ቀጥታ፡

የመቀሌ ከተማን ሰላምና መረጋጋት ለማጽናት ከባለአደራ አስተዳደሩ ጋር በትብብር እየሰራን ነው-የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች

መቀሌ፤ ህዳር 19/2019 (ኢዜአ)፦በመቀሌ ከተማ የሰፈነው ሰላምና መረጋጋት ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከትግራይ ክልል የፌደራል መንግስት ባለአደራ አስተዳደር ጋር በትብብር እየሰሩ መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰባተኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን አራተኛ መደበኛ ጉባኤ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ የትግራይ ህዝብ ሰላም ወዳድ፣ ትጉና ታታሪ ሠራተኛ መሆኑን አንስተዋል።

የክልሉ ህዝብ በፌደሬሽኑ ተወካዮችን መላክ እንዲችል ምርጫ ማካሄድን ጨምሮ የተለያዩ ልማቶችን ማከናወን እንዲቻል መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ምላሽና ማብራሪያ በማስመልከት ኢዜአ በመቀለ ከተማ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች፤ በከተማዋ ተከስቶ የነበረው የሰላም እጦት ተወግዶ ሰላምና መረጋጋት መምጣቱን ገልጸዋል። 

ነዋሪዎቹ ከቤት ወጥቶ በሰላም መመለስ አስቸጋሪ እንደነበር አስታውሰው፣ በተለይ ወጣቶች በህገወጡ የህወሓት ቡድን አስገዳጅ የውትድርና ምልመላ ችግር ውስጥ ገብተው ነበር ብለዋል።

በነዳጅ እጥረት ሳቢያ የኑሮ ጫና ሲደርስባቸው እንደነበረም ገልጸው በከተማዋ ሰላምና መረጋጋት መስፈኑን ተከትሎ ችግሩ እየተፈታ መምጣቱንና የሰላም አየር እየተነፈሱ መሆናቸውን ተናግረዋል።    

ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል በራይድ የትራንስፖርት አገልግሎት የተሰማሩት ገብረህይወት ገብረስላሴ፤ በመቀሌ ከተማ የነበረው የሰላም እጦት እየተሻሻለ በመምጣቱ የሰላም አየር መተንፈሳቸውን ተናግረዋል።


 

በተለይ በከተማው ተቋርጠው ከነበሩ አገልግሎቶች መካከል የነዳጅ አቅርቦት አንዱ እንደነበር አስታውሰው፣ ሰላም በመስፈኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በማደያዎች ነዳጅ በማግኘታቸው የትራንስፖርት አገልግሎት ስራውን መጀመራቸውን ገልጸዋል።

የሰፈነውን ሰላምና መረጋጋት ይበልጥ ለማጠናከር የሁሉም አካላት አስተዋጽኦ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፣ ለዚህም የከተማዋ ነዋሪዎች ከከተማው የባለአደራ አስተዳደር ጎን በመሆን መትጋት አለብን ብለዋል።

ሌላው አስተያየት ሰጪ በመቀሌ ከተማ የዓዲ-ሐቂ ክፍለ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ሠራተኛ ወጣት ጎይቶኦም ካልአዩ፣ በመቀለ ከተማ የሰፈነው መረጋጋትና ሰላም ተስፋ ሰጪ ነው ብሏል።


 

ተከስቶ በነበረው የሰላም እጦት በከተማው የወንጀል ድርጊት ተበራክቶ እንደነበር አስታውሶ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰላም በመስፈኑ በነጻነት ወጥተው መግባት መቻላቸውን ተናግሯል።

በከተማዋ ሰላምና መረጋጋት እንዲጠናከር የተሰማሩ የመንግስት የጸጥታ አካላት አዎንታዊ ሚና እየተጫወቱ መሆናቸውን የገለጸው ወጣቱ ነዋሪዎችም ከጎናቸው ልንሆን ይገባል ብሏል።

በተለይ ወጣቱ የሰላም እጦቱ ቀጥተኛ ተጎጂ በመሆኑ የሰፈነውን ሰላም ለማጽናት ከክልሉ የፌደራል መንግስት ባለአደራ አስተዳደር ጋር በትብብር እንደሚሰራ አረጋግጧል። 

በመምህርነት ሙያ ለረዥም ዓመታት ያገለገሉት መምህር ወልደስላሴ ይግዛው በበኩላቸው፣ በከተማው የሰፈነው ሰላምና መረጋጋት የከተማዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚ እያደረገ መምጣቱን ተናግረዋል።

በከተማዋ የሰፈነውን ሰላም ተከትሎ የህዝቡን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ለማሳለጥ የሚያግዙ የኢንተርኔት፣ የኤሌክትሪክ ሀይል ጥገናና ዝርጋታ እንዲሁም የትምህርት ቁሳቁስ አቅርቦት መጀመሩን ገልጸዋል።

የተለያዩ አገልግሎቶችን መልሶ ለማስጀመር እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ለዘላቂ ሰላም ግንባታ አጋዥ በመሆናቸው ተጠናክረው መቀጠል  አለባቸው ብለዋል።

በከተማው የታየውን ሰላምና መረጋጋት የማስቀጠል ሃላፊነት የጸጥታ አካላት ብቻ ሳይሆን የህዝብም ጭምር በመሆኑ ከባለአደራ አስተዳደሩ ጋር በመሆን የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም