዘመናዊው ቴክኖሎጂም እነሱን ከጀርባው ሆኖ አላገዛቸውም።
ዘመናዊውን ኪነ-ጥበብ ከነባሩ ባሕል ጋር እንዲጣጣም፣ ዕድገቱም በተገቢው መስመር እንዲቀጥል፣ ጥንቃቄ ባልጎደለው ሁኔታ እንክብካቤ ማድረግ ተገቢ ነው። በተለይ አዳዲስ የኪነ-ጥበብ ፈለጎች በምርጫና በአስተውሎት መስተናገድ አለባቸው። መድረኩን በሽሚያ ወይም በአምቧጓሮ እንዲይዙ ማበረታታ ሳይሆን፣ በሀቀኛ ኪነጥበባዊ ትሩፋታቸው ተመርጠውና ነባሩን ባሕል መሠረት አድርገው የማደግ ዕድሉን ማግኘት ይኖርባቸዋል። ማንኛውንም ድጋፍ ሊሰጣቸው የሚችለውም ከዚህ አንጻር ብቻ ሊሆን ይገባል ።
የኪነ-ጥበብ ሁሉ ምንጭ ሕዝብ ስለሆነ፣ ጥበቡ በሕዝብ ውስጥ ሰርጾ እንዲገባ፣ በጸና በአገር በቀል ዕውቀት መሰረት ላይ መደራጀት አለበት። የዕድገቱ መፋጠን፣ የመሠረቱ መጽናት፣ የአገልግሎቱም ሕዝባዊ መሆንና መጠናከር፣ በአጠቃላይ ነባሩን ባሕል መሠረት ያደረገ የኪነ- ጥበብ ግንባታ በአሸናፊነት የመውጣቱ ሁኔታ የሚወሰነው ኪነ-ጥበብ ከሕዝብ፣ ሕዝብም ከኪነ- ጥበብ ጋር በሚኖራቸው ቀጥተኛ መተሳሰር ነው። ለዚህም በዘመናዊው ፈጠራና በፈጣሪው በራሱ፣ በነባሩ ሕዝባዊ ባሕልና በአዲሱ የፈጠራ ሥራ መካከል የተጋደመው ግንብ መናድ ይኖርበታል። በፍርስራሹም ላይ ቱባውን ሕዝባዊ ባሕል መሠረት ያደረገ አዲስ የኪነ-ጥበብ ድልድይ መገንባት የግድ ይላል። ለከያኒውም ሕዝብ ካበለፀገው የትውፊት

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
ምንጭ ጨልፎ ፈጠራውን የሚያረካበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት። ከዚህ ሁሉ አስቀድሞ ግን ነባሩን ባሕል መሠረት አድረገው የሚያብቡ የፈጠራ ሰዎችን የሚያፈራ የባሕል ማዕከል ወይም ተቋም ማቋቋም ሌላው አስፈላጊ ጉዳይ ነው።
በሕብረተሰብ ግንባታ ሂደት ውስጥ ኪነ- ጥበብ የራሷ የሆነ ሰፊ ድርሻ አላት። አገር በቀል ኪነ-ጥበብ ተጠናክራ ሙሉ ተግባሯን እንድታከናውን መንግሥታዊና ሕዝባዊ ድርጅቶች ይበልጥ ጥረት ሊያደርጉላት ይገባል። የኪነጥበባትንና የሕዝብን ቀጥተኛ የሆነ መተሳሰር ለመፍጠርም ከሕብረተሰቡ መንጭተው የሕዝቡን መንፈሳዊ ሕይወት መልሰው የሚያበለጽጉ “የአማተር የኪነ- ጥበብ” ቡድኖችን በልማት ተቋማትና በሕዝባዊያን ድርጅቶች ሥር ማቋቋም የሕዝባዊ ባሕል ግንባታ አንዱ ገጽታ ነው።
የዘመናችን ግኝት ስለሆኑት የባሕል ማዕከላት ምሥረታ ያለፈን ተሞክሮና አሁን ያለበትን ሁኔታ በተመለከተ ወደፊት በሌላ ዓምድ የምንመለስበት ጉዳይ ሆኖ የአገር በቀል ዕውቀት ማስፋፊያ ዓቢይ መሠረቶች፤ እነዚህ የአማተር ኪነ ጥበባት ቡድኖች። የታላላቅ የጥበብ ሰዎቻችን ምንጮች እነዚህ የአማተር ኪነጥባበት መሆናቸው እሙን ነው። መሠረቱ የፀና ቤት አይፈርስም። ስለሆነም የጠቢባን መፍለቂያዎች የሆኑት አማተር ኪነጥበባት ጥሩ መሠረት ካላቸው ኪነጥበቡም የፀና ይሆናል።
ስለ አገር በቀል ኪነ ጥበብ ይህን ካልን፤ በኪነ
ጥበባት ውስጥ የታቀፉትን የፈጠራ ዘርፎች በወፍ በረር ለማየት እንሞክራለን። እይታችን ከአገር በቀል ዕውቀት አኳያ ስለሆነ፤ ጽንሰ-ሐሳቡን አጉልተን የማሳየት ፍላጎት የለንም። የጽሑፉም ዓላማ በኪነ- ጥበብ ጥላ ሥር ያሉት የፈጠራ መስኮች ምን ያህል በራቸው ለአገር በቀል ዕውቀታችን መዳበር ክፍት ነው? ምን ያህል አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይችላሉ? አሁን ያሉበት ሁኔታስ ምን ይመስላል? በእነዚህ ጥበባት ውስጥ ከእኛ አልፎ ለዓለም የሚተርፍ የጥበብ ትሩፋት አላቸው ወይ ወዘተ..? የመሳሰሉ ጥቆማዎች ለማጫር ጭምር ነው።
ሙዚቃ
ኢትዮጵያ በሙዚቃው ዓለም ያላት ሚናና ያበረከተችው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በኪነጥበቡም ዓለም እጅግ ተደናቂና ተወዳጅ ጣዕመ ዜማ ያለው ሙዚቃ አላት። በሊቃውንት እንደሚነገረው ከሆነ ኢትዮጵያ በዘመነ ኦሪት ከብሉይ ኪዳን የተውጣጣ የቤተ-መቅደስ ዜማ እንደነበራት ይታወቃል። ዛሬ ግን ለመንፈሳዊውም ለዓለማዊው ሙዚቃ መሠረት የሆነው የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ዕንዚራ የተባለው ያሬድ ነው። ቤተክርስቲያን ያሬድ ጥበቡን ከሰው ብቻ ያገኘው ሳይሆን “ከመንፈስ ቅዱስም ጭምር ነው..” ብላ ታምናለች። የያሬድን የዜማ ድርሰት ሊቃውንት ዮሐንስ፤ አስተምሮ፤ ጾመድጓ፤ ፋሲካ በማለት በአራት ይመድቧቸዋል። የዜማው ስልት ደግሞ ግዕዝ፤ ዕዝል፤ አራራይ ብለው በሦስት ይከፍሏቸዋል። ይህም የዜማ ጥበብ ከትውልድ ወደ ትውልድ በታላቅ ክብር ሲተላለፍ ከእኛ ደርሷል።
በሥርዓተ ዜማው ውስጥ ቁልፍ የሆኑ ምልክቶች በዘመኑ አጠራር ኖታዎችን እናገኛለን፤ “..ድፋት፣ ይዘት፣ ሒደት፣ ጭረት፣ ቅናት፣ ቁርጥ፣ ርክርክ፣ ደረት፣ ድርስ፣ እና አንብር..” ይሰኛሉ። ሌሎችም እንዳሉ ሊቃውንቱ ይጽፋሉ። እነዚህ ኖታዎች ለዓለም የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ዕድገት ከፍተኛ ሚና መጫወታቸው የአደባባይ ምስጢር ነው። ይህ ዜማና ምልክቶች ታዲያ አገር በቀል ፈጠራ እንጂ ከውጭ የተኮረጁ አይሉም። ከያሬድ በፊት በኖታ ሙዚቃ የፃፈ የሙዚቃ ሰው ለመኖሩ የተመዘገበ መረጃ አላገኘሁም። ቢኖር እንኳ ያሬድ ዜማዎችን ከራሱ አመነጫቸው እንጂ ከውጭ አልቀዳቸውም። ሊቃውንት እንደሚሉት ምንአልባት አዕዋፍ አበድረውት ሊሆን ይችላል። በአጭሩ የያሬድ ዜማ የሚያኮራ የአገር በቀል ዕውቀት የፈጠራ ውጤት እንጂ፤ ስልቱም፣ ይዘቱም፣ ቋንቋውም ከሌላው ዓለም የተቀዳ አይደለም።
ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርሁት፤ ኢትዮጵያ በዘመነ ኦሪት ይዘመሩ ለነበሩት መዝሙሮች ጥንታዊ አገር በቀል መሣሪያዎችን ትጠቀም እንደነበር አሁንም ሊቃውንቱ ያበስራሉ። እነዚህንም መሣሪያዎች እስከ ዛሬ አገሪቷ በመንፈሳዊም ሆነ በሥጋዊው ዓለም ትጠቀምባቸዋለች። እነዚህ መሣሪያዎች መለከት፣ በገናና መሰንቆ፣ ከበሮ፣ አውታር፣ እምቢልታ፣ ጽናጽል…ናቸው።
ያሬድ የጣዕመ-ዜማችን ምንጭ ብቻ ሳይሆን ዓለም ሙዚቃን በምልክት ለመፃፍ ከማሰቡ በፊት የኖታን ግኝት ፈጥሮ ለሙዚቃ ጥበብ ዕድገት ያበረከተ የምንኮራበት ሊቅ ነው። ይህም ያሬዳዊ የሆሄ ምልክት ለዓለም የሙዚቃ ኖታ ቀረፃ መነሻ እንደሆነ ይገመታል። ይህ አባባል አውነት ከሆነ ከዚህ ዜማ ጋር አያይዘን የምንጠቀምባቸውና ያሬድ
ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
የኖታው አካል ያደረጋቸው ጽናጽል፣ መቋሚያና ከበሮ፤ በዜማው ሒደት ውስጥ የራሳቸው የሆነ ትርጉምና ሚና ያላቸው ናቸው። ከበሮውና ጽናጽሉ አድማቂዎች ብቻ ሳይሆኑ የዜማው አካል ናቸው። መቋሚያው የጠቅላላው ዜማ መሪ ነው። መውጣት መውረዱ..፣ ግራና ቀኝ መዝመሙ በውስጡ ከፍተኛ ምስጢርን አካቶ የያዘ ነው። የዜማውን “..ድፋት፣ ይዘት፣ ሒደት፣ ጭረት፣ ቅናት፣ ቁርጥ፣ ርክርክ፣ ደረት፣ ድርስ፣ አንብር..” የሚመራው መቋሚያው ነው። መቋሚያው ዘመናዊው የሙዚቃ ኮንዳክተር ጨብጦ ሙዚቃውን የሚመራባትን ቀጭን እንጨት ያስገኘ ነው። የዛሬውን ዓለም የፋንፋር፤ የሲንፈኒ ሙዚቃን ከፊት-ለፊት ሆነው የሚመሩት ኮንዳክተሮች የያዙት የተዥጎረጎረ ዱላ የተገኘው ከያሬዳዊው መቆሚያ እንደሆነ ማመን ይቻላል።
ዓለም ግን ለሙዚቃ ጥበብ ዕድገት ቀድመን ላበረከትነው ለኖታችንም ሆነ ለሙዚቃ መምሪያ መቋሚያችን ምስጋና ሊሰጠን ቀርቶ ዕውቅናም ነፍጎናል። እኛም ፈጣሪውንና ፍጣሪውን ጠልቀን ስለማናውቀው ወይም ተመራምረን ልንደርስበት ስላልቻልን፣ ወይም ጥንታዊ እሴታችንን የማወቅ ፍላጎቱ ስለሌለን፣ ነጣቂ ነጮችን ሽንጣችንን ገትረን ልንሞግታቸው ከቶ አልቻልንም ወይም አልደፈርንም።
በያሬድ የተሰየመው የሙዚቃ ተቋማችን የምርምር ጊዜውን የሚያጠፋው ነጮች ተመራምረው በአገኙት የአገራቸው የሙዚቃ ሊቃውንት ላይ እንጂ፤ ስማቸውንና ሥራቸውን ጫካ በሸፈናቸው በአገራቸው ጥንታዊ የፈጠራ ሰዎች ላይ አይደለም። በእነ ያሬድ ላይ ማጥናትና መፈላሰፍ ጊዜው ያለፈበት ኋላቀር አድርገው የሚቆጥሩ አሉ። ከዚያም ባሻገር
የጥናቱ ውጤት ምስጉን ዲግሪ አያሸልምም፤ አንቱም አያሰኝም። ዲግሪ ሸላሚውም፤ ፈታኙም፤ መምህሩም ከአንድ ወንዝ የተቀዱ ናቸው - ከአስኳላ።
ከዚህ ውጭ እጅግ በርካታ የብሔር ብሔረሰቦቻችን አገር በቀል ሙዚቃዎች በጠራራ ፀሐይ በነጮች እየተዘረፉ “የእኛ ፈጠራ ውጤቶች ናቸው” እየተባሉ ናቸው። የደራሼ የሙዚቃ ድምጽ ተመንትፎ የፈረንጅ የፈጠራ ውጤት ሆኗል። ለዚህ ሁሉ ዝርፊያ ቅድሚያ ተጠያቂ ዘራፊዋች ቢሆኑም፤ መስኮታችንን ከፍተን እነሱን ሌባ ያስባልናቸው እኛም የዘረፋው ተባባሪዎች ነን። ቢያንስ ሌባ ሲዘርፈን አልጮኽንም። ለእርዳታም ጎረቤት አልጠራንም። ብዙ ምክንያቶች መደርደር ይቻላል። ቦታው ስላልሆነ በዚሁ እንዝለለው።
ለመጠቅለል ያህል ጥቂት ነገሮችን ልጠቃቅስ፤ ኢትዮጵያ በልዩነት-አንድነት የተገነባች፤ የተለያዩ ባሕሎች፣ ኃይማኖቶች፣ ልማዶች፣ ቋንቋዎች፣ ጥበቦችና ሙዚቃዎች ወዘተ.. ያሉባት የብዙ ብሔረሰቦች መገኛ አገር ናት።
ሙዚቃዋ በሁለት ይከፈላል፤ ኃይማኖታዊና ዓለማዊ። ሦስት የሙዚቃ ዓይነቶች አሏት እንጉርጉሮ፣ መዝሙር እና ዘፈን። የሙዚቃ ደረጃዎችን ስናይ በኢትዮጵያ ምድር በአብዛኛው ጥቅም ላይ የሚውለው አገር በቀል ሙዚቃ ፈረንጆች Pentatonic የሚሉት አምስት የሙዚቃ ድምጽ ኖታ ያለው ነው። እነዚህን አራት ቅኝቶቻችንን ትዝታ፣ ባቲ፣ አምባሰል እና አንቺ-ሆዬ ከሞላ-ጎደል በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች እንጠቀምባቸዋለን። እነዚህ ቅኝቶች በሚሰሙባቸው አካባቢዎች ሁሉ በተለያዩ ቋንቋዎች ቢዘፈኑም፤ ዜማቸው በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ሳይጎረብጥ የሚደመጥ ሲሆን፤ በሚፈጥሩት ስሜት በሕዝቦች መካከል አንድነትንና ፍቅርን ይገነባሉ። ቅኝቶቹ እንዴት ተሰየሙ? ማን ፈጠራቸው? የሚሉ ጥያቄዎች ያነሳን እንደሁ ሠፊ ጥናት የሚጠይቁ ናቸው።
ከፈረስ ጭራ ማሲንቆን አዘጋጅቶ፤ የዋርካ ግንድ ጠርቦ በበሬ ቆዳ ወጥሮ ከበሮ ያሰናዳው፤ ከታረደ የእንስሳ አንጀት ክር ፈትሎ ክራርን የሠራው፤ ከተፈጥሮ ሸንበቆ ቆርጦ ዋሽንትን የፈጠረው ማን ነው..? ዘመናዊው አበሻ ከሞላ ጎደል የአውሮፓን ሙዚቃ አፈጣጠራቸውን ከእነ ደራሲዎቻቸው በጥልቅ ያውቃቸዋል። በአስኳላ ቤትም ተምሯቸዋል-አስተምሮባቸዋል። በእኛ ግን.. በታላቁ ያሬድ ስም የተሰየመው ተቋም ባልደረቦች ጭምር በአገራዊው ሙዚቃ ላይ ትኩረት የሰጡ አይመስሉም። የአስኳላ ትምህርት የፈጠረን ነጭ አምላኪዎች እኛ ከራሳችን ጥበብ ተፋተን የውጭ ሙዚቃ አድናቂ ሆነናል፤ ቱባ ፈጠራዎቻችንን በውጭ ጩኸት በርዘናቸዋል፤ አድናቆትም ነፍገናቸዋል።
የአገር በቀል የኪነ-ጥበብ ሰው በአንድ እጁ ጊታር ሲጨብጥ በሌላው እጁ የሕዝቡን እሮሮ፣ ለቅሶ፣ ደስታ፣ ትግል፣ ምኞትና ተስፋ የሚገልጽበት ባሕላዊ ክራር፣ ማሲንቆ፣ ዋሽንት… መያዝ ይኖርበታል። ያለዚያ ግን እርምጃው ውሱን፣ ሥልጣኔው ግንጥል ጌጥ ይሆንበታል። ዘመናዊ ሥልጣኔውም በአገር በቀል ዕውቀት ላይ ስላልተገነባ መሠረቱ የላላና በአሸዋ ላይ የተገነባ ቤት ይሆናል።
ሥነ-ጽሑፍ
ስለ ኢትዮጵያ አገር በቀል ድርሰት የምንለውን
ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
ከማለታችን በፊት አንባቢው መጀመሪያ “ምን ያህል በራስ የመተማማን መንፈስን በውስጡ አዳብሯል..!?” ብለን ልንጠይቅ እንገደዳለን። የአገር በቀል ዕውቀትን በተጨባጭ ወደ ተግባር የሚተረጉመው በመጀመሪያ ራሱን የገመገመ ሰው ነው። ራስን ማወቅ ለሰው ልጅ ከሁሉም በፊት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ መመሪያ ነው። አንድን ነገር ለመማር፤ ለማወቅ፤ ለመረዳት፤ ለመሥራት፤ የራስና በራስ መተማመመንን በኅሊና ውስጥ ማሳደር ወሳኝ ነው። በራስ መተማመን ከሌለ የራስን ሀብትና ፀጋ “የእኔ ነው” ብሎ መቀበል እንኳ ያስቸግራል። በራስ መተማመን ሲጎድለን ያጎረሱንን ሁሉ ሳናቅማማ መዋጥ እንጀምራለን። የሚሉንን ሁሉ ሳናቅማማ እናምናለን። ጥሉ ያሉንን እንጠላለን፤ ውደዱ ያሉንን እንወዳለን። የእኛ የሆነን ሁሉ አስወግደን የውጭ የሆነን መሸከም እንጀምራለን። የእኛን አቡጊዳ ዕድሞ ውስጥ ቀብረን፤ በእነሱ ABC እንካናለን። ለእነሱ ዕድገት መሠረት የሆነውን የእኛን ጥንታዊ ሥልጣኔ ንቀን የእነሱን ቴክኖሎጂ ከራሳችን አገር በቀል ዕውቀት ጋር ሳናዛምድ በዕውር ድንብሩ እንከተላቸዋለን። አገር በቀሉን፤ መሬት አቅላጁንና አበልጻጊውን የፍግ ማዳበሪያ ወደጎን ብለን አፈር አቃጣዩን . . . ብቻ የሸጡልንን ሁሉ እንሸምታለን።
በራስ መተማመን በሰዎች ህሊና ውስጥ ያለ መሆኑን ከመገንዘብ ውጭ የምናየው፣ የምንዳስሰው፣ የምናሸተው ወይም የምንቀምሰው ቁስ-አካል አይደለም። በአጭሩ በራስ መተማመን ማለት በራስ ዕውቀት ላይ የተገነባ የመረዳትና የማወቅ ብቃት ነው። ማንኛውንም ችግር ለመቆጣጠር የሚያስችል በውስጣችን የሚሰማን እምነትም ነው።
ድርሰቶቻችን በራሳችን ጥንታዊ ሆሄያት የተፃፉ ናቸው። ጎረቤቶቻችን በሔሮገራፊ (በምልክት ጽሑፍ) በሚዳክሩበት ዘመን፤ እኛ ብራና ዳምጠን፣ ፊደልና መንጎል ቀርፀን..፣ ቀይና ጥቁር ቀለም በጥብጠን፣ ድንጋይ ጠርበን..፣ ቁም ጽሕፈት የጀመሩ ሊቃውንትን ያፈራን ሕዝቦች ነን። እነዚህ ምሁራን የፈለቁት ከአሜሪካ ወይም ከእንግሊዝ ዩኒቨርሲቲዎች ሳይሆን ከቤተ እምነቶች ጓዳ ነው። ለዚህም በየአድባራቱ በብራና ሠፍረው የተደጎሱ እጅግ በርካታ መፃሕፍትን፤ በአክሱም በድንጋይ ላይ የተቀረጹ ጽሑፎችን መቃኘት ይቻላል።
ጥንታዊያን የኢትዮጵያ ሊቃውንት ሆሄያትን ያዋቀሩት በሕግና በሥርዓት ነው። ይህንን ሕግና ሥርዓት ሳይከተል የሚፃፍ ግድፈቱና ስህተቱ ጉልህ ስለሚሆን በሊቃውንቱም ሆነ በአንባቢ ዘንድ ተቀባይነት አይኖረውም። ይህን ሕግና ሥርዓት ለማወቅ ደግሞ ፀሐፊው አስቀድሞ በአገር በቀሉ ዕውቀት ሊጠመቅ ግድ ይለዋል። ገቢርና ተገብሮ፤ አንድና ብዙ፤ የሴትና የወንድ ፆታን ለይቶ መፃፍ የሚችለው አስቀድሞ በጥበቡ ተክኖ የሆሄያትን አግባብ ጠንቅቆ ማወቅ ሲችል ብቻ ነው። ጥንታዊ አባቶቻችን ያዘጋጇቸውን ሥርዓተ ነጥቦች በአግባቡ ከተጠቀምንባቸው፤ ለሥነ ጽሑፋችን ብቻ ሳይሆን ለንግግራችን ጭምር በእጅጉ አስፈላጊ ይሆናሉ። ለንግግር ሥርዓተ ነጥብ ይበጅለታል። የሥነ ጽሑፍ ዋናው ክፍል ደግሞ አበው የፈጠሩት የሥርዓተ ነጥብ አደራደር ነው። በዚያን ዘመን የፈጠሩት የዓረፍተ ነገር መጨረሻ ሥርዓተ ነጥቦች የሚባሉት አራት ነጥብ፣ የጥያቄ ምልክት፣ ቃለ አጋኖ ወይም ትዕምርተ አንክሮ፤ ትዕምርተ ስላቅ… የተባሉት ናቸው። የውስጥ ሥርዓተ ነጥቦች የምንላቸው ደግሞ፤ ሁለት ነጥብ፣ ነጠላና ድርብ
ሠረዝ..ናቸው። ለአንድ ጽሑፍ ግልጽነትና ጥራት ሥርዓተ ነጥቦች ዐቢይ ጠቀሜታ አላቸው።
ፀሐፊዎች በትክክል ከአንባቢው ለመድረስ፤ የጽሑፉን ዓላማ፤ ምስጢርና መልዕክት አንባቢው በአግባቡ እንዲረዳው ለማድረግ፤ ጽሑፉ ሚዛናዊ አጽንኦትና ተቀባይነት እንዲያገኝ፤ ሥርዓተ ነጥቦች የሚጫወቱት ሚና በእጅጉ ወሳኝ ነው። ከሥርዓተ ነጥቦች ጎን የሚመደቡ ሌሎችም አሉ። ነቁጥ፣ እመጫት፣ ጭረት፣ ሕዝባር፣ የኮከብና የማጥበቂያ ምልክት፣ ድርብ ሠያፍ፣ ነጠብጣብ የመሳሰሉት ሲሆኑ፤ አብዛኛዎቹ በጥንት ምሁራን የተፈጠሩ፤ ጥቂቱ ከዘመኑ ጋር እየጎለበቱ የመጡ ናቸው። ኢትዮጵያዊያን ይህን ታላቅ አገር በቀል ዕውቀት በአግባቡ አለማወቃችንና በሥርዓት አለመጠቀማችን ያሳዝናል።
ኢትዮጵያ በጥንታዊ ሥልጣኔዋ የግሪክ ቋንቋም ተናጋሪና ፀሐፊም ነበረች ። ሳባ፤ ግዕዝና ግሪክ ሦስቱም ቋንቋዎች በአገሪቱ እኩል ይነገርባቸውና ይፃፍባቸው እንደነበር መረጃዎች ያረጋግጣሉ። የሚገርመው ግን በቋንቋ ዕድገትም ሆነ በሥልጣኔ በተመጣጣኝ ደረጃ ላይ ከነበሩት ሁለት አገሮች መካከል ግሪክን ከኢትዮጵያ ነጥለው የሥልጣኔ ሁሉ “ቁንጮ ናት” አሏት። ቲያጥሮን የሚል ቃል በጥንታዊው የግዕዝ ቋንቋችን ሠፍሮ እያለ የቴአትር ፈጣሪዋ ግሪክ ናት ተባለች። ግሪካዊያን ፈላስፋዎች ሳይቀሩ ያደነቋትን አገር ዘመናዊያን ታሪክ ፀሐፊዎች ለዓለም ሥልጣኔ ያበረከተችውን ትሩፋቷን ጨምድደው ካዱ። ከእሷም ሞጭቀው ለግሪክና ለግብፅ ሰጡባት። መች ይሆን ይህቺ አገር ለዓለም ሥልጣኔ ዕድገት ላደረገችው አስተዋጽኦ ዋጋ የሚሰጣት ትውልድ ብቅ የሚለው?
ከአርባ ሦስት ጊዜ በላይ ስሟ በቅዱስ መጽሐፍ መጠቀሱ እንኳ በሐይማኖቱ ግንባር ቀደም ተጠሪ አላደረጋትም። የብሱን አቋርጦ..፣ ባህሩን ተሻግሮ ከሩቅ አገር የመጣውን ጃንደረባ..፣ ሕዝቡንና አገሩን የወከለ መሆኑን ለመግለጽ ቅዱስ መጽሐፍ በስም ለይቶ “ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ” ይለዋል። የራሱ የኢየሱስ ደቀመዝሙር የሆነው ፊሊጶስ በመንፈስ ተሞልቶ ሠረገላው ድረስ ሔዶ አስተምሮ አጠመቀው..፣ ከጃንደረባው በፊት ከሩቅ አህጉር መጥቶ፣ ጌታን የተቀበለ ሌላ ምዕመን ነበረ ብሎ ለማመን ያስቸግራል። ለዚህ ታላቅ ቋሚ ታሪክ እኛም አጽንኦት አልሰጠነውም ፈረንጅም ትውፊቱ እንዳይጎላ፤ ነጭን በጦር ግንባር ተፋልማ ድል የተቀዳጀች አገር ስም በደግ እንዳይጠራ ብሎ እውነቱን ሰልቅጦ ዝም ብሏል።
ይህን የመሳሰሉ የበለፀጉ የአገሪቱ ታሪኮች፤ በየጦር ሜዳው የተገኙ አኩሪ ድሎች፤ የእነ አንድሮ ሜዳ የከዋክብት ግኝቶች፤ በእኛ ዘመናዊያን የታሪክ ምሁራን አልተጠኑም። ቢጠኑም አንድም አጥኚው ፈረንጅ ከሆነ “ጌታ ለሥጋው አደላ” ይሆናል። አጥኚዎች የእኞች ከሆኑ ደግሞ ሌሎች ችግሮች ይኖራሉ።
የተማርንበት የትምህርት ሥርዓት የተቃኘው በፈረንጆች ስለሆነ፣ የእኛን ታሪክ ዘወር ብለን የምናይበት አንገት አልተቀጠለልንም። ስለ ፈረንጆች አገር ታሪክ በጥልቅ የምናውቀው እኛ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን ለአገራችን ታሪክ ባዳዎች ብቻ ሳይሆን ባንዳዎች ጭምርም ሆነናል። በቅኝ ግዛት የነበሩ የሩቅ ምሥራቅ ወንድሞቻችን ነፃ ሲወጡ የፈረንጅን ግሳንግስ ባሕል ከነጮች ጋር አስወጥተው፤ ቴክኖሎጂውን አስቀርተው አስቀድመው በአገራቸው ባነፁት ቱባ ባሕል ላይ

ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
ገነቡት። ቴክኖሎጂው ቶዮታን ይዞ ብቅ አለ እንጂ ባሕላቸውን አልረበሸም፤ ቱባ አልባሳታቸውን አላስጣላቸውም፤ ባህላዊ መጠጥና ምግባቸውን አልቀየረባቸውም፤ ባህላዊ መድሃኒታቸውንና መገልገያ የቤት መሣሪያዎቻቸውን ሙሉ፤ የትምህርት ሥርዓታቸውን፤ ቋንቋቸውን ወዘተ.. አልለወጠባቸውም። እኛም በቅኝ ባንገዛም የነጭን ውራጅ ከቴክኖሎጂው ጋር ለምነን አግበስብሰን አስገባነው። ቴክኖሎጂው በአገር በቀል ዕውቀት ላይ ስላልተገነባ ሟሸሸ። ከእኛ ጋር ሙጥኝ ብሎ የቀረው ውራጃቸው ብቻ ሆነ። በዚህ መሠረት በቅኝ የተገዙ አገራት ሰዎች በባሕላዊ አልባሳታቸው ቆንጅተው ሲወጡ፤ እኛ ግን በዓለም ዓቀፍ መድረክ ላይ የእኛ ባልሆነው ተውበን እንገኛለን።
ስለ አገራችን ታሪክ እንድናነብ የሚፈቀድልን ፈረንጆች፤ የእኛን ሊቃውንት ጠቅሰው ስለ አበሻ የፃፉትን የታሪክ መፃሕፍት ብቻ ነው። እኛ እንኳን ደፍረን ስለራሳችን ታሪክ እንፃፍ ብንል “መረጃችን” ብለን መጥቀስ የምንችለው ነጭ በአስተርጓሚ የእኛን ምሁራን ጠይቆ የፃፈውን አርቲ-ቡርቲ የታሪክ ድርሳን ነው።
ጥንታዊያን ኢትዮጵያዊያን ታሪክ ፀሐፊዎቻችን በደረሱትና የዛሬዎቹ በፃፉት የታሪክ መጽሐፍ መካከል የሚታየው የታሪክ ክፍተት ከዚህ የመነጨ ሳይሆን አይቀርም። የአበው ምሁራን የመረጃ ምንጫቸው ከቋንቋ ግዕዝ..፣ እብራይስጥ..፣ ጽር..፣ አረማይክ..፣ ዓረብኛ ናቸው። የዘመናዊያን
የታሪክ ልሒቃን ምንጫቸው ከቋንቋ የእንግሊዝ..፣ የፈረንሳይ..፣ የኢጣሊያ ..፣ የጀርመን ወዘተ.. ናቸው። የእኛ ጥንታዊ ታሪክ ደግሞ ተደብቆ ያለው በላይኞቹ ቋንቋዎች ማህደር ውስጥ ነው። ከእኛ ዘመናዊ የታሪክ ፀሐፊዎች መካከል ከላይ ከተጠቀሱት ቋንቋዎች ውስጥ ግዕዝ የሚችል ስንቱ ነው? የዚህች አገር በተለይም የሰሜኑ ክፍል ታሪክ መፍቻ ቁልፍ ያለው በግዕዝ ቋንቋ ውስጥ ነው። ፈረንጁም-አበሻውም ታሪክ ፀሐፊዎች እኩል በአስተርጓሚ የሚጠቀሙ ከሆነ ተዓማኒው የማን ሊሆን ነው?
በአፍሪካ ምድር ላይ ፈረንጅ ያልባረከው አይጸድቅም፤ ያልመረቀው አያድግም፤ ያልተከለው አይፀድቅም፤ ለምሣሌ የንግሥት ሳባ ታሪካዊ ጉዞ ነጭ ስላልባረከው አፈ-ታሪክ ተብሎ ተጥሏል። ይህ ታሪክ የአንድ የበለፀገ የነጭ ሕዝብ ታሪክ ቢሆንና፤ በቅዱስ መፅሐፍ ተከትቦ ቢያገኘው ኖሮ የሚፃፍለት ልብወለድ፤ የሚዘጋጅለት ቴአትርና ፊልም፤ የሚቀነባበርለት የሙዚቃ ኮንሰርት ዓለምን የሚያስደምም በሆነ ነበር። አሁን- አሁንማ በራሳቸው አኩሪ ታሪክ ላይ የሚዘምቱ ኢትዮጵያዊያንም እየተስተዋሉ ነው።፡ የንግሥት ሳባ ትውፊት ተቃዋሚ ራሳችን አበሾች ስንሆን በእጅጉ ያሳፍራል። በነጭ ላይ ዋጀን የምንለውን አኩሪ የነፃነት ድል አውግዘው፤ ቅኝ ግዛትን የሚናፍቁ ነጭ-አምላኪ አበሾችን በአገራችን እያየን ነው። ለእነዚህ ሰዎች ቱባ ታሪክ እየጠቀሱ ስለ አገር በቀል ዕውቀት መስበክ ጉንጭ ማልፋት ነው። በአጭሩ ይህንና መሰል የተጣሉ የአበሻ አኩሪ ታሪኮችን በዓለም መድረክ ላይ ለማግነን፣ ስለ ጥንታዊው ታሪካችን ቀድሞ የሚያቀነቅንልን መጠበቅ ሳያስፈልገን የታሪካችን ባለቤቶች እኛው በተግባር ቀደምት መሆን ይኖርብናል።
ሥዕል
የሰው ልጅ ሀሳቡን ከሚያንፀባርቅባቸው ጥበቦች አንዱ ሥነ-ሥዕል ነው። ይህ የጥበብ ዘርፍ ከጥንት ጀምሮ የሰው ልጅ በአካባቢው ያሉትን የተፈጥሮ ሀብቶች ባህሪይ እንዲያውቅ ያገዘ የዕውቀት መሣሪያ ነው። የኢትዮጵያ አገር በቀል ሥዕል ያደገው ምን አልባትም የተፈጠረው በቤተ እምነቶች አካባቢ ነው። አብዛኛዎቹም የሥዕል ፈጠራዎች ከቤተ አምልኮ ጋር በጥብቅ የተቆራኙ ናቸው። ጥንታዊያኑ መፃሕፍት በሥዕል የተደገፉ፤ ቤተ እምነቶቹም በሥነ-ሥዕል የተዋቡ ለመሆናቸው ከመፃሕፍቱ ጋር የተደጎሱ ሥዕሎችና በየገዳማቱና በየአድባራቱ ጣሪያዎችና ግድግዳዎች ላይ ተስለው የሚገኙት የሥዕል ቅርሶች በቂ ማስረጃዎች ናቸው። የጥንታዊያን ሠዓሊያን ሥራዎች የሚያንፀባርቁት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፤ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና ልምላሜ፤ በውስጧ የሚገኙትን ወንዞች፤ እንስሳት፤ የዱር እንስሳት፤ አዕዋፋትና ዕፅዋት፤ የሕዝቧን ጀግንነት፤ የትውልዱን የአገር ፍቅር ስሜት ነው። እነዚህ ሁሉ የፈጠራ ሥራዎች ከውጭ ያልተኮረጁ፤ የውጭ ሐሳብና ቁሳቁስ ያልተቀየጠባቸው ንፁህ የአበሾች ቱባ ባሕላዊ ፈጠራዎች ናቸው።
ጥንታዊውን የአገራችንን የሥዕል ጥበብ ከሌሎች ከሚለዩት አንዱ በሥዕሉ ላይ ያሉት ገፀ-ባህሪያት ዓይኖቻቸው ትላልቅ መሆናቸው ነው። ቀለማቱም ቀይ-ቢጫ-አረንጓዴ ሲሆኑ ስዕሎችን ደማቅ ያደርጓቸዋል። ጥንታዊያን ሠዓሊያንም ሆኑ ደራሲያን በፈጠራ ሥራዎቻቸው ላይ ስማቸውን አይጽፉም። ይህን የሚያደርጉት ከትህትና የተነሳ
ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
ቢሆንም፤ የሠዓሊያኑን ወይም የደራሲያኑን ስም ለማወቅ ለተመራማሪዎች ከባድ ፈተና ሆኗል። ጥንታዊ የኢትዮጵያ ቱባ የሥዕል ጥበብ ለዘመናት አገሪቷን አስከብሮና አስደምሞ የዘለቀ የጥበብ ዘርፍ ነው።
ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ ለዓለም ያበረከተቻቸው የጥበብ ትሩፋቶች ቀላል አይደሉም። በሕቡዕ ወይም በይፋ ከተዘረፉብን ጥንታዊ ሥዕሎች መካከል አንዱ እንግሊዞች መቅደላ ላይ የዘረፉት የኩራተ ርዕሱ ሥዕል ነው። እኛ ይህን ሥዕል የት ቦታ እንደደበቁት እስካሁን ያደረግነው ጥረት ያለ አይመስለኝም። ከመቅደላ በፊትና በኋላም አያሌ ጥንታዊ ቅርሶቻችን ተዘርፈውብናል። ”እሾህን- በሾህ” እንዲሉ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብና ትውልዱ ሪቻርድ ፓንክረስት የተሰረቁ ጥንታዊ ቅርሶቻችንን ከሌቦች ለማስመለስ ያደረጉትን ትግል ፈጽሞ አይረሱትም።
ዛሬ በመዲናችን የሚገኙት የቅርሳቅርስ መደብሮች በአብረቅራቂ ሥዕሎች ተጣበው የሚታዩት በጥንታዊው ቱባ የሥዕል ጥበብ ውጤቶች ሳይሆን በውጭ አገር ሥዕሎች ነው። በአገራችን ሠዓሊያን የተሠሩ አብዛኛዎቹ የሥዕል ሥራዎችም ቢሆኑ የአገር በቀል ጥበብ መሠረት የሌላቸው የውጭ ቅጂዎች ናቸው። በታላቁ ሠዓሊ በአለ ፈለገ ስም የተሰየመው ተቋም ለአገር በቀል የሥዕል ጥበብ ምን ያህል ቅርበት እንዳለው ሩቅ ስለሆንሁ ደፍሬ መተቸት አልችልም። ከዚህ ተቋም የተመረቁት አብዛኞቹ ግን ቱባውን የአገር በቀል ጥበብ ፀበል ከዚህ ተቋም የቀመሱ አይመስሉም። ቢኖሩም በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። አበቃ!!
ቅርፃቅርጽ

አንዳንድ ሊቃውንት የቅርፃቅርጽ ሥራ የተገኘው በቀጥታ ከፈጣሪ ነው ይላሉ። የቅርፃቅርጽ ሥራ በአፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያ በዓይነቱም ሆነ በይዘቱ የራሱ የሆነ ባሕል አለው። አፍሪካዊያን ቅርፃቅርጽን ለባሕላዊ ጭፈራቸው ጭምብል አድርገው ይጠቀሙበታል። ጥንታዊያኑ ኢትዮጵያዊያን ቅርፃቅርጽን የሚጠቀሙት ለከባድ ተግባራትና መልዕክት ነው፤ ቀራፂያኑም በሐውልቶች ላይ ረቂቅና ሰብዓዊ ባሕሪይን የመግለጽ ችሎታ አላቸው። በአክሱምና በሌሎች አካባቢዎች በቁፋሮ የተገኙ በኢትዮጵያዊያን የተሠሩ ሐውልቶች አሠራራቸው በእጅጉ የረቀቀ ነው። በውስጣቸው የያዟቸው መልዕክቶች እስከአሁን ዓለምን ማስደመማቸውና መነጋገሪያ መሆናቸውን ቀጥለዋል። ጥንታዊያን ኢትዮጵያዊያን በቅርፃቅርጽ ሙያ የተካኑ ሊቃውንት እንደነበሩ የቆሙትና ተቆፍረው የወጡት ሐውልቶች ቋሚ ምስክሮች ናቸው።
በዘመኑ የንግድ ማዕከል በነበረችው በአክሱም የታነፁት እስከ 33 ሜትር ርዝማኔ ያላቸው ሐወልቶች ረቂቅ የአሠራር ምስጢር ዛሬም ድረስ ለማንም አልተገለፀም። በምን መሣሪያ ተቀረፁ..!? ለምን ዓላማ ቆሙ..!? እንዴት ተሠሩ..!? የት ቦታ ተቀረፁ..!? በምን ተጓጓዙ..!? የሚሉ ጥያቄዎች እስከ አሁን ምላሽ ያገኙ አይመስለኝም። በዚህ ጥናት ላይ ያልተሳተፈና እጁን ያላስገባ የዓለም ተመራማሪ የለም። ትልቁን ሐውልት መርጠው በምርኮ ወደ አገራቸው የወሰዱት ጣሊያኖች ለዘመናት መንገድ ዳር አቁመው መለሱት እንጂ
ነጋሪ 7ኛ ዓመት ቁጥር 29 መጋቢት 2017 ዓ.ም
የሐውልቱን ምስጢር ጨርሰው አላገኙትም። ይህም የጥንታዊ አበሾች የፈጠራና የመመራመር ችሎታ የደረሰበትን የዕድገት ደረጃ በሚገባ ያሳያል።
የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን አሠራር በእጅጉ የረቀቀ ነው። አሥራ አንድ አብያተ ክርስቲያናት ከአንድ ወጥ ቋጥኝ ድንጋይ ተፈልፍለው ታንፀዋል። የሥራው ረቂቅነት መላ ዓለምን ያስደነቀ ነው። እያንዳንዱ ቤተክርስቲያን የየራሱን ውበት ተጎናጽፏል። አንዱ ከሌላው አይመሳሰልም። የሥራው ጥራትና ርቀት ምንጊዜም ለዓይን እንግዳ ነው። የውጭም ሆኑ የአገር ውስጥ ጎብኚዎች ይህ አስገራሚ ሥራ “በሰው እጅ ተሠራ” ብለው ለማመን ይከብዳቸዋል። ይህን ሁሉ የፈጠራ ሥራ ያበረከቱልን በአገር በቀል ዕውቀት የበለፀጉት ጥንታዊያን አባቶቻችን ናቸው። ይህን ጥንታዊ የሥልጣኔ አሻራ ጠብቆ ማቆየትና ለዘመናዊው ጥበብ መሠረት እንዲሆን ማብቃት የትውልዱ ታሪካዊ ኃላፊነት ነው።
ዛሬ በአገራችን እየተሠሩ ያሉትን ቅርፃቅርፆች መመልከት አለብን። ግማሾቹ ከውጭ የተኮረጁ ናቸው። ግማሾች ዛሬ ተሠርተው ነገ የሚፈርሱ ናቸው። አንዳንዶች ለኢትዮጵያዊያን አንድነት ጠንቅ በሆነው አፍራሽ ትርክት ላይ ተመሥርተው የታነፁ ናቸው። በዘመኑ ቀራፂያን የተሠሩ በአደባባይ የቆሙ ሐውልቶችን ለማየት ከጓጓንና ከናፈቀን ቆይተናል። የጠፋው ቀራጭ....!? ተቀራጭ ወይስ መራጭ..!? ቀራጮችም ሆኑ ተቀራጮች አይጠፉም። አክሱምን የቀረፁ አባቶች ልጆች ከቱባው ባሕል ርቀው እንጂ ቀራጺያን ይኖሩናል። በተለያዩ ሙያዎች ታሪክ የሠሩ ተቀራጮችም አሉን። የጠፋውን ፈልገን እንድረስበት። ያም ሆነ ይህ ዘመኑን የምናስታውስባቸው በአገር በቀል ዕውቀት ላይ የተገነቡ ቅርፆች ዛሬም ለአገራችን ያስፈልጓታል። የአለ-ፈለገ ተቋም ለዚህ ሙያ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል።
በመጨረሻ. . .
ዘርፈ ብዙውን አገር በቀል ዕውቀታችንን እንዲህ ባለ አጭር ፅሁፍ መግለፅ አዳጋች ቢሆንም ከዘመናዊው ትምህርት ጋር ሲዋሃድ አሁን ለኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ በእጅጉ የሚያስፈልገውን ኅብረተሰቡን ከጎታችና ኋላቀር አመለካከት፣ እምነት የሚያላቅቅ፤ ድህነትን የሚያስወግድ..፣ ረሀብን የሚያጠፋ..፣ ፍትህን የሚያሰፍን..፣ የሕዝቦችን አብሮነት የመፍጠር አቅም አለው። በጋራ-ጥረት ለጋራ-ብልጽግና መሥራትን ያበረታታል። ሥነ-ምግባርንም ያሰርጻል። የአገር ፍቅርንና አርበኝነትን ይገነባል። ዓለም አቀፋዊነትን ያጠነክራል። የውጭ የባሕል ወረራን ይዋጋል። በምትኩም የሕዝቡን እሴት..፣ አገር በቀል ዕውቀት ያዳብራል። በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አዲስ ስብዕና ያለው ባሕላዊ ሰው ይፈጥራል።
ከዚህ ጎን ለጎን የኢትዮጵያና የሕዝቦቿ ዕድገት እንዲፋጠን፣ ነባር ዕውቀቶች እንዲዳብሩ፣ ድህነት እንዲወገድ፣ የፀና ሠላም በምድሪቱ እንዲሰፍን፣ ዘመናዊው ትምህርት በኅብረተሰባችን ውስጥ የሚጫወተውን ወሳኝ ሚና ጠጋ ብሎ መገምገምና ቀጥተኛ ፈር የሚያስይዝ መዋቅር መዘርጋት አስፈላጊ ነው። እዚህ ላይ ለማበልፀግ የምንፈልገው ትምህርት መሠረቱ ምን መሆን አለበት? የሚለው ጥያቄ ምላሽ የሚያሻው ጉዳይ ነው።
ቸር እንሰንብት!

